በቁሉቢ ቅዱስ ገብርኤል: ይፈጸማል የተባለው “ኃይለኛ ሙስና” ተጣርቶ ርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ

 • ገዳሙ፣ “አቤቱታ አቅራቢዎቹ ስም የሌላቸውና በወንጀል የሚፈለጉ ናቸው፤” ይላል
 • በኹለቱ ዓመታዊ ክብረ በዓላት፣ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የስዕለት ገቢ ተሰብስቧል
 • በወርኃዊ በዓላት የሚሰበሰበው ጥሬ ገንዘብ እና ንዋያተ ቅድሳት ለምዝበራ ተጋልጧል
 • ማሠልጠኛዎች እንዲገነቡ እና የማኅበራዊ ልማት ተሳትፎው እንዲጠናከር ተጠይቋል
 • ለረጅም ጊዜ የቆዩት ሓላፊዎች፡- ሙስናን በሚጸየፉ፣ በተማሩና በነቁ አገልጋዮች ይተኩ

*                 *              *

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ 16 ቁጥር 884፤ ቅዳሜ፤ ታኅሣሥ 15 ቀን 2009 ዓ.ም.)

kulubi-saint-gabriel-church
በቁሉቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ውስጥ፣ እየተፈጸመ ነው በሚል ከምእመናን በተደጋጋሚ የቀረበው የሙስና አቤቱታ፣ ተጣርቶ አስፈላጊው ርምጃ እንዲወሰድ፣ የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን መስተዳደር ጽ/ቤት አሳሰበ፡፡

የመስተዳድሩ ጽ/ቤት ማሳሰቢያውን ያቀረበው፣ ባለፈው ወር መጀመሪያ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ በዞኑ ሜታ ወረዳ ቁሉቢ ከተማ በሚገኘው የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ውስጥ፣ “ኃይለኛ ሙስና እየተፈጸመ” መኾኑን በመጥቀስ ጉዳዩ እንዲጣራ የአጥቢያው ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ለመስተዳድሩም በግልባጭ አስታውቀው እንደነበር ጽ/ቤቱ አስታውሷል፡፡

አቤቱታውን ለማጣራት፣ ከገዳሙ አስተዳደርም ይኹን ከምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳልተደረገ፣ ከምእመናኑ በድጋሚ መረዳቱን የጠቀሰው የዞኑ መስተዳድር፤ “ለሕዝበ ክርስቲያኑ ክብር አለመስጠትን ያመለክታል፤” ሲል ተችቷል፡፡

“ጉዳዩ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳያመራ”፣ በገዳሙ እየተፈጸመ ነው ስለተባለው ሙስና፣ በቤተ ክርስቲያን አመራር በተገቢው መንገድ ተጣርቶ አስፈላጊው ርምጃ እንዲወሰድና ለሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲገለጽ የፓትርያርኩን ቢሮ ጠይቋል፡፡

kulubi-st-gabriel-church
ጉዳዩ፣ በመንግሥት ደረጃ የፓትርያርኩ ቢሮ እስኪጠየቅ ድረስ ቸል መባሉ፣ በእጅጉ ቅር እንዳሰኛቸው የገለጹት የአጥቢያው ምእመናን፦ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ መዳከሙን፤ በገዳሙ የተከናወነ ተጠቃሽ አካባቢያዊ ማኅበራዊ ልማት አለመኖሩን፤ የአገልጋዮች ደመወዝ የገቢውን ያኽል አለመሻሻሉንና ካህናቱ ከሚያሳዩት ትጋት ውጭ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ለማጠናከር በአስተዳደሩ የሚደረገው ጥረት እዚኽ ግባ የማይባል መኾኑን፤ ሙስናን ብልሹ አሠራርን በመቃወም ከአስተዳደሩ የተለየ አቋም የሚይዙ ሠራተኞች በየምክንያቱ እንዲርቁ መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

በየዓመቱ ታኅሣሥ 19 እና ሐምሌ 19 ቀን ለገዳሙ በስዕለት ከሚገባው ጥሬ ገንዘብ እና የተለያዩ ዓይነት ንዋያተ ቅድሳት ውጭ ባሉት ወርኃዊ በዓላትም ከፍተኛ ገቢ እንደሚገኝ ምእመናኑ ይናገራሉ፡፡

የኹለቱ ዓመታዊ ክብረ በዓላት ገቢ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና በዞኑ መስተዳድር አካላት ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበትን ያኽል በሌሎቹም ወራት አለመደረጉ፣ ለከፍተኛ ሙስና አጋልጦታል፤ የሚሉት ምእመናኑ፤ በየዓመቱ ለክብረ በዓል በሚጎርፉት በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ተሳላሚዎች፡- የጸበል ቦታው እንዲታወቅ፣ ማረፊያዎችንና መጸዳጃዎችን ማመቻቸቱ እንኳ ትኩረት አልተሰጠውም፤ ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡

[የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በሚገኝበት በቁሉቢ ከተማ ዙሪያና በወረዳው ቀበሌዎች፦ እንደ ቀርሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኮረሜ ቅድስት ማርያም፣ ወተር ኪዳነ ምሕረት እና ላንጌ ቅዱስ ራጉኤል ያሉት ችግረኛ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ከሐረርና ከድሬዳዋ በሚጓዙት ምእመናን የሚረዱ እንጂ ከገዳሙ የሚያገኙት ድጋፍ አለመኖሩም ጠቁመዋል፡፡]  

የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ ኃይል አባ ወልደ ጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ የዞኑን ጥያቄ በተመለከተ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጋር መወያየታቸውንና የተሰጠውን ምላሽም ትላንት ለመስተዳድሩ ማድረሳቸውን አዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ “ጉዳዩ መታየት ያለበት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ነው፤” ያሉት አስተዳዳሪው፣ የሙስና አቤቱታ አቅርበዋል የተባሉት ሰዎች ራሳቸው፣ በወንጀል የሚፈለጉ መኾናቸውን ጠቅሰው፣ ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቀናል፤ ብለዋል፡፡

የገዳሙ ሒሳብ ሹሙ ወ/ሪት ወይንሸት ግርማም፣ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ማንነታቸውን አለመግለጻቸውን ጠቅሰው፣ አቤቱታ የቀረቡባቸውን ጥያቄዎች ከሀገረ ስብከቱ ጋር ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በአካል አቅርበን በደብዳቤ የተሰጠውን ምላሽ ደግሞ፤ አዲስ አበባ ለሚገኘው ክልላዊ ቢሮና ለምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጽ/ቤት መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡

[ቀደም ሲል፣ ከምእመናኑ የቀረቡ አቤቱታዎችን መሠረት በማድረግ፣ አስተዳዳሪውን ጨምሮ የጽ/ቤቱ ሓላፊዎች፦ ከደለበ የባንክ ተቀማጭ ጀምሮ በተለያዩ የንግድ ተቋማት ባለአክስዮኖች መኾናቸውን፤ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ ውድና ዘመናዊ የመኖርያ ቤቶችን መግዛታቸውን እንደ ማሳያ በመጥቀስ ገዳሙን እየመዘበሩ እንዳሉ መዘገቡ ይታወሳል፡፡]  

ገዳሙ፣ በገቢረ ተኣምራቱ ያለውን ታዋቂነትና የገቢ መጠኑን ያኽል፣ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ለከተማው ምእመናን ተደራሽ በኾነ አኳኋን እንዲያስፋፋ፤ ቀድሞም የነበሩት የካህናት ማሠልጠኛ እና የአብነት ት/ቤቶች በተደራጀ መልኩ እንዲከፈቱ፤ እንደ ድሬዳዋና ሐረር ባሉት ከተሞች ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ የራስ አገዝ ግንባታዎችን በማካሔድ ማኅበረሰባዊ አገልግሎቱን የሚያጠናክርበት አቅም እንዲፈጥር፤ ጠቁመዋል፤ ምእመናኑ፡፡ ለዚኽም ገዳሙ፣ ለረጅም ጊዜ ከቆዩት ሓላፊዎች ይልቅ፡- ሙስናን የሚጸየፉ፣ የተማሩና የነቁ አገልጋዮች ያስፈልጉታል፤ ይላሉ፤ ምእመናኑ፡፡

በዓመት ኹለት ጊዜ ለሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ወደ ገዳሙ ከሚጓዙ ተሳላሚዎች፣ ከ23 ሚሊዮን 587 ሺሕ ብር በላይ በስዕለት መግባቱን የሐምሌ 19 ቀን 2007 እና የታኅሣሥ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ይኸው ገቢ፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የበጀት ዕቅድ እየወጣለት፥ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የነገረ መለኰት ኮሌጆች፣ ለአብነት መምህራን፣ ለሰባክያነ ወንጌልና ለሠራተኞች ደመወዝ የሚከፈል ሲኾን፤ የሙከራ ሥርጭት እያካሔደ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን ጣቢያ የ9 ሚሊዮን ብር አስተዋፅኦ ማድረጉም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በስዕለት የሚሰበሰቡትን የተለያዩ ዓይነት ንዋያተ ቅድሳት፣ ዋጋ አጥንቶና ተማኝ ኮሚቴ አቋቁሞ የሚያሰራጭ የማደራጃ መምሪያ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተቋቋመ ሲኾን፤ ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ሕንፃ ለማሠራትም ዕቅድ መያዙን ማደራጃው በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

Advertisements

One thought on “በቁሉቢ ቅዱስ ገብርኤል: ይፈጸማል የተባለው “ኃይለኛ ሙስና” ተጣርቶ ርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ

 1. Anonymous December 24, 2016 at 7:12 pm Reply

  በሰመአብ ወወልድ ወመንፈሰቅዱስ ፩ዱ አምላክ አሜን በቅድሜያ የግዜአብሔር ፀጋ ይብዛ ላችሁ
  እባካችሁ በፀሎት እንበርታ በዚህ ዘመን ሰወች እራስ ወዳድ እየሆኑ ነዉ በዉጩአለም ያለንኢትዮጵያዉያን እንተዛዘን
  አለን በሀገርቤትያሉ ወገኖቻችን ግን መተዛዘን ቀርቶ መገዳደል በቀረ ሰዉ መንፈስ እርቆታል ከሡዳን ዘመዽጥየቃ ወደበለሣ ሒጄ አይኔ እያየ በጥይት መተዉ ሲል ያየዉን እና የታዘበዉን ከሱዳን ለዶቸበሌ ዛሬቅዳሜ ሲናገር ሰምቻለሁ ስለዚህ ለምነዉ በወገኑለይ ሠውየሚጨክነዉ መንግስትንብቻ ማአማረር ዋጋየለዉም ቆም ብሎ ሰዉ ቅድሚያ ያስብ ነዉ ያለአድማጩ እኔምያሣቡ ተጋሬነኝ ህዝቡ እራሱ አንዱ ባንዱለይ እየሣቀያለበት ሰሀአት ሁኗአል ልብያለዉ ልእብ ይበል እንላለን ህዝብ ሆይ ተፋቀር አትገዳደል ለወገን ወገን ነዉ ደራሽ እና ሰላም ይስጠን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: