ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ዛሬ ምሽት ወደ ጄኔቭ ያቀናሉ

  • በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ም/ቤት ጽ/ቤት፣ የሥራ ጉብኝት ያደርጋሉ
  • ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በኋላ፣ ኹለተኛው ፓትርያርካዊ ጉብኝት ነው
  • እንደ መሥራች አባል፣ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነታችንን የምናጠናክርበት ነው
  • በስዊዘርላንድና በሮም አብያተ ክርስቲያናትም ትምህርትና ቡራኬ ይሰጣሉ

*                     *                    *

pat-wcc-ecumenical-center-official-visit
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ስዊዘርላንድ – ጄኔቭ በሚገኘው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት የኢኩሜኒዝም ማዕከል(Geneva Ecumenical Center)ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገለጸ፡፡

ዛሬ ማምሻውን፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፤ ከምዕራብ ሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ጋር ወደዚያው የሚያቀኑት ቅዱስነታቸው፣ ከነገ የካቲት 1 ቀን ጀምሮ በሚያካሒዱት የአራት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት፣ የምክር ቤቱን ሓላፊዎች ያነጋግራሉ፤ የሥራ ክፍሎቹን ተዘዋውረው ይጎበኛሉ፡፡

wcc-ecumenical-center
ጄኔቭ፣ ምክር ቤቱ፣
አስተዳደራዊ ተግባራቱን የሚያከናውንበት ዋና ጽ/ቤቱ ያለበት ሲኾን፤ የኢኩሜኒዝም ማዕከሉም፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር በተቋቋመበት የኢኩሜኒዝም መንፈስ(ecumenical engagement)፦ በነገረ ሃይማኖት ለመወያየትና የእርስ በርስ ተራድኦን ለማጠናከር፥ የአባል አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ ልኡካን፣ የነገረ መለኰት ምሁራንና ተማሪዎች፣ ካህናትና አማኞች በቡድንም በተናጠልም እየተገናኙ የሚመክሩበት ተቋም ነው፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የምክር ቤቱ ጉብኝት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር መሥራች የኾነችው ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን፣ የቋሚ አባልነት አስተዋፅኦዋን እንደምትወጣበት እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቷን እንደምታጠናክርበት ተገልጿል፡፡ የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ በ1985 ዓ.ም. በምክር ቤቱ አድርገውት ከነበረው በመቀጠልም፣ ለኹለተኛ ጊዜ የሚካሔድ ፓትርያርካዊ ጉብኝት እንደሚኾን ተጠቅሷል፡፡

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር(World Council of Churches) መሥራች ጉባኤ፣ እ.አ.አ በ1948 በአምስተርዳም ሲካሔድ፣ በወቅቱ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እንደራሴና የሐረር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ልኡካን በመምራት መሳተፋቸው ይታወሳል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በእስክንድርያ መንበረ ማርቆስ ሥር ለ1600 ዓመታት ያኽል ከቆየች በኋላ በራስዋ ጳጳሳት፣ ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትርያርክ መመራት ከጀመረች ወዲኽ የውጭ ግንኙነቷ እያደገና እየሰፋ መጥቶ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ተጎናጽፋለች፡፡ የውጭ ግንኙነት የምታደርገውም፡- በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ፣ በመላው አፍሪቃ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ፣ በኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ እንዲኹም በመሪዎች ደረጃና በመልእክተኞች ጉብኝትና ልውውጥ ነው፡፡

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር፣ እ.አ.አ በ1948 በአምስተርዳም ከአደረገው መሥራች ጉባኤ ቀጥሎ፥ በኢባንስተን/አሜሪካ/ በ1954፣ በኒውዴልሂ/ሕንድ/ በ1961፣ በኡፕሳላ/ስዊድን/ በ1968፣ በናይሮቢ/ኬንያ/ በ1975፣ በባንኮበር /ካናዳ/ በ1983፣ በካምቤራ/አውስትራልያ/ በ1991፣ በሐራሬ/ዝምባቡዌ/ በ1998፣ በፖርት አሌግሬ/ብራዚል/ በ2006፣ በቡሳን/ደቡብ ኮርያ/ በ2013 በአጠቃላይ ዐሥር ጠቅላላ ጉባኤያትን አካሒዷል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ማኅበሩ፣ በ1963 ዓ.ም. ያካሔደውን አራተኛ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከማስተናገዷም በላይ፣ እ.አ.አ በ2006 በፖርት ኤልግሬ – ብራዚል በተደረገው 9ኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ የኦርየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን በመወከል የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ኾነው በመመረጣቸው ምክር ቤቱን በአመራርነት ለማገልገል ችላለች – “ለቤተ ክርስቲያናችን ሲደርስ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለኾነ በዓለም አቀፍ መድረክ የተገኘ የቤተ ክርስቲያናችን ክብር ኾኖ ተመዝግቧል፡፡”

የአብያተ ክርስቲያናት ዓለም አቀፍ ተቋም የኾነው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር፣ የምሥረታ ሰነድ እንደሚገልጸው፣ ማኅበሩ የተቋቋመው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አዳኝ መኾኑን በሚያምኑና በዚያም እምነት አንድ አምላክ ለሚኾን ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ የሚገባውን ክብርና ምስጋና በአንድ ቃል ለማቅረብ በተባበሩ አብያተ ክርስቲያናት ነው፡፡

ዓላማና ተግባሩም፣ ምሥጢረ ቊርባንን በአንድነት ለመፈጸም እስከሚቻል ድረስ አባል አብያተ ክርስቲያናት ስለ እምነት አንድነት የሚያደርጉትን ጥረት ማበረታታትና የክርስትናው ዓለም አንድነቱን በተግባር እንዲያሳይ ማብቃት ነው፡፡ በአባል አብያተ ክርስቲያናት መካከል ሊኖር የሚገባውን የእርስ በርስ ተራድኦ ማጠናከርም ሌላው የድርጅቱ ተግባር ነው፡፡

ማኅበሩ፣ ዓላማውን ተግባራዊ የሚያደርገው፦ በጠቅላላ ስብሰባ፣ በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ፣ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባና በሌሎችም የሥራ ክፍሎች ነው፡፡ ሕጉ ለአባል አብያተ ክርስቲያናት ተከታዮች ብዛት ከፍተኛ ግምት ስለሚሰጥ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም፣ እንደ ምእመናንዋ ብዛት በሰባት ዓመት አንድ ጊዜ በሚካሔደው ጠቅላላ ስብሰባ ዐሥራ ኹለት፣ በዓመት አንድ ጊዜ በሚደረገው የማዕከላይ ኮሚቴ ስብሰባ ደግሞ ኹለት መቀመጫዎችን በመያዝ ትሳተፋለች፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነቷንም ታጠናክራለች፡፡

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በአኹኑ ወቅት፣ ጥንታውያን ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ በተለያዩ አደረጃጀቶች ያሉና በ110 የዓለም አገሮች የሚገኙ 348 የክርስትና እምነት ተቋማትን በአባልነት ይዟል፤ በእኒኽም ከ500 ሚሊዮን በላይ የዓለም የክርስትና አማኞች እንደሚወክሉ የምክር ቤቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የኢኩሜኒዝም መንፈስ፣ የራስን ጠብቆና የሌላውን መብት አክብሮ እርስ በርስ በመተዋወቅና በመጠናናት ጥላቻንና ክፉ አስተሳሰብን ለማስወገድና አብሮ ለመሥራት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማኅበሩ መሥራች አባል የኾነችው፣ የኢኩሜኒዝምን መንፈስ በትክክለኛ ዓላማው በመቀበል ነው፡፡ ይኹንና፣ በክርስትናው ስም በሚጠሩ “እናድሳለን ባዮች” ፕሮቴስታንታውያን የመንጋ ቅሠጣ ተግባር መታወኳ መሠረተ ዓላማውን የሚፃረር ነው፡፡

ማኅበሩ፣ በዝምባቡዌ – ሐራሬ 8ኛ ጠቅላላ ጉባኤው፣ የኢኩሜኒዝምን “የጋራ መግባባትና ርእይ” (a shared understanding of and vision for ecumenical engagement) የተመለከተ የፖሊሲ ዶኩመንት በማእከላዊ ኮሚቴው ማዘጋጀት አባል አብያተ ክርስቲያናት እንዲፈርሙበት ያደረገውም፣ በተለይም ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት በዚኽ ረገድ በሚደርስባቸው ፈተና ለማኅበሩ ሲያቀርቡት በቆዩት አቤቱታ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕም፦ “በኢኩሜኒዝም ስም፣ ለገንዘብ ብሎ ራስን መቸርቸር ወይም የሌላውን ትውፊት ከራስ ጋር ማዳበል፣ በታሪክና በትውፊት ላይ ማመፅ ነው፤” ብለው ነበር፡፡

በተያያዘ ዜና፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዚኹ ይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸው አጋጣሚ፣ በስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ተገኝተው ጸሎተ ቅዳሴ በማድረግ፣ ትምህርትና ቡራኬ እንደሚሰጡ ተጠቁሟል፡፡

swiss-eotc-parishes-and-congregations-service-schedule
ከስዊዘርላንድ ዐሥር ከተሞች መካከል በአምስቱ አብያተ ክርስቲያናት ተቋቁሞባቸዋል፡፡ እነርሱም፡- ጄኔብ መድኃኔዓለም፣ ሎዛን ቅዱስ ገብርኤል፣ በርን ቅድስት ሥላሴና ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ዙሪክ ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲኹም ባዝል ቅዱስ ሚካኤል ሲኾኑ፣ በተቀሩት ከተሞችም በየወሩ የቅዳሴ አገልግሎት፣ በየሦስት ወሩም ጉባኤ እየተሠራ ትምህርት እንደሚሰጥ፤ በመልአከ ገነት ቆሞስ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደ ማርያም ሰብሳቢነት በሚመራው የአብያተ ክርስቲያናቱ የሰበካ አስተዳደር የወጣው መርሐ ግብር ያሳያል፡፡

swiss-eotc-parishes-and-congregations-service-schedule2
ጄኔብ የሚገኙት የመላው አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ፣ ከአብያተ ክርስቲያናቱ አስተዳዳሪ ጋራ በመኾን፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የሚመራውን ልኡክ ተቀብለው ያስተናግዳሉ፡፡ በጉብኝታቸው መጨረሻ ወደ ሮም የሚዘልቁት ቅዱስነታቸው፣ በእሑድ ሰንበት በዚያ ለሚገኙት የቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምእመናን ቡራኬና የሥራ መመሪያ ሰጥተው ይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸውን በማጠናቀቅ እንደሚመለሱ ተገልጿል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: