ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት፤ መንግሥትን የሚያዳምጥ ሕዝብ

gondar-protest2

 • ማዳመጥ ማለት፥ ይኹነኝ ብሎ መስማት፤ ሰምቶ ማስተዋል፤ አስተውሎም መመለስ ነው
 • የሕዝብ የመናገር ነጻነት ዋጋ የሚያገኘው፣ በመንግሥት የመደመጥ መብት ሲኖረው ነው
 • የሚያዳምጠው ሲያጣ፣ ራሱን ማዳመጥ ይጀምርና በኋላ የሚኾነውን ለመገመት ያስቸግራል
 • ጠያቂውን የሕዝብ ወገን የችግሩ መነሻ ማድረግ፣ ሕዝብን ያለመስማት ዋና መገለጫው ነው
 • ሕዝብ፣ አክብሮ ይሰማኛል ብሎ የሚያምነውን መንግሥት ያዳምጣል፤ መደማመጥ የጋራ ነው፤

*               *               *

 • የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅኔ ሕዝብ ነውና፣ ሕዝቡን ለማዳመጥ ባለቅኔ መንግሥት ያስፈልገዋል
 • እወደድ ባዮች፣ ለመንግሥት የሚያስፈልገውን ትተው እርሱ የሚፈልገውን ብቻ ይነግሩታል
 • ከሕዝብ መክሮ ከሚፈልገው ይልቅ የተጠየቀውን የመለሰ መንግሥት፣ ሕዝብን የሚሰማ ነው
 • መንግሥት ማዳመጡን በምላሹ ይገልጣል፤ ምላሹ ለማዳመጥ በሰጠው ማስተዋል ይወሰናል
 • ሕዝብ ባለመደመጡ ተስፋ ሲቆርጥ፡- አይቀበለውም፤ ልብ አይለውም፤ ምላሽ አይሰጠውም፡፡

*               *               *

Dn. Daniel Kibret
(አዲስ አድማስ፤ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ቅዳሜ፣ ነሐሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም.)

‹ደንበኛ ንጉሥ ነው› እያልን ‹ሕዝብ ንጉሥ ነው› የሚለውን እንዴት መቀበል ያቅተናል? ‹ደንበኛ አይሳሳትም› እያልን ‹ሕዝብ አይሳሳትም› የሚለውን እንዴት ማመን ይሳነናል?

ሀገር ሰላም እንድትኾን፤ ሰላም ኾናም በብልጽግና ጎዳና እንድትራመድ ከተፈለገ ኹለት ነገሮች ያስፈልጓታል – ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት እና መንግሥትን የሚያዳምጥ ሕዝብ፡፡ ማዳመጥ ከመስማት ይለያል፡፡ መስማት ጆሮ ለተፈጠረለት ኹሉ የሚቻል ነው፡፡ ይህን ጽሑፍ ስናነብ እንኳን፣ ስንትና ስንት ድምፆችን ፈልገንም ሳንፈልግም እንሰማለን፡፡ ማዳመጥ ግን ሦስት ነገሮችን ይፈልጋል፡- ይኹነኝ ብሎ መስማት፤ ሰምቶ ማስተዋል፤ አስተውሎም መመለስ፡፡

ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት ስንልም፣ ይኹነኝ ብሎ ሕዝብን የሚሰማ፣ ሰምቶ ሕዝቡ ምን እንዳለው የሚያስተውልና ከዚያም አስተውሎ መልስ የሚሰጥ መንግሥት ማለት ነው፡፡ ለሕዝብ የመናገር ነጻነት ብቻውን ምንም አያደርግለትም፤ የመደመጥ መብት ከሌለው በቀር፡፡ ሰሚ ከሌለ እንኳን ሕዝብ ፈጣሪ አይናገርም፤ ቢናገርም ጥቅም የለውም፡፡ ለዚኽም ነው ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን፤ መላእክት እስኪፈጠሩ ድረስ ፈጣሪ ፍጥረታትን በአርምሞ ብቻ የፈጠረው፡፡ ለምን? ቢሉ ሰሚ ሳይኖር መናገር ምን ያደርጋል ብሎ፡፡ መላእክት ከተፈጠሩ በኋላ ግን ‹‹ብርሃን ይኹን›› ብሎ ሲናገር እንሰማዋለን፡፡ አኹን ሰሚ ተገኝቷልና መናገር ዋጋ አለው፡፡

ሕዝብም መናገሩ ብቻ ጥቅም የለውም፡፡ የተናገረውን የሚያዳምጠው መንግሥት ያስፈልገዋል፡፡ ሕዝብ የሚያዳምጠው ሲያጣ፣ ጩኸቱን የሚያዳምጠው አጥቶ ቤቱ እንደተዘረፈበት ውሻ ‹‹ነባህነ ነባህነ ከመ ዘኢነባህነ ኮነ፤ ጩኸን ጩኸን እንዳልጮኽን ኾን›› ብሎ አይቀመጥም፡፡ ራሱን በራሱ ማዳመጥ ይጀምራል፡፡

የልቤን መከፋት ሆዴ እያዳመጠ
ሊመረው ነው መሰል ነገር አላመጠ
… የሚል የቆለኛ ፉከራ አለ፡፡ ሰውዬው በልቡ መከፋቱን ለሰው ቢናገር ቢናገር የሚሰማው ዐጣ፡፡ እርሱ ሰሚ ሲያጣ፣ ሆዱ ግን የልቡን መከፋት እየሰማ ይቃጠል ጀመር፡፡ በኋላም ሆዱ እየቆረጠ ሲሔድ ጊዜ ነው እንዲኽ የፎከረው፡፡ ሕዝብ ራሱን ማዳመጥ ሲጀምር፣ ‹ሊመረው ነው መሰል› የሚለው ፉከራ ላይ እየደረሰ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የሚኾነውን ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡

ሕዝብን በርእዮተ ዓለም፣ በሐሳብ እና በአመለካከት አንድ ለማድረግ እጅግ ጽኑ ትግል፣ እጅግ ብርቱ ጥረት፣ እጅግ ብዙ ልፋት ይጠይቃል፡፡ ሕዝብን በቀላሉ የሚያስተባብረው አንድ ነገር ነው – መጠቃት ወይም መገፋት፡፡ ያን ጊዜ ወዲያ ማዶ ኾኖ አንዱ የተጣራውን፣ ወዲኽ ማዶ ኾኖ ሌላው ይሰማዋል፡፡

እዚያ ማዶ ኾኖ አንድ ሰው ተጣራ
እዚኽ ማዶ ኾኖ ሌላ ሰው ወይ አለው
ጎበዝ ተነቃቃ ይህ ነገር ለኛ ነው
… ማለት የሚችለው የሚያዳምጥ መንግሥት ካለ ብቻ ነው፡፡

መንግሥት ሕዝብን ይኹነኝ ብሎ ማዳመጥ አለበት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕዝብ የተናገረው ላይደርሰው ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሕዝብ ያልተናገረውን ሊሰማ ይችላል፡፡ ሕዝብ የተናገረው ለመንግሥት ካልደረሰው ወይም ሕዝብ ያልተናገረውን መንግሥት ከሰማ፣ እወደድ ባዮች ለመንግሥት የሚያስፈልገውን ትተው መንግሥት የሚፈልገውን ብቻ ይነግሩታል ማለት ነው፡፡

ሕዝብ ብዛት ብቻ አይደለም ያለው፤ ውጥንቅጥም ነው፡፡ በእምነት፣ በርእዮተ ዓለም፣ በመፍትሔ አቅጣጫ፣ በባህል እና በቋንቋ፣ በዕውቀት እና በሥልጣኔ፣ በዕድሜ እና በፆታ የተወነቀጠ ነው – ሕዝብ፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ማለት እነዚኽን ኹሉ በየደረጃቸውና በየመልካቸው ማዳመጥ ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ውስጥ መንግሥትን የሚወዱና የሚደግፉ፣ መንግሥትን የሚጠሉና የሚቃወሙም አሉ፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ማለት እነዚኽን በየመልካቸው ማዳመጥ ማለት ነው፡፡

ሕዝቡ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው? ለምን እንዲኽ አለ? ምን ስለሠራኹ ወይም ምን ስላልሠራኹ ነው? የትኛውን ችግሬን ስፈታው የሕዝቡ ጥያቄ ይመለሳል? ብሎ ማስተዋል ነው፣ ሕዝብን ማዳመጥ ማለት፡፡ ሕዝቡ ስላልገባው ነው? ስላልተረዳ ነው? ስላልተማረ ነው? ስላልሠለጠነ ነው? እያሉ ጠያቂውን የችግሩ መነሻ ማድረግ፣ ሕዝብን ያለመስማት ዋናው መገለጫው ነው፡፡ ‹ደንበኛ ንጉሥ ነው› እያልን ‹ሕዝብ ንጉሥ ነው› የሚለውን እንዴት መቀበል ያቅተናል? ‹ደንበኛ አይሳሳትም› እያልን ‹ሕዝብ አይሳሳትም› የሚለውን እንዴት ማመን ይሳነናል?

በደርግ ጊዜ አንድ የገጠር ሕዝብ ያምፃል፡፡ መሬት ሲከፋፈል:- የመሬት ኮሚቴዎች በጉቦ አስቸገሩት፡-
ከዛፍ ወደ ዛፍ ላይ ትዘላለች ጦጣ
መሬትን ያገኘ ኮሚቴን ያጠጣ
ብሎ አዜመ፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ ትንሽ ቆይቶ የመንደር ምሥረታ ተባለና የኖረበትን ቀዬ ልቀቅ ተባለ፡፡
ቤቱን አፍርሱ አሉን የበላንበትን
ማፍረስስ አልጋውን ትኋን ያለበትን
ብሎ አዜመ፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ፣ ልጆችኽ ይዝመቱ ተብሎ ወታደር ተመራበት
ልጅኽን አምጣ ይላል የኛ ዘመናይ
እኔ ልጄን ስወልድ አዋልዶኛል ወይ
ብሎ ገጠመ፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ በመጨረሻ፣ ‹‹ከእንግዲኽ ደርግ ጠላታችን ነው፤ ለጠላታችን ለደርግ አንገዛም›› ብሎ ተማማለ፡፡ ነገሩ እየከረረ መሔዱን የሰሙ ካድሬዎች ወረዱና ሕዝቡን ሰበሰቡት፡፡ ሲነግሩት ዋሉ፡፡ ሲሰማቸው ግን አልዋለም፡፡ ስብሰባው ሲያልቅ፣ ‹ጠላቶቻችን ይውደሙ› ብሎ ካድሬው መፈክር አሰማ፡፡ ሕዝቡም በአንድ ድምፅ እጁን አውጥቶ ‹ይውደሙ› አለ፡፡ ካድሬዎቹም ደስ ብሏቸው ስብሰባውን በመፈክር አሳርገው ሔዱ፡፡ ለአለቆቻቸው ሕዝቡን አሳምነው እንዳስፎከሩት ተናገሩ፡፡ ሕዝቡ ያለው ሌላ እነርሱ ያዳመጡት ሌላ፡፡

ሕዝብን ማዳመጥ ማለት ሕዝብ የሚለውን ለማዳመጥ መቻል ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅኔ ሕዝብ ነውና ሕዝቡን ለማዳመጥ ባለቅኔ መንግሥት ያስፈልገዋል፡፡

ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት፣ ማዳመጡን በሚሰጠው ምላሽ ነው የሚገልጠው፡፡ ምላሹ የሚወሰነው ለማዳመጥ በሰጠው ማስተዋል ነው፡፡ የመጣው ከዚኽና ከዚያ፣ ከነእንቶኔና ከነእንትና ነው ማለቱን ትቶ፣ ሕዝብ ተናግሯል ብሎ የሚያምን ከኾነ፣ ያንንም ይዞ ከየዓይነቱ ሕዝብ ጋር የሚመክር ከኾነ፣ መክሮም መንግሥት የሚፈልገውን ሳይኾን ሕዝቡ የጠየቀውን የሚመልስ ከኾነ፣ ያ መንግሥት ‹ሕዝብን የሚሰማ መንግሥት› ይባላል፡፡

ሕዝብን የሚሰማ መንግሥት፣ መንግሥትን የሚሰማ ሕዝብ መፍጠር ይችላል፡፡ ሕዝብ የሚያከብረውን፣ የሚወደውንና ይሰማኛል ብሎ የሚያምነውን መንግሥት ይሰማል፡፡ መደማመጥ የጋራ ነው፡፡ ሕዝብ ፈጣሪው የሚለውን የሚሰማውኮ፣ ፈጣሪዬ የምለውን ይሰማኛል ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ ፈጣሪ አይሰማኝም ካለማ ፈጣሪውን ማስማት ያቆማል፡፡ ማንም የማያዳምጠውን አያዳምጥም፡፡ ፈጣሪ ‹ኑ እንዋቀስ› ያለው የሚወቀስ ነገር ኖሮት ሳይኾን ሕዝቡን እንደሚያዳምጥ ሲናገር ነው፡፡

Ethiopian-protesters-in-gondar
ሕዝብ፣ መንግሥት አያዳምጠኝም ብሎ ተስፋ ሲቆርጥ፣ ቀስ በቀስ መንግሥትን ማዳመጥ ያቆማል፡፡ መንግሥት የመናገርያ መሣርያ ስላለው ብቻ ይናገራል፤ ሕዝብም ጆሮ ስላለው ብቻ ይሰማል፤ ግን አያዳምጥም፡፡ ነገሩን እውነት ነው ብሎ አይቀበለውም፡፡ ለእኔ ነው ብሎ ልብ አይለውም፡፡ አዳምጦም የሚፈልገውን ምላሽ አይሰጠውም፡፡

አንተ ስትናገር ያልፋል በእኔ ላይ
እኔም ስናገርህ ያልፋል በአንተ ላይ
ከንግዲኽ ኾነናል ወንዝና ድንጋይ
የተባለው’ኮ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ወንዝ በድንጋይ ላይ ሲያልፍ ይጮኻል ግን ድንጋዩ አይሰማውም፤ ድንጋዩም ውኃው በላዩ ላይ ሲያርፍ ይጮኻል፤ ግን ወንዙ አይሰማውም፡፡

ሕዝብን የማያዳምጥ መንግሥት እና እርሱ የሚፈጥረው፣ መንግሥትን የማያዳምጥ ሕዝብ እንዲኽ ናቸው፡፡

Advertisements

8 thoughts on “ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት፤ መንግሥትን የሚያዳምጥ ሕዝብ

 1. Anonymous August 21, 2016 at 4:37 pm Reply

  ቃለ ሕይወት ያሰማልን ወንድማችን! መልእክቱ መሠረታዊና ወቅታዊ ነው፡፡

  ብቻ ‹‹ነባይነ ነባይነ ከመ ዘኢነባይነ ኮነ›› የሚለው የግእዙ ጥቅስ ‹‹ነባህነ ነባህነ ከመ ዘኢነባህነ ኮነ›› ተብሎ ቢስተካከል መልካም ነው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም ግሱ ‹‹ነብሀ – ጮኸ›› እንጂ ‹‹ነብየ – ጮኸ›› አይልምና ይህንን ተከትለው ሌሎችም እንዳይሳሳቱ፡፡

  እግዚአብሔር ለእኛም፣ ለመንግሥትም የሚያዳምጥ እዝነ ልቡናን ያድለን!

 2. Anonymous August 21, 2016 at 5:20 pm Reply

  Dear ato Daniel
  thank U for this statement . ጥሩ ፅሑፍ ነው።
  መንግሥትን ወክለናል የሚሉ ፡የመንግሥትን ተልዕኮ የሚያበላሹ ሆዳሞች ረዳቶችህ ጆሮቻቸውን እንዲከፍት ይጠቅማቸው ይሆናል።
  ጥሩ ቅስቀሳም ነው ሰሚ ካገኘህ።

 3. Anonymous August 23, 2016 at 6:51 am Reply

  ‹‹የተማረ ሰው ታናሹንም ይሰማል!›› እንደሚባለው በእውነት አስተያየቴን ተቀብላችሁ ‹‹ነባይነ›› የሚለውን ወደ ‹‹ነባህነ›› በመቀየር እርማት ስለሰጣችሁ በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ፡፡

 4. Anonymous August 23, 2016 at 1:08 pm Reply

  “ልጅኽን አምጣ ይላል የኛ ዘመናይ
  እኔ ልጄን ስወልድ አዋልዶኛል ወይ” ይህ አባባል በዘመነ መልአኩ ተፈራ የተባለና መባል የነበረበት ነው አሁን አንተ ቀላዋይ ይህ ስትገል ለማንና ለምን መሆኑን አለማስተዋልህ ለነገሩ መች ታስተውላለህና ይህ ትግራዋይ ከመግደል ጋር ምን አገናኘው አሳፋሪ

 5. Kasse August 28, 2016 at 8:54 pm Reply

  እኔ የምለው ያልሰማው የማይሰማው ማን እንደሆነ ግልጽ ነው በትክክል ለማይሰማው መንግሥታችን ብትናገር እስሩን ፈርተህ ነው ወይስ አድርባይነትህ በልጦብህ ነው መናገርህ ካልቀረ እንደ ወንጌል ሰባኪነትህ ብትናገር ስ አለበለዚያ……ትዝብት ነው

 6. Anonymous August 29, 2016 at 11:05 pm Reply

  አባ ሲራክ የወያኔ ካድሬ በወሮሞና በአማራ ስለሞቱት ይትዮጵያዉያን ምህላአደርጋለሁብሎ የሞቱትና ንብረታቸዉ የጠፍባቸዉን እያመሳሰለበመናገሩ የሞተና ንብረቱየጠፋበት አንድባለመሆኑ ብዙክርስቲያኖችንአሣዝኖ ውላል
  አባ ሲራክ
  ምዕመኑን በመከፋፈልና የሙስና ችግሮቻቸው እንዳይጋለጥ ሲሉ የቤተክርስቲያን ልጆችን ከፍራንክፈርት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባረዋል።
  አዲስ ቤተ ክርስቲያን እንዲፈጠር በማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት አናግተዋል።
  በማስተዳደር ላይ በሚገኙት ቤተ ክርስቲያን ከምዕመናን የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ፤ በማዋል ላይም ናቸው።
  የሰበካ ጉባኤውን በፈለጉት ጊዜና በሚፈልጓቸው ሰዎች በመተካት ሰንበት ትምህርት ቤቱንም አፍርሰዋል በአጭሩ ቤቱን በአምባገነንነት እየመሩት ይገኛሉ።
  የቤተክርስቲያኗ ሂሳብ ተወራርዶ የማያውቅ ከመሆኑም በላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቆተ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት ለራሳቸው ደሞዝ እንኳን መክፈል አቅቷቸው ምዕመኑ በየጊዜው እያዋጣ እየደጎመ ይገኛል።
  በቤተክርስቲያኗ ገንዘብ የተገዛችውን መኪና በስማቸው አድርገው ወጪዋን ሁሉ ከደሞዛቸው ውጭ በተጨማሪ ከቤተ ክርስቲያኗ ወጪ እያደረጉ አሁንም እየተገለገሉ ናቸው።
  በቅርቡ የቤተ ክርስቲያኗ አቅም ሲዳከም ብር ማጣት ሲጀመር ለመጀመሪያ ጊዜ ከ፩፮ ዓመት በሁዋላ የባንክ ቡኩን ቤተ ክርስቲያኗን ለማዳን ለተቋቋመው ኮሚቴ አስረክበዋል። ይህ በንዲህ ይሁንና መነኩሲዉ ከዜህ በፌት የዝሙት መንፈስ እዳደረበት ብዙቢባልም እዉነትነው ዉቨትነዉ እያለ የሚጠራጠር መኖሩ አጠያያቂ አይደለም
  ነሀሴ አስራሶስት ፩፫ የድብረታቦርለት ከቤታቸዉ ጥግ የግሬክ ዜጋ የሆነች ዳቦቤት አላት በጡአቱ አባ ዳቦገዝተዉ ሲሂድተገናኝን እኔነኝ እማዉቃቸዉ እሳቸዉ አያዉቁኝም ቤታቸዉም መንገድዳርስለሆነ መስኮት ዘግተዉየሚሠሩት ይታያል ቫልተሩን ዝቅአድርገዉ ቁርሳቸዉን ተያያዙት ከሰሐት የቅዳሴስሐት ደርሶ አባ ቀደሰ
  በኞ ስራት በልቶ መቀደስ አፍርሶመቀደስ አልተለመደምነበረ የሲራክጉድ እወቁትክርስቲያኖች አትሞኞ
  ሌለዉ የሐገራችን ጉደይ ወገኖቻችን እየሞቱ ከሀገራችን ከዚህ ደግሞ ሲራክ ሊገላችሁ አይገባም
  ይህ ለቁሙ የገማ አባ ጪራቅ ከሡ ቡራኬ ሰይሆን መርገምነዉ የምታገኞት ፈረየእግዚአብሔር ስለለዉ ቁርባን
  ብሎ ምን እደሚሰጣችሁ አይታወቅም ባለፈዉ ሀገርቤት በሔደስሀት ደብረብርሀን ጠንቋይ ቤትእደሄደም የሚስጢርጏደኝዉ ተረድተናል ስለዚህ ከሡእድትርቁ እና ወደትክክለኞች ካህናት ሂዳችሁለነፍሳችሁ ስንቅሰንቁላት
  ለትግሬዎች ክርስቲያኖችበጣምአዝናለሁ መነፍሣቸዉም በስጋቸዉም ተጫዎተባቸዉ ሲራክ ሆይ ንስሀግባ
  ተኝተህ ሰይጣን አያንኮራፍብህ

 7. Endeshew Abatenh August 31, 2016 at 12:06 pm Reply

  thank you very much

  2016-08-20 16:59 GMT-07:00 “ሐራ ዘተዋሕዶ” :

  > haratewahido posted: ” ማዳመጥ ማለት፥ ይኹነኝ ብሎ መስማት፤ ሰምቶ ማስተዋል፤ አስተውሎም መመለስ ነው
  > የሕዝብ የመናገር ነጻነት ዋጋ የሚያገኘው፣ በመንግሥት የመደመጥ መብት ሲኖረው ነው የሚያምጠው ሲያጣ፣ ራሱን ማዳመጥ
  > ይጀምርና በኋላ የሚኾነውን ለመገመት ያስቸግራል ጠያቂውን የሕዝብ ወገን የችግሩ መነሻ ማድረግ፣ ሕዝብን ያለመስማት ዋና
  > መገለጫው ነው ሕዝብ፣ አክብሮ ይሰማኛል ብሎ የሚያምነውን መ”
  >

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: