የአ/አበባ ሀ/ስብከት: “የተከፈለው 50ሺሕ ብር፥ የፐርሰንት ውዝፍ እንጂ ጉቦ አይደለም፤” ሲል ዘገባውን አስተባበለ

  • ፐርሰንት፥ ከደመወዝ ተቀንሶ አይከፈልም፤ አሠራሩም አየር ባየር እንጂ ሕጋዊ አይደለም!”

/የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ/

*              *            *

(አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ፣ የካቲት 4 ቀን 2009 ዓ.ም.)

a-a-diosces-head-office

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የደብረ ተኣምራት ዳግማዊት ጻድቃኔ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ሠራተኞች፤ ለተፈቀደላቸው የደመወዝ ጭማሪ ማጸደቂያ፣ ለሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች የተሰጠው ብር 50 ሺሕ ጉቦ እንዲመለስ ታዘዘ፤” በሚል ርእስ፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ያወጣው ዘገባ፣ “ያልተጣራና መሠረተ ቢስ ነው፤” ሲሉ ሀገረ ስብከቱ እና የደብሩ ጽ/ቤት አስተባበሉ፡፡

ሀገረ ስብከቱ፣ በዋና ጸሐፊው ቀሲስ ኃይሉ የማነ ቲተርና ፊርማ ለዝግጅት ክፍሉ ባደረሰው ማረሚያና ማስተባበያ እንደገለጸው፣ የደብሩ ካህናትና ሠራተኞች፣ እንደማንኛውም ገዳማትና አድባራት አገልጋዮች ኹሉ፣ ወቅቱን የጠበቀ የደመወዝ ጭማሪ ማግኘት፣ በቃለ ዐዋዲው እና በሕገ ቤተ ክርስቲያን የተፈቀደ መብታቸው እንጂ የግለሰቦች ችሮታ እንዳልኾነ አስገንዝቧል፡፡

አያይዞም፣ ደብሩ ከማንኛውም ገቢው ላይ ኻያ በመቶውን የሀገረ ስብከት ድርሻ እንዲከፍል በቃለ ዐዋዲው መደንገጉን አስታውሶ፤ በዘገባው የተጠቀሰውና ከደብሩ ጽ/ቤት ወጣ የተባለው 50ሺሕ ብርም፣ በወቅቱ ያልተከፈለ የደብሩ የኻያ ፐርሰንት ውዝፍ ሒሳብ መኾኑን አስረድቷል፡፡ ይህም፣ ሀገረ ስብከቱን ወክሎ በሚሠራው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ስም፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ገቢ መደረጉን በመጥቀስ ደረሰኙን በአስረጅነት አቅርቧል፡፡ “ወደ ተቋሙ ባንክ የገባውን ገንዘብ ለግለሰቦች እንደተሰጠ አስመስሎ መዘገቡ ሚዛናዊነት የጎደለው ነው፤” ሲልም ዘገባውን ተቃውሟል፡፡

አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ ከአምስት የማይበልጡና መላውን ካህናትና ሠራተኞች የማይወክሉ ናቸው፤ ያለው የደብሩ ጽ/ቤትም በተመሳሳይ፤ 50ሺሕ ብሩ፣ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ ከነበረው ውዝፍ ላይ በታዘዝነው መሠረት የከፈለነውና ገቢ የኾነ ነው፤ ብሏል፡፡ የካህናቱና የሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪም፣ ውዝፍ ፐርሰንቱ እንዲከፈል በማድረግ በወቅቱ ጸድቆ፣ ከኅዳር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እየተከፈለ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅም ወደ ደብሩ የመጡት፣ በአስተዳደሩ ጥያቄና በክፍለ ከተማው ደብዳቤ፣ የልማት እንቅስቃሴውን ለመጎብኘትና የሥራ መመሪያ ለመስጠት ተጋብዘው እንጂ፣ አቤቱታ አቅራቢዎቹ እንዳሉት፣ “ሊመክሩባቸው አይደለም፤” ሲል ዘገባውን አስተባብሏል፡፡

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ መጋቤ ሠናያት የቻለው ለማ በበኩላቸው፤ ሰበካ ጉባኤው ሳይነጋገርበትና ሳይወስንበት የደብሩ ጽ/ቤት ሓላፊዎች፣ በሌላቸው ሥልጣን አየር ባየር የፈጸሙትና ግልጽነት የጎደለው አሠራር ከማኅበረ ካህናቱ ጋራ የተፈጠረውን ልዩነት እንዳሰፋውና ሒደቱም ሕጋዊነት እንደሌለው ይናገራሉ፡፡


ማንኛውም ሰው ለቤተ ክርስቲያንም፣ ለግለሰብም እንደሚለግሰው፥ ካህናትና ሠራተኞች በጸደቀላቸው ጭማሪ ስኬል መሠረት ደመወዛቸውን ከተቀበሉ በኋላ ተጠይቀው በፈቃዳቸው ቢሰጡ ይችላሉ፡፡ የደብሩ ጽ/ቤት ሓላፊዎች ግን፣ ገንዘቡ ወጪ ሳይደረግና ሳይሰጧቸው ገና አየር ባየር ሥራ ነው፣ አካሔዳቸው፡፡

ደመወዛችኹ ይህን ያኽል ጸድቆላችኋል ብለው በግልጽ ደብዳቤ ጽፈው አልሰጧቸውም፤ ደብዳቤ ባይጽፉም፣ ሠራተኞቹን ሰብስበው፥ ይህ፣ ይህ ኾኖላችኋል፤ ብለው በዐዋጅ አልነገሩም፡፡ ይኼ ጉዳይ ነው፣ ካህናቱ ላይ ቅሬታ የፈጠረውና፣ የተዋዋልነው ስለሌለ አቤቱታ እናቅርብ፤ ብለው ወደኛ ሊመጡ የቻሉት፡፡ በማጣራቱ ይኼን ይኼን ጭምር እኮ ነው አግባብነት የለውም፤ ያልነው፡፡


የደብሩ የኻያ በመቶ ውዝፍ ዕዳ መከፈል ያለበት፣ ከደብሩ ገቢ እንጂ ከሠራተኞች ደመወዝ ተቀንሶ መኾን የለበትም፤ ያሉት መጋቤ ሠናያት የቻለው፣ የኹለት ወሩ የደመወዝ ጭማሪም የተቀነሰው፣ የጽ/ቤቱ ሓላፊዎች በራሳቸው እንጂ፣ የሚመለከተው ሰበካ ጉባኤ በተገኘበት ተነጋግረውና ወስነው እንዳልኾነ ጽ/ቤታቸው ባደረገው የደረሰኝና የገጽ ለገጽ ማጣራት ማረጋገጡን ገልጸዋል፡፡


የደብሩ ጽ/ቤት፦ “ከሠራተኞች ጋራ ተስማምተን፣ ተነጋግረን ተደራድረን፣ ደመወዙ ጸድቆ ከመጣ ብር እንለቃለን ብለው በገቡት ቃል ነው የቀነስንባቸው፤ ደመወዝ እንዲጨመርልን ይህን ዕዳ ከፈልን ነው፤” የሚለው፡፡ ካህናትና ሠራተኞች ቃል የገቡበትንና ስምምነቱን የሚገልጽ ቃለ ጉባኤ ግን አላቀረበም፡፡ እዚኽ ሒደት ውስጥ የገባውም ደመወዝ ለማስጨመር ነው፤ ደመወዝ ለማስጨመር ከኾነ ደግሞ ከደመወዝ ተቀንሶ አይደለም፤ ሰው እንዳቅሙ ነው የሚያገኘው፤ እንዳቅሙ ነው መብላት ያለበት፤ በሌለው ሰዓት ከሠራተኛ ላይ ደመወዝ ማጸደቂያ ብሎ መቀነሱ የአሠራር ግድፈት አለው፡፡ ይህን ይህን መሠረት በማድረግ ነው፣ እኛ ያጣራነው፡፡


የደብሩ ጽ/ቤትና ሀገረ ስብከቱ፥ “ለፐርሰንት ውዝፍ የተከፈለና ገቢ የተደረገ ነው፤” ስለሚሉት 50ሺሕ ብር የተጠየቁት መጋቤ ሠናያት የቻለው፣ “የክፍለ ከተማው ጥያቄ የ50ሺሕ ብር አከፋፈል ሒደት አይደለም፤ ከሠራተኞች ላይ የተቀነሰው የገንዘብ አከፋፈል ሒደትና አሠራሩ ትክክል አይደለም፤ ፍትሐዊ አይደለም፤ ነው፤” በማለት የተባለው ክፍያ ከደመወዝ ጭማሪው ጋራ ግንኙነት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡


ለሚፈለግባቸው የፐርሰንት ውዝፍ፣ እንዳሉት፣ ኃምሳ ሺሕ ብር ለሀገረ ስብከቱ ገቢ አድርገው ይኾናል፡፡ ከካህናቱ ደመወዝ ተቀንሶም ይኹን፣ ከሌላም ቦታ አምጥተውም ይኹን፣ እኛ አናውቅም፤ ፐርሰንት ከመክፈል ጋራ ግንኙነት የለውም፡፡ የክፍለ ከተማው ጥያቄ፣ እነርሱ ያሉት 50ሺሕ ብር አከፋፈል ሒደት አይደለም፤ የክፍለ ከተማው ጥያቄ፥ ከደብሩ ካህናትና ሠራተኞች ላይ የተቀነሰው የገንዘብ አከፋፈል ሒደትና አሠራሩ ትክክል አይደለም፤ ፍትሐዊ አይደለም፤ ነው፡፡


Advertisements

One thought on “የአ/አበባ ሀ/ስብከት: “የተከፈለው 50ሺሕ ብር፥ የፐርሰንት ውዝፍ እንጂ ጉቦ አይደለም፤” ሲል ዘገባውን አስተባበለ

  1. Binyam Solomon February 11, 2017 at 2:45 pm Reply

    በዚህ አገር በረቀቀ ሁኔታ ስርቆትና ሌብነት ይካሄዳል ቢባል ቤተ ክህነትና ቤተ ክህነት ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ጭንቅላታቸው እውቀት አልባ ቢኾንም ስርቆትን ግን ከማንም በላይ ቀጽለዋታል፡፡ አንድ ነገር ሲያደርጉ መውጫቸውን አዘጋጅተው ነው፡፡ በዚህኛው አካሄድ ግን ሁነኛ መውጫ ያዘጋጁ አይመስልም፡፡ ዬት አገር ነው የአንድ አጥቢያ ፐርሰነት ከካህናት ኪስ የሚከፈለው? እነሱም ቤተሰቦቻቸውም በረሐብ እየተሰቃዩ ቀንና ሌሊት የሚያገለግሉት ከፐርሰንት በላይ አይደለም ወይ? ጸሎተ ሃይማኖትን በአግባቡ ለማይወጣ ሌባ በሺዎች ደሞዝ የምትከፍል፣ ለቁጥር የሚታክት ገንዘብ እንዲሰርቅ በተመቸ ቦታ የሚያስቀምጥ ቤተ ክህነት እኮ ነው ያላት ይህች እምነቷ የቀና፣ ሥርዓቷ የተስተካከለ፤ በእውነት ቅዱሳንን ሊቃውንትን ያፈራች ቤተ ክርስቲያን፡፡ እኔ መንግሥት ጣልቃ ይግባ አልልም ቢያንስ ለአሁኑ፡፡ ምእመናን ጣልቃ ይግቡ፡፡ ሁሉም የሚደረገው በእነሱ ገንዘብ ነው፡፡ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር – ቃለ ዐዋዲው እስከ አሁን ሠርቶ ቤተ ክርስቲያኒቱን መከራውን አሻግሮ ዛሬ አድርሷታል፡፡ አሁን በዘመነ ዘረፋ ቃለ ዐዋዲው ምእመናንንም ኾነ ካህናቱን የሚጠቅምበት ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ ሌላ የአሠራር ሕግ መውጣት አለበት፡፡ የአጥቢያን አስተዳደራዊ ማእከልና ሥልጣን ለምእመናን የሚሰጥ፡፡
    ለእናንተም የምለው አለኝ፡፡ ዘገባ አታስረዝሙ፡፡ አጠርና ጉዳዩ ላይ ያተኮረ አድርጉት፡፡ የማንበብ ጊዜውም፣ ልምዱም፣ ባሕሉም የሌለን መኾኑን እወቁ፡፡ ለመኾኑ እነዛ ካህናት አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው ያሉት? እስቲ በየደብሩ በተመሳሳይ ሁኔታ ለእውነት ቆመው የተቀጡና እየተቀጡ ያሉ ካህናትን ቢያንስ ስማቸውን አውጡ፡፡ እኔ እነዚህ ሰዎች ተሰባስበው ሌላውንም አስተባብረው ሰላማዊ ሰልፍ ቢወጡ እላለሁ፡፡ የሚሰማ የቤተ ክህነት በለስልጣን ካለ፡፡ ገንዘብ የማይቀበል፤ ለሌባ ያላደረ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: