ቋሚ ሲኖዶስ: የአቴንሱን አባ ወልደ ሚካኤል ጣውዬን ሥልጣነ ክህነት ያዘ፤ በማንኛውም አገልግሎት እንዳይሳተፉ ታገዱ!

 • ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ቢጠሩም ወደ ካናዳ ሸሹ፤ ካህናትና ምእመናን፥ ዕወቁባቸው!
 • ሌላ አስተዳዳሪ አባት እስኪመደብ፣ አገልግሎቱን የሚያስፈጽሙ 4 ካህናት ተወክለዋል
 • ያለበትን ትቶ ወደሌላ የሔደና እንዲመለስ ተጠርቶ ያልተመለሰ ካህን ከሹመቱ ይሻራል

*                    *                    *

 • በአገልጋዮች ምርጫና ምደባ መስፈርት፥ ልዩ ክትትልና ማስተካከያ እንዲደረግ ተጠይቋል
 • ለአንድነቱና ለአገልግሎቱ ምሉእነት፥ የእምነት አቋም፣ ክህነታዊና ሞያዊ ብቃት ይተኮርበት
 • ለዓለም አቀፋዊ ተልእኮና ማዕከላዊ አሠራር መጠናከር፣ የተጠና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ!

*                    *                    *tawuye's-ordination of priesthood held-2009

የዛሬው የሉላዊነት ዘመን፥ የትኛውም የዓለም ሕዝብ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኝበት ነው፤ ስደት፣ ዝርወት ወይም ዳያስጶራነት እንግዳ ነገር አይደለም፤ የኢትዮጵያውያንም ስደትና ዝርወት የሉላዊው እንቅስቃሴ አካል ተደርጎ የሚታይ ነው፡፡ በዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ ላይ ያለው ኦርቶዶክሳዊው ኢትዮጵያዊ ከሚሻቸው ዐበይት ነገሮች አንዱ፣ ቤተ ክርስቲያኑ እንድትከተለው ነው፤ የሀገሩን ናፍቆት በዋናነት የሚወጣው፣ በቤተ ክርስቲያኑ መጽናኛነትና መሰባሰቢያ ማዕከልነት ነውና፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የአገልግሎት አድማስዋን በማስፋፋት ኢትዮጵያውያን ባሉባቸው የውጭ ሀገራት ቤተ ክርስቲያን እያቋቋመች፣ ዜጎቿን እንደምታስተምርና እንደምታጽናና የሚታወቅ ነው፡፡ በውጭ አህጉረ ስብከት፣ ቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው የምትመሠረተው፣ በስደትና በዝርወት ባሉት ኦርቶዶክሳውያን ነው፡፡

በመላው ዓለም ተበትነው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ቤተ ክርስቲያን፥ የሥርዐተ አምልኮ መፈጸሚያ ብቻ ሳትኾን፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ችግራቸውን የሚፈቱባት፤ በኑሯቸው ልዩ ልዩ ተጽዕኖ ያለባቸው ስደተኞችም፣ ጉዳያቸውን ለሚመለከተው አካል ለማድረስ ዕድል የምትፈጥርላቸው ናት፡፡ በስደትም፣ በመከራም፣ በእስራትም ጊዜ ከመንጋው የማትለይና ስለ ሕዝቧ በነገር ኹሉ እንደምትቀድም በጉልሕ ያረጋገጠችበት አጋጣሚ በመኖሩም፥ “ከሀገር ውጭ ያለች ኢትዮጵያ”፤ “የኢትዮጵያ ኤምባሲ” ብትባል ማጋነን አይኾንም፡፡

ከዚኽ አኳያ፣ የውጭ ሀገራት ሐዋርያዊ ተልእኮ፣ የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ጉዳይ መኾኑ ታውቆ፣ ቤተ ክርስቲያናችን በየክፍለ ዓለሙ እንድትስፋፋና እንድትጠናከር፤ ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናትን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን የመመለሱ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ በአጠቃላይ፥ ማዕከላዊ አሠራራቸውና መንፈሳዊ አገልግሎታቸው በበለጠ እንዲጠናከር፤ ይህንንም በባለቤትነት ለመምራት፣ ለመቆጣጠርና ለመከታተል የሚያስችል የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ በባለሞያዎች በተገቢው ኹኔታ ተዳሶ እንዲዘጋጅና ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ በዘንድሮው የጥቅምት ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡

የምልአተ ጉባኤውን ውሳኔ መነሻ ያደረገው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሪፖርት እንደሚገልጸው፥ ባለፈው የአገልግሎት ዓመት፣ ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት በቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ አገልጋይ ካህናትና አስተዳዳሪዎች ተልከዋል፡፡ ይኸውም፦ በቤይሩት፣ በሊባኖስ፣ በዱባይ፣ በቃጣር፣ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም፣ በካሪቢያን ደሴቶች፣ በሮም፣ በኦስትሪያ፣ በጅቡቲ እና በግሪክ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መኾኑን ዘርዝሯል፡፡ የትምህርተ ወንጌል ልኡካን፣ ለዐበይት በዓላት፥ ለአውሮጳና ለደቡብ አፍሪቃ አህጉረ ስብከት ተልከው አገልግለው መመለሳቸውን አስፍሯል፡፡

በጃፓንና በኮርያ አዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲቋቋሙ፣ መምህራንም እንዲላኩ ምልአተ ጉባኤው ከዓመት በፊት ወስኖ የነበረ ቢኾንም፣ ሪፖርቱ፣ ስለ አፈጻጸሙ ያለው ነገር የለም፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ልዩ ክትትልና ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል!” ያለውን አንድ ጉዳይ ግን በአጽንዖት አስቀምጧል፡፡ ይህም፣ ስደተኞች በብዛት የሚገኙባቸውን አብያተ ክርስቲያናት ይመለከታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሳታውቃቸው፣ በሔዱበት ቦታ እናገለግላለን፤ የሚሉ ሰዎች፣ በስደት የሚኖሩ ምእመናንን ሕይወት ለችግር ዳርገዋል፤” የሚለው ሪፖርቱ፣ የውጭ ሀገሩን መንፈሳዊ ሕይወት ለመምራት የሚያስችልና ከአገሮቹ የውስጥ ደንብ ጋራ የተጣጣመ መመሪያ አለመኖሩን በምክንያትነት ጠቅሷል፡፡

ይህም በራሱ የፈጠረው ውስንነት እንዳለ ኾኖ፣ ውስንነቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፥ “ለቤተ ክርስቲያን ማዕከላዊ አመራር አንታዘዝም፤ ሀገረ ስብከት ምን አገባው? ቤተ ክህነት ምን አድርጎልናል?” በሚል፥ የቅዱስ ሲኖዶሱን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑና መዋቅርን የሚንዱ ማፈንገጦች መታየታቸውን፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ አደረጃጀት፦ ለፖሊቲካ፣ ለንግድ፣ ለግልና ለቡድን ጥቅም ለማዋል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መበራከታቸውን አትቷል፡፡

ይብሱኑ፣ እንደ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን፥ ከሲኖዶሳዊ መዋቅር የወጣ ገለልተኛ አደረጃጀት በመፍጠርና፣ ቀኖናዊና ትውፊታዊ ያልኾነ የምስጢራት አፈጻጸም በመከተል በይፋ የመከፋፍልና የማደናገር ድርጊት የሚፈጽሙ መኖራቸውንም አመልክቷል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም፣ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅራዊ አንድነት የሚያጸና ዝርዝር መመሪያ በማውጣት ክትትል እንዲያደርግበት ጠይቋል፡፡

ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የተወያየበት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም፣ በየክፍለ ዓለሙ ለተስፋፋው የቤተ ክርስቲያናችን ዓለም አቀፋዊ አገልግሎት፣ እስከ አኹን ያለው ማዕከላዊ አሠራር አመርቂ እንዳልኾነ ገምግሟል፡፡ የአስተዳደር ነክ የሕግ ጥሰቱን አስመልክቶም፣ ኹለት ዐበይት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ የመጀመሪያው፥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የተቋቋሙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ከመንበረ ፓትርያርኩ ማዕከላዊ አስተዳደር፥ በባለቤትነት መመራትን፣ መቆጣጠርንና መከታተልን የሚያጠናክር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በባለሞያ በተገቢው ኹኔታ እንዲዘጋጅና ሥራ ላይ እንዲውል ነው፡፡ ኹለተኛው ደግሞ፣ የሚሻሻለው ቃለ ዐዋዲ፥ ከሀገር ውስጥ ባሻገር የውጭ አህጉረ ስብከትንም ማዕከል ባደረገና የመንግሥታትን ተቀባይነት በሚያገኝበት መልኩ ከነዝርዝር አፈጻጸሙ በአስቸኳይ እንዲዘጋጅ ነው፡፡

የበለጠ አሳሳቢው ጉዳይ ግን፣ የተዘረዘሩት ችግሮች፣ በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው፣ ቤተ ክርስቲያን በማታውቃቸውና በተለያየ ምክንያት ወደ ውጭ በሔዱ ግለሰቦች ብቻ ሳይኾን፣ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ በሚላኩ አስተዳዳሪዎችና ካህናትም መፈጸማቸው ነው፡፡ በውጭ ሀገራት በሚገኙ አህጉረ ስብከትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለአገልግሎት ስለሚመደቡ ካህናትና ሊቃውንት፣ የምልመላና ምርጫ መስፈርት የማውጣት ተግባር የቅዱስ ሲኖዶስ ሲኾን፤ የመምረጥና በምደባዎቹ ላይ ውሳኔ የመስጠት ድርሻ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቁ ሕግጋት፣ ደንቦችና መመሪያዎች በሥራ ላይ መተርጎማቸውን የሚከታተለውና የሚቆጣጠረው ቋሚ ሲኖዶስ ነው፡፡

ይህም፣ የአገልጋዮቹ የእምነት አቋምና ለተመደቡበት ተልእኮ ያላቸው የኖላዊነት ብቃት፣ የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ከግምት ሳይገባ፣ በቀረቤታ፣ በትውውቅና በመጠቃቀም ብቻ መመረጣቸውን ሲያሳይ፤ በቋሚ ሲኖዶሱ ምደባ ወቅትም፣ ለትክክለኛ ውሳኔ የሚያበቃ ሐቀኛና በቂ መረጃ አለመቅረቡን ያረጋግጣል፡፡ ለማሳያ ያኽል፣ በምሥራቅ አፍሪቃ ሀገረ ስብከት የጅቡቲ ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ምእመናን፣ ከመጋቢት 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የሚያሰሙት “የድረሱልን ጥሪ” እና አምባሳደሩም ጭምር በግንባር ቀርበው ቢያሳስቡም፣ ተገቢው ውሳኔ ያልተሰጠው የአስተዳዳሪውና መሰሎቻቸው፥ ዓምባገነንነት፣ ምዝበራ፣ አባካኝነትና ምግባረ ብልሹነት በአስረጅነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በደቡብ አፍሪቃ ሀገረ ስብከት፣ በመንበረ ጵጵስናው ጆሐንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኃኔዓለም የቆዩ ውዝግቦችና በቅርቡም፣ ቋሚ ሲኖዶስ ካደረጋቸው የስድስት ሓላፊዎች ምደባዎች ጋራ በተያያዘ እስከ አኹን ካልተቋጩት ጉዳዮች አንዳንዶቹ፣ ይህንኑ በጉልሕ ያስረዳሉ፡፡

ይህም ኾኖ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ፦ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና አገልግሎት በቀኖናው እንዲመራ ማድረግ፤ ካህናት በመንፈሳዊ ተልእኳቸው እንዲፋጠኑ ማስተባበር፤ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋትና በማጠናከር ምእመናንን በሃይማኖትና በምግባር ማጽናትና ማብዛት፤ የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና አንድነት ማስከበርና መቆጣጠር፣ አገልግሎቷንም ማሟላት የሚጠበቅበት ቅዱስ ሲኖዶስ፥ አብነታዊ የእርምትና ማስተካከያ ርምጃዎችን መውሰዱ አልቀረም፡፡ የሚበዙት ኢትዮጵያውያን ምእመናን በስደት በሚሸጋገሩባትበአቴንስ – ግሪክ የምክሐ ደናግል ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን፣ ላለፉት 6 ወራት ሲያወዛግቡ በቆዩት አስተዳዳሪ፣ በአባ ወልደ ሚካኤል ጣውዬ ላይ፣ ሰሞኑን ጠንካራ ውሳኔ አሳልፏል፡፡


ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ጥር 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሔደው ሳምንታዊ ስብሰባ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱንና የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና የሚፃረር ድርጊት ሲፈጽሙ የተገኙትን፣ የአባ ወልደ ሚካኤል ጣውዬን ሥልጣነ ክህነት ይዟል፤ ከማንኛውም አገልግሎት እንዲታገዱም ወስኗል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተፈርሞ ጥር 24 ቀን 2009 ዓ.ም. የወጣው የልዩ ጽ/ቤቱ ደብዳቤ፥ አባ ወልደ ሚካኤል ጣውዬ፣ ከካህናትና ከምእመናን ጋራ በፈጠሩት አለመግባባት ምክንያት፣ ከአስተዳዳሪነት ሥራቸው ተነሥተው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱና ለመንበረ ፓትርያርክ ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ ጥቅምት 2 እና ኅዳር 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አስታውሷል፡፡

tawuyes-priesthood-held
ኾኖም ተጠሪው ግለሰብ፣ በሓላፊነት ላስቀመጣቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ባለመታዘዝና ውሳኔዎቹን ባለማክበር ወደ ሀገር ቤት እንዳልተመለሱና ሪፖርት እንዳላደረጉ ገልጿል፡፡ በተደጋጋሚ የተደረገላቸውን ጥሪ በማጣጣል አለመቀበላቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱንና የቅዱስ ሲኖዶሱን ልዕልና የሚፃረር ድርጊት ሲፈጽሙ መገኘታቸውንም ጠቅሷል፡፡

በመኾኑም፣ ከጥር 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ሥልጣነ ክህነታቸው የተያዘና በቤተ ክርስቲያኒቱም ስም ማንኛውንም አገልግሎት እንዳይፈጽሙ መታገዳቸውን ደብዳቤው አስታውቋል፦ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም በማንኛውም መንፈሳዊም ኾነ ማኅበራዊ አገልግሎት እንዳይሳተፉ የተወሰነ መኾኑን እናስታውቃለን፤” ይላል፣ በአድራሻ ለአባ ወልደ ሚካኤል ጣውዬ የተጻፈው የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ደብዳቤ፡፡

በግሪክ፥ የሀገር ውስጥ ጉዳይ እና የሃይማኖት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንዲኹም፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ቆንስላ ጽ/ቤትን ጨምሮ የሚመለከታቸው የመንግሥት እና የሃይማኖት አካላት ውሳኔውን እንዲያውቁት መደረጉን፣ የደብዳቤው ግልባጭ ዝርዝር ያስረዳል፡፡


በኤጲስ ቆጶስ አንብሮተ እድ መንፈሳዊ ሥልጣን የተሰጠው ቄስ፦ በቤተ መቅደስ፥ በቅዳሴ፣ በውዳሴ፣ በዝማሬና በሰዓታት ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግል፤ ባራኪ፣ ቀዳሽና ናዛዥ የንሥሐ አባት ነው፡፡ የተጸለየበትንና የተባረከውን ቆብ የጫነው መነኩሴም፦ በራሱ ፈቃድ ዓለማዊ ግብርን ኹሉ መንኖ(ትቶ) እንደ ሞተ ሰው ተገንዞ ጸሎተ ፍትሐት የተደረሰለት ካህን ነው፡፡

በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ በትእዛዘ ቀሳውስት እንደተደነገገው፤ ቄስ፣ ያለበትን ቤተ ክርስቲያን ትቶ ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን ከሔደ፣ እንዲመለስ ተነግሮት ካልተመለሰ ከሹመቱ ይሻራል፡፡ (ፍት.ነገ.6፤ ረስጣ 1፤ ቀሌምንጦስ 14፤ ኒቂያ 4)

ዳግመኛም፣ በሀገሩ የተሾመውን ኤጲስ ቆጶስ ንቆና አቃሎ ለብቻው ቤተ ክርስቲያን ከሠራ፣ ኤጲስ ቆጶሱ ሦስት ጊዜ ጠርቶት ካልመጣ፣ እርሱና የመሳሰሉት ከሹመታቸው ይሻራሉ፡፡ (ፍት መን.6፤ ረስጠብ 2፤ ቀሌምንጦስ 22)

ቄስም ኾነ ዲያቆን ከሹመቱ በኃጢአት ከተሻረ በኋላ ደፍሮ ለአገልግሎት ቢገባ ከቤተ ክርስቲያን ተወግዞ ከምእመናን ይለያል፡፡ እያወቁ በዚኽ ድፍረት የተባበሩት ኹሉ ከምእመናን ይለያሉ፡፡ (ፍት.ነገ.6 ረስጠብ 2፤ ቀሌምንጦስ 19)


በተያያዘ ዜና፣ ለተፈጠረው የአስተዳደር ክፍተት የመጨረሻ ዕልባት እስኪሰጥና ሌላ አስተዳዳሪ እስኪመደብ ድረስ፣ የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ የሚያስፈጽሙና የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልግሎት የሚከታተሉ አራት ካህናትን፣ ቋሚ ሲኖዶሱ በውክልና መመደቡን፣ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

scan0089

ውሳኔው ከተላለፈበት ጥር 19 ቀን ጀምሮ፣ የምእመናኑ ተወካይ በመኾን እንዲያገለግሉና ሕዝበ ክርስቲያኑን እንዲያጽናኑ፤ የቅዱስ ሲኖዶሱንም ውሳኔ እንዲያስፈጽሙ የተመደቡት አራቱ ካህናት፡- መሪጌታ ዶ/ር መርዓዊ መለሰ፣ ቀሲስ አየለ ወልደ ጻድቅ፣ ቀሲስ ሰሎሞን ገብረ መድኅንና ዲያቆን ኢዮብ ማንደፍሮ የተባሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ነባር አገልጋዮች ሲኾኑ፤ የአባ ወልደ ሚካኤል ጣውዬውን፥ አባካኝነት፣ ዓምባገነንነትና ኑፋቄ በመቃወምና በማስረጃ በማጋለጥ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወሰድ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል፣ ‘አባ’ ወልደ ሚካኤል ጣውዬ፣ ወደ ካናዳ መሸሻቸው ታውቋል፡፡ በውጩ ሲኖዶስ በተዋቀረውና በሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ሥራ አስኪያጅነት በሚመራው በካናዳ ሀገረ ስብከት፣ የሎንዶን ቅዱስ ገብርኤል ደብር መመደባቸውም ተነግሯል፡፡

ወደ ካናዳ ከማምራታቸው በፊት፥ ያለሀገረ ስብከቱ ዕውቅናና ያለሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ ከሆላንድ ኪዳነ ምሕረት ሌላ ካህን በመጥራት መተካታቸው ተገልጧል፡፡ በተጨማሪም፣ ለሕክምና አንድ ቦታ ደርሼ በ15 ቀን እመለሳለኹ፤” በሚል ሽፋን ከአንዳንድ ምእመናን በርከት ያለ ገንዘብ መሰብሰባቸው ተጠቁሟል፡፡ ቋሚ ሲኖዶሱ ከወሰነ ከኹለት ቀን በኋላ፣ ጥር 21 ቀን፣ በምእመናን ፊት ቆመው፣ በአስተዳዳሪነት ወደ አቴንስ የላካቸውን ቅዱስ ሲኖዶሱን፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱንና ሀገረ ስብከቱን በስድብ ቃል ሲዘልፉ እንደነበርም ተሰምቷል፡፡

ፊቱኑም ለሚያውቋቸው፣ የዕለቱ ስድብና ዘለፋ ዐዲስ አልኾነባቸውም፡፡ ሕጋዊውን ሰበካ ጉባኤ አፍርሰው፣ “ሕዝባዊ ኮሚቴ” በሚል ያደራጇቸውንና “ቦዲጋርዶቼ ናቸው፤ ስለእኔ ደማቸውን ያፈሳሉ” ለሚሏቸው የዋሃት፦ “በጨለማ ቡድን የተጻፈ ደብዳቤ አልቀበልም፤ በአክስዮን የተመረጡ ጳጳሳት አያዙኝም፤ የእኔ ሲኖዶስ እናንተ ናችኹ፤” እያሉ፥ በደላቸውን በማጣራት ያረጋገጠባቸውን ሀገረ ስብከትና ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ የጠራቸውን ቋሚ ሲኖዶስ ሲያጣጥሉ ቆይተዋል፡፡

ጠብና ክርክር እንጂ ሰላምና ፍቅር የማይሰማበት የጥላቻና የንቀት ‘ትምህርታቸው’ መግፍኤ የሚጋለጠው ግን፣ “አዳራሽም ቢኾን አምልኰት እንፈጽማለን” በሚለው የተለመደ የተሐድሶአዊ ኑፋቄ ዛቻቸው ነው፡፡ “የላካቸውን የበላይ አካል በመፍራትና በማክበር እንጂ ከኢትዮጵያ ከመምጣታቸውም በፊት የእምነት ጉድለት እንዳለባቸው መረጃው ደርሶን ጥንቃቄ እንዲደረግ ተናግረን ነበር፤” ይላሉ፤ የሥርዐት ጥሰታቸውንና የአስተዳደር በደላቸውን በማስረጃ ሲያጋልጡ የቆዩት ካህናትና ምእመናን፡፡

ለቋሚ ሲኖዶስ ከቀረቡትና ተደራራቢ በደሎቻቸውን ከሚያሳዩት ማስረጃዎች ለመገንዘብ እንደሚቻለው፤ ‘አባ’ ወልደ ሚካኤል ጣውዬ፣ “ካህንና ዐዋቂ ነኝ” የሚሉትን ያኽል፣ የካህንና የዐዋቂ ጠባይ የላቸውም፡፡

 • መቅደሱን አያከብሩም፤ ሥርዓተ ጸሎቱን አይጠነቅቁም፡፡ ከውጭ ሲመጡ እንደ ጦር ተወርውረው ወደ ቤተ መቅደስ ይገባሉ፤ የመግቢያ ጸሎትና ኑዛዜ አያደርጉም፤ ውዳሴ ማርያም ሳይደገም፣ ተፈሥሒ ብለው መልክአ ሥዕል ሲደርስ፣ ተረኛው ተናጋሪ ጀምሮ ሳይፈጽም ከአፉ ነጥቀው ለመጨረስ የሚታይባቸው ጥድፊያ የመቃብር አፈር ምለሳ ያኽል ነው፡፡ በተለይ የእመቤታችንን ምስጋና በተመለከተ፣ እሴብሕ ጸጋኪ ብሎ የሚያዜም ካለ በንባብ እንዲጨርስ ያጣድፉታል፤ በመዝሙር የሚያመሰግኗትንኳ፥ “የማርያም አጨብጫቢ” ነው የሚሏቸው፤ “ማርያምና ኪዳነ ምሕረት አንድ አይደሉም” ይሉት ማደናገርያም አላቸው፡፡
 • ከቤተ መቅደስ ውስጥ ገብተው ሌሎች ካህናት ሲቀድሱ እርሳቸው ጎዝጉዘው ይተኛሉ፤ ሲነቁ በሞባይል ኢንተርኔት ይጫወታሉ፤ ቡራኬ አይሰጡም፤ አያሳርጉም፤ መስቀል በእጃቸው እንዲገባ አይፈልጉም፤ የእጃቸውንም መስቀል ዘቅዝቀው ይዘው፥ “ከዳቦ መባረኪያ ያለፈ ዋጋ የላትም” እያሉ ይዘብታሉ፤ ሥጋወደሙን ሳይቀበሉ ያቀብላሉ፤ ጸሎተ ምሕላውንና ጸሎተ ፍትሐቱንም በርጋታ አያደርሱም፡፡ ቃለ እግዚአብሔር ቢወድቅ ቢነሣ፣ ቢሠበር ቢሰነጠር ግድ የላቸውም፤ ለነገሩ፣ ገና እንደመጡ፣ “ከ45 ደቂቃ በላይ ጸሎት አስማት ነው፤ ጥቅም የለውም፤ እኔ የመጣኹት፣ ከእናንተ ጋራ ዝቅ ብዬ ኪዳን ላደርስ ቅዳሴ ልቀድስ አይደለም፤ አይመጥነኝም፤ ወንጌል ልሰብክ ላስተምር ነው፤” ብለው ነበር፤

fb_img_1472125575832

 • “የግብረ ዲቁና ብቃት አለው፤ ሊቅ ነው፤ ምሁር ነው፤” ብለው በቤተ ክርስቲያኑ ገንዘብ የአየር ትኬት ገዝተው ወደ ዐዲስ አበባ በመላክ ማዕርገ ዲቁና ያሰጡት አቶ ገድሉ የሚባል የ55 ዓመት ጎልማሳ አለ፤ ባለትዳርና ኹለት ልጆች ያሉት ሹፌራቸው ነው፡፡ ወዳቂውን ቀለም አንሥቶ ሲያፈርጠው፣ ተነሺውን ቀለም ሲዘረጥጠው፣ በተለይ በእመቤታችን መልክአ ሥዕል፥ ወንዱን ሴቴ ፆታ፣ ሴቴውን ወንድ ፆታ፣ ቅርቡን ሩቅ፣ ሩቁን ቅርብ፣ ነጠላውን ብዙ፣ ብዙውን ነጠላ እያደረገ ከመጠን በላይ በመጮኽ በወፍ ዘራሽ ዜማ ሲጫወትበት ይደሰታሉ፤ ገድሉ ዲያቆን ብቻ አይደለም፤ ክርስትና ያነሣል፤ ሜሮን ይቀባል፤ ተጠማቂዎችን በሥላሴ ስም ይቀባል፤
 • ለክብረ በዓል ታቦት ሲወጣ፣ መጎናጸፊያ እንኳ እንዳይነካቸው ይጠነቀቃሉ፤ ታቦቱን ማክበርና መዳሰስ አይወዱም፤ ታቦቱን የሚያከብሩላቸውንና ቅዳሴ የሚቀድሱላቸውን ካህናት፣ ከጀርመንና ከሆላንድ አድባራት ነው፣ ገንዘብ እየከፈሉ የሚያስመጡት፤ አንድ ጊዜ እርማቸውን ታቦቱን ቢያከብሩ፣ ደጋፊዎቻቸው ካህናቱ ላይ ጮኹባቸው፤ ለታቦቱም ለቅዱሳኑም ያላቸው ጥላቻ ልክ የለውም፤ ገድላቸውን በትዕቢት ያስተባብላሉ፤ “ጊዮርጊስ ጊዮርጊስ ትላላችኹ፤ ተራ ወታደር እንጂ ሰማዕት አይደለም” “የተክለ ሃይማኖት እግር የተቆረጠው በጦርነት ነው” በሚሉ የነተቡ ኑፋቄአቸው፡፡
 • በቅዱሳኑ መታሰቢያ ዕለት፣ ስለ ተራዳኢነታቸው ይኹን ስለ ቃል ኪዳናቸው አንድም ቃል አንሥተው አያስተምሩም፤ በጻድቁ የተማፀነ፣ ዐፅማቸውን የዳሰሰ ካደረበት ደዌ ተፈወሰ፤ የሚል የዐይን ምስክርነት በተነገረበት ጉባኤ፥ “በቀጥታ የኢየሱስን ልብስ ንኩት” ብለው እያስታከኩ፣ አማላጅነታቸውን ያረሳሳሉ፤ በአጠቃላይ፣ ‘አባ’ ወልደ ሚካኤል ጣውዬ፣ በእምነት አቋማቸውም፣ በትምህርታቸውም በክህነታቸውም የታመኑ ሰው አይደሉም፤ በታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም መማራቸውንና ቅዳሴውም፣ አቋቋሙም፣ ብሉያቱና ሐዲሳቱም እንዳልቀራቸውና የጉባኤ መምህርም መኾናቸውን ቢናገሩም፣ በተግባር ሊያረጋግጡልን ግን አልቻሉም፤ መምህርነቱ ቀርቶ፣ ከቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ የ2ኛ ዓመት ትምህርታቸውን እንኳ በወጉ ሳያጠናቅቁ ያቋረጡ ሰነፍ ተማሪ እንደነበሩ ነው የሚታወቀው፡፡
 • የግለሰቡ አካሔድ፣ በዋና ዋና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ስልቶች፣ የኖረውን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አፍርሶ ሕዝበ ክርስቲያኑን ዐዲስ ትምህርትና ዐዲስ ሥርዓተ እምነት በመስበክ ከእናት ቤተ ክርስቲያኑና ከማዕከላዊ አስተዳደሩ መነጠል ነው፤ ለዚኽም፣ ሐቀኞቹን ካህናት በመርዛም አንደበታቸው እየጎነተሉ በማሳደድ፣ ገድሉን የመሳሰሉ ምልምሎችን በራሳቸው አምሳል ቀርፀው አባቶችን በማታለል እያስካኑ ያባዛሉ፤ ሕጋዊውን አስተዳደር(የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ) በአድማ አፍርሰው በሕገ ወጥ ምርጫ መዋቅሩን ይቆጣጠራሉ፤ ሕጋዊነትን በመላበስም፣ ካህናቱ፥ ከግሪክ መንግሥት ይሰጣቸው በነበረ የስኮላርሽፕ ክፍያ እየተረዱ፣ ምእመናኑም፣ ዳቦ ጋግረው፣ ሻሂና ቡና አፍልተው በመሸጥ ባጠራቀሙት የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቀማጭ ላይ እንዳሻቸው ለማዘዝ ይመኛሉ፤
 • ከቤተ ክርስቲያን ዕድገትና ልማት ይልቅ የራሳቸውን ምቾት በሚያስቀድመው ግለኛ አስተሳሰባቸው፣ ፋይናንሳዊ አቅሟን የሚያደቁና ለዕዳና ኪሳራ የሚዳርጉ ከፍተኛ ወጪዎችን ይፈጽማሉ፤ ላለፉት 27 ዓመታት ቤተ ክርስቲያኒቱን ያስተዳደሩ አራት አባቶች፣ በወር 200 ዩሮ በዓመት 2ሺሕ400 ዩሮ በቁጠባ ያስገኙበት የነበረውን፣ ከግሪክ ቀይ መስቀል በጎ አድራጎት ድርጅት የተለገሰ ከኪራይ ነጻ ቤት በመተው፣ በየዓመቱ ከ3 እስከ 10 በመቶ ጭማሪ ያለውን የሕንፃ ክፍል በወር 240 ዩሮ በዓመት 2ሺሕ800 ዩሮ ኪራይ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትከፍል አድርገዋል፤ ከ800 ዩሮ በላይ የምትከፍላቸው ደመወዝ እያለ፣ ከ7ሺሕ200 ዩሮ በላይ ወጪ አድርጋ ሙሉ የቤት ዕቃ አስረክባቸዋለች፡፡ ዘግይቶ በተሰማው የሒሳብ ሪፖርት ደግሞ፣ ሌላ ዐዲስ አልጋ መገዛቱ ተገልጾ ነበር፤ በየመንፈቁ አልጋ የሚለውጥ መነኵሴ ምን ይሉታል? የጥፋት እንጂ የልማት ሰው አይደሉም!!

‘አባ’ ነኝ ባዩ ወልደ ሚካኤል ጣውዬ፣ ከሆላንድ እየጠሩ እንዲቀድሱና ታቦት እንዲያከብሩ በማድረግ ሲከፍሏቸው የቆዩትን አምሳያቸውን፣ በሌላቸው ሥልጣን በአስተዳዳሪነት ተክተው፣ ምእመናኑን በመሸንገል ሸሽተዋል፡፡ እስከ አኹን፣ እዚያው አውሮፓ እንዳሉ አልያም ወደ ኢትዮጵያ የሔዱ የሚመስላቸው ጥቂት ወዳጆቻቸው እየጠበቋቸው ቢኾንም፣ እርሳቸው ግን በድብቅ ወደ ካናዳ ሸሽተው በተመደቡበት ደብር፣ ካለፈው እሑድ ጀምሮ እንደ ጅቡ፥ ቁርበት አንጥፉልኝ፤ ሊሉ ጀምረዋል፡፡

 • የአንዲት ቤተ ክርስቲያን በአስተዳደር መለያየት የጠቀማቸው፣ እንደ ‘አባ’ ወልደ ሚካኤል ላሉት፣ ከሀገርና ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ የራሳቸውን ጥቅምና ምቾት የሚያስቀድሙ፣ በእግዚአብሔር ሥልጣነ ክህነትና በመቅደሱ የሚሣለቁ አማሳኞችንና መናፍቃንን ነው፤ ሕገ ወጥ ጥቅማቸውን ሲያጡና ኑፋቄአቸው ሲጋለጥ፣ መሸሻና ማኩረፊያ እያደረጉት ነውና፡፡ በአንጻሩ፣ የወልደ ሚካኤል ጣውዬን ኩብለላ ከጅምሩ በመከታተል፣ የቶሮንቶ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቀናዒና ንቁ ምእመናን፣  ያሳዩት ተቃውሞ የሚጠቀስ ነው – ቤተ ክርስቲያን በአስተዳደር ብትለያይም፣ የተሐድሶ መናፍቅ መፈንጫ መኾን የለባትም፤” ብለው በጽኑ የሚጋደሉ ናቸውና፡፡
 • የአስተዳደር ልዩነቱ፣ በተጀመረው የሰላም ሒደትና እግዚአብሔር በፈቀደው ጊዜ ኹነኛ እልባት እስኪያገኝ ድረስ፣ ቢያንስ እንደ ‘አባ’ ወልደ ሚካአል ጣውዬ ያሉ፣ በትምህርታቸውም በክህነታቸውም የማይታመኑ ጒግማንጒጐችን እንወቅባቸው!! የስዱዳኑ መጠለያ፣ መጽናኛና መማፀኛ የኾነችውን አንዲትና ኵላዊት ቤተ ክርስቲያን እንዳያውኩ እናጋልጣቸው!! 
Advertisements

8 thoughts on “ቋሚ ሲኖዶስ: የአቴንሱን አባ ወልደ ሚካኤል ጣውዬን ሥልጣነ ክህነት ያዘ፤ በማንኛውም አገልግሎት እንዳይሳተፉ ታገዱ!

 1. Anonymous February 16, 2017 at 1:27 pm Reply

  በጣም ጥሩ ነዉ እንግዴህ መጭዉን ሰንበት እንጠብቃለን ቅዱስ ሲኖድስ የፈቀደላቸዉ ሊቃዉንቶች በክብር ወደ ቀደመ አገልግሎት ይመለሳሉ ማለት ነዉ እንደ ሐራ ዘገባ እናም ሥረአተ ቅዳሴዉ በካሕናቱ መዝሙሩ ደግሞ በመርጌታዉ ይካሔዳል የእሁድ ሰዉ ይበለን።

  • Anonymous February 16, 2017 at 8:02 pm Reply

   Ante sew chirstyan neh new yesu teketay neh kehonih telo bileh bensha tateb metsafe qadirm yasifelighal yehonewin yetederegewin yemideregewin enka ayteh atasitewilm masitewalun ystih lela min elalehu ayin yaweta kihdet yebatechirstyan amilak libona ystih minm alilm… kalitetemeqih yemiketilew wedeanite new…..yewahanese ywerswa lemir. ..yewahan is midrin ywersalu nitsuh tenagarywoch kenesu ychemirh

   • Anonymous February 21, 2017 at 6:09 pm

    ለማንኛዉም ደብዳቤዉ ከወጣ ሐራና ቤተክሕነት ተከታያቸዉ ዘመድኩን የአንድን ካሕን ክሕነት ከያዙ በምትካቸዉም አራት ሰዉ ከመደቡ አንድ ሰንበት አልፎል ።ቀጣዮን እናያለን እኔ በግሌ። የግለሰብ ጉዳይ አይደለም ደግሞም አላጠፉሁም መነኩሴዉ ምንም አልበደሉም ነገሩ የተገላቢጦሽ መሆኑ ዉሳኔዉ በቀል በመሆኑ ክሱ አሉባልታ የተሞላ በመሆኑ ነዉ ይልቅ እርሶ ንሰሐ ግቡ ካልገባዎትነገሩን በጥልቀት ይመርምሩ አባ ወልደሜካኤል የሐይማኖት ችግር የለባቸዉም የአስተዳደርም እንደዚሁ።

 2. Anonymous February 17, 2017 at 7:41 am Reply

  Egziabiher hulem tsnatun yesitachihu. birtulin…..

 3. Anonymous February 18, 2017 at 8:56 am Reply

  ማውገዝ የሚችል ጳጳስ አለ እንዴ? ካለ ግን
  ነፍስ ያልገደለ
  በዝሙት ያልረከሰ
  በሙስና ያልጨቀየ
  በዘር በሽታ ያልተለከፈ
  በድንቁርና ጨለማ ያልተዋጠ
  ቤተመንግስት ጢስ ሲጨስ የማያሳክከው
  ወፈ ገዝት ያልሆነ
  የፅዋ ማህበር የፈረስ ጋሪ ያላደረገው
  ግራ ቀኙን ማየት የሚችል
  ከጥንቆላ ይልቅ በእግዚአብሔር የሚመካ
  በግምት የማይፈርድ
  ለቤተክርስቲያን ምሁራን የሚሳሳ
  ከበቀል ይልቅ በፍቅር አይን የሚያይ መሆን ይገባዋል
  በአቡነ ማትያስ የሚመራው የ አራት ኪሎው ሲኖዶስ ግን ከላይ ከጠቀስኳቸው በተቃራኒው የቆመ የነፍሰ በላዎች ስብስብ መሆኑን አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው ይህንኑም ሀቅ ከስጋ ዘመዶቻቸው ጀምሮ በበቀል ጅራፍ የገረፏቸው ሊቃውንት ቋሚ ምስክሮች ናቸው ከዚህም ባሻገር በረከት እናገኛለን ብለው የቀረቧቸውን እናቶችና እህቶች እንደ ጆፌ አሞራ በማፈን ከበረከት ይልቅ መርገምን ከጽድቅ ይልቅ ዲቃላን የሚያሳቅፉ አብዝተው የሚያሸክሙ የፈሪሳውያን ስብስብ ነው
  የሚሰሩት ስውር ሴራ ፀሐይ እንዳያገኘው የጨለማን በርኖስ አብዝተው ይደፋሉ በዚሁ ጨለማቸው ውስጥ ሙዳየ ምፅዋትን ጨምሮ ብዙ ነገር ይደፋሉ ግን እስከ መቼ ? ? ? ?
  እውነት ነው የምላችሁ በአቡነ ማትያስ የሚመራው የባለጌ ስብስብ ማውገዝ ከተቻለ እኔም እነርሱን አውግዣአለሁ ምክንያቱም ቅድስና የሌለው ክህነት ፈሪ እጅ ያለ ዱላ ነው ! ! ! !
  ከውግዘት በኋላ ማትያስን ፓትርያሪክ አድርጎ ያሳየን ምን አልባት የጀግናው አባ ወልደሚካኤል ዘመነ ፕትርክና ደርሶ ይሆናል
  የቀደሙት ሳኦሎች እንጂ ዳዊቶች አይደሉምና ምክንያቱም የሴይጣን የግብር ልጆች እነ ሳዊሮስ ፣ ዲዮስቆሮስ እነ ሐራ ያለ አንድ ነገር አልተተከሉም

  መልአኩ አብስሯል ጌታ ሊወለድ ነው ! ! !

 4. shewandagn February 18, 2017 at 9:53 pm Reply

  ሰላም ወቅታዊ ዜና ማስተላለፋችሁ ይሚያበረታታ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ በሚቀርብ ዜና ላይ ቅዱሳን አባቶችንና ሰማእታትን በተመለከተ እገሌ ይህን አለ በማለት የተሀድሶዎችንና የፕሮቴስታንቶችን ቃል መድገሙ ራስን ሰድቦ ለሰዳቢ ማስተላለፍ ስለሞሆን ይስተካከል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዘገባ ላይ የአቴንሱ መነኩሴ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስና ስለ ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ..… እንዲህ አሉ ይሚለው ትክክል አይደለም፤ ያሉትን ከመድገም ቅዱሳንን ያቃልላሉ ቢባል በቂ ነበር፡፡
  ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር

  >

 5. Anonymous February 20, 2017 at 3:36 pm Reply

  ደቡብ አፍሪካ የተመደቡት አገልጋዮች ስማቸው ይታወቃል ወይ?
  እነማን እንደሆኑ የት እንደ ነበሩ ምን እንደሰሩ ለሕዝቡ ይፋ ሆኖ ከወዲሁ ግልጽ አስተያየት እንዲሰጥባቸው አይደረግም?

 6. Anonymous February 20, 2017 at 7:06 pm Reply

  ከላይ የቀረበው ገለፃ ጥሩ ነው፣ ስለ አባ ወልደ ሚካኤል የማውቀው ጉዳይ የለም፣ ስለዚህ መረጃውን እቀበለዋለሁ፡፡ ነገር ግን “ከሆላንድ እየተመላለሱ፣ እየተከፈላቸው…..መሰላቸው” እየተባለ የተገለጹት አባት ላይ የተጻፈው በጥንቃቄ ይታይ፡፡ እኒህን መነኩሴ በቅርብ ስለማውቃቸው ማውራት እችላለሁ፡፡ ወደ ግሪክ፣ አቴንስ እየተመላለሱ እንደሚያገለግሉ ሁሉም ሰው ቢያውቀውም አሁን ክህነታቸው ተያዘባቸው ከተባሉት ጋር ምንም ዓይነት የግብር መመሳሰል እንደማይኖራቸው ነው መገመት የምችለው፡፡ ግን “ለምን ይመላለሱ እንደነበር፣ ማን የትራንፖርት እንደሚከፍልላቸው” ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ተቸግረው እንደሚመላለሱ አውቃለሁ፣ ለምን ብዬ ጠይቄያቸው ግን አላውቅም፡፡ “ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” እንዳይሆን ነገሩ፡፡ከዚህም በላይ ከግሪኩ በተጨማሪ በአራት አብያተ ክርሰቲያናት እየተዘዋወሩ ሲቀድሱ፣ ለሲኖዶስም ሆነ ለሀገረ ስብከት ታዛዥ ሲሆኑ፣ ከምእመናን ጋር ተግባብተው፣ ደረጃቸውንና ድርሻቸውን አውቀው ሲያገለገሉ ነው የማውቃቸው፡፡ ለዚህ የሐራ ተዋሕዶ ዜና እንደ ምንጭ ሆነው ከቀረቡት ሰዎች ይልቅ በእኒህ መነኮስ ላይ የተሻለ እርግጠኛ መሆን እችላለሁ፡፡ ቢያንስ የተጣራ መረጃ እስኪገኝ ድረስ ከስድብ እና አብሮ ከመፈረጅ ብንቆጠብ ጥሩ ነው-እናስተውል! በኔ በኩል ይህን ፍረጃ ለማመን በጣም ይከበደኛል፡፡ መነኮሴውም እዚህ ላይ እንደተጠቀሰው “አስተዳዳሪ” ተብለው እንደተሾሙ የሚያስቡ ከሆነ አዝናለሁ፣ ያደርጉታል ብዬ አላምንም፡፡ በሌላ በኩል፣ አስተዳዳሪነት በሌላ አስተዳዳሪ የሚሾም እንዳልሆነ እና ያለ ሹመት ደበዳቤ እንደማይደረግ እየታወቀ እዚህ ዜና ላይ “በሌላቸው ሥልጣን በአስተዳዳሪነት ተክተው” ተበሎ ተራ የሆነ አገላለፅ መቀመጡ ስህተት ነው ባይ ነኝ፡፡ የሆነው ሆኖ ሰው ላይ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል የሚሆነውን በቀጣይ እናያለን፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያንን እና ምእመናንን ለመጠበቅ መረጃዎቸን የመለዋወጡ ጠቃሚነት ያክል፣ በመታዘዝ የሚያገለግሉ ካህናትን ሰብእና በከንቱ እንዳናጎድፍ እንጠንቀቅ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: