ኢኦተቤ-ቴቪ: በዕቅበተ እምነት፣ በሰላምና በልማት ላይ ጠንክሮ እንዲሠራ ፓትርያርኩ አሳሰቡ፤“በስመ አብ የሚሉ አጋንንትንም የምናጠምቅበት ነው”/አቡነ ማርቆስ/

  • ባለን ሀብት መጠንና ከችግራችን አኳያ፣ ቀደም ብለን ልንጀመረው ይገባ ነበር
  • አኃት አብያተ ክርስቲያናት ብዙ ሥራ እየሠሩበት ነው፤ ቀድመውን ሔደዋል
  • ቋሚ የመሥሪያ ቢሮ እና በቂ ተሸከርካሪ አለመኖር ዋና ፈታኝ ችግሮቹ ናቸው
  • በሕዝቡ እንዳይናቅ የአደረጃጀት ችግሩ ሊፈታና ጠንክሮ ሊሠራ ያስፈልገዋል 
  • ባለቤቶቹ፥ አገልጋዮችና ምእመናን ናቸው፤ በሞያና በገንዘብ ሊደግፉት ይገባል

    *                    *                    *

ዛሬ፣ ኃሙስ፣ ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. ረፋድ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ የተከናወነው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሳተላይት ቴሌቭዥን(EOTC TV) የመደበኛ ሥርጭት ማስጀመርያ መርሐ ግብር በሥዕላዊ መግለጫዎች

eotc-tv1
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ(የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሊቀ ጳጳስ)ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ(የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ)፤ ብፁዕ አቡነ ማትያስ(የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ)ብፁዕ አቡነ ማርቆስ(የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሓላፊ፣ የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) በተገኙበት ጸሎተ ወንጌል ደርሶአል፤


 

eotc-tv2

በደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ወረብ ቀርቦአል፤ በሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችተወልደ ኢየሱስ በቤተ ልሔም የሚለው መዝሙር ተዘምሯል፤


eotc-tv3
“ብዙ ነቢያት እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ወደዱ፤ አላዩም፤ እናንተ ግን አያችኹ፤”
የሚለውን ቃለ ወንጌል መነሻ በማድረግ “ዛሬ ልዩ ቀን ነው” ያሉት የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ “ባለቤቶች እናንተ ናችኹ፤ እስከ አኹን ያላየነውን አይተናልና እንኳን ደስ አላችኹ፤” ብለዋል፡፡

ብፁዕነታቸው፣ መደበኛ ሥርጭቱን ለማስጀመር የነበረውን ውጣ ውረድ የገለጹት፣ “የቤተ ክርስቲያን ሥራ ትራፊክ ይበዛበታል፤” በማለት ነበር፡፡

“ዛሬ አጋንንት ብቻ ሳይኾኑ በስመ አብ የሚሉ አጋንንት ተፈጥረዋል፤” ሲሉ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች የኾኑ ሰርጎ ገብ ፀራውያንን ጠቁመዋል፡፡ ጣቢያው፦ መናፍቃንን የምንዋጋበት ነው፤ ጠንክረን ከሠራን በሚዲያ እናጠምቃቸዋለን ሲሉም፣ ቤተ ክርስቲያን በማስተዋወቅና አስተምህሮዋን በመግለጥ የዕቅበተ እምነት አገልግሎት ላይ አበክሮ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡


eotc-tv4
የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤልየመደበኛ ሥርጭቱን የፕሮግራም ዓይነቶች አስተዋውቀዋል፡፡ በቂ ነው ባይባልም፣ መደበኛ ሥርጭቱን ለማስጀመር የሚያስችል የሰው ኃይል ዝግጅት መደረጉንና የፕሮግራሙን ይዘት የሚገመግምና የሚያርም የኤዲቶሪያል ኮሚቴም፣ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ መሠየሙን ገልጸዋል፡፡

በስም ለይተው ያልጠቀሷቸውና “የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ያልጠበቁ” ያሏቸው ሚዲያዎች፣ የጣቢያው የሙከራ ሥርጭት በሕዝቡ ዘንድ ትኩረት እንዳያገኝ ተግዳሮት እንደ ኾኑ ተናግረዋል፡፡ የመደበኛ ሥርጭቱ መጀመር ዘገየ የሚባል ባይኾንም፣ እስከ አኹን የቆየው፣ ቀደም ብሎ የተደረገ ዝግጅት ባለመኖሩና ቀረፃ ባለመካሔዱ ነው፤ ብለዋል፡፡

በቀጣይ የመርሐ ግብሩን ዝግጅት ስለሚፈትኑ እጥረቶች በተመለከተም፤ ቋሚ ቢሮ እና ተንቀሳቅሶ ለመሥራት የሚያስችል ተሽከርካሪ አለመኖሩን በዋናነት ዘርዝረዋል፡፡ ቋሚ ቢሮው፦ በርከት ያሉ ስቱዲዮዎች፣ ለቅድመ ሥርጭትና ለድኅረ ሥርጭት ተግባራት የሚኾኑ በርካታ ክፍሎች፣ ቤተ መዛግብት፣ የአስተዳደርና የልዩ ልዩ ሞያተኞች ክፍሎች በመኾን የሚያገለግል ነው፡፡


eotc-tv5
የቴሌቭዥን ጣቢያው(ኢኦተቤ-ቴቪ)
ወደ መደበኛ ሥርጭት መሸጋገሩን በይፋ ያበሠሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ “ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ተስፋ ነው፤” ብለዋል፡፡ ይኸውም፣ እንደ ቅዱስነታቸው ገለጻ፣ “በዚኽ መሣርያ” ብዙ ሥራ ለመሥራት ስለሚቻል ነው፡፡

“አኃት አብያተ ክርስቲያናት፣ ብዙ ሥራ እየሠሩበት ነው፤ ጥለውንም ሔደዋል፤” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ÷ ካላት የሀብት ብዛትና ከችግሯ ክብደት አንፃር፣ ቀድመን ብዙ መሥራት ይገባን እንደነበር አስገንዝበዋል፡፡

ከሙከራ ሥርጭቱ መጀመር በኋላ ወደ መደበኛ ሥርጭቱ ለመሸጋገር ብዙ ዘግይቷል ብለው እንደማያምኑና ይልቁንም፣ የሰው ኃይሉን ማሟላትና በጀቱም ፈተና እንደነበር አውስተዋል፡፡ አገልግሎቱን የበለጠ ለማደራጀት የተጠቀሱት እጥረቶቹ መፍትሔ ማግኘት እንዳለባቸውና ለዚኽም ኹሉም በሞያም በገንዘብም ሊደግፉት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጣቢያው አገልግሎት ሊያተኮርባቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ሲናገሩም፣ ፍልሰትን በመግታት ምእመናንን በእምነታቸው ማጽናት፣ መማረክና ማብዛት አንዱና ዋነኛው ሊኾን እንደሚገባ አሳስበዋል –ጊዜው እየሔደ፣ የቤተ ክርስቲያናችን ልማትም እየተፋጠነ ነው፤ ስለ ሰላም እንስበክ፤ ከቤተ ክርስቲያን ወጥቶ የሚሔደው ሰው እየበዛ ነው፤ በሚዲያው ሥራ መሥራት አለብን፡፡


ጣቢያው፣ ካለፉት ስድስት ወራት የሙከራ ሥርጭት ቆይታው በኋላ ወደ መደበኛ ሥርጭት መሸጋገሩን በማስመልከት በብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅቱ የተዘጋጀው ይኸው የማስጀመርያ መርሐ ግብሩ፣ የልደት በዓል በሚከበርበት፣ ከነገ በስቲያ ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን በቴሌቭዥኑ እንደሚተላለፍ ከወዲኹ ተገልጿል፡፡

 

Advertisements

One thought on “ኢኦተቤ-ቴቪ: በዕቅበተ እምነት፣ በሰላምና በልማት ላይ ጠንክሮ እንዲሠራ ፓትርያርኩ አሳሰቡ፤“በስመ አብ የሚሉ አጋንንትንም የምናጠምቅበት ነው”/አቡነ ማርቆስ/

  1. Anonymous January 7, 2017 at 6:58 pm Reply

    ቴሌቪዥኑን ለማስታዋወቅ ላደረጋችሁት ጥረት እናመሰግናለን፣ ብትችሉ ደግሞ የሠራተኞቹን ጥረት እና ትጋት ብታክሉበት የድጋፍ ጥሪም ብታስተላልፉልን በጣም የተሟላ ዘገባ ያደርግላችኋል፣ እናመሰግናለንቴሌቪዥኑን ለማስታዋወቅ ላደረጋችሁት ጥረት እናመሰግናለን፣ ብትችሉ ደግሞ የሠራተኞቹን ጥረት እና ትጋት ብታክሉበት የድጋፍ ጥሪም ብታስተላልፉልን በጣም የተሟላ ዘገባ ያደርግላችኋል፣ እናመሰግናለን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: