ጵጵስናው ያልተሳካላቸው አባ ገብረ ሕይወት ገ/ሚካኤል: “በዶላር ተሽጧል” አሉ፤ በዘማነታቸው ከድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል እልቅና ተባረሩ!

Nibure'Ed Aba Gabrehiwot Gabremikael

 • ሰበካ ጉባኤ አባሏን፣ በምሽት እየደወሉ በብልግና ጥያቄዎች ሲያስጨንቁ ቆይተዋል፤
 • ምንኵስናቸው እንደማይከለክላቸውና ሲሾሙ እንደሚወስዷቸው በመግለጽ አባብለዋል፤
 • “ሲያስጨንቁኝና ዕንቅልፍ ሲነሱኝ ስለቆዩ ላጋልጣቸው ወሰንኩ”/ተበዳዩዋ ምእመንት/
 • የክህነት አገልግሎታቸውበቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተመርምሮ እንዲወሰን ተጠይቋል፤
 • በሕዝቡ ጥያቄና በሊቀ ጳጳሱ መመሪያ፣ የወር ደመወዝ ተሰጥቶአቸው ተሰናብተዋል!
 • ቀድሞም ከአኵስም ጽዮን ንቡረ እድነት የተነሡት፣ ቀኖናዊ ባልኾነ ድርጊታቸው ነው፡፡

*                *               *

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በየአህጉረ ስብከቱ ክፍት በኾኑ መንበረ ጵጵስናዎች ብቁ ኤጲስ ቆጶሳትን መርጦ ለመሾም ባለው ዕቅድ መሠረት፣ ከድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ከተጠቆሙት አባቶች አንዱ የነበሩትና በመጀመሪው ዙር ማጣሪያ የወደቁት የሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል አስተዳዳሪ፣ ንቡረ እድ አባ ገብረ ሕይወት ገብረ ሚካኤል፣ “ጵጵስናው በገንዘብ ተሽጧል” ማለታቸው ካህናትንና ምእመናን ያስቆጣ ሲኾን፤ እየፈጸሙት ባለው የዝሙት ነውርና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የኾነ ድርጊት ከሓላፊነታቸው እንዲወገዱ ሲቀርብ በሰነበተው ጥያቄ መሠረት፣ ዛሬ፣ ሐምሌ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል በተላለፈ መመሪያ እንዲሰናበቱ መደረጉ ተገለጸ፡፡

የካቴድራሉ 16 መምህራን፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት፤ ትላንት፣ ሐምሌ 8 ቀን 2008 ዓ.ም.፣ በአድራሻ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ በግልባጭ ደግሞ ለሊቀ ጳጳሱና ለሰበካ ጉባኤው ጽ/ቤት፣ ባቀረቡት የተቃውሞ አቤቱታ፤ አስተዳዳሪው ንቡረ እድ አባ ገብረ ሕይወት፣ ወደ አንዲት የሰበካ ጉባኤው አባል፣ ለወራት ስልክ እየደወሉ በአጸያፊ ንግግሮች ለዝሙት ድርጊት መወትወታቸውንና በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ የሚሰጠውን የማዕርገ ጵጵስና ሹመት“በገንዘብ ተሽጧል” እያሉ ሲናገሩ መደመጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ጡመራ መድረኩ የደረሰውና፣ አስተዳዳሪው ለዝሙት በሚያነሣሡ(sexually explicit) ቃላት ለማግባባት በሚጥሩበት የስልክ ምልልሳቸው፣ “ጵጵስናው በዶላር ነውኮ የኾነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ምእመንዋ፣ ባለትዳርና የልጆች እናት እንደኾነች፤ እርሳቸውም፣ ለጵጵስና እንደተጠቆሙ መስማቷንና መነኵሴ እንደኾኑ በማስታወስ፣ ከኃጢአትና ከሕገ ወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማሳመን ብትሞክርም፣ “አይከለክለንም፤ ችግር የለውም” ያሉት ንቡረ እድ አባ ገብረ ሕይወት፣ “ስሾም ይዠሽ እሔዳለኹ፤ አመነኵስሽና እኅቴ ናት ብዬ አስቀምጥሻለኹ” ለማለት አላፈሩም፡፡ 182 ደቂቃ የሚወስድ ነው በተባለው የስልክ ምልልሱ፣ “እንኳን ከአንድ መነኵሴ ከተራ ምእመን እንኳ የማይጠበቅ፣ በጣም አጸያፊና ብልግና የተሞላባቸው” ሌሎችም ነገሮች መሰማታቸውን የዜናው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ካለፈው ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ አንሥቶ፣ በካቴድራሉ የሰበካ ጉባኤ አባልነት ተመርጣ በማገልገል ላይ እንዳለች የጠቀሰችው ምእመንዋ በበኩሏ፤ አስተዳዳሪው፣ በሰበካ ጉባኤው ጽ/ቤት በተመዘገበው የእጅ ስልክ አድራሻዋ፣ ላለፉት ወራት፣ ከምሽቱ 2፡00 እስከ 3፡00 እየደወሉ፣ ሲያስጨንቋትና ዕንቅልፍ ሲነሥዋት መቆየታቸውን፣ ለሰበካ ጉባኤው ጽ/ቤት በጻፈችው ደብዳቤ አስታውቃለች፡፡

ከተደጋጋሚ ድርጊታቸው የማይማሩና፣ እንዲያውም ለነውራቸው ሃይማኖታዊ ሥዕል እየሰጡ በቆብ ውስጥ በመደበቅ ምእመኑን በእምነቱና በቤተ ክርስቲያኑ ተስፋ የማስቆረጥ ተግባር እየፈጸሙ እንደኾነ ሲገባኝ፤ ወሳኝ ጉዳዮችን እያዋዛኹ በመጠየቅ በቀረጽሁት ቃላቸው ላጋልጣቸው ወሰንኩ፤” ትላለች ምእመንዋ፣ በደብዳቤዋ፡፡

አያይዛም፣ እንዲህ የምንኵስና ጭንብል አጥልቀው ቤተ ክርስቲያንን የሚያሳጡና የሚያስነቅፉ ሰው ላይ፣ ሰበካ ጉባኤው ከጥፋታቸው የሚመለሱበት አስተማሪ ርምጃ እንደወስድባቸው ጠይቃ፣ “ለዚኽም አስፈላጊ ማስረጃዎችን ኹሉ ለማቅረብ ዝግጁ ነኝ፤ ጽ/ቤቱ አፋጣኝ መፍትሔ የማይሰጠኝ ከሆነ ግን በየደረጃው ወደሚቀጥለው አካል የምሔድ መሆኔን አሳውቃለሁ፤” ስትልም አሳስባ ነበር፡፡

ነውረኛው አስተዳዳሪ፥ በፈቃደ ካህን፣ በምክረ ካህን ተወስነው በቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው ጸንተው በሰበካ ጉባኤ አባልነት የሚያገለግሉትን ምእመን ለዝሙት ለማነሣሣትና ከእግዚአብሔር መንገድ ለማውጣት በመጣራቸው ልባቸው በሐዘን መድማቱን የካቴድራሉ ካህናት፣ የአስተዳዳሪው ድርጊት ኮንነዋል፡፡ ንቡረ እዱ፣ መንፈሳዊ አገልግሎት ለመፈጸምም ሆነ ካቴድራሉን በአስተዳዳሪነት ለመምራት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ ያሉባቸውን በደሎች ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ባስገቡት ባለስድስት ነጥቦች አቤቱታቸው ዘርዝረዋል፡፡

ካህናቱ እንደሚሉት፣ አስተዳዳሪው፡- ማኅበረ ካህናቱን በአንድ ዓይን በማየት አስተባብረው በፍቅር ከማገልገልና ከማስገልገል ይልቅ፣ በመከፋፈልና በመለያየት ሠራተኛውን አንድነት ለማሳጣት ይጥራሉ፤ በገባሬ ሠናይ ቀድሰው፣ ቁጭ ብለው ሥጋ ወደሙን ለምእመናን በማቀበል ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ይጥሳሉ፤ በጾመ አርባ፥ መምህራኑ በስብሐተ ነግህ፤ ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ በሰዓታቱና በቅዳሴው፤ ምእመናኑ በመጾምና በማስቀደስ ከእግዚአብሔር ዋጋ ለማግኘት ተግተው በሚያገለግሉበትና በሚጾሙበት ወቅት፣ ለስብሐተ ነግህም ሆነ ለኪዳን እንኳ ወደ ቤተ ክርስቲያን አልመጡም፤ በምትኩ አርፍደው እየመጡ፥ እንደዚህ አይቀደስም፤ እንደዚህ አይገለገልም፤ በማለት በጾም ወራት ግራ ሲያጋቡና ሲያበጣብጡ ከርመዋል፤ ከካቴድራሉ ርቀው በመከራየትና በወር 8ሺሕ400 ብር እንዲከፈልላቸው በማስገደድ ካቴድራሉን ለከፍተኛ ወጪ ዳርገውታል፤ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ወጥ ለማድረግ በሀገረ ስብከቱ የተላለፈውን መመሪያ ባለመቀበልና የራሳቸውን መመሪያ በትእዛዝ መልክ በማስተላለፍ ሠራተኛውን ትርምስ ውሰጥ ለመክተት እየጣሩ ነው፡፡

በመኾኑም፣ ከአስተዳዳሪው ጋር፣ “መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት የማንችልበት ደረጃ ደርሰናል፤ በተለይ ዓይን ያወጣና ልማድ ያደረጉት ዘማዊነታቸው፣ በምእመናን ዘንድ የአባትነት ማዕርጋችንን ተቀባይነት የሚያሳጣና ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓትም አንፃር ነገ ከነገ ወዲያ የሚያስጠይቀን ነው፤” ያሉት ካህናቱ፤ ነገሮች ወደአልኾነ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ በአስቸኳይ ከአስተዳዳሪነታቸው እንዲያነሣቸው፤ እየፈጸሙት ያለው ነውርም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተመርምሮና ተጣርቶ በክህነት አገልግሎታቸው ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት አመልክተዋል፡፡

አስተዳዳሪው፣ በምእመንዋ ላይ የፈጸሙት በደል በሰፊው መሰማቱን ተከትሎ፣ አቤቱታ ያነሡባቸውን ወገኖች፣ የአንዳንድ ብፁዓን አባቶችን፣ የመንግሥትንና የፓርቲ ባለሥልጣናትን ስም በመጥራት ለማስፈራራት ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም፡፡ እንዲያውም፣ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው ከካቴድራሉ እንዲወጡ ካልተደረገ፣ ካህናቱ እንደማያገለግሉ፤ የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ ምእመናንና የሀገር ሽማግሌዎችም፣ ተቃውሟቸውን በማጠናከር የተለያዩ ርምጃዎችን እንደሚወስዱ በመግለጻቸው፣ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ለሀገረ ስብከቱ በሰጡት መመሪያ መሠረት፣ ዛሬ ከቀትር በኋላ ከካቴድራሉ ሓላፊነታቸው መሰናበታቸው ታውቋል፡፡

aba gabrehiwot gabremikael2
በብፁዕነታቸው መመሪያ መሠረት፣ ከካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ጋር የተነጋገረው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ ካለፈው ዓመት ጥር መጀመሪያ አንሥቶ ካቴድራሉን በአስተዳዳሪነት የመሩት ንቡረ እድ አባ ገብረ ሕይወት ገብረ ሚካኤል፣ የአንድ ወር ደመወዛቸው ተሰጥቷቸው እንዲሰናበቱ መደረጉ የተገለጸ ሲኾን፤ ማዕርገ ምንኵስናቸውን ያዋረዱበት የዝሙት ተግባራቸው ከቀረቡት ማስረጃዎችና አቤቱታዎች አንፃር ተመርምረው በሥልጣነ ክህነት አገልግሎታቸው ቀጣይነት ላይ ውሳኔ እንደሚተላለፍ ተጠቁሟል፡፡

ንቡረ እድ አባ ገብረ ሕይወት ገብረ ሚካኤል፣ በሕዝብ ጥያቄና ግፊት ሲባረሩ፣ የአኹኑ ለኹለተኛ ጊዜ ሲኾን፣ የመጀመሪያው፣ ከአኵስም ጽዮን ንቡረ እድነት ሥራቸው የተነሡበት የጥቅምት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. የቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ነው፡፡ በወቅቱ የማእከላዊ ዞን ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሰላማ እያሉ፣ “ቅዱስ” በማለት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የኾነ ድርጊት በመፈጸም፤ ካህናቱና ምእመናኑ፣ “አቡነ ሰላማ ይነሡልን” ብለዋል በሚል የሐሰት አቤቱታ ማቅረባቸው በአጣሪ ልኡክ በመረጋገጡ ነበር፣ ከሓላፊነታቸው የተወገዱት፡፡

Nibure'd Aba Gabrehiwot Gabremikael00
ከንቡረ እድነት ሥራቸው በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ተወግደው፣ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት መጥተው ሪፖርት ካደረጉ በኋላ፣ በድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ባለፈው ዓመት ወርኃ ጥር ሲመደቡ፤ የአኵስም ጽዮን ታሪካቸውን ያወቀው የካቴድራሉ ምእመን፣ መመደባቸውን በመቃወሙ፤ ዛሬ በሐፍረት እስኪሰናበቱበት ድረስ ግንኑኘታቸው በውጥረት የተሞላና መተማመን የራቀው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

በመኾኑም፣ የዛሬው የብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ መመሪያ፤ ሕዝቡ፣ የምንኵስና ቆብን ጭምብል ያደረጉ ነውረኛ አማሳኞችን ከውስጥና ከውጭ ግብረ አበሮቻቸው ጋር ድል አድርጎ ቢያንስ ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ አለኝታውን ያሳየበት ተጋድሎ አስደሳች ፍፃሜ ነው፤ ለማለት ይቻላል፡፡ በ1968 ዓ.ም. የተመሠረተው የካቴድራሉ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን፣ በዕድሳቱ ወቅት በተፈጸመበት ዘግናኝ ምዝበራ ሲታወክ ቆይቷል፡፡

ለስድስት ዓመታት ከመቅደሱ ወጥቶ በመቃኞ የነበረው ታቦቱ፣ ባለፈው ዓመት ሐምሌ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመልሶ የገባውም፣ የከተማው ቀናዒና ተሟጋች ምእመናን ባለመታከት ባደረጉት መንፈሳዊና ሞያዊ ጥረት እንደነበር ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

Advertisements

2 thoughts on “ጵጵስናው ያልተሳካላቸው አባ ገብረ ሕይወት ገ/ሚካኤል: “በዶላር ተሽጧል” አሉ፤ በዘማነታቸው ከድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል እልቅና ተባረሩ!

 1. Gabriel Kuloba July 23, 2016 at 5:09 pm Reply

  Hello hara tewahido . I would like to say somethhing about Aba Hiruy wondyifraw. He is not completely qualified for being Bishop. He did everything bad from this world . Some of them are
  1. He borrowed money from one of church members and refused to pay back. He loves money more than God
  2. People say that he watches sex movies
  3. He said that he regretted to be monk
  4. He said that he paid 70000 birr before to be Bishop
  5. In general he is not Monk.
  Please you can get more information about him and try to post in order to protect our church from this evil person.
  Please post something before the final.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: