አህጉረ ስብከት: በፀረ – ተሐድሶ ኑፋቄ ተጋድሎ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን አስታወቁ

 • አብዛኞቹ አህጉረ ስብከት፣ የፀረ – ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤያትን በጥምረት አደራጅተዋል
 • ለተሐድሶአውያኑ“የእምነት መግለጫ”  የጽሑፍ ምላሽ ዝግጅት ተጠናቋል/ሊቃውንት ጉባኤ/
 • “ወዳጅም ጠላትም ይስማ! ሀ/ስብከታችን ለተሐድሶ መናፍቃን ቦታ የለውም!” /ምዕ. ወለጋ/
 • “በሀገረ ስብከታችን÷ ተሐድሶ የሚባል ስም አጠራሩ ከምድረ ገጽ ጠፍቷል!” /ጅማ/

*               *               *

35th-pat-gen-assembly-2009

፴፭ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባውን በማካሔድ ላይ

የቤተ ክርስቲያን ቀዋሚና የማይነጥፉ ሀብቶቿ ምእመናን ናቸው፡፡ ምእመናን ሀብቶቿ ያሉበትን በውል ማወቅ፣ ዐውቃም ወደ ለመለመ የወንጌል ማዕድ በማሰባሰብ በቃለ እግዚአብሔር መጠበቅና በሥነ ምግባር መከባከብ፤ ለንስሐና ለሥጋ ወደሙ ማብቃትና የመንግሥተ እግዚአብሔር ወራሾች እንዲኾኑ ማድረግ ቀዳሚ ትኩረቷ ነው፡፡

ማኅበረ ካህናት ወምእመናንን አቅፎ የተደራጀው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፥ ይህንኑ ክህነታዊ ግዴታውን ለመወጣት ያስችለው ዘንድ፣ በስብከተ ወንጌልና በማኅበራዊ ልማት መስፋፋት፤ በሰንበት ት/ቤቶችና በአብነት ት/ቤቶች መጠናከር ውጤታማ ለውጦችን እያስመዘገበ እንዳለ፣ በ35ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እየቀረቡ ያሉ የአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡

ምእመናን፣ ለሃይማኖታቸው ቀናዒ እንዲኾኑና በምግባር እንዲጸኑ የተጠናከረ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንደተሰጠ፤ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሐዲሳን አማንያን ከክሕደትና ከኑፋቄ ተመልሰው ለጥምቀተ ክርስትና እንደበቁና ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት እንደተጨመሩ፤ ተዘግተው ቆይተው በመልሶ ማቋቋም የተከፈቱና በአዲስ የተተከሉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲኹም የታነፁ የስብከተ ወንጌል አዳራሾች ቁጥር ከፍተኛ እንደኾነ ከሪፖርቶቹ ለመረዳት ተችሏል፡፡


ይህንኑ መሠረታዊ ሐዋርያዊ ተልእኮ ከማስፈጸም ጋር፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ኦርቶዶክሳዊ ማንነትና ማዕከላዊ አስተዳደር የህልውና ስጋት የኾነውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ለመከላከል፣ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤያት በጥምረት በማደራጀት ተጋድሏቸውን ማፋፋማቸውን የሚበዙት አህጉረ ስብከት በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ጉባኤያቱ(ኮሚቴዎቹ) መቋቋምና መጠናከር፡- ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ምልዓት ጉባኤው ያሳለፈውን ውሳኔ የሚያስፈጽምና፤ በዚያው ዓመት የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤው፣ የውሳኔውን አተገባበር በመገምገም የሰጠውን አቅጣጫ ያገናዘበ ነው፡፡

ሪፖርቶቹ እንደሚያሳዩት፥ ቋሚ ጉባኤያቱን በጥምረት በማደራጀት የኑፋቄውን ስልቶች የሚያጋልጡና በአኳያውም የኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ሥልጠናዎች በስፋትና በተደጋጋሚ ተከናውነዋል፤ በርካታ የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት ተካሒደዋል፡፡

img_7493

ቀደም ሲል የተሠሩና ውጤት የተመዘገበባቸውን የሥራ ሒደቶች መነሻ በማድረግ፣ በበጀት ዓመቱ አዲስና ውጤት ሊያስመዘግቡ የሚችሉ ሥራዎችን በማቀድ ወደ ተግባር ለመግባት መዘጋጀታችንን ስገልጽ፤ በተለይም በስብከተ ወንጌል አገልግሎትሕዝበ ክርስቲያኑ በስፋት የሚሳተፍበትን አሠራር በመዘርጋት የቤተ ክርስቲያኑን ተጠቃሚነትና የምእመናኑን ፍላጎት የሚያሟላ ሥራ በመሥራት የምናከናውናቸውን ሥራዎች ኹሉ በተቋም ደረጃ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ እንዲኾኑ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስባለኹ/ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ/

የየአህጉረ ስብከቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በየደረጃው በሰጧቸው መመሪያዎች እንዲኹም ከማኅበረ ቅዱሳንና ከፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጥምረት አደረጃጀቶች ጋር በመቀናጀት በተዘጋጁት መርሐ ግብሮች፥ የአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ ካህናትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ድጋፍና ተሳትፎ አድርገዋል፤ የሰንበት ት/ቤቶች፣ የአጥቢያ ማኅበራትና ምእመናንም ኑፋቄውን በንቃት ለመከላከል፣ ለማጋለጥና ለማምከን የሚያበቃ ግንዛቤ ጨብጠዋል፡፡ “መነሻቸውና መድረሻቸው የማይታወቁ ሕገ ወጥ ሰባክያንን” ለመግታት ተችሏል፡፡

በተለይ የጅማ እና የምዕራብ ወለጋ አህጉረ ስብከት፡- “የኑፋቄውን እርሾ ከማጽዳት” እና “እንዳያንሰራራ መዋቅሩን ነቅሎ ከማስወገድ” ጀምሮ “ስም አጠራሩን ከምድረ ገጽ እስከ ማጥፋት” የደረሰ ውጤት መመዝገቡን ሲያበሥሩ ጉባኤተኛው የጋለ ድጋፉን ገልጾላቸዋል፡፡

የምዕራብ ወለጋው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ፣ ቁርጠኛ አመራር በሰጡበትና በቅርበት በተከታተሉት የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዘመቻ፣ ኑፋቄው ምንጩ እየደረቀ ነው፡፡ ለወደፊቱም፣ ትልቁ ሥራና ዋነኛው ተግባር፣ “የተሐድሶን እርሾ ከቤተ ክርስቲያናችን ማጽዳትና እንዳያንሰራራ ነቅሎ መጣል ነው፤” ያለው ሀገረ ስብከቱ፣ ወዳጅም ጠላትም ይስማ! ሀገረ ስብከታችን ለተሐድሶ መናፍቃን ቦታ የለውም!በማለት ነው ያስጠነቀቀው፡፡

በጅማ ሀገረ ስብከት፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን ስም አጠራር ከምድረ ገጽ ያጠፋው ደግሞ፡- ለስብከተ ወንጌል ቅድሚያ እንስጥ የሚለው የብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ እስጢፋኖስ ኃይለ ቃል እንደኾነ በሪፖርቱ በቀዳሚነት ተጠቅሷል፡፡ የኑፋቄውን ባሕርያትና ስልቶች የሚያጋልጥ፣ “ጥልቀትና ምጥቀት ያለው ማብራሪያ” የተሰጠባቸው ሥልጠናዎች መካሔዳቸውን ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡ 17 የወረዳ ሊቃነ ካህናት፣ 58 ሰባክያነ ወንጌል፣ 35 የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ 85 የሰንበት ት/ቤቶችና የማኅበራት ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የ48 ታላላቅ አድባራት ሰበካ ጉባኤያት አባላት በሥልጠናዎቹ ተሳትፈዋል፡፡ ከዚኽም የተነሣ፣ በሀገረ ስብከታችን÷ ተሐድሶ የሚባል ስም አጠራሩ ከምድረ ገጽ ጠፍቷል፤ ብሏል – ሪፖርቱ፡፡

በአሶሳ ሀገረ ስብከት፣ አንድ በጎ አድራጊ በለገሱት 150ሺሕ ብር ድጋፍ፣ ከየአድባራቱ ለተውጣጡ 360 ካህናትና የሰበካ ጉባኤያት አባላት፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን የጠነሰሱትን ድብቅ ሤራ የሚያጋልጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተካሒዷል፤ ሕዝበ ክርስቲያኑንም በኑፋቄው ከመሰናክል ለመታደግ ተችሏል፡፡

በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት፣ በሚዘጋጁ የፀረ ተሐድሶ ጉባኤያት የሰንበት ት/ቤቶች ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ በብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሃም መሪነት፣ በርካታ ምእመናን የተሳተፉበት የኹለት ቀናት ሥልጠናዊ ጉባኤ ተከሒዷል፤ ለኹሉም የሰንበት ት/ቤቶች፣ ኹለገብ የኾነ ትምህርት የሚሰጡ መምህራን ተቀጥረውላቸዋል፡፡

በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት፣ ሜጫ ወረዳ መርአዊ ከተማ ማኅደረ ስብሐት ለማርያም ደብር፣ 712 ሊቃውንት የተሳተፉበት ሥልጠናዊ ጉባኤ ተካሒዷል፡፡ በኑፋቄው ሲጠረጠሩ የነበሩ ስምንት ካህናት በብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሃም ቀኖና ተሰጥቷቸው፣ አምስቱ ሲመለሱ ሦስቱ በቀኖና ላይ ይገኛሉ፡፡ በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት፣ በወቅታዊ የኑፋቄው እንቅስቃሴ ዙሪያ የኹለት ቀናት፤ በደጋ ዳሞት ወረዳ፣ በተዋሕዶ እና በቅባት ልዩነት ለ700 ሊቃውንት የኹለት ቀናት ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡

በጉራጌ ሀ/ስብከት፣ የዕውቀትና የአመለካከት ችግር የታየባቸው፤ ኦርቶዶክሳዊ ዶግማን፣ ቀኖናንና ትውፊትን የሚያዛቡ፤ በሰበካ ጉባኤና በሰንበት ት/ቤቶች መካከል መዋቅራዊ አሠራርን የሚያውኩ ሰባክያን በብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቀሌምንጦስ በተመራው የአስተዳደር ጉባኤ መታገዳቸው ታውቋል፡፡ የችግሩ ሰለባዎች በቀኖና፣ ምክርና ተግሣጽ እንዲስተካከሉ የተደረገ ሲኾን፣ ለወደፊቱም ሰፊ ሥልጠና ለመስጠት መርሐ ግብር ተነድፎ ለተፈጻሚነቱ እየሠራ እንዳለ ሀገረ ስብከቱ በሪፖርት ጠቁሟል፡፡

35th-pat-gen-assembly3
በማዕከልም፣
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሊቃውንት ጉባኤ መምሪያ፡- ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን፣ የኑፋቄአቸውን የተለያዩ አንጃዎች አስተባብረው በመምራትና በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ግንባር በመፍጠር፣ “ለመጨረሻው ማጥቃት ተዘጋጅተንበታል” ላሉበት “የእምነት መግለጫቸው”፤ የምላሽ ጽሑፍ አሰናድቶ ማጠናቀቁን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡

የኑፋቄው ግንባር ቀደም መሪዎች፣ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ በሚል ርእስ ላዘጋጁት የስሕተት ጽሑፍ፣ የተሰጠው ምላሽ በ55 ገጾች የተሰናዳ ሲኾን፣ ለሚመለከተው ክፍል እንደተላለፈ በሪፖርት ተጠቅሷል፡፡ የጽሑፍ ምላሹ በቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አካል ተረጋግጦ ለኅትመት ሲበቃ፣ የአህጉረ ስብከቱን የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤያት ተጋድሎ ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ይታመናል፡፡

መምሪያው በተጨማሪም፣ በትምህርተ ሃይማኖት፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያንና በክብረ ቅዱሳን ተጠርጥረው መረጃ በተጠናቀረባቸው አምስት ግለሰቦች ላይ የቀረበውን ሰነድ በመመርመር፣ ተጠርጣሪዎቹንም ጠርቶ በመጠየቅ እንደየኹኔታው የውሳኔ ሐሳብ አስተላልፏል፡፡ በተለያዩ ዘማሪዎች የተዘጋጁ መዝሙሮችን አርሞና አስተካክሎ ለኅትመት እንዲበቁ ሲያደርግ፣ በአምስት ግለሰቦች የቀረቡ የመጽሐፍ ረቂቆችም፣ በአግባቡ እንዳልተዘጋጁ ገምግሞ መልሷል፡፡

የስብከተ ወንጌል መምሪያ በበኩሉ፣ በዐበይት በዓላት፣ በአጽዋማትና በቤተ ክርስቲያናችን ቴሌቭዥን የሙከራ ሥርጭት፣ የሰባክያነ ወንጌል ምደባና ስምሪት በመመሪያው መሠረት መፈጸሙንና ማስፈጸሙን፤ የአህጉረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ሥራዎችን መከታተሉንና መገምገሙን፤ የሰባክያን ሥልጠናዎችንና የልምድ ልውውጥ ስብሰባዎችን እንዳዘጋጀ በሪፖርቱ አስፍሯል፡፡

በፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተጋድሎው እነኚህ ተስፋ ሰጪ ድሎች በአህጉረ ስብከቱ ቋሚ ጉባኤያት ይመዝገቡ እንጂ፣ አሳሳቢ ችግሮችና መሰናክሎች ማጋጠማቸው አልቀረም፡፡ የከፋ ሀገረ ስብከት፣ በተጠናከረ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት 4ሺሕ450 ሐዲሳን አማንያንን ከክሕደትና ከኑፋቄ መልሶ ለአሚነ ሥላሴ ያበቃ ቢኾንም፣ የኑፋቄው እንቅስቃሴና ቅሠጣው በከፍተኛ ኹኔታ እየተፈታተነው እንዳለ ገልጧል፤ የፈለሱ ምእመናንን በአኃዝ ባያቀርብም፣ “ቁጥራቸው ቀላል አይደለም” ነው ያለው፡፡

የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኝ መኾኑ ተረጋግጦ ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተባረረው ከፍ ያለው ቱፋ፣ በምዕራብ ሐረርጌ ሀ/ስብከት አሰበ ተፈሪ ከተማ ከሚገኙ የኑፋቄው ተጠሪዎች ጋር በመመሳጠር፣ 18 የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችን አደራጅቶ በግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሲቀሥጥ እጅ ከፍንጅ ተይዟል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ሠራተኞችና በደብሩ ሰበካ ጉባኤ ክትትልና አመልካችነት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲውል ተደርጎ ክሥ ከተመሠረተበት በኋላ ግን፣ “ምክንያቱ ሳይታወቅ” ከአምስት ቀናት እስር በኋላ እንደተለቀቀ በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡

በዳውሮ ሀ/ስብከት ከፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ተፈጥሯል የተባለው “ትርምስና ሁከት”፣  በሀገረ ስብከቱ ጠቅላላ ጉባኤ ታይቶ የመፍትሔ አቅጣጫ እንደተሰጠበት ተገልጧል፡፡ ይኹንና የኑፋቄው ተከታዮች፡- በዛቻ፣ ቤት ለቤት ጉዞ በማድረግ ባለትዳርን በማለያየት፣ አገልጋይ ካህናት እቤታቸው ድረስ ገብቶ በማነቅ፣ ማዕተባቸውን በመበጠስ፣ ሥዕለ አድኅኖን በመቅደድና በመደብደብ ጥቃት እያደረሱ እንደኾነ በሪፖርቱ ተዘርዝሯል፡፡

በተለይም ጥቃቱ፣ በሎማ ወረዳ የኮይሻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ካህን ላይ በአስከፊ ኹኔታ ከመፈጸሙም በላይ፣ በማኅበራዊ ኑሯቸውም እንዲሸማቀቁና እንዲገለሉ መደረጋቸውን አስረድቷል፡፡ ጉዳዩ በሃይማኖት ተቋማት ፎረም ቢታይም ባለመፈታቱ፣ በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ በኩል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እንዲያውቁት ተደርጎ ለመንግሥት ደብዳቤ ተጽፏል፡፡ ነገር ግን፣ “እስከ ዛሬ ድረስ የተገኘ ምላሽ አለመኖሩን” ሀገረ ስብከቱ ገልጾ፣ “የነበረንን መልካም የኾነውን ግንኙነት ግን እያጠናከርን መምጣት እንዳለብን ወስነን በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፤” ብሏል፡፡

አጠቃላይ ጉባኤው፣ ነገ፣ ኃሙስ ጥቅምት 10 ቀን በሚያጠናቅቀው 35ኛ ዓመታዊ ስብሰባው፣ አህጉረ ስብከቱ በኑፋቄው ላይ ላስመዘገቡት ውጤት አጽንዖት በመስጠት፣ የተጋድሎውን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ የጋራ አቋም መግለጫ እንደሚያወጣና ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በመቋቋም ረገድም ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡

Advertisements

5 thoughts on “አህጉረ ስብከት: በፀረ – ተሐድሶ ኑፋቄ ተጋድሎ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን አስታወቁ

 1. Anonymous October 19, 2016 at 11:28 pm Reply

  ምድረ ገጽ አይባልም ገጸ ምድር እንጂ ።

 2. Egualetsyone October 20, 2016 at 3:28 am Reply

  So nice struggle antitehadiso! Keep it up!

 3. Anonymous October 20, 2016 at 7:56 am Reply

  amlakachen bete kerestaneyachen yetebekelen leba na acheberbarin yastedalen

 4. Anonymous October 20, 2016 at 2:01 pm Reply

  እግዚአብሔር አምላክ ቢዘገይ በእኛው ምክንያት እንጂ በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን አይተዋትም፡፡ የአባቶችና የማኅበረ ቅዱሳን የሰንበት ት/ቤቶችና የትጉሃን ምዕመናን ጥረት ተስፋም የትም አይቀርም፡፡ አባቶቻችን በርቱልን፡፡ አሸናፊ ዘ አዲስ አበባ

 5. temesgenz October 20, 2017 at 3:24 pm Reply

  ጅማ ምን ሰራ በጸረ ተሐድሶ ? መናፍቃን እንደ ፈለጉ የሚጨፍሩበት ሀገረ ስብከት ጅማ አይደለም፡፤ሊቀጳጳሱ ሰልጣኞችን እንደ በጋሻው ሁኑ በማለት አይደለ የመረቁት( ናትሪ ገብርኤል የክረምት ሰልጣኞችን) የውሸት ሪፖርት ነው

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: