የኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በአንድ ዓመት እስርና በገንዘብ ተቀጣ፤“እኔ የታሰርኩት ለእውነት ነው!”

ፍ/ቤቱ ይህን ውሳኔ ያሳልፍ እንጂ፡-

  • የፖሊስ ምርመራ፡- “ዘገባው ለክሥ አያበቃም” ሲል ውድቅ አድርጎት የነበረ ነው፤
  • ምዝበራን ያጋለጠው ሰበካ ጉባኤ፣ በአስተዳደሩ ማናለብኝነት ታግዶ የፈረሰበት ነው፤
  • ፓትርያርኩ መመሪያ የሰጡበት የውጭ ኦዲት ምርመራ፣ እስከ አኹን አልተከናወነም፤
  • ከሓላፊዎቹ፣ በድክመት ወደሌሎች አድባራት የተዛወሩና ከሀገር የሸሹም ይገኙበታል፤
  • እኔ የታሰርኩት ለእውነት ነው! የጋዜጣችንም መርሕ ያን ያመለክታል”/ዋና አዘጋጁ/

*               *               *st-marry-vs-ethio-mihdar

(ሰንደቅ፤ በጋዜጣው ሪፖርተር፣ ረቡዕ፣ ኅዳር 07 ቀን 2009 ዓ.ም.)

ኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣና ዋና አዘጋጁ፣
በፓትርያርኩ መቀመጫ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ምርመራ እንዲካሔድ ተጠየቀ
በሚል ርእስ በተሠራው ዜና፣ “የስም ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞብኛል” ሲል የገዳሙ አስተዳደር በመሠረተው ክሥ ጥፋተኛ ኾነው በመገኘታቸው፣ የገንዘብ እና የእስር ቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው፤ የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 6ኛ ወንጀል ችሎት ውሳኔውን የሰጠው፣ ትላንት ማክሰኞ፣ ኅዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው።

በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በኩል፣ በኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣና በዋና አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ ላይ የተመሠረተው የክሥ ዝርዝር እንደሚያስረዳው፤ ተከሣሾቹ፣ በሌላ ሰው መልካም ስም ላይ ከባድ ጉዳት ለማድረስ አስበው፣ ኢትዮ-ምኅዳር በተባለው ጋዜጣ ቅጽ 03 ቁጥር 107፤ ግንቦት 22 ቀን 2007 ዓ.ም በታተመው ዜና፣ የግል ተበዳይ የኾነችውን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ስም አጥፍቷል፤ በሚል ያትታል።

የወንጀል ዝርዝሩ እንደሚያስረዳው፡-

1ኛ) በገዳሙ የሚገኘው ታሪካዊ እንጦንስ ጽላት በአርተፊሻል ተቀይሯል፤ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትና የወርቅ ጽንሐሕ ወጥተዋል፤ የስእለትና የስጦታ ወርቅና የብር ጌጣጌጦች በየመሸታ ቤቱ እየተሸጡ ነው። ይህም ድርጊት የሚፈጸመው በአሳቻ ጊዜ በማውጣት በዕቃ ማጣሪያና ሽያጭ ሰበብ፤ እንዲሁም፣ ሰነዶችን በመደለዝና በማጥፋት እንደኾነ፤ ከበጎ አድራጊዎች ለገዳሟ በስእለት የተበረከቱ ላፕቶፕና ፕሮጀክተር በግለሰቦች ተሽጧል፤ የሚለው ይገኝበታል።

2ኛ) የገዳሟ የንብረት ቁጥጥር ክፍል ሓላፊዎች፣ የውጭ ኦዲት እንዲካሔድ በፓትርያርኩ የተሰጠውን መመሪያ፣ የተለያዩ ስልቶችን በመከተል ተግባራዊ እንዳይኾን እያደረጉ ነው፤ “መልአከ ብሥራት አባ ገብረ ሥላሴ፣ ቄሰ ገበዝ አባ ሳሙኤል ቀለሙና ሌላ ካህንን ጨምሮ÷ ለምንኵስና ሥርዓት በማይስማማ ተግባር አልባሌ ቦታ መገኘት፤ እንዲኹም መነኰሳቱም ልናጠምቅ ነው በሚልና በምግብ አብሳይነት ሰበብ በገዳሙ ቅጽር በሚገኘው ማረፊያ ቤታቸው የሚገቡ ሴቶች እስከ መንፈቀ ሌሊት እየቆዩ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፍ ነገር መፈጸም፤ በየግሮሰሪው ዓምባጓሮ እየፈጠሩ ከአስተናጋጆች ጋር ለድብድብ በመጋበዝ፤ በስካር ወደ ገዳሙ በመግባት ቅጽሩን የአሉባልታና የአድማ መናኸሪያ በማድረግ አስነቅፈዋል፤ ሲል ያትታል።

3ኛ) “የፓትርያርኩ ልዩ ፀሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ለችግሩ መባባስ ተጠያቂ ተደርገዋል” በማለትና ሌሎች በጋዜጣው ላይ የተጠቀሱ የስም ማጥፋት ይዘት ያላቸው ጽሑፎች ማጣራት ሳይደረግባቸው ሰፍረዋል፤ ሲል የክሡ ጽሕፈት ይዘረዝራል።

የገዳሟ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ለመሠረተው ክሥ፣ ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች ለችሎቱ ያቀረበ ሲኾን፤ የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ ለቀረበበት ክሥም በጠበቃው በኃይሉ ተስፋዬ በኩል፤ የመከላከያ ምስክሮችን ከማቅረቡም ባሻገር፤ በአስተዳደራዊ፣ በፋይናንስና በሥነ ምግባር ዙሪያ ለክሡ ምላሽ ይኾናሉ ያላቸውን መከራከሪያዎችና የጽሑፍ ማስረጃዎች ጭምር ለችሎቱ አቅርበዋል።

የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 6ኛ ወንጀል ችሎትም፤ የግራ ቀኙን ክርክር ሲያደምጥ ቆይቶ ውሳኔ አሳልፏል። በዚህም፣ የኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣንና የጋዜጣዋን ዋና አዘጋጅ ጥፋተኛ ናቸው፤ ሲል፣ ጥቅምት 24 ቀን 2009 ዓ.ም ባሳለፈው ብይን ላይ ተመሥርቶ በትላንት ውሎው፣ የሕግ ሰውነት ባለው በኢትዮ-ምኅዳር አሳታሚ፣ ሁለንታ የኅትመትና ማስታወቂያ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ላይ የ10 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ ወስኗል፤ የፍርዱ ግልባጭም ለመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት እንዲላክ ችሎቱ ወስኗል፤ የጋዜጣው ኅትመት የሚቀጥል ከኾነ ቅጣቱን ተከታትሎ እንዲያስፈጽምም ትእዛዝ ሰጥቷል። እንዲሁም፣ በዋና አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ ላይ፣ የአንድ ዓመት እስርና የ1ሺሕ 500 ብር የገንዘብ መቀጫ ወስኖባቸዋል።

getachew-worku

የኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ፤ እውነት ትመነምናለች እንጂ አትጠፋም፤ እውነቱ አንድ ቀን ይወጣል፡፡ ይህ ፍርድ የተፈረደብኝ ጋዜጣውን ለመዝጋት ታቅዶ ነው፡፡”

ከቅጣት ውሳኔው በኋላ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ በችሎቱ ለታደመው ሰው ኹሉ እንዲሰማ አድርጎ፡- “እኔ የታሰርኩት ለእውነት ነው! የጋዜጣችንም መርሕ ያን ያመለክታል፤” ሲል ተደምጧል። ጠበቃው በኃይሉ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ የችሎቱን የቅጣት ውሳኔ እንዳልጠበቁት ገልጸው፤ “በቀጣይ ቀናት ይግባኝ እንጠይቃለን” ብለዋል።

በጋዜጣው ዘገባ በማስረጃነት ከቀረቡት ሰነዶች፣ የሒሳብ አሠራሩን ብልሹነትና ምዝበራን የሚጠቁመውን ሪፖርት ይመልከቱ፤Financial ReportSt Marry Financial report
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: