“መነኵሴ ነበርኩ” ባዩ ፓስተር ናትናኤል ታዬ: በቅሠጣ ተግባር በቁጥጥር ሥር ዋለ! በማጭበርበር ወንጀል የክሥ አቤቱታ ቀርቦበታል

 • ግቢ ጉባኤያት በኩል፣ በማኅበረ ቅዱሳን መዋቅር ሰርጎ የመግባት ዓቅዱ ተጋልጧል፤
 • በአብነት ት/ቤቶች ርዳታ ስም፣ ‘ጳጳሳትንና ቴዎሎጂያንን የመቅረፅ’ ውጥኑን ገልጿል፤
 • ገዳማዊነትን በማጥላላት፣ ምንኵስናን በፈቃዱ ትቶ ወደ መናፍቃን የከዳ ኮብላይ ነው!
 • ለቅሠጣ ተግባሩ፣ የቤተ ክህነቱን አስተዳደራዊ ክፍተት እንደሚጠቀም ግልጽ አድርጓል፤
 • እንደ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎች፣ ‘ቸርች’ አቋቁሞ ተልእኳቸውን እያስፈጸመ ይገኛል፤

*                     *                     *

pastor-natnael-taye-arrested
ሥርዓተ ምንኵስናንና ገዳማዊ ሕይወትን በመሠቀቅና በማጥላላት፣ ምንኵስናውን በገዛ ፈቃዱ ትቶ ወደ መናፍቃን አዳራሽ ከኮበለለ በኋላ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያንን ተልእኮ ለማስፈጸም የተሠማራው ፓስተር ናትናኤል ታዬ በአንድ የቤተ ክርስቲያናችን ዐጸደ ሕፃናት ውስጥ በቅሠጣ ተግባር ላይ ሳለ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለጸ፡፡

የቀድሞው ‘አባ’ ነኝ ባይ የዛሬው ‘መጋቢ’ ናትናኤል ታዬ፤ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ከቀትር በኋላ፣ በማኅበረ ቅዱሳን የደብረ ብርሃን ማዕከል በሚያስተዳድረው የአቡነ ጎርጎርዮስ ዐጸደ ሕፃናት ቅጽር ውስጥ፣ የግእዝ ትምህርት በመከታተል ላይ የነበሩ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ለመቀሠጥ ሲሞክር ተይዞ በከተማው ፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጧል፡፡

ቀሣጢው ፓስተር ናትናኤል ታዬ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ታስሮ ጥያቄ እየተደረገለት ሲኾን፤ የማኅበረ ቅዱሳን የደብረ ብርሃን ብርሃን ማዕከል ጽ/ቤትም፣ ትላንት ሰኞ ለወንጀል ምርመራ ክፍሉ የክሥ አቤቱታ እንዳቀረበበት ተጠቅሷል፡፡

ያለፈቃድ ወደ ዐጸደ ሕፃናቱ ግቢ ገብቶ ሕገ ወጥ የምስል ቀረፃ በማካሔድ ግቢ በመድፈር፤ የሃይማኖቱ ተከታይ ሳይኾን እንደኾነ በማስመሰል ቤተ ክርስቲያኒቱን በማጥላላት፤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ሳይላክ እንደተላከ በማስመሰል የሐሰት ውክልናን መጠቀም የሚሉ የወንጀል አድራጎቶች በአቤቱታው መካተታቸው ተመልክቷል፡፡

ግለሰቡ በተጠቀሰው ዕለትና ሰዓት፣ ማዕከሉ ከሚያስተባብረው የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ጋር የተገናኘው የዐጸደ ሕፃናቱን ክፍሎችና ዙሪያውን በቪዲዮ ካሜራ ሲቀርፅና ፎቶ ሲያነሣ ከቆየ በኋላ ነው፡፡ በሰዓቱ የግእዝ ትምህርት በመማር ላይ የነበሩት የኮሌጅና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹ፣ ስለ ማንነቱ የሚያውቁት ነገር ካለመኖሩም በላይ፣ ወደ ግቢው ለመግባትና ቀረፃውን ለማካሔድ የሚያስችል አንዳችም ዕውቅና እና ፈቃድ አልነበረውም፡፡

ይህም ኾኖ ናትናኤል ታዬ ራሱን ለተማሪዎቹ ያስተዋወቀው፣ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንደተላከ አድርጎ ሲኾን፤ የአብነት ትምህርት ቤቶችን የመርዳት ፍላጎት እንዳለውም ገልጾላቸዋል፡፡ “አኹን የአብነት ተማሪዎችን መርዳትና ማጠናከር የሚያስፈልግበት ወቅት ነው፤” ያለው ናቲ፣ ከዚኹ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ውጭ ሳይቀር መጓዙንም ነግሯቸዋል፤ ዓላማውንም ሲያስረዳ፡- “በደንብ ቀርፀን እናወጣችኋለን፤ ከእናንተ ጳጳስ፣ የቴዎሎጂ ተማሪ[ቴዎሎጅያንን] ማውጣት እንፈልጋለን፤ ለዚያ ነው የመጣኹት፤” በማለት ነው ያብራራላቸው፡፡

ከዚኹ ጋር በተገናኘ መረጃ እንደሚያስፈልገው የተናገረው ናትናኤል፣ “ቤተ ክህነት ላይ ሔጄ ብጠይቃቸው የመልካም አስተዳደር ችግር ስላለባቸው መረጃውን በአግባቡ አይሰጡኝም፤ በቀጥታ መረጃውን ማግኘት የምንችለው ከናንተ ነው፤” በማለት የመምጣቱን ምክንያት አስቀምጧል፡፡ በዚኹም ሳያበቃ፣ “ቤተ ክርስቲያኒቱ ወድቃለች፤ በአኹኑ ሰዓት እጅግ ብዙ ችግር ነው ያለባት፤” የሚሉ የማጥላላት ንግግሮች ማከሉ ተጠቅሷል፡፡

pastor-natnael-taye
ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተልኬ ነው የመጣኹት ባለውና በተጠቀማቸው የማጥላላት ንግግሮች የተጠራጠሩት ተማሪዎቹም፣ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ የተጻፈለት ደብዳቤ እንዳለው ሲጠይቁት፣ “አይ፣ ደብዳቤ አልያዝኩም” ይላቸዋል፡፡ ደብዳቤ ካልያዘ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ እንዲያሳይ ጫን አድርገው ይጠይቁታል፡፡ የቀሣጢው ማንነትም ለተማሪዎቹ የታወቀው ይህን ጊዜ ነበር –“እስቲ የተጻፈልኽን ደብዳቤ ሲባል፣ አይ፥ ደብዳቤ አልያዝኩም አለ፤ መታወቂያኽን ሲባል መታወቂያውን ሲያወጣ፣ ስም፡- አቶ ናትናኤል ታዬ፤ ሥራ፡- ፓስተር ይላል፡፡ ወዲያው ፖሊስ ተጠራና ጉዳዩን ካወቀ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰደ፤” ብለዋል ስለ ኹኔታው የተናገሩ የዓይን እማኞች፡፡

ናትናኤል በፖሊስ ከተያዘ በኋላ ስለሚከተለው እምነት ሲጠየቅ፣ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ እንደኾነና ከአኹን በፊት ግን ‘ኦርቶዶክስ እንደነበረ’ ነው ምላሽ የሰጠው – “ኦርቶዶክስ ነበርኩ፤ አኹን ፕሮቴስታንት ኾኛለኁ፤ አኹን ሃይማኖቴ ፕሮቴስንታንት ነው::” ናትናኤል ታዬን ቀሣጢ የሚያሰኘውና የሚያደርገው፤ በራሱ አንደበት እንደነገረን፥ በእምነቱ ፕሮቴስታንት ኾኖ ሳለ ከቤተ ክህነቱ እንደተላከ በማስመሰል በርዳታ ስም ሰርጎ ገብቶ የመናፍቃኑን የጥፋት ተልእኮ ለማሳካት መንቀሳቀሱና በግሉም ለመጠቀም ማሰቡ ነው፡፡

pastor-natnael-taye-arrested04ግለሰቡ በአንድ ወቅት፣ ‘ትሪኒቲ’ ለተሰኘ ፕሮቴስታንታዊ መጽሔት በሰጠው ቃለ መጠየቅ፤ዐማኑኤል ኅብረት የተሰኘና ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኝ ፕሮቴስታንታዊ ማኅበር አባል መኾኑን እንዲኹም፤ ክራይስት ኢንተርናሽናል ዎርሺፕ ሴንተር (Christ International Worship Center) በሚል መጠሪያ የሚኒስትሪ ፈቃድ አውጥቶ “በአምልኮና ወንጌል ሥርጭት ዙሪያ” እየሠራ እንዳለ ተናግሮ ነበር፡፡

ኦርቶዶክሳዊነቱን ክዶ ወደ መናፍቃን አዳራሽ የኮበለለበት ኹኔታም ዴማሳዊ እንደነበር፣ ‘አባ’ ናቲ እየተባለ በተጠራበት በዚያው ቃለ መጠየቅ ግልጽ አድርጓል፡፡ ደጋጎቹ አባቶቻችን፣ ፍትወታት እኵያትን በማሸነፍ ከነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ የደረሱበትን ሥርዓተ ምንኵስናና ገዳማዊ ሕይወት ለማጥላላት ቢሞክርም ሆዱ ስለበለጠውና ለዓለማዊ ምቾት ስለተሸንፈ ነበር፣ በገዛ ፈቃዱ የተዋት፡፡

pastor-nati-on-trinity-mag
ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን የሚፈለፍሏቸውን የእፉኝት ልጆች የኾኑ የኑፋቄ ማኅበራት ፈለግ በመከተል የራሱን ‘ቸርች’ አቋቁሞ ለቅሠጣ የተንቀሳቀሰው ናትናኤል፣ ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ዐጸደ ሕፃናት የመጣበት ኹኔታ፤ ዋነኞቹ የኑፋቄው አዝማቾች በአኹኑ ወቅት እየተከተሉት ያለውን ስልት እንደሚያሳይ ተጠቁሟል፡፡

“የቤተ ክህነቱን ጉዳይ ጨርሰናል፤ በኹሉም መዋቅር ውስጥ ገብተናል፤ የቀረን በማኅበረ ቅዱሳን መዋቅር ውስጥ መግባት ነው፤” እያሉ የሚለፍፉ ሲኾን፤ ለሰርጎ ገብነቱም የትኩረት ቦታ ያደረጉት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተደራጀ መልኩ የሚማሩባቸውን ግቢ ጉባኤያትን ነው፤ ተብሏል፡፡ በአብነት ትምህርት ከሚሳተፉትም፣ ወደ መንፈሳውያን ኮሌጆች የሚገቡትንና በምንኵስና ካሉትም ለጵጵስና ሢመት የሚታጩትን በመመልመል በአምሳላቸው የመቅረፅ ውጥን እንዳላቸው ከቀሣጢው ናትናኤል ተልእኮ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

mahibere-kidusan-logo
የማኅበረ ቅዱሳን ዶክመንቴሽን ክፍል፣ “የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ: በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከትላንት እስከ ዛሬ” በሚል ርእስ በሚያዝያ ወር 2003 ዓ.ም. ባወጣው ኅትመት፣ ቤተ ክርስቲያናችንን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠርና ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ ትኩረት ያደረጉባቸው ስትራተጅያዊ ቦታዎች፥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የአብነት ት/ቤቶች እና ገዳማት እንደኾኑ ዘርዝሯል፡፡

በእኒኽም ወስጥና ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን ባለፉት ዐሥር ዓመታት፣ “ከጓዳ ወደ ሜዳ፤ ከኅቡእነት ወደ ግልጽነት፤ ከግለሰብ ወደ ማኅበር፤ ከድርጅት ወደ ድርጅቶች” መበራከታቸውን ገልጿል፡፡ የኑፋቄአቸው ሤራና አደጋ እንዳይነቃበትም፣ ማኅበረ ቅዱሳን የፈጠረው እንጂ በእውን የሌለ አጀንዳ እንደኾነ አድርገው ሲያዘናጉ መቆየታቸውን፤ ጉዳዩን አስመልክቶ የሚቀርቡ ማስረጃዎችንና ማጋለጦችንም የግለሰቦችና የማኅበራት ጠብ በማስመሰል ውስጥ ውስጡን ብዙ ለመሥራት እንደተጠቀሙበት አትቷል፡፡

ይኹንና በተጠቀሱት ተቋማት ያሉ ቀናዕያን አገልጋዮችና ምእመናን ባካሔዱት ተጋድሎና የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አመራር፤ የኑፋቄው አካሔድ ውስጥ ውስጡን እየጎዳን ያለና በአስቸኳይ ካልተቀለበሰም የህልውና ስጋት መኾኑን በመገንዘብ ዐበይት ሲኖዶሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፏል፤ በውሳኔዎቹ ላይ ተመሥርቶ በተደረገው የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ፣ የኑፋቄ ማኅበራቱ ባተኮሩባቸው ተቋማትና በአህጉረ ስብከት የማይናቁ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንዳለ ይታወቃል፡፡

የአኹኑ የናትናኤል ታዬና የመሰሎቹ አካሔድ፣ በፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተጋድሎው የቤተ ክርስቲያናችን አንዱ ኀያል አቅም በኾነው ማኅበረ ቅዱሳን ውስጥም ገብተናል ብሎ ለማሳየት የተደረገ መቃጣት ነው፡፡ የማኅበሩ መርበብ ይህንኑ ዓቅዳቸውን በቀላሉ ሊያከሽፈው እንደሚችል የሚጠበቅ ቢኾንም፤ ጥንተ መሠረቱ ለኾነውና ተረካቢ ትውልድ ለሚያወጣባቸው ግቢ ጉባኤያት ግን፣ በስትራተጅያዊ ዕቅዱ መሠረት ኹለንተናዊ ክትትሉንና ድጋፉን ሊያጠናክር እንደሚገባ የሚጠቁም ነው፡፡

megabi-natnael-taye
ከዚኽም ባሻገር ናትናኤል ታዬ የሚቀሥጠው፥ የቤተ ክርስቲያናችንን አልባሳት እንዲኹም መቋሚያ፣ ከበሮ፣ ጸናጽል የመሳሰሉትን ንዋያተ ማሕሌት በመጠቀም ጭምር እንደኾነ ባወጣው ቪሲዲ ታይቷል፡፡ የራሳቸውን ያልኾነውን የራሳቸው በማስመሰል የሚጠቀሙ የእምነት ተቋማት መኖራቸውን የሚያረጋግጥ በመኾኑ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በጥቅምት 2008 ዓ.ም. ምልዓተ ጉባኤው፣ በጉዳዩ ሰፊ ጥናት ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ ለማድረግ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ለቅሠጣው አንድ መልክና እልባት እንዲሰጥበት ያስፈልጋል፡፡

Advertisements

9 thoughts on ““መነኵሴ ነበርኩ” ባዩ ፓስተር ናትናኤል ታዬ: በቅሠጣ ተግባር በቁጥጥር ሥር ዋለ! በማጭበርበር ወንጀል የክሥ አቤቱታ ቀርቦበታል

 1. Anonymous November 30, 2016 at 5:09 am Reply

  እግዚአብሔር ልባና ይስትን

 2. Anonymous November 30, 2016 at 7:23 am Reply

  አባ ናቲ እና መሰሎቹ፤ የተጋለጡም ሆኑ የተሰወሩ፤ የተሸፈኑም ሆኑ የተገለጡ ከሃድያን እርሱ የቤቱ ባለቤት ልዑለ ባህርይ ቅዱስ እግዚአብሔር፤ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም እና እግዚአብሔር ኃይልና ስልጣን ቅድስና የሰጣቸው ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታት በሚጎበኟት ተዋሕዶ ቤ/ክ ውስጥ በክህደት ለዘለቄታው መቆየት ከቶ ከቶ ከቶ የማይቻላቸው መሆኑን አላወቁም፡፡ እግዚአብሔርንና ቅዱሳኑን፤ እውነተኛውን ሕይወት ሽተው በቤቱ የጸኑ ታዳጊና ወጣቶች ለጊዜው ያደናገሯቸው ቢመስላቸውም መጨረሻቸው ግን ጸሐይ ላይ መሰጣት ነው፡፡ ተጋድሎው ይቀጥላል፡፡
  አይዘንጋወ – ደጀ ሰላም

 3. በለው! November 30, 2016 at 5:06 pm Reply

  __ የቀድሞው ‘አባ’ ነኝ ባይ የዛሬው ‘መጋቢ’ ናትናኤል ታዬ፤ የሚቀሥጠው፥ የቤተ ክርስቲያናችንን አልባሳት እንዲኹም መቋሚያ፣ ከበሮ፣ ጸናጽል የመሳሰሉትን ንዋያተ ማሕሌት በመጠቀም ጭምር እንደኾነ ባወጣው ቪሲዲ ታይቷል፡፡

  __ የሚያደርጉትን ጠንቅቀው ያውቁታልና ይቅር አትበላቸው ተገቢውን ቅጣት ያገኙ ዘንድ ትውልዱ የፀዳና የኮራ ያልተበረዘና ያልተመረዘ ይሆን ዘንድ ሁሉም ዘብ ይቁም!!በቸር ይግጠመን

 4. Anonymous December 1, 2016 at 9:43 am Reply

  ይህ ሰው ጨርሶ መነኩሴ አልነበረም፡፡ በመተሐራ መድኃኒአለም ገዳም በዲቁና ሲያገለግል በስነምግባሩ በጣም አሳፋሪ ሥራ ይሠራ የነበረና በዚሁ ጥፋቱ በተደጋጋሚ ተመክሮ አልመለስ ያለ፤ ከዚህም አልፎ በአካባቢው ካለው መናፍቃን አዳራሽ አገልጋዮች ጋር አላስፈላጊ ግንኙነት ፈጥሮ የተባረረ፤ በገዳሙ ያሉ አባቶችን በንቀት ዐይን የሚያይ፤ በትዕቢት የተወጠረ በቤተክርስቲያን ውስጥ እያለ የቤተክርስቲያን ልጅ ግብር ያልነበረው አስመሳይ ነው፡፡
  መጽሐፋችን ከእኛ ጋር ነበሩ ነገር ግን ከእኛ ጋር ሕብረት እንዳልነበራቸው ይታወቅ ዘንድ ከእኛ ወጡ ያለው ቃል የተፈጸመበት ሰው ነው፡፡
  ከገዳሙ ከተባረረ በኋላ ሙሉ በሙሉ ከማናፍቀኑ አዳራሽ ገብቶ የተቀላቀለ፤ ከዚያምወደ ሌላ ቦታ መነኮሳትን ያሳስት ዘንድ በአላማ የተላከ፤ ሳይመነኩስ መነኩሴ ነኝ ብሎ የምንኩስና ልብስ የለበሰ በዚያም ሲቀስጥ የተያዘና የተባረረ ትክክለኛ ስሙ ዋልተንጉስ(ዋለታ) ብለን እንጠራው የነበረ ዲያቆን ነውና እወቁት፡፡ ሙሉ መረጃውን መተሐራ መድኃኔአለም ገዳም ሄዳችሁ ብትጠይቁ ነባር አባቶች ያስረዷችኋል፡፡

 5. Anonymous December 1, 2016 at 9:50 am Reply

  Poletica atawra

 6. Anonymous December 1, 2016 at 1:46 pm Reply

  እውነተኛ መነኩሴዎች ልብሳችሁ እንጅ ልባችሁ አልመነኮሰም
  ከእውነት እርቃችሁ ወደመቃብር ትወርዳላችሁ።

 7. abrham December 1, 2016 at 1:49 pm Reply

  abetuta maqireb bicha sayihon masrejawochun bedenb asebasibo lefird maqireb new lelielochim mastemaria yihonal

 8. Anonymous December 5, 2016 at 6:36 am Reply

  በጣም ከሚገርመኝ አንድ መናፍቅ እንዲሁ የቀደሙትን የማህበሩን መስራቾች ስም በመጥራት የማህበሩ አባል እንደነበር በማውራት ሊያወናብድ ይሞክራል ፡፡ ሁላችንም ልንነቃ ይገባናል፡፡ ይህ ሰው እግዚአብሔር ሲያጋልጠው ነው እንጂ ፎርጅድ ዶክመንት አዘጋጅቶ ቢመጣ ኖሮ ይሆን የነበረው ማሰብ ይቻላል፡፡ እንደዚህ ይዘው ቢመጡ እንኩዋን አባላቱ ማንን ማናገር እንዳለባቸው በየማእከላቱ ያሉ ጭምር ሊያውቁ ይገባል፡፡ ይህ አስተማሪ ሆኖዋል ፍርዱንም ሲያገኝ ወደፊት ለሚመጡትም ማስተማሪያ ይሆናል፡፡ በተለየ መልኩም እንደሚመጡ በማሰብ ማህበሩ እስከ ላይ ደረስ የሚኖረውን ግንኙነትና የክትትል ስራ ሊያጠናክር ይገባል፡፡ የትኛውም ሰው እረዳለው ብሎ ቢለን እንኩዋን ከማን ጋር መገናኘት እንዳለበት ማሳወቅ እንጂ ማንኛውንም አይነት ንግግር ማድረግ እንደማይገባ ይሰማኛል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በ 2008 ዓ. ም ውሳኔ ማስተላለፉ ብቻ በቂ አይደለም ከፍጻሜ መድረሱም ግድ ይላል፡፡ ብዙ ጊዜ ይሰናል ምንም ሲደረግ ግን አናይም፡፡ አንድ ፓትርያርክን ለምን አስተያየት ሰጠህበት ብሎ ፍርድ ቤት ከማቆም ቤተክርስቲያንን የተዳፈሩትን ንዋየ ቅዱሳትዋን እንደ አልባሌ የሚያደርጉትን በየመጽሐፋቸው የተናገሩዋትን መናፍቃን ፍርድ ቤት ማቆም ይሻላል፡፡ አቅም ካነሰ ለእምነታቸው ቀናእያን የሆኖ የህግ ምሁራን ስላሉ በበጎ ፈቃደኝነት ለቤተክርስቲያን ህልውና እንቅፋት የሆኑትን መረጃ ያለቸውን በፍርድ ቤት እንዲከታተሉ ማድረግ ይገባል፡፡ በንብረት ዙሪያ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊውንም ሀብትዋን ልንጠብቅላት ይገባል፡፡

  • ዳሞት December 6, 2016 at 3:40 am Reply

   አንተ ራስህ ውስጥህን መርምር ለፓትርያርክ አስተያየት ሰጠህ ተብሎ የተጠየቀ/የተከሰሰ/ የለም ወደ ላይ ከፍ ብሎ ስለተሳደበ ግን የተጠየቀ አለ፤ እንደውም እኝህ የዋሁ ፓትርያርክ ላይ ጥሎት እንጂ የቀደሙትማ እስከአሁን ምን እንደሚያደርጉ ፀሐፊውም፣ አንተም ታውቃለህ! እሱም አፉን ያላቀቀው ይህንኑ አውቆ ነው፣ ጥፋት ድሮም በከፋ መልኩ ነበረ፣ እሱም ይጽፍ ነበረ ምነው ታዲያ በቀድሞው ሳይጽፍ አሁን…… እናውቅሻለን አለ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: