በአ/አበባ ሀ/ስብከት የአለቆች ዝውውር ተደረገ፤ “ችግራቸው በተጨባጭ ተጣርቶ ከቀረበ በኋላ መመደባቸው ልዩ ያደርገዋል”/ሀገረ ስብከቱ/

 • የአቅም ማነስ፣ የጥቅመኝነት እና የምግባር ጽኑ ችግር እያለባቸው የተመደቡት ይበዛሉ
 • ገድል እንዳይነበብ፤ የወንጌልን ጊዜ ይሻማል” የሚል መመሪያ የሰጡ አለቃ ይገኙበታል
 • ምደባው፣ “ከአድባራቱ ሰላም ይልቅ ለግለሰቦች ቅድሚያ የሰጠ ነው፤” በሚል ተተችቷል
 • ሀገረ ስብከቱ ግን፥ “ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ ለቆየው ተገቢ ምላሽ የተሰጠበት ነው፤” ይላል

*                *                *

 • ዝውውሩን የተቃወሙቱ፣ የፌዴራል እና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩን አነጋግረዋል
 • “የሚያገናኘን የሰላም ጉዳይ ነው” ቢሉም፣ የፋይናንስ ሒደቱ በምዝበራ መናጋቱን ጠቅሰዋል
 • እርምት ለመውሰድ ውስብስብ ቢኾንም “በዝምታ ማየቱ ተገቢ እንዳልኾነ እናምናለን” ብለዋል
 • ከፍተኛ ርምጃ በሚወሰድባቸው አማሳኝ አለቆች ላይ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መኾኑ ተጠቁሟል

*                *                *

eotc-aa-diosces-head-office

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት

ከሙስና፣ ከመልካም አስተዳደርና ከኑፋቄ ጋር በተያያዙ ጥያቄዎችና አለመግባባቶች ዘወትር እንደተጨናነቀ በሚገኘው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ ከደርዘን የሚልቁ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ዝውውር መደረጉ ተገለጸ፡፡

ዝውውሩ የተካሔደው፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ፣ ኅዳር 2 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በተካሔደው የቋሚ ሲኖዶስ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ፣ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ቀርቦ ከታየና ከተወሰነ በኋላ ነው፡፡

አስተዳዳሪዎቹ የሚዘዋወሩበት ምክንያት በዝርዝር መታየቱን የጠቀሱት የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች፤ “ከጥቂቶቹ በስተቀር የሚበዙት ጽኑ ችግር ያለባቸውና ይህም በዝርዝር ተብራርቶ በሪፖርት ቀርቦ በቋሚ ሲኖዶሱ ከተመረመረ በኋላ የተወሰነ መኾኑ ከወትሮው የተለየ ያደርገዋል፤” ብለዋል፡፡

በዝውውሩ የተካተቱት 13 አለቆች ሲኾኑ፣ በአለመግባባት የታወከውን አገልጋይና ምእመን ያረጋጋሉ በሚል ታምኖባቸው የተዛወሩት ኹለት ብቻ መኾናቸውንና የተቀሩት ግን፣ በአግባቡ መምራት ያለመቻል፤ የአቅም ማነስ፣ የጥቅመኝነትና የሥነ ምግባር የመሳሰሉት ጽኑ ችግሮች እንዳሉባቸው በተጨባጭ መጣራቱ ተገልጧል፡፡

“በቦታቸው ላይ ሰላም አድርገው መምራት አልቻሉም፤ በሚፈጥሩት ውዝግብ ምክንያት ወደ ደብራቸው ሔደው ለማገልገል እስከ መቸገር የደረሱ ናቸው፤ እነርሱን አዘዋውረን ለማሠራት ተገደናል፤” ይላሉ አንድ የጽ/ቤቱ ሓላፊ፡፡


ዝውውር የተደረገባቸው አድባራትና ገዳማት ዝርዝር

 • የደብረ ሰላም ሰሚት መድኃኔዓለም ወደ ብሔረ ጽጌ ማርያም
 • የብሔረ ጽጌ ማርያም ወደ ደብረ ሰላም ቅ/እስጢፋኖስ
 • የደብረ ሰላም ቅ/እስጢፋኖስ ወደ ደብረ ይባቤ ቅ/ያሬድ
 • የደብረ ይባቤ ቅ/ያሬድ ወደ ደብረ ሰላም ሰሚት መድኃኔዓለም
 • የላፍቶ ቅ/ሚካኤል ወደ ቡልቡላ መድኃኔዓለም
 • የቡልቡላ መድኃኔዓለም ወደ ጠሮ ቅድስት ሥላሴ
 • የጠሮ ቅድስት ሥላሴ ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅ/ጳውሎስ ገዳም
 • የሰዋስወ ብርሃን ቅ/ጳውሎስ ገዳም ወደ ላፍቶ ቅ/ሚካኤል
 • የኮንጎ ሰፈር ኪዳነ ምሕረት ወደ ቃሉ ተራራ ጻድቁ አቡነ ሀብተ ማርያም
 • የቃሉ ተራራ ጻድቁ አቡነ ሀብተ ማርያም ወደ ኮተቤ ቅ/ዑራኤል
 • የኮተቤ ቅ/ዑራኤል ወደ ኮንጎ ሰፈር ኪዳነ ምሕረት
 • የካራ ቆሬ መዝገበ ምሕረት ቅ/ፋኑኤል ወደ ጉለሌ ኪዳነ ምሕረት
 • የጉለሌ ኪዳነ ምሕረት ወደ ካራ ቆሬ መዝገበ ምሕረት ቅ/ፋኑኤል

በተለይም፣ በመዝገበ ምሕረት ካራ ቆሬ ፋኑኤል፣ በሰሚት ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም፣ በብሔረ ጽጌ ማርያምና በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ አብያተ ክርስቲያናት በተፈጠሩ ውዝግቦች፤ ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት አባላት ለእስርና እንግልት እየተዳረጉ ለረጅም ጊዜ አቤቱታዎች ሲያቀርቡባቸው የቆዩባቸው እንደነበር ጠቅሰው፤ አለቆቹን በማዘዋወር አገልጋዩንና ምእመናኑን ከሥቃይ ለማሳረፍና ትክክለኛ ምላሽ በመስጠት አጥቢያዎቹን ለማረጋጋት የታሰበበት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

ለ35ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቓላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቀረበው የሀገረ ስብከቱ ሪፖርት፤ በአድባራትና በገዳማት፣ በአስተዳደር ሠራተኞችና በሰበካ ጉባኤ አባላት እንዲኹም በሰንበት ት/ቤቶች መካከል የአለመግባባቶች መንሥኤ፣ “ድርሻን ባለማወቅ” እንደኾነ ተገልጧል፡፡

ይኹን እንጂ፣ ከለየለት ጥቅመኝነታቸውና ከአማሳኝነታቸው ባሻገር፣ በእምነት አቋማቸውና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አክብሮ በማስከበር ረገድ መሠረታዊ ጥያቄ የተነሣባቸው እንደ ብሔረ ጽጌው ነአኵቶ ለአብ አያሌው ያሉቱ፤ ገድል እንዳይነበብ፤ የወንጌልን ጊዜ ይሻማል የሚል መመሪያ ለስብከተ ወንጌል ሓላፊ በጽሑፍ የሚሰጡና ዐውደ ምሕረቱን የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኞች መፈንጫ ያደረጉ፤ እየጠጡ አንግተው መቅደስ ገብተን ካልቀደስን የሚሉ፤ በጉልበት ተደፋፍረው ከገቡ በኋላ አስከፊ መተላለፍ የሚፈጽሙና ክብረ ክህነትን የሚያዋርዱ መኾናቸው፣ “ድርሻን ያለማወቅ” በሚል ብቻ በዋዛ የሚታለፍ አያደርገውም፡፡ ሀገረ ስብከቱ፣ ስለእነኝኽ በደሎች ተጨባጭ ማስረጃዎች አሉት፤ ተመጣጣኝ ርምጃ በወቅቱ አለመውሰዱ ሳያንስ በዝውውር መመደቡ ጥያቄ የሚያስነሣ ነው፡፡

ይህም ኾኖ፣ አንዳንድ አለቆች፣ ያለደረጃችን ነው የተመደብነው በሚል ዝውውሩን በመቃወም ለፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ክሥና ስሞታ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ ለዓመታት ጉልተኛ ኾነው ሕገ ወጥ ሀብት ሲያካብቱ የኖሩና በዝውውሩ ጥቅማቸው የተቋረጠባቸው አለቆች ያስተባበሩበት ሲኾን በጸሐፊ፣ በቁጥጥርና በክፍለ ከተማ ሥራ አስኪያጅነት የሚሠሩ ጥቂት የአድባራት የሥራ ሓላፊዎችም እንዳሉበት ተሰምቷል፡፡

“150ሺሕ ካልከፈልክ ተብዬ ነው እስጢፋኖስ የተወረወርኩት” በሚል ምደባቸውን ተቃወመዋል የተባሉት ነአኵቶ ለአብ አያሌውና ሌሎችም የስሞታው አሰሚዎች፤ የዝውውር አሠራርን ጨምሮ ከሰው ኃይል አስተዳደር አኳያ በሀገረ ስብከቱ ያለው አያያዝ፣ ተረጋግቶ ለመሥራትና ለአጠቃላይ የከተማው ሰላም ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ለሚኒስትሩ ማስረዳታቸው ተመልክቷል፡፡

ato-kassa-teklebirhan

የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን

የሚኒስትሩ ምላሽ፣ “መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፤” የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ መነሻ ማድረጉን የተናገሩ የውይይቱ ተሳታፊ፣ አቶ ካሳ፣ “እኛ የሰላም ጉዳይ ነው የሚያገናኘን፤ ስለ ሰላም ደግሞ ከዚኽ በፊት ሲኖዶስ መካከል ክፍተት ተፈጥሮ ሔደን ሰላም አድርገን ችግሮችን ለመፍታት ሞክረናል፤” ማለታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይም ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች ለመፍታት፣ “ረጅም ትልምና ፕሮግራም” መያዙን እንደሚያውቁና በሒደትም እየተቀረፉ እንደሚሔዱ እምነታቸውን ለተወያዮቹ ገልጸውላቸዋል፤ ብለዋል፡፡

ባለፈው ወር መጨረሻ ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ጋር በተገናኙበት አጋጣሚ፣ ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ በሰፊው ማውራታቸውን አቶ ካሳ አውስተዋል፡፡ ከሥራቸው ተፈናቅለው የነበሩ መመደባቸውንና አኹንም በጥናት ብዙ ሥራ ለመሥራት መታቀዱን ሥራ አስኪያጁ እንደነገሯቸው የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ “በሰላሙ ዙሪያ ላይ ላናግረው እችላለኹ፡፡ ቅዱስ አባታችንም ላወራቸው እችላለኹ፤ ሰላም ኾናችሁ ሥራችኹን ማከናወን እንዳለባችሁ ነው የማስበው፤” የሚል ምላሽ መስጠታቸው ተሰምቷል፡፡

የሰው ኃይል አስተዳደርን በተመለከተ፣ እናት አባት የሞቱባቸው የሠራተኞች ልጆች ሥራ እንዲያገኙ ቅድሚያ መሰጠቱን የሚገልጸው የሀገረ ስብከቱ የ2008 ዓ.ም. ሪፖርት፤ በበጀት ዓመቱ ለ1ሺሕ90 ያኽል ሠራተኞች፡- ቅጥር፣ ዝውውር፣ ዕድገትና የቋሚነት ሠራተኝነት ማጽደቂያ እንዲሰጣቸው መደረጉን አስፍሯል፡፡ ኾኖም፣ የባለጉዳዮች መብዛትና መጠነ ሰፊ የኾነ ያልተገደበ ፍላጎት እንደሚንጸባረቅበት አትቷል፡፡ ይህም፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ከማገዝ ይልቅ በጊዜውም ያለጊዜውም ሀገረ ስብከቱን በማጨናነቅ ለሌላ ሥራ የሚውለውን ሰዓትና ጊዜ በመሻማት ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረበት እንደኾነ ያማርራል፡፡

ሥራ ፈላጊዎችን በግልጽ ማስታወቂያ አወዳድሮ እንደየውጤታቸውና እንደየሞያቸው መመደብ፤ አለመግባባት በሚፈጠርባቸው አድባራት አጣሪ ልኮ መንሥኤውን በመለየት ኹሉም ድርሻውን ዐውቆ እንዲሠራ በማድረግ ችግሩን ለማቃለል ሞክሯል፡፡ በተያዘው የ2009 ዓ.ም. በጀት ዓመትም፤ ከግንዛቤ ማስጨበጫ ጀምሮ የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሞችን የማዘጋጀትና በሰው ኃይል አስተዳደሩም የመመዘኛ መስፈርት በማውጣት በአግባቡ እንዲከናወን የማድረግ ዕቅዶችን መያዙን አስታውቋል፡፡


 • የባለጉዳይ መስተንግዶ ፕሮግራም በማውጣት የተቀላጠፈ ማድረግ፤

 • የሚያስተዳድሩትን ደብር በሰላም እየመሩ ያሉትን አስተዳዳሪዎች ማበረታታትና ሌሎችም ከእነርሱ እንዲማሩ፣ የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም ማዘጋጀት፤
 • ለቅጥር፣ ለዝውውር እና የደረጃ ዕድገት መመዘኛ መስፈርት በማውጣት በአግባቡ እንዲከናወን ማድረግ፤
 • መልካም አስተዳደር፣ ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እንዲሰፍን ተግቶ መሥራት ወዘተ… የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ይህም ኾኖ ለዓመታት ሥር የሰደደውና መንፈሳዊ ሓላፊነት በማይሰማቸው እኵያነ ምግባር የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ዘወትር ጽ/ቤቱን የሚያጨናንቀው የፍትሕ ጥያቄ በዚኽ ብቻ የማይመለስና ከዚኽም በላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚረጋገጥበት መዋቅራዊ መፍትሔ እንደሚሻ ብዙዎች ያምናሉ፡፡

በሰሞኑም ኾነ በቀደመው የተደረጉ የአድባራት ሓላፊዎች ዝውውር፣ “ለአጥቢያዎች ሰላምና ማረጋጋት” የሚል መነሻ ቢኖራቸውም፣ ገደብ የለሽ ፍላጎትንና ጥቅመኝነትን(አንቃዥነትና አማሳኝነት) የሚገራ የተቋማዊ ለውጥ አሠራር በቦታው እስከሌለ ድረስ ትርጉም የሚኖረው አይኾንም፡፡ በጥፋታቸው የሚጠየቁበትና የሚታረሙበት አካሔድ ባልተበጀበት ኹኔታ እየተዛወሩ ቢመደቡም የሚጎዱት አሐቲ ቤተ ክርስቲያንን ነው፡፡ ዝውውሩ፣ “ከአድባራቱ ሰላም ይልቅ ለግለሰቦቹ ያደላ ነው፤” በሚል የሚተቸውም በዚኽ ምክንያት ነው፤ ከተዘዋወሩ በኋላ ያለአንዳች ተጠያቂነት፣ ስልታቸውን እየቀያየሩ የአድባራቱን የፋይናንስ ሥርዓት በሚያናጋ አኳኋን ምዝበራቸውን ከቀጠሉት ከነኃይሌ ኣብርሃ በላይ ማረጋገጫ አይኖርምና፡፡

በርግጥ ሀገረ ስብከቱ፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን የሒሳብ አሠራር በመከተል፣ የገዳማትና የአድባራት የሀብትና የንብረት ፍሰት ጤናማ ይኾን ዘንድ፣ ለማንኛውም የፋይናንስ እንቅስቃሴ ደንብና መመሪያ አዘጋጅቶ ሓላፊነቱን እየተወጣ እንዳለ ጠቅሷል፡፡ በዚኽም መሠረት፣ ሕጋዊ ተቀባይነት ያለውን የጥንድ ሒሳብ አክሩዋል አመዘጋገብ መርሕን(ኮምፒዩተራይዝድ ፒችትሪ አካውንቲንግ) በመከተል፣ ወጭን፣ ጥራትንና ጊዜን ቆጣቢ አሠራር ገቢራዊ አድርጌአለኹ፤ ብሏል፡፡

የጽ/ቤቱን የሒሳብ አሠራር ዘመናዊ ከማድረግ ጎን ለጎን፣ የተመረጡ አድባራትንና ገዳማትን የሒሳብና የቁጥጥር ባለሞያዎችን በማሠልጠን የፋይናንስ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ እንዲኹም የውስጥ ቁጥጥርና የኦዲት መመሪያ እንዲዘጋጅ፤ ልዩ ልዩ ሞዴላሞዴሎችን በማሳተም ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉን ዘርዝሯል፡፡ በዚኽም፣ በ2008 ዓ.ም.፣ በ160 አድባራትና ገዳማት ከተገኘው ከ687 ሚ. ብር በላይ አጠቃላይ ገቢ፡- የሀገረ ስብከቱን የ20 በመቶ ፈሰስ(ከ137 ሚ. ብር በላይ) እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የ65 በመቶ ፈሰስ(ከ96 ሚ. ብር) በላይ በማስገኘት፤ ከ2007 ዓ.ም. የበለጠና ከፍተኛ ዕድገት የታየበት ገቢ መመዝገቡን አስታውቋል፡፡

ይህን የአድባራትና የገዳማት የገንዘብ ፍሰት ተቆጣጥሮና አጠናክሮ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በፋይናንስ አቅሟ ለማጎልበትና ራሷን እንድትችል ለማድረግ፤ የፐርሰንት ገቢው በአግባቡ እንዲሰበሰብ ከአለፈው ዓመት በተሻለ ተግቶ እንደሚሠራ ነው – ሀገረ ስብከቱ የገለጸው፡፡ በተጨማሪም፣ ገደብ የለሽና ተገቢ ባልኾነ ጥቅመኝነታቸው ቃለ ዐዋዲውንና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን፤ የቋሚ ሲኖዶስን ውሳኔና የጠቅላይ ጽ/ቤቱን መመሪያ እየጣሱ በማናለብኝነት ምዝበራቸውን በተለያየ ሽፋን የቀጠሉ የአድባራትና የገዳማት የሥራ ሓላፊዎች በመለየት ጥብቅ ርምጃ ለመውሰድ፣ ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንዳለ ነው፤ የጠቆመው፡፡

የሀገረ ስብከቱን ዝውወር በመቃወም ከአቶ ካሳ ጋር የተወያዩት የአድባራት አለቆች፣ ጸሐፊዎችና ቁጥጥሮችም፣ በሚኒስትሩ ምላሽ የሰሙት አስተያየት መልሰው ያፈሩበትና አንዳንዶቹንም ያስደነገጠ እንደነበረ ነው፤ የተነገረው፡፡ በአድባራት የሥራ ሓላፊዎች ዙሪያ የሚነገሩት የምዝበራና ሕገ ወጥ ሀብት የማካበት ዘመቻ፣ “መደረግና መቀጠል የሌለበት ነገር ነው፤” ያሉት ሚኒስትሩ፣ መነሻውን ተከትሎ ርምጃ ለመውሰድም የተወሳሰበ ኹኔታ እንዳለው አልሸሸጉም፡፡ ይህም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን የፋይናንስ ሒደት እያናጋው መኾኑን እንደሚረዱና፤ መንግሥት ዝም ብሎ ማየቱ ተገቢ እንዳልኾነ ነው፤ እምነታቸውን የገለጹት፡፡


በአድባራት የሥራ ሓላፊዎች ዙሪያ የሚነገሩ የተለያዩ ነገሮች አሉ፤ ባለመኪና ያልኾነ የለም፤ ሙዳይ ምጽዋት ይገለበጣል፤ የሚባሉ ነገሮች አሉ፤ ስም ኹሉ የወጣላቸው አሉ – 60ጎራሽ ምን ጎራሽ የሚባሉ ኹሉ አሉ፤ ይኼ ኹሉ መደረግና መቀጠል የሌለበት ነገር ነው፤ ርምጃ ለመውሰድ ደግሞ ምቹ ነገር የለም፤ ውስብስብ ያለ፣ ከየት ጋራ እንዴት እንደሚነሣ አስቸጋሪ የኾነ ነገር ስላለ ነው፤ መንግሥት፡- የፋይናንስ ሒደቱ ሲናጋ ዝም ብሎ ማየቱ ተገቢ እንዳልኾነ እናምናለን፡፡


 

Advertisements

2 thoughts on “በአ/አበባ ሀ/ስብከት የአለቆች ዝውውር ተደረገ፤ “ችግራቸው በተጨባጭ ተጣርቶ ከቀረበ በኋላ መመደባቸው ልዩ ያደርገዋል”/ሀገረ ስብከቱ/

 1. Anonymous November 17, 2016 at 8:41 pm Reply

  አለባብሶ ቢያርሱ ባአረም ይመለሱ እንዲሉ ይህ ሁሉ የተግማማ ስራ የማለዉ ያለሙያ የተቀጠሩ
  መነኮሣት ነን ባዮች ናቸዉ፡፡ አብዛኝዎቹ ሙሠኞየደብር ፎርጂድ አለቃ ተብየወች ናቸዉ፡፡

  ዋና ዋነወቹ ግን አልተነኩም፡፡ ሽጉዉጥና ክላሽ ከመንግስት ፈርመዉ የወሰዱ የደብር አለቀወች አልተነኩም፡፡ ህዝብና ሽማግሌ ካህናት በማስለቀስ ለይ ይገኝአለን ማህመረ ቅዱሣን መንፈሣዊ ህይወታቸዉን እየተፈተኑ ይገኞል
  ቅዱሣን ፅኑ አበጣይጠፍል

 2. mulugeta ayana November 19, 2016 at 12:23 am Reply

  Thank for ur fast and an open info.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: