የኮሌጆቻችን ምሩቃን: እንኳን ደስ አላችኹ፤ በጎች ምእመናንን በአደራ የተቀበላችኹበት ቀን ነው፤ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ምስክር መኾን ይጠበቅባችኋል

grad class of 2008

 • በቀጣዩ ዓመት የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ወደ ሙሉ ዩኒቨርስቲ ይሸጋገራል
 • የሥርዓተ ትምህርቱና የዩኒቨርስቲ ኮሌጆች አወቃቀር ጥናቱ እየተከናወነ ነው
 • አጋዥ የዕውቀት ዘርፎች የሚበለጽጉበት ማዕከል ይኾናል /አቡነ ጢሞቴዎስ/
 • የማይነጥፉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ምንጭ ይኾናል /አቡነ ዲዮስቆሮስ/
 • የዕውቀት ችሎታን ከፍ ለማድረግ እንጂ ለይስሙላ አልተደረገም/ፓትርያርኩ/

*               *               *

ያለፉት ኹለት ሳምንታት፣ ለቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳውያን ኮሌጆች፣ የደቀ መዛሙርት ምረቃ ሳምንታት ነበሩ፡፡ ከሦስቱም ኮሌጆች፥ በተለያዩ የቀን መደበኛ፣ የማታ ተከታታይና የርቀት መርሐ ግብሮች የተመረቁት ደቀ መዛሙርት አጠቃላይ ብዛት 604 ነው፡፡

ከእኒኽም፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፡- 287፤ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፡- 237፤ የአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ቅዱስ ፍሬምናጦስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፡- 80 ደቀ መዛሙርትን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ አስመርቀዋል፡፡

ምሩቃን ደቀ መዛሙርትንና ዕጩ መምህራንን በሙሉ፤ እንኳን ደስ ያላችኹ፤ እያልን፣ መልካም የአገልግሎት ጊዜ እንመኝላቸዋለን፡፡ በምረቃው መርሐ ግብራት ላይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የኹለቱ ኮሌጆቹ የበላይ ሓላፊዎች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ጢሞቴዎስ እና አቡነ ሕዝቅኤል እንዲኹም ሓላፊዎች እና መምህራን ካስተላለፉት ምዕዳንና ትምህርቶች የሚከተሉትን መልእክቶች አቅርበናል፡፡


on grad of St. Paul college ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

“ወይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ንዑ ትልዉኒ ወእሬስየክሙ መሠግራነ ሰብእ”(ማር.1፥17-18)

ከኹሉ በፊት ለዓመታት የደከማችኹበትን የቤተ ክርስቲያን ትምህርታዊ ቅዱስ ተልእኮ በተመደበላችኹ ጊዜ በማጠናቀቅ፣ በዛሬው ዕለት ለመመረቅ በመብቃታችኹ እንኳን ደስ አላችኹ፡፡

እግዚአብሔር ፍጥረታትን ካለመኖር ወደ መኖር ሲያመጣ ዓላማና ግብ አለው፤ ፍጥረታትም ከፈጣሪ በጸጋ የተሰጠና የየራሳቸው የኾነ ተልእኮ አላቸው፤ ይልቁንም አእይንተ እግዚአብሔር የኾኑ ካህናት፣ በዚኽ ዓለም ከኹሉም የላቀ፣ የሰው ሕይወትና የፍጡራን ህላዌ፣ እንዲኹም በምድር ሥነ ተፈጥሮ ጥበቃ ከባድ ሓላፊነት አላቸው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ፍጥረት በአጠቃላይ ቅዱስና ክቡር ነውና በካህናት በኩል ተገቢ ጥበቃ እንዲደረግለት እግዚአብሔር የውክልና ሥልጣን ከአደራ ጋር ለቤተ ክርስቲያን ሰጥቶአል፤ “ሰውን የምታጠምዱ አደርጋችኋለኹ” የሚለው ኃይለ ቃል ይኸው የካህናት ሥልጣንና ተልእኮ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በዚኽ ዓለም ሰው ኾኖ የተገለጠበት ዓቢይ ዓላማ፣ የሰው ልጅን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመጥራትና ለማብቃት ነው፡፡ ጥሪውን ለሰው ኹሉ የማዳረስ ተግባር እርሱ ባርኮና ጀምሮ ለደቀ መዛሙርቱ፣ ማለትም ከሐዋርያት ጀምሮ እስከ ዕለተ ምጽአት በእግዚአብሔር ልዩ ጥሪ ለምንነሣ ደቀ መዛሙርት አስተላልፏል፡፡ ይህንንም ብቻችንን ኾነን እንደማንወጣው ስለሚያውቅ፣ “እኔ እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ፤” ብሎ በኹሉም ነገር ከእኛ እንደማይለይ ቃል ገብቶልናል፡፡(ማቴ.28፥19)

“ኑ! ተከተሉኝ” የሚለው የጌታችን ጥሪ፣ የግዴታ ሳይኾን የውዴታ ነው፤ የቁጣ ሳይኾን የፍቅር ነው፤ የባርነት ሳይኾን የነፃነት ነው፤ የሎሌነት ሳይኾን የወዳጅነት ነው፤ ክርስቲያኖች ኹሉ የተጠሩት በዚኽ ቅዱስ አጠራር ነው፤ ይልቁንም ዛሬ በመመረቅ ላይ የምትገኙ ደቀ መዛሙርት ልጆቻችን፣ በዚኽ ቅዱስ ጥሪ ለላቀ ሓላፊነትና አገልግሎት እርሱም ሰውን ኹሉ በቃለ ወንጌል መረብ በማጥመድ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ልትሰበስቡ ተጠርታችኋል፡፡

ከአኹን ጀምሮ እግዚአብሔር ከእናንተ አዎንታዊና ተግባራዊ የኾነ ግብረ መልስ ይጠብቃል፤ “ተከተሉኝ” የሚለው ጽዋዔ እግዚአብሔር ለዐራት ዓመታት ያኽል በጥልቀትና በተደጋጋሚ በጆሯችን ፈሷል፤ አኹን የሚቀረው እርሱን በእግር መከተል፣ በግብር መምሰል ነው፤ የዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርት “ኑ! ተከተሉኝ” ሲባሉ ሳይውሉ ሳያድሩ ወዲያውኑ አዎንታዊ ተግባራዊ መልስ ሰጥተዋል፡፡ መጽሐፉ “ወሐድጉ መሣግሪሆሙ ወተለውዎ ሶቤሃ፤ ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት” ይላል፡፡

የዛሬ ተመራቂ ደቀ መዛሙርትስ፣ ማለቂያ የሌለውን አመክንዮውን እርግፍ አድርጋችኹ በመተው፣ በአገልጋይ እጥረት የተዘጋችውን የገጠር ቤተ ክርስቲያን ለመክፈት፣ በወንጌል ረኀብ የተጠቃውንና ጠባቂ እንደሌለው በግ እዚያም እዚኽም የሚወራጨውን የኦርቶዶክስ ወጣት ልጅን ለመታደግ ተዘጋጅታችኋል ወይ? ምላሻችኹ አዎን እንደሚኾን ተስፋ እናደርጋለን፤ የቤተ ክርስቲያን ዓቢይ ተልእኮ ይኸው ነው፤ አባቶቻችን ይህችን ቤተ ክርስቲያንና ይህችን ሀገር ያቆዩልን በተንደላቀቀ ኑሮ፣ በተመቻቸ ሕይወት፣ አልጋ በአልጋ በኾነ መንገድ ሳይኾን፤ ከዓለም መራራ ውጣ ውረድ፣ እስከ ኅልፈተ ሕይወት ድረስ መሥዋዕትነትን ከፍለው ነው፡፡

ለእኛም፣ ለእናንተም፣ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ከዚኽ የበለጠ ደስታ የለንምና ኹላችንም እንኳን ደስ አለን፤ በዚኽ ኹሉ ሥራችንን እየባረከ፣ መልካም ምኞታችንን እያሳካ በጎ የኾነውን ዕድል ኹሉ ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር አምላካችን ክብርና ምስጋና ይኹን፤ እያልን፣ አኹንም በድጋሚ እንኳን ደስ አላችኹ፤ እንላለን፡፡

ሃይማኖታችኹንና ሀገራችኹን በቅንነት ለማገልገል ተዘጋጁ፤ እግዚአብሔር ይባርካችኹ፤ ይቀድሳችኹ፡፡

*               *               *

His Grace Abune Dioscoros, EOTC gen mgr.ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ
በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው የደቡብ ምሥራቅ ትግራይና የምሥራቃዊ ዞን ዓዲግራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

“አንትሙሰኬ አእርክትየ አንትሙ እምከመ ገበርክሙ ኵሎ ዘአዘዝኩክሙ = እኔ ያዘዝኋችኹን ኹሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችኹ”/ዮሐ.15፥17/

በክርስቶስ ዐጸደ ወይን ቤተ ክርስቲያን፣ በእግዚአብሔር ተመርጣቸርኹ ያማረ ፍሬ ለማፍራት ዛሬ የተመረቃችኹ ውድ ልጆቻችን፤ እንኳን ለዚኽ ዕለት አደረሳችኹ፡፡

ከላይ የተጠቀሰው ኃይለ ቃል፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አዕማደ ምድር ለተባሉ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ አልጫውን ዓለም ጨው ኾነው የሚያጣፍጡበትን ወንጌለ መንግሥተ ሰማያት፣ በቃል እና በተግባር ለሦስት ዓመታት ከሦስት ወር ካስተማራቸው በኋላ፣ በመጨረሻ፣ እኔ ያዘዝኋችኹን ኹሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችኹ፤ የሚል እውነተኛ አደራ ሰጥቷቸዋል፡፡

ይህ አምላካዊ ትእዛዝ የቤተ ክርስቲያን አደራ ነው፡፡ በሐዋርያት ስም ደቀ መዛሙርት ተብላችኹ ስትጠሩ ቆይታችኹ ዛሬ የተመረቃችኹ ምሩቃን ልጆቻችን፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮዋንና ሐዋርያዊ ትውፊቷን ጠብቃችኹ በማስተማር፣ ሰው ራሱን ለመንግሥተ እግዚአብሔር እንዲያዘጋጅ እንድታደርጉ፤ ቤተ ክርስቲያን ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበለችውን አደራ በግልጥ አስረክባችኋለች፡፡

HHTC02
“ኢትትኀደግ መጽሐፈ ለዝንቱ እምአፉከ ወአንብብ ቦቱ መዓልተ ወሌሊተ ከመ ታእምር ኵሎ ገቢረ ዘጽሑፍ ውስቴቱ እስመ ትረትዕ ፍኖትከ ወቦቱ ትጠብብ = ይህም መጽሐፍ ከአፍኽ አይለይ፤ ሥራኽ ትቀናለችና፣ በሱም ዐዋቂ ትኾናለህና፣ በሱ የተጻፈውን ሥራ ታውቅ ዘንድ በመዓልትም በሌሊትም እሱን አንብብ”(ኢያ.1፥8) የሚለውን በመከተል፣ ያለንበት ዘመን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት በመኾኑ፣ በምንኖርበት ዓለም በዘመኑ ደረጃ በመንፈሳዊ ጥበብ ቤተ ክርስቲያናችን ተሳታፊ መኾን ይኖርባታል፡፡ የዚኽ ጥበብ መሠረቱ፣ በትምህርት አእምሮው የለማ ደቀ መዝሙር፣ መንፈሳዊ ሕይወትን አብዝቶ በሚያለማበት መልኩና ብልሃት ማሰማራት ለቤተ ክርስቲያናችን አስፈላጊ ነው፡፡

በዚኽ ወቅት የቤተ ክርስቲያናችን ፈተና የኾነው፣ የምእመናን ቅሠጣና የምእመናንን ሕይወት የመጠበቅ ዕውቀትና መንፈሳዊ አርኣያ የታጠቀ ትውልድ በኮሌጆችዋ እያፈራች ትገኛለች፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለዚኹ ግንባር ቀደም ተልእኮ ማስፈጸሚያ የሚኾነው ሕንፃ በመገንባት የቤተ ክርስቲያንዋን ትምህርት እስከ ፒኤች.ዲ ለማድረስ ተግቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ የኮሌጁ የልማት እንቅስቃሴ ዋና ዓላማ፣ የማይነጥፉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ምንጭ መኾን እንደኾነ ለመገንዘብ የሕንፃ ግንባታው ይመሰክራል፡፡

በዘመናችን ዓለማዊ ጥበብ ዕውቀት፣ ዩኒቨርስቲዎች እጅግ እየተስፋፉ በመሔዳቸው፣ ሕዝቡን በዚኹ መንገድ እየመሩት በሚገኙበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን በውስን አቅም መንቀሳቀስ የለባትም፡፡ ይልቁንም የጥበብ መንፈሳዊት መሠረት በኾነችው፣ በትምህርተ ወንጌል የጎለመሰ ዕውቀት ያላቸው ምሁራን በብዛትና በብቃት ማፍራት በዚኽ ዘመን የሚጠበቅ የቤተ ክርስቲያን መሪ ተግባር መኾን እንዳለበት ይታመንበታል፡፡

ይህ ለሌሎች መንፈሳውያን ኮሌጆች አርኣያ የኾነ፤ ቤተ ክርስቲያንን በትምህርት የማበልጸግ ተግባር ሌሎች ኮሌጆችም ሊከተሉትና ቤተ ክርስቲያን ተኮር የትምህርት ዘርፎችን ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ ተልእኮዋ፣ ዕቅድዋ፣ የሀብት አስተዳድርዋ ሥርዓትዋን በተከተለ መንገድ በተቋሞችዋ ለማጥናትና በምሁራንዋ ቤተ ክርስቲያናዊ መንፈስ እንድትመረምር ያግዛታል፡፡


እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል፤ እንዳለ ሐዋርያው፣ ቤተ ክርስቲያን በላከቻችኹ ስፍራ ኹሉ ታዝዛችኹ በመሔድ ኢአማንያንን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር በማምጣት፤ አማንያንን በእምነት በማጽናት፤ ዕውቀት ያላቸውን ለቅድስናና ለምስክርነት በማዘጋጀት የተላካችኹበትን የመንግሥተ እግዚአብሔር ዓላማ በመስበክ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ምስክር መኾን ከምሩቃን በእጅጉ ይጠበቃል፡፡

ውድ ምሩቃን ልጆቻችን፤ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ላሉት ልጆችዋ ብዙ ሰባክያንን በምትፈልግበት ወቅት መመረቃችኹ፣ ለትልቅ ዓላማ ነውና፣ ከእግዚአብሔር የተሰጣችኹን መንፈሳዊ ሓላፊነት በታማኝነት ለመፈጸም ጸጋ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይኹን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

*               *               *

Dr. Abune Timothy, Archbishop of Holy Trinity Theological Collegeብፁዕ ዶ/ር አቡነ ጢሞቴዎስ
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ

የኮሌጃችን ታሪካዊ ጉዞ – ከትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርስቲ

በሀገራችን የትምህርት ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የመሥራችነት እና የባለቤትነት ድርሻ የምትይዝ መኾኗ የሚታወቅ ነው፡፡ የጠለቀና የመጠቀ ዕውቀት ይነገርባቸው የነበሩ የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን፣ ለዘመናት የትምህርት ማዕከልነትን ሚና፣ የሃይማኖታዊ እና ባህላዊ መልካም ሥነ ምግባርን ከመፍጠር ጭምር አስተባብረው በመያዝ አኹን ድረስ የማይፋቅ ግዙፍ አሻራ በማሳረፍ በዘመን ተሻጋሪነታቸው ቀጥለው ይገኛሉ፡፡

የአገራችን የትምህርት አደረጃጀት ታሪክ እንደሚነግረን፣ ዘመናዊው ትምህርት መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ፣ ነባሩን የአብነት ትምህርት ዘይቤ መነሻ በማድረግ የተሻለ ጥምረት መፍጠር ይጠበቅ የነበረ ቢኾንም፣ እንዳለመታደል ኾኖ ዛሬ ያለን ሥርዓተ ትምህርት ቋንቋው ጭምር የተውሶ ነው፡፡

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ በ1935 ዓ.ም. በትምህርት ቤት ደረጃ ሲመሠረት ይዞ የተነሣው ዋናው ዓላማ፣ ከላይ ከተጠቀሱት ጥንታዊ የአብነት ት/ቤቶች ተምረው ያለፉትን ሊቃውንት ከዘመናዊው ዓለምና ኹኔታው ጋር የሚያስተዋውቅ ብሎም ለጥምረት የሚያግዝ፣ በዚኽም በኹለቱም ወገን የበቁ ሊቃውንትን ለማፍራት ነው፡፡

በዚኽ ረገድ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት በነበራቸው መልካም ግንኙነት ምክንያት፣ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ጥረት እጅግ የሚመሰገን ሲኾን፣ ትምህርት ቤቱም ወደ ዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ(የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ) የሚገቡ ዕጩዎችን ሲያበቃ ቆይቷል፤ ነገር ግን በዩኒቨርስቲም ደረጃ ቀደም ሲል የተጠቀሱት የቋንቋ እና የሥርዓተ ትምህርት ችግሮች ስላሉ ዘመናዊው ትምህርት ከአብነቱ ሊጠቀም የሚችለውን ወሳኝ ጥቅም ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

እንዲኽ ባለ ኹኔታ ቀጥሎ፣ ጥቅምት 5 ቀን 1960 ዓ.ም. በልዩ ሥነ ሥርዓት፣ ትምህርት ቤቱ “ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ” ተብሎ የኮሌጅነት ማዕርግ አገኘ፡፡ ይህም የመጀመሪያው የአገሪቱ መንፈሳዊ ኮሌጅ መኾኑን ይመሰክራል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ1961 ዓ.ም. ሲመሠረትም፣ ኮሌጃችን በአንድ አካልነት ታቅፎ ቀጠለ፡፡ ይኹን እንጂ ባለፈው ወታደራዊ ሥርዓት ለ17 ዓመታት የተዘጋበት ኹኔታ፣ እስከ አኹን ድረስ በኮሌጁ ዕድገት ላይ በጥቁር ጠባሳነት የሚወሳ ጉዳይ ኾኖ አልፏል፡፡

በኹለተኛው ምዕራፍ የኮሌጃችን ታሪክ፣ በ1986 ዓ.ም. በተደረገው ከፍተኛ ጥረት እንደገና ተከፍቶ እስከዚኽ ጊዜ ድረስ፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በዘመናዊ የትምህርት አቀራረብ በማብቃት የድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

በተደጋጋሚ እንደተጠቀሰው፣ አኹን ኮሌጃችን የሚገኝበት ደረጃ እና የትምህርት አድማሱ የበለጠ መጠናከርና መስፋፋት አለበት፡፡ ለዚኽም ይረዳ ዘንድ፣ ባለፉት ዓመታት ከመደበኛው የትምህርት ፕሮግራም በተጨማሪ የማታ ተከታታይ የትምህርት ፕሮግራም፤ የርቀት ትምህርት ፕሮግራም በሠርተፊኬትና ዲፕሎማ፣ የግእዝ ቋንቋ ትምህርት በዲፕሎማ ደረጃ፤ የኹለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም(ድኅረ ምረቃ) በስልታዊ ትምህርተ መለኰት(Systematic Theology) እና በተግባራዊ ትምህርተ መለኰት(Practical Theology) በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡

በእነዚኽ በየዓመቱ በሚመዘገቡ ዕድገትና የመስፋት ጅምሮች መሠረትነት፣ ኮሌጃችን ወደ ሙሉ ዩኒቨርስቲ ደረጃ የሚሸጋገርበትን ኹኔታ ለመፍጠርም መሠረታዊ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በኮሌጃችን ቅጽር የሚገኘው የግዙፍ ሕንፃ ግንባታ፣ ለዚኽ ዋና ማሳያ ሲኾን፤ በተያያዥነትም የሥርዓተ ትምህርት አዘገጃጀትና የዩኒቨርስቲ ኮሌጆች አወቃቀር ጥናትም እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ስለዚኽ በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ ከመጪው ዓመት ጀምሮ እነዚኽን ጥናቶች በማጠናቀቅ፣ በግንባታ ላይ የሚገኘው ግዙፍ ሕንፃ መጠናቀቅንም ተከትሎ ይህን ሕልም እውን ለማድረግ ከፍተኛ ትግል እያደረግን መኾናችን ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይህም ሲኾን ከትምህርት ቤትነት ደረጃ የመጀመረው ኮሌጃችን ደረጃውን ጠብቆ በመጣ የዘመናት ዕድገት፣ ከዩኒቨርስቲ ደረጃ ደርሶ የማየታችን ጉዳይ ይሳካል ማለት ነው፡፡

ይህ ደረጃ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጠንካራና የተሟላ የጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲኖራት የሚያስችል ነው፡፡ የትምህርተ መለኰት እና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ትምህርቶችን ከመስጠት በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያንን የሚያግዙ ሌሎች የዕውቀት ዘርፎች የሚጠናከሩበትና የሚበለጽጉበት ጠንካራ የዕውቀት ማዕከልም እንደሚኾን እናምናለን፡፡

ውድ ተመራቂዎች፤ ይህ ተስፋ የእናንተም ነው፡፡ ከሠርተፊኬት እስከ ማስትሬት ዲግሪ የደረሰው የትምህርት ዕውቅና በዓላችኹ፣ ነገ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር በዶክትሬት ዲግሪ የሚበሠርበትን ጊዜ እናያለን፡፡

በመጨረሻም ምሩቃን፣ የምሩቃን ቤተሰቦችና በአጠቃላይ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ኹሉ፣ እንኳን ደስ አላችኹ፤ እንላለን፡፡

መጪው የአገልግሎት ጊዜአችኹን እግዚአብሔር ይባርክላችኹ፡፡

*               *               *

His Grace Abune Hizkiel, St Paul college headብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፤ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት፤ የካፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ

“ረዐይኬ አባግዕየ፤ በጎቼን ጠብቅ”(ዮሐ.21፥20)

ይህንን ቃል የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲኾን፣ ከሙታን በተነሣ በ25ኛው ቀን በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጦላቸው፣ ምሳ ከበሉ በኋላ፣ ቅዱስ ጴጥሮስን፣ ትወደኛለኽን? ትወደኛለኽን? እያለ ሦስት ጊዜ ጠየቀው፡፡ ጌታችን፣ ቅዱስ ጴጥሮስን፣ ዶሮ ሳይጮኽ ዛሬ ሦስት ጊዜ ትክደኛለኽ፤ ያለውን በማስታወስ፤ የሰው ልጅ እያመኑት የሚከዳ፤ እየወደዱት የሚጠላ፤ በነበረበት የማይጸና ደካማ ስሑት ፍጥረት መኾኑን ስለተረዳ፣ በትሕትና አንደበት፣ እወድኃለኹ፤ ከማለት ይልቅ “ጌታ ሆይ፥ እንደምወድኽ አንተ ታውቃለኽ” አለው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የተነገረውንና የተደረገውን ብቻ ሳይኾን፣ የታሰበውን ከመነገሩ በፊት፤ ያልታሰበውንም ከመታሰቡ በፊት፤ የሚያውቅ የባሕርይ አምላክ መኾኑን ስለሚያውቅ፣ “እንደምወድኽ አንተ ታውቃለኽ” ብሎ በመመስከሩ የተሰጠው መንፈሳዊ የሥራ ሓላፊነት፣ “በጎቼን ጠብቅ” የሚል ነው፡፡

የሚወዱትን ነገር ኹሉ ለሚወዱት አደራ እንደሚሰጥ ኹሉ፣ ጌታችን እስከ ሞት ድረስ ያፈቀራቸውን ሕፃናት፡- ግልገሎቼን አሰማራ፤ ወጣቶችን፡- ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ ሽማግሌዎችንም፡- በጎቼን ጠብቅ፤ በማለት በፍቅር እንዲጠብቅ ቅዱስ ጴጥሮስን አዘዘው፡፡

መልካም እረኛ በጎቹን በመልካም ቦታ በማሰማራት ከተለያየ አደጋ ይጠብቃል፡፡ ይመግባል፡፡ የባዘነውን ይፈልጋል፡፡ የተሰበረውን ይጠግናል፡፡ ግልገሎቹንም ይሸከማል፤ መንጋዎቹም የእረኛውን ድምፅ ያውቃሉ፤ ይከተሉትማል፡፡ እንደተባለ፣ በበጎች የተመሰሉትን ምእመናንን ጥበቃ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ እና በእርሱ እግር ለተተኩት አገልጋይ ካህናት አደራ ሰጠ፡፡

ዛሬም ጌታችን የሚያፈቅራቸውን ሕፃናት፣ ወጣቶች እና ሽማግሌዎች የኾኑ ምእመናንን፣ በቅዱስ ጴጥሮስ ለተተኩ ለሚያፈቅራቸው አገልጋዮች ለኾንን ለእኛ የመጠበቅ አደራና ሓላፊነትን ሰጥቶናል፡፡

መልካም እረኛ በጎችን ከቀበሮ እንደሚጠብቅ ኹሉ፣ እኛም ምእመናንን ከኑፋቄና ከክሕደት ትምህርት በመጠበቅ፣ ኦርቶዶክሳዊውን ትምህርትና ሥርዓት በማስተማር፤ በሌሎች እንዳይሰረቁና ባዝነው እንዳይቀሩ ልንጠብቅ ይገባል፡፡

በዛሬው ቀን የምትመረቁ ልጆቻችን፣ የበጎች ባለቤት ለማይወደውና ለማያምነው በጎቹን እንዲጠብቅለት አደራ አይሰጥም፡፡ ለሚያምነንና ለሚወደን ለእኛ፣ በበጎች የተመሰሉትን ምእመናን እንድንጠብቅ አደራ የሰጠን፣ እንደ ምንደኛ እረኛ ለጥቅማጥቅም ሳይኾን በፍቅር እንድናሰማራቸው ነው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ከጌታችን በተማረው መሠረት፣ “በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በግድ ሳይኾን በውድ፣ ጥቅምን በመመኘት ሳይኾን በበጎ ፈቃድ ጠብቁ፤ ለመንጋው ምሳሌ ኹኑ እንጂ መንጋውን በኃይል አትግዙ፤” (1ጴጥ.5፥ 2-3) እንዳለ፣ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን እንድንጠብቅ፤ እና በመንጋው ላይ መልካም እረኛ ለበጎች ሊያደርግ የሚገባውን ክብካቤ ለበጎች ባለቤት እስክናስረክብ ድረስ ልንከባከብና ልንጠብቅ አደራ ተቀብለናል፡፡

ዛሬ በምረቃችኹ ዕለት፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እስከ ሞት ድረስ የወደዳችኹን መጠን የለሽ ፍቅሩን በመስቀል ላይ የገለጸላቸው፣ በጎች ምእመናንን በአደራ የተቀበላችኹበት ቀን ነውና እንኳን ደስ አላችኹ፡፡ ዘመናችኹንም ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ ሥራ የምትሠሩበት ያድርግላችኹ፡፡

*               *               *

Mmr. Fisseha Tsion Demoz, Ext Division Headመ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝ
/የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር ሓላፊ/

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ክርስቶስ ምሳሌዎችን እየተጠቀመ ካስተማራቸው ከታላላቅ የታሪክ መዛግብት መካከል አንዱ ነው፡፡ ምሳሌዎቹም የሚደነቁ ምስሎችንና በዓለም ላይ ያሉትን ነባራዊ መልእክቶች በድራማ መልክ የያዙ በመኾናቸው ላለፉት ኹለት ሺሕ ዓመታት የክርስቲያኖችን ቀልብ ማርከው ኑረዋል፡፡ ምሳሌዎቹም፣ ሃይማኖታዊ እውነታን የሚያንጸባርቁ ታሪኮች በመኾናቸው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ በጣም ጥልቀት ያላቸው የነገረ መለኰት ምስጢራትን፣ ምሳሌን እንደ ዘዴ በመጠቀም ለተሰበሰበ ሕዝብ አስተምሯል፡፡

በታሪክ እንደሚታወቀው፣ አይሁዳውያን ከግሪክ ሰዎች ለየት ባለ መልኩ፣ ወደ መደምደሚያ የሚያደርስ ተግባርን ማዕከል ያደረገ ባህል የሚከተሉ በመኾናቸው ምክንያት፣ ምሳሌን እንደ አንድ ጥበብ ይጠቀሙበታል፡፡ ክርስቶስም በትውልዱ አይሁዳዊ እንደመኾኑ መጠን፣ ምስጢር አዘል የኾኑ ትምህርቶቹን በቀላሉ መግባባት ይፈጥር ዘንድ፣ ይህን የአይሁድ ባህል፣ በተለይም በብሉይ ኪዳን ነቢዩ ናታን(2ኛሳሙ.12፥ 1 – 4)፤ ኢሳይያስ(ኢሳ.5፥ 1 – 7) እና ሕዝቅኤል(17፥ 22 – 24) ይከተሉት የነበረውን በምሳሌ የማስተማር ዘዴ ተግባራዊ ሲያደርግ እንመለከታለን፡፡

ሕዝብ በቀላሉ ሊረዳቸው ያልቻላቸውን ጥልቀት ያላቸውን ምስጢራት፣ ምሳሌን ተጠቅሞ ማስረዳት የተለመደ አሠራር በመኾኑ፡- ኹኔታዎችን ይቀይራል፤ የሰማዕያንን ቀልብ የመሳብ ኃይል አለው፤ እንደዚኹም ትምህርትን በምሳሌ የሰማ ሰው አቋም ይይዛል፤ መሐል ሰፋሪ አይኾንም፡፡

በማቴዎስ ወንጌል በ13ኛው ምዕራፍ ውስጥ፣ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል፣ “የዐዋቂው እና የባለመዝገቡ ጸሐፊ” የመጨረሻው ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ምሳሌ ለእያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያናችን የነገረ መለኰት ምሁርና ደቀ መዝሙር፣ ከተማረው የወንጌል ትምህርት አሮጌ እና አዲስ ከሣጥኑ እያወጣ፣ ክርስቲያኖችን እያሠለጠነ ለመንግሥተ ሰማያት እንዲበቁ እንዲያደርግ የቀረበ ጥሪ ነው፡፡

በአይሁድ እምነት ዘንድ ጸሐፍት፣ የነገረ መለኰት ምሁራንና ዐዋቂዎች ናቸው፡፡ ጠበቃዎችና መተርጉማነ ሕግ በመባልም ይታወቃሉ፡፡ በአይሁድ ሕዝብ መካከል የመሪነትን ቦታ በመያዝ በተከበረ ስም መምህር(Rabbi) በመባል ይታወቃሉ፡፡ በሐዲስ ኪዳን ውስጥ የእግዚአብሔርን መንግሥት ማዕከል ያደረገውን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ምንም እንኳ በራስ ወዳድነታቸውና በአስመሳይ ባሕርያቸው የመንግሥተ ሰማያት በር በመዝጋት አቅጣጫውን ቢያስቀይሩት፣ ደቀ መዛሙርት በብሉይ ኪዳን በአይሁድ ጸሐፍት ቦታ ተተክተው የሐዲስ ኪዳን የወንጌል ጸሐፍት ኾነው ከአሮጌው እና ከአዲሱ መዝገባቸው እያወጡ ሰዎችን ለመንግሥተ ሰማያት እንዲያሠለጥኑ የተሾሙ አዲሶቹ ጸሐፊዎች መኾናቸውን ያስገነዘበበት ምሳሌ ነው፡፡

“ስለ እግዚአብሔር መንግሥት” በኹለቱም ኪዳናት የተሟላ ዕውቀት ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተማሩ እነርሱ በመኾናቸው ጥሩውንና መጥፎውን ገምግመው የክርስቲያኖቹን ሕይወት በጥሩ መንገድ መርተው ሕዝቡን ለመንግሥተ ሰማያት እንዲበቁ ማድረግ ነው፡፡

በማቴዎስ ወንጌል ምዕ.2 ቁ.17 ላይ፣ “በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈሳል፤ አቁማዳውን ያጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፤ ኹለቱም ይጠባበቃሉ፤” የሚለውን የጌታን ቃል፣ ተግባራዊ ለማድረግ የተሾሙ ናቸው፡፡

በአኹኑ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ የቤተ ክርስቲያናችን ጸሐፍት ኾነው በአራት እና በአምስት ዓመት የሰበሰቡትን አሮጌውንና አዲሱን የጠለቀ የነገረ መለኰት ትምህርት ተጠቅመው ሕዝቡን በማስተማርና በማሠልጠን፣ የመጨረሻ የቤተ ክርስቲያናችን ግብ ለኾነው ለመንግሥተ ሰማያት እንዲያበቁ የተሾሙት ከነዚኽ ከታላላቅ የነገረ መለኰት ኮሌጆች ተመርቀው የሚወጡ ደቀ መዛሙርት ናቸው፡፡

በሐዋርያት እግር ሥር ተተክተው የሐዋርያትን ፈለግ ተከትለው፣ በሕዝብ መካከል ተሠማርተው፣ ክርስቲያኖች ኦርቶዶክሳዊ እምነታቸውን ጠብቀው እና አጽንተው እንዲይዙ በመምከር የመንግሥቱ ወራሽ ማድረግ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የተጣለ ሓላፊነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊኾን የሚችለው ከአሮጌም ይኹን ከአዲሱ ቀድቶ መስጠት የሚያስችል የተከማቸ የዕውቀት መዝገብ በውስጣችን ሊኖር ይገባል፡፡

የዕውቀት መዝገቡም እንደ ምንጭ ውኃ መቼም ቢኾን የማይደርቅ ኾኖ፣ ከምንጩ በሚፈልቀው አዲስ እና ንጹሕ ውኃ፣ ምእመናን የውኃ ጥማቸውን የሚቆርጡበት መኾን ይኖርበታል፡፡ ከነገረ መለኰት ምሁራን(Theologian) በእጅጉ የሚጠበቅ ነገር ቢኖር፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን በአግባቡ መምራት የሚያስችል በቂ ዕውቀት እና የግል ምግባር መያዝ ነው፡፡ ይህ የሚኾነው የእያንዳንዱ ክርስቲያን ቤተሰብ የሚጠብቅ(Steward) እና የሚንከባከብ(caretaker) ደቀ መዝሙር በመኾኑ ነው፡፡

የክርስቲያኖችን ኹለንተናዊ ዕድገት ለመጠበቅ፣ የአማኞች መንፈሳዊ እና ሥጋዊ ፍላጎታቸውንና ምኞታቸውን በቅርበት መከታተል የሚችል በመኾኑ ባለራእይና የእረኝነት መንፈስ በአእምሮው የተቀረፀ መኾን ይኖርበታል፡፡ ይህን እንድናደርግ የምንገደድበት ትልቁ ምክንያት፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለእግዚአብሔር መንግሥት ቁርጠኛ ኾነን ለማገልገል የገባንበት ቃል ነው፡፡

የመጀመሪያው ቃል፣ በእግዚአብሔር ላይ የሚኖረን ፍጹም እምነት ነው፡፡ በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ በተማርነው ትምህርት መሠረት ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ነው፡፡ ይህን መረዳት ከቻልን፣ ማንኛውም ዓይነት ችግር ማለትም ሃይማኖታዊም ኾነ ሥነ ምግባራዊ ችግር በበሰለ አእምሮና በተረጋጋ መንፈስ መፍታት የምንችልበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን፣ በምድር ላይ ለእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋይ እንደመኾንዋ መጠን፣ እኛ ደቀ መዛሙርትም፣ ለተመሳሳይ የቤተ ክርስቲያን ዓላማ በሀገር ውስጥም ይኹን በውጭ አገር ቁርጠኛ አገልጋዮች በመኾን ኹልግዜ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ተጠብቀው የሚገኙትን አስተምህሮዎች፣ በምልዓት በማስቀጠል ቤተ ክርስቲያንን ማገዝ ነው፡፡ የነገረ መለኰት ደቀ መዛሙርት እንደ መኾናችን መጠን፣ ከምርቃት በኋላ፣ የተማርነውን ትምህርት ለክርስቲያናዊ ሕይወት አገልግሎት ያለውን ሚና በተግባር ማሳየት ይኖርብናል፡፡

መንፈሳዊ ትምህርትን ለማግኘት በጉጉት ለሚጠባበቅ ለተጠማው ሕዝብ፣ መንፈሳዊ ትምህርት ምን ያኽል አስፈላጊ እና ጠቃሚ እንደኾነ ማንጸባረቅ ይኖርብናል፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችን ያለንን የጸና አቋም እና ቁርጠኝነት በተግባር ለማሳየት የምንፈተንበት ጊዜ አኹን መኾኑን ልንረዳው ይገባል፡፡ ይህን ለመፈጸም እንደ ደቀ መዝሙርነታችን ማንነታችንን፣ ክርስቲያናዊ ኩራታችንንና በራስ መተማመናችንን ጠብቀን ጊዜው የሚፈልገውን ሥራ ሠርተን የራሳችንን ታሪክ አስመዝግበን ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡

መጻኢ የአገልግሎት ዘመናችንም የተባረከና ብሩኽ ተስፋ የተሞላበት እንዲኾንልን የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ከኹላችን ጋር ይኹን፡፡

*               *               *

Mmr. Ferdawok Alemayehuመ/ር ፍርዱ(ፍርድ ዐወቅ) ዓለማየሁ
/የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክና የሳይኮሎጂ መምህር/

ለዘለዓለም የሚኖር የአባቶቻቸውን ድንበርና ርስት ለሚያፈርሱ ወዮላቸው
(ኄኖክ 38፥17)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ በአንድ አምላክ የማመንን መሠረት በማጽናት፤ ከዚያም በቅዱስ ፊልጶስ በኩል ጥምቀትና የክርስትና እምነት በ34 ዓ.ም. ወደ ሀገራችን መግባት(የሐዋ. ሥራ 8፥34)፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የታሪክ ባለቤት መኾኗን ያሳያል፡፡ ቀድመው የነበሩ የኢትዮጵያ ነገሥታት፣ ተረፈ አርዮሳውያን ወደ ቤተ ክርስቲያን ዘልቀው እንዳይገቡ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገው አልፈዋል፡፡

እንደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የመሳሰሉ የቤተ ክርስቲያን ድንቅ አባቶች መጽሐፈ ምሥጢር በተባለ ድርሰታቸው ላይ፤ የአርዮስን፣ የንስጥሮስን፣ የአውጣኪን፣ የአርጌንስን፣ የልዮንና የሌሎችንም ሐሳብ የሚቃወም ማብራሪያ ጽፈዋል፡፡ በወቅቱ ለተነሡት መናፍቃን ልዩ ልዩ መጻሕፍትን ጽፈው አኑረውልናል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስን በመስበክ በማስተማር ከዓለም ግንባር ቀደም መኾኗን ዓለም አቀፍ ሚዲያ የኾነው ቢቢሲ፣ የ2008 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓልን አስመልክቶ ባቀረበው ዘገባ፡- “በዓለም ላይ ትክክለኛ እምነታቸውን በተግባር የሚያሳዩ ኢትዮጵያውያን ናቸው፤” በማለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ቀዳማዊነትና ሥርዓቷን አሳይቷል፡፡ ይህ እውነታ አፋችንን ሞልተን የምንናገረውን ከአባቶቻችን ሲወርድ ሲወራረድ የመጣውን ትክክለኛ አስተምህሮ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ይህ በእንዲኽ እንዳለ፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ፣ በኢትዮጵያ መታየት ጀመረ ተብሎ የሚነገረው በ1924 ዓ.ም. አልፍሬድ ባክስተን በተባለ አሜሪካዊ እንደኾነና “ሠራዊተ ክርስቶስ” የሚባል ማኅበር እንዳቋቋመ የታሪክ ድርሳናት በሰፊው ይተርካሉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለማጥፋት፣ ከውስጥም ከውጭም ጫና እየፈጠሩባት ይገኛሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን እስከ አኹን ድረስ አልጠፋችም፤ ወደፊትም አትጠፋም፤ ምክንያቱም የጸናችው በክርስቶስ ደም ስለኾነ ነው፡፡(ማቴ.16፥18)

የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን ዓላማቸው፡- የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በተለያዩ ዘዴዎች በማታለል ወይም በጥቅም በመደለል እንዲኹም በኑፋቄ ትምህርታቸው በማጥመቅ በሒደት ቤተ ክርስቲያንን ወደ ፕሮቴስታንት መለወጥ አለባት፤ የሚል አስተሳሰብ ያለው ነው፡፡ ሙታስፍ ኦሬን የተባለው አሜሪካዊ ፓስተር ሲናገር፣ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞችን መንፈሳዊ ሕይወት ለማደስ(ድርጅታችን) ይተጋል፤ ይህንንም ለማስፈጸም እጅግ አስተዋይ የኾኑት ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻችንም ከእኛ ጋር ናቸው፤” በማለት ጽፏል፡፡ (The Evangelical Faith Movement in Ethiopia; p.338)፡፡

ቤተ ክርስቲያንን ለባዕዳን የእምነት ተቋማት አሳልፈው ለመስጠት ያሰፈሰፉትን የቤተ ክርስቲያኒቷን የእናት ጡት ነካሾች፣ ከውጭም ከውስጥም ከጉያችን እንዳሉ ቢታወቅም፣ በግልጽ ‘ወንጌል እና ክርስቶስ ተሸፍኗል’ እንዲኹም ‘ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን አርጅታለችና መታደስ አለባት’ በማለት በተለያዩ ጊዜአት ይናገራሉ፡፡ ይኹን በደመ ክርስቶስ የታነፀችው ቤተ ክርስቲያን፥ እምነቷም፣ ሥርዓቷም ጉልላቷም ሕያው በኾነው በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ በመኾኑ ማርጀትና ማፍጀት የሌለባት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቆላ.1፥24፤ ኤፌ.1፥23፤ 1ቆሮ.12፥27፤ ሮሜ 12፥5፡፡

ስለኾነም የተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ፣ በዘመናችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ እየተፈታተኗት ካሉት ጉዳዮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው እንደኾነ ከምንጊዜውም በላይ ልንገነዘበው ይገባል፡፡

“እኔ እግዚአብሔር አምላካችኹ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ኹኑ”(ዘሌዋ.19፥2፤ 1ጴጥ.2፥15) ባለው መሠረት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በቅዱሳን አማላጅነት አምና በስማቸው ቤተ ክርስቲያን አንጻ፤ በቅድስናቸው በተጋድሏቸው የምታከብራቸውን ቅዱሳን፣ ‘ስግደትም ኾነ አክብሮት አይገባቸውም’ በማለት፤ አምላክ ያከበራቸውን ሲያቃልሉ፣ በአውሮፓና በአፍሪቃ ያሉት ፓስተሮቻቸው ግን ምእመናኑን አንድ ጊዜ እንደ ፈረስ እየጋለቧቸው፤ በሌላ ጊዜ ከፊት ለፊታቸው እንዲሰገድላቸው በማድረግ በሕዝቡ ላይ ሲሳለቁ፤ በሌላ መልኩ፣ ራቁታችኹን ኾናችሁ ካልጸለያችኹ እግዚአብሔር ጸሎታችኹን አይሰማችኹም፤ በማለት ከወጣት እስከ አዛውንት እርቃናቸውን በዐደባባይ እንዳቋሟቸውና የሚጸለይላቸው ፓስተር ግን ሙሉ ልብስ ለብሶ እንደታየ፤ በተለያዩ ድረ ገጾች ላይ የተዘገበና ብዙ ሰው ያየው የዐደባባይ ምስጢር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ እርቃናችኹን ካልኾናችኁ ጸሎታችኹ አይሰማም፤ የሚል ዓይነት አስተምህሮ በታሪክም አስተምራ አታውቅም፡፡ ክርስቶስም ሐዋርያትም ከእነርሱም በኋላ የተነሡ አባቶቻችን አስተምረው አያውቁም፡፡ ይልቁን አዳምና ሔዋን ጸጋቸው በበደል ኃጢአት እንደተገፈፈ፤ እርቃናቸውን በኾኑ ጊዜ የቁርበት ልብስ(ቅጠል ልብስ) አለበሳቸው፤ ይላል(ዘፍጥ.3፥21) እንጂ እርቃን በመኾን የሚገኝ ጸጋ ወይም በረከት እንደሌለ ቤተ ክርስቲያናችን አበክራ ታስተምራለች፡፡

ስልቶቻቸው፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው(በአገኙት አጋጣሚ)፣ እምነቷ ይህ ነው፤ ብለው የተበረዘ ትምህርት ማስተማር፤ ራሳቸው በገዳማትና አድባራት፤ በአብነት ትምህርት ቤት፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆች፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች፣…ወዘተ ሰርገው በመግባት የተሐድሶ ኑፋቄን በሥርዋጽ በማስገባት ማስተማር፤ ካልኾነም ጥርጣሬ ይዘው እንዲወጡ ማድረግ፤ በሚጽፏቸው መጻሕፍት ራሳቸውን ቀሲስ፣ ዲያቆን፣ መጋቤ ጥበብ፣ መጋቤ ብሉይ፣ መጋቤ ሐዲስ እያሉ የቤተ ክርስቲያኗን ማዕርግ መጠቀምና በዚኽም ስሞቻቸው ምእመናንን ማደናገር ዋናው ስልታቸው ሲኾን፤ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር በእነርሱ ሥር ማድረግ እንደኾነ ይናገራሉ፡፡

መፍትሔ፡- “ሕዝቤ ዕውቀትን ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል”(ት.ሆሴዕ 4፥6) እንደተባለው፣ ከመንፈሳዊ ኮሌጆችና ከካህናት ማሠልጠኛ የሚመረቁትን ደቀ መዛሙርት እንዲኹም፣ በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ የንስሐ ልጆቻቸውን፤ የሰንበት ተማሪዎችና ወጣቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከርና ጊዜውን የዋጀ ትምህርት በተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ ማስተማር፤ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አጋር ልጆች ጋር በመቀናጀት የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ በመንደፍ ቤተ ክርስቲያንን በዚኽ ዘመን መታደግና ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ሃይማኖታዊ ግዴታችን ነው፡፡

በመጨረሻም፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የረጅምና ገናና አኩሪ ታሪክ ባለቤት እንደ መኾኗ መጠን አባቶቻችን ያስረከቡንን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ማወቅና ማጽናት፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከካህን እስከ ምእመን የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ በትንቢተ ኤርሚያስ ምዕ.6 ቁ.16፤ ላይ “የቀደመችውን መንገድ ጠይቁ፤ በእርሷም ላይ ሒዱ፤ ለነፍሳችኹም ዕረፍት ታገኛላችኹ” እንደተባለው፣ አባቶቻችን ሐዋርያት የተሰደዱባት፤ ቅዱሳን ሰማዕታት ዋጋ የከፈሉላት፤ አበው የሰበኩላት፤ ነገሥታትና መሳፍንት አንገታቸውን የተቀሉላት፤ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን አንዲት ናት፡፡

ስለኾነም ሕይወታቸውን ከፍለው/ገብረው/ በኩራት እንድንኖርና የቤተ ክርስቲያናችንን ትውፊት፣ ዶግማ፣ ሥርዓት፣ ቀኖና እንድንጠብቅ ላደረጉን ቅዱሳን አባቶች፣ ክብር ምስጋና ይግባቸው፤ የእምነታቸውን ፍሬ እየተመለከትን በእምነታችንም እስከ ሞት ድረስ ጸንተን እንድንቆይ የአምላካችን መልካም ፈቃድ ይኹንልን፤ አሜን፡፡

Advertisements

2 thoughts on “የኮሌጆቻችን ምሩቃን: እንኳን ደስ አላችኹ፤ በጎች ምእመናንን በአደራ የተቀበላችኹበት ቀን ነው፤ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ምስክር መኾን ይጠበቅባችኋል

 1. Bete Zewudu July 4, 2016 at 11:36 am Reply

  ስራ ባለቤቴ በድንገት መስሬቤት ትቀነሳች እንዲህ ከሆነገች አስር ይበቃናል ብለን መክፈል ስንጀምር
  አንድቀን እድቀን እደአባት ሰላም ብሎየማያውቀው የስም መነኩሴ ተብየ አባ ሲራክ እንዴት አስሩን ትቀንሣላችሁ እየተመካከራችሁ አይደል ስብሰባ ገብታችሁ ለመናገር እንዲያመቻችሁ ብላችሁ እንጂ እስካሁን ጨርሶ ትወጡነበር
  እኔን ለመበጥበጥ ነው ከዚህ የምትመጡ ብሎሰደባት ባለቤን ተመልከቱ
  አባ ሐይለመለኮት ተስፋማርያም የሗላታሬኩ እደሜስረደው ከአርባምንጪ ገብርኤል ወደቅዱስሜካኤል
  በምን ምክንያት እደተዛወረ አርባምንጪ አገርስብከት መረዳት አዲስ አበባቅድስትማርያም ምንይሰራእንደነር
  በአጭሩ መረዳት ይቻላል ቆቡን አውልቆ በየሴታዳሬወች ሲዞር
  እንዲሁም ባለትዳሮችን ለማስቀደስ ፈተና እስከሚሆንባቸው ድረስ
  ሌላው በጫት ሱስ እና በሲጋራ አጫሽነት ሀገርቤት ይታወቃል
  ከዚህ ፋንክፈርት ጀርመን ህይወቱ ተመሣሣይ
  ነው በተለምዶ ፋራንክፈርት ካይዘር እስትራሰ እየተባለ በሜጠራው ሴታዳሬወች ቦታ
  ሲመላለስ ሁሉም ሰውያገኝዋል ክርስቲያኑ ቀርቶ አስላች ያውቁታል
  በዝሙቱ ይህንን ስእፅፋ ልዮጥላቻ ለእሱ ኑሮኝ ሣይሆን ካህን ስላይደለነው
  ገዳም ነበርኩኝ ይላል አወገዳም ነበረ ፈተነውን መቇቇም አቅቶት ይህንን ሁሉ
  ሐጤያት የሚያሠረው ከገዳም ያወጣው ሰይጣን ነው አንዴ አባ ሲራክ
  አንዴ አባ ሐይለመለኮት መልም ሰራእንጄ ሰም በመቀየር ሹመት አይገኝም
  ጉልቻ መቀየር ወጥ አያጣፍጥም ይባላል
  የያዘው ሰይጣን ክርስቴያኖችን ማሳደድ አስር ጌዜየ ማህበረቅዱሳን እረበቨኝ
  በነጻ እየረዱት ሄኖክ ወንድወን
  እባክህ ብለን ብንለመነው ማህበረቅዱሣን ይውጣልኝ ብሎ ከፈላችው
  ይህ ኖለት ጳጳስ ቢሆን ጥሩይሰራይሆን እውነቱን እናጋልጥ አለም አዲትመንደር ሁናለች
  እና እውነትወታ በሲራክ ሴራ ከሁለት የተከፈለው የፍራንክፈርት ቅድስትማርያም ምመናን አንድመሆን
  አለበት እንላለን እውነቱን ስንናገር እኔ ትግሬስለሆንኩኝ ነው እያለ በየዋህ ክርስቴያኖች ቤት ማልቀሱ የማይቀርነው
  ግን ትግሬ በመሆኑሣይሆን ሐጤያተኞ የመቤታን ካዝና በአዶ ያስቀረ ህዝብ የበተነ ዛሬየተናገረውን ነገ የማይደግም
  ትግሬኮሜቴ ካልተመረጠ ብሎ ተመረጠለት ግን የለመደ ልማድ ያሰርቃል ከማድ ነውና
  ትክክል እንስራ ሲሉት ሲቆጣጠሩት ስም መጥራት ጀመረ ቴዎድሮ እላሠራኝ አለ ሰለተቆጣጠረው እኮነው
  ሰለዚህ ገንዘብ ያላግባብ ሲዘርፋ እና ሲዘሙት እያየ ዘምያላለሰው ለአባ ሲራችክ ጥሩ አይደለም
  ኮሦኮሦም ቢይላቸው አባ ሲራክ ተብየው እውነት እንናገራለን ለድንግልርያም ብለንከፋል ኑረን
  Gefällt mir · Antworten · 2. Juli um 13:33

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: