ጠቅላይ ቤተ ክህነት: ኹለት ባለዘጠኝ ፎቅ ኹለገብ ሕንፃዎችን በድሮው ቄራ ሊያስገነባ ነው፤ 193 የተወረሱ ቤቶች ርክክብ እየተካሔደ ነው

 • ግንባታውን ለማስጀመር፣ የ50 ሚሊዮን ብር በጀት በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቋል
 • በቤተ ክርስቲያን ክፍት ይዞታዎች የሚካሔድ ተከታታይ ልማት አካል ነው
 • የሥራ ሒደቱን በበላይነት የሚቆጣጠር የቴክኒክ ኮሚቴ በጽ/ቤቱ ተቋቁሟል
 • ከባንኮ ዲሮማው “ትንሣኤ” ሕንፃ ቀጥሎ የተገነቡ ንግዳዊ ሕንፃዎች ይኾናሉ

*                   *                    *

 • የቤቶች አስመላሽ ኮሚቴ፣ 193 የተወረሱ ቤቶችን ከመንግሥት እየተረከበ ነው
 • ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ሠራተኞች ቅድሚያ ሰጥቶ ለማከራየት ታስቧል
 • የኪራይ አስተዳደሩ፣ በግልጽ አሠራር የሚያስተናገድ መመሪያ እያዘጋጀ ነው
 • የመንበረ ፓትርያርኩን ይዞታዎችና ሕንፃዎች ለማስመለስ መጻጻፉ ቀጥሏል

*                    *                    *

laying-the-foundation-stone

ቅዱስነታቸው ዕብነ መሠረቱን ባስቀመጡበት ወቅት

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ አሮጌው ቄራ አካባቢ በተለምዶ እቴጌ መስክ እየተባለ በሚጠራው የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ላይ፣ እያንዳንዳቸው ባለዘጠኝ ፎቅ የኾኑ ኹለት ኹለገብ ሕንፃዎችን ሊያስገነባ ነው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፦ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ከቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከመምሪያና የድርጅት ሓላፊዎች ጋር በመኾን፣ ባለፈው ኅዳር 26 ቀን፣ የግንባታውን የመሠረት ደንጊያ አስቀምጠዋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ካህናት ጸሎተ ወንጌል አድርሰዋል፡፡

ከሥነ ሥርዓቱ በኋላ ዜና ቤተ ክርስቲያን በስፍራው የጠየቃቸው ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፦ የኹለቱ ሕንፃዎች ግንባታ፣ በዋና ከተማዋ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ክፍት ይዞታዎች ለማስጠበቅ የልማት ሥራ እንዲሠራባቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ በመመሥረት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተያዘው ሰፊ ዕቅድ አካል መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ሦስት ክፍት ቦታዎችን ለማልማት መታቀዱን ያስታወቁት ብፁዕነታቸው፣ ለኹለቱhis-grace-abune-diyoscoros ሕንፃዎች ቅድሚያ የተሰጠውም፤ በአካባቢው የከተማ ማደስ/መልሶ ማልማት መርሐ ግብር/፣ ባለይዞታዎች የየራሳቸውን ልማት በሦስት ወራት ውስጥ እንዲጀምሩ በክፍለ ከተማው በታዘዘው ውስን የጊዜ ገደብና “ራሳችንም ባለን የልማት ተነሣሽነት” መኾኑን አስረድተዋል፡፡

አማካሪ ድርጅቱ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ያቋቋመውና ዐሥር አባላት ያሉት የቴክኒክ ኮሚቴ ባካሔደው ግልጽ ጫረታ ተለይቷል፤ የሥራ ተቋራጩንም በተመሳሳይ አኳኋን ለመምረጥ ኮሚቴው እየሠራ እንዳለ ብፁዕነታቸው ጠቅሰው፣ አሸናፊው ሲታወቅ ግንባታው የሚጠይቀው ጠቅላላ“የብዝኃ ንዋይ መጠንና የጊዜ ገደቡም ወደፊት የሚገለጥ ይኾናል፤” ብለዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 1 በሚገኘውና በቤት ቁጥር 569 እና 570፣ በንግድና በመኖርያ ቤት በተያዘው 1ሺሕ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው በዚኹ የቤተ ክርስቲያን ቦታ ላይ፣ ጎን ለጎን የሚገነቡትን የኹለቱን ባለዘጠኝ ፎቅ ሕንፃዎች ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል የ50 ሚሊዮን ብር በጀት፣ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መጽደቁ ተገልጿል፡፡

የኹለቱ ሕንፃዎች ግንባታ በታቀደው ጊዜ ውስጥ ሲጠናቀቅ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ከ1966ቱ ለውጥ ወዲኽ ካስገነባውና ባለፈው ዓመት ግንቦት፣ በቸርችል ጎዳና ካስመረቀው የባንኮ ዲሮማው ባለዘጠኝ ፎቅ ትንሣኤ ሕንፃ ቀጥሎ በኹለተኛ ዙር የሚጠቀሱ ይኾናሉ፤ ተብሏል፡፡

Banko de Roma new bld complex inagurationለኹለገብ የንግድ አገልግሎት የሚውሉት ሕንፃዎቹ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን የገቢ ምንጭ በማጎልበት የወደፊት የልማት ራእይዋን በራስዋ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ እንደኾኑ ይታመናል፡፡ የባንኮ ዲሮማው ትንሣኤ ሕንፃ፣ በዓመት ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚያስገኝ፣ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የ2008 ዓ.ም. ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ ድርጅቱ ባለፈው በጀት ዓመት ብር 31 ሚሊዮን 087ሺሕ 395 ብር የኪራይ ገቢ ያስገኘ ሲኾን፣ ይህም ከ2007 ዓ.ም. ከተመዘገበው የገቢ ክንውን ከ8.35 በመቶ በላይ ዕድገት ማሳየቱን ያስረዳል፡፡

ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ፡- በድሬዳዋ፣ በዐዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በመቐለ፣ በማይጨው፣ በዐድዋ፣ በአኵስም፣ በሽሬ እንዳሥላሴና በሽራሮ ከተሞች፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ት/ቤቶች፣ ቤቶችና ሕንፃዎች በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የቤቶች አስመላሽ ኮሚቴ አማካይነት ከመንግሥት ለቤተ ክርስቲያን የተመለሱ ሲኾን፤ ከእነኚኽም ውስጥ 626ቱ በአዲስ አበባ የሚገኙና በቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅቱ አማካይነት ለመኖርያና ለድርጅት አገልግሎት የተከራዩ ናቸው፡፡ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የተዋቀረውና ከፍተኛ የሥነ ሕንፃና የሕግ ሞያተኞች ያሉት የቴክኒክ ኮሚቴ፣ ከድርጅቱ የሥራ ሒደት ጋር በተያያዘም ሞያዊ እገዛ እንደሚሰጥ ተመልክቷል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ በሐረር ከተማ የሚገኙ 25 ቤቶችን ጨምሮ ገና ያልተመለሱ ቤቶችን ለመረከብ ጥረት በማድረግ ላይ ያለው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የቤቶች አስመላሽ ኮሚቴ፣ በአዲስ አበባ አስተዳደር ቤቶች ኤጀንሲ ሥር ከሚገኙ 283 የቤተ ክርስቲያን ቤቶች ውስጥ 193ቱን ከነተከራዮቹ በመረከብ ሒደት ላይ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡ እስከ አኹን የ50 ቤቶች ርክክብ ተጠናቆ፣ ነዋሪዎቹ ከድርጅቱ ጋር የኪራይ ውል መፈጸማቸውም ተጠቅሷል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ፣ በጉለሌ፣ በየካ፣ በልደታና በአራዳ ክፍላተ ከተማ የሚገኙት ቤቶቹ፣ ለመኖርያነትና ለሱቅ እያገለገሉ ያሉ ናቸው፡፡ ለመኖርያነት ከሚያገለግሉት ውስጥ የሚለቀቁ ቤቶችን፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ሠራተኞች ቅድሚያ ሰጥቶ በግልጽ አሠራር ለማከራየት የሚያስችል መመሪያ በድርጅቱ አስተዳደር እየተዘጋጀ መኾኑም ተጠቁሟል፡፡

The Freedom Tower
የኦሮሚያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንንና የፊንፊኔ/ዱክ/ ሆቴልን
ጨምሮ ከጸጥታ አኳያ ለቤተ ክርስቲያን እንደማይመለሱ በተወሰኑት በተወካዮች ምክር ቤትና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕንፃዎች፣ ብር 71 ሚሊዮን 051ሺሕ 517 ብር ከ80 ሳንቲም ያኽል ካሳና አንደኛ ደረጃ 22 ሺሕ 856 ካሬ ሜትር ምትክ መሥሪያ ቦታ ከመንግሥት ቢሰጥም፣ በካሳው ተመጣጣኝነት ላይ በቤተ ክርስቲያን አመራር የተነሣው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም፡፡

Arat Kilo twins tower
በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ፊት ለፊት ከመንበረ ፓትርያርኩ ጎን ተገንብተው ከፍተኛ ጥቅም በመስጠት ላይ የሚገኙት ኹለት ባለ12 ፎቅ መንትያና 4 መለስተኛ ሕንፃዎች፣ መሠረታቸው የተጣለውና ሥራቸው የተጀመረው ቤተ ክርስቲያን ከውጭ ባስገኘችው የርዳታ ገንዘብ ኾኖ ሳለ እስከ አኹን እንደተወረሱ መኾናቸውን፣ ዜና ቤተ ክርስቲያን በዘገባው አስታውሷል፡፡ አያይዞም፣ በዙሪያው የሚገኙት ሲፒዩ ኮሌጅ፣ ቀዳማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት፣ ዕንባ ጠባቂ መሥሪያ ቤት፣ ባንክ ቤቶች፣ ልዩ ልዩ የንግድ ቤቶችንና ካልዲስ ሕንፃን የመሳሰሉት ኹሉ የተገነቡት በመንበረ ፓትርያርኩ ይዞታ ላይ መኾኑን ጋዜጣው ዘርዝሯል፡፡

እነኚኽንና የመሳሰሉትን በመንበረ ፓትርያርኩ ዙሪያ ያሉ ቀሪ ሕንፃዎችንና ቦታዎችን፤ ግምታቸውን እየከፈሉ ለማስመለስ የተደረገ ጥረት የለም ወይ? ሲል ላቀረበላቸው ጥያቄ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፡- ጉዳዩን እየተከታተለ የሚያስፈጽም የቤቶች አስመላሽ ኮሚቴ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዋቀሩን አውስተው፤ “ስለመንትያ ሕንፃዎችና ስለሌሎችም ያልተመለሱ ሕንፃዎች፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለመንግሥት ደብዳቤ ጽፈዋል፤ በየጊዜውም ተከታታይ ደብዳቤዎች እየተጻፉ በአቤቱታ ላይ እንገኛለን፤” በማለት ምላሽ መስጠታቸውን ጽፏል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመኾን ባለፈው ዓመት ግንቦት የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ በሀገረ ስብከታቸው አያሌ የልማት ተግባራትን ያከናውኑ ፈጣን የሥራ አባትና የለውጥ ሐዋርያ መኾናቸውን በማጠቃለያው ያሰፈረው ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ የልማት ዕቅዶቻቸው እንዲሳኩና ጥያቄዎቹም በሥራ ዘመናቸው ተግባራዊ ምላሽ እንዲያገኙ፣ “ከላይ እስከ ታች ያለነው የቤተ ክርስቲያን አካላት ከጎናቸው በመቆም ልናበረታቸውና ልንደግፋቸው ይገባል፤” ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

Advertisements

2 thoughts on “ጠቅላይ ቤተ ክህነት: ኹለት ባለዘጠኝ ፎቅ ኹለገብ ሕንፃዎችን በድሮው ቄራ ሊያስገነባ ነው፤ 193 የተወረሱ ቤቶች ርክክብ እየተካሔደ ነው

 1. Anonymous January 3, 2017 at 6:20 am Reply

  ዛሬ ቦታ በሊዝ በካሬሜትር 315ሺ በገባበት (ባለፈው የሊዝ ጨረታ መርካቶ አሜሪካ ግቢ አካባቢ የተሠጠ ዋጋ ነው) ብር 71 ሚሊዮን 051ሺሕ 517 ብር ከ80 ሳንቲም ካሳ ተመጣጣኝ አይመስለኝም ፤አይመለሱም የተባሉት ይዞታዎችም ሰፋፊ ቦታዎች ናቸው፤ መንግሥት ይዞታዎቹ የቤተክርስቲያን መሆናቸውን ሕጋዊ የምስክር ወረቀት (የባለቤትነት ማረጋገጫ) ይስጣት እና ከቤተክርስቲያኗ ይከራያት

 2. tesfaye legesse January 3, 2017 at 6:25 am Reply

  ዛሬ ቦታ በሊዝ በካሬሜትር 315ሺ በገባበት (ባለፈው የሊዝ ጨረታ መርካቶ አሜሪካ ግቢ አካባቢ የተሠጠ ዋጋ ነው) ብር 71 ሚሊዮን 051ሺሕ 517 ብር ከ80 ሳንቲም ካሳ ተመጣጣኝ አይመስለኝም ፤አይመለሱም የተባሉት ይዞታዎችም ሰፋፊ ቦታዎች ናቸው፤ መንግሥት ይዞታዎቹ የቤተክርስቲያን መሆናቸውን ሕጋዊ የምስክር ወረቀት (የባለቤትነት ማረጋገጫ) ይስጣት እና ከቤተክርስቲያኗ ቢካራይ የተሻለ ነው ፤

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: