የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ: ዳዊት በቀለን ጨምሮ 8 የኑፋቄ ተላላኪዎችን አባረረ: “ለኦርቶዶክሳዊ ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት መከበር ዕንቅፋት ኾነዋል”

 • በኑፋቄአቸው ከተሰናበቱ በኋላ በይቅርታ ተመልሰው በተመሳሳይ ጥፋት የተገኙ አሉበት
 • በተፈቀደው የኮሌጁ ጉባኤ ላይ ቀንደኞቹን የተሐድሶ መናፍቃን በመጥራት አሳትፈዋል
 • ዳዊት በቀለ፣ ከደሴ መድኃኔዓለም የተባረረና በሀገረ ስብከቱ የታገደ ዘማሪ ነኝ ባይ ነው
 • ውሳኔ ለማስቀልበስ የሞከረው የክፋትና የኑፋቄ መዘውሩ ብርሃኔም ከቦታው ተዛውሯል

*               *               *

 • የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ፣ የአስተዳደር ጉባኤው በወሰደው ርምጃ ላይ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ ለቀጣዩም ከጎንዎት ነን ተብለዋል፡፡
 • ኮሌጁ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋም እንደመኾኑ መጠን፣ የሚያስተምረው፥ ዶግማዋን፣ ቀኖናዋንና ትውፊቷን በጠበቀ መልኩ ብቻ ነው፡፡
 • ቤተ ክርስቲያናችን በማታውቃቸውና ኮሌጃችን በማይቀበላቸው የኑፋቄ እንቅስቃሴዎች የተገኙትንና በእምነታቸው የተጠረጠሩትን በደቀ መዝሙርነት ለማስተማር ተቸግሯል፡፡
 • የሌሎች አብያተ እምነትን፥አስተሳሰብ፣ አቋምና ጠባዕያት አለማንጸባረቅ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አምልኮና ሥርዓት በመጠበቅና በማስጠበቅ የደቀ መዝሙርነትን ዓላማ መፈጸም/የእውነተኛ ደቀ መዝሙርነት የሥነ ምግባር ቅጽ/

*               *               *

dawit-bekeles-unconditional-dismissal-from-httc
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፤ “የእውነተኛ ደቀ መዝሙርነት”ን የሥነ ምግባር ስምምነት በመጣስ፣ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት ለማስከበር በሚያደርገው ጥረት ላይ ዕንቅፋት ኾነዋል፤ ያላቸውን ስምንት ደቀ መዛሙርት አሰናበተ።

በመንፈሳዊ ኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ተፈርሞ የወጣውና ለተማሪዎቹ በየስማቸው የተጻፈው ደብዳቤ፤ ደቀ መዛሙርቱ፥ ቤተ ክርስቲያን በማታውቃቸውና ኮሌጁ በማይቀበላቸው የኑፋቄ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንደተገኙ መረጋገጡን እንዲኹም፤ “ኮሌጁንና ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያስነቅፍ ጉልሕ የሥነ ምግባር ጉድለት” እንደታየባቸው ገልጿል።

“ከአንድ መንፈሳዊ ደቀ መዝሙር የማይጠበቅ ነው” የተባለው የሥነ ምግባር ጉድለቱ፤ የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት ለማስከበር ኮሌጁ በሚያደርገው ጥረት ላይ ዕንቅፋት የፈጠረና ደቀ መዛሙርቱ በመማር ማስተማሩ ሒደት የገቡትን ግዴታ የሚተላለፍ እንደ ኾነ ደብዳቤው አስረድቷል።

ጉዳዩም፣ ጥቅምት 1 ቀን 2009 ዓ.ም የኮሌጁ አስተዳደር ጉባኤ ባካሔደው ስብሰባ ቀርቦ መታየቱን ጠቅሶ፤ በተማሪዎች መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 11 ንኡስ ቁጥር 11(8) መሠረት፣ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ከኮሌጁ የሚያሰናብት ኾኖ በመገኘቱ፣ ስምንቱ ደቀ መዛሙርት እንዲሰናበቱ በአስተዳደሩ መወሰኑን አስታውቋል።

ደቀ መዛሙርቱ፣ የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች በጻፉላቸው የቤተ ክርስቲያን የአባልነት መረጃዎች መሠረት በመንፈሳዊ ኮሌጁ ገብተው በቀንና በማታው መርሐ ግብር በመማር ላይ የነበሩ ሲኾኑ፤ እነርሱም፡-

 1. ባዬ ከድር – ጅማ ሀገረ ስብከት
 2. ገብረ መድኅን ብርሃኑ – ቦንጋ ሀገረ ስብከት
 3. አክሊሉ ተካ በርሄ – ዓዲ ግራት ሀገረ ስብከት
 4. ኤልያስ ሙላቱ – ሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀገረ ስብከት
 5. ጥላሁን አንቢሳ – ባሌ ሀገረ ስብከት
 6. ስሜነህ በፈቃዱ – ኢሉ አባቦር ሀገረ ስብከት
 7. ደጋጋ ባልቻ – ኢሉ አባቦር ሀገረ ስብከት
 8. ዳዊት በቀለ – አዲስ አበባ ናቸው፡፡

ከስምንቱ መካከል ሁለቱ ማለትም ባዬ ከድር እና አክሊል ተካ ቀደም ሲል፣ ከተላኩበት አህጉረ ስብከት በተጻፈ ደብዳቤ ከኮሌጁ ተሰናብተው የነበሩና በኋላም ከጥፋታቸው ታርመዋል በሚል ይቅርታ ተደርጎላቸው የተመለሱ የቀን መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት ናቸው፡፡ ከሌሎቹ አምስት መሰሎቻቸው ጋር፣ በኮሌጁ ግቢ በተካሔደ ጉባኤ፣ ቀንደኛ የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆችን በመጥራት እንዲሳተፉ አድርገዋል፡፡

baye-kedirs-and-aklil-berhe-tekas-unconditional-dismissal-from-httc
ጉባኤው፣ የ2008 ዓ.ም. የኮሌጁን ምሩቃን በማስመልከት የተካሔደና በአስተዳደሩ የተፈቀደ ሕጋዊነት እንደነበረው ቢገለጽም፤ በመስሐቲነቱ የቴዎሎጂ ዲግሪውን የተቀማውና በኑፋቄ መረቡ ደቀ መዛሙርትን በማስኮብለል የሚታወቀው እንደ አሰግድ ሣህሉ ያሉ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን በተናጋሪነት የተጋበዙበት እንደነበር በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡

በተ.ቁ(8) የተጠቀሰው ዘማሪ ነኝ ባዩ ዳዊት በቀለ ደግሞ፣ በማታው መርሐ ግብር ሲማር የነበረና ቀደም ሲል ከደሴ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ወልድ ዋሕድ ሰንበት ት/ቤት በኑፋቄ ተላላኪነቱ የተባረረና በሀገረ ስብከቱም የታገደ እንደነበር ታውቋል፡፡ ከእነአሸናፊ ገብረ ማርያም ጋር “ኢየሱስ አማላጅ ነው፤ ኢየሱስን ሰብኬ ብሞት ምናለበት” እያለ በነገረ ክርስቶስና በክብረ ቅዱሳን ላይ የሚለፋደድበት ኑፋቄው በማስረጃ የተረጋገጠ ነው፡፡

የሰንበት ት/ቤቱ፣ ከአጥቢያው አስተዳደር ባሻገር በሀገር ሽማግሌዎች ሳይቀር በማስመከር ስሕተቱን አምኖ በቀኖና እንዲመለስም በብርቱ ጥሮለታል፡፡ እርሱ ግን፣ በማጭበርበር ዲቁና ለመቀበልና የማይገባውን ምሥጢር ለማየት ከመሹለክለክ ጀምሮ ከሌሎች ሕገ ወጥና የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኝ ሰባክያንና ዘማርያን ነን ባዮች ጋር የሀገረ ስብከቱን ሰላም ለማወክ መንቀሳቀሱን በመቀጠሉ ከሰንበት ት/ቤት አባልነቱ ተባሯል፤ በሀገረ ስብከቱም ታግዷል፡፡

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ “የእውነተኛ ደቀ መዝሙርነት ሥነ ምግባር” የተሰኘ ባለ12 አንቀጾች የስምምነት ቅጽ ያለው ሲኾን፤ የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት ጠንቅቀው ያወቁ ትጉሃን አገልጋዮችን ለማፍራት እንዲሁም የመማር ማስተማር ሒደቱንና የምርምር ሥራውን የተቃና ለማድረግ የተዘጋጀ ግዴታ ነው፡፡

the-true-discipleship-code-of-conduct

“የእውነተኛ ደቀ መዝሙርነት ሥነ ምግባር” ስምምነት ቅጽ

በቅጹ አንቀጽ(4)፥ የሌሎች አብያተ እምነትን፣ የማኅበራትን፣ የፖሊቲካ ንቅናቄዎችን አስተሳሰብ፣ አቋምና ጠባዕያት አለማንጸባረቅ፤ በአንቀጽ(5)፥ የአካዳሚክ ነፃነት የተጠበቀ መኾኑን፤ ነገር ግን፣ የሚጠየቁ ጥያቄዎች፣ የሚሰጡ ምላሾችና ሐሳቦች ገንቢና የሚያንፁ፤ መንፈሳዊ ሥርዓትን የተከተሉና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና ዶግማ የማያጣጥሉ መኾን እንደሚኖርባቸውበአንቀጽ(10)፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አምልኮና ሥርዓት በመጠበቅና በማስጠበቅ የደቀ መዝሙርነትን ዓላማ መፈጸም እንደሚገባ ሰፍሯል፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ስምምነቱን ተፈጻሚ በማድረግ ትምህርታቸውን የመከታተል ግዴታ አለባቸው፤ አንቀጾቹ ተጥሰው ሲገኙም፣ አስተዳደሩ በሚወስደው ርምጃ፣ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ ኮሌጁን ለቅቀው ለመውጣት ተስማምተው ነው የሚፈርሙት፡፡

በተያያዘ ዜና፣ የማታ ትምህርት ክፍል ሓላፊው ብርሃኔ ገብረ ጻድቃን ከቦታው ተነሥቶ ወደ ቤተ መጻሕፍት ክፍል ሓላፊነት ተዛውሯል፡፡ ለዝውውሩ የቅርቡ ምክንያት፣ የአስተዳደር ጉባኤው በስምንቱ ደቀ መዛሙርት ላይ ያሳለፈው ውሳኔ እንዳይተገበር ከሓላፊዎች ጋር በመወዛገብ ዕንቅፋት መፍጠሩ ነው፡፡ ብርሃኔ በኮሌጁ ሳይወሰን፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትና በመንበረ ፓትርያርኩ ያሉ ተባባሪዎቹን ይዞና ጥቂት ደቀ መዛሙርትን አስከትሎ እስከ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ድረስ ዘልቆ ውሳኔውን ለማስቀልበስ ተጣጥሯል፡፡

ይኹንና፣ የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ጉዳዩን ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ አስቀድመው በማሳወቃቸውና ለፓትርያርኩም በቂ ማብራሪያ በመስጠታቸው እንዳልተሳካለት ታውቋል፤ እንዲያውም የበላይ ሓላፊው፣ “ለቀጣዩም ከጎንዎት ነን” የሚል ማበረታቻና አጋርነት ከቅዱስነታቸው ማግኘታቸው ተገልጧል፡፡

ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን ኮሌጁን በኅቡእ ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን እንቅሰቃሴ በመርዳት ዋነኛ የኾነው ብርሃኔ ገብረ ጻድቃን፤ ቀናዕያን ደቀ መዛሙርትን በክፋት እየወነጀለ ከትምህርት ገበታቸው በማፈናቀል በብርቱ እየሠራ ያለ ነው፡፡ በመምህራንና በደቀ መዛሙርት ከሚታወቅበት ድኩም አካዳሚያዊ ብቃቱና የማስተማር ክሂሉ ጋር ተያይዞ፤ ዝውውሩ፡- “የተሻለ እንዲያነብና እንዲዘጋጅ ተብሎ ነው” የሚል ተሣልቆ ቢያጭርም፣ የበለጠ ክትትልና ጥብቅ ርምጃ የሚያሻው እንደኾነ ነው ብዙዎች የሚያምኑት፡፡

ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያንን ጨምሮ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳውያን ኮሌጆቻችን ውስጥ የሚፈጥሩትን ችግር ከመሠረቱ ለመቅረፍ፡- በደቀ መዛሙርት ምልመላና አቀባበል እንዲኹም በመምህራኑ ሃይማኖታዊ አቋም፣ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና የመማሪያ መጻሕፍት አጠቃቀም ጥልቅ ፍተሻና ጥንቃቄ እንዲደረግ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 2007 ዓ.ም. ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔው መመሪያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅም፣ ስምንቱን ደቀ መዛሙርት ባሰናበተበት ደብዳቤው፡- ኮሌጁ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋም እንደ መኾኑ መጠን፣ የሚያስተምረው፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት በጠበቀ መልኩ ብቻ መኾኑን ሳያስታውቅ አላለፈም፡፡

elias-mulatus-and-gebramedhin-birhanus-unconditional-dismissal-from-httctilahun-anbissas-and-simeneh-befekadus-unconditional-dismissal-from-httcdegaga-balchas-dismissal

Advertisements

5 thoughts on “የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ: ዳዊት በቀለን ጨምሮ 8 የኑፋቄ ተላላኪዎችን አባረረ: “ለኦርቶዶክሳዊ ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት መከበር ዕንቅፋት ኾነዋል”

 1. Anonymous November 21, 2016 at 7:46 pm Reply

  በትክክል ደቀመዛሙርቱ ከጌኤታጋር ሁነዉከሆነ ከዚህ በታች ስማአቸዉ የተጠቀሱዉት ክብር ይገባቸዋል ደቀ መዛሙርቱ፣ የአህጉረ ስብከት ጽ፨ቤቶች በጻፉላቸው የቤተ ክርስቲያን የአባልነት መረጃዎች መሠረት በመንፈሳዊ ኮሌጁ ገብተው በቀንና በማታው መርሐ ግብር በመማር ላይ የነበሩ ሲኾኑ፤ እነርሱም፡፡

  ባዬ ከድር – ጅማ ሀገረ ስብከት
  ገብረ መድኅን ብርሃኑ – ቦንጋ ሀገረ ስብከት
  አክሊሉ ተካ በርሄ – ዓዲ ግራት ሀገረ ስብከት
  ኤልያስ ሙላቱ – ሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀገረ ስብከት
  ጥላሁን አንቢሳ – ባሌ ሀገረ ስብከት
  ስሜነህ በፈቃዱ – ኢሉ አባቦር ሀገረ ስብከት
  ደጋጋ ባልቻ – ኢሉ አባቦር ሀገረ ስብከት
  ዳዊት በቀለ – አዲስ አበባ ናቸው፡፡
  ለምን ቢባል ብዞች ስራትና ቀኖና አፍርሰዉ በዝሙትና በሙስና ወድቀዋልና ታዲያ ይህስ መና ፍቅነት አይደለም
  እና ለምን ዝም ተ ባሉ

 2. Anonymous November 22, 2016 at 10:21 am Reply

  ዉድ ኢትዮጵአያ ዉያን እንደምን ሰነበታችሁ ዛሬ ያለንበት አለም ከሩቅም ከቅርብም ያሉትን
  ዘመዶቻችን በመገናኞ ብዙሐን በድምፅም በፎቶም የምንመለከትበት ነዉናአ በጀርመንሀገር በሙኒክ ከተማ
  እደዛሬዉ ሁሉ ካህናት ሣይበዙ በመለዋ ጀርመን ደከመኝ ሰለቸኝ ሰይሉ በሚያምር እና ምመናን በሚማርክ ስብከታቸዉና
  ቅዳሴያቸው የሚታወቁትን ካህ መላከብረሀ ቀሲስ መስፍን ፈለቀን ፎቶ ብዙዉምመናን ዙሬያቸዉን ከበዋቸዉ ካመታት
  በሁአላ ተመለከትኩኝ በሰላም ጊዜ ሁሉዘመድ ነዉና ከፎቶዉ ዉስጥ ብዙወች ካህኑን ከእግዜአብሔር ቤት የለዩናቸዉ
  ካህኑን ያኔ በቅዳሴ በትምህርታችዉ ወይም በፀሎታቸዉ እዲያስቡን በየሰፈራችን ያደከምናቸዉ ወይም የምሣ ሰሐታቸዉን
  ተጋፍተን ቀኑንሙሉ በቤታቸዉ ያዛጋነ ዛሬካህኑን አስበናቸዋል አንድቃል ያስተማረህን እደአባጥተመልከትዉ
  እንጀረየን የበላ ተረከዙን አነሣ አለ አብረን በልተን አብረን ጠጥተን እራሳችን ነፃአድርገን ገንዘብ ጠፍብህ ብለን
  ከቤተክርስቲያን ለየናቸዉ ዘወር ብላችሁ አስቡት ያሣለፋችሁትን ዘመን አቤት ክርስትና እሣቸዉ ክርስትና ያነሡአቸዉ
  ልጆቻችሁ ሰንታመትሞላቸዉ ቄስመስፍን አማራአማራ አማራ የዉም ጎንደሬ ስለሆኑ ተባረሩ ሌለዉ አለ ከነዝክንትሉ
  ፎቶአቸዉን በፌስቡክ ፖስት ስታረጉ አታፍሩም እና ለነገሩ በሰዉ ድግእስ

 3. Anonymous November 22, 2016 at 7:09 pm Reply

  በሃይማኖት ዘር የለም ከስርአት ውጭ ከሆነ ለምን የናት ልጅ ኧይሆንም

 4. Anonymous November 23, 2016 at 11:55 am Reply

  ደብዳቤው ጭብጥ የሌለውና በቂ ነው ብዬ አላምንም ማንም በመሰለኝና በደሳለኝ ተነስቶ አገልጋዮችን ማሳደዱ በአሁኑ ሰአት ለኛ ቤተክርስቲያን አዲስ አይደለም፡፡
  ኢየሱስ ከመንግስቱ ሲጽፋቸው ከኮሌጅ መባረር ምንም እንዳልሆነ እወቁ እየሱስ ጌታ ነው ብሎ የመሰከረ በአለም ቦታ የለውም ኢየሱስን የሰቀለች አለም የሱ ለሆኑትም ቦታ የላትም ነገር ግን ደስ ይበላችሁ ስለስሙ መነቀፋችሁ ለበጎ ይሆንላችኋልና፡፡ የጌታ ልጆች በርቱ ድሮም ካህናት ነበሩ በኢየሱስ ላይ ያስፈረዱት እግዚአብሄር ቀን አለው፡፡

 5. Anonymous November 23, 2016 at 7:02 pm Reply

  ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ከ እመቤታችን ከድንግል ማርያም መወለዱን የማያምን የ ድንግል ማርያምን እና የቅዱሳንን ምልጃ የማይቀበል በክርስትና ውስጥ እድል ፈንታ ፅዋ ተርታ የለውም ምክንያቱ ክርስትና ከ ቤተልሔም ኣንስቶ እስከ ቀራንዮ ድረስ ከዝያም ቀጥሎ እስከ ምፅኣት ነው በዚህም ሁሉ ድንግል ማርያም ኣለች ያለ ድንግል ማርያም ክርስቶስ ያለ ክርስቶስ ክርስትና የለም ቢመራችሁም እውነታው ይሄ ነው ተሃድሶዎች ኣትንጫጩ መስራችዋ ክርስቶስ ነው እርሱ ደግሞ ሲሰራ እንከን የለበትም ተዋህዶ ኣትታደስም ይልቁንስ ራሳችሁን ኣድሱ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: