የሳተላይት ቴሌቭዥናችን(EOTC TV): አስተማሪና ተመራጭ፥ የካህናት፣ የምእመናንና የሀገር ድምፅ ይኾን ዘንድ…

eotc-tv-test-transmission
ባለፈው ዓመት ሰኔ አጋማሽ፣ የሙከራ ሥርጭቱን በይፋ የጀመረው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሳተላይት ቴሌቭዥን አራተኛ ወሩን አስቆጥሯል፡፡ መደበኛ ሥርጭቱን ለመጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ኹኔታዎችን በማመቻቸት ላይ መኾኑን በቅርቡ የገለጸው የብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ፤ የሰው ኃይል ቅጥርና የዕቃ ግዥ ተግባራትን በማጠናቀቅ ላይ እንዳለ አስታውቋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ድምፅዋን የምታሰማበት የራሷ ሚዲያ ባለቤት እንድትሆን ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየ ከመሆኑ አኳያ፣ የሙከራ ሥርጭቱ ይፋ መኾን አገልጋዮችንና ምእመናንን በእጅጉ አስደስቷል፡፡ ይኹንና፣ አራት ወራትን ያስቆጠረውን የሙከራ ስርጭት የገመገሙ፣ ተክለ ኢየሱስ ሀብቴ የተባሉ የቤተ ክህነቱ ባልደረባ፣ “ሚዲያው ከጅምሩ፣ በይዘቱና በአቀራረቡ የጥንታዊትዋና ሐዋርያዊትዋ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሚዲያ ለመኾን ተስኖታል፤” ሲሉ ዛሬ ለኅትመት በዋለው ቁም ነገር መጽሔት ተችተዋል፡፡

ጸሐፊው፥ ለትችታቸው መነሻ ያደረጉት፣ የብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ የቦርድና የሥራ አመራር አባላት አደረጃጀት ሞያዊ አግባብነት፣ የሥርጭት ክፍያውን ተመጣጣኝነትና በሙከራ ሥርጭቱም ወቅት ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንፃር ጥንቃቄና እርማት አልተደረገባቸውም ያሏቸውን ጉዳዮች ነው፡፡ በአራት ወራት የሙከራ ሥርጭት ጉዞው “ያሳየው አፈጻጸሙ ደካማ ነው፤”  ሲሉ ጠንከር ያለ ሒስ ሰንዝረዋል፤ ጸሐፊው፡፡ “የቤተ ክርስቲያኒቱን ልሳን ከመዝጋት ያነሰ ተደርጎ ሊታይ አይገባውም፤”  በማለትም አደጋውን ያመለክታሉ፡፡

ተዝቆ ከማያልቅ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብት ጋር ብዙ ሊቃውንት ያለፉባትና ያሏት ቤተ ክርስቲያን ሚዲያ፣ “ሀብታም፣ ማራኪ፣ አስተማሪና ገላጭ” የመሆን ከፍተኛ ዕድሎች እንዳሉት ገልጸው፤ ቦርዱና ሥራ አመራሩ፥ ሚዲያው፣ የካህናት፣ የምእመናንና የሕዝብ መሆኑን በተቆርቋሪነት ለማሳየት መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ይመክራሉ፡፡ ስለዚህም፣ ጣቢያው “በሕዝብ ዘንድ ፈጽሞ ሳይረሳና ትልልቅ ስሕተቶችን ሳይሠራ” አራሚ ርምጃ መውሰድ የመንበረ ፓትርያርኩ ሓላፊዎች ወቅታዊ ግዴታም እንደሆነም አሳስበዋል፡፡

የተወሰኑ የጸሐፊው ትችቶች፣ ጣቢያው በሙከራ ሥርጭት ላይ የሚገኝ ከመኾኑ አንፃር፣ ከጊዜው የቀደሙ የሚመስሉ ሐሳቦች የሚታይበት ከመሆኑ በቀር፤ አስተማሪ፣ መካሪና መረጃ ሰጪ መኾን በሚገባው ሕዝባዊ የሚዲያ አገልግሎታችን ዙሪያ ገንቢና ጠቋሚ የዐደባባይ ውይይቶችን ለማበረታታት አስተዋፅኦ ይኖረዋል በሚል እምነት እንደሚከተለው ተስተናግዷል፡፡


የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን የሳተላይት ቴሌቭዥን: ክፍያው እጅግ ውድ ነው፤ ተወዳዳሪና አስተማሪ የቤተ ክርስቲያን ድምፅ ለመሆን ግን እየተሳነው ነው

ተክለ ኢየሱስ ሀብቴ
/ከቤተ ክህነት/

(ቁም ነገር መጽሔት፤ 15ኛ ዓመት ቅጽ 15 ቄጥር 273፤ ኅዳር 2009 ዓ.ም.)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሳተላይት ቴሌቭዥን ለሕዝብ መቅረብ ከጀመረ ወደ አራተኛ ወሩ እየተሸጋገረ ነው፡፡ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናት፣ ምእመናንና ዜጎች በተከፈተው የሳተላይት ቴሌቭዥን እንደሚደሰቱ ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም፣ ምእመናን ከልጆቻቸው ጋር ቁጭ ብለው የሚመለከቱት የቤተ ክርስቲያን ሚዲያ፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ አንድ ቀን እውን ይሆናል፤ በማለት በተስፋ ይጠብቁ ነበርና፡፡

ይሁን እንጂ፣ ሚዲያው ከጅምሩ፣ በይዘቱና በአቀራረቡ የዚያች ታላቅ፣ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሚዲያ ለመኾን እንደተሳነው፣ በየዕለቱ በሚያሠራጫቸው ነገሮች እየታየ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሳተላይት ቴሌቭዥን፣ ለምን ብቃትና ጥራት አነሰው? ለዚህስ ተጠያቂው ማነው? መፍትሔውስ ምንድን ነው? ብለን በዚህች ጽሑፍ ለመጠየቅና ለማሳሰብ ምክንያት ኾነን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቴሌቭዥን ጣቢያ፥ በጣም ያማረ፣ ሙሉ ይዘት ያለው፣ እጅግ አስተማሪ መሆን የሚያስችሉት ብዙ ሀብቶችና ሊቃውንት እያሉት፣ እንዲህ ጭልምልም ያለ እንዲሆን የፈረደበት ማን ነው?… ካህናት፣ ምእመናንና ዜጎች ከሚዲያው የመማር ዕድላቸውን የሚያቀጭጭ ክፉ አሳቢ ማን ነው?… ገና ከጅምሩ አድማጭ ተመልካች እንዲያጣ የማድረጉ አያያዝ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልሳን ከመዝጋት የማይተናነስ ነውና፣ ቀናዒ የሆነ ሁሉ ሊጠይቅና ሊናገር ይገባል፡፡ ለመሆኑ፣ የቴሌቭዥን ጣቢያው የአራት ወራት የሙከራ ስርጭት ቆይታ ምን ይመስላል?

ቦርዱን በተመለከተ

የቤተ ክርስቲያኒቱ ሚዲያ በቦርድ ይመራል፡፡ ቦርዱ ሰባት አባላት አሉት፡፡ ከእኒህም፣ የሚዲያ ዕውቀት ያለው አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡ ሌሎቹ፣ የቤተ ክርስቲያንና ከሚዲያ ጋር ግንኙነት የሌለው ሞያ ያላቸው እንደሆኑ ይታያል፡፡ ስለዚህም፣ የሚዲያው ቦርድ ጠንካራ ለመሆን እንዳይችል ተደርጓል፡፡ ወደዚህ ድምዳሜ የሚወስደን አመክንዮ ወይም ማረጋገጫ፣ ጣቢያው እስከ አሁን ያሳየው ደካማ አፈጻጸምና ቅድመ ዝግጅት ነው፡፡

በጀትን በተመለከተ

eotc-tv-opinion-on-the-test-transmission
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን ጣቢያ፣ ከአንድ የእስራኤል ኩባንያ ጋር በተደረገ ስምምነት ወደ ሳተላይት የደረሰ ሲሆን፤ በወር ከ30ሺሕ ዶላር በላይ እየተከፈለ መሆኑም በሚዲያ ለሕዝብ ይፋ ሆኗል፡፡ በዓመት፣ 12 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት የተመደበለት የብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ፣ የሥርጭቱ ወርኃዊ ክፍያ እጅግ ውድ መሆኑ ሌላው አስገራሚ ነገር ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለኩባንያው ከምትፈጽመው በግማሽ የቀነሰ የሳተላይት ኪራይ ክፍያ አማራጭ አለ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን እየተከፈቱ ያሉት የመዝናኛ የሳተላይት ጣቢያዎች፤ ከ12ሺሕ እስከ 14ሺሕ ዶላር በሆነ ዋጋ አገልግሎቱን እያገኙ እንደ ሆነ ማወቁ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

እጅግ ውድ ሊባል በሚችል ዋጋ የተገዛው የቤተ ክርስቲያናችን የሳተላይት የአየር ጊዜ እንዲሁ እየባከነ፤ ጣቢያው፣ ገና ከጅምሩ ሳቢነትና ቁምነገር የለውም እየተባለ ተመልካች እያጣ ነው፤ ቤተ ክርስቲያንም በሁለት መንገድ እንድትጎዳ እየተደረገ ነው፡፡

የሥራ አመራሩን በተመለከተ

ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሳተላይት ቴሌቭዥን፣ የዕለት ተዕለት ሥራ እንዲመሩ የተመደቡት ሰዎች፤ ከሚዲያ አንፃር ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ እንዲሁም የሚዲያ ውድድሩ እያየለ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የተመረጡ አይደሉም፡፡ ምደባው፣ የሃይማኖትንና የሚዲያ ዕውቀትን አጣጥሞ የመያዝ መርሕን እስካላገናዘበ ድረስ በተቀጣሪዎቹ መፍረድ አይቻል ይሆናል፡፡

እስከ አሁን ባለው ጉዞ፣ ተገቢ ሞያተኞችን ይዞ ትክክለኛውን የሚዲያ አወቃቀር ለመዘርጋት ልግመኛና ፈቃደኛ ያለመሆን ይታያል፡፡ ሥራ አመራሩ፣ ከዚህ እስራት ካልወጣ፣ የሿሚዎቹ ሎሌ እንጂ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሚዲያ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ከተጠያቂነትና ከተወቃሽነት አይድንም፡፡

የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ከመጠበቅ አንፃር

እስከ አሁን በሙከራ ስርጭት ከተላለፉት ዝግጅቶች፣ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያልሆኑ ነገሮች ሳንመለከት አልቀረንም፡፡ የተወሰኑትን ለመግለጽ፡- ሴቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ራሳቸውን ይሸፍኑ፤ የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ሥርዓትና ትውፊት አለን፡፡ ይህን የሚተላለፉ ምስሎች በተደጋጋሚ ይቀርባሉ፡፡ እንስት ምእመናን፣ ፀጉራቸውን ሳይሸፋፈኑና የቤተ ክርስቲያንን አለባበስ ሳይከተሉ ዐውደ ምሕረት ላይ ሳይቀር መታየታቸው፥ ትውፊቱን የሚያውቅ አባት የለም ወይ፣ ያሰኛል፡፡ ዕውቀቱና የባለቤትነት ስሜቱ ካለ በቀላሉ ከምስሉ ላይ ሊታረሙ ይችሉ ነበር፡፡

የአባቶችን ክብር ከመጠበቅ አንፃር

በተላለፉት የክምችት ምስሎች፣ የቅዱሳን ፓትርያርኮችን፣ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትንና የካህናቱን ክብር ሊጎዱ የሚችሉና ለሚዲያ መቅረብ የሌለባቸው የአካልና የድምፅ ይዘቶች፣ ተገቢው የአርትዖት ሥራ ሳይሠራባቸው በተደጋጋሚ ተሠራጭተዋል፡፡ በቀረፃ ወቅት አባቶች ሳይዘጋጁ ያደረጓቸው አካላዊ እንቅስቃሴዎችና ንግግሮች፣ በቅንብር ወቅት በትኩረት አርትዖት ሊሠራባቸው ይገባ ነበር፡፡

ባልተገባ ጊዜ ሥርዓተ ቅዳሴ ማቅረብ

በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ምእመናን፣ ትችትና አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣል፡፡ ምእመናን፣ ከጸሎተ ቅዳሴ ተመልሰው ቤታቸው ገብተው ሲመገቡ ጣቢያው ቅዳሴ ይጀምራል፡፡ የሥርዓተ አምልኳቸው ዐቢይ አገልግሎት የሆነው ጸሎተ ቅዳሴ በሚዲያ ሲቀርብ፣ ቁጭ ብለውና እየተመገቡ ማየት ይከብዳቸዋል፡፡ እንዴት እንዲህ ያደርጋሉ ብለው መጠየቃቸውም አይቀርም፡፡ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በአንድ ቀን ሁለት ጊዜ ቅዳሴ የለም፡፡

በዚህ ዓይነቱ ሥርጭት ወቅት፣ ምእመናን፣ ጣቢያውን መቀየር ወይም ቴሌቭዥናቸውን መዝጋት እንደሚመርጡ ይነገራል፡፡ በአመራሩ በኩል ምእመናንን ምን ያህል እንደሚያውክ ለመገንዘብ አለመቻሉ፣ በዕቅድና በሓላፊነት ስሜት እየተሠራ አለመሆኑን ያሳያል፡፡

ባዕድ ድምፆችና ተገቢ ያልሆኑ አለባበሶች

የቤተ ክርስቲያን ያልሆኑ ድምፆች፣ ከምስል ክምችቱ ላይ እንደተገኙ ማስተካከያ ሳይደረግባቸው ይተላለፋሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ቪዲዮዎቹ ሲቀረፁ የገቡ ዓለማዊ ዘፈኖች፣ እርማትና ጥንቃቄ ሳይደረግባቸው አብረው ለምእመናን ይቀርባሉ፡፡ ደንብና መመሪያ ያልተከተሉ አልባሳት መታየታቸውም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ማጓደል ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡

በወቅታዊና አገራዊ ሁኔታ አራሚ አስተዋፅኦ አለማድረግ

በአገራችን በታየው መልካም ያልሆነና ድንገተኛ አጋጣሚ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚዲያ ታላቅ አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበት ነበር፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ግንባር ቀደም ድርሻ ሊኖረው ይገባ ነበር፡፡ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ላይ፣ ጉዳዬ ብሎ መሥራት ሲገባው ሰምቶ እንዳልሰማ፣ አይቶ እንዳላየ አልፎታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሚዲያ፣ ሕዝብን ከማጽናናትና ስለ ሰላም ከማስተማር ውጭ ምን ዓላማ አለውና ነው፣ በዝምታ ያለፈው? ቦርዱና ሥራ አመራሩ፥ ሚዲያው፣ የካህናት፣ የምእመናንና የሕዝብ መሆኑን በተቆርቋሪነት ካላሳየና ካልተንቀሳቀሰ፣ ያን ሁሉ ገንዘብ መክፈል የድኃዎቹን ካህናት የዕለት ጉርሻ ከመንጠቅ ያለፈ ፋይዳ ይኖረዋልን?

ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ እጅግ ብዙ ሊቃውንት ያለፉባትና ያሏት በመሆንዋ ተዝቆ የማያልቅ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ ይህን ያህል ሀብት ያላት ቤተ ክርስቲያን፣ ሚዲያዋ፡- ሀብታም፣ ማራኪ፣ አስተማሪና ገላጭ መሆን ይኖርበታል፡፡ እየሆነ ግን አይደለም፡፡

በቦርድ አመራር ያሉ ግለሰቦች፣ ሚዲያውን እንደ ግል ንብረት የመያዝ አካሔዳቸውን ሊያርሙ ይገባል፡፡ ከሃይማኖትና ከሀገር በላይ ያለመሆናቸውን ነግሮ ማስተካከል፥ የቋሚ ሲኖዶሱ፣ የፓትርያርኩ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ሓላፊነት ነው፡፡

በመሆኑም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የቴሌቭዥን ጣቢያ በሕዝብ ዘንድ ፈጽሞ ሳይረሳና ትልልቅ ስሕተቶችን ሳይሠራ አራሚ ርምጃ መውሰድ ወቅታዊ ግዴታ ይሆናል፡፡ ቦርዱና ሥራ አመራሩ፣ ዕንቅፋቶቹ ተወግደውለት አግባብነት ባላቸው ባለሞያዎች ሊጠናከር ይገባል፡፡ በትውውቅ፣ በጥቅማጥቅምና በእከክልኝ ልከክልህ ምክንያት ሓላፊነት ከተዘነጋ፤ ካህናትና ምእመናን ብሎም ዜጎች ከሚያነሡት ተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም፡፡ ፈጣን ምላሽ ያሻል፤ እላለሁ፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: