የደቡብ ወሎ ሀ/ስብከት: በሉተራዊ ኑፋቄ ያገኘውን ዲ/ን ቴዎድሮስ ተክሉን አውግዞ ለየ፤ ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕድልና ድርሻ የለውም!!!

 • ‘ሐዋርያዊት’ በሚል ቸርች አቋቁሞ ቤተ ክርስቲያንን የሚፃረር ቅሠጣ ያካሒዳል
 • ቀርቦ እንዲጠየቅ በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግለትም፣ በኑፋቄው ቀጥሏል
 • በመንፈሳዊ ኮሌጅ እየተማረ፣ ከተወገዘው አሸናፊ መኰንን ጋር ኑፋቄን ሲያስፋፋ ነበር
 • ከተመረቀ በኋላ ወደላከችው ቤተ ክርስቲያን ሳይመለስ የመናፍቃን ሰለባ ኾኖ ቀርቷል
 • ከሰንበት ት/ቤቶችና ከፀረ ተሐድሶ ጥምረት ጋር አብነታዊ ርምጃዎች እየተወሰዱ ነው

*                    *                    *

 • በሐዋርያት አስተምህሮ መሠረት ሊመለስ ስላልቻለ፤ ከዛሬ ጥቅምት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተለየና የተወገዘ ስለኾነ በማንኛውም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕድልና ድርሻ የለውም!!!
  (ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፤ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ)

*                    *                    *

dn-tewodros-teklu-excommunicated

በሉተራዊ ኑፋቄው ተወግዞ የተለየው ቴዎድሮስ ተክሉ

ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊትና ታሪካዊት የኾነችውን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን፤ ባለችበት የመለወጥ አልያም ማዕከላዊ አስተዳደሯን በማናጋት ከፍሎ የመረከብ ውጥን ያላቸው ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን፤ አስተዳደራዊ ክፍተቶችን በመጠቀም ጭምር ውስጥ ለውስጥ የሚያካሒዱት እንቅስቃሴ በአገልግሎትዋ ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ እንዳለ የታወጀ ነው፡፡

የእነዚኽንና የሌሎችንም ፀራውያን ተጽዕኖ ለመቋቋም፤ የአሠራር ችግሮቻችንን በአስተዳደራዊ መርሖዎች ከማሻሻል ጎን ለጎን ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እስከ አህጉረ ስብከት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ፥ ከሊቃውንት፣ ከማኅበረ ካህናት፣ ከማኅበረ ምእመናንና ከሰንበት ት/ቤቶች የተውጣጡበት የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤያት እንዲቋቋሙ፤ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ምእመናንን በእምነታቸው የማጽናትና የጠፉትንም የመመለሱ አገልግሎት በትጋት እንዲከናወን በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኗል፤ በመመሪያም ተላልፏል፡፡

የኑፋቄውን ሤራና አደጋ በትምህርት የመከላከልና በማስረጃ የማጋለጥ ተልእኮ ያላቸው ቋሚ ጉባኤያቱ፤ በሚበዙት አህጉረ ስብከት እንደተቋቋሙና በእንቅስቃሴአቸውም ከፍተኛ ውጤት እንዳስመዘገቡ፣ በ35ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ካቀረቧቸው ሪፖርቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከየሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና የፀረ ተሐድሶ ጥምረት ጋር በመቀናጀት አብነታዊ ርምጃዎች እየወሰዱ ካሉት አህጉረ ስብከት መካከል በአንጋፋው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የሚመራው የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት አንዱ ነው፡፡


በሀገረ ስብከቱ፣ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን በቅጥረኛነት የሚሠሩ ተላላኪዎች፥ በወረዳ ቤተ ክህነት፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና በሰንበት ት/ቤቶች ውስጥ በስውርም በግልጽም ይንቀሳቀሳሉ፤ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቅነትን፣ የሰንበት ት/ቤት አባልነትን፣ ሰባኪነትንና ዘማሪነትንም በሽፋንነት ይጠቀማሉ፡፡ ከእነርሱም፡- “ዲያቆን” ቴዎድሮስ ተክሉ፣ “ዘማሪ” ዳዊት በቀለ እና “ቀሲስ” ሞገስ ዳምጤ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

“ዲያቆን” ቴዎድሮስ ተክሉ፥ በሀገረ ስብከቱ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ወልድ ዋሕድ የሰንበት ት/ቤት አባል ኾኖ ለረጅም ጊዜ በአገልጋይነት ቆይቷል፤ ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሲላክም፣ ለበለጠ አገልግሎት እንዲበቃ ታስቦ ነበር፡፡ እርሱ ግና፣ የኹለተኛ ዓመት የኮሌጁ ደቀ መዛሙር ሳለ ነበር፣ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዘው አሸናፊ መኰንን ባጠመደው መረብ ተጠልፎ ኑፋቄን አብሮት ማስፋፋት የጀመረው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ እየበላ ከተመረቀም በኋላ ወደላከችው ቤተ ክርስቲያን አልተመለሰም፡፡

ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የተመለሰውም፣ እንደ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን፥ ‘ሐዋርያዊት’ በሚል የራሱን ‘መሰብሰቢያ ቸርች’ ለማቋቋም ነበር፡፡ በዚያም እንክርዳድ በተመላበት ሰበካው ምእመናንንና የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችን መቀሠጥ ጀመረ፡፡ ኦርቶዶክሳዊውን ዶግማና ቀኖና የሚፃረረው ኑፋቄውም፣ “የኛ ጾም ጸሎት አያስፈልግም፤ ምልጃ የሚባል ነገር አያስፈልግም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፤ በእርሱ አምላክነት ነው የምንቀርበው፤” የሚል ነበር፡፡

የጥፋት እንቅስቃሴውን ሲከታተልና ሲያጠና የቆየው የደሴ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ሰበካ ጉባኤም፣ በቁጥር ደ/መ/043/2008 በቀን 25/04/2008 ዓ.ም. ለሀገረ ስብከቱ በጻፈው ደብዳቤ፣ ኹኔታውን በዝርዝር በማሳወቅ፣ ምእመናንን ከመደናገር ለመጠበቅ አስፈላጊው ርምጃ እንዲወሰድ ያሳስባል፡፡

ሀገረ ስብከቱም፣ ቴዎድሮስ ተክሉ ቀርቦ እንዲጠየቅ በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ በኩል ተደጋጋሚ ጥሪ ያደርግለታል፡፡ አካሔዱ ግን የዓላማ ነውና ለጥሪው የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሎ ቀርቦ ለመጠየቅና የእምነት ክሕደት ቃሉን ለመስጠት አልፈቀደም፤ እንዲያውም ሉተራዊ ኑፋቄውን ማሠራጨቱን ይቀጥላል፡፡

ከክሕደቱ እንደማይመለስ ያረጋገጠው ሀገረ ስብከቱም፣ ቴዎድሮስ ተክሉን እንደወትሮው በማገድ ብቻ አልተወሰነም፤ መናፍቅነቱ በግልጽ እንዲታወቅና ምእመናን እንዲጠበቁ ለማስቻል፣ በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ከቤተ ክርስቲያን ተለይቶ እንዲወገዝ ተደርጓል – በሐዋርያዊ አስተምህሮ መሠረት ሊመለስ ስላልቻለ፣ ከዛሬ ጥቅምት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተለየና የተወገዘ ነው፡፡ በማንኛውም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ዕድልና ድርሻ የለውም!!” ይላል፤ ከመንበረ ጵጵስናው የወጣው የብፁዕነታቸው ቃለ ውግዘት፡፡

ይኸውም ቃለ ውግዘት በአገልጋዩና በምእመናን ኹሉ ይታወቅ ዘንድ፣ የመድኃኔዓለም ታቦት ለክብረ በዓሉ ዑደት አድርጎ በቆመበትና ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ በተገኙበት የደብሩ ዐውደ ምሕረት፣ በሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ዋና ክፍል ሓላፊ መሪጌታ ፈንታ አበራ አማካይነት በንባብ ተሰምቷል፡፡

abune-atnatewos
ኦርቶዶክሳውያን፥ ሃይማኖታቸውን፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናቸውንና ሐዋርያዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ብርቱ ጥበቃ የማድረግ አባታዊ ሓላፊነት ያለባቸው ብፁዕነታቸው፣ ያሳለፉት ቃለ ውግዝት ቀኖናዊ ነው፤ ሀገረ ስብከቱም፣ ምእመናን በእምነታቸው እንዲጸኑና መንፈሳዊ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ያደረገበት ዐቢይ ሕገ ቤተ ክርስቲያናዊ ርምጃ ነው፡፡

ይህም ብቻ ሳይኾን፣ፀረ ተሐድሶ ጥምረትና ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጋር በመናበብ የሚሠራው ሀገረ ስብከቱ፤ መዋቅሩን ጠብቆ በሚደርሱት መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ፤ የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶችና የአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያት በሕጉ እንዲመሩና እንዲተዳደሩ በየወቅቱ የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችና ማሳሰቢያዎች አብነታዊ ናቸው፡፡

moges-damtie
የኮምቦልቻ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ የነበረው ‘ቀሲስ’ ሞገስ ዳምጤ፣
ያለበት ኑፋቄ በሰበካ ጉባኤውና በማኅበረ ካህናቱ በማስረጃ ተደግፎ ከቀረበለት በኋላ፣ ጉዳዩ እስኪጣራ ከሥራና ከደመወዝ ታግዶ እንዲቆይ ባለፈው ዓመት ሰኔ አጋማሽ በአስተዳደር ጉባኤው ወስኖበታል፤ ይህንኑም ለደብሩ አሳውቋል፡፡

ቴዎድሮስ ተክሉን ከመሰሉ መናፍቃንና ሕገ ወጥ ሰባክያን ጋር፤ “ወንጌል እሰብካለሁ፤ ዝማሬ እዘምራለሁ፤ መጽሐፍና ካሴት እሸጣለሁ” በሚል ለመንቀሳቀስ የሞከረውን ዘማሪ ነኝ ባዩን ዳዊት በቀለንም ያገደው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጀመሪያ ነበር፡፡

dessie-diosces-on-dawit-bekele-etal
የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትም ከእኒኽ የሀገረ ስብከቱ ርምጃዎች ጋር በመቀናጀት፣ አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋሉ፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ኹሉ፥ ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች፣ ራሳቸውን ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሤራ እንዲጠብቁ ያስገነዝባሉ፡፡

ቴዎድሮስ ተክሉ በውግዘት ተለይቷል! ከሰንበት ት/ቤት የተባረረውና ሀገረ ስብከቱ ያገደው ዳዊት በቀለ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተጋልጦ ተወግዷል! በእልቅና በመራው ደብር ኑፋቄው በማስረጃ የቀረበበት ሞገስ ዳምጤ፣ ጉዳዩ እስኪጣራ ከሥራና ከደመወዝ ታግዶ እንዲቆይ ተወስኖበታል፤ ነገር ግን፣ ወደ ወረዳው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተመልሶ፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ክፍል ሓላፊ ኾኗል መባሉ በአስቸኳይ ሊጤንና ሊፈተሽ ይገባል፡፡

Advertisements

2 thoughts on “የደቡብ ወሎ ሀ/ስብከት: በሉተራዊ ኑፋቄ ያገኘውን ዲ/ን ቴዎድሮስ ተክሉን አውግዞ ለየ፤ ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕድልና ድርሻ የለውም!!!

 1. Anonymous November 24, 2016 at 11:21 pm Reply

  አለም ቢያሣድዳችሁ ከናተበፌት እኔን እዳሣደዱኝ እወቁ ስለስሜ በአለም የተጠላችሁ ትሆናላችሁ
  ብርቱ የጌታ ወዳጂ እያንዳአ ድህ ቆብ ደፌ ሁሉ ጌታ ይቫልህ አል አለም ቢያሣድዳችሁ ከናተበፌት እኔን እዳሣደዱኝ እወቁ ስለስሜ በአለም የተጠላችሁ ትሆናላችሁ
  ብርቱ የጌታ ወዳጂ እያንዳአ ድህ ቆብ ደፌ ሁሉ ጌታ ይቫልህ አል

 2. Anonymous November 25, 2016 at 2:53 pm Reply

  በውሸት ጠግቦ ከማደር ስለ ክርስቶስ ስም መሠደድ ትልቅ ማትረፊያ ነው፡፡በደብዳቤ መሠደብ ቀላል ነው እስከ ሞት ድረስ እንኳን ቢሆን ስለ ጌታ ስም ስንል ለመሞት ዝግጁ ነን፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: