ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾመው ከቆሞሳት መካከል በትምህርቱ በትሩፋቱ ልቆ የተገኘ አባት ነው – ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በምሥጢረ ክህነት እንዳስተማሩት

 • ሐዋርያት ከጌታ በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት ያስሩና ይፈቱ ነበር፡፡ የማሰርና የመፍታት ማለትም አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የመለየት፣ በይቅርታ ወደ ቤተ ክርስቲያን የመመለስ፤ ምሥጢራትን የመፈጸም ተልእኮ እስከ ኅልፈተ ዓለም የሚቆይ ነው፡፡
 • የቤተ ክርስቲያን ክህነት ከምኩራቡ ዘርዐ ክህነት የተለየ ነው፡፡ የምኩራቡ ክህነት፣ ሌዊንና አሮንን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ በእነርሱ የዘር ሐረግ ብቻ የሚተላለፍ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ክህነት ግን ክርስቶስን መሠረት አድርጎ ነው፤ የዘር እና የጐሳ ልዩነት አይደረግበትም፡፡
 • በቤተ ክርስቲያን የዲቁና ማዕርግ የሚሰጠው ከጋብቻ በፊት ነው፡፡ ዲቁናውን እንደተቀበለ ለመመንኰስ ቢፈልግ ገዳም ገብቶ፣ በረድእነት አገልግሎ ይመነኵሳል፡፡ ከመነኰሰ በኋላ የቅስና ማዕርግ ይቀበላል፡፡ ለቁምስናና ለኤጲስ ቆጶስነትም መንገዱ ይህ ነው፡፡
 • ኤጲስ ቆጶሱ በማይገኝበት ቦታ እንደ ኤጲስ ቆጶስ ኾኖ የሚያገለግል ቆሞስ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ይሾማል፡፡ የቁምስና ሹመት የሚሰጠው በኤጲስ ቆጶስ ነው፡፡ ቆሞስ የሚኾኑት በድንግልና የመነኮሱ፣ የቅስና ማዕርግ ያላቸው ናቸው፡፡
 • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት፣ ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾመው፣ ከቆሞሳት መካከል በትምህርቱ በትሩፋቱ ልቆ የተገኘ አባት ነው፤ የሚመረጠውም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ነው፡፡
 • ፓትርያርኩና የአህጉረ ስብከት ጳጳሳት የሚሾሙት፣ በካህናትና በምእመናን ተመርጠው ሲኾን፤ የሚመረጡት፣ በድንግልና መንኵሰው በቁምስና ማዕርግ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ የኖሩ ብቻ ሊኾኑ እንደሚገባ በቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ ተደንግጓል፡፡
 • ኤጲስ ቆጶሱ፣ ቄሱም ኾነ ዲያቆኑ ሲሾሙ፥ ጸሎተ ሃይማኖትን አሰምተው አንብበው፣ ቤተ ክርስቲያን የምትቀበላቸውን ጉባኤዎችና ውሳኔዎቻቸውን ቆጥረው እናከብራለን፤ እናስከብራለን ብለው ቤተ ክርስቲያን የማትቀበላቸውን ግን አውግዘው ይሾማሉ፡፡
 • አባ ጎርጎርዮስ፣ ያገራችንን መንፈሳዊ ዕውቀት በስፋትና በጥልቀት ገብይተዋል፡፡ ብቃታቸው ከተመሰከረላቸው ሊቃውንት ተምረዋል፤ አደላድለውም ተመርቀዋል፡፡ ዘመናዊውንም ትምህርት በየደረጃው ቀስመው በማስትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል፤ ቋንቋዎችንም አጥንተዋል፡፡
 • ልጆቼ ዓለማዬን ተከተሉ” የሚለው አባታዊ ምክራቸው አኹንም በወጣቱ ልብ በየሰንበት ት/ቤቱ ይንቦገቦጋል፡፡ “እኛ የመነኰስነው ለፍትፍት አይደለም፤ የመስቀሉ ፍቅር ይግባችኹ” እያሉ የዘሩት ፍሬ፣ ቢረሱት የማይረሳ፤ እፍ ቢሉት የማይጠፋ የማለዳ ጎሕ ነው፡፡

*               *               *

zena betekirstian's obituary of the late abune gorgoryos

ጳጉሜን 1 ቀን 1982 ዓ.ም. የወጣው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ፣ መልኩም ኾነ ዜናው ከወትሮው ለየት ያለ ነው፡፡ መልኩ የወየበ ደም ይመስላል፡፡ አትኩረው ሲያዩት፣ የደበዘዘ ወይንማ ገጽታ፣ አልያም የገረጣ ሐምራዊ ቀለም ነው፡፡ መልሶ መላልሶ ላስተዋለው በሦስቱም መልክ ኾነ ባንድያው የጌታን ክቡር ደም ያስታውሳል፡፡ በቀራንዮ የፈሰሰውን የክርስቶስ ደም በሕሊና እየሣለ የመሥዋዕትነትን ቅዱስነት በለሆሳስ የሚያስተላለፍ ድምፅ ከወረቀቱ ግዘፍ ነስቶ ይሠርፃል፡፡ ከዚኹ ገጽ፣ በቀኝ ዓምድ በኩል፣ “ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ዐረፉ” የሚል ዜና በጥቁር ቀለም ሠፍሯል፡፡ መስቀሉን በቀኝ እጅ የጨበጠው ምስላቸው ምእመናንን ይሰናበታል፡፡

ዳሩ ግን፣ አባ ጎርጎርዮስ ሊቀ ጳጳስ ዛሬም ሕያው ናቸው፡፡ በሰዎች ልቡና፣ በገዳማት ዐጸድ፣ በአድባራት ዓውደ ምሕረት፣ በቅኔ ማሕሌት፣ በቅድስቱ ዙሪያና በሕገ ታቦታት ማረፊያ መንበር ጭምር ሐዋርያዊ ድምፃቸው ያስተጋባል፡፡ “ልጆቼ ዓለማዬን ተከተሉ” የሚለው አባታዊ ምክራቸው አኹንም በወጣቱ ልብ በየሰንበት ት/ቤቱ ይንቦገቦጋል፡፡ “እኛ የመነኰስነው ለፍትፍት አይደለም፤ የመስቀሉ ፍቅር ይግባችኹ” እያሉ ከጭንጫ ሳይኾን ከጥቂት የለሰለሰ ማሳ ላይ የዘሩት ፍሬ፣ በብዙ ምእመናን ደም ሥር ውስጥ ዛሬም ይዘዋወራል፡፡ ለእርሳቸው የነበራቸው፣ ያላቸውና ወደፊትም የሚኖር ጽኑ ፍቅር፥ በቃለ እግዚአብሔር የተፈተለና በንጽሐ ባሕርይ የተቋጨ ነውና ቢረሱት የማይረሳ፤ እፍ ቢሉት የማይጠፋ የማለዳ ጎሕ ነው፡፡

በሕፃን ልባቸው የመስቀሉ ፍቅር የተለኮሰው አባ ጎርጎርዮስ፣ ያገራችንን መንፈሳዊ ዕውቀት በስፋትና በጥልቀት ገብይተዋል፡፡ ዝናቸው ከታወቀው የተለያዩ የኢትዮጵያ ገዳማትና ብቃታቸው ከተመሰከረላቸው ሊቃውንት ዘንድ፥ ዜማ፣ ትርጓሜ መጻሕፍት፣ አዕማደ ምሥጢር፣ ባሕረ ሓሳብ፣ ቅኔ፣ ትምህርተ ሃይማኖት አጠናቅቀው ተምረዋል፤ አደላድለውም ተመርቀዋል፡፡ ዘመናዊውንም ትምህርት በየደረጃው በብሩህ አእምሮአቸው ቀስመው፣ ከአቴና ዩኒቨርስቲ በቴዎሎጂ(ነገረ መለኰት) በማስትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል፤ ፈረንሳይኛና ዐረብኛ ቋንቋም አጥንተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሣልሳይ ፓትርያርክ በነበሩት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ፣ በ1971 ዓ.ም. ኤጲስ ቆጶስ ኾነው ከተሾሙበት ጊዜ አንሥቶ ሕይወታቸው በመኪና አደጋ እስከአለፈበት እስከ ሐምሌ 22 ቀን 1982 ዓ.ም. ድረስ በጣም ድንቅና ሰፊ መሠረት ያላቸው በርካታ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ ልዩ በኾነና ፍቅርን በተመላ መንፈሳዊ ስሜት ዘወትር እንዲታሰቡ ከሚያደርጓቸው፡- መንፈሳዊ አገልግሎታቸው፣ ትምህርታቸው፣ ሰብአዊ ጠባይዓቸው ጋር የሚጠቀሰው የምርምር፣ የሥነ ጽሑፍና የማስተማር ተሰጥዎአቸው ነው፡፡

ለሕያውነታቸው ኹነኛ ምስክሮች መጻሕፍታቸው ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ብፁዕነታቸው፣ በሕይወት ዘመናቸው ስምንት መጻሕፍትን ደርሰዋል፡፡ እነርሱም፡- መሠረተ እምነት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ ትምህርተ ሃይማኖት(ዶግማ)፣ የስብከት ዘዴ(ኦርቶዶክሳዊ)፣ ቤተ ክርስቲያንህን ዕወቅ፣ ሥርዓተ ኖሎት እና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሲኾኑ፣ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ታትመው ዛሬም በከፍተኛ ተነባቢነት፣ ማመሳከርያነትና መማርያነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክ በስፋት የሚያወሳውና በጥሞና ለዘለቀው ትውልድ ኹሉ “ራስን የማወቅ ግርዶሽ” ለመግፈፍ በእጅጉ በሚረዳው፣ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” መጽሐፋቸው፤ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከግብጥ ቤተ ክርስቲያን 111 ጳጳሳትን ብዙ ወርቅ እየከፈለች እያስመጣች ለ1ሺሕ600 ዓመታት መቆየቷን አንክድም፤” ይላሉ፤ ብፁዕነታቸው፡፡ ኾኖም ጵጵስናን ከእስክንድርያ ማምጣት ክርስትናን ማምጣት አለመኾኑንና ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሐዋርያት ዘመን መኾኑን በአጽንዖት ይገልጻሉ፡፡

የቤተ ክርስቲያን ክህነት እንደ ምኩራብ ክህነት በዘር የሚወርድ አይደለምና፣ ኢትዮጵያ ለጵጵስና ማዕርግ የሚበቁ ልጆች ካሏት ልጆቿን ለመሾም ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የሚፈቅድላት ኾኖ ሳለ፣ “ኢትዮጵያውያን ከሊቃውንቶቻቸው ጳጳሳት አይሹሙ” በሚለው የግብጻውያን ሰው ሠራሽ የፈጠራ ሐረግ ታስራ ለዘመናት በችግር መኖሯን ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሚገልጹት በከፍተኛ ቁጭት ነው፡፡ በቅዱስ ሐርቤ ተጀምሮ በዐፄ ዮሐንስ አራተኛ የቀጠለው፣ “ኢትዮጵያ የራሷን ልጆች ጳጳስ መሾም አለባት” የሚለው ጥያቄ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት፣ አምስት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት፣ ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም. ካይሮ ላይ ሲሾሙ ፍጻሜ ማግኘቱን ብፁዕነታቸው ጠቅሰዋል፡፡

01PatriarchAbuneBasilios1st_jpg
ይኸው ሥርዓተ ሢመተ ጵጵስና፣ “ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት በራሳቸው ሊቀ ጳጳስ መሾም አለባቸው” በሚለው ጥያቄ ተጠናክሮ፣ ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ፣ ጥር 6 ቀን 1943 ዓ.ም. የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሊቀ ጳጳስ ተብለው በካይሮ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ መሠየማቸውን አስፍረዋል፤ በኋላም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፥ በ1951 ዓ.ም. ከሊቀ ጵጵስና ወደ ፓትርያርክነት ከፍ ብላ፣ ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ሊቀ ጳጳስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በመኾን የመንበሩን ነጻነት ስትቀዳጅ፣ ራስን የመቻል ጥያቄዋ ከዳር መድረሱን ያስረዳሉ፡፡

“የቤተ ክርስቲያኒቱ ራስ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፤” የሚሉት ብፁዕነታቸው፣ የምትመራውም ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ተጠንቶና ተረቆ በተጻፈ ሲኖዶሳዊ ሕግ እንደኾነ ያስገነዝባሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመራው ፓትርያርኩና የአህጉረ ስብከት ጳጳሳት የሚሾሙት፣ በካህናትና በምእመናን ተመርጠው እንደኾነና፤ ለፓትርያርክነትም ኾነ ለጳጳስነት ማዕርግ የሚመረጡት፣ በድንግልና መንኵሰው በቁምስና ማዕርግ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ የኖሩ ብቻ ሊኾኑ እንደሚገባ በቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ መደንገጉን በመጽሐፋቸው አስፍረዋል – “ይህም ሕግና ሥርዓት፣ ለመላው የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ተጠብቆ የኖረና የሚኖር ነው፤” ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡

ብፁዕነታቸው፣ “ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን” በሚለው ያልታተመ ሕያው ሥራቸው፣ ስለ ምሥጢረ ክህነት በአጠቃላይና የመጨረሻው የክህነት ማዕርገ ስለኾነው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በተለይ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮና ሥርዓት ከሌሎች ጋር በማነፃፀር አብራርተዋል፡፡ ከወቅታዊው የቤተ ክርስቲያናችን የሐዲሳን ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫና ሢመት አጀንዳ፣ አኳያ ለጡመራ መድረኩ እንዲመች ተደርጎ ቀርቧል፤ እንዲያነቡት ተጋብዘዋል፡፡


ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን

ምሥጢር ማለት ድብቅ፣ ሽሽግ፣ ለልብ ወዳጅ ለቅርብ ዘመድ ካልኾነ በቀር የማይገለጥ ማለት ነው፡፡ በንባብ የተሰወረ ብሂል ምሥጢር ይባላል፤ ምሥጢር ዐዋቂ እንዲሉ፡፡ አስማምቶና አራቅቆ የሚተረጉመው ሊቅ፣ የሰው አእምሮ አስቦና መርምሮ የማይደርስበት የአምላክ ህላዌ፤ የአምላክ ግብርም ምሥጢር ይባላል፡፡ “ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ” ማለት ስለዚኽ ነው፡፡

በሃይማኖት ሥርዓት የጥንት አረማውያን የሚያሟርቱበትን የምትሐትና የጥንቆላ ዘዴ(ሜስቴርዮን) ምሥጢር ይሉት ነበር፡፡ ከሕዝብ የተደበቀ ማለት ነው እንጂ እነርሱስ ያውቁታል፡፡ በብሉይ ኪዳን፣ ምሥጢር የሚል ስም ባይሰጠውም፣ የሚሠዋው መሥዋዕት ምሥጢርነት ነበረው፤ ኃጢአትን ለማስተሥረይ፣ ከእግዚአብሔር ለመታረቅ የሚደረግ ነውና፡፡

ምሥጢር ሊያሰኘው የሚችለው፣ መሥዋዕቱን እግዚአብሔር እንዴት እንደሚቀበለው አይታይም፤ ተቀብሎም ስርየትን መስጠቱ በእምነት እንጂ በዓይን አይታይምና፤ ከኾነ በላይ እንጂ ያን ጊዜ አይታይምና ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን፣ የመንፈስ ቅዱስ የጸጋው ግምጃ ቤት ስለኾነች በመስቀል ላይ የተሰጠውን አምላካዊ ጸጋ በእምነት ለሚቀርቧት ኹሉ ታድላለች፤ ትምህርቷን አምነው የተቀበሉ ኹሉ የዚኽ ጸጋ ተካፋዮች ናቸው፡፡ ይህን ጸጋ ለምእመናን የምታድልባቸውን መሣርያዎች፣ ምሥጢራት ትላቸዋለች፡፡ ምሥጢራት መባላቸውም ስለ ሦስት ነገር ነው፡-

ሀ. ላመኑ እንጂ ላላመኑ አይሰጥምና፤

ለ. በዓይን የሚታየው በእጅ የሚዳሰሰው ግዙፍ ነገር በመንፈስ ቅዱስ ሲለወጥ አይታይምና፤

ሐ. ምእመናን በዚኽ በሚታየው የማይታየውን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ሲቀበሉ አይታይምና፤ ይህም የሚፈጸመው በግብር አምላካዊ ስለኾነ ምሥጢር ይባላል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት ሰባት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

 1. ምሥጢረ ጥምቀት
 2. ምሥጢረ ሜሮን
 3. ምሥጢረ ቍርባን
 4. ምሥጢረ ንስሐ
 5. ምሥጢረ ቀንዲል
 6. ምሥጢረ ክህነት
 7. ምሥጢረ ተክሊል ናቸው፡፡

ሰባት መኾናቸው ወይም መባላቸው፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በእነዚኽ ብቻ ይወሰናል ማለት አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስ አይወሰንም፤ ለስጦታውም ገደብ የለውምና፡፡/ዮሐ.3፥8/ ነገር ግን ሊቃውንት በፊት ጌታ፣ በኋላም ሐዋርያት ሥራ የሠሩባቸውን ከቅዱሳት መጻሕፍት ለቅመው ሰባቱን ምሥጢራት በቤተ ክርስቲያን መድበዋል፤ እነዚኽ ሰባቱ እንደ አርእስት ናቸው፡፡

አንዳንድ ሰዎች የሰባቱን ምሥጢራት ቁጥር ከፍና ዝቅ በማድረግ ይናገራሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ግን ምንም እንኳ ከሊቃውንት ብዙዎች ሰባቱን በሙሉ ቆጥረው ባያቀርቡም ኹለቱን አንዱ ሦስቱን ሌላው እያደረጉ ጽፈዋቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ምሥጢራት ሰባት ናቸው ብላ የምታስተምረው በምሳሌ ሰሎሞን ጥበብ ቤቷን ያቆመችባቸውን ሰባት አዕማድ ምሳሌ አድርጋ ነው፡፡/ምሳሌ 9፥11/

ከእኒኽ ከሰባቱ ሦስቱ ማለትም፡- ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ተክሊል፣ ምሥጢረ ክህነት አይደገሙም፡፡ ሌሎቹ አራቱ ግን እንደኹኔታው ይደገማሉ፡፡ የምሥጢረ ክህነትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመሠራረት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደሚሠራበት እንገልጣለን፡፡

ምሥጢረ ክህነት

ክህነት በግእዝ ቋንቋ “ተክህነ”፤“አገለገለ” ከሚለው ግስ የወጣ ነው፡፡ አገልግሎቱም ለሃይማኖት ብቻ ነው፡፡ “ክህነት” የሥልጣኑ ስም ነው፤ አገልጋዮቹ ካህናት ይባላሉ፡፡ ዕብራውያን ካህን ይሉታል፡፡ አወጣጡ እንደ ግእዝ ነው፡፡ ዮናናውያንም፣ ኢየራቲቪን – “ተክህኖ፣ ተክህኖት” ከሚለው አርእስት “ኢየሬብአ” ብለው ያወጣሉ፡፡ ካህን ማለት ነው፡፡

ምሥጢረ ክህነትን የመሠረተው ራሱ ጌታ ነው፡፡ በደሙ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ካህናት፣ የአገልግሎት ሥልጣን የሚቀበሉት ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ይህ የካህናት ሹመት “ምሥጢረ ካህናት” ይባላል፡፡ ጌታ በደሙ ቤተ ክርስቲያንን ከመሠረተ በኋላ ከትንሣኤው አያይዞ ለሐዋርያት ሥልጣነ ክህነትን ሰጥቷቸዋል፡፡ /ዮሐ.20፥22-23/ ሐዋርያትም የትንሣኤውን ዐዋጅ ለመንገር ወደ ዓለም በገቡ ጊዜ በክህነታቸው ተኣምራት ያደርጉ ነበር፡፡ /ማር.16፥16/ ሐዋርያት በሥልጣናቸው ያስሩ ይፈቱ ነበር፡፡/ማቴ.18፥18፤ 1ቆሮ.4፥1፤ 2ቆሮ.5፥20፤ ማቴ.16፥18/ ለምሳሌ፡- የሐናንያንና የሚስቱን የሰጲራን፤ የሲሞን መሠርይን ታሪክ ይመለከቷል፡፡ /የሐዋ.5፥1-11፤ 8፥24-28/ ቤተ ክርስቲያንን ይመግቡና ያስተዳድሩም ዘንድ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ /ዮሐ.20፥15/

ይህም፥ የማሰር እና የመፍታት ማለትም አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የመለየት፣ በይቅርታ ወደ ቤተ ክርስቲያን የመመለስ ሥልጣን፤ ምሥጢራትን የመፈጸም፣ ቤተ ክርስቲያንን የመመገብ ተልእኮ እስከ ኅልፈተ ዓለም የሚቆይ መኾኑን ጌታ ተናግሯል፡፡ /ማቴ.28፥20፤ 1ቆሮ.11፥26/ ስለዚኽ ሐዋርያትም ከጌታ ያገኙትን ሥልጣን ለተከታዮቻቸው አስተላለፉ፡፡ እነርሱ እስከ ዓለም ፍጻሜ አይኖሩምና፡፡ ወዲያው ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ በማስተንተን ተልእኮ የሚረዷቸውን ሰባት ዲያቆናት በምእመናን አስመርጠው በእንብሮተ እድ ሹመዋል፡፡ /የሐዋ. ሥ.6፥6/ በርናባስ እና ጳውሎስም ቀሳውስትን ሾሙ፡፡ /የሐዋ ሥ.14፥23/ ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ኤጲስ ቆጶሳት ሾመው፡፡ /1ጢሞ.4፥14፤ 2ጢሞ.1፥16/

በአዲስ ኪዳን በብዙ ቦታ ምእመናንን በጠቅላላ ካህናት ስለሚላቸው በፕሮቴስታንቱ /ፀረ ማርያም/ ዓለም ያሉ አንዳንድ ቅርንጫፎች፣ “ክህነት የተለየ ሥልጣን ሳይኾን በክርስቶስ ላመኑ ኹሉ የተሰጠ የክብርና የማዕርግ፣ የባለሟልነት መጠርያ/ደረጃ/ ነው፤” ይላሉ፡፡ ለሐሳባቸውም ድጋፍ የሚጠቅሱት በቀዳማዊ የጴጥሮስ መልእክት ምዕ.2 ከቁ.5 እስከ 9፤ በዮሐንስ ራእይ ከምዕ.1 ቁ.7 የሚገኘውን ነው፡፡

በርግጥ እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በኋላ፣ እግዚአብሔር/የሆዋ/ በሙሴ አማካይነት የሰጣቸውን ቃል ኪዳን ይመስላል፡፡ /ዘጸ.19፥5-6/ ይህ ቃል አሻሚና አደናጋሪ አይደለም፡፡ ጴጥሮስም ዮሐንስም የተናገሩት የብሉይ ኪዳኑን የቃል ኪዳን አነጋገር በመንፈሳዊ ምሥጢር ተርጉመው ነው፡፡ “ካህን” የሚለው ቃል መሠረቱ ብሉይ ኪዳን እንደመኾኑ መጠን የሚያሳየው ባለሟልነትን፣ ቀራቢነትንና ተወዳጅነትን ነው፡፡ ቃሌን ብትጠብቁ ካህናት ትኾናላችኹ፤ ብሎ እግዚአብሔር ለእስራኤል የተናገረውን ቃል የሚገልጥ ነው፡፡ የአሮንን ክህነት መደምሰሱ አልነበረም፡፡ ሕዝቡን በእምነት ለባለሟልነት መምረጡ ነበር እንጂ፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የጴጥሮስና የዮሐንስ ንባብ፥ ቀራቢነትን፣ ባለሟልነትን፣ ተወዳጅነትንና በክርስቶስ የተገኘውን የጸጋ መጠን መናገራቸው ነው እንጂ ጌታ ለሐዋርያት የሰጠውን የአገልግሎት ሥልጣን መሻራቸው አይደለም፡፡

በክርስቶስ ያመኑ ምእመናን ካህናት ብቻ ሳይኾኑ ነገሥታትም ይባላሉ፡፡ /ራእይ 5፥10/ ይህም የሚያሳየው በጥምቀት በልጅነት የተገኘውን የጸጋ ልዕልና ነው፡፡ የማዕርጋት ቁንጮዎች እነዚኽ ኹለቱ ናቸውና – ክህነት እና መንግሥት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ምእመናንን፣ “ካህናት ነገሥታት” የሚላቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን መቀባታቸውን ለመግለጥ ነው፡፡ ሐዋርያት በአንብሮተ እድ የተሾሙትን፤ አኹንም በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ ካህናት በየጊዜው በኤጲስ ቆጶሳት አንብሮተ እድ የሚሾሙትን ሹመት የሚሽር አይደለም፡፡ ይህን አንጋዶ ተርጉሞ፣ “ካህን ነኝ፣ ካህን አያስፈልግም፤ ንጉሥ ነኝ፣ መሪ አያስፈልገኝም” የሚል ክርስቲያን ነኝ ባይ በገዛ እጁ ዕዳ ይገባል፡፡ የቤተ ክርስቲያንም ቋንቋ እንዳልገባው ያሳያል፡፡

የክህነት ደረጃዎች

ክህነት በቤተ ክርስቲያን ሦስት ደረጃ አለው – ዲያቆን፣ ቄስ፣ ኤጲስ ቆጶስ፡፡ እነዚኽ ሦስቱም በሥራና በማዕርግ የተለያዩ ይኹኑ እንጂ ኹሉም የየራሳቸው ተልእኮ አላቸው፡፡ በሐዲስ ኪዳን በአንዳንድ ቦታ በቄሱ ስም ኤጲስ ቆጶሱ፣ በኤጲስ ቆጶሱ ስም ቄሱ ይጠራበታል፡፡ ይህም የስም እንጂ የሥልጣን ሞክሼ አይደለም፡፡ ሐዋርያት ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ናቸው፡፡ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን ይሾማሉና፡፡ በአንዳንድ ቦታ ደግሞ ቀሳውስት እያለ ይጠራቸዋል፤ “እመኒ ቀሲስ”/ዮሐ.ካል.1፥1/፡፡ ዲያቆናትም ይላቸዋል፡፡/1ኛ ቆሮ.3፥5፤ 2ቆሮ.3፥6/ ሐዋርያት ኤጲስ ቆጶሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ቢባሉም በሦስቱም ሥልጣን ሠርተውባቸዋል፤ ሦስቱም ሥልጣናት ተሰጥተዋቸዋልና፡፡ ጳጳሱ ቅስና፣ ዲቁና የለኽም፤ አይባልም፡፡ “አቡን ቄስ ናቸው ቢሉ ተርፏቸው ለሌላ ይናኛሉ” ይባላል፡፡

ነገር ግን፣ ይህን አጠራር ምክንያት አድርገው አንዳንድ የፕሮቴስታንት ቅርንጫፎች ሦስቱን የክህነት ደረጃዎች አይቀበሉም፤ በእነርሱ ትምህርት፣ ክህነት የሚባለው ቅስና ብቻ ነው፡፡ እርሱም እንደ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት፣ በአንብሮተ እድ በቅብዓት ሳይኾን፣ እገሌን መርጠናል ብለው አማኞቻቸው በሚሰጡት ድምፅ ነው፡፡ በእነርሱ አባባል፣ የኤጲስ ቆጶሳት ማዕርግ የክህነት ደረጃ አይደለም፡፡

በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምንገለገልባቸው ሦስቱም የክህነት ደረጃዎች በሐዲስ ኪዳን ግልጥ መረጃ አላቸው፡፡ ሐዋርያት ራሳቸው ኤጲስ ቆጶሳት ነበሩ፡፡ ይኸውም ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን በመሾማቸው ይታወቃል፡፡ ጢሞቴዎስና ቲቶ ቀሳውስትን የመምራትና የማስተዳደር ሥልጣን ነበራቸው፡፡ የኤጲስ ቆጶስነት ሥልጣን ነበራቸው፡፡ /1ጢሞ.5፥19፤ ቲቶ 1፥5/ የቀሳውስት ሹመት/የሐዋ. ሥራ 14፥23/ ዲያቆናት ከቀሳውስት በታች ደረጃ አላቸው፡፡ አገልግሎታቸውም የተለየ ነው፡፡ /የሐዋ. ሥራ 6፥2/

በቤተ ክርስቲያን አባቶችም ሦስቱ የክህነት ደረጃዎች የታወቁ የተጠበቁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ አግናጥዮስ፣ ስለሦስቱ ማዕርጋት መኖር ግልጥና ጭብጥ ያለውን መረጃ ይሰጠናል፡፡ ለኤፌሶን ምእመናን በላከው የምክርና የተግሣጽ መልእክት እንዲኽ ይል ነበር፡- “ለእግዚአብሔር የሚገባችኹን ኹሉ ለማድረግ ፍጠኑ፤ የሚመራችኹ ኤጲስ ቆጶስ የእግዚአብሔር እንደራሴ ነው፡፡ ቄሱም እንደ ሐዋርያት፣ ዲያቆናትም ለክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ባለአደራዎች ናቸውና”፡፡ እነዚኽ ሦስቱ የክህነት ደረጃዎች፣ ከፕሮቴስታንቱ ዓለም በቀር በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ይሠራባቸዋል፡፡

የክህነት አሰጣጥ

በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ክህነት የሚሰጠው ከጸሎትና ከምሕላ ጋር በምርጫ፣ በዕጣ ነው፡፡ ይህንንም በይሁዳ መንበር በተተካው በማትያስ ምርጫ እና ዕጣ ማየት ይቻላል፡፡ /የሐዋ.ሥ.1፥24/ የሰባቱም ዲያቆናት ሹመት በምርጫ ነው፡፡ /የሐዋ. ሥ.6፥6/ ከኹሉም በፊት ደግሞ ሐዋርያት በራሱ በጌታ ተመርጠው ተሹመዋል፡፡ /ማቴ.10፥1፤ 28፥19፤ ዮሐ.15፥16/ የጳውሎስም ጥሪ በምርጫ ነው፡፡ /የሐዋ. ሥራ 9፥1-18፤ ገላትያ 1፥1/ ጳውሎስና በርናባስ እንደገና ተመርጠዋል፡፡ /የሐዋ. ሥራ 13፥2‐3፤ 20፥28/

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ይልቁንም በምሥጢረ ቤተ ክርስቲያን እንደሚታወቀው፣ ለክህነት የታጩት ሰዎች ተመርጠው ሲቀርቡ፣ የመሾም ሥልጣን ያላቸው ደግሞ ጸሎትና ምሕላ አድርሰው በአንብሮተ እድ ይሾማሉ፡፡ በአንብሮተ እድ መሾም፣ በአንብሮተ እድ መባረክ፣ በአንብሮተ እድ ሥልጣንን ማስተላለፍ፣ መብት መስጠት ከብሉይ ኪዳን ቀደም ሲልም የተለመደ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- ያዕቆብ የልጅ ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን በአንብሮተ እድ ባርኮ ከልጆቹ እኩል እንዲወርሱ ሥልጣንና መብት ሰጥቷቸዋል፡፡ /ዘፍጥ.48፥14-17/ በብሉይ ኪዳንም ሌዋውያን የሚሾሙት በአንብሮተ እድ ነበር፡፡ /ዘኁ.27፥23/ ሙሴ በአንብሮተ እድ እስራኤልን የሚመራበትን ሥልጣን ለኢያሱ አስተላልፎለታል፡፡ /ዘዳግ.34፥9/ ከለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት በአንብሮተ እድ ይባርኩት ነበር፡፡ /ዘሌዋ.1፥14/

በአዲስ ኪዳን የአንብሮተ እድ ሹመት፣ ጌታ በአንብሮተ እድና በንፍሐት/በቅብዐት/ ሐዋርያትን ሹሟቸዋል፡፡ /ዮሐ.20፥23-24፤ ማር.10፥16፤ ሉቃ.24፥50-51/ ሐዋርያትም ከላይ እንደገለጥነው፣ በአንብሮተ እድ ይሾሙ ነበር፡፡ ኤጲስ ቆጶሳትም ይህን ሥርዓት በመያዝ በአንብሮተ እድ ይሾሙ ነበር፡፡

ከሦስቱ የክህነት ደረጃዎች ሌላ፡- ማለት ከዲቁና፣ ከቅስና፣ ከኤጲስ ቆጶስነት ሌላ በቤተ ክርስቲያን የታወቁ የውስጥ ክፍልፋይ ማዕርጋት አሉ፡፡ እነርሱም፥ አንባቢ፣ ንፍቅ ዲያቆን፣ መዘምር፣ በረኛ ናቸው፡፡ በፍትሕ መንፈሳዊ እንደተገለጸው፣ “ዲያቆናውያት” የሚባሉ ሴቶች የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ነበሩ፡፡ እነዚኽ ሴቶች ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ዘመናት ሲያገለግሉ የኖሩ ናቸው፡፡ ይልቁንም በዘመነ ሰማዕታት፣ ለሰማዕታት በመላላክ፣ ሰማዕታት ሲታሰሩ ስንቅ በማቀበል፤ አዲስ አማንያን ሲመጡም ሴቶቻቸውን በማስተማር፣ መመሪያም በመስጠት ብዙ አገልግሎት ሲያበረክቱ ኑረዋል፡፡ ለጢሞቴዎስ በላከው ምክርና መመሪያ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ “ከሠላሳ ዓመት ያላነሣት” የቤት እናት ምረጥ ብሎታል፡፡ /ቀዳ. ጢሞ.5፥9/

የቁምስና ሹመት

ኤጲስ ቆጶሱ በማይገኝበት ቦታ እንደ ኤጲስ ቆጶስ ኾኖ የሚያገለግል ቆሞስ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ይሾማል፡፡ የቁምስና ሹመት የሚሰጠው በኤጲስ ቆጶስ ነው፡፡ ቆሞስ የሚኾኑት በድንግልና የመነኮሱ፣ የቅስና ማዕርግ ያላቸው ናቸው፡፡ ቆሞሳት አዲስ ቤተ ክርስቲያን ይባርካሉ፤ አዲስ ጽላት ግን አይባርኩም፡፡ ክህነት አይሰጡም፡፡ ሜሮን አያፈሉም፡፡ የቁምስና ማዕርግ የሚገባቸው የገዳም አበ ምኔቶች ናቸው፡፡

ወደ ክህነት መምጣት የሚገባቸው እነማን መኾን አለባቸው?

ክህነት ከመቀበሉ በፊት ዕጩው ካህን ሃይማኖቱን ጠንቅቆ እንዲያውቅ ያስፈልጋል፡፡ /ጉባኤ ኒቅያ 325 ቀኖና 19/ ከአዲስ አማንያን መኾን የለበትም፡፡ /1ጢሞ.3፥6፤ ቀኖና ሐዋ.80፤ ጉባኤ ኒቅያ 325 ቀኖና 2 – 9፤ የሎዶቅያ ቀኖና 12/ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚያውቁ፤ ከዚኽም ጋር ሙሉ አካልና የመንፈስ ጤንነት ያላቸው ካህናት እንዲሾሙ ታዟል፡፡ /የሐዋ. ቀኖና 78/ ኤጲስ ኤጲስ ወይም ቄስ በሚካንበት ጊዜ ዕድሜው ከ30 ማነስ የለበትም፡፡ ዲያቆንም ሲሾም የ25 ዓመት እንዲኾን ታዟል፡፡ ዲያቆናት ሚስት ካገቡ በኋላ ወይም መንኩሰው የቅስና ማዕርግ ይቀበላሉ፡፡ /1ጢሞ.3፥2፤ 4፥12፤ የሐዋ ቀኖና 4፤ የስድስተኛው ሲኖዶስ ቀኖና 13፤ የጋንግራ ሲኖዶስ ቀኖና 4/

ኤጲስ ቆጶስ ለመኾን መብት ያላቸው ግን፣ በድንግልና የመነኮሱ፣ የቅስናና የቁምስና ማዕርግ ያላቸው ናቸው፡፡ /የስድስተኛው ሲኖዶስ ቀኖና 12/ ማዕርገ ዲቁና ከተቀበሉ በኋላ ሚስት ማግባት ይቻላል፡፡ /የዕንቆራ ጉባኤ ቀኖና 10/ የቅስና ማዕርግ ከተቀበሉ በኋላ ግን ለማግባት አይቻልም፡፡ /የሐዋ. ቀኖና 26፤ የቅድሎስ የትሩሎስ ሲኖዶስ ቀኖና 6፤ የኒቅያ ቂሣርያ ቀኖና 1፤ ቀኖና  ኒቅያ 325፥3-6፤ የባስልዮስ ቀኖና 6/ እነዚኽን ቀኖናዎች በማያፋልስ ሥርዓት፣ ኤጲስ ቆጶስ በፓትርያርኩ መሪነት በሲኖዶስ አባላት ይሾማል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በችግር ላይ በምትገኝበት ጊዜ ላይ ግን፣ በኹለት ኤጲስ ቆጶሳት ይሾማል፡፡ /የሐዋ ቀኖና 8፥4/ የሚሾመውም በአንብሮተ እድና በቅብዐት ነው፡፡

His Grace Abune Gorgoryos(Right) and His GraceAbune Mekariyos(Left) participating at a peace conf in Moscow
ኤጲስ ቆጶሱ፣ ቄሱም ኾነ ዲያቆኑ ሲሾሙ ጸሎተ ሃይማኖትን አሰምተው አንብበው፣ ቤተ ክርስቲያን የምትቀበላቸውን ጉባኤዎችና ውሳኔዎቻቸውን ቆጥረው እናከብራለን፤ እናስከብራለን ብለው ቤተ ክርስቲያን የማትቀበላቸውን ግን አውግዘው ይሾማሉ፡፡

የቤተ ክርስቲያን ክህነት ከምኩራቡ ዘርዐ ክህነት የተለየ ነው፡፡ የምኩራቡ ክህነት፣ ሌዊንና አሮንን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ በእነርሱ የዘር ሐረግ ብቻ የሚተላለፍ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ክህነት ግን ክርስቶስን መሠረት አድርጎ ነው፤ የዘር እና የጐሳ ልዩነት አይደረግበትም፡፡ የብሉይ ኪዳን ካህን የሚሾመው መሥዋዕተ ኦሪትን ለመሠዋት ነው፤ ማለት ስብ ለማጤስ ደም ለማፍሰስ ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ክህነት መሠረት ክርስቶስ ግን፣ የራሱን ደም አፍሶ የፈጠረውን ያዳነ እንደመኾኑ መጠን፣ በእርሱ የተሾሙ ሐዋርያትና ወራሾቻቸው ኤጲስ ቆጶሳትና ካህናትም የሚሾሙት ዓለምን በእርሱ ለማሳመን ነው፤ መሥዋዕቱም ቍርባኑም የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት መሠረት፣ ሦስቱም የክህነት ደረጃዎች ለእያንዳንዳቸው የተወሰነ ተልእኮ አላቸው፡፡

ሀ. የኤጲስ ቆጶሳት ተልእኮ፡-

ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ይሾማል፤ ያስተምራል፤ ያጠምቃል፤ ያቆርባል፡፡ ከዚኽም ኹሉ ጋር በሀገረ ስብከቱ ያሉት ምእመናን፣ በመንፈሳዊና በማኅበራዊ ኑሮ ችግር ሲደርስባቸው ችግራቸውን ያቃልላቸዋል፡፡ እንደ አባት እንደ አለቃ ኹኖ ይመክራቸዋል፡፡ እንደ ዳኛ ኹኖ ይፈርድላቸዋል፡፡ እነርሱም እንደ ልጅ ይታዘዙታል፤ ከፈቃዱ አይወጡም፡፡ አግናጥዮስ እንዳለው፣ “በክርስቶስ አምሳል በክርስቶስ የማስተማርያ ቦታ/ዙፋን/ የተቀመጠው ኤጲስ ቆጶስ፣ ምእመናንን የሚማርክ ቃና ያለው ትምህርት ለመስጠት የሚችለው፣ ምእመናንና ካህናት የእርሱን አባትነት ሲያውቁለት፤ እርሱም እንደ አባት ሲያስብላቸው ነው፡፡ መሰንቆ እንኳ ይላል አግናጥዮስ፣ አድማጮችን የሚማርከው ጭራዎቹ ከዕንጨቱ ጋር ተስማምተው ሲወጠሩና ሲቃኙ ነውና፡፡” ዮሐንስ አፈወርቅም፡- የኤጲስ ቆጶሱ ሥራ ምእመናንን ለጸሎት ማትጋት መኾኑን ሲገልጥ፣ “ኤጲስ ቆጶስ ሆይ፣ ሕዝቡን ጧትና ማታ ለነግህና ለሠርክ ጸሎት በቤተ ክርስቲያን ይገኙ ዘንድ እዘዛቸው፤” ብሏል፡፡

ለ. ቀሳውስት፡-

እንደ ኤጲስ ቆጶሱ ማስተማርና ማጥመቅ እንዲኹም ማቁረብ ነው፡፡ በተረፈም ኤጲስ ቆጶሱ ባልተገኘበት ቦታ፣ በኤጲስ ቆጶሱ የተወከለውን የእርሱን ሥራ ይሠራል፡፡ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን መሾም፤ ሜሮን ማፍላት፣ አዲስ ቤተ ክርስቲያን መባረክ አይችሉም፡፡ ቀሳውስት በሕግ በተክሊል ያገቡ ናቸው፤ በድንግልና የመነኰሱም የቅስና ማዕርግ ከተቀበሉ ቀሳውስት ይባላሉ፤ ቀሳውስት ናቸው፡፡ ለነዚኽም በሌሎች አገሮች ልዩ መጠሪያ አላቸው – ኢየሮመናሆስ ይባላሉ፡፡ በእኛ ግን መነኵሴ ይባላል እንጂ ልዩ መጠርያ የለውም፡፡ መነኵሴ መባል ደግሞ ሥልጣነ ክህነት ላለውም ለሌለውም መጠሪያ ስለኾነ ያሻማል፡፡

ሐ. ዲያቆናት፡-

ዲያቆናት፣ የኤጲስ ቆጶሱና የቄሱ ተላላኪዎች ናቸው፡፡ ምሥጢራትን የመፈጸም መብት የላቸውም፡፡ “እስመ እሙንቱ ከመ ሕዝብ = ቁጥራቸው ከምእመናን ነው፡፡” ንፍቅ ዲያቆን የሚባለው ዋናውን ዲያቆን ይረዳል፡፡ አንባቢ/አናጒንስጢስ/ የሚባለው በቤተ ክርስቲያን በተለይም በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡትን ምንባባት ያነባል፡፡ መዘምር/ደብተራ/ ደግሞ ስሙ እንደሚያስረዳው፣ በቤተ ክርስቲያን መዝሙር የሚዘምር የሚያቀነቅን ማለት ነው፡፡ ሌሎች እርሱን እየተከተሉ ይዘምራሉ፡፡ ኃፃዌ ኆኅት/በረኛ/ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ይጠርጋል፤ ያጠዳል፤ ያነጥፋል፤ ይደውላል፤ ቤተ ክርስቲያንን በጸሎት ጊዜ የሚከፍት፣ ጸሎቱ ሲፈጸም የሚዘጋ ነው፡፡

ኤጲስ ቆጶስ እና ኮሬ ኤጲስ ቆጶስ/ሆር ኢፒስኮፒ/፡-

ኤጲስ ቆጶሳት ሥልጣናቸው አንድ ሲኾን፣ ሊቀ ኖሎት ኾነው የሚሾሙበት ቦታ ባለው ስፋትና ታሪክ መሠረት የተለያዩ የማዕርግ ስም አላቸው፡፡ በአውራጃና በወረዳ የሚሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት ይባላሉ፡፡ አውራጃው፣ ወረዳው ሰፋ ያለ ሲኾን፣ ለማስተማርና ለማጥመቅ እንዲመች ኤጲስ ቆጶሱን ለመርዳት የሚሾሙ ኮሬ ኤጲስ ቆጶስ/ሆር ኢፒስኮፒ/ የሚባሉ አሉ፡፡ የገጠር ኤጲስ ቆጶስ ማለት ነው፡፡ ሥልጣናቸው እንደ ኤጲስ ቆጶሱ ኾኖ በአስተዳደር ግን በእርሱ ሥር ናቸው፡፡

His Holiness Abune Tekle haimanot03
መጥሮጶሊስ/ሜትሮፖሊቲስ/፡-

በአጠቃላይ የግዛቱ ከተማ ማለትም እንደ መቐለ፣ እንደ ደብረ ማርቆስ፣ እንደ አርባ ምንጭ ባሉት ከተሞች የሚሾሙት ደግሞ መጥሮጶሊስ/ሜትሮፖሊቲስ/ ይባላሉ፤ “የእናት ከተማዪቱ ኤጲስ ቆጶስ ማለት ነው”፤ እንደ አውራ፣ እንደ አለቃ ኾኖ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በአውራጃውና በየወረዳው ያሉትን ኤጲስ ቆጶሳት – ኮሬ ኤጲስ ቆጶሳት ይመራል፤ ያስተዳድራል፡፡ ይህ ማዕርግ በመጀመሪያ የተወሰነው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጉባኤ ኒቅያ ነው፡፡ /ጉባኤ ኒቅያ 325 ቀኖና 4/

ኹለተኛው ማዕርግ፣ ሊቀ ኤጲስ ቆጶስ ወይም ርእሰ ኤጲስ ቆጶስ የሚባለው ነው፡፡ በዚኽ ማዕርግ ስም እንደ ላሊበላ፣ እንደ ደብረ ሊባኖስ ባሉ ቦታዎች የሚሾመው ኤጲስ ቆጶስ የሚጠራበት ነው፡፡ አትናቴዎስ ኹልጊዜ የእስክንድርያውን ኤጲስ ቆጶስ እለእስክንድሮስን ሊቀ ኤጲስ ቆጶስ እያለ ይጠራው ነበር፤ እስክንድርያ በጥንታዊ ታሪኳ የታወቀች ነበረችና፡፡

ፓትርያርክ – ፓፓ/ፖፕ፡-

ፓትርያርክ የሚባል የማዕርግ ስም የተጀመረው በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በዚኽ የማዕርግ ስም የሚጠሩ፣ በመጀመሪያ፡- የሮም፣ የእስክንድርያና የአንጾኪያ መጥሮፖሊሶች ነበሩ፡፡ ኋላ ግን ራሳቸውን ችለው የሚተዳደሩ አገሮች ኹሉ የየራሳቸውን ፓትርያርክ ሹመዋል፡፡ ፓትርያርክ ማለት በፅርዑ ሊቀ አበው ማለት ነው፡፡ በመጨረሻም “ፖን፣ ፖፕ፣ ፓፓ” የሚባለው ማዕርግ፣ ከ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ ለሮም እና ለእስክንድርያው ሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳት የተሰጠ ስም ነው፡፡ /ጎርጎርዮስ ዘቂሳርያ ቀኖና 1/


abune gorgorewos and his holiness abune tekle
ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ጊዜ ስትገፋ ከኖረች በኋላ፣ በ1965 ዓ.ም. እንደ ሌሎች ክርስቲያኖች፣ የሰበካ ምእመናንን በማስተባበርና ከካህናቱ ጋር አብረው እንዲሠሩ ለማድረግ የሚያስችል የመተዳደርያ ደንብ ቃለ ዓዋዲ አውጥታ የሰበካ ጉባኤን መሠረተች፡፡ …ዛሬ ምእመናን ለየሰበካቸው ካህናት በቃለ ዓዋዲው መሠረት ደመወዝ እየከፈሉ ነው፡፡… በሌሎች አገሮች ፓትርያርኮችና ጳጳሳት የሃይማኖት እንግዶች ጥሪ እያደረጉ የሚጋብዙትና እነርሱም ጥሪ ሲደረግላቸው የሚሔዱት፤ በማንኛውም ጥሪና የስብሰባ ቦታ የቤተ ክርስቲያናቸውን ድምፅ ለማሰማት የሚገኙት፣ ከምእመናን በሚደረግላቸው አስተዋፅኦ ነው፡፡

ፓትርያርኩ ወይም የክፍሉ ጳጳስ ለክብሩ በማይመጣጠን መኪና ሲሔድ ያየው እንደኾነ፣ ምእመኑ ሃይማኖቱ እንደተዋረደና ቤተ ክርስቲያኑም ዝቅ እንዳለች ይቆጥረዋል፡፡ ስለዚኽ ኹሉም በክርስትና ዓላማው የተቻለውን ያኽል ለቤተ ክርስቲያኑ የሚገባውን ይከፍላል፡፡ እንዲያውም ሀብት ያላቸው ምእመናን ከኾኑ መጓጓዧ መኪና እንኳን ሳይቀር ለፓትርያርኮቻቸውና ለጳጳሶቻቸው ገጸ በረከት የሚሰጡ አሉ፡፡ የኛም ቤተ ክርስቲያን ብዙ ምእመናን አሏት፡፡ በሰበካ ጉባኤ ከተደራጁና ዓላማው ከገባቸው ለመንበረ ፓትርያርካቸውና ለክፍላቸው ጳጳስ ክብር፣ የክብር መጠበቂያ በአጠቃላይ ለቤተ ክርስቲያናቸው አስተዳደር አስተዋፅኦ ለማድረግ ከሌላው የሚሰንፉ አይደሉም፡፡ /የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ገጽ 162/


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ሦስቱ ዐበይት የክህነት ማዕርጋት፡- ዲቁና፣ ቅስና፣ ኤጲስ ቆጶስ ናቸው፡፡ አራቱ ንዑሳን ማዕርጋት ደግሞ፥ ንፍቀ ዲቁና፣ አንባቢነት፣ መዘምርነትና ኃፃዌ ኆኅት/በረኛ/ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሰባቱም ማዕርጋት ይሠራባቸዋል፡፡

ከእነዚኽ ሌላ ሥልጣነ ቡራኬ የሚባል ላልተማሩ ሰዎች የሚሰጥ ፈቃድ አለ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ምእመናን ምግባቸውን ሲመገቡም ጸሎቱን የሚመራው የቤቱ ባለቤት ነው፡፡ በቤት ውስጥ ከብትም ቢታረድ አስቀድሞ በስመ እግዚአብሔር መባረክ ስላለበት፣ ይህን ለማድረግ ከጳጳሱ ዘንድ እየሔዱ ልዩ ፈቃድ/ቡራኬ/ ይቀበላሉ፤ ጳጳሱም የቡራኬ ጸሎት አድርሶ ባርኮ ያሰናብታቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ከብት፣ ማዕዳቸውንም ባርከው ለመቁረስ ደስ ይላቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ዐበይት የክህነት ማዕርጋት እንዴት ይሠራባቸዋል? ከለሎቹም ያለውስ ልዩነት?

ሀ. ዲያቆንና ቄስ፡- በቤተ ክርስቲያን የዲቁና ማዕርግ የሚሰጠው ከጋብቻ በፊት ነው፡፡ በኋላ በተክሊል አግብቶ የቅስና ማዕርግ ይቀበላል፡፡ ከቅስና ማዕርግ በላይ ያለውን ማዕርግ አያገኝም፡፡ ዲቁናውን እንደተቀበለ ለመመንኰስ ቢፈልግ ግን ገዳም ገብቶ/ረድቶ፤ በረድእነት አገልግሎ/ ይመነኵሳል፡፡ ከመነኰሰ በኋላ የቅስና ማዕርግ ይቀበላል፡፡ ለቁምስና እና ለኤጲስ ቆጶስነትም መንገዱ ይህ ነው፡፡

በምሥራቅ የመለካውያን ሥርዓት፥ የዲቁና ማዕርግ የሚቀበለው ካገባ ወይም ከመነኰሰ በኋላ ነው፡፡ የዲቁና ማዕርግ ከተቀበለ በኋላ ማግባት ክልክል ነው፡፡ ሳይመነኵስ በድንግልናው ብቻ ዲቁና ተቀብሎ ከዚያው ላይ ቅስና ይሰጡታል፤ ይህም ላለማግባት መወሰኑን ካረጋገጡ በኋላ ነው፡፡ ይህ ግን ቢቸግር ነው እንጂ፣ እነርሱም ጥሩ ነው ብለው አያምኑበትም፡፡ ክህነቱን የሚያጐድፍ ወንጀል ካልሠራ አይሻርም፡፡

በላቲኖች/በካቶሊኮች/ ሥርዓተ ክህነት፥ ወደ ክህነት ለሚቀርቡ ኹሉ ማግባት ክልክል ነው፡፡ በፕሮቴስታንቶች /ፀረ ማርያሞች/ ግን ክህነትን ምሥጢር ብለው ስለማይቀበሉት እንኳን አንድ ጊዜ ኹለተኛ ያገባም ቄስ ይኾናል፡፡ እንደ ጭቃ ሹም፣ እንደ ምስለኔ ለተወሰነ ጊዜ/ወራት/ ነው፡፡ የአገልግሎቱ ወራት ሲፈጸም ይሻራል፡፡

Beale Simet
ለ.ኤጲስ ቆጶስ፡-
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት፣ ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾመው ከቆሞሳት መካከል በትምህርቱ በትሩፋቱ ልቆ የተገኘ አባት ነው፤ የሚመረጠውም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ነው፡፡

በምሥራቅ መለካያውንም፣ ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾሙት ደናግል መነኰሳት ናቸው፤ የሚመረጡትም በሲኖዶስ ነው፡፡ በሮማ ካቶሊክ ሥርዓት፣ ካህናቱ በሙሉ ያላገቡ ይኹኑ እንጂ ዓለማውያንና ገዳማውያን ተብለው ከኹለት የተከፈሉ ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ጳጳሳት፣ ካርዲናሎችና ፓፓዎችም የሚመረጡት፣ ዓለማውያን ካህናት ከሚባሉት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ከገዳማውያኑም ይሾማሉ፡፡ ፕሮቴስታንቶች/ፀረ ማርያሞች/ ግን የተወሰነ ቀኖና የላቸውም፤ ኹሉም ያገባ ነው፡፡

ይትባረክ እግዚአብሔር

*               *               *

በመጨረሻው ሓላፊነታቸው የደቡብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ በድንገተኛ የመኪና አደጋ በ50 ዓመታቸው ሕይወታቸው ያለፈው፣ ሐምሌ 22 ቀን 1982 ዓ.ም. ነበር፡፡ ጳጉሜን 1 ቀን ዕረፍታቸውን የዘገበው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ፣ በስፋት ያስነበበው የብፁዕነታቸው ዜና ሕይወትና ሥራዎች የሚከተለው ነበር፡፡ የብፁዕነታቸው በረከት ይድረሰን፡፡ አሜን፡፡Zena Betekirstian Obituary of the late abune gorgoryos0Zena Betekirstian Obituary of the late abune gorgoryos1Zena Betekirstian Obituary of the late abune gorgoryos2zena betekirstian obituary on the late abune gorgoryos2bZena Betekirstian Obituary of the late abune gorgoryos3Zena Betekirstian Obituary of the late abune gorgoryos4Zena Betekirstian Obituary of the late abune gorgoryos5Zena Betekirstian Obituary of the late abune gorgoryos6

Advertisements

3 thoughts on “ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾመው ከቆሞሳት መካከል በትምህርቱ በትሩፋቱ ልቆ የተገኘ አባት ነው – ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በምሥጢረ ክህነት እንዳስተማሩት

 1. Anonymous July 29, 2016 at 8:27 am Reply

  የብፁ አባታን አቡነ ጎርጎሬዎስ ዘዋይ ቀዳማዊ የሰሩትመልካምስራ አይተን።
  ባንጻሩ ደግሞ የቁልቢ ገብርኤል ገዳም አለቃ የሀያ አራት አመት ስራቸውን ስንመለከት።

  በአላክሲዎኑ አለቃ ለመሆኑ ማአንደሆነ ታውቁት አላችሁ ለመሆኑስ መነኩሴ ነው።
  የድሮው ዋናው አለቃ ዘመድ ታጋይ ሁኖ የመጣ

 2. Anonymous August 30, 2016 at 10:43 am Reply

  ምሥጢረ ክህነት በፍራንክፈርት ቅድስትማርያም የስም ካህን ትብየ አባ ሲራክ ወልደበድን ።ሐይለመለኮት ተስማርያም
  ከተሻረ አመታት አስቆጠር

  አባ ሲራክ በፍራንክፈርት ያሉ ሲታዳሬ ቀርቶባልትዳሮችየሚያማግጥ ከትዳራቸዉ የሚለይ
  እንደገና የሸሬ ተወላጂ የሆነች ወሮብርክት በምነቷ እስላም የነረች ወደወርቶዶክስ መታ አባ ሲራክ ለረጂምጊዜ በዉሽምነት
  ሲጠቀምባት ቆይቶ ሲተዋት አዝና ወደቀደመሐይማኖቷ ተመልሣሰለማለች
  አቶሙሉብረሐን የተባለ ምሽቱን አለያይቶት በሐዘን ሲኖር ቆይቷል ልጂቷንም ታዉቇትአላችሁ
  ከዚህምየከፋ ከቤተሰቡጋር ወሲብ እደፈፀመ ይቅርብ አዋቂወችይናገራሉ የቸገረዉ ዛፋከምን ይጠጋል እዺሉ
  ወንድምብላተጠግታ አስቀድሞ ክብረንፅህነዋን ስለገሰሣት ትዳርእቢ ብሏት ትገኝአለች ለነገሩ መነኩሴ የደፈራት ሴት በሐገራችን
  ማንአይጠጋት እደበሽታ ነዉ የሚቆጠር
  ከዚህምሌላ አባ ሲራክ ሰዶ ምዕምነዉ ከዚህበፌት ምሥጢርአዋቂዎች አደፃፍበት ሁሌማታማታ ወንድ በኪነዉ ሢአመላልስ
  ይታያል አንዳዴሰዉሲአዉቅበት አዲሥየመጣ ዲያቆን ይላል ዲያቆኖችን ሰዉያዉቃቸዋል ከነሱዉጪነዉ
  እየበላም ይቀድሣል ልምሣሌ የደብረታቦር በልቶነዉ የቀደሰ
  ታዲያምሥጢረ ክህነት በፍራንክፈርት ቅድስትማርያም ፈርሶአል አልፈረሰም አትሞኙ
  በጣም አታላይነዉ እሱስ መቸም አዴሰፍሮበታል ሥረዉምነዉ እንበል ማየት ማመን ነዉና
  አሁንም ሐያመትሙሉ የሰረዉን ጥፋት አይተዉ እንዃን ሰዉች መረዳትያቃታቸዉ አሉ
  ሰላሳምሥት ሺህ ማርያም አላት ተባለ ለምን ከተመሠረተበትጋር እኩል እንዲሆን ሐያሺህ አላረጋችሁትም
  ለምን ቤተክርስቲያኑ ከተመሰረተ ሀያአመትሁኖታል አሁንደግሞ ለማሥመሰል ቤክርስቲያንእስራለን
  ፌደልእናስተምራለን መጀሬያ አባ ጪራቅይማር ምክንያቱም ያልተማረሰዉ ሊያስተምር አይችልም
  መጀሬያጥሬት ባለአማረኞም ይሁን ትግሬኞ ፌደሎችን መለየትነዉ
  ሲራክ ሰዉንመክፈል ሰራህነዉና እንዃን እሣብህ ተሣካልህ ትላንት አማረወች ሰላሚንየነሱኝ ከዚህም
  ከዛአምእነሱናቸዉ ሰላምየሚነሱ ብለህያልከው እነሱማተበዳይናቸዉ አንተና ያንተቢጤ ሰላማቸዉን ቢነሡአቸዉ
  እኮነዉ ስለዚህ ቁርባን ፀበል እያለ ይህስበበኞ ሰውየ እደያጠቃችሁ ይትዯጵያውያን ካአባሲራየፍራንክፈርት ቅድስትማርያም
  ቤተክርስቲያንአስተዳዳሬ ጥንቃቄ እድታደርጉ ካደራጪምር ምልክቴን አሣስባለሁ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: