ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገራችን የሰላም ጉዳይ ይነጋገራል፤ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት አልተካተተም

  • በወቅታዊው የሰላም ኹኔታ፣ የቤተ ክርስቲያንን ተሳትፎ የሚያሳድግ መግለጫ ያወጣል
  • ግጭቶችና ሑከቶች፣ ያደረሱት የሰላም መደፍረስ እና የኅሊና ስብራት ቀላል አይደለም
  • ሕዝቡ፥ የስምምነት፣ የአንድነት፣ የሰላምና የፍቅር ሕዝብ እንዲኾን በበቂ አልሠራንም

***

  • ጳጳሳት፣ ሊቃውንት፣ ካህናትና ሰባክያን፥ አስተማሪ እና ሠርተን የምናሳይ መኾን አለብን
  • ቤተ ክርስቲያን፥ በማዕከላዊነት እና በገለልተኛነት የሰላም መልእክቷን ለኹሉም ታደርሳለች
  • ልማትን በማስፋፋትና ለወጣቱ የሥራ ዕድል በመፍጠርም እናትነቷን በተጨባጭ ታሳያለች

***

Holy Synod Tik2008
ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የ2009 ዓ.ም. የመጀመሪያ የምልዓተ ጉባኤ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን፣ ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ዛሬ ጥቅምት 12 ቀን ጠዋት፣ በብዙኃን መገናኛ ፊት ባሰሙት የጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳን ጀምሯል፡፡

የሰላም መጠናከርና መጠበቅ፣ የስብከተ ወንጌል መጠናከርና የልማት ሥራ መስፋፋት፤ ምልዓተ ጉባኤው ሰፊና ጥልቅ ውይይት በማድረግ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሕዝብና ለሀገር የሚጠቅሙ ውሳኔዎች የሚያሳልፍባቸው የትኩረት አጀንዳዎች እንደኾኑ ነው፣ ፓትርያርኩ በመክፈቻ ቃለ ምዕዳናቸው የጠቆሙት፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ በየጊዜው በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች የሚወያይባቸውን ጉዳዮች የማዘጋጀት ሓላፊነት ያለበት ቋሚ ሲኖዶስም፣ በመነሻነት ካቀረባቸው አምስት ነጥቦች መካከል፣ በአገሪቱ ወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ላይ መነጋገር የምልዓተ ጉባኤው ቀዳሚ አጀንዳ ኾኖ ተቀምጧል፡፡

የጥቅምቱ መደበኛ ስብሰባ፣ የመጀመሪያና ዓመታዊው የቤተ ክርስቲያን በጀት የሚጸድቅበት በመኾኑ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት የተዘጋጀው የበጀት ረቂቅና ተያያዥ የአህጉረ ስብከት ጥያቄዎች ሌሎቹ አጀንዳዎቹ እንደኾኑ ተገልጧል፡፡

በተጨማሪም፣ ቀደም ብሎ የተካሔደውና የ2008 ዓ.ም. መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጉዳይ የተደመጠበት፣ የ35ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብም ቀርቦ ከታየና ከጸደቀ በኋላ ለአህጉረ ስብከት የሥራ መመሪያ ኾኖ የሚተላለፍበት ነው፤ ምልዓተ ጉባኤው፡፡

ያለፈው ዓመት የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ፣ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም በአቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ አማካይነት የመጨረሻዎቹ ተጠቋሚዎች ተለይተው የቀረቡ ቢኾንም፤ ምልዓተ ጉባኤው በአጀንዳው እንዳላካተተው የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ የእንደራሴ ምደባና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ጨምሮ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ጋር በተያያዘ ያደሩ አጀንዳዎችም በዝርዝሩ አለመካተታቸው ተመልክቷል፡፡

እንደ ወትሮው፣ ተጨማሪ የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ ማቋቋም ሳያስፈልገው፣ በቋሚ ሲኖዶሱ የቀረቡለትን አምስት የመነጋገርያ ነጥቦች አጽድቆ ውይይቱን የቀጠለው ምልዓተ ጉባኤው፣ የቀጣይ ስድስት ወራት የቋሚ ሲኖዶስ አባላትን በመምረጥ ስብሰባውን በአጭሩ ሳያጠናቅቅ እንደማይቀር ተጠቁሟል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በዛሬው የመጀመሪያ ቀን ውሎው፣ በቅዱስ ፓትርያርኩ የጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳን ለተጠቆመውና በዋነኛ አጀንዳነትም በተቀመጠው፣ ወቅታዊው የሀገራችን አሳሳቢ የሰላም ጉዳይ ዙሪያ በስፋትና በጥልቀት ለመምከር፣ በምልዓተ ጉባኤው በተመረጡ ሦስት ብፁዓን አባቶች ተዘጋጅቶ የሚቀርበውን ጽሑፍ መነሻ እንደሚያደርግ ተሰምቷል፡፡

በስብሰባው መጨረሻ የሚያሳልፈው ውሳኔና የሚያወጣው መግለጫም፣ ለሕዝብና ለሀገር ደኅንነት መጠበቅ በተለያዩ ወገኖች በሚደረገው ጥረት፣ የቤተ ክርስቲያንን ተሳትፎ በማሳደግ ቀድሞም የነበራትን የማስተማር፣ የማቀራረብና የማስታረቅ ታሪካዊና አገራዊ ሚና እንደሚያጠናክረው ይጠበቃል፡፡


his-holiness-pat-aba-mathias
በሀገራችን ወቅታዊ የሰላም ኹኔታና ከቤተ ክርስቲያን በሚጠበቀው ሚና ላይ ያተኮረው የርእሰ መንበሩየጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳን፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ሑከቶች ለዘመናት በአንድነት የኖረውን ሕዝብ በማቃቃር ያስከተለው የሕይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመትና የኅሊና ስብራት፣ ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ ማሳዘኑን ገልጾአል፡፡

ችግሩ ከተፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ ቤተ ክርስቲያን ኃዘኗንና የሰላም ጥሪዋን በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጠቅሰው፣ ሕዝቡ፥ የስምምነት፣ የአንድነት፣ የሰላምና የፍቅር ሕዝብ እንዲኾን ለማድረግ ግን ገና የሚቀረን ሥራ እንዳለ ነው በቃለ ምዕዳናቸው ያመለከቱት፡፡

የሰላም ሐዋርያት ኾነው በጌታችን ከተሾሙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሕዝብን የሚያግባባና የሚያስማማ በንጹሕ የእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ትምህርት ማስተማር ይጠበቃል፤ ይህም፣ የኅሊና ስብራቱ ተጠግኖ እስኪሽርና ሰላሙ አስተማማኝ እስኪኾን ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

“ኦ አባ ቅዱስ ዕቀቦሙ በስምከ ለእለ ወሀብከኒ ከመ ይኩኑ አሐደ ብነ ከማነ = ቅዱስ አባት ሆይ፣ እነዚኽን የሰጠኽኝን እንደ እኛ አንድ እንዲኾኑ በስምኽ ጠብቃቸው”(ዮሐ. 17 ቁ.11) የሚለውን ወንጌላዊ ጥቅስ መነሻ ያደረገው ቃለ ምዕዳኑ፣ እግዚአብሔር በከሃሊነቱ ያቆራኘውን ሕዝብ ትስስርና ተመጋጋቢነት በተለያዩ ሰበቦች ለማለያየት መጣር፣ “ሙከራ ከመኾን አልፎ ዘላቂ ተቀባይነት አይኖረውም፤” ብሏል፡፡

ቤተ ክርስቲያን የሕዝቡ ኹሉ እናት እንደመኾኗ መጠን፣ የሀገርን አንድነት የሚፈታተኑ እንቅስቃሴዎችን፣ ሕዝቡ እንዲጠነቀቅባቸውና በአርቆ አስተዋይነት እንዲመለከታቸው በልዩ ትኩረት ማስተማር ይጠበቅባታል፡፡ ለዚኽም፡- ዘላቂና ብዙኃኑን የሚጠቅም ሰላም ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ተሳትፎዋን ማሳደግ ይኖርባታል፤ ወደዚኽም ወደዚያም ሳትል ማዕከላዊና ገለልተኛ ኾና የሰላም መልእክቷን ለኹሉም ማድረስ ይገባታል፡፡

በተለይ በወጣቱ በኩል፣ የሥራ አጥነት ችግር የአደጋው አንድ መንሥኤ እንደኾነ የተናገሩት ርእሰ መንበሩ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንት፣ ካህናትና ሰባክያን፡- የሕዝቡ አስተማሪዎች ብቻ ሳይኾኑ ሠርተው የሚያሳዩም እንዲኾኑ መክረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም፣ በኹሉም አቅጣጫ ልማትን በማስፋፋት ለወጣቱ የሥራ ዕድልን በመፍጠር እናትነትዋን በተጨባጭ እንድታሳይ አሳስበዋል፡፡

Advertisements

One thought on “ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገራችን የሰላም ጉዳይ ይነጋገራል፤ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት አልተካተተም

  1. Anonymous October 23, 2016 at 9:01 pm Reply

    ዋና ሁከት ፈጣሪና የአገሪቱ ሰላም አደፍራሽ እኮ የተነሱለትን አላማ የረሱ ለጎጠኝነት ያደሩ ፍፁም ሃይማኖታዊ ነት የሌለባቸው ሽጉጥ ታጣቂ መናፍቃን ጳጳሳት ና አስተዳዳሪዎች ናቸው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: