ለደብሩ የደመወዝ ጭማሪ ማጸደቂያ: ለሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ጎይትኦም ያይኑና ለሒሳብና በጀት ሓላፊው 50ሺሕ ብር ጉቦ ተከፈለ፤ እንዲመለስ ታዟል!

 • አለቃውና ጸሐፊ በቁጥጥር ሥር ቢውሉም፣ በጎይትኦም ልመና ተፈተዋል
 • ድርጊቱን ያጋለጡት ግን፥“ቀጣዩ የሥራ ዋስትናችን አስግቶናል” እያሉ ነው
 • የጽ/ቤቱ ሓላፊዎችም ለሕግ እንዲቀርቡ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ጠይቀዋል
 • የማጸደቂያ ጉቦው፣ በየአድባራቱ የተለመደ እና የሚደረግ እንደኾነ ታውቋል
 • የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ይገኙበታል

*                                       *

goitomdebra-tiguhan-officals-collusion

በወንጌል፣ “ይደልዎ ዓስቡ ለዘይትቀነይ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” (ማቴ.10፥10) እንደተባለው፣ በአንድ ሰበካ አስተዳደር ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች፣ እንደየሥራቸውና እንደየሞያቸው በሚሰጡት አገልግሎት መጠን ደመወዝና ተገቢ ጥቅማጥቅሞችን ማግኘት ሕጋዊ መብታቸው ነው፡፡ እንዲኹም፥ በሞያ፣ በአገልግሎት፣ በሥራ ጥራት፣ በታማኝነትና በሚያበረክቱት የሥራ ውጤት በቅተው ሲገኙም፣ የደረጃ ዕድገትና የደመወዝ ጭማሬ ማግኘት መብታቸው እንጂ ችሮታ እንዳልኾነ በቃለ ዐዋዲ ደንቡም በሕገ ቤተ ክርስቲያንም ተደንግጓል፡፡

በቃለ ዐዋዲው የተደራጀው ሰበካ ጉባኤ፣ ለምእመናን የሚሰጠውን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ከማሟላት ጋር፣ ለተጠቀሰው የካህናትና የልዩ ልዩ ሠራተኞች የኑሮ መሻሻልና የሥራ ዋስትና መረጋገጥ መሠረት የኾነ አስተዳደራዊ መዋቅር ነው፡፡ ከዐርባ ዓመት በፊት በኃምሳ ሳንቲም የምእመናን አስተዋፅኦ ተጀምሮ፣ ዛሬ በመቶ ሚሊዮኖች ገቢ ለመቁጠር ያስቻለን በመኾኑም፣ ለሐዋርያዊ ተልእኳችን መሳካት ትልቅና አስተማማኝ የሀብት ምንጭነቱ ታውቆ በሥነ ምግባር ሊመራ፤ ዘመኑ በሚፈቅደው የሒሳብ አሠራርና ቁጥጥር እየተያዘ ለሚገባው አገልግሎትና ልማት ሊውል ያስፈልጋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ የምታሳየውና በፋይናንስ አቅሟ ራሷን እንድትችል የሚያግዛት የገቢ ዕድገት፣ ሰበካ ጉባኤያቱ በየድርሻቸው በፈጸሙት ተግባር የተገኘ በመኾኑ፣ ጥረቱ ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ፣ ምእመናንን በማስተማር ተገቢውን የዐሥራት በኵራትና የአባልነት ክፍያ እንዲከፍሉ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወቱት በየደረጃው ያሉ የሥራ ሓላፊዎችና አገልጋይ ሠራተኞች፣ የኑሮ ውድነቱን እንደ አካባቢው የሚቋቋሙበት በቂ ደመወዝ እንዲያገኙ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ፥ የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤውን 35ኛ ዓመታዊ ስብሰባ የውሳኔ ሐሳብ ባጸደቀበት፣ የጥቅምት ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱም በኩል ለአህጉረ ስብከቱ የሥራ መመሪያ ሰጥቷል፡፡

የብዙ ባለሀብትና ንብረት ባለቤቶች የኾኑ 181 ያኽል ገዳማትንና አድባራትን ከኻያ ሺሕ በላይ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ጋር የያዘው የዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ መመሪያውን ጠብቆ መሥራት ቢኖርበትም፣ ወቅታዊ ያልኾነና ሕገ ወጥ የደመወዝና የአበል ጭማሬዎችን እንደሚያካሒድ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ64 በላይ(በአንዳንድ መረጃዎች ከመቶ በላይ) አጥቢያዎች ኹለት ዙር የደመወዝ አልያም የአበል ጭማሬዎች ማድረጋቸውን የሚጠቁሙ ምንጮች፤ ጭማሬውን ለማስፈቀድ የአንድና የኹለት ወራት ጭማሬዎችን ለሥራ አስኪያጁ ጎይትኦም ያይኑና ለሒሳብና በጀት ዋና ክፍሉ ሓላፊ ገብረ ሕይወት አስገዶም በእጅ መንሻነት መልቀቅ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

ከአራዳ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስና ከደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል አብያተ ክርስቲያናት፣ የሕንፃ አበል ጭማሬ ለማጸደቅ በሚል ብቻ፣ በእያንዳንዱ ሠራተኛ ስም ብር 1ሺሕ በድምሩ ከብር 150 ሺሕ እስከ 350ሺሕ ለኹለቱ ሓላፊዎች በጉቦ መሰጠቱ ተገልጧል፤ ከማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም፣ የደመወዝ ጭማሬ ለማጸደቅ ብር 200ሺሕ ለመስጠት ወጪ ተደርጎ የነበረ ቢኾንም፣ በሰበካ ጉባኤው ጥያቄና “ማወራረጃ በመጥፋቱ” ተመላሽ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

መደበኛ የደመወዝ ጭማሬ በየኹለት ዓመቱ እንደሚደረግ የጠቀሱት ምንጮቹ፤ አድባራቱ በቀጣይነት ለመክፈል ያላቸው ገቢና የልማት ይዞታቸው አስተማማኝነት እንዲኹም፣ ከጠቅላላ ገቢያቸው ለሀገረ ስብከቱ መክፈል ካለባቸው የኻያ በመቶ ፈሰስ ዕዳ ነፃ ስለመኾናቸው በአግባቡ ሳይረጋገጥና በአስተዳደር ጉባኤው ሳይታይ በኹለቱ ሓላፊዎች ምክር ብቻ እንደሚጸድቅ አስረድተዋል – በቀድሞው ሥራ አስኪያጅ ኹለት ተከታታይ ጭማሬዎች መደረጋቸውንም በማስታወስ፡፡ ይኸው ያልተጠናና ከአቅም በላይ የኾነ ጭማሬን የመፍቀድና የማጽደቅ አሠራርአድባራቱ የፈሰስ ድርሻቸውን ከመክፈል ይልቅ ደመወዝ በመክፈል ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል፤ ይላሉ፡፡


“የደመወዝና የአበል ጭማሬ በሚያስገርም ፍጥነት በብዙ አድባራት ተጧጡፏል፤ በ6 ወራት ልዩነት አብዛኞቹ አጥቢያዎች ደመወዝ ጨምረዋል፤ ቅድመ ኹኔታዎቹ ሳይታዩና የአስተዳደር ጉባኤው ሳይወያይበት በጎይትኦምና በገብረ ሕይወት ምክር ብቻ ቃለ ጉባኤ ተዘጋጅቶ በየቢሮው ለፊርማ ይዞራል፤ በቀረበው ጥያቄ መሠረት ጸድቆላቸው ይላክ፤ ተብሎ ይታዘዛል፤ ምእመናን እጃቸውን ለአንድ ወር ቢሰበስቡና ባይከፈልኮ ተቀማጫቸው ለስድስት ወራት እንኳን አያግደረድርም፡፡ ወጪው፦ በየጊዜው በደላሎች ጥቆማና በሌለ በጀት በዝውውር ሽፋን በከፍተኛ ደመወዝና ጥቅማጥቅም ከሚቀጠሩት የማይታወቁ ግለሰቦች ጋራ ተደማምሮ የአድባራቱን ካዝና እየተፈታተነው ነው፡፡ ዘመድ አዝማድ የሌላቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን ዋስ ጠበቃ አድርገው ከልጅነት እስከ ዕውቀት ሲያገለገሉ የኖሩ ካህናትን፣ መዘምራንና መምህራንን ሞራልም የሚጎዳ ነው፡፡


በሌላ በኩል ኹኔታው፣ የአድባራቱና የሀገረ ስብከቱ የሒሳብ አያያዝና ቁጥጥር፣ የሥራ አስኪያጁን ሪፖርት ያኽል የተሻሻለ አለመኾኑን ይጠቁማል፡፡ በሪፖርቱማ፦ ሀገረ ስብከቱ “ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን የጥንድ ሒሳብ(ደብል ኢንትሪ) አክርዋል አመዘጋገብ መርሖን በመከተል ከማንዋል ወደ ኮምፒዩተራይዝድ ፒችትሪ አካውንቲንግ ምዝገባ በማካሔድ፤ ወጭን፣ ጉልበትንና ጊዜን ቆጣቢ በኾነ መልኩ በመሥራት ላይ ይገኛል፤” ነበር የተባለው፡፡

ከዚኽም አልፎ የአድባራቱን የሒሳብና የቁጥጥር ባለሞያዎች፣ “የፋይናንስ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ እንዲኹም የውስጥ ቁጥጥርና የኦዲት መመሪያ በማዘጋጀትና ልዩ ልዩ ሞዴላሞዴሎችን በማሳተም ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፤” ነበር የተባለው፡፡

እውነታው ግን፣ የሀገረ ስብከቱ ሒሳብ እስከ አኹን እየተሠራ ያለው፣ በውጭ ባለሞያ(የአማካሪ ሠራተኞች) በመኾኑ ዕውቀቱና ክህሎቱ በእነ ገብረ ሕይወትና ስታፎቻቸው ገና እንዳልተጨበጠ ያሳያል፤ መጨበጡ ይቅርና፣ ቀድሞ የአንድ ብፁዕ አባት ሹፌር የነበሩት የዛሬው የዋና ክፍሉ ሓላፊ(በተሣልቆ፦“ድንግል በክልኤ”)፣ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንኳ በአግባቡ እንዳላጠናቀቁ ነው የሚነገረው፡፡ ለውጭ የሒሳብ ባለሞያዎቹም ከፍተኛ ገንዘብ እየተከፈለ ሲኾን፣ የክፍያው አግባብነት፥ የአስተዳደር ጉባኤው ይኹንታ ያልሰጠበትና ነጋ ጠባ የሀገረ ስብከቱ መሻሻል በሚነገራቸው በፓትርያርኩም ዘንድ እንደማይታወቅ ተገልጿል፡፡

ሠለጠኑ ከሚባሉት የአድባራቱ የሒሳብ ሹሞችም፣ ወደ ሌላ የሥራ መደብ ዝውውር የሚጠይቁት በርክተዋል፡፡ አዲስ አድማስ በዛሬው እትሙ እንደዘገበውም፣ “የደመወዝ ጭማሬውን በሀገረ ስብከቱ ያጸድቅነው፣ የተለመደውን የ50ሺሕ ብር ጉቦ ሰጥተን ነው፤” ከሚሉት ውስጥ የደብሩ ሒሳብ ሹም(ገንዘብ በሕጋዊ የሒሳብ አያያዝ መውጣቱንና መግባቱን እያረጋገጡ የመሥራት ሓላፊነት ያለባቸው) እና ተቆጣጣሪው(ወጪና ገቢውን የመመርመርና የካህናቱንም መብት የማስከበር ሓላፊነት ያለባቸው) የሚገኙበት መኾኑ ሥር ለሰደደው የሀገረ ስብከቱ ሥርዓታዊ ቀውስ አስረጅ ነው፡፡

ሐቁ ይህ ኾኖ ሳለ፣ የሀገረ ስብከቱ “ተለውጫለኹ፤ ተሻሽዬአለኹ” አደንቋሪ ሪፖርት ምን ያኽል ፌዘኛና ሐሰተኛ እንደኾነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በየመድረኩ በሚያሰሙት የመልካም አስተዳደርና የፀረ ሙስና አቋም ላይ ከመሣለቅም ተለይቶ አይታይም፡፡

የሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት በየዓመቱ እያስመዘገቡ ካሉትና ከሚችሉት ዓመታዊ የገቢ መጠን(በ2008 የበጀት ዓመት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ነበር) አኳያ፤ አኹን ሊያሳስበን የሚገባው የካህናት የኑሮ መሻሻልና የሥራ ዋስትና መጠበቅ ብቻ ሳይኾን፣ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተልእኮዋን የምታሳካባቸው ታላላቅ የትምህርት፣ የማኅበራዊ ተራድኦና የጤና ማዕከላት ማበብ ነበር፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሥርዓታዊ ቀውስ ሥርዓታዊ መፍትሔ ይሻል፡፡ ይህም በተጠናውና የብዙኃኑን ተቀባይነት ባረጋገጠው መዋቅርና አደረጃጀት ሰነድ ተግባራዊነት እንጂ፣ የጠገቡትን ያለአንዳች ተጠያቂነት እያሰናበቱ የተራቡትንና ኹሉ ብርቁ አማሳኞችንና የመናፍቃን ተላላኪዎችን በመተካት ከቶም ሊመጣ አይችልም፡፡


(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ 16 ቁጥር 890፣ ቅዳሜ፣ ጥር 27 ቀን 2009 ዓ.ም.)

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የደብረ ተኣምራት ጻድቃኔ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ሠራተኞች፤ ለተፈቀደላቸው የደመወዝ ጭማሬ ማጸደቂያ በሚል፣ ለሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ለሒሳብና በጀት ዋና ክፍሉ ሓላፊ በስጦታ እንዲከፈል የተጠየቁትን የ50 ሺሕ ብር ጉቦ(የኹለት ወራት ጭማሬያቸውን) ማጋለጣቸውን ተከትሎ፤ ገንዘቡ እንዲመለስላቸው ታዘዘ፡፡


debra-tiguhan-st-mary-scandals-exposed

የደብሩ አስተዳዳሪ፣ ዋና ጸሐፊ፣ ሒሳብ ሹም፣ ቁጥጥርና የገንዘብ ቤት ሓላፊ፤ ደመወዙን ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አጸድቀን ያመጣነው የስጦታና የማጸደቂያ ገንዘብ ከፍለን በመኾኑ የታኅሣሥና የኅዳር ወር ጭማሬያችኹን 50 ሺሕ ብር ለእኛ ትለቁልናላችሁ፤” እንዳሏቸው አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል፡፡

“ለምን እንለቅላችኋለን?” ብለው መጠየቃቸውን የጠቀሱት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ እንዲህ ዓይነቱ ነገር በሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት የተለመደና የሚደረግ መኾኑን ታውቃላችኹ፤ ይህ ብር ካልተከፈለ ደመወዙ ሊጸድቅ አይችልም፤” በማለት ሓላፊዎቹ እንደመለሱላቸው አስረድተዋል፡፡

አቤቱታ አቅራቢዎቹም፣ በወቅቱ የሓላፊዎቹን ምላሽ በአንድ ድምፅ ቢቃወሙም፣ የኅዳር ወር ጭማሬያቸው ብር 25ሺሕ፣ ለሥራ አስኪያጁ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ እና ለሒሳብና በጀት ዋና ክፍሉ ሓላፊ አቶ ገብረ ሕይወት አስገዶም፣ ለተባለው ‘ስጦታ’ ተቀንሶ በባንክ መከፈሉን አስታውቀዋል፡፡ በተመሳሳይም፣ የታኅሣሥ ወሩ ብር 25ሺሕ ሊቆረጥባቸው በመታሰቡ፣ በቀጥታ ደብሩ ለሚገኝበት የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ማመልከታቸውን በአቤቱታቸው አስፍረዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነትም፣ አቤቱታውን ተቀብሎና አጣሪ ልኡክ መድቦ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጋር በመቀናጀት ባካሔደው ማጣራት፣ በስጦታ ስም ካህናትና ሠራተኞች የኹለት ወራት የደመወዝ ጭማሬያቸውን እንዲለቁና በስማቸው እንዲከፈል እየተደረገ መኾኑን፤ ወደ ‘ስጦታ’ የተገባውም፣ በአንድ ዓመት ኹለት ዙር ደመወዝ ለማስጨመር በማሰብ አግባብነት የሌለው አሠራር መኾኑን አረጋግጧል፡፡

ይህን ተከትሎ የክፍለ ከተማው ጽ/ቤት ለደብሩ አስተዳደር በጻፈው ደብዳቤ፣ ከደመወዝ ጭማሬው ላይ ለ‘ስጦታ’ በሚል የተቀነሰው ገንዘብ፣ ለኹሉም ካህናትና ሠራተኞች ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተመላሽ እንዲኾንና አፈጻጸሙ በሪፖርት እንዲገለጽለት አዟል፡፡ ሰበካ ጉባኤው ሳያምንባቸው በአስተዳደሩ የተፈጸሙ ሕግና ሥርዓትን ያልተከተሉና ግልጽነት የጎደላቸውን አሠራሮች በመዘርዘርም፣ ደብሩ በሕግ አግባብ እንዲመራ አሳስቧል፡፡

ይህም ኾኖ፣ የደብሩ አስተዳደር አላግባብ የቆረጠባቸውን ገንዘብ እንዳልመሰላቸው እንዲኹም፣ ድርጊቱን ከጅምሩ በመቃወም ለ‘ስጦታው’ ላልከፈሉና አቤቱታ ላቀረቡ ሠራተኞችም፣ የጸደቀውን ደመወዝ በደብዳቤ እንዳላሳወቃቸውና ሊለቅላቸውም ፈቃደኛ አለመኾኑን፣ ካህናቱና መምህራኑ ባለፈው ማክሰኞ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ባደረሱት አቤቱታ አመልክተዋል፡፡

ይባስ ብሎም፣ “ድርጊቱን በማጋለጣችን፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ይይኑ ደብሩ ድረስ በመምጣት ከሙስና አቀባዮቻቸው ከጽ/ቤቱ ሓላፊዎች ጋር በመኾን እኛን ለማዛወርና ከሥራ ለማገድ መክረውብናል፤” ያሉት ካህናቱና ሠራተኞቹ፣ “ቀጣይ የሥራ ዋስትናችንም ለስጋት ተጋልጧል፤” ሲሉ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ተማፅነዋል፡፡

የደብሩን ጽ/ቤት ሕገ ወጥ አሠራሮች ባለመቀበል፣ አራት የሰበካ ጉባኤ አባላት ከሓላፊነታቸው ለመልቀቅ መገደዳቸውን አቤቱታ አቅራቢዎቹ ጠቁመው፤ በደብሩ የጽ/ቤት ሓላፊዎች የተፈጸመው የሙስና ወንጀል የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚነካ በመኾኑ፣ በሚመለከተው የፍትሕ አካል ተጣርቶ ጥፋተኞች ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል፡፡


ፍትሕ ፈላጊዎቹ የደብረ ተኣምራት ጻድቃኔ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ሠራተኞች፤ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ሙሉ ቃል፤

dabra-tiguhan-tsadkane-st-mary dabra-tiguhan-tsadkane-st-mary2 dabra-tiguhan-tsadkane-st-mary3

Advertisements

2 thoughts on “ለደብሩ የደመወዝ ጭማሪ ማጸደቂያ: ለሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ጎይትኦም ያይኑና ለሒሳብና በጀት ሓላፊው 50ሺሕ ብር ጉቦ ተከፈለ፤ እንዲመለስ ታዟል!

 1. Binyam Solomon February 6, 2017 at 6:57 am Reply

  መልካም ሪፖርት ነው፡፡ ግን አዲሰ ነገር አይደለም፡፡ እናንተም እንዳላችሁት በሀገረ ስብከቱ የተለመደ ዘረፋ ነው፡፡ እኔ በግሌ ካህናቱን አደንቃለሁ፡፡ በዚህ የጥብአት ተግባራቸው የሚመጣባቸውን በአገባቡ ያውቁታል፡፡ ነገ ሁሉም እንዲበተኑ ያውም ገቢያቸው ጥቂት ወደኾነ የአዲስ አበባ ጠረፍ አብያተ ክርስቲያናት፡፡ በዚህ ካህናዊ ተግበር እነሱም ቤተሰቦቻቸውም የሚሰቃዩ በርካታ ካህናት አሉ፡፡ እስቲ ጥናት አድርጉ፡፡ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚበጃት እሱ ነው፡፡ ሌባን ያውም የታወቀውን እየተከተሉ ‹ሌባ ሌባ› እያሉ ሲጮኹ ቢኖሩ ትርፉ ሌላ ሌባ ማፍራት ነው፡፡ አደራ የእነዚህን ካህናተ ነገር፡፡

 2. Dawit February 10, 2017 at 6:09 am Reply

  መንፈስ ቅዱስ የተለያት ቤተክርስቲያን ሙስነኛና ሌባ አገልጋይ ታፈራለች።
  እነርሱ ድህነታቸውን እንዲረሱ ድሀ እንዲያስለቅሱ ፈቃድ የተሰጣቸው ሌቦች ናቸው።
  አዲስ አበባ ሀ.ስብከት ገብቶ ያልዘረፈ ማን ነው? መሙ፣ ኑረዲኖች ዋቀዮ ጋዜጠኛው ተሀድሶ?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: