የቴሌቪዥናችን ኢኦተቤ – ቴቪ/EOTC TV/ መለዮ የኾነው የቤተ ክርስቲያናችን ዓርማ ምን ያመለክታል?

 • አስተምህሯችንና ትውፊታችን በቅዱስ መጽሐፍ ላይ መመሥረቱን ያመለክታል
 • የቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊ ክብር መገለጫና መለያ በመኾኑ ሌላ መጠቀም ክልክል ነው
 • ዓርማው የሌለበት የቤተ ክርስቲያን ማኅተምና የማዘዣ ደብዳቤ ተቀባይነት የለውም

/ሕገ ቤተ ክርስቲያን/

*                                       *eotc-emblem-ed

ለዘመናት ሕዝቡን ስለ ሰው ልጅ ድኅነት፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አገር ፍቅርና ስለ አብሮነት ጊዜው በፈቀደው መንገድ ኹሉ በማስተማር የኢትዮጵያ ባለውለታ የኾነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፤ ዛሬም፣ እነኾ ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ ልጆችዋንና ምልአተ ሕዝቡን ለመድረስ እንዲያስችላት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አጥንታ የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት አቋቁማለች፡፡ የድርጅቱ መተዳደርያ ደንብ፣ የአርትዖትና የቴክኒክ መመሪያዎችም ጸድቀው ሥራውን በሳተላይት ቴሌቭዥን ስርጭት አሐዱ ብላለች፡፡

ጣቢያው፣ ከስድስት ወራት የሙከራ ቆይታ በኋላ፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 29 ቀን፣ መደበኛ ሥርጭቱን ጀምሯል፡፡ በአገልግሎቱ 27 የፕሮግራም ዓይነቶች ያሉት ሲኾን፣ ቅድሚያ ሽፋን ይሰጥባቸዋል ከተባሉት 11 ያኽል ፕሮግራሞቹ የተወሰኑ ዝግጅቶችን ለአየር አብቅቷል፤ ሌሎቹንም ከወዲኹ እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡

የጣቢያው የሥርጭት መርሐ ግብር እንደሚያሳየው፣ አዳዲስ ዝግጅቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሜና እሑድ በተወሰነላቸው ሰዓት ይተላለፋሉ – በጥዋቱ ክፍለ ጊዜ በመደበኛነት የሚቀርበውን ጸሎተ ቅዳሴ ጨምሮ፡፡ በሳምንቱ የሥራ ዕለታት ደግሞ ቅዳሜ የተላለፉት ሰኞ፣ እሑድ የተላለፉት ማክሰኞ በድጋሚ ይቀርባሉ፤ ከእኒኽም መካከል የተመረጡ ዝግጅቶች ረቡዕ እና ኃሙስ በወጣላቸው መርሐ ግብር መሠረት የሚዞሩ ይኾናሉ፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት፣ ዓርብ ዕለተ ዕረፍት መኾኑንና በርካታ የጣቢያው ተከታታዮች እንዳሉ ታሳቢ በማድረግ፣ ያለፉት የቅዳሜና የእሑድ ዝግጅቶች በሙሉ በተከታታይ እንደሚቀርቡበት ታውቋል፡፡

ይኸው መርሐ ግብር ለመጪዎቹ ኹለት ወራት በተገለጸው አኳኋን ሊቀጥል እንደሚችልና እስከዚያው ድረስ ከሥርጭት ቴክኖሎጂው ጋር የበለጠ የመናበብና በየዘርፉና በየፕሮግራሞቹ የሰው ኃይሉንና ዝግጅቶቹን በከፍተኛ ደረጃ የማጠናከር ሥራ ሲሠራ እንደሚቆይ ተመልክቷል፡፡

እስከ አኹን ለእይታ በቀረቡ ዝግጅቶች አስተያየት የሰጡ በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ተመልካቾች፣ ጣቢያውን በታላቅ ተስፋ እንደሚጠብቁት በተለያየ መንገድ እየገለጹ ሲኾን፤ ሞያተኛና ባለሀብት ኦርቶዶክሳውያንም በተለይም በቪዲዮ ካሜራ፣ በቀረፃና በአርትዖት እንዲኹም በተሽከርካሪ ረገድ የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

eotc-tv-logo
የቴሌቭዥን ጣቢያው በራስጌ በስተቀኝና በግርጌ በስተግራ የሚያሳየው መለዮው/ሎጎው/፣ የቤተ ክርስቲያናችን ዓርማ ነው፤
በዜማ በታጀበው የዝግጅት መግቢያና መሸጋገርያም ዓርማውን ይጠቀምበታል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛው መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ሕግ አውጭና ወሳኝ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በ2007 ዓ.ም. አሻሽሎ ያወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለምትጠቀምበት ስለዚኹ ዓርማ ደንግጓል፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ፬ የሰፈረው ድንጋጌው፥ የዓርማውን ቅርፅና ይዘት፤ የዓርማውን ትርጉምና የዓርማውን ክብር በተመለከተ በሦስት ንኡሳን አንቀጾች የተዘረዘሩ መግለጫዎችን፣ ማብራሪያዎችንና ትእዛዞችን አስቀምጧል፡፡

ከማብራሪያዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው፣ በነጭ መደብ ላይ የስንዴ ዛላና የወይን ዘለላ ክበብ ይዞ የሚታየው ዓርማው፣ በትርጉሙ፡- የምሕረት፣ የደስታና የነፃነት ዘመን የኾነውን ዘመነ ሥጋዌን መሠረት አድርጎ፥ ነገረ ድኅነትን፣ ነገረ መስቀልን፣ ነገረ ማርያምን፣ ተልእኮ መላእክትንና ክብረ ቅዱሳንን በአጠቃላይ ድኂነ ዓለምን የሚሰብክ ነው፡፡

በተለይም ደግሞ፣ የዓርማው መሐል ቅዱስ መጽሐፍ ኾኖ ነዋ ወንጌለ መንግሥት የሚል ጽሕፈት በበላዩ ያለበት መኾኑ፥ የቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖት. ቀኖና እና የተቀደሰ ትውፊት በቅዱስ መጽሐፍ ትምህርት ላይ የተመሠረተ መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡

ዓርማው፥ ክርስቶስን በተዋሕዶ አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ ብላ የምታምነው፤ ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት፣ በኹሉም ያለች፣ አንዲትና ቅድስት የኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሉዓላዊ ክብር መገለጫና መለያ ነው፡፡

ስለኾነም፣ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ አህጉር የሚገኙ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ያሉ ጽ/ቤቶች፣ ከዚኽ ዓርማ በቀር ሌላ ሊጠቀሙ እንደማይችሉና እንደማይገባቸው በሕጉ ታዟል፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት የሚገለገሉባቸው ማኅተሞችና የማዘዣ ደብዳቤዎች ዓርማው እንዲካተትባቸውና ከሌለባቸው ተቀባይነት እንደማይኖራቸው አስታውቋል፡፡/የአንቀጹን ሙሉ ይዘት ቀጥለው ይመልከቱ/


አንቀጽ ፬

የቤተ ክርስቲያን ዓርማ

eotc-emblem

፩. የዓርማው ቅርጽና ይዘት፡-

፩.፩. መደቡ ነጭ፤
፩.፪. ዙሪያው የስንዴ ዛላና የወይን ዘለላ፤
፩.፫. ከላይ ከአናቱ አክሊል፤ ከታች ከግርጌው መሐል ለመሐል ወጥቶ አናቱ ከአክሊሉ ሥር የደረሰና መስቀል ያለበት ዓርዌ ብርት፤
፩.፬. በግራ ኹኖ በቀኝ እጁ ዓርዌ ብርት፤ በግራ እጁ ዘንባባ የያዘ መልአክ፤ በቀኝ ኹኖ በግራ እጁ ዓርዌ ብርት፤ በቀኝ እጁ ዘንባባ የያዘ መልአክ፤
፩.፭. ከዓርዌ ብርቱ ሥር “ነዋ ወንጌለ መንግሥት” ተብሎ የተጻፈበት ቅዱስ መጽሐፍ
፩.፮. ከቅዱስ መጽሐፍ ሥር መስቀለኛ የ”ጸ” ፊደል ቅርፅን የሚመስል፤ ኹለቱ ጫፎቹ ከመደቡ ወደ ውጭ የወጣ ሰበን፤
፩.፯. የስንዴ ዛላና የወይን ዘለላ በተገናኙበት የዓለም ምስል፤ ያለበት ይኾናል፡፡

፪. የዓርማው ትርጉም፡-

ሀ/ መደቡ ነጭ መኾኑ፦ ዘመነ ሥጋዌ የምሕረት፣ የደስታና የነፃነት ዘመን መኾኑን ያመለክታል፤ (ዮሐ.፳፥፲፪፤ የሐዋ. ሥራ ፩፥፲)

ለ/ የዓርማው ዙሪያ በወይን ዛላና በስንዴ ዘለላ የተከበበ መኾኑ፦ ምእመናን በቅዱስ ቊርባን አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር አንድነትን፣ ስርየተ ኃጢአትን፣ የዘለዓለም ሕይወትን የሚያገኙ መኾናቸውን ይገልጻል፤ (ዮሐ. ፮፥ ፶፫-፶፰፤ ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱፤ መዝ. ፬፥፯)

ሐ/ በዓርማው መሐል ቀጥ ብሎ የቆመ የዓርዌ ብርት ምስል በበላዩ ላይ መስቀል፣ ከዚያም ከፍ ብሎ አክሊለ ክህነት አለው፤ የዚኽ ትርጉም፦ ሕዝበ እስራኤል ዓርዌ ብርቱን ባዩ ጊዜ ከእባብ መርዝ እንደ ዳኑ ኹሉ መስቀል ላይ በተሰቀለ በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ኹሉ በዲያቢሎስ ምክንያት ከመጣባቸው ፍዳ ኃጢአት የሚድኑ መኾናቸውን፤ መስቀሉ፦ የቤተ ክርስቲያን የድኅነት ዓርማ መኾኑን፤ (ዘኍ. ፳፩፥፰፤ ዮሐ. ፫፥፲፬)

መ/ አክሊል፦ ቅዱሳን በሰማያዊ መንግሥት የሚቀዳጁትን አክሊለ ክብር እና ማኅተመ ጽድቅን ያመለከታል፤ (ዘጸ. ፴፱፥፴፤ ፩ተሰ. ፪፥፲፱፤ ፪ጢሞ. ፬፥፰፤ ፩ጴጥ. ፭፥፲፬፤ ራእይ ፪፥፲፤ ፬፥፲፬)

ሠ/ ኹለት መላእክት የዘንባባ ዝንጣፊና ዓርዌ ብርቱን ይዘው ይታያሉ፤ ይህም ዘንባባ፦ በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ መንፈሳዊ ደስታንና ድኅነተ ነፍስን ያመለክታል፤ ቅዱሳን መላእክት የቤተ ክርስቲያን ጠባቂዎችና የመልካም ዜና አብሣሪዎች መኾናቸውን ያሳያል፤ ዓርዌ ብርቱን ይዘው መቆማቸው፥ ነገረ መስቀሉን አምኖና ሃይማኖቱን አጽንቶ ይዞ የሚኖር የዘለዓለም ድኅነትን የሚያገኝ መኾኑን ያመለክታል፤ (መዝ. ፺፥፲፩፤ ሉቃ. ፲፫፥፮-፱፤ ዕብ. ፩፥፲፬)

ረ/ የዓርማው መሐል ቅዱስ መጽሐፍ ኹኖ፥ “ነዋ ወንጌለ መንግሥት” የሚል ጽሑፍ በበላዩ አለበት፤ የዚኽ ትርጉም፦ የቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖት፣ ቀኖና እና ትውፊት በቅዱስ መጽሐፍ ትምህርት ላይ የተመሠረተ መኾኑን ያመለክታል፡፡ (ማቴ. ፳፬፥፲፬)

ሰ/ ከቅዱስ መጽሐፉ ግርጌ የሚታየው ሰበን፥ ቅድስት ድንግል ማርያም ስታርግ ለቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ የሰጠችውን ሰበን የሚገልጽ ሲኾን፤ ትርጉሙ፦ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤንና ዕርገትን እንደዚኹም የምእመናን እናት መኾኗን የሚያመለክት ነው፡፡ (ዮሐ. ፲፱፥፳፯)

ሸ/ የስንዴው ዛላና የወይኑ ዘለላ በተገናኙበት ላይ የሚታየው ክብ ነገር፥ ዓለምን የሚወክል ኾኖ ዓለም በክርስቶስ መዳኑን ያመለክታል፡፡ (ዮሐ. ፫፥፲፯)

፫. የዓርማው ክብር፡-

ሀ/ ዓርማው፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሉዓላዊ ክብር መገለጫና መለያ ስለኾነ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ ሀገር የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ጽ/ቤቶች ከዚኽ ዓርማ በቀር ሌላ ሊጠቀሙ አይችሉም፡፡

ለ/ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል ኾኖ ይህ ዓርማ የሌለበት ማኅተምና የማዘዣ ደብዳቤ የሚጠቀም ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ጽ/ቤት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

Advertisements

3 thoughts on “የቴሌቪዥናችን ኢኦተቤ – ቴቪ/EOTC TV/ መለዮ የኾነው የቤተ ክርስቲያናችን ዓርማ ምን ያመለክታል?

 1. Anonymous January 10, 2017 at 9:03 pm Reply

  What about the 2 snakes?

  • Anonymous January 16, 2017 at 9:16 am Reply

   በዓርማው መሐል ቀጥ ብሎ የቆመ የዓርዌ ብርት ምስል በበላዩ ላይ መስቀል፣ ከዚያም ከፍ ብሎ አክሊለ ክህነት አለው፤ የዚኽ ትርጉም፦ ሕዝበ እስራኤል ዓርዌ ብርቱን ባዩ ጊዜ ከእባብ መርዝ እንደ ዳኑ ኹሉ መስቀል ላይ በተሰቀለ በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ኹሉ በዲያቢሎስ ምክንያት ከመጣባቸው ፍዳ ኃጢአት የሚድኑ መኾናቸውን፤ መስቀሉ፦ የቤተ ክርስቲያን የድኅነት ዓርማ መኾኑን፤ (ዘኍ. ፳፩፥፰፤ ዮሐ. ፫፥፲፬)

 2. Anonymous January 13, 2017 at 7:54 am Reply

  tell us about the snakes?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: