የቤተ ክርስቲያናችንን ቴሌቭዥን መደበኛ ሥርጭት ለማስጀመር ኹኔታዎች እየተመቻቹ ነው

 • 27 የመርሐ ግብር ዓይነቶችና ይዘታቸው በዝርዝር ተለይተዋል
 • በሦስት ዘርፎች፣ የሰው ኃይል ቅጥር ሒደቱ እየተጠናቀቀ ነው
 • ቅድሚያው፣ለቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና ሠራተኞች ነው”
 • ሞያውን ከነገረ ቤተ ክርስቲያን ያቀናጁትን በበቂ አላፈራንም

*               *               *

 • ከፍተኛ ግዥዎችን አከናዋኝ ኮሚቴው፣ ሥራ ጀምሯል
 • ኦርቶዶክሳውያን ዕቃ አቅራቢዎች እንዲሳተፉ ይፈለጋል
 • በርካታ ስቱዲዮዎችና ክፍሎች ያሉት ቋሚ ቢሮ ተጠይቋል
 • አህጉረ ስብከት የፊልም ክምችቶችን እንዲልኩ ጥሪ ቀርቧል

*               *               *

eotc-tv-test-transmission

በሙከራ ሥርጭት ላይ የሚገኘው፣ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሳተላይት ቴሌቭዥን(EOTC TV) የሚጠቀምበት ሎጎ፣ የቤተ ክርስቲያናችን ዓርማ ነው፡፡

በሙከራ ላይ የሚገኘውን፣ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሳተላይት ቴሌቭዥን (EOTC TV)፣ መደበኛ ሥርጭት ለማስጀመር የሚያስችሉ ኹኔታዎች እየተመቻቹ መኾኑን የአገልግሎት ድርጅቱ ገለጸ፡፡

ድርጅቱ፣ ለመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 35ኛ ዓመታዊ ስብሰባ ባቀረበው የ2008 ዓ.ም. ክንውን ሪፖርቱ እንደገለጸው፤ ላለፉት አራት ወራት በሙከራ የቆየው የቴሌቭዥኑ ሥርጭት መደበኛ በኾነ መልኩ መቀጠል የሚችልበት ኹኔታ እየተመቻቸ ሲኾን፣ “በዐዲሱ በጀት ዓመት የመደበኛ ፕሮግራም ሥርጭቱ ይጀመራል፤” ብሏል፡፡

ባለፈው ዓመት ሰኔ፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን ይፋ የተደረገውን የሙከራ ስርጭት፣ መደበኛ ፕሮግራም ለማስጀመር በመመቻቸት ላይ የሚገኙት ቅድመ ኹኔታዎች፡- የሠራተኛ ቅጥር፣ የውስጥ አደረጃጀትና የዕቃ ግዥ ተግባራት እንደ ኾኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጸደቀለት:- የመተዳደርያ ደንብ፣ የኤዲቶሪያል እና የቴክኒክ መመሪያዎች አገልግሎቱን የሚመራው ድርጅቱ፤ በሦስት ዘርፎች እያከናወነ ያለውን የባለሞያዎች እና የሠራተኞች ቅጥር እያጠናቀቀ ነው፡፡

እስከ አኹን ድረስ፣ በመርሐ ግብር ዝግጅት ዘርፍ የስድስት ጋዜጠኞች(2 የዶኩመንታሪ አዘጋጆች፣ 2 የትምህርት አዘጋጆችና 2 ሪፖርተሮች)፤ በቴክኒክ ዘርፍ የሰባት ባለሞያዎች(3 የምስል እና ድምፅ አቀናባሪዎች፣ 2 የካሜራ ባለሞያዎች ከአንድ ረዳት ጋር፣ አንድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሞያ) እንዲኹም በአስተዳደርና ፋይናንስ ዘርፍ የአምስት ሠራተኞች ቅጥር ሒደት፣ በድርጅቱ ቦርድ በተወከሉት የቅጥርና የምዘና ኮሚቴዎች መከናወኑ ተገልጧል፡፡

ድርጅቱን በዋና ሓላፊነት ከሚመሩት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር፣ አገልግሎቱን በመደበኛነት ለመጀመር ከሚያስፈልገው ኻያ ሦስት አጠቃላይ የሰው ኃይል አንፃር የቅጥሩ ሒደት እየተጠናቀቀ ሲኾን፣ በክንውኑም፣ “ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በውስጥ ማስታወቂያ አማካይነት ላመለከቱ ሠራተኞችና ለቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ቅድሚያ ትኩረት መሰጠቱን” ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

በየዘርፉ ያመለከቱት ተወዳዳሪዎች፣ ካቀረቧቸው የትምህርትና የሥራ ልምድ ማስረጃዎች ባሻገር በቃል እና በተግባር በተሰጡ ፈተናዎች መለየታቸው ታውቋል፡፡ በተለይ የትምህርትና የዶክመንተሪ ዝግጅቶች እንዲኹም የዘገባ ሞያዎች በተካተቱበት በመርሐ ግብር ዝግጅት ዘርፉ፣ በመስፈርት ከተቀመጡት የሥነ መለኰት እና የጋዜጠኝነት ዕውቀትና ክሂል ጋር፣ የአመልካቾችን ሃይማኖታዊ አቋምና ዝንባሌም በቃለ መጠየቅ እና በጽሑፍ ፈተናዎች ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት መደረጉ ተነግሯል፡፡

በመጀመሪያው ዙር በሰነድ ከተመረጡት 56 ጠቅላላ አመልካቾች፥ በጽሑፍ ፈተና፣ በቃለ መጠየቅና በካሜራ ፊት ክዋኔዎች(የድምፅ፣ የዜና ንባብ፣ የትረካና የቀጥታ ሥርጭት) ለጊዜው ስድስቱን ለመለየት ቢቻልም፣ ወደፊት በዘርፉ ተጨማሪ የባለሞያዎች ቁጥር ሊጠየቅ እንደሚችል ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ይኹንና፣ የጋዜጠኝነት ሞያን ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር ያጣጣሙ ብቁ አገልጋዮችን በማዘጋጀት ረገድ መንፈሳውያን ኮሌጆቻችንና የሥልጠና ማእከሎቻችን ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ከቅጥሩ ሒደት መገንዘባቸውን ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡

የመደበኛ ሥርጭቱን መርሐ ግብር በተመለከተ፣ 27 ያኽል የፕሮግራም ዓይነቶች መለየታቸውንና አጠቃላይ የይዘት መሰናዷቸውም ተጠናቆ ለሥራ ዝግጁ ኾኖ እንደሚገኝ በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡ የቦርድ አባላት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሚዲያ ባለሞያዎች በተካተቱበት ጊዜያዊ የይዘትና የዓይነት ዝግጅት ኮሚቴ(program and content development committee) የተሰናዳው የፕሮግራሞቹ ዝርዝር ረቂቅ፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ አጋማሽ በተጠራ የብዙኃን መድረክ ቀርቦ እንደተተቸበት ተጠቅሷል፡፡

“ቤተ ክርስቲያን ምን ዓይነት ሚዲያ ያስፈልጋታል?” በሚል ርእስ፡- የሥነ መለኰት መምህራን፣ ጋዜጠኞችና የአስተዳደር ሓላፊዎች በተሳተፉበት ውይይት ቀርቦ የዳበረው ረቂቁ፣ በድርጅቱ ኤዲቶሪያል ኮሚቴ ከተገመገመና አስፈላጊው እርማት ከተደረገበትም በኋላ ነው፣ ለሥራ ዝግጁ መኾኑ የተገለጸው፡፡ ሰነዱ፥ የፕሮግራሞቹን ስያሜ፣ ይዘት፣ የሥርጭት ዕለትና ሰዓት፣ ታላሚ ተመልካችና ፈጻሚውን አካል ያመለክታል፤ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ይዘገባሉ፤ ትምህርተ ወንጌል ይሰማል፤ በሳምንቱ ዕለታትና በሰንበታት፤ በዕድሜ፣ በሥነ ጥበባት መስኮች ተከፋፍለው የሚቀርቡ ዝግጅቶችም ይኖራሉ፡፡

mmr-daniel-sife-mikael

መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፤ የብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ

በድርጅቱ መተዳደርያ ደንብ መሠረት የተቋቋመው ኤዲቶሪያል ኮሚቴ፣ በቦርዱ ተመርጠው በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ፊርማ የተሠየሙ ሰባት ሊቃውንትና መምህራን ያሉት ሲኾን፤ በዋና ሥራ አስኪያጁ መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ሰብሳቢነት፣ የመገምገምና የማረም(የአርትዖት) ተግባር እንደሚያከናውኑ፣ ሰኔ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የተጻፈላቸው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

ለአገልግሎቱ የሚያስፈልጉ ቋሚና ተንቀሳቃሽ፣ አላቂና አላቂ ያልኾኑ ንብረቶችን ለይቶና ዘርዝሮ በማውጣት በግልጽ ጫረታ ግዥውን ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጧል፤ አግባብነት ባላቸው ባለሞያዎች የተዋቀረው የግዥ ኮሚቴም እንቅስቃሴ መጀመሩ ተጠቅሷል፡፡ ዘመናዊ የቪዲዮ ካሜራዎችን ጨምሮ የምስልና ድምፅ ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች፣ የቢሮ ዕቃዎችና የጽሕፈት መሣሪያዎች በግዥው የተካተቱ ሲኾን፣ ኦርቶዶክሳውያን ዕቃ አቅራቢዎች በጫረታው በመሳተፍ ለሒደቱ መፋጠን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ድርጅቱ ካለበት ሰፊ ሥራና ከባድ ሓላፊነት አንፃር፡- በርከት ያሉ ቋሚ ስቱዲዮዎች፣ ለቅድመ ሥርጭትና ድኅረ ሥርጭት ተግባራት የሚኾኑ ቤተ መዛግብት፣ የአስተዳደርና የልዩ ልዩ ሠራተኞች ክፍሎች እንደሚያስፈልጉት በሪፖርቱ ጠይቋል፡፡ እስከ አኹን ቋሚ ቢሮ አለማግኘቱን ገልጦ፣ ይህንንም ለማሟላት ከጠቅላይ ጽ/ቤቱና ከሚመለከታቸው አባቶች መመሪያን በመቀበል እየሠራ እንዳለ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት፣ ዋና መሥሪያ ቤቱን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሕንፃ ላይ በማድረግ ነው፣ የሙከራ ሥርጭቱን ዝግጅት እያካሔደና የመደበኛ ሥርጭት ቅድመ ኹኔታዎችን እያመቻቸ የሚገኘው፡፡ ዝግጅቶቹ በቢሮው አልቀው፣ በኢየሩሳሌም በሚገኝ የሳተላይት ኮሚዩኒኬሽን ካምፓኒ አማካይነት ሥርጭቱ ይከናወናል፡፡

የሥርጭቱ ሽፋንም፡- በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሰሜን አፍሪቃ፣ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ፣ በደቡብ ምዕራብ አውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ/በካናዳ/፣ በካሪቢያን፣ በሜክሲኮና አካባቢው የሚገኙ ተመልካቾችን የሚያዳርስ ሲኾን፤ ከዚኽ ውጭ ላለው የዓለም ክፍል በሒደት የሚሸፈን ኾኖ ማንኛውም ሰው ሊያገኘው በሚችል በድረ ገጽ ኹሉም ሥርጭቶች ተጭነው ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን

Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Television

Satellite: Eutelsat/Nilesat (ኢትዮጵያ)

Frequency …… 11353 (5) Vertical

Symbol Rate …. 27500/ FEC ….5/6

Satellite: Galaxy 19(G-19) (ሰሜን አሜሪካ)

Frequency ….. 11960/ Vertical

Symbol Rate … 22000/FEC …3/4

ክፍያውም፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት በኩል በውጭ ምንዛሬ እንዲከፈል በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ የሙከራ ሥርጭቱ ከተጀመረበት ካለፈው ዓመት ሰኔ ወዲኽ የመጀመሪያው ዙር ክፍያ መፈጸሙ ታውቋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በጥቅምት 2008 ዓ.ም. ምልዓተ ጉባኤው፣ ለድርጅቱ የ12 ሚሊዮን ብር የአንድ ዓመት በጀት ማጽደቁ ይታወሳል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን የራሷን ድምፅ የምታሰማበት ብዙኃን መገናኛ ባለቤት የመኾኗ ተስፋ በሙከራ ሥርጭቱ ይፋ መኾን በተበሠረበት ወቅት ብዙዎች ከፍተኛ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ የድርጅቱ መዋቅርና አገልግሎት ከሰርጎ ገቦች ተጠብቆ፥ ኦርቶዶክሳዊውን ትምህርተ ሃይማኖቷን፣ ሥርዓተ እምነቷን፣ ክርስቲያናዊ ትውፊቷንና ታሪኳን ለልጆቿና በተስፋ ለሚጠብቋት ኹሉ በስፋትና በጥልቀት ማስተማር ትችል ዘንድ ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባለውለታ እንደመኾኗ መጠንም፣ ለአጠቃላይ ሕዝቡ የሀገርን በጎ ገጽታ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ዕድገትን፣ ሰላምንና ተባብሮ መኖርን እንድትመክርበት በብዙ ይጠበቃል፡፡

ከዚኽ ጋር ተያይዞ፣ የሙከራ ሥርጭቱ ከሦስት ወራት በላይ እንደማይኾን ቀደም ሲል የተገለጸበት ኹኔታ ቢኖርም፣ እስከ አኹን ወደ መደበኛ ሥርጭት ባለመሸጋገሩ ጥያቄ የሚያነሡ ወገኖች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በአንዳንድ የዝግጅቶቹ ይዘት፣ የምስል ወድምፅ አቀራረብና ጥራት ላይም ቅሬታዎች መደመጣቸው አልቀረም፡፡ ከሌሎች ብዙኃን መገናኛዎች ልምድ አንፃር፣ ያለፉት አራት ወራት የሙከራ ጊዜ በዝቷል ሊባል እንደማይችል የገለጹ የድርጅቱ ባልደረቦች፤ የሙከራ ሥርጭቱን ከሚከታተሉ ኦርቶዶክሳውያን እየደረሳቸው ያለው ግብረ መልስ የሚያበረታታ እንደኾነ ይናገራሉ፤ በአሠራራቸውም ላይ አዎንታዊ ጫና እንደፈጠረባቸው አልሸሸጉም፡፡

ምስሎቹ፣ በአብዛኛው ከመንበረ ፓትርያርኩ ነባር ክምቾቶች የተገኙና፣ ጥራታቸው ከተቀረፁባቸው ካሜራዎችና ከቆይታቸው ጋር እንደሚያያዝ ያስረዳሉ፤ ለሙከራ ሥርጭቱም የሚውሉት በበጎ ፈቃድ ባለሞያዎች ኤዲት ከተደረጉ በኋላ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ጥያቄዎቹም ኾኑ ቅሬታዎቹ፣ ከጠንካራ ጉጉትም እንደሚመነጩ መገንዘባቸውንና ለመደበኛ ሥርጭቱ እየተመቻቹ ካሉ ሞያዊ አሠራሮችና የቴክኖሎጂው የተሻለ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ እንደሚስተካከሉ አስታውቀዋል፡፡ በሌሎች ተቋማት እንዳለው ልምድ፣ አህጉረ ስብከት፥ በቅዱሳት መካናትና በየአካባቢያቸው የክብረ በዓላት፣ የጉባኤያትና የመሳሰሉትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኹነቶችንና እንቅስቃሴዎችን በምስል አስደገፈው በመላክ ለብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ መጠናከር አጋር እንዲኾኑም ጥሪ ቀርቧል፡፡


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት፤ ለመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 35ኛው ዓመታዊ ስብሰባ ያቀረበው የ2008 ዓ.ም. በጀት ዓመት ሪፖርት፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት፤ ቤተ ክርስቲያን፥ ሰላምን፣ መከባበርን፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ዕድገትን፣ የሕዝብን በፍቅር ተባብሮ መኖርን፣ የሰው ልጅ ደኅንነትንና የሀገርን በጎ ገጽታ ማሳየትን መሠረት ያደረጉ ልዩ ልዩ የብዙኃን መገናኛን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባት ታምኖበት፣ ማእከላዊና ተጠያቂነት ያለው የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ሥርጭት እንዲቋቋም በቅዱስ ሲኖዶስ በተላለፈ ውሳኔ የተመሠረተ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት እንዲቋቋም ለማድረግ ጥናት እንዲካሔድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወሰነው በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ዓመት፣ በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም.፣ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በርካታ ባለሞያዎችና ሊቃውንት የተሳተፉበት ጥናት ለምልዓተ ጉባኤው ቀርቦ፡- የድርጅቱ መተዳደርያ ደንብ፣ የአርትዖት መመሪያና የቴክኒክ መመሪያ ጸድቀው ሥራው እንዲጀመር ኾኗል፡፡

በቋሚ ሲኖዶስ በተሠየመው ቦርድ፣ ከአንድ ዓመት በላይ ተጨማሪ ጥናቶችን ሲያደርግ ቆይቶ በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. ለሥራው የሚያስፈልገው በጀት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወስኖለታል፡፡ ቦርዱ፣ የተፈቀደውን በጀትና የተጠናውን ጥናት ወደ ተግባር ለመለወጥ ውድድር በማድረግ ለድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ እንዲቀጠር አድርጓል፡፡

አስፈላጊ የኾኑ ቅድመ ኹኔታዎችን በማሟላትና ካለው አስቸኳይነትም አንፃር፣ የድርጅቱ ቦርድ ተደጋጋሚ ውይይቶችንና ዓለም አቀፍ ዳሠሣዎችን በማድረግ ሥርጭቱን ለማስጀመር የሚያስችል የውል ስምምነት በማዘጋጀትና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አባታዊ መመሪያ፣ በኢየሩሳሌም ከሚገኝና ሥርጭቱን ከሚያከናውነው የሳተላይት ድርጅት ጋር ውል ተፈራርሟል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀው የድርጅቱ መተዳደርያ ደንብ መሠረት፣ የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት በጠቅላይ ጽ/ቤት ግቢ ኹኖ፣ ለሥርጭት የሚኾኑት ዝግጅቶች በሀገር ውስጥ ተዘጋጅተው በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ጋር በተደረገ ስምምነት፣ ኢየሩሳሌም በሚገኘው የሳተላይት ድርጅት አማካይነት ሥርጭቱ ይከናወናል፡፡

በዚኽም መሠረት በቅርቡ፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቃለ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን ተባርኮ የሙከራ ሥርጭቱን EOTC TV በሚል ስያሜ ጀምሯል፡፡

የሥርጭቱም ሽፋን፡- በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሰሜን አፍሪቃ፣ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ፣ በደቡብ ምዕራብ አውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ/በካናዳ/፣ በካሪቢያን፣ በሜክሲኮና አካባቢው የሚገኙ ተመልካቾችን የሚያዳርስ ነው፡፡ ከዚኽ ውጭ ያለው የዓለም ክፍል በሒደት የሚሸፈን ኾኖ ማንኛውም ሰው ሊያገኘው በሚችል በድረ ገጽ ኹሉም ሥርጭቶች ተጭነው ይገኛሉ፡፡ በዐዲሱ በጀት ዓመትም፣ የቴሌቭዥን ሥርጭቱ መደበኛ በኾነ መልኩ መቀጠል የሚችልበት ኹኔታ እየተመቻቸ በመኾኑ፣ የመደበኛ ፕሮግራም ሥርጭቱ ይጀመራል፡፡

የድርጅቱ መዋቅር የተሟላ እንዲኾን፥ በአስተዳደርና ፋይናንስ፤ በመርሐ ግብር ዝግጅት እና በቴክኒክ ዘርፎች ሠራተኞችን ለመቅጠር፣ የሥራ ማመልከቻ ተቀብሎ ቦርዱ በወከላቸው የቅጥርና የምዘና ኮሚቴዎች አማካይነት የቅጥር ሒደቱ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በዚኽም ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በውስጥ ማስታወቂያ አማካይነት ላመለከቱ ሠራተኞችና ለቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ቅድሚያና ትኩረት ተሰጥቶበታል፡፡

ለድርጅቱ አስፈላጊ የኾኑ ቋሚና ተንቀሳቃሽ፣ አላቂና አላቂ ያልኾኑ ንብረቶች ተለይተውና ተዘርዝረው በመውጣት፣ ባለሞያዎች ያሉበት የግዥ ኮሚቴ በማዋቀር ግዥ ለማከናወን በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡

የመደበኛና የሙከራ ሥርጭቱን አጠቃላይ ይዘትና ዓይነት በተመለከተ፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የቦርድ አባላትና የሚዲያ ባለሞያዎች በሚገኙበት ጊዜያዊ የይዘትና ዓይነት ዝግጅት ኮሚቴ አጠቃላይ የይዘት ዝግጅቱ ተጠናቆ ለሥራ ዝግጁ ኾኖ ይገኛል፡፡ ይዘቱንና ዓይነቱን የሚያርምና የሚገመግም የኤዲቶሪያል ኮሚቴ እንዲቋቋም በጸደቀው መተዳደርያ ደንብ መሠረት፣ ቦርዱ የመረጣቸው ሊቃውንት፣ በኤዲቶሪያል ኮሚቴ አባልነት በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ተሠይመዋል፡፡

ይህም ኾኖ በአኹኑ ጊዜ፣ ድርጅቱ ካለበት ሰፊ ሥራና ከባድ ሓላፊነት አንፃር ወደፊት በቋሚነት ለሚያስፈልጉት፡- በርከት ያሉ ስቱዲዮዎች፤ ለቅድመ ሥርጭትና ድኅረ ሥርጭት ተግባራት የሚኾኑ በርካታ ክፍሎች፤ ቤተ መዛግብት፤ የአስተዳደርና የልዩ ልዩ ሞያ ሠራተኞች ክፍሎች የሚያገለግል በቂ ቢሮ እስከ አኹን አላገኘም፡፡ ይኽንንም ለማሟላት፣ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱና ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶች መመሪያን በመቀበል በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

Advertisements

2 thoughts on “የቤተ ክርስቲያናችንን ቴሌቭዥን መደበኛ ሥርጭት ለማስጀመር ኹኔታዎች እየተመቻቹ ነው

 1. Anonymous November 3, 2016 at 2:01 pm Reply

  የመደበኛ ፕሮግራሙ መጀመር በጉጉት የምንጠብቀው ነው፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች የሚዘገይ ከሆነ በሙከራ ስርጭቱ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምሮቷን የጠበቁ ስብከቶች ቢለቀቁ መልካም ነው፡፡ ለአዘጋጆቹ አምላከ ቅዱሳን ብርታትን እንዲሰጣችሁ ፈቃዱ ይሁን አሜን

 2. see more – VISION Of Yohanis Nigus March 31, 2017 at 5:01 pm Reply

  […] […]

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: