ብፁዕ አቡነ ገሪማ የአ/አበባ ሀ/ስብከትን ሒሳብ በፊርማቸው ያንቀሳቅሳሉ፤ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የከፍተኛ ሓላፊዎች ሽግሽግ ተደረገ

 • በሀገረ ስብከቱ፥ ሥልጣን፣ የሀብት ማፍርያና የመጠቃቀሚያ መሣርያ ኾኖ የመቀጠሉ እውነታ!
 • የጠቅ/ ጽ/ቤቱ የሓላፊዎች ሽግሽግ፣ “ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት የተሻለ ውጤት ይኖረዋል”

*                    *                    *

eotc-patriarchate-and-aa-dio-head-off

መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት(ከላይ)የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት(ከታች)

የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የኾነውን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የባንክ ሒሳብ፣ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በፊርማቸው እንዲያንቀሳቅሱ፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መመደባቸው ተገለጸ፡፡

ብፁዕነታቸው፣ የልዩ ጽ/ቤቱ የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ሲኾኑ፣ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የነበሩትን ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልን በመተካት ሒሳቡን በፊርማቸው እንዲያንቀሳቅሱ ትላንት፣ ጥቅምት 18 ቀን ከፓትርያርኩ በተጻፈ ደብዳቤ መመደባቸው ታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ፣ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት እንዲኾኑ የተመደቡት የካፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ “የሥራ ጊዜዎ ስላለቀ” በሚል ከፓትርያርኩ በተጻፈ ደብዳቤ፣ የምደባቸው ጊዜ ማብቃቱ እንደተገለጸላቸው ተጠቅሷል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ባለፈው ዓመት ግንቦት፣ በፓትርያርኩ ተመርጠው በምልዓተ ጉባኤው ሲመደቡ፣ እስከ ዘንድሮው የጥቅምቱ ምልዓተ ጉባኤ ድረስ እንዲያገለግሉ ነው፣ በወቅቱ የደረሳቸው ደብዳቤ የሚገልጸው፡፡

ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አበባ፣ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደኾነ በደነገገው የሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 50 ላይ በሚደረገው ማሻሻያ መሠረት ራሱን ችሎ በሊቀ ጳጳስ እንዲመራ በርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤው ተወስኖ የነበረ ቢኾንም፣ የተባለው የማሻሻያ ረቂቅ እንደተጠበቀው ለጥቅምቱ ምልዓተ ጉባኤ ሳይቀርብ ቀርቷል፡፡

ከዚኽ ጋር ተያይዞ የብፁዕነታቸው ምደባ ሊራዘም እንደሚችል ቢገመትም፣ የሥራ ጊዜአቸው እንዳለቀ በፓትርያርኩ ተገልጾላቸዋል – “የሥራ ጊዜዎ ስላለቀ፣ በነበሩበት የካፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከትና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊነት እንዲቀጥሉ የተደረገ መኾኑን እናስታውቃለን፡፡” ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ ጋር፣ በተደጋጋሚ እየተፈጠረ ያለው የሥራ አለመግባባትም ለምደባቸው አለመራዘም የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው ተመልክቷል፡፡

abune-hizkiel-letter-to-the-patበሰው ኃይል ቅጥር፣ ዝውውርና ሽግሽግ ሳቢያ የሚፈጠረው ውዝግብ በዋና መንሥኤነት እየተጠቀሰ ይገኛል፡፡ አንዱ ከሌላው ዕውቅና ውጭ በመሥራትና አካሔዱን በሕገ ወጥነት በመክሠሥ ለፓትርያርኩ የሚያቀርበው ስሞታና የሚያሳልፈው እገዳም ውዝግቡን እያባባሰው ቆይቷል፤ በጥቅምና በጎጥ አንፃር የተሰለፉ ቡድኖችም፣ በተቃውሞና በድጋፍ ጣልቃ እየገቡ፣ በረዳት ሊቀ ጳጳሱና በሥራ አስኪያጁ መካከል ገና ከጅምሩ የተፈጠረውንና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሽምግልና ሳይቀር ያዳገተውን የተግባቦት ክፍተት አስፍተውታል፡፡

“ጭቅጭቅ፣ ንትርክ፣ ወሬና አሉባልታ ነው የነገሠው፤ ይኼ ተሠራ የሚባል ነገር የለም፤” ሲሉ ነው አንድ የጽ/ቤቱ ሠራተኛ፣ ኹኔታውን በሐዘን የገለጹት፡፡ አክለውም፣ እንዲኽ ያለ ትልቅ ሀገረ ስብከት ያለሊቀ ጳጳስ ማደር አልነበረበትም፤ የጥቅምና የጎጥ ቡድኖች የሚፈልጉትን ክፍተት አግኝተዋል፤ አኹን የሚያስፈልገው፡- በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ማሻሻያ የተደገፈ ሥር ነቀል የመዋቅርና የአሠራር ማሻሻያ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡

ከሚገባው በላይ የሰው ኃይል በተከማቸበትና ከባለጉዳዩ መብዛት የተነሣ ቅርበት ያለው የበላይ አካል ክትትልና ድጋፍ በሚሻው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ ይህ መሰሉ ውዝግብ በጽ/ቤቱ ሓላፊዎች መካከል ሲከሠት አዲስ አይደለም፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተመደበን ረዳት ሊቀ ጳጳስ፣ በፓትርያርኩ ቀጥተኛ ውሳኔ በማንሣት የባንክ ፈራሚ ሊቀ ጳጳስ ሲተካም የመጀመሪያው አይደለም፡፡ የአህጉረ ስብከት ማእከል የኾነው አዲስ አበባን፣ “የኹሉም አካባቢዎች ሠራተኞች የተካተቱበት፤ ግልጽነት፣ ፍትሐዊነት፣ ተኣማኒነትና ከሙስና የጸዳ መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ጽ/ቤት እንዲኾን ለማድረግ” በየጊዜው የሚተላለፉ መመሪያዎች፣ በአንድነትና በምክክር ጉድለት ሳቢያ የአማሳኞችና የጎጠኞች መሣለቂያ እየኾኑ ናቸው፡፡

በርግጥም በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የሚደረግ ሹመትና ምደባ በየጊዜው ያረጋገጠው ነገር ቢኖር፣ በፓትርያርኩ በተደጋጋሚ እንደሚገለጸው፡- ለሙስናና ለብክነት የተጋለጡ፤ ዘመኑን ያልዋጁና ጥራት የጎደላቸውን አሠራሮችን በወሳኝነት በመቅረፍ፣ አዲስ አበባን የአህጉረ ስብከት ሞዴል የሚያደርግ ሳይኾን፣ “ነገ የለኹም/አልኖርም” በሚል እስከ አጥቢያ ድረስ የጎጥና የጥቅም ሰንሰለት የዘረጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ሀብት የማፍርያና የመጠቃቀሚያ መሣርያ ኾኖ የመቀጠሉን እውነታ ነው!!*

በተያያዘ ዜና፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በልዩ መምሪያዎችና ድርጅቶች የከፍተኛ ሓላፊዎች ሽግሽግና ምደባ ተደርጓል፡፡ ርምጃው፣ በአንድ በኩል፣ ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት የሚያበረታታ ውጤት እንደሚያስገኝ የታመነበት እንደኾነ ሲገለጽ፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ሕግንና መመሪያን ተላልፈዋል፤ ሓላፊነታቸውንም አልተወጡም” በተባሉት ላይ አስተማሪነት ይኖረዋል፤ ተብሏል፡፡

ከተደረጉት ሽግሽጎችና ምደባዎች መካከል፡-

 • ከጎፋ ጥበበ እድ የካህናት ማሠልጠኛ ድርጅት ሥራ አስኪያጅነት ተነሥተው ወደ ገዳማት መምሪያ ምክትል ሓላፊነት ተዛውረው የነበሩት የሐዲሳትና የአቋቋም ባለሞያው መጋቤ ብርሃናት አባ ተክለ ያሬድ ዘጎርጎርዮስ፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያን በዋና ሓላፊነት እንዲመሩ መመደባቸው፤
 • የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊ የነበሩትና የሥነ መለኰትና የሥራ አመራር ምሩቅ የኾኑት የድጓው ባለሞያ መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጌታነህ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ድርጅት የአስተዳደርና ፋይናንስ ሓላፊነት መመደባቸው፤
 • ከአ/አበባ ሀ/ስብከት በጀትና ሒሳብ ዋና ክፍል ተነሥተው፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የገዳማት መምሪያ ጸሐፊ የነበሩት ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ፣ መዘምርና የአካውንቲንግ ምሩቅ ሲኾኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ድርጅት በቁጥጥር ሓላፊነት መመደባቸው፤
 • የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሒሳብና በጀት መምሪያ ምክትል ሓላፊ የነበሩት የአካውንቲንግ ባለሞያው ሊቀ ትጉሃን ሽመልስ ቸርነት፣ ቀድሞም በሠሩበትና በቅርበት በሚያውቁት የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በዋና ሥራ አስኪያጅነት መመደባቸው፤
 • የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ምሩቅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት፣ ወደ ጎፋ ጥበበ እድ የካህናት ማሠልጠኛ ድርጅት በተመሳሳይ ሓላፊነት መመደባቸው፤
 • የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት የንብረት ክፍል ሓላፊ የነበሩት መጋቤ ምሥጢር ጌራ ወርቅ ታደሰ፣ በበጀትና ሒሳብ መምሪያው በምክትል ሓላፊነት መተካታቸው፤
 • በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በጸሐፊነት ሲሠሩ የነበሩትና በፊሎሎጂ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው መሪጌታ ዶ/ር ሳሙኤል አየኹ፣ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲን ኾነው መመደባቸው እና የቀድሞው ዋና ዲን ሊቀ ኅሩያን ሠርጸ አበበ ወደ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተዛወረው የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ልዩ ጸሐፊ ኾነው መመደባቸው፤ 
 • የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያ ተልእኮ መምሪያ ምክትል ሓላፊ ሊቀ ማእምራን መኩሪያ ደሳለኝ ወደ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ በምክትል ሓላፊነት ተዛውረው፣ የገዳማት መምሪያ ምክትል ሓላፊ የነበሩት አባ ወልደ ጊዮርጊስ በቦታቸው መተካታቸው፤ ይጠቀሳሉ፡፡

his-grace-abune-diyoscoros
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ በ35ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መዝጊያ ላይ እንደተናገሩት፡- የሥራና ሠራተኛ አለመገናኘት፤ ትክክለኛው ሰው በትክክለኛው ቦታ አለመቀመጥ በተቋማዊ የለውጥ አሠራር፣ ቀዳሚው ወቅታዊ ችግራችን ነው፡፡

አኹን የተደረገው የከፍተኛ ሓላፊዎች ሽግሽግ እያንዳንዱ የሥራ ሓላፊና ሠራተኛ ተግባር ተኰር እንቅስቃሴ በማድረግ በሥራው የሚመዘንበትንና የሚገመገምበትን፤ የሚሾምበትንና የሚሸለምበትን ኹኔታ እንዲፈጥር፣ በ35ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ወቅት ያስተላለፉትን አባታዊ መመሪያ በተጨባጭ ለማሳየት የሚያግዝ መኾኑ ተጠቁሟል፡፡

በአዲሱ በጀት ዓመት፣ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይቻል ዘንድ፣ ሥራዎችን ኹሉ፣ በታቀደ፣ በተደራጀ፣ ውጤት በሚያመጣና ውጤቱም በሚመዝንና በሚገመገም አግባብ ማከናወን እንደሚገባ፣ በብፁዕነታቸው መልእክት አጽንዖት የተሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህም፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ቁልፍ ሥራዎች ማዕከል አድርጎ እንዲከናወን አሳስበዋል፡፡


*ልዩ ትኩረት ለብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት

                       እስክንድር ገብረ ክርስቶስ

/የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዕቅድና ልማት መምሪያ ዋና ሓላፊ/

LEAD Technologies Inc. V1.01

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፣ አንጋፋና ጥንታዊት ብቻ ሳትኾን፣ የሥልጣኔ፣ የሥነ ጥበብ፣ የፊደላት፣ የታሪክና የባህል በጥቅሉ የማንነታችንና የኢትዮጵያዊነታችን መሠረት፤ የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህላችን መገለጫ እንደኾነች ቀደምት በተዉልን ቅርስ የተመራመሩ ጠበብት የሚመሰክሩት ሐቅ ነው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ የራሷ የቀን አቆጣጠር፣ የበርካታ ቅርሶች መገኛና ፈሪሃ እግዚአብሔርን የተላበሰ ሕዝብ ባለቤት እንድትኾን ያስቻለች ስትኾን፤ በኢትዮጵያ የዘመናዊ አስተዳደር ሥርዓት መሠረት እንዲጣልና እንዲጠናከር በማድረግ፣ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅሙ ሥራዎችን የሠራችና በመሥራትም ላይ ያለች መኾኗ ግልጽ ነው፡፡

በአኹኑ ትውልድ፣ በሳይንሳዊ መንገድ ተቀምሮ በትምህርትና በክህሎት ዳብሮ የምንጠቀምበት የዘመናዊ አስተዳደር መሠረት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መኾኗ ላይ ከተግባባን፤ በአኹኑ ወቅት እናት ቤተ ክርስቲያናችን፣ ዘመናዊውን የአስተዳደር ዘይቤ ከመሠረታዊ መንፈሳዊ አቋሞቿ ጋር አስተሳስራ ለማስቀጠል ያልበቃችበትን ምክንያት፣ በሚከተሉት አንኳር ነጥቦች ለመመልከት የምንችል ይመስለኛል፤

 • ዘመናዊውን የአስተዳደር ሥርዓት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ነባራዊ ኹኔታ ጋር አጣጥሞ፣ ስትራተጅ ነድፎ ወደ ተግባር የሚያስገባት ማጣቷ፤
 • ከአሮጌው ተቋማዊ አሠራር ጋር የሙጥኝ ያለ አስተሳሰብ ባለቤት የኾነው ወገን የለውጥ ተግዳሮት መኾኑ፤
 • ሐቀኛ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት የሚፈልግና ቁርጠኛ ግፊት የሚያደርግ አካል ማጣቷ፤
 • በአስተዳደራዊ መዋቅሯ፣ ይሉኝታና የዘመድ አሠራር ተብትቦ የያዛት መኾኗ፤
 • ምሁራን ነን የሚሉት ልጆችዋም ቢኾኑ፣ የመተቸት፣ የመዘላለፍና አሉባልታ የመንዛት አባዜ ሰለባዎች መኾናቸው፤
 • በተራና ተፈላጊውን መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጡ በማይችሉ ሥራዎች ላይ ተጠምዶ መዋልና ለሕግ አውጭው አካል የተደራጀና የተተነተነ የለውጥ ሐሳብ የሚያቀርብ፣ በቅንነት ለኹለንተናዊ ለውጥ የሚተጋ አካል መጥፋቱ…ወዘተርፈ ናቸው፡፡

እኒኽም፣ ቤተ ክርስቲያናችን፣ በቅርቡ በአንዳንድ የሥራ ዘርፎች ከጀመረቻቸው ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓቶች ውጭ፣ ለተፈላጊው ለውጥና መሻሻል ባዕድ እንድትኾን ካደረጓት ዋና ዋና ችግሮች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ሲኾኑ፤ ሙስና እና የዘር ሐረግ ቆጠራ አሳሳቢው የወቅቱ አደጋዋ መኾኑ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡

የአማሳኞችን ጠንካራ ጡንቻና ትክሻ በመፍራት በየሥርቻው ከመወሸቅ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ከፍተኛ አመራር የፀረ ሙስና አቋምና መመሪያ መነሻ አድርጎ፣ ሙስናን መዋጋትና ሙስናን ለመዋጋት የሚያስችል መሠረታዊ ሥራ መሥራት፣ ከቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎች፣ ምሁራንና አገልጋዮች ይጠበቃል፡፡

ዘመኑን ጊዜን በአግባቡ ተጠቅሞና ሠርቶ ለውጥ ማስመዝገብን የሚጠይቅ መኾኑን በመገንዘብ፣ ሥራዎቻችን የግልጽነትና የተጠያቂነት መርሕን የሚከተሉ፣ የሚመዘኑና የሚገመገሙ እንዲኾኑ ማድረግ ይገባናል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያናችንን በዚኽ ትውልድ ውስጥ የማስቀጠልና ያለማስቀጠል ጉዳይ ስለኾነ፣ በተለይም በ35ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ የተላለፈው መልእክት ሊተኮርበት ያስፈልጋል፡፡

ለውጥ የማስመዝገብ ቁርጠኛ አቋምና የማስፈጸም ብቃት ተስፋ የታየበት የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በጎ ተነሣሽነትም፣ ውጤት እንዲያመጣ፣ የየምሪያውና የየድርጅቱ የሥራ ሓላፊዎች መላውን የቤተ ክርስቲያናችንን ሠራተኞች የማስተባበርና የመምራት ድርሻቸውን በርትተው በመወጣት ከታሪክ ተወቃሽነት መዳን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ምንጭ፡- ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ ጥቅምት 10 ቀን 2009 ዓ.ም.

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: