ክብረ ክህነታቸውን በብልሹ ምግባር ያዋረዱት የያቤሎ የ3ቱ አድባራት አለቃ ከሓላፊነታቸው ተነሡ፤ ወደ ሻኪሶ ሊቀ ካህንነት መዛወራቸውም እያወዛገበ ነው

 • ክህነታቸው እንዲሻር በማስረጃ የቀረበው አቤቱታ በቀኖናው እንዲወሰን በብርቱ እየተጠየቀ ነው
 • ምንኵስናቸውን በዝሙት አፍርሰዋል፤ በልቅ ዘማዊነታቸው ከየአድባራቱ በተደጋጋሚ ተባረዋል
 • መካኒቱን ስደስርብሽ ትወልጃለሽ ሲሉያባብላሉ፤ በመተት ያስፈራራሉ፤ ከዓላውያንም ይሰስናሉ
 • በመብል ፍቅር እየበሉ ይቀድሳሉ፤ ሲጠጡ ዕርቃናቸውን ጥለው ኃፍረታቸውን ገልጠው ያሳያሉ
 • በራሳቸው እና በልጆቻቸው ስም ያሠሯቸው አራት የከተማ ቤቶች ከፍተኛ ጥያቄ አሥነስተዋል
 • ከካህናቱ የመከሩበት ሊቀ ጳጳሱ፥ዋናው መንሥኤ መጠጥ ነው ሲሉ በዐውደ ምሕረት ገልጸዋል

*                    *                    *

 • ከአስተዳደርና ከክህነት አገልግሎት እንዲቆጠቡ ሊቀ ጳጳሱ ጊዜያዊ እገዳ አሳልፈውባቸው ነበር
 • መጽሐፋዊ፣ ቀኖናዊ እና ሰላማዊ ውሳኔ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚሰጡም ቃል ገብተው ነበር
 • እገዳው ያልከለከላቸው አለቃ መቅደስ ለመግባት ሲሞክሩ የተገቱት በከተማው ጸጥታ ዘርፍ ነው
 • ወደ ሻኪሶ ሊቀ ካህን ኾነው ቢዛወሩም፣ በእንቢተኝነት ሕዝቡን እያሳደሙና እየከፋፈሉ ይገኛሉ
 • ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ጉዳዩ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ አሳስበዋል፤
 • ጉዳዩ በዝውውር ብቻ ሳይድበሰበስ መፍትሔ ያግኝ፤ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና ደኅንነት ሲባል!!

*                    *                    *

melake-birhanat-fisseha-tsion-kebede
እኚህ ሰው መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽዮን ከበደ ይባላሉ፡፡ በዝዋይ ገዳም አቋቋም እና ቅኔ ተምረዋል፤ በወላይታ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም መንኵሰው እንደነበርም ይነገራል፡፡ ከ14 ዓመት በፊት በጉጂ ቦረና እና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከት ወደሚገኘው ሻኪሶ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሥራ የጀመሩት የደብሩ መሪጌታ ኾነው ነበር፡፡

ከጥንቱም ባለባቸው የከፋ ምግባረ ቢስነት፣ በወቅቱ የደብሩ አስተዳዳሪ በኋላ ሊቀ ጳጳስና የወቅቱ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ርምጃ ሲባረሩ ወደ ሜጋ ቅዱስ ሚካኤል አምርተዋል፡፡ ብዙም ሳይቆዩ በተጠናወታቸው የዝሙት ነውር ተከሠው ለኹለተኛ ጊዜ ሲባረሩ፣ አኹን ወዳሉበት የያቤሎ ከተማ ሦስቱ አድባራት(ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም፣ ደብረ ኢዮር እግዚአብሔር አብ ወአቡነ ሐራ ገዳምና ደብረ ብርሃን ቅዱስ ጊዮርጊስ) ይመጣሉ፡፡

በቅኔ ማሕሌቱ በትጋት አገልግለዋል፤ በሚል በአኹኑ የአድባራቱ ቄሰ ገበዝ በያኔው የያቤሎ ተልተሌና አሬሮ ወረዳዎች ሊቀ ካህን መልአከ ገነት ሐረገ ወይን ጥሩነህ ቦታም ይመደባሉ፡፡ የ3ቱ አድባራቱ አስተዳዳሪ መልአከ ጽዮን አባ ቃለ ወልድ ደስታ ሲያርፉም ሓላፊነቱን ደርበው በመያዝ፣ ሊቀ ካህናትም አለቃም ይኾናሉ፡፡ “ምዝበራውንና ዘማዊነቱን ያጧጧፈው ከዚኽ በኋላ ነው፤” ይላሉ ኹኔታውን በቁጭት የሚያወሱ የከተማው ምእመናን፡፡

በዝሙት ምክንያት ምንኵስናውን ከተዉት በኋላ፣ ትዳር መሥርተው ልጆች አፍርተዋል፡፡ በያቤሎ ከተማ አራት የግል ቤቶች አሠርተዋል፤ የተያዙትም በራሳቸውና በልጆቻቸው ስም ነው፡፡ የገንዘቡ ምንጭ፣ ተጠያቂነት የሌለበት ምዝበራቸው እንደኾነ በስፋት ይታመናል፡፡ ትዳር ቢመሥርቱም፣ የተነደፉበት የዝሙት ፆር ከጎልማሶች ሚስቶች እስከ ሴሰኞች አድርሷቸዋል፤ መካኒቱንም፣ “ከእኔ ብትገናኚ ትወልጃለሽ”  በሚል ማባበያ አልማሯትም፡፡ በመተት እያስፈራሩ ያነወሯቸውና የሌላ እምነት ተከታዮችም እንዳሉ ተነግሯል፡፡

ይህን ኹሉ አበሳቸውን እንዳላዩና እንዳልሰሙ የሸፈኑት የአድባራቱ ካህናትና ምእመናን፣ አንድ አጋጣሚ እስኪፈጠር የሚጠብቁ ይመስላል፡፡ ነሐሴ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በከተማው ሠርግ ኾነ፤ መልአከ ብርሃናት  ፍሥሓ ጽዮን ከበደም በዚያ እድምተኛ ነበሩ፡፡ አብሯቸው የኖረ ዓመል ነውና፣ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ሲተነኳኩሱ ሚስቴን ቀምተኽኛል ያለ አንድ ጎበዝ፣ በእድምተኛው ፊት በቡጢ ነርቶ ዘረራቸው፡፡

የጠቡ መንሥኤ እድምተኛውን አላከራከረም፤ ተግባብቶ የጋራ አቋም ለመያዝም ጊዜ አልፈጀም፡፡ “ከዚያች ቀን ጀምሮ፣ ምእመኑ በራሱ ተነሣስቶ፣ ይኼ ምግባረ ቢስ፣ ሃይማኖታቸንን እያጠፋ ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችንን እየዘረፈ ነው፤ ብለን ከሓላፊነቱ እንዲነሣ እንቅስቃሴ ጀመርን፤ ሥልጣነ ክህነቱም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲመረመር አቤቱታ አቀረብን፤” ይላሉ – ምእመናኑ፡፡

አቤቱታውን የተቀበለው የሦስቱ አድባራት ሰበካ ጉባኤ፣ ከኹሉ አስቀድሞ የክህነታቸው ጉዳይ በአለቃው ንስሐ አባት በኩል እንዲታይ አድርጎ ችግር መኖሩ በሪፖርት ይገለጽለታል፡፡ ካህናት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ያሉበት በሰበካ ጉባኤው የተቋቋመ ኮሚቴም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ማጣራት ያደርጋል፡፡ አለቃው መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽዮንም ተጠርተው የማጣራቱ ሪፖርት ይቀርብላቸዋል፡፡ እርሳቸውም፣ መቅደስ እንደማይገቡና የአስተዳደር ሓላፊነታቸውን በተመለከተ በሰላም ለማስተካከል(በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ) ተስማምተውና በቃለ ጉባኤው ላይ ፈርመው የኹለት ወራት ፈቃድ ይጠይቃሉ፡፡

yabelo-mariam
“የወሰዱትን ፈቃዳቸውን ሳይጨርሱ በቀን 29/01/2009 ዓ.ም. መቅደስ ገብተው ቃላቸውን አፍርሰዋል፤”
ይላል፣ በሦስቱ አድባራት ጸሐፊ ተፈርሞ ለክፍሉ ሊቀ ጳጳስ የተላከውና ችግሩ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጠው የሚጠይቀው ደብዳቤ፡፡ በዕለቱ፣ አለቃው መቅደስ ገብተው አገልግሎት ለመስጠት ሲጀምሩ ውዝግብ በመቀስቀሱ፣ ነገሩ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ከማምራቱ በፊት የተገታው በከተማው ጸጥታ ዘርፍ ትእዛዝና ጣልቃ ገብነት ነበር፡፡

አለቃው ቀደም ሲል ያመኑበትን በደላቸውን መሠረት አድርጎ ከተማው ሳይታወክ ሊቀ ጳጳሱ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጡ የሚጠይቅ 11 አባላት ያሉት የምእመናን የሰላም ኮሚቴ ባደረገው ጥረት፣ ኅዳር 3 ቀን በያቤሎ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተገኙት፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- የሦስቱ አድባራት የአገልግሎት ክፍል(ቄሰ ገበዝ) እና የአለቃውን የመልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽን ከበደን ንስሐ አባት ብቻቸውን በማናገር በቂ መረጃዎችን ተቀብለዋል፤ ከሦስቱ አድባራት ካህናት፣ ዲያቆናትና የስብከተ ወንጌል አባላት ጋር ባደረጉት ሰፊ ውይይትም በቂ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በማግሥቱ ኅዳር 4 ቀን፣ በአለቃው በደል የደረሰባቸው ሴቶች ምስክርነታቸውን ሊሰጡ ሲቀርቡም፣ በቃኝ! ከዚኽ በላይ አያስፈልግም፤ በቂ መረጃዎችን ወስጃለኹ፤” ብለው መመለሳቸውን የአድባራቱ ጸሐፊ ደብዳቤ ያትታል፡፡ በዚኹ ዕለት በዐውደ ምሕረት ለምእመናን ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን፡-ከደብሩ ካህናት ጋር ተነጋግረናል፤ ተወያይተናል፤ ኹሉንም ነገር ሰምተናል፤ አጣርተናል፤” ብለዋል፤ የችግሩ ኹሉ መንሥኤ መጠጥ መኾኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት፥ ሰላማዊ፣ መጽሐፋዊ እና ቀኖናዊ ውሳኔ እንደሚሰጡ ተስፋ ሰጥተው ሕዝቡን ማሰናበታቸውን ደብዳቤው ጠቅሷል፤ በወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትም ተገኝተው፣ ውሳኔውን በአስቸኳይ እንደሚልኩና፣ ይህን የሚቃወም ካለ ይሁዳ ነው፤ በማለት ሽማግሌዎችን መመረቃቸውን አውስቷል፡፡

ይህን ተከትሎም፣ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የአስተዳደር ሥራ እንዳይበደል ብለው ታኅሣሥ 3 ቀን በጻፉት ደብዳቤ፡- አለቃው መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽዮን ከበደ፣ ከአስተዳደር ሥራና ከውስጥ አገልግሎት ተቆጥበው እንዲቆዩና ሰበካ ጉባኤው በዋና ጸሐፊው፣ የውስጥ አገልግሎቱም በቄሰ ገበዙ እየተመራ እንዲቆይየባንክ ሒሳቡም በሌሎች ፈራሚዎች እንዲንቀሳቀስ በማዘዝ ጊዜያዊ እገዳ አሳልፈዋል፡፡
scan0022-1

ከዚኽ እገዳ በኋላ፣ በማስረጃና በማጣራት በተደረሰበት መሠረት ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ውሳኔው ቢጠበቅም፣ scan0023እንደተባለው በአጭር ጊዜ ውስጥ ባለመድረሱ፣ መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽዮን ሕዝቡን በተለያዩ ውዥንብሮች ለማደናበር ጠቅሟቸዋል፡፡ “ለብፁዕነታቸው ይዤ እሔዳለኹ፤ ፈርሙልኝ” እያሉ ከያቤሎ እንዳይነሡ ድጋፍ ለማሰባሰብ ሞክረዋል፡፡ ይህም በማስረጃ ተረጋግጦ፣ ሲያስፈርሙ የነበሩ ኹለት ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለዋል፤ የፈረሙ ጥቂቶችም በስሕተት እንደኾነ ቃላቸውን ሰጥተዋል፤ መልአከ ብርሃን ፍሥሓ ጽዮንም በከተማው አስተዳደር ፖሊስ ጣቢያ ተይዘው፣ ድርጊቱ ስሕተት መኾኑን ለከተማው ኮማንድ ፖስት አምነውና ፈርመው በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተለቀዋል፡፡

ኾኖም አለቃው፣ የብፁዕነታቸውን ትዕግሥት ተጠቅመው አማላጅ በመላክ፣ በልቅሶና በማሳዘን የውሳኔ ሐሳቦች እንዲቀያየሩና ርምጃው እንዲጓተት ከማድረግ አልተቆጠቡም፡፡ ይባስ ብለው፣ “ጉዳዩ በጓደኞቼ እንዲታይ አድርገዋለኹ” እያሉ መፎከራቸው ብዙኃኑን በማስቆጣቱ፥ ማኅበረ ምእመናን፣ አበው ካህናትና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሰፊው ከተወያዩበት በኋላ፣ ተወካዮችን ኹለት ጊዜ ወደ ሐዋሳ በመላክ፣ ለሕዝቡ ቃል በተገባው መሠረት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጣቸው በቃል ተማፅነዋል፤ በደብዳቤም ጠይቀዋል፡፡ የከተማው የፍትሕና ጸጥታ ጽ/ቤትም፣ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ፣ በስልክም በደብዳቤም ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱን በተደጋጋሚ መጠየቃቸው ተገልጧል፡፡

ከዚኽ ኹሉ በኋላ ግን፣ ታኅሣሥ 1 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ ከሐዋሳ መንበረ ጵጵስና የተሰማው ውሳኔ፣ መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽዮን ከበደ፣ ከያቤሎ የሦስቱ አድባራት እልቅና ተነሥተው፣ ወደ ሻኪሶ ወረዳ ተዛውረው ሊቀ ካህናት/ሥራ አስኪያጅ/ ኾነው መመደባቸውን የሚገልጽ ብቻ ነበር፡፡

ምደባው፣ ከክህነት ይልቅ የአስተዳደር ሓላፊነትን ቢያመለክትም፣ የሥልጣነ ክህነታቸው ጉዳይ እልባት ሳያገኝ በዝውውር መመደባቸው ተገቢ አይደለም፤ በሚል ክፉኛ እየተተቸ ይገኛል፡፡ አለቃው መረን በለቀቀ ምግባረ ቢስነታቸው ክብረ ክህነታቸውን ያዋረዱ በመኾናቸው፣ በቀረቡት የማያወላዱ ማስረጃዎች መሠረት ሊቀጥሉ እንደማይችሉ ግልጽ ውሳኔ እንደሚተላለፍ ነበር የተጠበቀው፡፡

ዘግይቶ ከስፍራው እንደተሰማው ግን፣ መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽዮን፣ በክህነታቸው ምንም ችግር እንዳልተገኘባቸውና ከቀረቡባቸው አቤቱታዎች ነፃ መኾናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ከሊቀ ጳጳሱ ደርሷቸዋል፡፡ እርሳቸውም ደብዳቤውን እያዞሩ በማሳየት፣ ከሦስቱ አድባራት እልቅናቸው ላለመነሣት ካህናቱንና ምእመናኑን እያሳደሙና እየከፋፈሉ እንደሚገኙ ነው፣ የተዘገበው፡፡

በሌላ በኩል፣ የተመደቡበት የሻኪሶ ወረዳ፣ ቀደም ሲል በምግባረ ቢስነታቸው የሚታወቁበትና የተባረሩበት በመኾኑ፣ ዝውውራቸውን የሚቃወሙና እንዳይመጡብን የሚሉ አቤቱታዎች፣ ከወረዳው አገልጋዮችና ምእመናን ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት እየደረሱ መኾኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

“የሐዋሳ መንበረ ጵጵስና ውሳኔ፣ በዚያም በዚኽም ላለችው አሐቲ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ኾኖ ይቀጥላል፤ አርኣያነትም አይኖረውም፤” የሚሉት አገልጋዮቹና ምእመናኑ፣ በራሱ ጊዜ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ከማምራቱ በፊት፣ በቀረቡት ማስረጃዎችና በተደረጉት ማጣራቶች መሠረት ክብረ ክህነትን የሚያሳይና ለቤተ ክርስቲያን ሰላም የሚበጅ ቀኖናዊ ውሳኔ በአስቸኳይ እንዲሰጥ በጥብቅ አሳስበዋል፡፡

የካህናት ተልእኮ፣ ምእመናንን በመንፈሳዊ ሥነ ምግባር መምራት ነው፡፡ ይህን አገልግሎት ቸል በማለት ምንደኛ እረኛ ከኾኑና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሊጠብቁት የሚገባቸውን የማይጠብቁ፤ እንዳይሠሩ የተከለከለውን የሚሠሩ፤ ሕዝቡን በአርኣያነት የማያስተምሩና የማይመሩ ቀሳውስት ቢገኙ ከክህነታቸው እንደሚሻሩ በፍትሕ መንፈሳዊ ተደንግጓል፡፡


ቀሳውስት፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ጋብቻ ፈጽመው እያንዳንዳቸው በአንዲት የሕግ ሚስት ተወስነው ማገልገል ይገባቸዋል፡፡ በሕግ ተወስነው የመኖርን ጉዳይ ወደ ጎን በማለት ኹለት ጊዜ አግብተው ከኾነ ሥልጣነ ክህነታቸው ይሻራል፡፡

በሲሞን መሠሪ ሐሳብ ተጠምደው ጉቦ ሰጥተው የተሾሙ፣ በሐሰት የሚመሰክሩና የሚምሉ፣ የሚኮሩ፣ የክፋትን ሥራ የሚሠሩ፣ የሚሰክሩኮከብ የሚቆጥሩ(የሚጠነቁሉ)፣ በአራጣ አብድረው አራጣ የሚቀበሉ፣ ከሴሰኛ ሴት የደረሱና ሲሰስኑ የተገኙ፣ የሚደባደቡ፣ የሰረቁ፣ የመናፍቃንን ቁርባን የተቀበሉ፣ አብረዋቸው የጸለዩ፣ አባለዘራቸውን በገዛ እጃቸው የሰለቡ፣ በገበያ መካከል የሚበሉ፣ በመሸታ ቤት የሚጠጡ፣ በአገልግሎት ምክንያት ሚስታቸውን የፈቱ፤ እመነኵሳለኹ፣ ተባሕትዎ እይዛለኹ ብለው ሚስታቸውን የተዉና ያሰናበቱ ካህናት ከሹመታቸው ይሻራሉ፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 6 ከገጽ 73 እስከ 74፤ 2ኛቀሌምንጦስ 4፤ 2ኛ ቀሌምንጦስ 5)

ቄስም ኾነ ዲያቆን ከሹመቱ ከተሻረ በኋላ ደፍሮ ለአገልግሎት ቢገባ፣ ከቤተ ክርስቲያን ተወግዞ ከአገልግሎት ይለያል፡፡ እያወቁ በዚኽ ድፍረት የተባበሩት ኹሉ ከምእመናን ይለያሉ፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አን. 6 ረስጠብ 2፤ 2ኛቀሌምንጦስ 22)

ቄስ ታሞ በሚመረመርበትና በሚታከምበት ጊዜ ከአልኾነ በስተቀር በማንም ጊዜ ፈጽሞ ዕርቃኑን ሊጥልና ሊጋለጥ አይገባውም፡፡ “ወኢትዓረቅ ቀሲስ ግሙራ ቅድመ መኑሂ እምሰብእ ዘእንበለ በጊዜ ዐጸባ” (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 6 ክፍል 4 በስ. 53)


 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: