“የእግዚአብሔር ምርጥ” ኤጲስ ቆጶስ ማን ነው? በፍቅረ ንዋይ ያበዱትንና የውድቀት ታሪክ የሞላባቸውን ጎጠኞችና ሲሞናውያን እናጋልጥ!

his-holiness-abune-mathias-with-thier-graces-the-archbishops

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት አባቶች ያኖሩትን ትምህርት በመጣስ፣ አንድ ሰው፣ አምኛለኹ፤ በቅቻለኹ ብሎ ቢቀርብ እንኳ ቤተ ክርስቲያን መሾም የለባትም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ማዕርግ በታማኝነት ሊያገለግሏት የሚችሉትን አገልጋዮች በጥንቃቄ መምረጥ አለባት፡፡

የአበውን ትውፊት በመጣስ፣ የዕድሜን የአገልግሎትን ኹኔታ ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡ ቢሾሙ፤ በዲያቢሎስ ሽንገላ በትዕቢት እየተነፉ፣ እነርሱም ሳይገለገሉ ቤተ ክርስቲያንንም ሳያገለግሉ የጥፋት መሣርያ ይኾናሉ፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥሯን መሠረቷን የሚያውቁ፤ በገድል የተቀጠቀጡና በትሩፋት ያጌጡ፤ በአጠቃላይ በቅድስና ሕይወት ጸንተው የኖሩ አባቶችን ከገዳም ጭምር እየፈለገች መሾም ይጠበቅባታል፡፡ በቅድስናቸው የተመሰከረላቸውን አባቶች መሾም፣ በእውነት ምእመናንን በጸሎታቸው የቅድስና ሕይወታቸው ተካፋይ ያደርጋቸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያንን በአግባቡ ያላገለገሉ፤ በገዳማዊ ሕይወት ያልተፈተኑ ሰዎች፤ በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድ የወደቁ፤ በፍቅረ ንዋይ ያበዱ፤ የውድቀት ታሪክ ያላቸው ሰዎች ያለምንም መስፈርት ሳይመረመሩ ቢሾሙ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሊመሯት አይችሉም፤ እንሥራ ቢሉም ይጎዷታል፡፡ ስለዚኽ በአገልግሎት ያልተፈተኑ በውጭ ባሉ ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር የሌላቸውን ሰዎች መሾም አደጋው የበዛ መኾኑ ሊስተዋል ይገባል፡፡


ሥልጣነ እግዚአብሔር – ክህነት እና የእግዚአብሔር እንደራሴዎች – ካህናት

ክህነት በመንፈሳዊ አገልግሎት ለተሰማሩና በእግዚአብሔርም በሰውም ለተመረጡ ሰዎች የሚሰጥ መንፈሳዊ ሹመት መኾኑን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ካህናት፣ ሥልጣነ ክህነትን የሚቀበሉት በሊቃነ ጳጳሳት አማካይነት ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

ካህናት በንፍሐትና በአንብሮተ እድ የሚሾሙት ሹመት ከረቂቅነቱ የተነሣ ምሥጢረ ክህነት ይባላል፡፡ ምሥጢር የተባለውም፣ ሥልጣነ ክህነት ለዐይን ግዙፍ መስሎ የሚታይ፣ ነገር ግን ለሕሊና ሳይቀር የሚረቅ አገልግሎት የሚፈጸምበት፤ በሚታይና በማይታይ ዓለም የሚሠራበት፤ ሰው ሥጋዊ ሲኾን መንፈሳዊ፤ ምድራዊ ሲኾን ሰማያዊ ሊኾን የሚችልበት፤ ምድራዊም ሰማያዊም ሥልጣን በመኾኑ ነው፡፡

እንደ እርሱ፥ ከባቴ አባሳ፣ ኀዳግያነ በቀል፣ ይቅር ባዮች፣ መሐርያን፣ ፈዋሾች፣ አስተማሪዎች እና አጽናኞች፤ ለበጎች ተላልፈው የሚሰጡ እረኞች እንዲኾኑ ይህን ታላቅ ሥልጣን ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጠው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

የሐዲስ ኪዳን ክህነት እንደ ብሉይ ኪዳን ክህነት፣ በዘር የሚወረስ፤ የእንስሳት ደም በማፍሰስ፣ ስብ በማጤስና የእህል ቍርባን በማቅረብ ለምልክት ብቻ የቆመ የተቀብዖ ሹመት ሳይኾን፤ ካህናት በየዓመርጋቸው ተራ በሚፈጽሙት ተልእኮ፣ በምድር ሳሉ ቅዱሳን መላእክትን የሚመስሉበት አገልግሎት ነው፡፡

ሊቁ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ የሥልጣነ ክህነትን ታላቅነትና የካህናትን ሥልጣን ምንነት ሲያብራራ፣ “ካህናት በምድር የፈጸሙትን ጌታ በሰማይ ያጸናዋል፤ የባሮቹን አሳብ ጌታ በሰማይ ይቀበለዋል፤” ብሏል፡፡ ከማንኛውም ምድራዊ ሥራ፣ ሀብትና ማዕርግ፣ ክህነት ከፍ ያለ ማዕርግ ነው፡፡ ሥልጣነ ክህነት ከማንኛውም ማዕርግ ከፍ ብሎ ሥልጣነ እግዚአብሔር ይባላል፤ ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት የራሱን የባሕርይ ሥልጣን በጸጋ ስለሰጣቸው ነው፡፡ የዚኽ ሥልጣነ ክህነት ወራሾች ካህናት፣ የእግዚአብሔር ወኪሎች ወይም እንደራሴዎች ይሰኛሉ፡፡

ካህናት፥ የእግዚአብሔር ወኪሎች ወይም እንደራሴዎች የሚያሰኛቸው፣ እርሱ ደሙን አፍስሶ፣ ሥጋውን ቆርሶ ላዳናቸው ሕዝቦች በማሰባቸው፣ በማስተማራቸው፣ በመጨነቃቸው፣ ሰማዕትነት በመቀበላቸው ፍጹም መድኃኔዓለም ክርስቶስን መስለው እንዲያገለግሉ ተመርጠው በመሾማቸው ነው፡፡

ከፍተኛው የክህነት ደረጃ – መዓርገ ጵጵስና

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት በንፍሐት/እፍ በማለት/ የሰጣቸውና እነርሱም ለተከታዮቻቸው በአንብሮተ እድ/እጅ በመጫን/ ያስተላለፉት የክህነት ሥልጣን ሰንሰለት ሳይቋረጥ፣ ሲወርድ ሲወራረድ እኛ ካለንበት ዘመን ደርሷል፡፡ ጌታችን “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ፤”/ማቴ. 28፥20/ ብሎ እንደተናገረው፤ የሥልጣነ ክህነት ሽግግር እስከ ዓለም ፍጻሜ/ዕለተ ምጽአት/ ድረስ ይቀጥላል፡፡

ሥልጣነ ክህነት ለተመረጡ ሰዎች፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በአንብሮተ እድና በንፍሐት የሚተላለፍ አምላካዊ ሀብትና ጸጋ በመኾኑ፣ ካህናት ሥልጣኑን ገንዘባቸው የሚያደርጉት፣ ከብዙ ጸሎት፣ ስእለትና ምርጫ በኋላ ነው/የሐዋ. ሥራ 6፥6/፡፡ ማንም ሰው በቃኹ፣ ነቃኹ ብሎ ካህን መኾን፤ የክህነት አገልግሎትን መፈጸም አይችልም፡፡ በድፍረት ላድርግ ብሎ ቢሞክረውም፣ በዘመነ ብሉይ በቆሬ ልጆችና በንጉሡ በዖዝያን እንደታየው ስጥመትና በለምጽ መቀጣትን ያስከትላል፡፡

ከሦስቱ ዐበይት መዓርጋተ ሥልጣነ ክህነት(ማዕርገ ዲቁና፣ ማዕርገ ቅስና፣ ማዕርገ ጵጵስና) መካከል፤ ኤጲስ ቆጶሳት የሚሾሙበት ማዕርገ ጵጵስና፣ በከፍተኛ መስፈርትና ጥንቃቄ የሚፈጸም ነው፡፡ ይኸውም ከሚጣልባቸው አደራና ከሚሰጣቸው ሓላፊነት ታላቅነት የተነሣ ነው፡፡

የሦስቱ ከፍተኛ መዓርጋት መነሻው፣ መዓርገ ዲቁና ነው፡፡ በማስከተል ተሿሚው መዓርገ ቅስና ይቀበላል፡፡ አንድ ዲያቆን፣ በድንግልና ጸንቼ ቤተ ክርስቲያንን አገለግላለኹ፤ ብሎ ሲወስን በዲቁና ሳለ ወደ ምንኵስና ሕይወት በመግባት መዓርገ ቅስና መቀበል ይችላል፡፡ በዚኽ የቅስና መዓርጉ ላይ የቁምስና ሥልጣን ተጨምሮለት ከቀሳውስት ከፍ ያለ አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል፡፡

ለምሳሌ፡- የቁምስና ሥልጣን ያለው መነኵሴ የገዳም አበምኔት ከኾነ ክህነት የመስጠት ሥልጣን ባይኖረውም፤ ከሥሩ ያሉትን ገዳማውያንን ማመንኮስ ይችላል፤ በአገልግሎቱ እና በትምህርቱ፤ በቅድስናው እና በትሩፋቱ ልቆ ሲገኝ ለከፍተኛው የክህነት ደረጃ ለጵጵስና በቅዱስ ሲኖዶስ ይታጫል፤ በአንብሮተ እድ ተሹሞ ጳጳስ ይኾናል፡፡ ባለትዳር ከኾነ ግን በቅስና ሥልጣኑ ተወስኖ ያገለግላል እንጂ ወደ ጵጵስና አይሸጋገርም፡፡

ኤጲስ ቆጶስ – የአንዲት ሚስት ባል ወይስ ድንግላዊ መነኰስ?

ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ፣ ኤጲስ ቆጶስ የአንዲት ሚስት ባል እንዲኾን የጻፈለትን እናስታውሳለን፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም፣ ይህን ሐሳብ ሲተረጉመው፣ “ሐዋርያው ይህን ትእዛዝ እንደ ግድ መስፈርት አድርጎ አላስቀመጠውም፤ ነገር ግን ከአንድ በላይ ሚስት ያገቡትን ከዚኽ ደረጃ(ሹመት) ለማገድ ነው፡፡ ይህን ማለቱ በጊዜው ከነበሩት የተሻለ ቅድስናና ንጽሕና የያዙትን ለመምረጥ ነው፡፡ ነገር ግን የድንግልናና የገዳማዊ ኑሮ በር ከተከፈተ በኋላ ኤጲስ ቆጶስ ከደናግል መነኰሳት መካከል ተመርጦ ይሾማል፤” ብሏል፡፡(Sacrament Rites – Priesthood; p.101)

በተለይም፣ በ325 ዓ.ም. በኒቂያ ጉባኤ፣ ከአገልግሎቱ ጠባይ አንፃር ቀሳውስት፣ በየቤቱ እየሔዱ ወንጌል እያስተማሩ በትዳር፣ በኑሮ ውስጥ ያለውን ችግር እንዲፈቱ፤ አንዲት ሚስት እንዲያገቡ ሲፈቀድላቸው፤ ኤጲስ ቆጶሳት ግን ደናግል እንዲኾኑ በ318ቱ ሊቃውንት ተወስኗል፡፡ ይህም ሐሳብ የቀረበው በቅዱስ ፓፍኖቲውስ(St. Pafnotuus bishop of Luxor) ነበር፡፡

በርግጥም፣ ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት የነበሩ፣ ለምሳሌ፡- ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስን የመሰሉ አባቶች ባለትዳር፤ ሕጋውያን ካህናት ነበሩ፡፡ በቁስጥንጥንያም፣ የፓትርያርኩ ልጅ የአባቱን ሥልጣን በመረከብ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ በኋላ ግን በጵጵስና መዓርግ ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ አባቶች ድንግላውያን እንዲኾኑ ተወስኗል፡፡ ይኸውም ለስብከተ ወንጌል ስለሚፋጠኑ፣ በዚኽ ዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተክተው የሚሠሩ ጳጳሳት በመኾናቸው ነው፡፡ በሕግ ተወስኖ ማገልገል የካህናቱን ቅድስና ዝቅ የሚያደርገው ኾኖ አይደለም፡፡ ትልቁ ትኩረት፣ አገልግሎትን በስፋትና በምልአት ለምእመናን ለማድረስ ድንግልናዊ ሕይወት ተመራጭ በመኾኑ ነው፡፡

የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት አመራረጥና አሿሿም

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፣ የጵጵስና መዓርግ የመጨረሻው ከፍተኛው መዓርግ ነው፡፡ ጵጵስና የአገልግሎቱ ስም ሲኾን ባለቤቱ ኤጲስ ቆጶስ ይባላል፡፡ የባላይ ጠባቂ፤ መምህር ማለት ነው፡፡ ጵጵስናም ማለት ፍቺው አባት ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ጵጵስና፣ ከኤጲስ ቆጶስነት ቀጥሎ በአገልግሎት ትጋት የሚሰጥ ሹመት ነው፡፡ ከዚኽ ሹመት ሲደርስም፣ የሀገረ ስብከት አስተዳዳሪ፤ የገዳማት የበላይ ጠባቂ ተብሎ ይሠየማል፡፡ ከጳጳሳት መካከል ለከፍተኛ አገልግሎት ሊቀ ጳጳሳት ይሾማል፡፡

ሊቀ ጳጳስ ማለት የጳጳሳት ታላቅ፣ አለቃ፣ ሓላፊ ማለት ነው፡፡ በሌሎች የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሜጥሮፖሊጣን(Metropolitan) ይሉታል፡፡ ቃሉ የግሪክ ሲኾን የአህጉረ ስብከት ዋና(መናገሻ) ከተማ ማለት ነው፡፡ ስያሜው ለሊቀ ጳጳስ መሰጠቱ በሥሩ ሌሎች አህጉረ ስብከትን ስለሚመራና ስለሚያስተዳድር ነው፡፡

የጵጵስና መዓርግ ያለው አባት፣ የቅስና መዓርግ ከተሰጠው ካህን በላይ ለመሾም፣ ለመሻር የሚችል የቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ነው፡፡ ለዚኽ መዓርግ የሚበቃ ሰው፣ የሐዋርያነት ምልክት ያለው፤ ክርስቶስን በግብር የመሰለ፣ በድንግል የመነኰሰ፣ በትምህርቱ ከፍተኛ ችሎታ ያለው፣ በጠባዩ የተመሰገነና ሙሉ አካል ያለው ጤናማ ሰው መኾን ይጠበቅበታል፡፡

ጳጳስ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “እናንተን የተቀበለ እኔን ተቀበለ” ሲል የመሰከረላቸው የቅዱሳን ሐዋርያትን ሥልጣን ወራሽና ተረካቢ ነው፡፡ ጳጰሳት፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያላቸው ሹመት፣ በብሉይ ኪዳን የሙሴ ሹመት በእስራኤል እንደነበረው ዓይነት የፈታሒነት ሥልጣን ያለው ነው፡፡ በምእመናን ላይም የተሾመ ነው፡፡

ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው፣ ሕሙማነ ሥጋን በተኣምራት ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት እንደፈወሰ፤ ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ የተበተኑትን እንደሰበሰበ፤ በመጨረሻ ራሱን ለበጎች አሳልፎ እንደሰጠ፤ ጳጳስም ለምእመናን ጌታችን ያደረገውን ነገር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

16PatriarchAbuneTewophilos2nd_jpg
ሦስተኛውና ከፍተኛው የክህነት ደረጃ፣ መዓርገ ኤጲስ ቆጶስ፣ የራሱ የአሰጣጥ ሥርዓት አለው፡፡
በኤጲስ ቆጶስነት የሚሾም መንፈሳዊ አባት፣ በሥጋዊና በመንፈሳዊ ተክለ ሰብእናው ነውር የሌለበት፤ ልቡናው ከሐኬት የራቀ ድንግላናዊ ኾኖ፣ ሥርዐተ ምንኵስና የፈጸመና ዕድሜው ኃምሳ ዓመት የሞላው/በማስፈጸሚያ ደንቡ መሠረት ከ45 ዓመት በላይ/ መኾን አለበት፡፡ በትምህርቱ ብሉይ እና ሐዲስ ኪዳናትን የተማረ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ ሒደት የተረዳ እንዲኾን ይጠበቃል፡፡

ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስ እንደጻፈለት፣ ለዚኽ ከፍተኛ ማዕርግ የሚመረጠው አገልጋይ ሊያሟላቸው የሚገቡትን 12 ጉዳዮች ሲገልጽለት፡- “እንግዲኽ ኤጲስ ቆጶስ እንዲኽ ሊኾን ይገባዋል…”፡-

 1. የማይነቀፍ – የሚነቀፍ ጠባይ ሊኖረው አይገባም፡፡ የእግዚአብሔር እንደራሴ፤ ቤተ ክርስቲያንንም የሚጠብቅ ነውና ከነቀፋ የጸዳ መኾን ይጠበቅበታል፡፡
 2. ድንግላዊ መነኰስ የኾነ፡– ቀደም ሲል “የአንዲት ሚስት ባል”  የተባለው ከአንድ በላይ ያገቡትን ከዚኽ ሹመት ለማገድ ነው፡፡ የገዳማዊ ኑሮ በር ከተከፈተ በኋላ ግን ኤጲስ ቆጶስ ከደናግል መነኰሳት መካከል ተመርጦ እንዲሾም በኒቂያ ጉባኤ ተወስኗል፡፡
 3. ልበኛ፡- ኤጲስ ቆጶስ የቤተ ክርስቲያንና የምእመናን ጠባቂ እንደመኾኑ፣ ስለ አገልግሎቱ ጥንቁቅና ንቁ የኾነ፤ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን የሚያይባቸው ብዙ ዓይኖች ያሉት አርቆ አሳቢ ሊኾን ይገባዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም፣ “ኤጲስ ቆጶስ ጦርን ከሚመራ መኰንን በላይ ጥንቁቅ መኾና አለበት፤” ይለዋል፡፡
 4. ራሱን የሚገዛ፡- ራስን መግዛት ትልቁ የመንፈሳዊነት መገለጫ በመኾኑ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ተብሏል፡፡ (ገላ.5፥23) አንድ የቤተ ክርስቲያን መጋቢ ደግሞ እንደምን አብዝቶ አያስፈልገውም?
 5. እንደሚገባው የሚሠራ፡- ኤጲስ ቆጶስ በደረጃው የተመደበለት ሥራ አለው፡፡ በትጋት እንደሚገባው ሊሠራ ይገባል፡፡ “ናዳብና አብድዩ፣ በእግዚአብሔር ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ፡፡ እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው፤” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ዘሌዋ.10፥1፡፡ ነቢዩ ኤርሚያስም፣ “የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚያደርግ ርጉም ይኹን፤” በማለት እንደሚገባው የማይሠራውን አገልጋይ አስጠንቅቋል፡፡
 6. እንግዳ ተቀባይ፡- ኤጲስ ቆጶሳት እንደ እግዚአብሔር ወዳጅ አበ ብዙኃን አብርሃም፣ ያዘኑትን የሚያረጋጉ፤ የተቸገሩትን የሚታደጉ፤ እንግዶችን ለመቀበል የሚተጉ መኾን አለባቸው፡፡
 7. ለማስተማር የሚበቃ፡- ስለዚኽ ነገር በዲድስቅልያ እንዲኽ ተብሎ ተጽፏል፡- “ኤጲስ ቆጶስ፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን አብራራ፤ ምእመኑንም መግብ፡፡ በሕግ ብርሃንም ሙላቸው፡፡ እነርሱም ስለ ትምህርትኽ ይጠነቀቃሉ፡፡” ንዋይ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስም፣ “ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ” በማለት ደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስን አስገንዝቦታል፡፡ /2ጢሞ.4፥13/ የኤጲስ ቆጶሳት ዋነኛ ሥራቸው መግቦት እንደመኾኑ፤ ምእመናንን በቃለ እግዚአብሔር ማሳደግ ይገባቸዋል፡፡
 8. የማይሰክር፡- ሐዋርያው “መንፈስ ይሙላባችኹ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ” በማለት እንዳስተማረው፣ ለዚኽ ታላቅ አገልግሎት የሚመረጥ ሰው በዚኽ የሚታማ መኾን የለበትም፡፡ ኤፌ.5፥18፡፡ ይህም መባሉ መጠጣት በራሱ ኃጢአት ኾኖ ሳይኾን ወደ ስሕተትና ወደ ጠብ ስለሚመራ ነው፡፡ “ወደ መገናኛው ድንኳ ሲገቡ” የብሉይ ኪዳን ካህናት የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ ተከልክለው ነበር፡፡ ዘሌዋ.10፥9፤ 1ጢሞ.5፥6፡፡
 9. የማይጨቃጨቅ፡- ጭቅጭቅና ክርክር የሥጋ ሥራዎች መኾናቸው በቅዱስ መጽሐፍ ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ ገላ.5፥21፡፡ ስለዚኽ እንዲኽ ያለ የሥጋ ሥራ የነገሠበት ሰው ለዚኽ ታላቅ አገልግሎት አይመረጥም፡፡
 10. ገንዘብን የማይወድ፡- ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ኹሉ ሥር ነው” በማለት ገልጦታል፡፡ 1ጢሞ.6፥10፡፡ የኤጲስ ቆጶስ ገንዘብ እግዚአብሔርን ማገልገል ነው፡፡
 11. ልጆቹን በጭምትነት ኹሉ የሚገዛ፡- ልጆቹ የተባሉ የተሾመላቸው ምእመናን ናቸው፡፡ በእነዚኽ ዘንድ በጭምትነቱ የሚታወቅ፤ በቅንነት የሚያአስተዳድራቸው፣ የሚመራቸው ይኹን ማለቱ ነው፡፡ ስለ ጌታችን፣ “አይከራከርም፤ አይጮኽምም፤ ድምፁንም በዐደባባይ የሚሰማ የለም” ተብሎ እንደተነገረ፣ ጌታውን መስሎ ሕዝቡን የሚመግብ ኤጲስ ቆጶስ ጭምት እንዲኾን ያስፈልጋል፡፡ ኢሳ.42፥14፤ ማቴ.12፥18-20፡፡
 12. በውጭ ካሉት መልካም ምስክር ያለው፡- ኤጲስ ቆጶስ በሕዝብ ተመርጦ ለሕዝብ የሚሾም የእግዚአብሔር አገልጋይ በመኾኑ ከላይ ለተዘረዘሩት ሠናይ ተግባራት በምእመኑ ሊመሰክርለት ይገባል፤ ለማለት ነው፡፡ በቆርንቶስ መልእክቱም፣ አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም እንዳለ፤ ነቅዕ፣ ነውር እያለበት ቢሾም ለሌሎች ማሰናከያ ይኾናልና ነው፡፡ 2ቆሮ.6፥3፡፡

ኤጲስ ቆጶሳት በእኒኽ 12 ከፍተኛ መስፈርቶች በጥንቃቄ መመረጣቸው፣ ከሚጣልባቸው አደራና ከሚሰጣቸው ሓላፊነት ታላቅነት የተነሣ ነው፡፡ እኒኽን መስፈርቶች የሚያሟላ ቆሞስ ሲገኝ፣ በዕድሜ ሠላሳ ዓመት የሞላቸው/የኾናቸው/ ምእመናን ቆሞሱን መጠቆምና መምረጥ ይችላሉ፡፡ ኤጲስ ቆጶስ የሚሾመው፣ በሚሾምበት ሀገረ ስብከት የሚገኙ፣ ዕድሜአቸው ሠላሳና ከዚያ በላይ የኾኑ ምእመናን ሲመርጡት፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሲፈቅዱ ነው፡፡

ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ማእመናን፣ በኤጲስ ቆጶስነት እንዲሾምላቸው ስለመረጡት አባት÷ ደግነት፣ ትሩፋት፣ ንጽሕና፣ ከነውር የራቀ ስለመኾኑ እማኝነት ወይም ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ይጠየቃሉ፡፡ ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስን “ትወደኛለኽ?” እያለ ሦስት ጊዜ መልሶ መላልሶ እንደጠየቀው፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሦስት ጊዜ እየመላለሰ ምእመናኑንና ካህናቱን ማረጋገጫ ይጠይቃቸዋል፡፡ ሕዝቡም አስረግጠው፣ “የሚገባው ነው” ብለው ሦስት ጊዜ መልስ ይሰጣሉ፡፡

በዚኽ ጊዜ ሕዝቡ መልስ ሲሰጡ፣ እጃቸውን አንሥተው “ይደልዎ፤ ይደልዎ = ይገባዋል፤ ይገባዋል” እያሉ ያረጋግጣሉ፡፡ በዚኽ መልኩ ማኅበረ ካህናቱና ሕዝበ ክርስቲያኑ እየመሰከሩላቸው ይሾማሉ፡፡ ይህን ሥርዓት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ አምስት ሲያብራራ፣ “ወኵሎሙ ሰብእ ይንብሩ በእንተ ተሠይሞቱ ሕዝብኒ ወካህናት እንዘ ስምዐ ይከውኑ ሎቱ = ካህናቱም ሕዝቡም በሙሉ ስለ ሹመቱ ምስክር ኾነው ይቀመጣሉ” ይላል፡፡ በሹመቱ ጊዜ ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር ሦስት ወይም ኹለት ጳጳሳት ይገኛሉ፡፡

ኤጲስ ቆጶስ የሚሾመው ሕዝበ ክርስቲያኑ፣ በስፋት በቤተ ክርስቲያን በሚሰበሰቡበት በዕለተ እሑድ ነው፡፡ ይኸውም ኹሉ እንዲያውቀውና በሕዝብ ፊት እንዲሾም ነው፡፡

በዚኽ ቀን የማኅበረ ካህናት እና ምእመናን ምስክርነት የተሰማለት ተሿሚ ዕጩ ኤጲስ ቆጶስ በተዘጋጀለት መንበር እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ ጸሎተ ሢመቱ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይመራል፡፡ በተሿሚው ላይ እጃቸውን በማኖር/በአንብሮተ እድ/ ሊሾሙ የመጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እጃቸውን ይናጻሉ፡፡ ከመሾማቸው በፊት፣ እጃቸውን የሚታጠቡበት ምክንያት፣ እኛ በምናውቀው በአፍኣ ንጹሕ ብለን ሾመንሃል፡፡ አንተ በምታውቀው በውስጡ ዕዳ የለንበትም፤ ዕዳው በአንተ ነው፤” ለማለት ነው፡፡

በማስከተል፣ “አንድ አምላክ በሚኾን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የእግዚአብሔር ምርጥ በኾነ በዚኽ አገልጋይ ላይ እጃችንን እናኖራለን” እያሉ፣ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መሪነት እንደየሹመት ዘመናቸው በየተራ እጃቸውን በአዲሱ ተሿሚ ላይ በማድረግ በአንብሮተ እድ ይሾሙታል፡፡ ቀዳማዊው ኤጲስ ቆጶሳት በተሿሚው እጅ ላይ እጁን የሚጭነው፣ “እስከ አኁን ድረስ ከእኔ በታች ነበርኽ፤ ከእንግዲኽ ወዲኽ ግን በሥልጣነ ክህነት ከእኔ ጋር አንድ ነኽ፤” ሲለው ነው፡፡ ከዚኽ በኋላ ጸሎተ ሢመቱን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይጸልያል፤ ሕዝቡም አሜን ይላሉ፡፡

በሐዲሳን ኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ላይ የተሳተፉ ኤጲስ ቆጶሳት አስኬማውን አንሥተው፣ “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብሩክ እግዚአብሔር አብ አኃዜ ኵሉ ዓለም፤ ወብሩክ ወልድ ዋሕድ እግዚእነ ኢየሱስ ወቡሩክ ጰራቅሊጦስ መንጽሒ ወመጽንኤ ኵልነ” እያሉ ሦስት ጊዜ ይባርኳቸዋል፤ አስኬማውንም ያደርጉላቸዋል፡፡ ቀጥሎም ጸሎተ ልብስ ሲፈጸም ልብሰ ተክህኖ አልብሰው በእጃቸው መስቀል ያስይዟቸዋል፡፡ መከራ ትቀበላለኽ፤ ለማለት ነው፡፡ የአንብሮተ እድን ሥርዓተ ጸሎት ከፈጸሙ በኋላ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መሪነት ለተሿሚዎች የተዘጋጀላቸውን ልብሰ ተክህኖ ያለብሳሉ፤ በራሳቸው ላይ አስኬማ ይደፋሉ፤ የእጅ መስቀልም ይይዛሉ፡፡

በዚኽ መልኩ ኤጲስ ቆጶስ በተሾመ ጊዜ ለሦስት ቀናት በዓል ይከበርለታል፡፡ ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ለመነሣቱ ምሳሌ ነው፡፡ ከበዓሉ በኋላ ተሿሚው ለአገልግሎቱ ሥምረት ሦስት ሱባኤ/21 ቀናት/ ይጾማል፡፡ የተሾመበት ወቅት በዓለ ኃምሳ ከኾነ በዚኽ ጊዜ መጾም ስለማይቻል፣ አሳልፎ በዚያው ዓመት በሌሎች ቀናት በየሱባኤው ሦስት ሦስት ቀን በመጾም በአንቀጸ ኤጲስ ቆጶስ የታዘዘውን ይፈጽማል፡፡

የኤጲስ ቆጶሳት ተልእኮ

ኤጲስ ቆጶስ ከሦስቱ የክህነት ደረጃዎች ከፍተኛውን ቦታ በመያዙ፣ የቤተ ክርስቲያን ዋና መሪ ይባላል፡፡ በዚኽ ሓላፊነት የማስተማር፣ የማስተዳደር እና ሥርዐተ አምልኮን የመምራት ሥራዎች ኹሉ በእርሱ መሪነት ይከናወናል፡፡

በዚኽ ሃይማኖትን የመጠበቅ ሓላፊነቱ፣ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለአገልግሎት እንደ ሾመ ኤጲስ ቆጶስም፣ ከአጻዌ ኆኅት እስከ ቅስና ያለውን ሥልጣን ይሰጣል፡፡ ከተጠቀሱት በላይ የኾነውን እርሱን መስለውና አክለው ከሚያገለግሉ ኤጲስ ቆጶሳት ጋር ኾኖ ይሾማል፡፡ በክህነት አገልግሎት ውስጥ ጥፋት ተፈጽሞ ሲገኝ እርሱን ከሚመስሉ ከኤጲስ ቆጶሳት በስተቀር ሌሎችን እንደ ጥፋታቸው መጠን መቅጣት፣ ከሥልጣን መሻር፣ ከአገልግሎት ማሰናበት፣ ማገድ…ወዘተ ይችላል፡፡

ወንጌልን ማስተማር፣ ከኤጲስ ቆጶሳት ተግባር የመጀመሪያው መኾኑን ተመልክተናል፡፡ ኤጲስ ቆጶሳት በሚያስተምሩበት ጊዜ መጻሕፍትን የሚያነቡ፤ ኦሪትን፣ ነቢያትን፣ ወንጌልን፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን፥ ምዕራፉን፣ ቁጥሩን፣ አንቀጹን እየለዩ የሚተረጉሙ፤ ዘወትር የሚያስተምሩ፣ ንቁሐን ትጉሃን ኾነው ተልእኳቸውን እንዲፈጽሙ ታዝዘዋል፡፡(ፍትሕ መን. አንቀጽ 5)

የኤጲስ ቆጶስን የጸሎት ሕይወት በተመለከተ፣ ፍትሕ መንፈሳዊ የሚከተለውን ይላል፡- “ኤጲስ ቆጶስ ከተሾመ በኋላ ቤተ ክርስቲያንን ዘወትር ያገለግላል፤ በመዓልትም በሌሊትም ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስለ ሀገሩ ስለ ዓለሙ ይጸልይ ዘንድ ታዝዟል፡፡”

ስለ ኤጲስ ቆጶሳት ተልእኮ ቅዱስ አግናጥዮስ (ምጥው ለአንበሳ) ሲናገር፥ “በክርስቶስ አምሳል በክርስቶስ የማስተማርያ ቦታ(ዙፋን) የተቀመጠው ኤጲስ ቆጶስ፣ ምእመናንን የሚማርክ ቃና ያለው ትምህርት ለመስጠት የሚችለው ምእመናንና ካህናት የእርሱን አባትነት ሲያውቁለት ነው፡፡ መሰንቆ እንኳ አድማጮችን የሚማርከው ጭራዎቹ ከዕንጨቱ ጋር ተስማምተው ሲወጠሩና ሲቃኙ ነውና፤” በማለት ገልጦታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም፣ “ኤጲስ ቆጶስ ሆይ፥ ሕዝቡን ጠዋትና ማታ ለነግህና ለሠርክ ጸሎት በቤተ ክርስቲያን ይገኙ ዘንድ እዘዛቸው፤” ብሏል፡፡

በአጠቃላይ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ሕዝብን በምሳሌነት ለማስተማር የሚተጉ፤ ኹሉንም ጾታ ምእመናንን የሚወዱ፤ ቂም በቀል የማይዙ፣ ኀዳግያነ በቀል፣ ልበ ሰፊዎች ነገር አላፊዎች መኾን አለባቸው፡፡ ከማንኛውም መጥፎ ሥራ ራሳቸውንም ሕዝብንም መጠበቅ እንዳለባቸው ታዝዘዋል፡፡ ነቢዩ ሆሴዕ “መምህሩ ደግ ከኾነ ሕዝቡም እንደ እርሱ ደጋግ ይኾናሉ” ብሎ እንደተናገረ፣ ኤጲስ ቆጶሳት መልካም አርኣያ በመኾን ሕዝብን መምራት ተልእኳቸው ነው፡፡

የኤጲስ ቆጶሳት ክብር

ኤጲስ ቆጶሳት በክብራቸው የቅዱሳን ሐዋርያት አምሳያ ናቸው፡፡ በዚኽ ዓለም ክርስቶስን የሚመስሉ ቅዱሳን ሐዋርያትን መስለው ይሠራሉ፡፡ በኃጢአት የታሰረውን በሀብተ ክህነታቸው ይፈታሉ፤ ሥጋ ወደሙን ለምእመናን ያቀብላሉ፡፡ በተመደቡበት ሀገረ ስብከት ስማቸው ዘወትር በጸሎት ጊዜ ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ(ከፓትርያርኩ) በመቀጠል ይጠራል፡፡

ያለበቂ አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ ምክንያት ኤጲስ ቆጶሳት አንዴ ከተመደቡበት ሀገረ ሰውብከት አይነሡም፡፡ ኤጲስ ቆጶሳትን ያለበቂ እና አስገዳጅ ምክንያት ከሀገረ ስብከታቸው ማንሣት ባልን ከሚስት እንደማፋታት ይቆጠራል፡፡ ኤጲስ ቆጶሳት ጥፋተኛ ተብለው ቢከሠሡ ያላመኑ ሰዎች ክሥና ምስክርነት አይሰማባቸውም፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ኢአማንያን የሚያቀርቧቸው ክሥና ምስክርነት በእነርሱ ላይ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ አማኞችም ቢኾኑ፣ የአንድ ኤጲስ ቆጶስ፣ የአንድ ቄስ፣ የአንድ ዲያቆንና የአንድ ምእመን ምስክርነት ብቻ በኤጲስ ቆጶሳት ላይ ተሰሚነት የለውም፡፡ ይኹን እንጂ ከአንድ በላይ የኾኑ ምእመናን፣ ዲያቆናት እና ቀሳውስት በኤጲስ ቆጶሳት ላይ የሚያቀርቡት ክሥና ስሞታ በቅዱስ ሲኖዶስ የሚታይበት አሠራር አለ፡፡

ምእመናን በየአህጉረ ስብከቱ የሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳትን ሊወዷቸው፣ ሊያከብሩአቸው፣ ሊታዘዙላቸው፤ በማንኛውም ሃይማኖታዊ ጉዳይ ተገቢ በኾነ መንገድ ሊደግፏቸው ይገባል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ በምእመናንና በካህናት ጥቆማ፤ በአገልግሎት ብቃታቸው በጉባኤ ተመስክሮላቸው የሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ከመንበር የሚወርዱት ከሥልጣን የሚሻሩት በሞት እና የሃይማኖት ሕፀፅ ሲገኝባቸው ብቻ ነው፡፡

ሊቃነ ጳጳሳት ወይም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በፖሊቲካ ተጽዕኖ ከታሰሩ እንዲኹም በሕመም ምክንያት በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ከተያዙ በኹለቱም ምክንያቶች ጉዳያቸው እስኪለይለት ድረስ በክብር በሓላፊነት የመቀጠል መብት አላቸው፡፡ ይህንም ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 4 ሲያብራራ፡- “ሊቀ ጳጳስ ወይም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የታመመ እንደኾነ እስከሚድን፣ የታሰረ ከኾነ እስከሚፈታ ይጠበቃል፤ ሹመቱ ለሌላ አይሰጥም፤ የማይድን ደዌ ከያዘውና ሊፈታ የማይቻል እስራት ከኾነ በላዩ ላይ ይሾማል፤ አይጠበቅም፤” ይላል፡፡

ሥርዓተ ምንኵስና እና ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዓርገ ክህነት የሚሰጠው፣ በአብዛኛው፣ ትሩፋትን አገልግሎትን፣ ቅድስናን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ እንደ ጥንቱ ሥርዓት ከኾነ፣ አንድ ምእመን ከገዳም ገብቶ ምንኵስና እንዲፈቀድለት በጠየቀበት ሰዓት፣ ሥርዓተ ምንኵስና አይፈጸምለትም ነበር፡፡ የገዳም አበምኔቶች የምንኵስና ፈላጊውን ምእመን ጥያቄ ብቻ ተቀብለው ሥርዓቱን አያደርሱም፡፡ በቅድሚያ ለምን የምንኵስና ሕይወትን እንደመረጠ ይጠይቁታል፡፡ ምንኵስና የመረጠው ከትዳር ለመሸሽ ወይም የሚወደውን ስላጣ በመሳሰሉት ሥጋዊ ምክንያቶች ከኾነ ራሱን እንዲመረምር ያደርጉታል፡፡

የምንኵስና ሕይወት፣ ከነዚኽ ነገሮች ለመሸሽ ሳይኾን፣ ዕድሜን በሙሉ ራስን ከክርስቶስ ጋር ሰቅሎ በገድልና በትሩፋት የሚኖሩበት ሕይወት መኾኑን አስረግጠው ይነግሩታል፡፡ የምንኵስና ሕይወት በዓለም ዘንድ መሞት መኾኑን ምእመኑ ከተረዳ በኋላ ምእመኑ በተለያዩ አገልግሎቶች እንዲፈተን ይደረጋል፡፡

በሌላ አነጋገር፣ የአመክሮ ጊዜ ይሰጠዋል፡፡ በቅድስናቸው የተመሰከረላቸው የበቁ አባቶችና ወንድሞች በጸሎት እንዲያግዙት ይደረጋል፡፡ በአባቶች ጸሎት እየታገዘ በትሩፋት ሥራ ተጠምዶ ካገለገለ በኋላ ለአንድ ምእመን ሥርዓተ ምንኵስና ይፈጸምለታል፡፡ በዚኽ መስመር የሚጓዙ መነኰሳት በአብዛኛው አገልግሎታቸው ሲሠምርላቸው ይታያል፡፡ በስሜት ተነሣስተው ለሚመጡ ሰዎች ግን የቀደሙት መምህራን ገዳማውያን አባቶች ሥርዓተ ምንኵስናን አይፈጽሙም ነበር፡፡

ይህ ትውፊት የተወሰደው ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ነው፡፡ ሐዋርያው ለአዲስ አማኝ የጵጵስና ማዕርግ መስጠት፣ ተሿሚው ገና ቀንበር ያልለመደ በመኾኑ ለፈተና ሊጋለጥ ስለሚችል፣ “አዲስ ክርስቲያን አይኹን”/1ጢሞ.3፥7/ በማለት ከልክሏል፡፡ ሐዋርያው ክልከላውን ያስቀመጠው፣ አዲስ ክርስቲያን ለኤጲስ ቆጶስነት ቢመርጡት፣ ሰይጣን በአመጣው ትዕቢት ተይዞ በዲያቢሎስ ሊወድቅ ስለሚችል ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያውን ትምህርት መሠረት በማድረግ ስትሠራበት ትኖራለች፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት አባቶች ያኖሩትን ትምህርት በመጣስ፣ አንድ ሰው አምኛለኹ፤ በቅቻለኹ ብሎ ቢቀርብ እንኳ ቤተ ክርስቲያን መሾም የለባትም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ማዕርግ በታማኝነት ሊያገለግሏት የሚችሉትን አገልጋዮች በጥንቃቄ መምረጥ አለባት፡፡

የአበውን ትውፊት በመጣስ፣ የዕድሜን የአገልግሎትን ኹኔታ ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡ ቢሾሙ፤ በዲያቢሎስ ሽንገላ በትዕቢት እየተነፉ፣ እነርሱም ሳይገለገሉ ቤተ ክርስቲያንንም ሳያገለግሉ የጥፋት መሣርያ ይኾናሉ፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥሯን መሠረቷን የሚያውቁ፤ በገድል የተቀጠቀጡና በትሩፋት ያጌጡ፤ በአጠቃላይ በቅድስና ሕይወት ጸንተው የኖሩ አባቶችን ከገዳም ጭምር እየፈለገች መሾም ይጠበቅባታል፡፡ በቅድስናቸው የተመሰከረላቸውን አባቶች መሾም፣ በእውነት ምእመናንን በጸሎታቸው የቅድስና ሕይወታቸው ተካፋይ ያደርጋቸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያንን በአግባቡ ያላገለገሉ፤ በገዳማዊ ሕይወት ያልተፈተኑ፤ በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድ የወደቁ፤ በፍቅረ ንዋይ ያበዱ፤ የውድቀት ታሪክ ያላቸው ሰዎች ያለምንም መስፈርት ሳይመረመሩ ቢሾሙ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሊመሯት አይችሉም፤ እንሥራ ቢሉም ይጎዷታል፡፡ ስለዚኽ በአገልግሎት ያልተፈተኑ፤ በውጭ ባሉ ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር የሌላቸውን ሰዎች መሾም አደጋው የበዛ መኾኑ ሊስተዋል ይገባል፡፡


ምንጭ፡-

 • በእንተ ክህነት፤ ቀሲስ ኃይለ ማርያም ላቀው፤ ፳፻፬ ዓ.ም.
 • ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፤ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ፤ ፲፱፻፹፬ ዓ.ም.
 • ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፤ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ፲፱፻፺፰ ዓ.ም.
Advertisements

13 thoughts on ““የእግዚአብሔር ምርጥ” ኤጲስ ቆጶስ ማን ነው? በፍቅረ ንዋይ ያበዱትንና የውድቀት ታሪክ የሞላባቸውን ጎጠኞችና ሲሞናውያን እናጋልጥ!

 1. Anonymous June 28, 2016 at 4:24 pm Reply

  Kesis Sintayehu Abate
  3 hrs ·

  በቁስላችን ላይ ጥዝጣዜ እንዳይጨመርብን
  በቀሲስ ስንታየሁ አባተ

  በቁስላችን ላይ ጥዝጣዜ እንዳይጨመርብን
  በቀሲስ ስንታየሁ አባተ

  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ከርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወርኀ ግንቦት 2008 ዓ.ም ባካሄደው ርክበ ካህናት በቅርቡ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም መወሰኑንና ለዚህም ዕጩዎችን የሚያቀርብ ኮሚቴ መሠየሙን በመግለጫው አሳውቋል። በርካቶች አኅጉረ ስብከት ብፁዓን ኤጲስ ቆጶሳቶቻቸውን በእርግና፣ በሕመም፣ በሞትና በመሳሰሉት ምክንያቶች በማጣታቸው ያለ አባት መቅረታቸውና አገልግሎታቸው መስተጓጎሉ ይታወቃል። ከችግሩ የተነሣም አንዳንድ ኤጲስ ቆጶሳት ሁለት ሦስት አኅጉረ ስብከት ደርበው እንዲይዙ ተደርጓል። ይህ ደግሞ በብፁዓን አባቶች ላይ የሥራ ጫናን ፈጥሯል፤ የአኅጉር ስብከት አገልግሎት የተቀላጠፈ እንዳይሆንም የበኩሉን አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

  ዘመናችን እንደ ጥንቱ በርቀት ሆኖ በመልዕክት አገልግሎትን መፈጸም ማስፈጸም የሚቻልበት አለ መሆኑን፣ ቤተ ክርስቲያናችን ከውስጥም ከውጪም እየተደነቀረባት ካለው ፈተናም ዓይነትና ብዛት አንጻር፣ ይልቁንም ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ልትጠራቸውና አጥምቃ ልታስገባቸው ከሚጠብቋት ነፍሳት አኳያ የቅዱስ ሲኖዶሱ አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሠየም መወሰኑ ወቅቱን የዋጀ ውሳኔ ነው። ይህ መልካም ሐሳብና ውሳኔ የአባቶቻችን የተልዕኳቸው አንዱ አካልና ከክርስቶስ የተቀበሉት አደራ ቢሆንም መልካም ማሰብ በራቀበት ዘመን ይህን ስላሰቡልን ከልባችን ልናመሰግናቸው ይገባል።

  አባቶች ድርሻቸውን ለመወጣት አንድ ርምጃ ተራምደዋል። በእነርሱ ርምጃ ልክ መከተል ደግሞ የማኅበረ ካህናቱ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና የማኅበረ ምዕመናን ድርሻ ነው። ይህ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የቀበሌ ምርጫ አይደለም። አካለ ክርስቶስ በሆነችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ምዕመናንን የመጠበቅ፣ የመቀደስ፣ የመመገብ፣ ወደ ጽድቅ ጎዳና የመምራት፤ ከእምነት በአፍኣ የሚገኙ አሕዛብን በወንጌል መረብነት የማቅረብ፣ የማንፃት፣ የመጠበቅ ታላቅና ሰማያዊ የሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚፈጽሙ ራሳቸውን ማለት እከብር ባይ ልቡናቸውን የካዱ መንፈሳውያን መሪዎችን ለመሠየም የሚደረግ ምርጫ ነው።

  ይህ ምርጫ ያለ ጥርጥር ቢያንስ ከአራት አቅጣጫዎች ከፍተኛ ፈተና ይደርስበታል ተብሎ ስጋት ፈጥሯል፤

  1. ከመንግሥታዊ ባለ ሥልጣናት

  ሕገ መንግሥቱ በአስራ አንደኛው አንቀጹ መንግሥት በሃይማኖት፣ ሃይማኖት በመንግሥት አንዱ በአንዱ ጣልቃ እንደማይገባ ቢደነግግም ሕጉ ከወረቀት አልፎ መሬት ሲነካ ማየት ግን የሕልም እንጀራ መሆን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ለዚህ ደግሞ ተወቃሹ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የራሳችን አባቶች ጭምር ናቸው። በቅርቡ በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቅዱስ ፓትርያርኩ መንግሥት ጣልቃ ይግባልኝ ባይነት የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን በስብሰባው ላይ መገኘታቸው ይታወቃል።

  ቅዱስ ፓትርያርኩም ይጠይቁ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱም ይፍቀዱ የክቡር ሚኒስትሩ በስብሰባው መገኘት ፍትሐዊ አይደለም። ቢጠየቅ እንኳን መንግሥት ጉዳያችሁን በራሳችሁ ፍቱ ብሎ ጉዳዩን ለባለ ጉዳዩ ብቻ መተው ነበረበት። ይህ ክስተት እንደ አስፈላጊነቱ መንግሥት “ሲያምንበት” በቤተ ከርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ያሳያል። ይህን ጉድ ብለን አድንቀንም አዝነንም ሳንጨርስ ከወደ ጋምቤላ ደግሞ የባሰ ነገር ሰማን። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር “የጋምቤላና የደቡብ ሱዳን አኅጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ኤጲስ ቆጶስነት ካልተሾሙ አብረን መሥራት አንችልም፤ ሌላ አባት አንቀበልም” የሚል ደብዳቤ ለቅዱስነታቸው መፃፋቸውን ሰማን፤ ደብዳቤያቸውንም በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች ተለጥፎ አነበብን።

  እነዚህ ክስተቶች እንደ ቀድሞው ሁሉ ዛሬም መንግሥታዊ ባለ ሥልጣናት ለሥርዓተ መንግሥታቸው መጠበቅ ወይም የቅርብና የልብ ወዳጃቸውን ወደ ከፍተኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን ወንበር ለማምጣት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚሠሩ መሆናቸውን ያሳያል። በመሆኑም በቅርቡ ይከናወናል ተብሎ የሚጠበቀው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ከሥርዓቱም ሆነ ከሥርዓቱ አስፈጻሚዎች ጫን ከበድ ያለ ፈተና ወይም ተፅዕኖ ይደርስበታል ተብሎ ይሰጋል።

  2. ከውሉደ ሲሞን

  ሲሞን በሐዋርያት ዘመን የነበረ ጠንቋይ ነው። በክርስቶስ አመንኩ በማለት ወደ ሐዋርያት ቀርቦ ነበር። መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳን ሐዋርያት እጅ የሚያደርገውን ገቢረ ተአምራት በተመለከተ ጊዜ የቀደመ ግብሩ ማለት ጥንቆላውና በዚያ ያገኝ የነበረው ገንዘብ ትዝ አለው። በክርስትና ስም የተወውን ጥንቆላ የክርስትና ካባ አልብሶ ያጣውን ገንዘብ ለመሰብስብ አቀደ። በመሆኑም ወርቅና ብር ይዞ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ በመቅረብ “እኔም እንደ እናንተ እጄን በመጫን መንፈስ ቅዱስን ማሳደር እንድችል ይህን ሥልጣን ስጡኝ” ብሎ ለመነ። በእምነትና በቅድስና እርሱ መንፈስ ቅዱስ ሲፈቅድ የሚገኘውን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በገንዘብ መግዛት ፈለገ። የሊቀ ሐዋርያነት ዓላማ አደራና ግብ በውል የተረዳው ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተም ገንዘብህም አንድ ላይ ጥፉ” ብሎ አሳፍሮታል። ከዚያን ወዲህ ሥልጣነ ክህነትን በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ምርጫ ሳይሆን እጅ መንሻ ወይም ጉቦ ከፍለው ማግኘት የሚሹ ውሉደ ሲሞን ሲባሉ ግብሩ ደግሞ ሲሞናዊ ይባላል። ይህ ግብር በዘመናችን በዓለማችን ባሉ አብያተ ክርስቲያናት እያደገ እንደመጣ ይነገራል። በእኛም ሀገር ማቆጥቆጥ መጀመሩ ይነገራል። ከማቆጥቆጥ አልፎም ደህና ገቢ ባላቸው አድባራት እልቅና ወይም ፀሐፊ ሆኖ ለመሾም እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ድረስ እጅ መንሻ (ጉቦ) መክፈል ተጀምሯል ተብሎ የሰሞኑን የአለቆች ዝውውር ተከትሎ በመወራት ላይ ነው። እውነታውን እግዚአብሔር ይወቀው። በቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ተሰማኒትና ተቀባይነት አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በስጦታ ብዛት ሕሊናቸውን ለመለጎም በአማላጅ ብዛት መውጫ መግቢያ በማሳጣት ምንጩን ራሳቸውና እግዚአብሔር የሚያውቁትን ገንዘብ እንደሲሞን በማፍሰስ ኤጲስ ቆጶስነትን ገንዘብ ለማድረግ የሚጥሩ በርካቶች ናቸው። በርግጥ በእልቅና ዘመናቸው የእግዚአብሔርን ቤት ሙዳየ ምፅዋት መገልበጥ የለመዱ ደፋሮች ከፍ ባለው የኤጲስ ቆጶስነት ሥልጣን የበለጠ እናገኛለን ብለው የቻሉትን ያህል ገንዘብ ቢያፈሱ ላይገርም ይችላል፤ ድፍረቱን ለምደውታልና ነው።

  በዘመናችን ገንዘብ “አምላክ” ሆኖ መመለኩን ስናስተውል እነዚህ ሰዎች ዕጩዎችን መርጠው ያቀርቡ ዘንድ በተሠየመው ኮሚቴ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ምን ያህል እንደሚከብድ መገመት አያስቸግርም።

  3. ከሐራ ጥቃ መናፍቃን

  ሰኔ 12/2008 ዓ.ም በአሜሪካ የተፈጸመውን “የኤጲስ ቆጶሳት” ምርጫ ተከትሎ በዓለም ዙርያ የሚገኙ የተሐድሶ ምንፍቅና አራማጆች ልዩ ደስታን ተጎናጽፈዋል። የዚህም ምክንያቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን በመናድና ክርስትናን እንደ ምዕራባውያኑ በተሐድሶ ስም ለመግደልና ለማጥፋት በዓላማ የሚተባበሯቸው ለዘመናትም የውስጥ አርበኛ ሆነው ሲሠሩ የነበሩት “ኤጲስ ቆጶስ” ሆነው በመመረጣቸው ነው። ይህን የሐራ ጥቃዎቹን ጮቤ መርገጥ ስናይ እነዚህ ሰዎች በተመሳሳይ መልኩ በሀገር ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታ ለመፍጠር ምን ያህል በዓላማ ሊሠሩ እንደሚሠሩ መገመት አይከብድም። ከአጥቢያ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት አላቸው ተብሎ የሚነገርለትን ሰንሰለታቸውን ስናጤነው ደግሞ ስጋታችን ያይላል። ስጋታችንም አንድ ሁለት ሰው አሾልከው ያሾማሉ በማለት ብቻ አይደለም። ራሳቸውን ወደ ኤጲስ ቆጶስነት ማዕረግ ካስጠጉ ወደፊት ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን አደጋ በማሰብ እንጂ። ከዚህም በተጨማሪም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ የቤተ ክርስቲያናችን አባላት የሃይማኖት ሕፀፅ፣ የምግባር ጉዳለት አለባቸው ብለው ለዘመናት አቤቱታ ሲያቀርቡባቸው የኖሩት መነኮሳት ለኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ጥቆማ ውስጥ መግባታቸው ራሱ የሐራ ጥቃዎች ድፍረት ምን ድረስ እየሄደ እንደሆነ ያሳያል።

  4. ከጎጠኝነት፣ ከወንዘኝነትና ከዘረኝነት መንፈስ

  የጥንት አባቶቻችን አንድን ሰው የሚያውቁት በእምነቱ ጽናትና በምግባሩ ቀናነት ነበር። ለአንድ ኀላፊነት ወይም ለሢመት ሲያጩትም መስፈርታቸው እምነቱ፣ ሥነ ምግባሩና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ጠንቅቆ ማወቅ የሚሉ ናቸው። ከዚህ ውጪ ብሔሩ፣ ቋንቋው፣ መንደሩና ወንዙ የመሳሰሉት ከግምት ውስጥ ፈጽመው አይገቡም ነበር። ለዚህም አስረጂ የሚሆነን በመልክ፣ በባሕል፣ በቋንቋ፣ በመልከዓ ምድር ከማይመስሉን ሀገር ወደኛ መጥተው ቤተ ክርስቲያናችንን ሲያገለግሉ የነበሩ አባቶችን ማንሣቱ ብቻ ይበቃናል። ከሣቴ ብርሃን አባ ሰላማ፣ ዕጨጌ ዕንባቆም፣ ተሠአቱ ቅዱሳን በትውልድ ኢትዮጵያውያን አይደሉም። በእምነታቸው ኦርቶዶክሳዊነት፣ በምግባራቸው ቅናነት ተቀብለናቸው ቅድስናቸውን ለዘመናት በማወጅ ላይ እንገኛለን።

  አሁን አሁን ግን ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ወርቃማ መለያ የሆነው ገጽታ በመቀየር ላይ ይገኛል። አንድ አገልጋይ እምነቱና ምግባሩ እንዲሁም ትምህርቱ ሳይሆን የትውልድ ቀዬው ቋንቋው ነው የሚጠየቀው። ይህ መጥፎ የሆነና የነቀዘ አመለካከት በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫውም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል ተብሎ በብዙዎች ተሰግቷል። ይህም ስጋት ከባዶ ሜዳ የመጣ አይደለም። በየገዳማቱ፣ በየአድባራቱ በወረዳ ቤተ ክህነትና በሀገረ ስብከት እንዲሁም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ለሚወጡ ክፍት የሥራ ቦታዎች በሚደረጉት ውድድሮች አሸናፊ ለመሆን ዋና መስፈርቱ የሥራ መደቡ የሚጠይቀው ሙያዊ ብቃትና ተገቢው የሥራ ልምድ ሳይሆን የኀላፊው “የሀገር ልጅ” እየሆነ ከመጣ ሰንበትበት ብሏል።

  የኤጲስ ቆጶሳቱን ምርጫ በተመለከተ ያነጋገርኳቸው አንዳንድ ሰዎች ከሌሎቹ ስጋቶች ሁሉ ይኸኛው እጅግ ከበድ እንደሚል ይናገራሉ። ለዚህም ዋና ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት “በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ስብሰባዎች የሚነሡ የሐሳብ ልዩነቶችን በአምክንዮአዊና በተጠየቃዊ መልኩ ከማሳመን ይልቅ በደጋፊ (ቲፎዞ) ብዛት ለማሳመን ወይም ተፅዕኖ መፍጠር የሚል እንግዳ አሠራር በአንዳንድ አባቶች ሳይቀር እያቆጠቆጠ መጥቷልና ነው” ይላሉ።

  ከላይ ለመጠቆም የሞከርኳቸውና ሌሎች ያልዳሰስኳቸው ነጥቦች በቅርቡ የሚካሄደውን የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ አስምራጭ ኮሚቴዎቹን ከፍተኛ ውዝግብና ተፅዕኖ ውስጥ ሊያስገቡ ይችላሉ።

  በዚህም የተነሣ ለአስመራጭ ኮሚቴነት የተመረጡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፦
  1. ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ
  2. ብፁዕ አቡነ ገሪማ
  3. ብፁዕ አቡነ ገብርኤል
  4. ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ
  5. ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
  6. ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ
  7. ብፁዕ አቡነ አብርሃም
  8. የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ተፅዕኖውን ተቋቁመው ቤተ ከርስቲያናችንን ወደ ቀደመ ልዕልናዋ ሊመልሷት ወይም በሰውም ሆነ በእግዚአብሔርም ዘንድ ሊያስጠይቃቸው በሚችል ሁኔታ በተፅዕኖው ሊደናቀፉ ይችሉ ይሆናል።

  ምን እናድርግ?

  ችግሮችን ብናወራ ለቤተ ክርስቲያናችን አይበጃትም። የተጠበቀው ሢመት የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት በጠበቀ መልኩ እንዲፈጸም በሰከነ አዕምሮ ልናስብና ፍጹም መንፈሳዊ በሆነ አካሄድ የድርሻችንን መወጣት አለብን። ለዚህም በሀገር ውስጥ ያሉ መላው ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምዕመናን ይልቁንም የቤተ ክርስቲያናችን ፈርጦች የሆኑ የሰንበት ተማሪዎች በውጪም ያሉት አገልጋዮችና ምዕመናን ካሁኑ መሠረታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅብናል። ከእንቅስቃሴዎቹም የተወሰኑትን ለመጠቆም ያህል፦

  1. እግዚአብሔር በቤቱ የራሱን ሰዎች እንዲያስቀመጥ አብዝቶ መጸለይ

  በጸሎት የማይደረግልን ነገር የለም። ይልቁንም ስለ ቤቱ በቀናነት የምናቀርበውን ልመና እግዚአብሔር ይሰማል። ይለማነናል። ከጥላቻ፣ ከሕሜት፣ ከቡድናዊ ስሜት ርቀን የራሳችንን ሃሳብ ወደ ጎን ትተን በሙሉ እምነት እንጸልይ። ይልቁንም ከፊታችን ታላቁና ተወዳጁ የፍልሰታ ጾም እየተቃረበ ስለ ሆነ በጾማችን ወቅት በእመቤታችን አማላጅነት ወደ እግዚአብሔር ከምናቀርበው ልመና አንዱና ተቀዳሚው የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ይሁን። በሥራና በጤና ምክንያት ይህን ማድረግ የማንችል ደግሞ መብዓውን ወደ ገዳማቱ እንላክና አባቶች እንዲጸልዩበት እናድርግ። ከወዲሁም በየገዳማቱ ያሉ አባቶች ጉዳዩን ተረድተው አጥብቀው እንዲጸልዩ አደራ እንበላቸው።

  2. መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችል መረብ መፍጠር

  ቤተ ክርስቲያናችን ዓለም አቀፋዊት እንደመሆንዋ አገልጋዮቿ በመላው ዓለም ተሰራጭተው ይገኛሉ። የሚመረጡትም ከነዚሁ በመላው ዓለም ተሰራጭተው ካሉት አገልጋዮቿ መካከል ነው። ስለዚህ ተኩላ ከበጎች ጋር ተመሳስሎ እንዳይገባ በዕጩነት ስለሚጠቆሙት ፍጹም የቤተ ክርስቲያን አባትነት መረጃ መለዋወጥ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የመረጃ መረብ ሊኖረን ይገባናል። በመሆኑም ሙያውና ለቤተ ክርስቲያን መቆርቆሩ ያላችሁ ወገኖች ጊዜ ሳትሰጡ አስቡበት። የመረጃ መረቡ የቤተ ክርስቲያናችንን ሕልውና ከነሙሉ ክብሯ ከማስጠበቅ ውጪ አንዳች ፖለቲካዊ አጀንዳ እንዳይኖረው አዘጋጆች ልዩ ጥንቃቄ አድርጉልን። ይህ አንድነታችንን ያላላዋል እንጂ አያጠብቀውም።

  3. በሚደረጉ ውይይቶች በንቃትና በትጋት መሳተፍ

  ለዕጩነት በሚቀርቡ አባቶች የእምነትና የሥነ ምግባር ብቃት ላይ በነበሩባቸው አድባራትና ገዳማት ባሉ ካህናት፣ ምዕመናንና የሰንበት ተማሪዎች ውይይት እንደሚካሄድ ተነግሯል። በዚሁ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶሳችን በመግለጫው ያሰማንን ቃል እንዲያከብር መጠየቅ፣ ለውይይቱ መድረክ ከተከፈተም በፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ጨዋነት ልንሳተፍ ይግባናል።

  መጥፎ ባሕል ሆኖብን ለውይይት ዕድሉ ሲሰጠን መናገር የማይሆንልን ከመድረክ ስንወርድ ማጉረምረምና ማማት የምንወድ ብዙዎች ነን። ይህ እንኳን ለቤተ ክርስቲያን ለጉርብትናም አይበጅም። ካለፈ በኋላ ተኩላው ከበግ ጋር ተመሳስሎ ገብቶ “ይድልዎ” ተብሎ ከተሠየመ በኋላ መጮሁ አይጠቅምም።

  4. እንቅስቃሴዎችን በንቃት መከታተል

  ቅዱስ ሲኖዶሱ የኤጲስ ቆጶሳቱ ምርጫ አጥቢያ ድረስ ወርዶ ውይይት ይደረግበታል ብሎ መወሰኑ ያስደሰተን የመኖራችንን ያህል ያሳዘናቸው አሉ። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ዓላማ አድርገው የተነሡት ነገር በውይይት የሚከሽፍባቸው መስሎ ከታያችው የተለያይ የማዘናጊያ ዘዴዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ለዘመናት የሰንበት ተማሪዎችን እንደ ጠላት በማየት አላሠራ ያላሉትን ያህል አሁን ከእነርሱ ድጋፍ ለማግኘት አዳራሽ እንዲሠራላቸው፣ አዲስ የደንብ ልብስ እንዲሰፋላቸው፣ የጉዞ መርሃ ግብሮች በሰንበት ትምህርት ቤት ብቻ እንዲካሄዱ፣ ካሀናት ደመወዝ እንዲጨመርላቸው፣ ቀድሞ ነጋ ለኪዳን መሸ ለቁርባን አልተገኘህም ብለው ደመወዝ ይቆርጡ የነበሩት አሁን እጅግ ትኁት ሆነው የካህናቱንና የሰበካ ጉባኤ አባላቱን ጉልበት ለመሳም የሚዳዳቸው፣ የተረሳውን የልማት ዕቅድ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ ደፋ ቀና ማለት የጀመሩ እንዳሉ በስፋት መታየት ጀምሯል።

  ከዚሁ በተጨማሪም በውይይቱ ላይ መላው ማኅበረ ካህናቱና መላው የሰንበት ተማሪዎች እንዳይሳተፉ የቦታ፣ የሰዓት ጥበትን፣ የጥበቃና የደኅነንት ጉዳይን በማንሣት የተወሰኑት ብቻ እንዲሳተፉ በሚል ሽፋን ባዘጋጇቸው ቡድኖቻቸው መልካምነታቸው ብቻ እንዲወራላቸው እስከማስደረግ ሊሄዱ ይችላሉ። ግፋ ሲልም በብርቱ ይቃወሙናል የሚሏቸውን የሰንበት ተማሪዎች በሰበብ ባስባቡ በውይይቱ ዕለት ሊያሳስሩ ይችሉ ይሆናል። ስለዚህ ካህናቱ ምዕመናኑና የሰንበት ተማሪው በንቃት ሊቀድማቸው ይገባል። “ዝምታ ለበግም አልበጃት፤ አሥር ሆና ወጥታ አንድ ቀበሮ ፈጃት” ነው የሚባለው?

  5. መረጃዎች ለአስመራጭ ኮሚቴው ማድረስ

  በእጃችን ያሉ ወይም ከተለያዩ ቦታዎች የምናገኛቸውን መረጃዎች ፎቶ ኮፒ እያነሣን ለአስመራጭ ኮሚቴው ብናደርስ የተጠቋሚዎችን ማንነት መላልሰው እንዲያጤኑት የሕዝቡንም ድምፅ እንዲሰሙ ያደርጋል። በርግጥ ባልተጣራ መረጃ ራሳችንን ወደ ስሕተት እንዳናስገባ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ንጹሑንና ኦርቶዶክሳዊውን አይገባውም፤ ነቀፋ ያለበትን ደግሞ ይገባዋል ብሎ ማቅረብ “በሐሰት አትመስክር” ያለውን የእግዚአብሔር ቃል መተላለፍ ነው። ይህ ደግሞ ማንንም ይሁን በፍርድ ቀን ያስጠይቃል። ስለዚህ መረጃዎቻችን እውነተኛ መሆናቸውን እንመርምር፤ ለአባቶቻችን እናድርሳቸው።

  6. ከቡድናዊ ስሜት መውጣት

  የተጠመቅነው ከምድራዊ ቡድናዊነት ወጥተን ወገንተኝነታችን ለእግዚአብሔርና ለመንግሥቱ ብቻ እንዲሆን ነው። አባ እገሌን ልናውቃቸው ልንቀርባቸው እንችላለን። ከእርሳቸው በፊት ግን በአርባና በሰማንያ ቀናችን ያወቅነው ቤተ ክርስቲያንን ነው፤ እግዚአብሔርን ነው። ዲያቆናቱን፣ ቀሳውስቱን፣ ጳጳሳቱን ያስገኘች ቤተ ክርስቲያን ናት። ራሷና ጉልላቷ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ ቡድናዊነታችን የመድኀኒታችንን ፈቃድ ከመፈጸም ጋር ነው መሆን ያለበት። እምነታችን የወንዝ፣ የጎጥ፣ የቋንቋና የፖለቲካ ዘረኝነትን ካላሸነፈ ገና ክርስቶስን ባለማወቅ በድንቁርና ጫካ ውስጥ
  ነው ያለነው።
  አንድ ነገር እናስብ። በቤተ ክርስቲያን ላይ ቀርቶ በአንድ ግለሰብ ላይ የሚደረገውን ደባ አምላካችን በደብረ ጽዮን በክብር ሲገለጥ ሁሉን ይፋ ያደርገዋል። ዋጋውን እንደሥራውም ይከፍለዋል። ስለዚህ ክርስቶስ በደሙ ይቀድሳትና ያነፃት ዘንድ በመስቀል ላይ የዋለላትን ቅድስት ቤተ ከርስቲያን ከከበቧት የበግ ለምድ ከለበሱ ተኩላዎች እንጠብቃት። እግዚአብሔር ሆይ ቤተ ክርስቲያንህን አስብ። አሜን።

  • Anonymous June 28, 2016 at 6:10 pm Reply

   ጥሩ ሀብሳ ነው ችግሩ ግን ይህን ሀሳብ የሰጠ ሰው ራሱ ካስቀ መጣ ቸው ሃጢአቶች ነጻ አይደልለም ቢያንስ ከዘረኝትነ

   • ከበደ June 29, 2016 at 7:59 pm

    አረ አባ እንቁ ስላሴ ብዙ ጉድ አለዉ ከሁለት ሴቶች ወልዷል አንዷ አካለ ጉዳተኛ ናት። በዚህ ጉዳይ ፐሊስ ይዞታል። ……….

  • Anonymous June 28, 2016 at 7:31 pm Reply

   ማጋለጥ ከሆነ የሚመረጡትን ብቻ ሳይሆን ተሾመው በፍቅረ ንዋይ የተዘፈቁትንና፣ በዝሙት የሰከሩትንም ሊሆን ይገባል።

  • Anonymous June 29, 2016 at 4:23 am Reply

   መልካም ነው።
   thank you
   Kessis

 2. F.A.M June 28, 2016 at 9:36 pm Reply

  ይደልዎ ብለናል

 3. Anonymous June 29, 2016 at 7:38 am Reply

  ለማንኛዉም ነገር እግዚአብሔር አገልጋዮቹን እርሱ እንዲመርጥ መጸለይ ይገባን በወግን በጎጥ በጎሳ ልዩነት ሳንፈጥር የቤተክርስቲያን አባት የሆነ አገልጋይ መምረጥ ይገባናል በተለይም በአሁኑ ጊዜ ተኩላ በበዛበት ዘመን መናፍቁን ከትክክለኛዉ መለየት በሚያዳግትበት ዘመን ትክክለኛዉን አባት እግዚአብሔር እንዲመርጥ መጸለይ ግድ ይላን፡፡
  በተራ ቁጥር 69 ላይ የተቀመጡት
  1ኛ. ስነ ምግባር የሌላቸዉ እና የምንኩስና ዓላማን በትክክል ያላወቁ
  2ኛ. ብዙ ወጣት ሴቶችን በማበላሸት የሚታወቁ እና በዚህ ምክንያት ታስረዉ የተፈቱ
  3ኛ.ምንም ዓይነት ትምህርት የሌላቸዉ እና ስራተ ቅዳሴ የማያዉቁ
  4ኛ.ፎርጅድ በማሰራት የቅኔ መምህር ነኝ በማለት ተፈትነዉ የተዋረዱ
  5ኛ.ወንጌል ከማስተማር ይልቅ ፊልም በማየት ጊዜአቸዉን የሚያቃጥሉ
  በመሆናቸዉ እንካን ጳጳስ ሊሆኑ ተራ ሰራተኛ አገልጋይ መሆን የማይችሉ ተራ ምዕመን በመሆናቸዉ ኮሚቴዉ ማጤን ይኖርበታል መጠንቀቅም አለበት በቅርቡ ከላሊበላ ካህናት ታምሜ ወደ ዉጭ ልጻከም ልኄድ ና በማለት ከምስኪኑ ካህን የሰበሰቡትን 100000 ብር ለዚሁ ዓላማ አዉለዉታል ስለዚህ የዚህን አባት መመረጥ በእጅጉ እቃወማለሁ አይመጥኑም፡፡

 4. yared June 29, 2016 at 8:02 am Reply

  በርግጥ ባልተጣራ መረጃ ራሳችንን ወደ ስሕተት እንዳናስገባ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ንጹሑንና ኦርቶዶክሳዊውን አይገባውም፤ ነቀፋ ያለበትን ደግሞ ይገባዋል ብሎ ማቅረብ “በሐሰት አትመስክር” ያለውን የእግዚአብሔር ቃል መተላለፍ ነው። ይህ ደግሞ ማንንም ይሁን በፍርድ ቀን ያስጠይቃል። ስለዚህ መረጃዎቻችን እውነተኛ መሆናቸውን እንመርምር፤ ለአባቶቻችን እናድርሳቸው።

 5. Anonymous June 29, 2016 at 12:21 pm Reply

  ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በሙሉ ቤተ ክርስቲያናችን እንክርዳዱን ከስንዴው የመለየት ሥራ በይበልጥ በዚህ ዓመት በትጋት እየሰራች እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው አሁንም ወደ 16 የሚጠጉ መነኮሳትን በንጸሕናቸው፡ በዕምነታቸው፡በሥነ ምግባራቸው በሕብረተሰቡ ዘንድ የተመሰከረላቸውን ጳጳስ ለመሾም ዝግጅት ላይ ትገኛለች ስለዚህም ጳጳስ የሚሾመው ንጽሕናው የተመሰከረትና ድንግል የሆነ ነው ድንግል ያልሆነ የተልከሰከሰና ዓላማውን የሳተ የረከሰ ያበደ ውሻ ከተገኘ በምንም ዓይነት ተዓምር ጳጳስ አይሾምም በፍጹም አይሆንም፡ይሄ የድፍረት ድፍረት ነው እንደውም ክህነቱ ተሽሮ “አባ” የሚለው ስም ይነሳና ተልዕኮውን ስለረሳ አቶ ተክለ ማርያም አምኜ የሚል ይሰጠዋል ጳጳስ የሚሾመው ራሱ ፀድቆ ሊያፀደቀን እንጂ ተቀስፎ ሊያስቀስፈን አይደለም ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሚሾሙት ጳጳሳት የዕምነቱ ተከታይ የሆነ ሁሉ ያየውን የሰማውን አስተያየቱን እንዲሰጥ ለመላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡በዝምታ ራስን ማግለል ከተባባሪነት ተለይቶ የሚታይ አይደለም ቤተክርስቲያንን ከአደጋ በጎችንም ከተኩላ ለመታደግ የሚያበቃ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል ዝም ማለት ለአጥፊዎች እንጅ ለቤተክርስቲያን አይጠቅምም፡፡ በእግዚአብሔርም ዘንድ ከተጠያቂነት አያድንም፡፡
  እውነት መመስከር እውነት መናገር በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ ያሰጣል፡፡በዚህ ዓለምም ምንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍልም፡ስለቤተ ክርስቲያን ሲባል እውነት መናገር ሰማዕትነት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡
  የአንድ ምዕመን አስተያየት ትልቅ ዋጋ አለውና በፍጹም እንዳይዘናጉ
  በዚህ አጋጣሚ ይህን መልዕክት ያልሰሙ ምዕመናኖች ሊኖሩ ስለሚችሉ ሁሉም ሰምቶ
  ክርስቲያናዊ ግዴታውን እንዲወጣ በwhatsApp: በviber በmessenger…በመሳሰሉት ሼር በማድረግ ይተባበሩ”ጅብ ከሄደ፡ውሻ ጮኸ” እንዳይሆን ነገሩ ካሁኑ የተሰጠንን የቤት ሥራ በትጋት እንወጣ፡፡እግዚአብሔር አምላክ ለቅድስናው ሥፍራ የሚመጥን አባቶችን ያስቀምጥልን፡፡
  እስከ አኹን ድረስ በተለያዩ መንገዶች የተጠቆሙና በአብዛኛውም አስመራጭ ኮሚቴው ከብፁዓን አባቶች እንደተቀበላቸው የተገለጹ ቆሞሳትና መነኰሳት ስም ዝርዝር በሃራ ተዋሕዶ ብሎግ https://haratewahido.wordpress.com/2016/06/25/%e1%88%88%e1%8a%a4%e1%8c%b2%e1%88%b5-%e1%89%86%e1%8c%b6%e1%88%b3%e1%89%b5-%e1%88%9d%e1%88%ad%e1%8c%ab-%e1%8b%a8%e1%89%86%e1%88%9e%e1%88%b3%e1%89%b5%e1%8a%93-%e1%88%98%e1%8a%90%e1%8a%b0%e1%88%b3/ ይመልከቱ፡፡

 6. GECH KING June 29, 2016 at 3:31 pm Reply

  መልካም ሃሳብ ነው ፡
  ምርጫው በትክክል መከናወን አለበት ፡ ሁሉም ሃላፊነቱን በሚገባ መወጣት አለበት ፡ በቅድሚያ የምርጫው አላማ መሆን ያለበት መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያገለግሉ የእግዚአብሄር አገልጋዮችን መምረጥ ወይም መሾም ብቻ መሆኑን ተረድተን ስለአላማው መሳካት እግዚአብሔር እንዲረዳን እንፀልይ ፡፡ ምርጫው የሚከናወነው በእግዚአብሄር ቤት ነውና የሁሉ ባለቤት እየሱስ ክርስቶስ ሰላማዊና እውነተኛ ያድርገው፡፡ ለጊዜው በስልጣን በመመካት ፤ በዘር በመጠቃቀም ፤ የራሳቸው ያልሆነውን ገንብና ሃብትን መመኘት የሚጠቅማቸው ቢመስላቸውም እግዚአብሔር የሚስኪኖችን በደል ያስመልሳል ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ !!
  አ ሜ ን !!

 7. Anonymous June 30, 2016 at 4:02 am Reply

  ይሄ ሁሉ ሃተታ በቅርቡ ውጭ ያለው ሲኖዶስ የሾማቸውን ሊቃነ ጳጳሳት ሲመት ለመንቀፍ መዋሉ አንድም አሳፋሪ ሁለተኛም አላዋቂ ወይም አውቆ አደናጋሪ ከመሆን ባሻገር ከመንፈሳዊ ይዘቱ ይልቅ ፓለቲካዊ ቅኝት ያለው የተራ ደብተራ ዘለፋ ነው ,ይነስም ይብዛ እኒህ ዛሬ የተሾሙት አባቶች ይህንን ቡትቶ ከጻፈው “ቀላል” ሰው የተሻለ አገልግሎት ለቤ/ክ አበርክተዋል እያበረከቱም ጭምር ነው ።ሲጀመር አባ ጳውሎስን የመሰለ የኖርዝ አሜሪካ ዱርዬ ፓትርያርክ አድርጎ የተቀበለ ቡድን በምን አይነት ሞራል የሌሎችን ሹመት ለመንቀፍ መሞከሩ ከአባ ጳውሎስ ሞትም በሁዋላ እባ ማትያስን ከጾም እና ከጸሎት ይልቅ እንደ ፓለቲካ መሪ በምርጫ ኮረጆ በእነ አቦይ ስብሃት አጋፋሪነት በዘረኝነት የተጨማለቀ “ሲኖዶስ” የሾመ ድርጅት እንዲህ አይኑን በጨው አጥቦ ያልበላውን ሲያክ ማየት እኛ ኢትዮጵያውያን የደረስንበትን የሞራል ዝቅጠት አመላካች ነው !!! ለነገሩ ፍርድ ከላይ ስለሆነ ይሄ ሁሉ ዝብዘባ ከመተዛዝብ ውጭ የሚያመጣው ለውጥ የለም ,ልብ ይስጣችሁ!!

 8. አምሳሉ አይዛ June 30, 2016 at 3:38 pm Reply

  ከምንም በላይ እግዚአብሄር ለራሱ ያለዉን አገልጋይ ይምረጥ፡፡ በዝህ ቦታ እግዚአብሄር ራሱ ተከታትሎ እንዲፈጽ የሾመዉ አባት እግዚአብሄር በሰጠዉ ጸጋ እግዚአብሄርን የምያገልግል ትጉህና ስራቱን የምያሟሉ እንድመርጡ እግዚአብሄር በመንፈሱ ያግዛቸዉ፡፡
  እኛን በበተክርስትያናችን ያጽናን፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: