የቤተ ክርስቲያናችን ቴሌቭዥን(EOTC TV): ከሙከራ ወደ መደበኛ ሥርጭት ሽግግር ነገ ይፋ ይኾናል

  • የማስጀመርያ ዝግጅቱ፣ ቅዳሜ በልደት ክብረ በዓል በቲቪው ይቀርባል፤
  • የቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ካላቸውጋ፣ በአጋርነት ለመሥራት ዝግጁ ነው፤
  • “ከሌሎች ሚዲያዎች በተነፃፃሪ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተደረገ ሽግግር ነው”

*                    *                  *

eotc-tv-test-transmission
በሙከራ ሥርጭት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ24 ሰዓት ሳተላይት ቴሌቭዥን ጣቢያ፣ ወደ መደበኛ ሥርጭት መሸጋገሩን ነገ፣ ታኅሣሥ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ እንደሚያደርግ ተገለጸ፡፡

ሽግግሩን በተመለከተ፣ በብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅቱ፣ ነገ፣ ከጥዋቱ በ3:00 በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ መርሐ ግብር የተዘጋጀ ሲኾን፤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በሚሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ሥርጭቱን በይፋ እንደሚያስጀምሩ ተጠቁሟል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመምሪያና የድርጅት ሓላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ተወካዮችና የብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ የቦርድ አባላት የመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች ናቸው፤ ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 29 ቀን በሚከበረው የልደት በዓልም የማስጀመርያ ዝግጅቱ በሳተላይት ቴሌቭዥኑ እንደሚተላለፍ ተገልጧል፡፡

ባለፈው ዓመት ሰኔ የጀመረውን የሙከራ ሥርጭት ላለፉት ስድስት ወራት ሲያቀርብ የቆየው የሳተላይት ቴሌቭዥኑ፣ በመደበኛ ሥርጭቱ፣ ከ28 ያላነሱ የፕሮግራም ዓይነቶችን እንደሚያቀርብ ተጠቅሷል፡፡

ወደ መደበኛ ሥርጭት የተደረገው ሽግግር፣ ከሌሎች ሚዲያዎች ሲነፃፀር አጭር ጊዜ የወሰደና፣ ይህም ድርጅቱ ባሉት ጥቂት ሠራተኞች ከፍተኛ መነቃቃትና የሌት ተቀን ትጋት የተከናወነ መኾኑ ተነግሯል፡፡

አኹን ያለውን ከ18 የማይበልጥ የሰው ኃይል በቀጣይ ለማሳደግ ቢታሰብም፤ የበጎ ፈቃድ ሞያተኞች እገዛ ያስፈልናል፤ ይላሉ፣ አንድ የድርጅቱ ከፍተኛ ሓላፊ፡፡ ብዙ ሚዲያዎች የአየር ሰዓታቸውን የሚሸፍኑት በውጭ ባሉ ድርጅቶች/በኮሚሽን ሲኾን፣ “እኛ በራስ አቅም ለመምጣት ነው ጥረት እያደረግን ያለነው፤” ብለዋል፡፡

ከደራሽ ዜናዎች ውጭ በ24 ሰዓት በእያንዳንዱ ዓዲስ ፕሮግራም የሚያስተላልፉ ሚዲያዎች አሉ ለማለት እንደማይቻልና፣ ፕሮግራሞች ከ6 እስከ 8 ሰዓታት ባሉት ልዩነቶች የሚደጋገሙበት አሠራር መኖሩን አስገንዝበው፤ መደበኛ ሥርጭቱ እንደተጀመረ የታሰቡትን የፕሮግራም ዓይነቶች ኹሉ ለማካተት ባይቻልም፣ የሚቀርቡ ዝግጅቶች በወጣላቸው የጊዜ መርሐ ግብር እንደሚዘዋወሩ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅቱ፣ ፍላጎቱና አቅሙ ካላቸው አካላት ጋር በአጋርነት ለመሥራት ዝግጁ መኾኑን ሓላፊው አስታውቀዋል፡፡ አጋርነቱ፥ አህጉረ ስብከትን፣ የሰንበት ት/ቤቶችን፣ መንፈሳውያን ማኅበራትን ጨምሮ ከአስተምህሯችን ጋር የማይጋጭ አገልግሎት ያላቸውንና በቤተ ክርስቲያናችን በኩል አገልጋዩንና ምእመኑን በቀናነት ለመድረስ የሚፈልጉ የውጭ አካላትን ሊያካትት እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

የአየር ሰዓት ኪራይ ገና እንዳልተጀመረና ለቦርዱ በአግባቡ የቀረበ ጥያቄ ስለመኖሩም እንደማያውቁ ጠቅሰው፤ ወደፊት በማስታወቂያ ጥሪው ሲተላለፍ የየራሳቸውን ዝግጅት ይዘው በመቅረብ መነጋገር እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን
Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Television

Satellite: Eutelsat/Nilesat (ኢትዮጵያ)
Frequency …… 11353 (5) Vertical
Symbol Rate …. 27500/ FEC ….5/6

Satellite: Galaxy 19(G-19) (ሰሜን አሜሪካ)
Frequency ….. 11960/ Vertical
Symbol Rate … 22000/FEC …3/4

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሳተላይት ቴሌቭዥን፦ ቤተ ክርስቲያናችን፥ ሰላምን፣ መከባበርን፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ዕድገትን፣ የሕዝብን በፍቅር ተባብሮ መኖርን፣ የሰው ልጅ ደኅንነትንና የሀገርን በጎ ገጽታ ማሳየትን መሠረት ያደረጉ የብዙኃን መገናኛዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ታምኖበት የተቋቋመ ነው፡፡

ሥርጭቱም፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ፣ በደቡብ ምዕራብ አውሮፓ አካባቢ፣ በሰሜን አሜሪካ/በካናዳ/፣ በካሪቢያንና በሜክሲኮ እና በአካባቢው ለሚገኙ ተመልካቾች የሚደርስ ሲኾን፤ ማንኛውም ሰው ሊያገኝ በሚችልበት መንገድ በድረ ገጽም እንደሚጫን ተመልክቷል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: