የቅዱስ ሲኖዶስ መክፈቻ ጸሎት ተካሔደ፤ ለሰላም ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠይቋል

 • ቤተ ክርስቲያን፣ መምህር ወመገሥጽ ዘኢያደሉ ለገጽ በመኾን ከክርስቶስ በተቀበለችው አደራና ሓላፊነት፥ መንጋውን የመጠበቅ፣ የማጽናናትና የማስታረቅ ሥራ ልትሠራ ይገባል/ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል/

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከፍተኛ መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ሕግ አውጭና ወሳኝ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖስ፣ የ2009 ዓ.ም. የመጀመሪያ መደበኛ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባውን ነገ ይጀምራል፡፡

በፍትሕ መንፈሳዊ በአንቀጽ 5 ቁጥር 164 በታዘዘው መሠረት፣ ነገ ቅዳሜ፣ ጥቅምት 12 ቀን ለሚጀመረው የምልዓተ ጉባኤው ስብሰባ፣ ዛሬ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡

በመክፈቻ ጸሎቱ የዕለቱን ወንጌል(ማቴ. ምዕ. 22 ቁ. 35) በንባብ በማሰማት ትምህርት የሰጡት፣ የሶማሌና የአርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ከአበው ሐዋርያት ሲያያዝ በመጣው ትውፊት መሠረት፣ የቤተ ክርስቲያንን ዐበይት ጉዳዮች በአጀንዳነት ቀርጾ በመወያየት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተናግረዋል፡፡

እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ነፍስና በፍጹም ሐሳብ በመውደድ፣ ጾምና ጸሎትን ገንዘቡ ያደረገ የወሰነው ውሳኔ ነቀፌታ እንደማይኖረውም ብፁዕነቸው በአጽንዖት አስረድተዋል፡፡

ከመክፈቻ ጸሎቱ ቀደም ሲል በተካሔደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ጉባኤ ላይ የአህጉረ ስብከታቸውን ሪፖርት ያቀረቡት፣ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ለሀገራችን የሰላም ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚነጋገር ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን፣ እንደ አበው አነጋገር፣ መምህር ወመገሥጽ ዘኢያደሉ ለገጽ በመኾን ከክርስቶስ በተቀበለችው አደራና ሓላፊነት፥ መንጋውን የመጠበቅ፣ የማጽናናትና የማስታረቅ ሥራ ልትሠራ እንደሚገባም መክረዋል፡፡

img_7660

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፤ የዋሽንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት

ለ35ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የቀረበው የዋሽንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት የ2008 ዓ.ም. የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት ከፊል ይዘት

የ2008 ዓ.ም. የበጀት ዓመት፣ የዋሽንግተን ዲሲና የምዕራብ አሜሪካ – ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት፣ በአህጉረ ስብከቱ ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ከምንጊዜውም ይልቅ ከኪራይ ቤት ወጥተው የራሳቸው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለመግዛትና ባለቤት ለመኾን ጥረት ያደረጉበት፣ ስኬታማም የኾኑበት ዓመት ነው፡፡ በዚኽም መሠረት ስድስት አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው ሕንፃ አብያተ ክርስቲያን ገዝተው ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል፡፡

 1. የሲያትል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያ
 2. የዳላስ መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያ
 3. የዳላስ ደብረ መንክራት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን
 4. የሳክራሜንቶ ፍኖተ ሎዛ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን
 5. የሜሪላንድ ኆኅተ ምሥራቅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን
 6. የአትላንት ቅድስት ሥላሴ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሲኾኑ፣
 7. በዳላስ የደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን(በትውፊታዊው የቤተ ክርስቲያናችን ሥነ ሕንጻ ቅርፅ ለመሥራት መሬት ገዝተው ዕብነ መሠረቱ ተጥሏል)

ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናትን በተመለከተ፤ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ለመመለስ ጥረቱ ቀጥሏል፡፡ በአገልግሎት ዘመኑ፣ ሦስት አብያተ ክርስቲያን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰዋል፡፡

 1. በቨርጅንያ ስቴት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን
 2. በኮሎራዶ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን
 3. በዳላስ የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡

ዐበይት በዓላትን በተመለከተ፤ የ2008 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል፣ 15 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በተገኙበት በዳላስ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በርካታ ካህናትና በሺሕ የሚቆጠሩ ምእመናን በተገኙበት፣ ደመራ በመደመር በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡ በአትላንታ፣ በዳላስ ቴክሳስ፣ በሲያትል እና በሌሎችም ከተሞች አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ በዓሉ በኅብረትና በደመቀ ኹኔታ ተከብሮ ውሏል፡፡ የጥምቀት በዓልም እንዲኹ በተመሳሳይ ኹኔታ ተከብሯል፡፡ የኹለቱንም ዓበይት በዓላት ዝግጅት በዩቲዩብ ድረ ገጽ መመልከት ይቻላል፡፡

ሥልጣነ ክህነትን በተመለከተ፤ በአህጉረ ስብከታችን በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በመኖራቸው፣ በአሜሪካ የተወለዱ ልጆች ግብረ ዲቁና በመማር አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት በዲቁና የሚያገለግሉት በአሜሪካ የተወለዱ ልጆች ናቸው፡፡ ቅዱስነትዎና ወደ አሜሪካ ጎራ ያላችኹ ሊቃነ ጳጳሳት የዓይን ምስክሮች ናችኹ፡፡ አህጉረ ስብከታችን ለወደፊት ቤተ ክርስቲያንን የሚረከቡ ተተኪዎች በማፍራት ውጤታማ እየኾነ ይገኛል፡፡ በበጀቱ ዓመት፣ አሜሪካ ተወልደው ያደጉ 35 ዲያቆናትና 6 ቀሳውስት ሥልጣነ ክህነት ተቀብለዋል፡፡

በሀገራችን ለተከሠተው ድርቅ፣ እግዚአብሔር አምላክ ዝናመ ምሕረቱን ጠለ በረከቱን እንዲሰጥ ጸሎተ ምሕላ ተደርጓል፡፡ ከጠቅላይ በተጻፈው ደብዳቤ መሠረት(ዘግይቶ ቢደርሰንም) ከኹለቱም አህጉረ ስብከት፣ የተቻለንን ያኽል ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በማሰባሰብ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ባስተላለፍልን የሒሳብ ቁጥር ገቢ አድርገናል፡፡ ከዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት ጥቂት አብያተ ክርስቲያናት፣ 1 ሚሊዮን 267 ሺሕ 992 ብር በታዘዝነው የሒሳብ ቁጥር ገቢ ተደርጓል፡፡ ገቢ የተደረገባቸውን ደረሰኞችም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት አስረክበናል፡፡ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱን፣ በቅዱስነትዎ፣ በብፁዓን አባቶችና በአጠቃላይ ጉባኤው ፊት ላመሰግናቸው እወዳለኹ፡፡

የሀገርን ሰላም በተመለከተ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ በሀገራችን ኢትዮጵያ በአንዳንድ ክልሎች በተፈጠሩ ችግሮች፣ ከኹሉም ወገን የንጹሐን ወገኖች ሕይወት አልፏል፤ አካል ጎድሏል፤ የሕዝብና የመንግሥት ንብረቶች ወድመዋል፡፡ በዚኽም ምክንያት ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶናል፡፡

ችግሩ በሰላም እንዲፈታ እግዚአብሔር አምላክ፡- ለመንግሥት ማስተዋልንና ጥበብን፤ ለሕዝቡ መረጋጋትንና መጽናናትን፤ በአጠቃላይ ለሀገራችን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ይወርድ ዘንድ ጸሎተ ምሕላ፣ ለሞቱትም ጸሎተ ፍትሐት በአህጉረ ስብከታችን ባሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ተካሒዷል፡፡ አኹንም ሰላም እስኪወርድ ድረስ የምሕላ ጸሎቱ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

ከምንም በላይ የሀገራችን ሰላም በእጅጉ ያሳስበናል፡፡ በቅዱስነትዎ የሚመራው ይህ ዐቢይ ጉባኤ እና በቀጣይም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ በሰላም ጉዳይ ላይ ትኩረት እንደሚሰጥበት ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን፣ እንደ አበው አነጋገር፣ መምህር ወመገሥጽ ዘኢያደሉ ለገጽ በመኾን ከክርስቶስ በተቀበለችው አደራና ሓላፊነት መንጋውን የመጠበቅ፣ የማጽናናትና የማስታረቅ ሥራ ልትሠራ ይገባል፤ ብለን እናምናለን፡፡

በመጨረሻም ለአህጉረ ስብከታችን መጠናከርና መስፋፋት፣ ጸሎታችኹ አይለየን እያልን ከዋሽንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት በረከት ለመቀበል ያኽል 120 ሺሕ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ገቢ አድርገናል፡፡ ስላዳመጣችኹኝ አመሰግናለኹ፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: