ጠቅላይ ቤተ ክህነት: “የፓትርያርኩ ስም ጠፍቷል” በሚል በሰንደቅ ላይ ያቀረበውን ክሥ እንዲያሻሽል ፍ/ቤቱ በየነ

  • ክሥ የማቅረብ መብቱ፣ የተበደልኩ ባዩ እንጂ የሌላ አካል ሊኾን አይችልም
  • ጠቅላይ ጽ/ቤቱ፣ ለፓትርያርኩ የኅሊና ጉዳት ካሳ የመጠየቅ መብት የለውም
  • ፓትርያርኩን የሚመለከተው፣ ከክሡ ወጥቶና ተሻሽሎ እንዲቀርብ አዟል

*               *               *

journalist-firew-and-the-patriarch-aba-mathias
(ሰንደቅ፤ በጋዜጣው ሪፖርተር፤ ረቡዕ፤ ኅዳር 7 ቀን 2009 ዓ.ም.)

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቂርቆስ ምድብ ኹለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ በቀረበ ጹሑፍ፤ “የፓትርያርክ አቡነ ማትያስን ስም አጥፍቷል” በሚል ያቀረበው ክሥ፤ ከሣሽን የማይመለከተው በመኾኑ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጠ።

ፍ/ቤቱ ብይኑን የሰጠው፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ያቀረበውን ክሥ አስመልክቶ፣ በተከሣሽ የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ በኩል የቀረበውን መቃወሚያና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል የተሰጠውን መልስ መርምሮ ትላንት ባዋለው ችሎት ነው።

ከሣሽ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ለክሡ መነሻ የኾነው፣ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተጽፎ በሰንደቅ ጋዜጣ 11ኛ ዓመት ቁጥር 551፤ ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም፤ “ፓትርያርኩ ለኢትዮጵያ የደኅንነት ስጋት፤ ለምእመናን የድህነት ስጋት” በሚል ርእስ የታተመው ጹሑፍ፤ “የፓትያርክ አቡነ ማትያስን ስም ያጠፋ ነው፤” የሚል ይዘት ያለውና ደረሰብኝ ላሉት ጉዳት የ100ሺሕ ብር የኅሊና ጉዳት ካሳ የሚጠይቅ ነው።

ተከሣሽ ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ፣ አምስት ነጥቦች ያሉት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያውን ለፍ/ቤቱ በጹሑፍ እና በቃል ክርክር ያቀረበ ሲኾን፤ ፍ/ቤቱም፣ ጉዳዩን ግራና ቀኝ መርምሮ አንደኛውን መቃወሚያ ማለትም፣ “… ጹሑፉ ስም የሚያጠፋ ነው ቢባል እንኳን ክሥ የማቅረብ መብቱ የተበደልኩ ባዩ እንጂ የሌላ አካል ሊኾን አይችልም። ስም ማጥፋት የሚፈጸመው በግለሰብ ላይ በቀጥታ በመናገር ወይም በመጻፍ ነው። በሕግ ፊት፣ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ እንደ አንድ ሰው ናቸው። በስም መጥፋት ምክንያት የደረሰባቸው የኅሊና ጉዳት ቢኖር ክሥ የማቅረብ መብቱ የራሳቸው ወይም የወከሉት ሰው ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በአቡነ ማትያስ ላይ ለደረሰ የኅሊና ጉዳት ካሳ የመጠየቅ መብት የለውም። በመኾኑም ከሣሽ ክሡ በተመሠረተበት ጉዳይ ላይ ጥቅም የለውም፤ አያገባውም፤…” በሚል ያቀረበውን ተቃውሞ ፍ/ቤቱ ተቀብሎታል።

በዚኽም መሠረት፣ ክሡ በአጠቃላይ ከርእሱ ጀምሮ፣ ፓትርያርኩን የሚመለከት በመኾኑና ጠቅላይ ጽ/ቤቱ እርሳቸውን ተክቶ ክሥ ሊያቀርብ እንደማይችል በመጥቀስ፣ ከክሡ ውስጥ፣ ፓትርያርኩን የሚመለከተው ርእሰ ጉዳይ ወጥቶና ክሡ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ለኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ፍ/ቤቱ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ባቀረበው ክሥ ላይ፣ “ዓመፅ ለማነሣሣት…” በሚል የጠቀሰው፤ ኾኗል ቢባል እንኳን ዐቃቤ ሕግን እንጂ ጠቅላይ ቤተ ክህነትን የሚመለከት ጉዳይ ባለመኾኑ ይህንንም በክሥ ማሻሻያው ላይ ሰርዞ እንዲቀርብ አዝዟል።

በተመሳሳይ ኹኔታ በጋዜጠኛ ፍሬው አበበ ላይ በወንጀል የቀረበው ክሥ፣ ኅዳር 15 ቀን 2009 ዓ.ም የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

Advertisements

2 thoughts on “ጠቅላይ ቤተ ክህነት: “የፓትርያርኩ ስም ጠፍቷል” በሚል በሰንደቅ ላይ ያቀረበውን ክሥ እንዲያሻሽል ፍ/ቤቱ በየነ

  1. Anonymous November 17, 2016 at 6:42 am Reply

    ሰዎች ሲካሰሱ በስብከታቸው ለምን ይሆናል ተስማሙ ይላሉ የራሳቸው ሲሆን ደግሞ ፍርድ ቤት ይቆማሉ ማፈሪያዎች ናቸው፡፡ ስም ጠፋ ከማለት እራስን ማረም አይሻልም፡፡ ሌብነታችሁን ማንም ያውቀዋል፡፡

  2. Anonymous November 17, 2016 at 6:50 am Reply

    መንፈሳዊ አባት ነኝ ካሉ ነገሮችን መተው አቡነ ጳውሎስ ስንት ነገር ነው የተጻፈባቸው ግን ምንም አልከሰሱም ይልቁንም እራሳቸውን አስተካከሉ እንጂ ፡፡ እርሶም እራሶትን ይመርምሩ ያስተካክሉ የወረደ ቦታ ነው የእርሶ ስም ጠፋ ተብሎ ፍርድ ቤት መገኘት፡፡ ቤተክርስቲያን ስንት ንብረት ሲጠፋ ለምን አይከሱም ያጠፉትን፡፡ የማነ ዘመንፈስ ቅዱ ስንት ንብረት ይዞ ነው አሁንም በበፊቱ ቦታው የሚሰራው፡፡ አጠፋ ከቦታው ተነሳ የሚባሉት ሁሉ ሲከሰሱ አናይም ስራችሁን የሚናገረውን ግን ትከሳላችሁ፡፡ መናፍቃን የቤተክርስቲያንን ንዋየ ቅድሳት እንደፈለጋቸው ሲያደርጉ ምነው ከሳችሁ አልማስከበራችሁ፡፡ የቤተክርስቲያን ክብር ይበልጣል ወይስ የግለሰብ ክብር፡፡ ይቅር ባይነትን ከማን እንማር፡፡ አውደምህረት ላይ መጮህ ሳይሆን ሰውን በተግባር አሳዩት፡፡ እውነታን በመክሰስ መደበቅ አይቻልም የኢትዮጵያ ህዝብ ያወቃችሁዋል ግን በሆዱ ይይዛል የቡና ማጣጫ እየሆናችሁ እንደሆነ ልታውቁ ይገባል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: