በቁሉቢ የቅ/ገብርኤል በዓል: በዐውደ ምሕረቱ ዙሪያ የእርድና የመጠጥ ሁካታ የአስተዳደሩ ቸልታ ተተቸ፤ “እነሆድ አምላኩና ፀረ ኦርቶዶክሶች እየተጠቀሙብን ይኾናል”/ዜና ቤተ ክርስቲያን/

  • ድንኳን በመትከልና ጊዜያዊ ቤት በመከራየት በስእለት መልክ ይቀናጃሉ
  • ሠንጋ እየጣሉ፣ ጮማ ሲቆርጡ እና ውስኪ ለውስኪ ሲራጩ ይስተዋላሉ
  • ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን ቸል እያሉ እንደ ዋዛ ፈዛዛ ይቆጥራሉ
  • በዓሉን አከብራለኹ ብሎ ከሩቅ ከሔደ ሕዝበ ክርስቲያን የሚጠበቅ ነውን?
  • በጾምና በጸሎት የጸኑትን የሠለስቱ ደቂቅን አሠረ ጽድቅ አለመከተል ነው!

*                      *                  *

scan0027
ቅዱስ ገብርኤል እንዴት ሊታደገን ይችላል?

(ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ ርእሰ አንቀጽ፤ 63ኛ ዓመት ቁጥር 76፤ ታኅሣሥ 2009 ዓ.ም.)

በመብላትና በመጠጣት ወተት እንደ ጠገበ ጥጃ ጠግበው ሲፈነጥዙና እንደ ሰብኣ ትካት በየዕለቱ አስረሽ ምችው ሲሉ፤ በዛፉ፣ በቅጠሉ፣ በወንዙ፣ በሣሩ፣ በጋራው፣ በሸንተረሩ በጠቅላላው በሰው ሠራሽ ምስልና በሥነ ፍጥረቱ ኹሉ ሲያመልኩ፣ በንስሐ አእምሮአቸው ወደራሳቸውና ወደ ፈጣሪያቸው እስኪመለስ ድረስ በፈጣሪያቸው ትእዛዝ በቅዱሳን መላእክት አማካይነት ለመአትና ለጥፋት ተላልፈው ይሰጣሉ፤ ወይም ፈጣሪያቸው ለመአትና ለጥፋት የተዘጋጁ የሰማይ መላእክትን ይልክባቸዋል፡፡

እሥራኤላውያን በረኃብ ምክንያት፣ ከከነዓን ወደ ግብጽ ተሰደው፣ በግብጽ ፈርዖናውያን እጅ ወድቀው ለአራት መቶ ሠላሳ ዘመናት ያኽል በግፍ አገዛዝ ከኖሩ በኋላ፣ ምሕረትና ርኅራኄ የባሕርዩ የኾነ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር ግፋቸውን ተመልክቶ፣ እነራሔል ወደ ሰማይ የረጩትን እንባ ተቀብሎ ጊዜው ሲደርስ እንደ አምላክነቱ የኤርትራን ባሕር ከኹለት ከፍሎ በየብስ በማሻገር ወደ ሀገራቸው ወደ ከነዓን በሰላምና በጤና እንዲመለሱ ሲያደርግ፤ ሊያስቀሩአቸው ከኋላ ከኋላ ተከታትለዋቸው የመጡትን ግብጻውያን በኤርትራ ባሕር ሰጥመው እንዲቀሩ ያደረገው በመልአከ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል አማካይነት ነው፡፡

ዳግመኛም ከሕገ እግዚአብሔር ፈቀቅ ባሉበት ወቅት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልተው ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ሰጥቷቸው ተማርከው ወደ ፋርስ ባቢሎን ወይም ወደ ዛሬዎቹ ኢራንና ባግዳድ በወረዱበት ጊዜ፣ ሠለስቱ ደቂቅ በምርኮ ላይ እያሉ አልፎ አልፎ ለቁመተ ሥጋ ያኽል አንድ አንድ ጥርኝ ቆሎ በመቆርጠምና አንድ አንድ ጉንጭ ውኃ በመጎንጨት፣ ጊዜ ሳይወስኑ ዘወትር በጾምና በጸሎት እንዲኹም በስግደት ተጠምደው፣ አምልኮተ እግዚአብሔርን አጽንተው ሲኖሩ፤ አምልኮተ እግዚአብሔርን ትተው በወቅቱ የባቢሎን ንጉሥ የነበረው ናቡከደነፆር ላቆመው ጣዖት እንዲሰግዱ በታዘዙ ጊዜ፣ “አምልኮተ እግዚአብሔርን ትተን ለጣዖት አንሰግድም” በማለታቸው ከዕቶነ እሳት ውስጥ በጨመሩአቸው ጊዜ ፈጣሪያቸው እግዚአዘብሔር ከዕቶነ እሳት የታደጋቸው ወይም ያዳናቸው መልአከ ኃይል ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ ነው፡፡

እንዲኹም በአምልኮቱ፣ በጾሙና በጸሎቱ፣ በምግባሩ በትሩፋቱ የእግዚአብሔር ሰው የነበረው ትሩፈ ምግባር ጦቢት በዚያው በባቢሎን ከወገኖቹ ከእሥራኤላውያን ጋር በምርኮ(በስደት) ላይ እያለ የትሩፋት ሥራ ሲሠራ ዐይኑ ስለጠፋበት(ስለታወረበት)፤ ከዚኽ ኹሉ መከራ ነፍሱን ከሥጋው እንዲለያት ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎቱ ተሰምቶ፣ በዓሣ ሐሞት ከዓይነ ስውርነት ያዳነውና ሣራ ወለተ ራጉኤል ትባል በነበረችው ሴት ርኵስ መንፈስ አድሮባት ባሎቿ በተከታታይ እየሞቱባት በቤተሰቦቿና በኅብረተሰቡ ዘንድ ተሸማቃ ስትኖር በዓሣ ጉበት ርኵስ መንፈሱን አስወጥቶላት ለጦቢት ልጅ ለጦቢያ አጋብቶ በሰላምና በጤና እንዲኖሩ ያደረገውም፣ “ሐኪም ሰማያዊ መወልድ መንፈሳዊ” የተባለውን መልአክ ቅዱስ ሩፋኤልን በአምሳል ሰብእ ማለት በሰው አምሳል ወደ ጦቢት ልኮ ነው፡፡ ሰዶምና ገሞራንም በብዝኃ ዝሙታቸው በእሳት የቀጣቸው ኃያላን መላእክትን ልኮ ነው፡፡

kulubi
እንግዲኽ የመላእክት ተልእኮ ከረዥም በአጭሩ ከዚኽ በላይ በተገለጸው ዓይነት ሲኾን፣ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ በሀገረ ባዕድ በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንተውና በጾምና በጸሎት ተወስነው ይኖሩ የነበሩት ሠለስቱ ደቂቅ፣ ንጉሡ ላቆመው ጣዖት አንሰግድም፤ በማለታቸው ከዕቶነ እሳት ውስጥ በጨመሩአቸው ጊዜ ፈጣሪአቸው እግዚአብሔር መልአከ ኃይል ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ የታደገበት ዓመታዊ የመታሰቢያ በዓል፣ በየዓመቱ ታኅሣሥ 19 ቀን በመላው ኢትዮጵያ አህጉረ ስብከት በቅዱስ ገብርኤል ስም የተተከሉ አብያተ ክርስቲያናት ባሉበት ቦታ ኹሉ በታላቅ ድምቀት(ክብር) ይከበራል፡፡

በተለይ በስእለት ሰሚነቱ ዝናው በመላው ዓለም የገነነው የቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል÷ ነጩም፣ ጥቁሩም ተቀላቅለው በሚገኙበት እጅግ በላቀና በገነነ ኹኔታ ይከበራል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሠለስቱ ደቂቅ ከዕቶነ እሳቱ ሊወጡና ሊድኑ የቻሉት በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንተው፣ በጾምና በጸሎት ተወስነው፣ “ለእውነተኛው አምላክ እንጂ ለአምልኮተ ጣዖት አንሰግድም፤ አንገዛም” በማለታቸው መኾኑን እየጠቃቀሰች ለአክብሮ በዓል ከየአቅጣጫው ለተሰበሰበው ወገን ታስተምራለች፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ኹሉ የሠለስቱ ደቂቅን አሠረ ጽድቅ በመከተል አምልኮ ባዕድ ላልተለየው ሥርዓት መገዛቱን ካቆመና በአምልኮተ እግዚአብሔር ከጸና በማንኛውም ጊዜ በሕይወቱ ላይ ከሚደርሰው ከማንኛውም ችግርና ፈተና ኹሉ ሊድን እንደሚችል ትመክራለች፤ ታሳስባለች፡፡

ይኹን እንጂ በአንድ ጎን ደግሞ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን ትምህርት ቸል በማለት ወይም እንደ ዋዛ ፈዛዛ በመቁጠር፣ በዐውደ ምሕረቱ ዙሪያ ድንኳን በመትከልና ጊዜያዊ ቤት በመከራየት በስእለት መልክ በመቀናጀት የሐረርን ሠንጋ እየጣለ፣ ጮማ ሲቆርጥና ውስኪ ለውስኪ ሲራጭ ይስተዋላል፡፡

ይህ ድርጊት፣ ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል አከብራለኹ፤ ብሎ ከሩቅ ከሔደ ሕዝበ ክርስቲያን የሚጠበቅ ነውን? የሠለስቱ ደቂቅን አሠረ ጽድቅስ የተከተለ ነወይ? የሀገር ጎብኚዎችስ ሊታዘቡንና መጥፎ ታሪክ ሊቀርፁብን አይችሉም ወይ? የምንወደውና የምናከብረው ቅዱስ ገብርኤልስ፣ ችግርና ፈተና በደረሰብን ጊዜ እንዴት ሊታደገን ይችላል? ከኹሉም በላይ አምላካችን እግዚአብሔር አያዝንብንምን? በዚኽ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ላይ፣ ቤተ ክርስቲያናችን እስከ ዛሬ ድረስ ለምን ተገቢውን ርምጃ አልወሰደችበትም? እርሷም ተባብራ ነው እንዴ?

ማን ያውቃል፣ የፀረ ኦርቶዶክስ እምነት አራማጆች የቤተ ክርስቲያናችንን እምነትና ሥርዓት በትውልዱ ዘንድ ለማስጠላት ኾን ብለው እያደረጉት ይኾናል ወይም “እለ ከርሶሙ አምላኮሙ = ሆዳቸው አምላካቸው” የተባሉት፥ ሃይማኖታቸው መብል መጠጥ ብቻ የኾነ እግዚአብሔር አልባ ቡድኖች በዓሉን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው እየፈጸሙት ይኾናል፤ ማን ያውቃል?

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: