35ኛው አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ ተጠናቀቀ፤ በተለያዩ አካባቢዎች ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ኹሉ ሐዘኑን ገለጠ፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ተመኘ

35th-pat-gen-assem

ባለፈው ሰኞ የተጀመረው፣ 35ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ ባለኻያ ነጥቦች የጋራ አቋም መግለጫ በማውጣትና ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የውሳኔ ሐሳብ በማቅረብ፣ ትላንት፣ ኃሙስ ቀትር ላይ ተጠናቋል፡፡

አጠቃላይ ጉባኤው፣ በኦሮሞ ሕዝብ ባህል በየዓመቱ በቢሾፍቱ በሚከበረው የኢሬቻ ሥነ ሥርዓት ላይና በሌሎቹም አካባቢዎች በተፈጠረ “ሁከትና ግርግርሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ኹሉ፣ ቋሚ ሲኖዶስ የሰባት ቀን ጸሎተ ምሕላ ዐውጆ ሥርዓተ ጸሎቱ መፈጸሙን አስታውሶ፤ የተሰማውን ሐዘን ገልጧል፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ተመኝቷል፡፡

በዓመታዊ ስብሰባው መዝጊያ፣ “ሰላሜን እተውላችኋለኹ” ባለው የወንጌል ቃል መነሻ፣ ቃለ በረከት የሰጡት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ቤተ ክርስቲያናችን የሰላም ባለቤት መኾኗን ገልጸው፣ የጉባኤው ልኡካን ስለ ሰላም እንዲሰብኩና እንዲያስተምሩ አሳስበዋል፡፡

አያይዘውም፣ “ችግር ነበር፤ አኹን ግን ጥሩ ኾኗል፤ ረግቧል፤” ያሉት ፓትርያርኩ፣ “የሚጥመው ይጥመዋል፤ የማይቀበለው የራሱ ጉዳይ ነው፤ በሪሞት ኾነው የሚያተራምሱትን ሐሳባቸውን መደገፍ የለብንም፤” ብለዋል፡፡

ከፓትርያርኩ ቀደም ብለው የማጠቃለያ የሥራ መመሪያ የሰጡት የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ÷ ቤተ ክርስቲያን ማንም እንዲጠፋ ምኞቷ አለመኾኑን ተናግረዋል፡፡ ይኹንና፣ “የእናት ጡት ነካሾች” ሲሉ የገለጿቸው የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች እየበዙ መምጣታቸውን በመጠቆም ለአጠቃላይ ጉባኤው ልኡካን ጥብቅ መመሪያ ሰጥተዋል – “በእግረ ኑፋቄ ጸንተው የሚቆሙ ካሉ ነቅሎ መጣል ያስፈልጋል!!”

ብፁዕነታቸው አክለውም፣ “እኛ የሠራነውን አባቶቻችን ሠርተውና ጠብቀው ካቆዩልን ጋር በንጽጽር ሲታይ እንዴት ነው?” ሲሉ ጉባኤተኛውን ጠይቀዋል፡፡ የሥራና ሠራተኛ አለመገናኘት የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ችግር መኾኑንም በአጽንዖት አመልክተዋል፡፡

his-grace-abune-lukas1
ባለፈው ዓመት የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ የሦስት ዓመት የሥራ ዘመናቸውን አጠናቅቀው ያስረከቡት፣ የቀድሞ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ እና የቀድሞ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ አቅራቢነት፣ በውጤታማ አመራራቸውና አገልግሎታቸው የምስክር ወቀረትና የእጅ መስቀል ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተበርክቶላቸዋል፡፡

his-grace-abune-mathewos2
ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ለኹለቱ ብፁዓን አባቶች የሥራ ስኬት ለሰጠው ዕውቅና፣ አጠቃላይ ጉባኤው ይኹንታውን በከፍተኛ ስሜት ነው የገለጸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስም፣ “በበር የገባ በመስኮት መውጣት የለበትም” በማለት፣ የሠራን መሸለምና ማመስገን ሊለመድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

አህጉረ ስብከትም÷ ባስመዘገቡት የገቢ ዕድገት፣ የጠቅላይ ጽ/ቤት የመቶኛ ፈሰስና በራስ አገዝ ልማት አፈጻጸማቸው እየተነጻጸሩ ከፍተኛ ውጤት ላመጡት ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ የሽልማቱ መመዘኛ፣ በሪፖርት ላይ ያተኮረ መኾኑ ውድድሩን ሚዛናዊነትና ፍትሐዊነት እንደሚያሳጣው ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሳይተቹበት አላለፉም፡፡ ማወዳደርያ ነጥቦችና የሚሰጣቸው ዋጋ፣ የሪፖርቱን እውነታዎች በሚያረጋግጡና የአህጉረ ስብከቱን ተጨባጭ ኹኔታዎች በሚያገናዝቡ የቢሮና የመስክ ግምገማዎች ሊታገዝ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ፣ ከአርባ ዘጠኙ አህጉረ ስብከት፣ ብር 167 ሚሊዮን 606 ሺሕ 936 ብር ከ59 ሳንቲም ገቢ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የተደረገ ሲኾን፤ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር፣ የብር 41 ሚሊዮን 656 ሺሕ 008 ከ76 ሳንቲም ብልጫ ተመዝግቦበታል፡፡ ከዚኹ አጠቃላይ ገቢ ውስጥ ከብር 6 ሚሊዮን በላይ በልማት ገቢ የተደረገ ሲኾን፣ ከአምናው ገቢ አንጻር የ1 ሚሊዮን 352 ሺሕ 546 ከ83 ሳንቲም ልዩነት በብልጫ እንዳሳየ የበጀትና ሒሳብ መምሪያው ሪፖርት ያስረዳል፡፡

የገቢ ዕድገቱ የተመዘገበው፣ ኹሉም በየድርሻው በፈጸመው ተግባር በመኾኑ ቀጣይነት እንዲኖረውና የቤተ ክርስቲያን የፋይናንስ አቅም አስተማማኝ እንዲኾን፣ ምእመናንን ግዴታቸውን እንዲወጡ ማስተማርና የልማቱንም ሥራ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አጠቃላይ ጉባኤው በጋራ መግለጫው አሳስቧል፡፡

ሲኖዶሳዊ የኾነውንና ማዕከላዊ አሠራር ያለውን የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደር በሚፈታተን መልኩ ስለሚፈጠረው አስተዳደር ነክ የሕግ ጥሰት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በአምናው ጉባኤው ውሳኔ ቢሰጥበትም ዘንድሮም መከሠቱን የጠቀሰው የጋራ መግለጫው፣ ዝርዝር የሥራ መመሪያ በማውጣት ክትትል እንዲያደርግበት አጠቃላይ ጉባኤው በአክብሮት አሳስቧል፡፡

የአጠቃላይ ጉባኤው የጋራ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ፡- የሰበካ ጉባኤ መደራጀትን፤ የሰንበት ት/ቤቶች፣ የአብነት ት/ቤቶችና መንፈሳውያን ኮሌጆች መጠናከርን፤ የስብከተ ወንጌል መስፋፋትን፣ የራስ አገዝና ማኅበራዊ ልማት መጎልበትንና የቅርሶች መጠበቅን እንዲኹም የውጭ ግንኙነትን የተመለከቱ ጉዳዮች የተዳሠሡበት ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤ ከመከረባቸው በኋላ ጸድቀው በየአህጉረ ስብከቱ የሥራ መመሪያ እንዲኾኑም ይጠበቃል፡፡

የጋራ መግለጫው እና የውሳኔ ሐሳቡ ዐበይት ነጥቦች፡-
 • የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ እንዲከናወን በማድረግ፣ ያልተፈቀደላቸውና መነሻቸው የማይታወቅ ሰባክያን ነን ባዮችን በመከላከል፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶን እንቅስቃሴን በንቃት በመከታተልና በመከላከል በትምህርተ ወንጌል ምእመናንን ለመጠበቅ ቃል እንገባለን፡፡
 • በቤተ ክርስቲያናችን የተጀመረው፣ የቴሌቭዥን የሙከራ ሥርጭት ፕሮግራም፣ ኹሉን አካባቢ ተደራሽ በማድረግ መደበኛ ሥርጭቱ እንዲጀመር እንጠይቃለን፡፡
 • በአንዳንድ አህጉረ ስብከት፣ በአፅራረ ቤተ ክርስቲያን በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን የንብረት መውደም፣ የአካል መጉደልና የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠልና መደፈር ጉባኤው ያዘነበት ሲኾን፤ ኹሉም ባለድርሻ አካላት፣ እየተፈጸመ ያለውን ጉዳት በመከታተል፣ ከመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር የቤተ ክርስቲያኒቱንና የአማኞቿን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር ቃል እንገባለን፡፡
 • ጥንታውያን የአብነት ት/ቤቶችና መንፈሳውያን ኮሌጆች፣ በቤተ ክርስቲያናችን ቀጣይ ህልውናና አቅጣጫ ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመኾኑ፣ ለትምህርት ተቋማቱ ትኩረት እንዲሰጣቸው ጉባኤው አስምሮበታል፡፡ ከተቋማቱ በሚወጡት ደቀ መዛሙርት እየተሰጠ ያለው አገልግሎትም መጠነ ሰፊ ነው፡፡ በመኾኑም ለሚሰጣቸው ትኩረትና ድጋፍ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
 • የአብነት ት/ቤቶች የሚሰጡት ትምህርት ፖሊሲ እንዲኖረው፣ የሥርዓት ትምህርት ሞያው ባላቸው እየተጠና ያለው የሞያ እና የዕውቀት ደረጃ አሰጣጥ በሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ዝርዝር የማስፈጸሚያ አመራር እንዲሰጥበት እንጠይቃለን፡፡
 • በየጊዜው በሚከሠተው ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚፈጠረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ በመኾኑም ለሕዝበ ክርስቲያኑ ተገቢውን ትምህርት በመስጠት፣ በሚፈጠሩት ችግሮች አቅም በፈቀደ መልኩ ለመረዳዳት ቃል እንገባለን፡፡
 • በአገራችን ለዓመታት ተጠብቆ የኖረው እርስ በርስ የመከባበርና የመተሳሰብ ዕሴት በትውልድ መካከል እንዳይሻርና እንዳይሸረሸር፣ የአገራችንና የሕዝባችን ሰላም ተጠብቆ እንዲኖር ተገቢውን ትምህርት እንሰጣለን፡፡
 • የቤተ ክርስቲያን ሀብቷና ንብረቷ ምእመናን እንደኾኑ በሰፊው ተገልጧል፡፡ ይህም ሲባል፣ ያሉትን በትምህርተ ወንጌልና ተገቢውን መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ከመከባከብ ጎን ለጎን፤ የምእመናንን ቁጥር በተሻለ ማብዛትና ተተኪ ማፍራት ግድ ስለኾነ፤ ወጣቱን በየሰንበት ት/ቤቶች አቅፎ ለመያዝ ዶግማቸውን፣ ቀኖናቸውንና ታሪካቸውን እንዲማሩ በማድረግ ተተኪነታቸውን እንዲያረጋግጡ ተገቢውን ሥራ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡
 • ቅርሶች የቤተ ክርስቲያናችን ሀብቶችና የማንነታችን መገለጫዎች በመኾናቸው፣ በያለንበት ተገቢው ጥበቃና ክብካቤ ለማድረግና የቱሪስት መስብሕነታቸውን ለማስቀጠል እንሠራለን፡፡
 • ቤተ ክርስቲያናችን ለራስ አገዝ ልማት ለምትገነባቸው ሕንፃዎች፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት በዕውቀታቸውና በሞያቸው ለማገዝ የቴክኒክ ኮሚቴ፣ በማቋቋም በቋሚ ሲኖዶስ የሥራ መመሪያ እንዲሰጠው በማድረግ ለተወሰደው የሥራ ርምጃ አጠቃላይ ጉባኤው በአድናቆት ተቀብሎታል፡፡ ይህም በየአህጉረ ስብከቱ ዋና ከተሞችም ጭምር የሚቋቋምበትና ቤተ ክርስቲያን በኹሉም ዘርፍ በልጆቿ ተጠቃሚ የምትኾንበት አሠራር መዘርጋት፣ ጊዜውን የዋጀ አፈጻጸም በመኾኑ በየደረጃው ተጠክሮ እንዲቀጥል፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረት እንዲሰጥበት እንጠይቃለን፡፡
 • ቤተ ክርስቲያናችን፣ ከመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጋር ኩታ ገጠም አድርጋ የሠራቻቸውን፣ ከቤት ቁጥር 1166 እስከ 1169 የተመዘገቡትን 12 ፎቅና መለስተኛ ሕንፃዎች፣ የቤተ ክርስቲያናችን አንጡራ ሀብት ስለመኾናቸው ማስረጃዎች እያረጋገጡ እያለ መንግሥት ለመመለስ ፈቃደኛ እንዳልኾነ ለአስመላሽ ኮሚቴው የሰጠው ምላሽ አጠቃላይ ጉባኤው በሐዘን ሰምቶታል፡፡ በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚመለከታቸው የፖሊቲካና የፖሊሲ ውሳኔ ሰጭ የኢፌዴሪ ሥራ አስፈጻሚ አካላት ጋር በትዕግሥት በመነጋገር ቀና አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጥቶ፣ የቤተ ክርስቲያናችን ሀብትና ንብረት እንዲመለስ፤ በባዶ ቦታዎችና ይዞታዎች ኹሉ ላይ ዘመናዊ ሕንፃዎች እንዲገነቡ ያደርግ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
 • በኹሉም ክፍለ ዓለም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያሉ አህጉረ ስብከት፣ መንፈሳዊ አገልግሎትና አስተዳደር ካለፈው በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጊዜ ሳይሰጠው ተቀርጾ እንዲሠራበት ቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ይሰጥበት ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
 • በቅዱስነታቸውና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሚደረገው የውጭ ሀገር ሐዋርያዊ ጉዞ የተፈጸሙ አገልግሎቶች፣ በተለይም የቤተ ክርስቲያናችንን ዓለም አቀፋዊነትና በተለይም የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት በተገቢው መንገድ የሚያጎለብት በመኾኑ፣ አኹንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንጠይቃለን፡፡
 • በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ ከተማ፣ የኦሮሞ ብሔር በሚያከብረው የኢሬቻ ሥነ ሥርዓት ላይና በሌሎቹም አካባቢዎች በተፈጠረ ሁከትና ግርግር ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ኹሉ፣ ቋሚ ሲኖዶስ የሰባት ቀን ጸሎተ ምሕላ ዐውጆ ሥርዓተ ጸሎቱን ማድረሳችን ይታወሳል፡፡ በመጨረሻም በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በሰላም መታጣት ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ኹሉ ጉባኤው ሐዘኑን ገልጧል፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ተመኝቷል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ጥቅምት ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ

Advertisements

One thought on “35ኛው አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ ተጠናቀቀ፤ በተለያዩ አካባቢዎች ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ኹሉ ሐዘኑን ገለጠ፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ተመኘ

 1. Anonymous October 21, 2016 at 3:01 pm Reply

  ሐሳብ ነበረኝ እንዴት ነው የምትገኙት

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: