የኦርቶዶክሳውያን አገልጋዮች መረዳጃ ዕድር ተቋቋመ፤ “ብር ከመሰብሰብና አስከሬን ከመሸኘት የላቀ መረዳዳትና ቤተ ክርስቲያንን የመጥቀም ዓላማ አለን”/ኮሚቴው/

 • ዕድሩ፥ ቤተ ሳይዳ ተብሏል፤ ዓላማውን የሚደግፉቱ በመመዘገብ ላይ ናቸው
 • በአገልጋዮች እና በሠራተኞች መካከል ወዳጅነትንና ቤተሰባዊነትን ያጠናክራል
 • ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲያጋጥም ለመረዳዳትና ለመተሳሰብ ያስችላል
 • ተደራጅቶ በጋራ በመሥራት ራስንና ቤተ ክርስቲያንን የመጥቀም ዓላማ አለው
 • ፖለቲካን በተመለከተ ከየትኛውም አካል ጋር ግንኙነት አያደርግም

*                 *            *

 • አገልጋዩ፥ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የአባልነት መታወቂያ ያለው ሊኾን ይገባል
 • ኦርቶዶክሳዊ ዶግማንና ቀኖናን በመጠበቅ ከሚያስነቅፉ ተግባራት መራቅ አለበት
 • በማጽናኛ መርሐ ግብር ላይ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዋወቅ አተኩሮ ይሠራል
 • ከዕድሩ ዕድገትጋ ተያይዘው ከሚመጡ ጥቅሞች ኹሉ የመጋራት መብት አለው
 • የአዲስ አባላት መግቢያ ብር 500 እና መደበኛ ወርኃዊ ክፍያ ብር 50 ተወስኗል

*               *                *

yeagelgayoch-meredaja-edir_2

ከመረዳጃ ዕድሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በከፊል(ከግራ ወደ ቀኝ)፡- መጋቤ ሥርዓት ደስታ ጌታሁን፣ ወ/ሪት ፌቨን ዘሪሁን፣ ዘማሪ ይትባረክ ተገኝ፣ መምህር ዐቢይ መኰንን፣ መምህር ሱራፌል ታደሰ፣ መምህር ዮናስ ነጌሶ፤

“ቤተ ሳይዳ” የተሰኘ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ሠራተኞች መረዳጃ ዕድር ምሥረታ ተካሔደ፡፡

ባለፈው ወር፣ ኅዳር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በዐዲስ አበባ የተመሠረተው የመረዳጃ ዕድሩ፣ በቁጥር ከ70 ያላነሱ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ሠራተኞች በተገኙበት መቋቋሙ ታውቋል፡፡

የመረዳጃ ዕድሩ፦ ፆታ፣ ቀለምና ጐሣ ሳይለይ በጥቂት ወንድሞችና እኅቶች የራስ አነሣሽነት መቋቋሙ የተጠቀሰ ሲኾን፤ በመተዳደርያ ደንቡ የሰፈረውን ዓላማ የሚደግፉ ኦርቶዶክሳውያን አገልጋዮችና ሠራተኞች ኹሉ የመግቢያ ግዴታዎችን በማሟላት መመዝገብ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

በምሥረታ ጉባኤው ላይ፣ 27 አንቀጾች ያሉት የመረዳጃ ዕድሩ መተዳደርያ ደንብየማቋቋሙን ተነሣሽነት በወሰዱትና አገልጋዩና ሠራተኛው በመረጣቸው የኮሚቴ አባላት በንባብ ቀርቦ ተደምጧል፡፡ ከተደረገው ሰፊና ግልጽ ውይይት በተገኙ በርካታና ጠቃሚ የማሻሻያ ሐሳቦችም፣ ዳብሮና ተቃንቶ መዘጋጀቱ ተመልክቷል፡፡

በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ሠራተኞች መካከል ቤተሰባዊነትንና ወዳጅነትን ማጠናከር፥ መተዳደርያ ደንቡ በቀዳሚነት ያሰፈረው የመረዳጃ ዕድሩ ዓላማ ነው፡፡ በዚኽም፦ በሐዘንና በደስታ ጊዜ በመረዳዳት በማንኛውም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ለመተሳሰብ ያስችላል፤ በሀገሪቱ ሕጎችና ደንቦች መሠረትም፣ በጋራ ተደራጅቶ ሥራ በመፍጠር ራስንና ቤተሰብን እንዲኹም ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን የመጥቀም ዓላማ ይኖረዋል፤ ተብሏል፡፡

ከአባላቱ የሚበዙት፣ በምእመኑ የሚታወቁ የሕዝበ ክርስቲያኑ አገልጋይ እንደመኾናቸው፣ “ቢሞቱ የሚሸኛቸውና የሚቀብራቸው አያጡም፤” ያሉት የምሥረታ ጉባኤው ተካፋዮች፣ ዕድሩ በሕይወት ሳሉ በጋራ እየሠሩ በመደጋገፍ ዓላማ ላይ እንዲያተኩር አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

“ብር መሰብሰብ፣ ንፍሮ መቀቀልና አስከሬን መሸኘት ብቻ ሳይኾን፣ አገልጋዩና ሠራተኛው በጋራ ተደራጅቶ ኑሮውን የሚያሻሽልበት፤ ሀገሩንና ቤተ ክርስቲያኑን የሚጠቅምበት አስቻይ ኹኔታ የሚፈጠርበት ነው፤” ብለዋል – መተዳደርያ ደንቡን ያብራሩ የኮሚቴ አባላት፡፡

“አገልጋይ ሲባል ማን ነው?” የሚለው ነጥብ፣ መሥራቾችን በስፋት ያወያየና ያከራከረ ጉዳይ ነበር፡፡ ዕድር ማኅበራዊ መረዳጃ ቢኾንም፣ በአባልነት መስፈርቱ የእምነት አቋምን ከማስረገጥ ጀምሮ በጥንቃቄ ተጠንቶ በደንቡ መስፈር እንዳለበት ስምምነት ተደርሶበታል፡፡

የአባላትን ቁጥር መወሰን እንደ ሐሳብ ቢጠቆምም፣ ኦርቶዶክሳዊ ዶግማንና ቀኖናን መጠበቅና እንዲኹም የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መታወቂያ መሠረታዊ የአባልነት አንቀጾች ኾነው ተቀምጠዋል:: የአባላት ቁጥርም ሳይወሰን፣ መተዳደርያ ደንቡን የተቀበለ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ኦርቶዶክሳዊ አገልጋይና ሠራተኛ ተመዝግቦ መግባት እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡

አባሉ፣ በደንቡ በተዘረዘሩ ኹኔታዎች ወቅት የገንዘብና ሌሎች ማበረታቻዎች የማግኘት፤ በአጠቃላይ አካሔዶች ላይ በተገቢው መንገድ ሐሳብ የመስጠት፤ በሥራ አስፈጻሚነት ተመርጦ የማገልገል፤ ከዕድሩ ዕድገት ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ጥቅሞች ኹሉ የመጋራት መብት ይኖረዋል፡፡

በአንፃሩ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከሚያስነቅፉ ተግባራት የመራቅ፤ የማጽናኛ መርሐ ግብሮችን ጨምሮ በጠቅላላ ጉባኤና በሥራ አስፈጻሚው በሚጠሩ ሌሎች ስብሰባዎች የመሳተፍ፤ በደንቡ የተቀመጠውን የመግቢያና ወርኃዊ ክፍያ በተወሰነው ጊዜ የመክፈል፤ በሚመደብባቸው መርሐ ግብሮችና ሓላፊነቶች የማገልገል ግዴታዎች አሉበት፡፡

ye-eotc-aglegayoch-meredaja-edir

የመረዳጃ ዕድሩ ሥራ አስፈጻሚ አስመራጮች በሥራ ላይ(ከግራ ወደ ቀኝ)፤ መምህር ተስፋዬ ሞሲሳ፣ መጋቤ ምሥጢር ቡሩክ አሣመረ፣ ሊቀ ትጉሃን ደረጀ ነጋሽ(ደረጀ ዘወይንዬ)፤

በአባሉና በተመዘገቡ ቤተ ሰዎቹ የደስታና የሐዘን ወቅቶች የሚኖሩ ማኅበራዊ መድረኮች፣ ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ የማስተዋወቅ ፋይዳም እንዳላቸው ግንዛቤ ተወስዶ፣ ለመርሐ ግብሮቹ ዝግጅት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ላይ ተመልክቷል፤ በዚኹም መግባባት፣ የመርሐ ግብር ዝግጅት ራሱን ችሎ እንዲዋቀር መደረጉ ታውቋል፡፡

መረዳጃ ዕድሩ፦ ዋና ሰብሳቢውን፣ ምክትል ዋና ሰብሳቢውንና ጸሐፊውን ጨምሮ ዘጠኝ ኮሚቴዎች ያሉት ሲኾን፤ በምሥረታ ጉባኤው ተካፋዮች በተቋቋመ ሦስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ አማካይነት፣ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ተካሒዷል፡፡ በዚኽም መሠረት፡-

 1. መጋቤ ሥርዓት ደስታ ጌታሁን – ዋና ሰብሳቢ
 2. መምህር በላይ ወርቁ – ምክትል ዋና ሰብሳቢ
 3. መምህር ዐቢይ መኰንን – ጸሐፊ
 4. መምህር ሱራፌል ታደሰ – ተቆጣጣሪ
 5. መምህር ደስታ በዛብህ(አባቴ ኃይለ ጊዮርጊስ) – ሕግ አገልግሎት
 6. ዘማሪ ይትባረክ ተገኝ – የመርሐ ግብር ዝግጅት
 7. መምህር ዮናስ ነጌሶ – ሒሳብ ሹም
 8. ዘማሪት ቅድስት አረጋ – ግምጃ ቤት
 9. ዘማሪ ፈቃዱ አማረ – ገንዘብ ያዥ
 10. ወ/ሪት ፌቨን ዘሪሁን – የሕዝብና የአባላት ግንኙነት ኾነው ተመርጠዋል፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለአንድ ዓመት በሓላፊነት ይቆያል፤ በሥራ እንቅስቃሴውም፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት እና የልማት ድርጅቶች እንዲኹም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እንደሚያደርግና ፖለቲካን በተመለከተ ከማንኛውም አካል ጋር እንደማይገናኝ፤ በፖሊቲካና ፖሊቲካ ነክ ጉዳዮችም ጣልቃ እንደማይገባ በደንቡ ተደንግጓል፡፡

copy-of-ye-eotc-aglegayoch-meredaja-edir

የመረዳጃ ዕድሩ መሥራች ጉባኤ ተሳታፊዎች በከፊል

የመረዳጃ ዕድሩ አባላት በሙሉ የሚገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ በየአራት ወሩ የሚጠራ ሲኾን፤ የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤው ጥር 1 ቀን(ጥር 4 ቀን) እንደሚካሔድ ሥራ አስፈጻሚው አስታውቋል፡፡ ይኸው ጠቅላላ ጉባኤው እስከሚደረግ ድረስ ባለው ጊዜ በአባልነት የሚገቡ አገልጋዮችና ሠራተኞች፣ ብር 300 በመክፈል በመሥራችነት ይመዘገባሉ፤ ከዚያ በኋላ የሚገቡ አዲስ አባላት ብር 500 የሚከፍሉ ሲኾን፣ መደበኛ ወርኃዊ ክፍያውም ብር 50 እንዲኾን ተወስኗል፡፡

በጥቅምት 2007 ዓ.ም.፣ በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀው ሕገ ቤተ ክርቲያን ትርጓሜ መሠረት፣ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሠራተኛ” ማለት፦ በቤተ ክርስቲያኒቱ መሥሪያ ቤቶች በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት ተመድቦ(ተቀጥሮ)፥ መንፈሳዊ፣ አስተዳደራዊ ወይም ሌላ ዓይነት አገልግሎት የሚያበረክት ሰው ነው፡፡

እንደ ሕገ ቤተ ክርቲያኑ ትርጓሜ፡– “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ” ማለት፦ በቅዳሴ ወይም በማሕሌት ወይም በሌላ መንፈሳዊ ግልጋሎት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት ተመድቦ በክፍያ ወይም በነፃ መንፈሳዊ ግልጋሎት የሚሰጥ ሰው ማለት ነው፡፡

“ቤተ ሳይዳ” – የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአገልጋዮችና ሠራተኞች መረዳጃ ዕድር፣ ከአብነት ት/ቤቶች፣ ከመንፈሳውያን ኮሌጆች፣ ከካህናት ማሠልጠኛዎችና ከሰንበት ት/ቤቶች ተምረው በወጡና ቤተ ክርስቲያን በላከቻቸው፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ የአድባራትና የገዳማት፣ የሰንበት ት/ቤቶች እና የመንፈሳውያን ማኅበራት መደበኛ እና የትሩፋት አገልጋዮች አነሣሽነት የተቋቋመ መኾኑ ተገልጧል፡፡

Advertisements

2 thoughts on “የኦርቶዶክሳውያን አገልጋዮች መረዳጃ ዕድር ተቋቋመ፤ “ብር ከመሰብሰብና አስከሬን ከመሸኘት የላቀ መረዳዳትና ቤተ ክርስቲያንን የመጥቀም ዓላማ አለን”/ኮሚቴው/

 1. Kassu Sileyew December 24, 2016 at 5:51 am Reply

  Is the members of this edir from only addis ababa or with people from other ethiopian state?

 2. Anonymous December 24, 2016 at 7:57 am Reply

   “በአገልጋዮች እና በሠራተኞች መካከል ወዳጅነትንና ቤተሰባዊነትን ያጠናክራል
   ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲያጋጥም ለመረዳዳትና ለመተሳሰብ ያስችላል
   ተደራጅቶ በጋራ በመሥራት ራስንና ቤተ ክርስቲያንን የመጥቀም ዓላማ አለው”
  ዓላማው መልካም ነው፡፡ ይበል……

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: