ሰበር ዜና – የኤጲስ ቆጶሳት የመጨረሻዎቹ 31 ዕጩዎችና ተወዳዳሪዎች ታወቁ

Askema Abew Papasat

 • የሐዋሳ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አባ ሀ/ማርያም ገ/መስቀል ተካተዋል
 • የጋምቤላው አባ ተክለ ሃይማኖት ንጉሤ ያለተወዳዳሪ በብቸኝነት ቀርበዋል
 • ራሳቸውን ከጥቆማ አግልለው የነበሩት አባ ሚካኤል ገ/ማርያም ተይዘዋል
 • የቅ/ላሊበላው አለቃ አባ ወ/ትንሣኤ አባተ እስከ2ኛው ዙር ተወዳዳሪ ነበሩ

*               *              *

ቅዱስ ሲኖዶስ በየአህጉረ ስብከቱ ክፍት በኾኑ መንበረ ጵጵስናዎች፣ ብቁ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም ባለው ዕቅድ መሠረት፣ ለምልአተ ጉባኤው ቀርበው ከታመነባቸው በኋላ በምርጫ የሚወዳደሩ የኤጲስ ቆጶሳት ዕጩዎች ታወቁ፡፡

የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ፥ ተጠቋሚ መነኰሳትንና ቆሞሳትን፤ በአየካባቢው በመለየት የመመርመር፣ የማጥናትና የማጣራት ሥራውን በማጠናቀቅ ዛሬ፣ ረቡዕ፣ ሐምሌ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀትር በፊት፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ቀርበው በዕጩነታቸው ከታመነባቸው በኋላ በምርጫ የሚወዳደሩ 31 የኤጲስ ቆጶሳት ዕጩዎችን ለይቷል፡፡

ኮሚቴው፣ የመጨረሻዎቹን 31 ተጠቋሚዎች መለየት ብቻ ሳይኾን፣ ሢመቱ ለሚካሔድባቸው 16 አህጉረ ስብከት የሚወዳደሩትን ዕጩዎች እያጣመረ ማቅረቡም ታውቋል፡፡

ከዕጩዎቹ መካከል፣ የጋምቤላና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ንጉሤ፣ ያለተወዳዳሪ ለብቻቸው በመቅረባቸው፣ 32 መኾን የሚገባውን የዕጩዎች ጠቅላላ ቁጥር በአንድ ቀንሶታል፤ የጉዳዩን ተከታታዮች ትኩረት የሳበ ሲኾን፤ ቅዱስ ሲኖዶስም አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚወስንበት ተጠቁሟል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ሀገረ ስብከቱን ባለፈው መጋቢት አጋማሽ በጎበኙበት ወቅት፣ ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ጋቱሉዋክ ቱት ኮት፤ ሥራ አስኪያጁ አባ ተክለ ሃይማኖት ጵጵስና እንዲሾሙላቸው በክልሉ መንግሥት ስም ሲጠይቁ ለሰባተኛ ጊዜ መኾኑን ለቅዱስነታቸው ከመግለጻቸውም በላይ፤ ከጉብኝታቸው በኋላ ብዙም ሳይዘገይ በቀጥታ በአድራሻ በጻፉላቸው ደብዳቤም፣ ሌላ ጳጳስ ተመድቦ ቢመጣ እንደማይቀበሉና ከባሮ ቆላ ከኤርፖርት እንደማያሳልፉ ማስጠንቀቃቸው ብዙዎችን አነጋግሯል፤ አስቆጥቷልም፡፡

ከተጠቋሚዎቹ መካከል፣ የዱራሜ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አባ ሚካኤል ገብረ ማርያም፣ ራሳቸውን በፈቃዳቸው ማግለላቸውን በመግለጽ ከተጠቋሚነት ለመውጣት ለኮሚቴው ደብዳቤ ጽፈው እንደነበር ቢገለጽም፤ በመጨረሻ ካለፉት የኤጲስ ቆጶሳት ዕጩዎች ዝርዝር ተይዘዋል፡፡ አባ ሚካኤል፣ በአቤቱታ ከቀረበባቸው ብርቱ የሥነ ምግባር ችግር አንፃር ከተጠቋሚዎቹ ለመውጣት በራሳቸው ጊዜ መጠየቃቸው ጥቂት በማይባሉ ወገኖች ዘንድ በበጎ ታይቶላቸው ምስጋናን አትርፎላቸዋል፡፡

ያመረሩባቸው አቤቱታ አቅራቢ ወገኖች ግን፣ “ቀድሞም መጠቆም አልነበረባቸውም፤” ይላሉ፡፡ ራሳቸውን የማግለል ጥያቄ ያቀረቡትም፤ የተጠቋሚዎቹ ዝርዝር በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ ይፋ መኾኑን ተከትሎ ከካህናትና ከምእመናን የጎረፈው የተቃውሞ አቤቱታ በቀጣይነት ከሚፈጥርባቸው ተጽዕኖ ለመትረፍ ሲሉ መኾኑን ገልጸው፣ ብርቱ የሥነ ምግባር ችግራቸው የበለጠ መጋለጥና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተመርምሮ ሕጋዊና ዲስፕሊናዊ ርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ ይከራከራሉ፡፡

በቅርቡ የተጠቋሚዎች ዘገባ፣ ከወሎ አህጉረ ስብከት ተዘርዝረው ከነበሩት መካከል የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ጽጌ ሥላሴ መዝገቡ መጠቀሳቸው ስሕተት እንደነበር የገለጹ ምንጮች፤ ለዙሩ ደርሰው የነበሩት የላሊበላ ደብር አለቃ፣ አባ ወልደ ትንሣኤ አባተ እንደነበሩ ተናግረዋል፤ ከዛሬዎቹ የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች ባይካተቱም፡፡

በተጨማሪም፣ የሐዋሳ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ አባ ሀብተ ማርያም ገብረ መስቀል፤ በዕጩነት ካለፉት የመጨረሻዎቹ ተወዳዳሪዎች መካተታቸው ታውቋል፡፡

በርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተሠየመው የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ፣ በቅርቡ እንደሚጠራ ለሚታሰበው ምልአተ ጉባኤ፤ ተጠቋሚ ቆሞሳትንና መነኰሳትን የማጥናት፣ የመመርመርና የማጣራት ውጤቱን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡ የተወዳዳሪዎቹ ዕጩነት በቅዱስ ሲኖዶስ ታምኖበት የጋራ ተቀባይነት ሲያገኙ ምርጫው ተካሒዶ ሢመቱ ሊፈጸም እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

*               *               *

ለ16ቱ አህጉረ ስብከት በየአካባቢው ከተለዩት ዕጩዎች መካከል ለየመንበረ ጵጵስናው የሚፈለጉ ተሿሚዎች ብዛት

 • ከትግራይ – 2
 • ከጎጃም – 3
 • ከጎንደር – 1
 • ከወሎ – 1
 • ከዋግ ኽምራ – 1
 • ከሰሜን ሸዋ – 1
 • ከኦሮሚያ – 3
 • ከጉራጌ – 1
 • ከከምባታና ሐዲያ – 1
 • ከወላይታ – 1
 • ከጋምቤላና ኢሉባቦር – 1

በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለየመንበረ ጵጵስናው በሚካሔደው ምርጫና ሹመት ያለፉ 31 የኤጲስ ቆጶሳት ዕጩዎችና ተወዳዳሪዎች የስም ዝርዝር

ከትግራይ አህጉረ ስብከት

አባ ገብረ እግዚአብሔር ኃይሉ(መቐለ መድኃኔዓለም)Vs.
አባ ጥዑመ ልሳን ኪዳነ ማርያም(የአ/አበባ ማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ካቴድራል አለቃ)

አባ ኢያሱ ገብረ አልፋ(የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የቅኔ መምህር)Vs.
አባ ዘርዓ ዳዊት ኃይለ ሥላሴ(የመርካቶ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል አለቃ)፤

ከጎጃም አህጉረ ስብከት

አባ ወልደ ሐና ጸጋው(የባሕር ዳር መካነ ቅዱሳን ቤተ ደናግል ገሪማ እናቶች ገዳም አስተዳዳሪና የሀገረ ስብከቱ ሊቃውንት ጉባኤ)Vs.
አባ ገብረ ሥላሴ ጎበና(የካርቱም መድኃኔዓለም ደብር አለቃ)፤

አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ መንግሥቱ(ጀርመን – በርሊን ቅዱስ ዐማኑኤል)Vs.
አባ ገብረ ሥላሴ ይርሳው(የአዲስ አበባ ጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል ደብር አለቃ)፤

አባ ገብረ ሥላሴ(ኢየሩሳሌም ገዳም)Vs.
አባ ኅሩይ ወንድ ይፍራው(አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት)፤

ከጎንደር አህጉረ ስብከት

ሊቀ ሊቃውንት አባ ዕዝራ ሐዲስ(የጎንደር መድኃኔዓለም አለቃና የአራቱ ጉባኤያት መምህር)Vs.
ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ(የመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ)፤

ከወሎ አህጉረ ስብከት

አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎርዮስ(የጎፋ ጥበበ እድ ማሠልጠኛ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ)Vs.
አባ ሳሙኤል ገላነው(የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ኮሌጅ መምህር)፤

ከዋግኽምራ ሀገረ ስብከት

አባ ወልደ ዐማኑኤል(የባሕር ኪዳነ ምሕረት ገዳም አበምኔት)Vs.
አባ ብርሃነ መስቀል ዕንቊ ባሕርይ ወልዱ

ከሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት

አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ(የናዝሬት ቅድስት ማርያም ደብር አለቃ)Vs.
አባ ፊልጶስ አሻግሬ(አሜሪካ – ሚችገን ዴትሮይት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደብር)፤

ከኦሮሚያ አህጉረ ስብከት

አባ ገብረ ሕይወት ፍሥሓ(ጀርመን – ሙኒክ)Vs.
አባ ሞገስ ኃይለ ማርያም(የመናገሻ ቅድስት ማርያም አለቃ)፤

አባ ኃይለ ሚካኤል ወልደ አምላክ(የደብረ ሊባኖስ ገዳም መጽሐፍ መምህር)Vs.
አባ ተክለ ወልድ ገብረ ጻድቅ(የደብረ ጽጌ ማርያም አለቃ)፤

አባ ወልደ መድኅን ተክለ ብርሃን(እንጦጦ ቅዱስ ራጉኤል)Vs.
አባ ዘተክለ ሃይማኖት(ደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል ሰባኬ ወንጌል)፤

ከጉራጌ ሀገረ ስብከት

አባ ዘድንግል ኑርበገን(ፈረንሳይ)Vs.
አባ ገብርኤል ወልደ ዮሐንስ(ቡታጅራ ቅድስት ማርያም ደብር አለቃ)፤

ከከምባታ እና ሐዲያ ሀገረ ስብከት

አባ ኄኖክ ተክለ ጊዮርጊስ(የመካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ደብር አለቃ)Vs.
አባ ሚካኤል ገብረ ማርያም(የሆሳዕና ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ)፤

ከወላይታ ሀገረ ስብከት

አባ ዮሐንስ ገብረ ሥላሴ(የወላይታ ሥራ አስኪያጅና የደ/መንክራት አቡነ ተክለ ሃይማኖት አበምኔት)Vs.
ሊቀ ጉባኤ አባ ሀብተ ማርያም ገብረ መስቀል(የሐዋሳ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ)፤

ከጋምቤላና ኢሉባቦር አህጉረ ስብከት

አባ ተክለ ሃይማኖት ንጉሤ(የጋምቤላ እና ደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ)፤

Advertisements

72 thoughts on “ሰበር ዜና – የኤጲስ ቆጶሳት የመጨረሻዎቹ 31 ዕጩዎችና ተወዳዳሪዎች ታወቁ

 1. Anonymous August 4, 2016 at 9:34 am Reply

  “አድኅነኒ እግዚኦ እስመ ኀልቀ ኄር፣ አቤቱ አድነኝ ደግ ሰው አልቋልና” በሚል መሪ ጥቅስ የሚጀምረው ደብዳቤው “… ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የወደቀችበትን አዘቅት ስንመለከት ትንቢቱ ደርሶ ሊቃውንቱን፣ ካህናቱንና ምእመናኑን በብዙ መንገድ አንገት ያስደፋ ተግባር ተከስቷል፡፡ እየተከሰተም ይገኛል፡፡ በሁሉም ስፍራ በመንፈሳዊው አሰራርና አኗኗር ደግ ሰው አልቋልና አቤቱ አድነኝ የሚለው ዝማሬ የሁሉም እንጉርጉሮ ከሆነ ቆይቷል፡፡” ካለ በኋላ ቤተ ክርስቲያኗ “ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ያለው ጊዜ ቁልቁል የወረደችበት፣ የነበረው ክብርዋ ጥላሸት ተቀብቶ አኩሪ ታሪኳ ተቀብልሶ መብቷንና ኃላፊነቷን ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ አሳልፋ ለማይመለከታቸው አካላት ያስረከበችበት፣ ዶግማና ቀኖናዋ ፈተና ላይ የወደቀበት” ጊዜ መሆኑን ገልጿል፡፡ በማስከተልም አስመራጭ ኮሚቴው የፈጸማቸውን ስሕተቶችና ጥፋቶች በሚከተሉት ስድስት ነጥቦች ሥር በዝርዝር አቅርቧል፡፡
  ፩። ፍትሕ መንፈሳዊንና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መጣሱ
  ፪። በምንኩስናና በመነኮሳት ህልውና ላይ የፈጠረው አደጋ
  ፫። የቤተ ክርስቲያንን ዓላማ በሚጻረር መልኩ ጵጵስናን በብሔርና በጎጥ እንዲሆን ማድረጉ
  ፬። ኮሚቴው የመንፈስ ቅዱስ ጥሪ የሆነውን ጵጵስናን ለገንዘብ ፍጆታ ማዋሉ
  ፭። ያለ ብሔራቸው የተቀመጡትና በአገልግሎት ላይ ያሉትን ሊቃነ ጳጳሳት የሚያፈናቅል ተግባር መሆኑ፣
  ፮። በሀገር ደኅንነትና ሰላም ላይ ሥጋትን የሚያመጣ መሆኑ በሚሉት ነጥቦች ስር በማስረጃ የተደገፈና ምክንያታዊ የሆነ አስተያየትና ሐተታ አቅርቧል፡፡
  በመጨረሻም በደብዳቤው ኮሚቴው ስለፈጸመው ስሕተት በሕገ ቤተክርሰቲያን እንዲጠየቅና የሄደበት የተሳሳተ መንገድ ያቀረበው የተጭበረበረ ጥቆማም እንደገና እንዲመረመር ተጠይቋል፡፡ ፓትርያርኩና ብፁዓን ጳጳሳት ጉዳዩን በቀላሉ እንደማያልፉት እምነት አለን ያሉት የተቃውሞ ድምጻቸውን ያሰሙት ሊቃውንቱ፣ የደብር አለቆቹ፣ ካህናቱና ሰባክያነ ወንጌሉ “በምንም ምክንያት እንዲሆን ከተደረገ ግን ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳንና ቤተ ክርሰቲያንን ለመታደግ ሲባል በአደባባይ ተቃውሞአችንን ለመግለጽ የምንገደድ መሆኑን ስናሳስብ በትሕትና ነው፡፡” ብለዋል፡፡
  ደብዳቤው ከተነበበ በኋላ ከተቃውሞ ድምጽ አሰሚዎቹ የተሰጡ አስተያየቶች የነበሩ ሲሆን ከአስተያየቶቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
  · ጵጵስናውን ላያገኙት ነገር ተደብቀው ያሉ ሁሉ ተሰድበዋል
  · አስመራጭ ኮሚቴው ሙያ ተኮር ምሁራንን አላካተተም ቢያንስ ላወጣው የቤተክርስቲያን መስፈርት ተጠያቂ መላሽ ጳጳሳትን አላካተተም፡፡
  · የቀረቡት ማስረጃዎች ፎርጅድ ለመሆናቸው ማረጋገጫ አለን፣ የሐዲሳት፣ የቅኔ፣ የመጻሕፍት መምህራን ነን ብለው ያቀረቡ ሰዎች በዚህ ሙያ እንዳላለፉ ማረጋገጫ አለን፡፡
  · ገንዘብ ተጠይቀን ሰጥተናል ያሉ ገጥመውናል እውነት ነው ማለት ነው፡፡
  · ጥሩ የዘሩ ተገልብጠው አሁን ኮሚቴው ጓያ ዘራበት
  · ሂደቱ አስከፊ ከመሆኑ የተነሣ የአብነት መምህራን፣ የቆሎ ተማሪዎች፣ ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን አላካተም
  ይባልንጂ ጉደዮ ሌላ ነው እሱም ከብሔር ብሔረሰቦች ጳጳስ መሾም ዛሬ አይደለም የተጀመረ ይህንን የከፈሉትና የቀደድቱ
  አባ ጳዉሎስ ናቸዉ የደብር እልቅና ያመክሮስራ ልምድየለላቸውን እየጠሩ የቮሟቸዉ
  አሁን ኮሚቴው በትክክል ነው የሰረው
  ነገሩ ግን የትግሬመነኮሣት በብዛት እኞስካልተቮምን ድረስ ሹመቱ እደይፈፀም አድማ እየቀሰቀሱ ነዉ
  ምክንያቱም በሁሉም ሀገሬቱ እነሱናቸዉ ቛንቛባይችሉም ልብሱን እያለበሱ የሚልዃቸዉ
  በትግረይ ግን ከትግሬዉጭ ወይፍንክች
  ለምሣሌ ምሥራቅ ሀረርጌ ትግሬ ምራብሀረርጌ ትግሬ አዳማትግሬ ጂማ ትግሬ ወላይታ ትግሬ ሙተዋልእንጂ ስለዚህ
  መተዳደሪያስላረጉት ለምንያመልጠናል በማለት ምግባረብልሹወች የትግሬ መኮሣት ናቸው ህዝቡ አልደገፈዉም
  ኮሚቴዉ በሙስና ወድቛል በለውየሀሰት ፓሮፓጋንደ ለፖትርያሬኩ እየነዙ ስራቸዉን እደያከናዉኑ እየረበሿቸዉ
  የሚገኙት ፀሎት ፀሎት ያስፈልጋል ይቆየን

 2. Anonymous March 16, 2017 at 7:41 am Reply

  ሊቀሊቃውንት ይመረጡጥሩ ነው 2ኛም አባወልደ ሀና ይመረጡ

 3. […] ዕቅድ መነሻ፣ በኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ የተለዩት 31 ዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ግለ ታሪክ ለምልአተ ጉባኤው ቀርቦ […]

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: