ልማደኛው አማሳኝ ኃይሌ ኣብርሃ በ“ልማት አባት” ስም ምዝበራውን ቀጥሏል፤ ኹለተኛውን ዶልፊን መኪና በሽልማት ሽፋን ወሰደ

  • ከ700ሺሕ ብር በላይ ያወጣ፣ ቶዮታ – D4D መኪና በሽልማት ወስዷል
  • የቋሚ ሲኖዶስንና የጠቅላይ ጽ/ቤቱን የሽልማት መመሪያ የጣሰ ነው
  • ሀገረ ስብከቱና መንበረ ፓትርያርኩ፣ርምጃ እንደሚወስዱ ተጠቁሟል

*               *               *

haile-dolphin
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅና የአገልጋዮቿን የኑሮ ኹኔታ ለማሻሻል በወጣው ቃለ ዐዋዲ እና ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት፤ ማንኛውም ካህንና ሠራተኛ፡- እንደ የሞያውና እንደየሥራው በሚሰጠው አገልግሎት መጠን፡- ደመወዝ የማግኘት፤ በዘር፣ በቀለም፣ በጎሣ፣ በሀብትና በሌሎችም መንገዶች ከሚፈጸሙ አድሏዊ አሠራሮች ተጠብቆ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ ፊት በእኩልነት የመታየት፤ በጥራትና በታማኝነት በሚያበረክተው የሥራ ውጤት የመመዘንና ብቁ ኾኖ ሲገኝም የደረጃና የደመወዝ ዕድገት የማግኘት ሕጋዊ መብት አለው፡፡

በአንፃሩም፣ አገልጋዩና ሠራተኛው፥ ብቁ የአእምሮና የአካል ጥንካሬ ዝግጅት አድርጎ፡- የተመደበበትን አገልግሎትና ሥራ በትክክል የማከናወን፤ ሥራውን በሚመለከት ጉዳይ ከቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር አካላትና የበላይ ሓላፊዎች የሚተላለፉትን ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች፣ ትእዛዞችና ውሳኔዎች የመቀበልና የማስፈጸም፤ ቤተ ክርስቲያንን ከሚያስነቅፍ ነውርና ሙስናዊ አሠራር ራሱን ነፃ በማድረግ ግብረ ገብነትንና ቅን አገልግሎትን የማሳየት፤ በአጠቃላይ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ በማስጠበቅ ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን በመንፈሳዊነትና በታማኝነት የማገልገል ግዴታ አለበት፡፡

እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ሓላፊና ሠራተኛ፣ ሊሾምና ሊሸለም የሚችለው በሚያደርገው ተግባር ተኰር እንቅስቃሴው መኾኑን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ በቅርቡ በተካሔደው፣ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 35ኛ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል፡፡ ይህም ኹኔታ ሊፈጠር የሚችለው፣ ሥራዎቻችን፣ በቤተ ክርስቲያናችን የመልካም አስተዳደር መመሪያዎች መሠረት፣ የተጠያቂነትና የግልጽነት መርሕን በመከተል የሚመዘኑና የሚገመገሙ ማድረግ ሲቻል እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡ ጉዳዩ፣ ቤተ ክርስቲያንን በትውልዱ ውስጥ የማስቀጠልና ያለማስቀጠል መኾኑን በመጥቀስ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩና ቅዱስ ሲኖዶሱ ልዩ ድጋፍ፣ ትኩረትና ክትትል ሊያደርጉበት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ይህን ቢሉም፣ ጠቅላይ ጽ/ቤታቸውን ጨምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ እና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በየጊዜው የሚተላለፉ መመሪያዎችን፣ በሀገረ ስብከት ይኹን በአጥቢያ ደረጃ ማክበርና ማስከበር ባለመቻሉ፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርሖዎቹን ተፈጻሚነት የሚገዳደሩ ከፍተኛ ጥፋቶች እንደሚፈጸሙ ነው፣ ጥናቶች የሚያሳዩት፡፡ ለአብነት ያኽል፡- የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አንዳንድ አለቆች፣ የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ ጠንቅቀው እንደማያውቁትና ቢያውቁትም እየሠሩበት እንዳልኾነ የገለጸ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የ2007 ዓ.ም. ጥናት፤ እስከ ሀገረ ስብከቱ የዘረጉት የጥቅም ትስስር ኔትወርክና በማጣራትና በምርመራ ወቅት ምዝበራቸውን ለማድበስበስ የሚፈጽሙት እጅ መንሻ ለጥፋቱ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን አረጋግጧል፡፡

ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በ48 የሀገረ ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ላይ፣ የሕንፃዎች፣ የሱቆች፣ የባዶ መሬት፣ የመካነ መቃብር የኪራይ አፈጻጸም እንዲኹም የመኪና ሽልማት አሰጣጥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ያካሔደው ይኸው የናሙና ጥናት፤ የቤተ ክርስቲያንን መብቶችና ጥቅሞች ከማስከበር ይልቅ ለግለሰቦች ሕገ ወጥ ተጠቃሚነት ያደላ ብልሹ አሠራር መስፈኑን አጋልጧል፡፡ የጥናት ሪፖርቱ ነሐሴ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ በታየበት ወቅት፣ በመፍትሔነት የተጠቆሙትን ሐሳቦች በማጽደቅ ውሳኔ አሳልፏል፤ ጠቅላይ ጽ/ቤቱም ውሳኔውን፣ ጳጉሜን 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሀገረ ስብከቱ በጻፈው ደብዳቤ በማሳወቅ በትኩረት ተግባራዊ እንዲደረግ በጥብቅ አስታውቆ ነበር፡፡

የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የጥናት ቡድን ካተኰረባቸውና ቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ካሳለፈባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ ለአለቆች የሚሰጥ የመኪና ሽልማት ይገኝበታል፡፡ ለልማት ዐርበኝነታቸው እና ለበጐ ሥራቸው በሚል የሚሰጠው ይኸው የመኪና ሽልማት፣ የደብሩን ካህናትና ሠራተኞች የወር ደመወዝ በበጎ ፈቃድ በማሰባሰብ እንደሚገዛ ቢገለጽም ይኼ “ለስሙ ነው” ይላል – ጥናቱ፡፡ የገንዘቡ ዋነኛ ምንጮች፣ የደብሩ ቦታ ወይም ሱቅ ወይም ሕንፃ በቅናሽ ዋጋ የተሰጣቸው ባለሀብቶች እንደኾኑም በግልጽ አስቀምጧል፡፡
bisrate-gabriel
የቤተ ክርስቲያን ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል ተደርጎ ዘረፋና ምዝበራ በተጧጧፈበት ደብር የሚሠሩ አለቆች፣ “ምስጉን፣ ጠንካሮች፣ የልማትና የሰላም ዐርበኞች” ተብለው በካህናትና በምእመናን ስም የሚሸለሙበት ኹኔታ፣ ለብልሹ ሥራቸው ከለላን የሚሰጥ በመኾኑ፣ ይህ ዓይነቱ ሥነ ሥርዓት እንዲቆም በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አባታዊ መመሪያ መሰጠቱንና ብፁዕ ሥራ አስኪያጁም መመሪያውን ለሀገረ ስብከቱ አስታውቀው እንደነበር በጥናቱ ሪፖርቱ መግቢያ ተጠቅሷል፡፡
scan0197
በጥናቱም፣ የተሸላሚው አካል ዝርዝር የሥራ አፈጻጸም ተገምግሞ፣ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና በቅዱስ ፓትርያርኩ ተወስኖና ታምኖበት የተከናወነ ሽልማት ነው ወይ? የሽልማቱ ወጪ ከየት የተገኘ ነው? የሚሉት ነጥቦች መፈተሻቸው ተገልጧል፡፡ በጥናቱ ከተሸፈኑትና በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ከተዘረዘሩት 15 አድባራት መካከል፣ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል እና የአራዳ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናት ይገኙበታል፡፡

በኹለቱም አድባራት ከሕንፃ ግንባታና ከልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ መዋቅራዊና ሕጋዊ አሠራርን እየተፃረረ በሚፈጽማቸው፣ ራሱንና ግለሰቦችን በሚጠቅሙ የተጭበረበሩ ውሎች፣ የቤተ ክርስቲያንን መብቶች አሳልፎ በመስጠትና ለዕዳ በመዳረግ ስሙ በጉልሕ የሚነሣው መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ ነው፡፡ ይህም ኾኖ፣ በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል አለቃ በነበረበት ወቅት፣ በአጥቢያው ምእመናን ስም ዶልፊን መኪና ተሸልሟል፡፡

የወቅቱ የሰበካ ጉባኤ አባላት የመኪናውን ሽልማት በተመለከተ የሚያውቁት እንደሌለና የአጥቢያው ምእመናንም ለአለቃው ሽልማት ብለው ያዋጡት ገንዘብ እንዳልነበረ በሥፍራው ለተገኘው አጣሪ ቡድን ተናግረዋል፡፡ የ‘ሽልማት’ መኪናው የተገዛው፣ በአለቃው የጥቅመኝነት አሠራር ባተረፉ ግለሰቦች ኾኖ ሳለ የደብሩ ምእመናን እንደሸለሟቸው ተደርጎ መገለጹ ምእመናኑን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡ በደብሩ ተሠራ የተባለውን ሥራ በማያረጋግጥ፣ ባልተገመገመና በካህናቱም ኾነ በምእመናኑ ይኹንታ ባልተሰጠበት በሐሰት የተበረከተ ሽልማት በመኾኑም እንደሚቃወሙት ዛሬም ድረስ ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡

ይኹንና የካህናቱና የምእመናኑ ተቃውሞና ሐዘን፣ ኃይሌ ኣብርሃን ወደ አራዳ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ተዛውሮ ከመሥራት አላገደውም፡፡ ያለአንዳች ተጠያቂነት በዝውውር ከተመደበበት መስከረም ወር 2006 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ታሪካዊውን ደብር ለከባድ ዕዳና ለብክነት በሚዳረጉና ካህናትንና ሠራተኞችን የሥራ ዋስትና በሚያሳጡ የማናለብኝነት አሠራሮች ቀጥሎባቸው ይገኛል፡፡ የሰበካ ጉባኤውን አካላት እያዳከመና በዛቻ እያሸማቀቀ በኦሆ ባይ ጥቅመኞች በመተካት ያልተገባ አመራር ይሰጣል፤ በባለሞያ አስተያየት ያልተደገፉና መመሪያውን ተከትለው ያልጸደቁ ከፍተኛ ወጪዎችን ያዝዛል፡፡

በደብሩ በሚከናወኑ የኹለ ገብ ሕንፃዎች ግንባታዎች፣ ከተቋራጮች ጋር የሚፈጸሙ ውሎች ሕጋዊ ተቀባይነት የጎደላቸው ናቸው፤ ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የታየበትን የሕንፃ ዲዛይን ክለሳ ከሀገረ ስብከቱ ዕውቅናና ፈቃድ ውጭ፣ የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ በመጣስ በአዲስ ጥናትና ተቆጣጣሪ መሐንዲስ መሪነት እየተካሔደ መኾኑ፣ አግባብነት እንደሌለው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ አጥኚ ቡድን ሪፖርት ያመለክታል፡፡

በገለልተኛ ባለሞያዎች ተገምግሞ ውጤቱ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አማካይነት ለፓትርያርኩ ቀርቦ እስኪጸደቅ ባለበት እንዲቆይ፣ የቀድሞው ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሀገረ ስብከቱ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ኾኖም፣ መመሪያው የውኃ ሽታ ኾኖ ሕገ ወጥነቱ ቀጥሎ ይገኛል፡፡ ከአለቃው ኃይሌ ኣብርሃ ጋር የደብሩ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ በወቅቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የነበሩ በመኾናቸው፣ ጠያቂም አጽዳቂም በመኾን የግልጽነትና የተጠያቂነት መርሖው በኅብረትና በግላጭ የተጣሰበት ዓምባገነናዊነት ነበር የታየው፡፡


ባለፈው ሰኞ፣ ጥቅምት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር አዳራሽ ለኃይሌ ኣብርሃ በተደረገው የመኪና ‘ሽልማት’ ሥነ ሥርዓት ወቅት ይኸው የኹለቱ ያልተቀደሰ ኅብረት ዳግመኛ ታይቷል፡፡ የቤትና የመኪናን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት የሽልማት ሥነ ሥርዓት አስመልክቶ፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በመመሪያ መልክ ለሀገረ ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ያሳለፈው የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ፡- የተሸላሚው የሥራ አፈጻጸም በሀገረ ስብከቱ ተገምግሞና ታምኖበት ለቅዱስ ፓትርያርኩ በቢሮ ደረጃ ቀርቦ ሳይታይና በቋሚ ሲኖዶስ ሳይጸደቅ እንዳይፈጸም የሚል ነበር፡፡ ከሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ከተነሡ በኋላ በደብሩ ዋና ጸሐፊነታቸው የቀጠሉት ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ግን፥ “ሽልማቱ ይገባቸዋል” በማለት ነው በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተናገሩት፡፡

pat-head-to-aa-dio
ከካህናቱና ከሠራተኞቹ አንዳንዶቹም፥ “ብዙ አለቆችን አሳልፈናል፤ በየጊዜው የሰበካ ጉባኤና የልማት ኮሚቴ ስንመርጥ ስናስመርጥ በርካታ የሥራ ዓመታት ባልባሌ ኹኔታ አልፈዋል፤ በሕይወታችንም ለውጥ አልነበረም፤ ጅምር እንጂ ፍጻሜ አናውቅም ነበር፤ ክቡር መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ ከመጡበት ጀምሮ ከጸሐፊው ጋር ባሳዩት እንቅስቃሴ ሰላማችን ተጠበቀ፤ ልማታችን ተፋጠነ፤ ኑሯችን ተሻሻለ፤” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በአስተዳደሩ ላይ ጥያቄና ሒስ የሚሰነዝሩ ወገኖችም፣ “የኛ ሰላም፣ የኛ ጥቅም የማያስደስታቸው ሰዎች የሚፈጥሩት የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው፤ ከዚኽ በፊት ዚአከ ለዚአየ የነበረው የቀረባቸው ናቸው፤” ሲሉ አጣጥለዋል፡፡

“የካህናትና የሠራተኞች ተጠቃሚነት” በሚል ለሽልማቱ አግባብነት የተሰጠው ምስክርነት፣ በዋናነት በደብሩ አስተዳደር የተደረገውን የደመወዝና የአበል ጭማሪ የሚጠቅስ ነው፡፡ በ2007 እና በ2008 ዓ.ም. በተከታታይ በተደረገው የደመወዝና የአበል ጭማሬ፣ “24 ሰዓት ደም የሚተፋው ካህን ተጠቃሚ ኾኗል፤” ተብሏል፡፡ የሕንፃዎቹን የኪራይ ገቢ ቀዳሚ የገንዘብ ምንጭ ማድረጉም ተነግሯል፡፡ ጭማሬው አስድስቷቸዋል የተባሉቱ ካህናት፣ “ለአለቃው ምን ብናደርግ ይሻላል?” በሚል በቄሰ ገበዙ አስተባባሪነት ኮሚቴ አቋቁመው፣ ከእያንዳንዱ ካህን የወር ደመወዝ የሚታሰብ ከ2ሺሕ እስከ 4ሺሕ500 ብር ‘በበጎ ፈቃድ’ ማሰባሰባቸው ተገልጧል፡፡

ከ140 ከማያንሱ ካህናትና ሠራተኞች በአጠቃላይ ብር 550ሺሕ ያኽል የተዋጣ ሲኾን፣ “ቀሪውን አለቃው ራሳቸው ሞልተው ከ700 ሺሕ ብር በላይ በኾነ ወጪ በተለምዶ ዶልፊን እየተባለ የሚጠራውን የ2007 ቶዮታ – D4D መኪና ተሸልመዋል፤ ሰበካ ጉባኤው አምስት ሳንቲም አላወጣም፤” ብለዋል የሥነ ሥርዓቱ ታዳሚ ነበርኩ ያሉ ካህን፡፡ ከሌሎች አድባራት፣ እንደ መልአከ ብርሃናት ዘካርያስ ሐዲስና መልአከ ገነት ጽጌ ከበረ ያሉት አለቆች በተገኙበትና ከብር መቶ ሺሕ ያላነሰ ወጥቶበታል በተባለው ድግስ፣ መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ የመኪናውን ቁልፍና ሊብሬ የደብሩ አንጋፋዎች ከተባሉ ካህናት እጅ መቀበሉ ታውቋል፡፡ “የልማት አባት” በሚል ሽልማቱ እንደሚገባቸው የደብሩ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ማእምራን የማነም መስክረውለታል፤ “በሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነታቸው ወቅት ኃይሌ ኣብርሃም በተሳተፈበት ኮሚቴ የሕክምና ርዳታ በማሰባሰብ ላስተባበሩበት የሰጡት ግብረ መልስ ነው፤” ይላሉ ታዛቢዎች፡፡

የኃይሌ ኣብርሃ – የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ አስተዳደር፣ አደረግኹት ባለው ተከታታይ የደመወዝና የአበል ጭማሬ፣ ደብሩ በወር ከ680 ሺሕ ያላነሰ ወጪ እያደረገ እንደኾነ የተናገሩ ምንጮች፤ “አላማረንም፤ ዛሬስ ይኼን አገኘን፤ ወደፊት ምንድን ነው የምንኾነው?” በማለት መጠየቃቸው አልቀረም፡፡ “ባመት ባመት የሚደረገው ጭማሬ ለሌላ ነው፤ የተጋነነ ነገር እየኾነ ነው፤ ነገ ቤተ ክርስቲያኑ ሊዘጋ ይችላል፤” ሲሉም ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ “በአግባቡና በዕቅድ እንመራ” በሚል ለአስተዳደሩ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ “ድኾች እንዲያድጉ ስለማትፈልጉ ነው፤ ቦታውን መልቀቅ ትችላላችኹ!” የሚል የንቀትና የፌዝ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

ሽልማቱ፣ በበጎ ፈቃድ በተቋቋመ የካህናት ኮሚቴ በተሰበሰበ መዋጮ የተሰጠ ነው፤ ቢባልም፣ “ዋና ጸሐፊውን ጨምሮ ለአለቃው ቅርበት ባላቸው አነሣሽነትና ተጽዕኖ” መፈጸሙን ጠቁመዋል፡፡ ለነገሩ፡- የአጥቢያ ካህናትና ሠራተኞች የደመወዝና የአበል ጭማሬ በሀገረ ስብከቱ ሲደረግ፣ “የምስጋና መዋጮ” በበጎ ፈቃድ እንደተደረገ በማስመስል “የምስጋና ስጦታ” ለሓላፊዎች መስጠት ሕገ ወጥነቱ ቀርቶ ልማድ ኾኗል፡፡ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ባለፈው ዓመት፣ የቦሌ መድኃኔዓለም ካህናትን የጥር ወር ደመወዝ ጭማሬ – 104ሺሕ 90 ብር – ከወቅቱ የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ጋር መቀበላቸው የሚታወስ ነው፡፡ በተመሳሳይ፣ ለኃይሌ ኣብርሃ የመኪና ‘ሽልማት’ አስተባብረዋል ቢባል ሐሰት አይኾንም፡፡

ስለጉዳዩ የተጠየቁት የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች፣ የመኪና ሽልማቱን ፈጽሞ እንደማያውቁት ገልጸዋል፡፡ የደመወዝ ጭማሬ/ዕድገት፣ በቃለ ዓዋዲው የተደነገገ የአገልጋዩና የሠራተኛው መብት እንጂ የአስተዳደሩ ችሮታ አለመኾኑንና ይህም እንደ ደብሩ የገቢ አቅምና ከፈሰስ ውዝፍ ነፃ መኾኑ እየታየ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጥያቄው ቀርቦ በሊቀ ጳጳሱ/በፓትርያርኩ መመሪያ ሲሰጥበት መጽደቅ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ ይኹንና ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ የተጠራቀመ የፈሰስ ውዝፍ ባለበት ደብር፣ የኃይሌ ኣብርሃ ዓምባገነናዊ አስተዳደር የሚያደርገው ተከታታይ የደመወዝና የአበል ጭማሬ፣ ለጊዜው በሕንፃ ገቢ ስም እየተከፈለ ቢኾንም፣ “የፋይናንስ ሥርዓቱን በሚያናጋ መልኩ የኾነ ነገር ነው፤” ብለዋል፡፡

“ለራሱ ዓላማና ስኬት እንጂ ለካህናቱ ዘላቂ ጥቅም በማዘን እየሠራ አለመኾኑን” የገለጹት ሓላፊዎቹ፤ የመኪና ሽልማት ሥነ ሥርዓቱም፣ “በገንዘቤ ኹሉን የማድረግ አቅም አለኝ በሚለው ልማዱ እየተመራ፤ የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ተላልፎ በማን አለብኝነትና ማን ይነካኛል፤ በማለት ያደረገው መኾኑን” ጠቅሰው፤ በቅርቡ ከባድ ዋጋ ሳያስከፍለው እንደማይቀር አስታውቀዋል፡፡

በ1990ዎቹ መጀመሪያ በሀገረ ስብከቱ አድባራት በጥበቃ በኋላም በጥብቅ እልቅና ሥራ የጀመረው ኃይሌ ኣብርሃ፤ ከብሥራተ ገብርኤሉ የዶልፊን ‘ሽልማት’ በኋላ፤ የልዩ ልዩ ገልባጭ፣ መጫኛና መቆፈሪያ ተሸከርካሪዎች እንዲኹም የትራንስፖርትና የቤት መኪኖች ባለቤት በመኾን ራሱን አበልጽጓል፡፡

እንዲኽ፤ የውስን ግለሰቦች ገደብ የለሽ ጥቅመኝነትና አማሳኝነት በሚያጨናንቀው ሀገረ ስብከት፣ ይወሰዳል የተባለው ጥብቅ ርምጃ፡- የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አመራር፣ በሲኖዶሳዊ ይኹን በፓትርያርካዊ መግለጫዎቹ፣ በሙስናና አማሳኝነት ላይ የያዙትን ጽኑ አቋም የሚያስረግጥ፤ አስተማሪና ተመጣጣኝ ሊኾን ይገባል፤ ቤተ ክርስቲያናችን፣ በምታስተዳድራቸው ካህናትና ምእመናን ላይ ባላት የዳኝነት ሥልጣን መሠረት፣ በአስተዳደሯ ውስጥ ለሚፈጸሙ ጉድለቶች፣ በሕጓና በሥርዓቷ፡- ምክርና ተግሣጽ ከመስጠት ጀምሮ እንደ ጥፋቱ መጠን በገንዘብ ወይም በቀኖና የመቅጣት፤ ከሥራ የማዛወር፣ ከሥራ የማገድ፣ ከሥራ የማሰናበትና ከአባልነት የማግለል ሥልጣን አላትና፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: