የመስቀሉ ሰዎች፣ በመሸነፍ ውስጥ ማሸነፍ እንዳለ ይናገሩ! በመሸነፍ አሸናፊነት ለኢትዮጵያችን እንበጃት!

meskel-demera2009

የ፳፻፱ ዓ.ም. መስቀል – ደመራ በዓል፣ በአዲስ አበባ መስቀል ዐደባባይ

  • መስቀልን ስናከብር፡- ማኅተመ ፍቅር፣ ትእምርተ ሰላም፣ ትእምርተ መዊዕ መኾኑን እናስባለን
  • የሰው ልጆችን በፍቅር ዐይን መመልከት፣ በማኅተመ መስቀሉ የምናስረግጠው ዐቢይ ጉዳይ ነው
  • የጎሰኝነት አዋራን፣ ከደመራው በሚነሣው የዕጣን ጢስ ጥዑም መዓዛ ሳንተካ ማለፍ አይገባንም
  • በአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች መሀል ጠብ የሚዘራው ርኩስ መንፈስ በመስቀሉ ሊወገዝ ይገባዋል

*                       *                      *

  • በመንፈሰ ኤልያስ የሚሔዱና በመጥምቁ ዮሐንስ ጥብዓት የሚናገሩ ሰባክያነ ሐዲስ ያስፈልጋሉ
  • ስብከተ መስቀሉ የዐደባባይ ነውና፣ ጸዋርያነ መስቀል ነቀፋ ካለበት አሰላለፍ ሊታረሙ ይገባል
  • የመስቀሉ ሰዎች ራሳቸው ቀድመው ይቅር መባባል አለባቸው፤ ሳይታረቁ ማስታረቅ አይቻልም
  • የሕዝብን ጥያቄ በመቀበል እና ጥያቄንም ለሀገር ጥቅም በማስገዛት፣ ለኢትዮጵያችን እንበጃት!

*                       *                      *

የመስቀሉ ሰዎች፣ በመሸነፍ ውስጥ ማሸነፍ እንዳለ ይናገሩ! በመሸነፍ አሸናፊ ኾነን ለኢትዮጵያችን እንበጃት!

/ዲያቆን ዓባይነህ ካሴ/

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችኹ!

የዘንድሮ በዓለ መስቀል በዐደባባይም ይኹን በቤት ሲከበር በአእምሮ የሚጉላላ (የሚወጣ እና የሚወርድ) አንድ ብርቱ ጉዳይ በጀርባው ታዝሎ ይታያል፡፡ እርሱም ወቅታዊው ነገረ ኢትዮጵያ ነው፡፡ እኛ ክርስቲያኖች መስቀልን ስናስብ፣ ወይም በአንገት ማዕተብ ስናደርግ፣ ወይም ስንሳለም፣ ወይም ስናማትብ፣ ወይም ከእግረ መስቀሉ ወድቀን ስንማፀን፤ ሦስት ዐበይት መራሕያን ጉዳዮችን በልባችን ጠብቀን ነው፡፡ እርሱም መስቀል – ማኅተመ ፍቅር፣ መስቀል – ትእምርተ ሰላም፣ መስቀል – ትእምርተ መዊዕ የሚሉትን ያጠቃልላል፡፡ በእነዚህ ላይ ነገረ ኢትዮጵያ ታዝሎ ይታሰበናል፡፡

እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍጹም ፍቅር የተገለጠው በመስቀል ላይ ሲኾን፣ ይህን መደምደሚያነቱን ለማጠየቅ የፍቅር ማኅተም ብንለው የሚገባ ነው፡፡ እኛም የክርስቶስ ተከታዮች ነን እስካልን ድረስ የፍቅር ማኅተሙ በልባችን ተሥሎ፣ በአእምሯችን ተቀርጾ እንደሚኖር አንጠራጠርም፡፡ በመስቀሉ ማኅተም የምናረጋግጠው ዐቢይ አጀንዳ ቢኖር፣ የሰው ልጆችን ኹሉ በፍቅር ዐይን መመልከትን ይኾናል፡፡ አርኣያችን ወልደ እግዚአብሔር፣ በመስቀሉ ላይ መሥዋዕት ሲኾን፣ ለእገሌ ወእገሌ ተብሎ የተከፈለ አንዳች ነገር አይገኝበትም፡፡ ለኹሉም እኩል የተከፈለ የጋራ ዕሴት ኾኖ የታወጀ የፍቅር ማኅተም ቀርጾ አስረክቦናል፡፡

በቀደምት ሮማውያን የወንጀለኞች መቅጫ የነበረው መስቀል፣ አኹን ታሪኩ እና ግብሩ ሙሉ በሙሉ ተለውጦ ትእምርተ ፍቅር ኾኖ ተሰጥቶናል፡፡ ስለኾነም ይህን የፍቅር ማኅተም፣ በልብሳችን፣ በሰውነታችን፣ በአንገታችን፣ በቤተ ክርስቲያናችን፣ በቤታችን . . . ወዘተ. እያደረግን የፍቅር ፀሩን ዲያብሎስን ከእነጭፍሮች አጋንንቱ እናርቅበታለን፡፡

meskel-demera09

በአ/አበባ ሀ/ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አስተባባሪነት፣ በዛሬው የመስቀል ደመራ ክብረ በዓል መንፈሳዊ ትርዒቶችን ካቀረቡት 5ሺሕ ወጣቶች መካከል፤ በምሥራቅ እና በደቡብ ክፍላተ ከተማ 2ሺሕ500 የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች የቀረበው ያሬዳዊ ወረብ

በዓለ መስቀሉን ስናከብር፣ በመስቀሉ መርሕ እየተመራን መኾን አለበት፡፡ መስቀል የፍቅር መርሕ የተሰበከበት አንዱ ዐውደ ምሕረት እንደ መኾኑ፣ በፍቅር ቃል ታስረንና ተወስነን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ በአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች መካከል ጠብ ሊዘራ የተነሣው ሰይጣናዊ መንፈስ በመስቀሉ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ ኹላችንም የመስቀሉ በረከት ተካፋዮች፣ ከጠብ መራቅ ያለብን ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ልናሳብለው የማንችለው የጎሰኝነትና የጎጠኝነት አዋራ እየቦነነ ይታያል፡፡ ከደመራው በሚነሣው የዕጣን ጢስ ጥዑም መዓዛ እስካልተካነው ድረስ፣ ኹላችንንም የሚያስነጥሰንን አዋራ እየቦነነ እንዳላየን ማለፍ አይገባንም፡፡ የመስቀሉ ሰባኪዎችም ዳር ዳር ማለቱን ትተው ወደ ፍቅር ማዕከል ገብተው የፍቅር ሰባኪዎች የመኾን ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን የመወጣት አጣብቂኝ ላይ መኾናቸውን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ በመንፈሰ ኤልያስ የሚሔዱ ኤልያሳውያን፣ በመጥምቁ ዮሐንስ ጥብዓት የሚሰብኩ ሰባክያነ ሐዲስ ያስፈልጋሉ፡፡

ወቅቱ የዳር ተመልካቾች ጊዜ አይደለም፡፡ መስቀልን ይዞ፣ ‹‹እገሌ የተረታ እንደኾነ እገሌ አሸናፊው ይቀየመኛል›› የሚል የመሐል ሰፋሪ ጨዋታ መጫወት አይቻልም፡፡ መስቀል ለእውነት እንጂ ለተለየ ወገን አያደላም፡፡ ዛሬም ጥንትም መድኃኒትነቱ ለኹሉም ነው፡፡ እናንተም ባለመስቀሎች የኹሉም መኾንን ታሳዩ ዘንድ ጊዜው በዐቢይ ዜማ ይጠራችኋል፡፡ አድልታችኹ ቆማችኹ ከኾነ ለተገፋው መኾኑን አረጋግጡ፡፡ ከዚኽ ውጭ ባለ መደብ ራሳችኹን መድባችሁ ወይም ተመድባችኁ ከኾነ ግን ራሱ መስቀሉ ይቃወማችኋል፡፡ እንደዚኽ ያለው መልእክት ከዚኽ ቀደም ክህነታዊ ተልእኳቸውን ወይም ኖላዊነታቸውን አክብረው ብቅ ያሉትን በጣት የሚቆጠሩትን አይመለከትም፡፡ በቀረው ግን፣ በዚኽም በዚያም ነቀፋ ባለበት አሰላለፍ የተሰለፋችኹ ጸዋርያነ መስቀል ግን ደጋግማችኹ ታስብቡት ዘንድ ጥቂት ዕድል ብቻ እንደቀረችላችኹ ይሰማኛል፡፡ ቀን ያልፋል፣ ታሪክም ይወሳል፡፡

ኹለተኛው መርሕ፣ መስቀልትእምርተ ሰላም የሚለው ነው፡፡ አዎ፣ መስቀል የሰላም ምልክት፣ የሰላም ዓርማ፣ የሰላም ሰንደቅ መኾኑ የታመነ እና የተገለጠ እውነት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ገብረ ሰላመ በደመ መስቀሉ = በመስቀሉ ደም ሰላምን አደረገ ሲል መናገሩም ይህን ያጠይቃል፡፡ በመስቀል ሰው እና እግዚአብሔር፤ ምድር እና ሰማይ፤ ሰው እና መላእክት ታርቀውበታል፡፡ ለዘመናት የዘለቁ ጠበኞች የታረቁበት የዕርቅ ምልክታችን ነው፡፡ ስለኾነም እኛ የመስቀል ሰዎች በመስቀሉ ሰላም እንኖራለን፡፡

ይህ መርሐ መስቀል በራሱ ወደ አንድ አቅጣጫ እንድንመለከት ያዞረናል፡፡ እርሱም፣ ሰላም ለራቃት ኢትዮጵያ፣ የሰላምን በር እንድንከፍት ነው፡፡ በዋሻ እንደዘጋ ባሕታዊ፣ እየጸልይን ነው፤ ብሎ ማሳበል አይቻል ነገር፡፡ የዐደባባይ ሰዎች ነገራቸውም በዐደባባይ የተገለጠ ሊኾን ይገባዋል፡፡ ይነስም ይብዛም ወቅታዊው አገራዊ ኹኔታ የማያስከፋው የማያሳዝነውም አለ ብዬ አላምንም፡፡ የከፋ እና የከረፋ ንግግር የሚያደርጉትም በየፊናቸው ከመስቀሉ ሰዎች በማይወጣ ቃል ሲናገሩ እየሰማናቸው እንገኛለን፡፡ በዚኽ በኩል ሕዝቡ ኹለት ነገርን ከመስቀሉ ሰዎች ይጠብቃል፡፡

አንደኛው በዚኽም ኾነ በዚያ፣ አንዳንድ የተነገሩ ሰንካላ ቃላት የመስቀሉ ሰዎች ቃል አለመኾኑን ማረጋገጥ እና ኹለተኛው ደግሞ፣ አማናዊው የመስቀሉ ሰዎች ቃል የቱ እንደኾነ መስማት ናቸው፡፡ አለበለዚያ ብዙ የከፋቸው ምእመናን፣ ቀድመው ወይም አልፈው መሔዳቸው አይቀርም፡፡ ያለፈን ትውልድ ልምራ ማለት ደግሞ እንደማይቻል መገንዘብ ግድ እንጂ ምርጫ አይደለም፡፡ ለምን አንድ ሰውስ እንኳ ይሞታል? ለምን ቅራኔ ይፈጠራል? ተኩስ እና ሰላማዊ ሰልፍ ደግሞም ቤት ውስጥ የመዋል ዐድማ ለምን ተበራከቱ? አልሰማና አልዳኝ ያለው ማን ነው? ለምን ሔደን ወይም ጠርተን አንነግረውም? የሚሉ የመስቀሉ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡

በተቃራኒው ግን የመንግሥትን ብቻ እየሰሙ ለመሔድ የሚደረጉ ጥረቶች ወንዝ አይሻገሩም፡፡ አንዳንድ መንፈሳዊ ተቋማትም፣ በብዙ መሰወሪያ ተሰውረው ለመላላክ የሚያደርጉት እኖር ባይነት የማያዋጣቸው መኾኑን መጠቆም ግድ ሳይኾን አይቀርም፡፡ ዐደባባይ የወጣውን ችግር መፍታት የሚቻለው በዐደባባይ እንጂ ተሸፋፍኖ በመሔድ አይደለም፡፡ እከክልኝ ልከክልኽ የሚባለው ፈሊጥ፣ በእንደዚኽ ዓይነት ቀውጢ ሰዓት ምንም ስፍራ አይገኝለትም፡፡ ፈጥነው መታረም ያለባቸው፣ ጊዜ ባያባክኑ ሠናይ ይኾንላቸዋል፡፡

ስብከተ መስቀሉ የዐደባባይ እንጂ የሹክሹክታ አይደለም፤ የሰላም ጥሪውም ሊከናወን የሚገባው በዚያው ፈለግ እንጂ በመሠሪነት አይደረግም፡፡ እንዲኽ ማድረግ በመስቀሉ ላይ ሌላ ነውር መፈጸም ነው፡፡ ያገባኛል ብሎ መሔዱ ተደርጎ ቢኾን ያማረ በኾነ፤ ነገር ግን ተጠርቶ እና አጀንዳ ተቀብሎ ለመሔድ መሰናዳት እጅግ አሳፋሪ ይኾናል፡፡ ካልቻሉ ደግሞ፣ ከነገሩ ጦም እደሩ ባይመረጥም ይሻላል፡፡

meskel-demera-2009c
ሦስተኛው መርሐ መስቀል፣ ትእምርተ መዊዕ (የድል ምልክት ወይም ዓርማ) መኾኑ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት፣ ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩኽ ምልክትን ሰጠሃቸው እንዲል፡፡ በመስቀሉ፣ ኹለት ጠላቶች ተረትተዋል፡፡ ሞት እና ዲያብሎስ፡፡ በሞት የተሸነፉ ጠላቶች ናቸው፡፡ ስለዚኽም በእነርሱ ፊት መስቀል አስደንጋጭነቱ ተነግሮ የሚያልቅ፣ ተተርጉሞ የሚጠገብ አይደለም፡፡ የመስቀሉ ሰዎች ይህን ድል አድራጊነት ሊዘምሩት ይገባል፡፡

አኹን በአገራችን ያለው እልቂት በአሸናፊነት መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ አሸናፊ ለመኾን ግን፣ የግድ አንዱ ገዳይ ሌላው ሟች ኾነው መቅረብ አይጠበቅባቸውም፡፡ ኹለቱም አሸናፊ የሚኾኑበት መድረክ ተዘጋጅቶ ሳለ የአንድ ወገን አሸናፊነት የሚናፈቅበት ምክንያት አይኖርም፡፡ አንዱ፣ የሕዝብን ጥያቄ በፍጹም ልቡ መቀበል፤ ሌላው ደግሞ፣ ጥያቄውን ለኢትዮጵያ ጥቅም ብቻ ማስገዛት!

መንግሥት መሳሳቱን፣ ወይም ጥልቅ ተሐድሶ እንደሚያስፈልገው በተደጋጋሚ እያመነ እንደ ኾነ ይታወቃል፡፡ ታማሚነቱን ማረጋገጡ ሌላ ማረጋገጫ ፍለጋ እንዳንደክም ያደርገናል፡፡ ከዚኽ ቀደም በታሪኩ ኹለት ጊዜ መበስበስ እንዳጋጠመው እና ተሐድሶ እንደሚያደርግ ሲናገር ነበር፡፡ ግን ከመታደስ ወደ ጥልቅ መታደስ ከማደግ ውጭ ያመጣው ለውጥ እንደሌለ እያረጋገጠ ይሰማል፡፡ በዚኽ ጊዜ አሸናፊ የሚኾንበት አንድ ንጹሕ መንገድ እንዳለው ማሳሰብ ይፈልጋል፡፡ አለመቻሉን አምኖ ለሚችል ለመልቀቅ መዘጋጀት፡፡ ይህ በራሱ አሸናፊነት ነው፡፡ እስኪ እንደዚኽ ያለ ጀግና ለመኾን ይዘጋጅ፡፡ ክርስቶስ ሞቶ ማሸነፉን የመስቀሉ ሰዎች ሊናገሩ ይገባቸዋል፡፡ በመሸነፍ ውስጥ ማሸነፍ እንዳለ ይናገሩ፡፡

meskel-demera099
በሌላ በኩልም፣ በዚኽ ወቅት ብድግ ያለ አዲስ ዘውጌኛነትም ሊሸነፍ ይገባዋል፡፡ በምንም መሥፈርት ያለፈው ስሕተት አኹን ትክክል አለመኾኑ የተረጋገጠውን አፈር እየለበሰ ያለውን መልሶ ለማስነሣት መጣር ሌላው ሊሸነፍ የሚገባው ሐሳብ ነው፡፡ እነርሱ ሲተዉ፣ ኢትዮጵያ ከፍ ትላለች፡፡ ለኢትዮጵያችን ሲባል፣ እነዚኽም ተሸንፈው አሸናፊ እንዲኾኑ የመስቀሉ ሰዎች ድምፃቸውን ሊያሰሙ ይገባል፡፡ ጌታችን በመስቀሉ ላይ ዕርቁን ሲፈጽም አንዱ ታራቂ ራሱ ነበረ፡፡ ስለዚኽም ቀድሞ ይቅር አለ፤ የመስቀሉ ሰዎችም ራሳቸው ቀድመው ይቅር ማለት አለባቸው፤ ሳይታረቁ ማስታረቅ አይቻልምና፡፡ ጠላት ድል የሚነሣው በዚኽ መንገድ ነው፡፡ ስለኾነም በመሸነፍ አሸናፊ ኾነን ለኢትዮጵያችን እንበጃት!

መልካም በዓለ መስቀል!

Advertisements

One thought on “የመስቀሉ ሰዎች፣ በመሸነፍ ውስጥ ማሸነፍ እንዳለ ይናገሩ! በመሸነፍ አሸናፊነት ለኢትዮጵያችን እንበጃት!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: