35ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጀመረ፤ ጸሎተ ምሕላ ከማወጅ ጋር ትልቅ የሰላም አጀንዳ ቀርጾ መወያየት ይጠበቅበታል!

 • የሰላም ዕጦት ቤተ ክርስቲያኒቱን እየለበለባት ነውና ከዳር ቆማ የምታይበት ሰዓት አይደለም
 • መንግሥት ሲናገር በመናገር፣ ዝም ሲልም ዝም በማለት የሚታለፍ ጉዳይ መኾን የለበትም
 • የችግሩን መንሥኤ አጥንታ መፍትሔ በማመንጨት፣ በያገባኛል ስሜት ልትንቀሳቀስ ያሻል
 • መሪዎችዋ፥ በአንድ ልብ ሊወያዩ፣ ያለአድልዎ ኹሉንም ሊያስተምሩና ሲገሥጹ ያስፈልጋል
 • ምሕላ ከማወጅ ባሻገር፣ በግጭቱ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍ አለኝታነቷን ማሳየት ይገባታል

  *                 *               * pat-gen-assembly2009

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መተዳደርያ ደንብ ቃለ ዓዋዲ ድንጋጌ መሠረት፣ በየዓመቱ ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የሚካሔደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ ዛሬ፣ ጥቅምት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠዋት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የስብሰባ አዳራሽ ተጀምሯል፡፡

ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመምሪያዎች፣ ድርጅቶችና አገልግሎቶች ዋና ሓላፊዎች ጀምሮ ከ49 የሀገር ውስጥና የውጭ አህጉረ ስብከት የተውጣጡ ከአንድ ሺሕ ያላነሱ፡- የሰበካ ጉባኤያት፣ የካህናት፣ የስብከተ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤቶችና የምእመናን ተወካዮች የሚሳተፉበት ነው – አጠቃላይ ዓመታዊ ጉባኤው፡፡

የጉባኤው ርእሰ መንበር ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በመክፈቻ ቃለ በረከታቸው፣ “ሰበካ ጉባኤ፣ እኛ ካህናት ሀብታሞች መኾናችንን ያረጋገጠ ወንጌላዊ መሣሪያ እንደኾነ ከቶውንም ልንዘነጋ አይገባም፤” ብለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ ላቀ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የዕድገት ደረጃ በማሸጋገር ሉዓላዊ ክብሯን ለማረጋገጥ ብቸኛውና ዋነኛው ቁልፍ ሰበካ ጉባኤ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም፣ ሰበካ ጉባኤ፣ ትልቅና አስተማማኝ የሀብት ምንጭ መኾኑ ተረጋግጦ ባለበት ኹኔታ፣ ዕድገቱ አዝጋሚ ኾኖ መታየቱ፣ ችግሩ የኛ እንጂ የመሠረተ ዓላማው አለመኾኑን ገልጸው፣ ካህናት ሁሌም መጨነቅ ያለባቸው ስለ ሀብት ሳይኾን ስለ ምእመናን ጥበቃ እንደኾነ ጠቅሰዋል፤ ሌት ተቀን ምእመናንን እንደ እግዚአብሔር ቃል በመጠበቅና በመንከባከብ ማገልገል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን አንድነቷንና አስተዳደሯን ለማጠናከር የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤን በማቋቋም ከምንጊዜውም በላይ አገልግሎቷን አጠናክራ መቀጠሏን የጠቀሱት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአጠቃላይ ጉባኤው ሊቀ መንበር ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ በዓመታዊ ስብሰባው ላይ ከየአህጉረ ስብከቱ የሚቀርቡ ዘገባዎች ተደምጠው በጉባኤው ውይይት ይደረግባቸዋል፤ ብለዋል፡፡

በስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር የታዩ ውጤቶችና ተሞክሮዎች በሚገባ ተደራጅተውና ተቀምረው፣ የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንደሚመክርባቸውና በአጠቃላይ ጉባኤው የውሳኔ ሐሳብ የቀረበባቸው ጉዳዮችም በምልዓተ ጉባኤው ትኩረት እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡

የአጠቃላይ ጉባኤው አዘጋጅና አስተናባሪ የኾነው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፣ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ተቋማትን በልማት አስፋፍታ ለምእመናን ተደራሽ መኾን በክርስቶስ የተሰጣት ሓላፊነት መኾኑን በመልእክታቸው ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ቀዳሚ ሀብቶቻችንን ምእመናንን በማስተባበር መንፈሳዊ አገልግሎታችንን ሊያፋጥንልን ስለሚችለው ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በዓመታዊ ስብሰባው፣ የቤተ ክርስቲያናችን የበጀት ዘመኑ የሥራ ውጤቶች እንደሚገመገሙና አንዱ ሀገረ ስብከት ከሌላው ልምድ የሚቀስምበት እንደሚኾን ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን አመልክተዋል፡፡

ከማደራጃ መምሪያው ያለፈው ዓመት ዕቅዶች ዋነኛው፡- የካህናት፣ የምእመናን፣ የአብያተ ክርስቲያናትና የገዳማት ቁጥርና ያሉበት ኹኔታ፤ የተጓደለባቸውን መንፈሳዊ አገልግሎት ቦታው ድረስ ሔዶ መዝግቦ ማወቅ እንደነበር ዋና ሓላፊው አስታውሰዋል፡፡

ዕቅዱን ለማከናወን በኃምሳውም አህጉረ ስብከት ጥረት መደረጉን ጠቅሰው፣ ወጣቶችን፣ ምእመናንንና ካህናትን በማስተባበር የሠሩትን አህጉረ ስብከትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አመስግነዋል፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያት ሳያከናውኑ የቀሩ አህጉረ ስብከት፣ በዚኽ ዓመት ለመሥራት ሊተጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የማደራጃ መምሪያው ዋና ጸሐፊ መምህር ማርቆስ ተበቃ በበኩላቸው፣ ለ35ኛው ዓመታዊ ስብሰባ ተዘጋጅቶ በተሠራጨው “ዐዋጅ ነጋሪ” መጽሔት ላይ ባሰፈሩት አጭር ጽሑፍ፣ የሰላም ጉዳይ፣ የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ በመኾኑ፣ የቤተ ክርስቲያናችን መሪዎችና አካላት፣ ትልቅ አጀንዳ ቀርጸው መወያየት እንደሚበጠቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

የሰላም ዕጦት ቤተ ክርስቲያኒቱን እያቃጠላት ባይኾንም እየለበለባት ስለኾነ፣ ተዳር ተቁሞ የሚታይበት ሰዓት አይደለም፤ ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ጸሎተ ምሕላ ከማወጅ ባሻገር፣ የችግሩን መንሥኤ በራሷ አጥንታ የመፍትሔ ሐሳብ ልታመነጭ፣ ለተግባራዊነቱም መንቀሳቀስ እንደሚጠቅባት፤ በየአካባቢው በተከሠቱ ግጭቶች ምክንያት ለኅልፈት በተዳረጉት ወገኖች የተጎዱ ቤተሰቦችንም በሐሳብና በማቴሪያል በመርዳት አለኝታነቷን ልታሳይ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ባቀረቡት የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሪፖርት የተጀመረው ዓመታዊ ስብሰባው፣ እስከ ኃሙስ ጥቅምት 10 ቀን በሥራ ላይ ይቆያል፡፡ በቀጣይም የውስጥና የውጭ አህጉረ ስብከት የሚያቀርቧቸውን የሥራ ሪፖርቶች አዳምጦ፣ በመጪው ዓርብ ጥር 11 ቀን በመክፈቻ ጸሎት ለሚጀመረው የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የውሳኔ ሐሳብና የጋራ መግለጫ በማውጣት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡


ወቅቱ ምን ይላል?

መምህር ማርቆስ ተበቃ
/የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ጸሐፊ/

mmr-markos-tebeka
እነኾ ቤተ ክርስቲያናችን፣ መሪዎች ልጆቿንና የአህጉረ ስብከት ተወካዮችን፣ በአንድ መድረክ አሰባስባና አገናኝታ፣ ስላለፈው በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምና ስለ መጭው ጊዜ የሥራ ዕቅድ የምታወያይበት፣ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 35ኛ ዓመታዊ ስብሰባዋን፣ ጥቅምት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ለማካሔድ ቀጠሮ አስይዛ ቀኑ ዛሬ እውን ሆኗል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በአጠቃላይ ጉባኤው ወቅት፣ ብዙ ጉዳዮች እንዲመለሱ ትጠብቃለች፡፡ በተለይም የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ በኾነው በሰላም ዙሪያ፣ የሰላም ጉዳይ ሁሉንም ፍጥረት የሚነካ እንደመኾኑ መጠን፣ መሪዎችና የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ትልቅ አጀንዳ ቀርጸው መወያየት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ስለ ሰላም፣ ከማንኛውም ተቋም ይልቅ ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ ያሳስባታል፤ ምክንያቱም፣- ሰላም ከሌለ፣ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” ብሎ ለማስተማር መድረክ አይኖርም፡፡ ወንጌልን ማስተማር ከሌለ ተከታይ ምእመን አይኖርም፤ ምእመናን ከሌሉ ቤተ ክርስቲያን የለችምና ነው፡፡ በሰላም ጉዳይ ላይ የቤተ ክርስቲያን አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደ መኾኑ መጠን፣ የችግሩን መንሥኤ በማጥናትና የመፍትሔ ሐሳብ በማመንጨት፣ ለመፍትሔው ተግባራዊነትም በያገባኛል ስሜት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ፤ በሰላም ዕጦት ምክንያት ለኅልፈት ለተዳረጉት ወገኖቻችን ጸሎተ ምሕላ ከማወጅም በላይ፣ ለቤተሰቦቻቸው በሐሳብና በማቴሪያል አለኝታነቷን ማሳየት ይገባታል፡፡ በተጨማሪም የሰላም ዕጦት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን እያቃጠላት ባይኾንም እየለበለባት ስለኾነ ተቀዳር ተቁሞ የሚታይበት ሰዓት አይደለም፡፡ መንግሥት ሲናገር በመናገር፣ መንግሥት ዝም ሲል ዝም በማለት የሚታለፍ ጉዳይ መኾን የለበትም፡፡ ይልቁንም፣ “ኢታድልዉ ለገጸ ሰብእ” የሚለውን መጽሐፋዊ ቃልን በመመርኮዝ፣ በእውነተኛ አካሔድ፣ አንተም ተው፤ አንተም ተው ሊባል የሚገባውን አካል በማነጋገር ሰላም እንዲፈጠር መጣር ይገባል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ይህን ተግባራዊ ለማድረግና ውጤታማ ለመኾን የምትችለው፡-

 • መሪዎች ልጆችዋ በአንድ ልብ ኾነው ሲጾሙና ሲጸልዩ፤
 • በአንድነት መፍትሔ ሲፈልጉ፤
 • እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው ሲወያዩ፤
 • ከፖለቲካዊ አስተሳሰብ ነጻ ኾነው እንደ ሃይማኖቱ አስተምህሮ በፍጹም የርኅራኄ መንፈስ ያለአድልዎ ኹሉንም በማቀፍ ሲረዱና ሲደግፉ፤ ሲያስተምሩና ሲገሥጹ ነውና፤ በ35ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ብዙ ይጠበቃል – ይላል ወቅቱ፡፡

“ሰላም ለኵልክሙ፤ ምስለ መንፈስከ”

Advertisements

2 thoughts on “35ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጀመረ፤ ጸሎተ ምሕላ ከማወጅ ጋር ትልቅ የሰላም አጀንዳ ቀርጾ መወያየት ይጠበቅበታል!

 1. Anonymous October 18, 2016 at 7:21 am Reply

  ye Ethiopia mengest yikuwakuwam:: hizb aygedel:: Ethiopiawyan leweyane aygezu::

 2. Egualetsyone October 19, 2016 at 1:19 am Reply

  Bettam tiru melekt yalew hasab new! Bezihu ketilu, ketayun yemenfesawi gubaewin wutet akrbulin. Egzeabher yebarkachihu!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: