ፓትርያርኩ: በደላሎች የሚዘወረው የጎይትኦም ያይኑ የአ/አበባ ሀ/ስብከት አመራር፣ በአድባራት ሠራተኞች ላይ ያካሔደው ዝውውር እንዲጣራ አዘዙ

  • ደረጃና ደመወዝ የተቀነሰባቸው፤ ከሥራና ከደመወዝ የታገዱና የተሰናበቱ ይገኙበታል
  • ማኅደርና በጀት ሳይኖራቸው እንዳላቸው እየተደረገ በከፍተኛ ደመወዝ የተዛወሩም አሉ
  • የደብር አለቃው፣ አባ ኃይለ መለኰት ይኄይስ ከጎይትኦም ደላሎች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ
  • “የሥራ አስኪያጁ የቡድንና የደላላ – መር አካሔድ፣ የፓትርያርኩን ትእዛዝ የጣሰ ነው”

*                    *                    *

goitom-vs-abune-mathias
ከሚገባቸው በላይ የሰው ኃይል ክምችት በመያዝ እየተጨናነቁ በሚገኙት የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት፣
የሚካሔደው፣ የሓላፊዎችና የሠራተኞች ዝውውር እንዲኹም ከሥራ የማገድና የማሰናበት ርምጃ በአስቸኳይ እንዲጣራ፣ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አዘዙ፡፡

ፓትርያርኩ ትእዛዙን የሰጡት፣ በመ/ር ጎይትኦም ያይኑ ዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚመራው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ ከሕግና ሥነ ሥርዓት ውጭ የአስተዳደር በደል አድርሶብናል፤ የሚሉ የኻያ አመልካቾችን አቤቱታ፣ በአካልና በጽሑፍ ከተቀበሉ በኋላ በልዩ ጽ/ቤታቸው በኩል በጻፉት ደብዳቤ ነው፡፡

a-a-dio-row
ከአስተዳዳሪነት ጀምሮ ባሉት የጽ/ቤት ሓላፊነቶች የሚሠሩት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፦ ደመወዝ፣ አበልና የሥራ ደረጃን በሚቀንስ እንዲኹም፣ የተዛወሩበትን የሥራ መደብ፣ ደመወዝና አበል በማይጠቅስ ውሳኔ ተገቢ ያልኾነ ዝውውር ተፈጽሞብናል፤ ባልተጣራና ባልተወሰነ የሥራ ግድፈት ከሥራና ደመወዝ እንድንታገድና እንድንሰናበት በማድረግ በደል ደርሶብናል፤ በሚል ማመልከታቸውንና ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ልዩ ጽ/ቤቱ በደብዳቤው ገልጿል፡፡

ሠራተኞቹ፣ ከአንዱ አጥቢያ ወደ ሌላው እንዲዛወሩ፤ ከሥራና ደመወዝ እንዲሰናበቱ የተደረገበት ማስረጃ ተገቢነት፣ ካቀረቡት አቤቱታና ከቤተ ክርስቲያን ሕግጋት አንፃር እየተገናዘበ በሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ እንዲመረመር ፓትርያርኩ አዘዋል፤ አፈጻጸሙም፣ ሕጋዊውን አሠራር ያልተከተለ ኾኖ ሲገኝ፣ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር በምልዓተ ጉባኤ አስተካክሎና አርሞ አፋጣኝ ውሳኔ በመስጠት፣ ውጤቱ በአስቸኳይ እንዲገለጽላቸው በመመሪያቸው ማሳሰባቸውንም ልዩ ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡

አቤቱታው፣ ባለፈው ኅዳር ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ቀርቦ የታየና ሀገረ ስብከቱ በሕጉ መሠረት አስቸኳይ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጥ አስቀድሞ የታዘዘበት ከመኾኑም በላይ፤ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ለሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርም ደርሶ በሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲያገኝ ሲጠየቅበት መቆየቱ ተወስቷል፡፡

teshome-deneke-etal
አቤት ባዮቹ፣ በተለይ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በጻፉት ደብዳቤ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፥ ከሕገ ወጥ ዝውውር በተጨማሪ፣ የሙስና ተግባራትን እንደሚፈጽሙና ያለምንም ጥፋት ከባድ ማስጠንቀቂያ የጻፉባቸውም፣ ይህን በመቃወም የመብት ጥያቄ በማንሣታቸው እንደኾነ በቅሬታቸው ጠቅሰዋል፡፡

a-a-dio-row2በሌላ በኩል፣ አቤቱታውን የሚያጣራ ስምንት አባላት ያሉት ቡድን ባለፈው ማክሰኞ በዋና ሥራ አስኪያጁ ተቋቁሞ ጉዳዩን የሚመለከት ሰነድ በማስቀረብ ሲያጠና መቆየቱን የጠቀሱ የሀገረ ስብከቱ ምንጮች፤ የማጣራቱ ውጤትም፣ ባለፈው ኃሙስ በተካሔደውና ዋና ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ 10 የዋና ክፍል ሓላፊዎች በተገኙበት የአስተዳደር ጉባኤ ታይቶ ውሳኔ ማግኘቱን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

ምንጮቹ እንደተናገሩት፣ ከኻያዎቹ አቤቱታ አቅራቢዎች መካከል፣ ሦስት የአድባራት ጸሐፊዎች፣ በዝውውሩ የተቀነሰባቸው ደመወዝ ካለ፣ ባሉበት እንዲስተካከል፤ ታቦት ታቅፈው ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ድረስ ይዘው በመምጣት ከፍተኛ ድፍረትና የቀኖና ጥሰት ፈጽመዋል በሚል ከሥራና ደመወዝ በተሰናበቱ አንድ አለቃና ሦስት ሠራተኞች ላይ የተወሰደው የማሰናበት ውሳኔ ባለበት እንዲጸና፤ የተቀሩት 13 ሠራተኞችም፣ ይቅርታ እየጠየቁ በተገኘው ቦታ እንዲመደቡ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

በበርካታ የሰነድ ማስረጃዎች የተደገፈውን አቤቱታ ማጣራት የሚገባው፣ 15 አባላት ያሉት የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ እንጂ፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ በራሳቸው መርጠው ያቋቋሙት ቡድን አለመኾኑን የሚጠቅሱ ወገኖች በበኩላቸው፤ አካሔዱ፣ የፓትርያርኩን መመሪያ እንደሚፃረር፤ በጥቅማጥቅምና በአቅም ማነስ የተሠሩ የጽ/ቤቱን ስሕተቶች ለመሸፋፈን የተደረገ ሙከራ በመኾኑ እንደሚቃወሙት ገልጸዋል፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያን በሰፈረው የልዩ ሀገረ ስብከት ድንጋጌ መሠረት፣ በፓትርያርኩ የበላይ ሓላፊነት የሚመራው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፤እገሌ ሥራና በጀት እየተባሉ፥ መዋቅርን፣ ዕውቀትን፣ ልምድንና በጀትን ማዕከል ባላደረጉ የዝውውር፣ ቅጥርና ሽግሽግ አሠራሮች ሳቢያ በሚነሡ ውዝግቦች እየታወከ ይገኛል፡፡ ሀገረ ስብከቱ፣ ራሱን ችሎ ሊቀ ጳጳስ እንዲመደብለትና ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ጠንካራ መዋቅርና አደረጃጀት እንዲዘረጋለት የተላለፉ ውሳኔዎች አፈጻጸምም መጓተቱ ተገልጿል፡፡

*********************

goitom-yayenu
የጎይትኦም ያይኑ የዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር፤
ደላሎች[የአለቃ፣ የጸሐፊ፣ የሒሳብ ሹምና የቁጥጥር] በከፍተኛ ኹኔታ ሥራ ያገኙበት ነው፤ ቁጥራቸውም በርክቷል፤ በየተወላጆች መሥመር በተዘረጋው የምዝበራ ሰንሰለት፡- ገንዘብ ይዞ ከመጣ እምነቱ እንኳ በቅጡ ሳይታወቅ ማንኛውም ሰው ሊቀጠር ይችላል፤ የሚባልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ የደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት አለቃ÷ አባ ኃይለ መለኰት ይኄይስ፣ የጽርሐ አርኣያም ሩፋኤል ጸሐፊ÷ አፈ ወርቅ ወልደ ገብርኤልን ያኽል ግን ደላላና ተጠቃሚ የለም፡፡

አባ ኃይለ መለኰት፣ ወደ ደብሩ ተዛውረው ለመምጣት በከፈሉት ብር 250ሺሕ፤ ከገነተ ኢየሱስ ጉዳይ አስፈጻሚነት ወደ ፊልጶስ ተቆጣጣሪነት እየተመነደገ አኹን ጸሐፊ የኾነው አፈ ወርቅም፣ በሓላፊነት ቦታ እንዳይመደብ በፍ/ቤት ጭምር ቢወሰነበትም የጎይትኦም ሚዜ በመኾኑና በዝምድናው ነው፡፡ ቢዝነስ የት ደብር ነው የሚሠራው፤ በሚል እያጠኑ ይደልላሉ፤ ከየደብሩም አማሳኝነታቸውንና ለዝርፊያ የተዘጋጁበትን አሠራር የሚቃወሙ ንቁ  ሠራተኞችንና ካህናትን ለማራቅና ለማሸማቀቅ ተጠቅመውበታል፡፡

በሠራተኛነት የሚታወቁበት ማኅደርና በጀት ለሌላቸው ግለሰቦች ሳይቀር፣ እንዳሉና እንደነበሩ በማስመሰል በርካታ ሕገ ወጥ ዝውውሮችን አስፈጽመዋል፡፡ አባ ኃይለ መለኰት ይኄይስ፣ ሰነድ እየፈበረኩ መሰል ሕገ ወጥ ዝውውሮችን በዋናነት ከሚያመቻቹት የጎይትኦም ያይኑ ደላሎች ተጠቃሹ ናቸው፡፡

dn-kibrom-gm-casekes-sisay-chekol-case
በአገልጋይነት ይኹን በቢሮ ሠራተኛነት የማይታወቁ ግለሰቦች፣ እንደ ነባር ሠራተኛ ፋይል እየተከፈተላቸው፣ በዝውውር ሽፋን በከፍተኛ ደመወዝና ጥቅማጥቅም ይመደባሉ፡፡
በምትኩም፣ ጥፋታቸውን ሳያውቁት፣ ደመወዛቸውና ጥቅማጥቅሞቻቸው ተቀንሶ በመዛወራቸው፣ ትራንስፖርትን ጨምሮ ለእንግልት የተዳረጉ ነባር ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው አቤት ቢሉም የሚሰማቸው አጥተዋል፡፡

kesis-fikre-yohannes-hm
በዝውውር ሽፋን የሚቀጠሩት የማይታወቁ ግለሰቦች፣ ከሥራ አስኪያጁ ጋር የጥቅም፣ የዝምድና አልያም የኑፋቄ ትስስር ያላቸው ሊኾኑ እንደሚችሉ ተመልክቷል፡፡ በቀጣይም፣ የገዳማቱንና የአድባራቱን ካዝና በመፈታተን የፋይናንስ ሥርዓታቸውን ስለሚያናጋው ተቃውሞ ቢቀርብበትም፣ ተቀበል በሚል ትእዛዝና አግድሃለሁ በሚል ማስፈራሪያ በማስገደድ እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡

በአጭሩ፣ ከሒሳብና በጀት ዋና ክፍሉ ጋር በመመሳጠር፥ ሳይጠኑና ወቅት ሳይጠብቁ በሚደረጉ የደመወዝና የአበል ጭማሬዎች እንዲኹም፣ ከሕገ ወጥ ዝውውር፣ ዕድገትና ሽግሽግ ባሻገር፣ ሕገ ወጥ ቅጥርም፣ በደላሎች የሚዘወረው የዐቅመ ቢሱና የኑፋቄ ተላላኪው ጎይትኦም ያይኑ ዋነኛ የጥቅም ማካበቻ መንገድ መኾኑ የዐደባባይ እውነት ኾኗል፡፡

የሰው ኃይል እንቅስቃሴውን በሓላፊነት መከታተል ያለበት የሰው ኃይል አስተዳደሩ እንዲኹም፣ አሠራሩንና አስፈላጊነቱን የመመዘንና የመገምገም ሥልጣን ያለው ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚ አካል የኾነው የአስተዳደር ጉባኤው፣ በጎይትኦም ያይኑ ደላሎች የጥቅም አቀባባይነትና ቤተሰባዊ ምክክር መተካቱ ሌላ ምስክር አያሻውም፡፡ አቤቱታን ለበላይ አካል በይግባኝ አቅርቦ አፋጣኝ ምላሽ ለማግኘትም አዳጋች ኾኗል፡፡ ይህም ኾኖ፣ በሀገረ ስብከቱ ያለን ማናቸውም አሠራር በተመለከተ፣ ለደጉም ኾነ ለክፉ፣ ከኹሉም በፊት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተጠያቂነትና ሓላፊነት እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡

ስለዚኽም፣ ቢዘገይም ጨርሶ ከመቅረቱ ይሻላልና፣ የኋላ ኋላ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለሀገረ ስብከቱ ያስተላለፉት መመሪያ ተፈጻሚነት፣ አቤቱታ ባቀረቡት ኻያ ሠራተኞች ጉዳይ ብቻ ሳይወሰን፣ ከሕግና ከአስተዳደር ጉባኤው ዕውቅና ውጭ የተካሔዱትንና ለአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት አደገኛ ውጤት የሚኖራቸውን ዓይን ያወጡ የምደባዎች አማሳኝነትም ሊያካትት ይገባል፤

“… ከቃለ ዐዋዲው ድንጋጌና ከአስተዳደር ጉባኤው ዕውቅና ውጭ በሥራ አስኪያጁ የተደረጉ ምደባዎችና ዝውውሮች፣ በመዝገብ ቤት ሰነዶች ተለይተውና ተጣርተው ተገቢው ርምጃ ሊወሰድ ይገባል፤ ለፓትርያርኩ የፀረ ሙስና አጀንዳና ለመልካም አስተዳደር ዐዋጅ የማይመጥነው ጎይትኦም ያይኑ፣ ሀገረ ስብከቱ በታሪኩ ካያቸው ሥራ አስኪያጆች አቅመ ቢሱና የእምነት አቋሙም አጠያያቂ በመኾኑ በአስቸኳይ ተነሥቶ በሕግ እንዲጠየቅ፤ ንቡረ እድ ኤልያስ ሊመጣ ነው፤ የማነ ይመለሳል፤ ከሚል የቲፎዞ ጨዋታ በመውጣት፡- ጠንካራ የእምነት አቋምና መንፈሳዊነት፤ በቂ የትምህርት ዝግጅትና የአገልግሎት ልምድ ያለው ሥራ አስኪያጅ ይመደብ፡፡ በተጠናው መዋቅርና አደረጃጀትም፡-  ዋነኛ ተልእኮውን፣ ሓላፊነቱንና ተግባራቱን የሚያውቅ፣ የሥራ መዘርዝርና ዕቅድ ያለው ሀገረ ስብከት ይኑረን፡፡ (ከአቤቱታ አቅራቢዎች)

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: