ቅዱስ ፓትርያርኩ: ምእመናን፣ የቴሌቭዥን አገልግሎቱን እንዲደግፉና እንደ ዓይን ብሌን እንዲጠብቁት ጥሪ አቀረቡ

 • የምእመናን ሀብትና ንብረት የኾነ የቤተ ክርስቲያኗ ልዕልና መገለጫ ነው
 • ሃይማኖታዊ ሰብእና ያለው ጤናማ ማኅብረሰብ ለመገንባት የታሰበበት ነው
 • በተለይ ወጣቱ፣ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን በንቃት ሊከታተልበት ይገባል
 • ደማቁን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሲማር ኢትዮጵያንም እዚያው ያገኛታል

*               *               *

የሙከራ ስርጭቱ መጀመር በመንበረ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት በይፋ በተበሠረበት ወቅት(ፎቶ: አ/አበባ ሀ/ስብከት)

ቤተ ክርስቲያናችን ለሚዲያ አገልግሎት ትኩረት መስጠቷ፥ ዐዋቂውም ኾነ ወጣቱ ትውልድ፥ ስለሃይማኖቱ እና ስለታሪኩ፣ ስለሀገሩና ስለማንነቱ፣ ስለባህሉና ስለትውፊቱ ማወቅ የሚገባውን ዐውቆ የባለቤትነትና የታሪክ ጠባቂነት ሓላፊነትን እንዲሸከም ለማድረግ ነው፤ ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፤ ገናናዋ ቤተ ክርስቲያናችን ድምፅዋን በመላው ዓለም ለሚገኙ ልጆችዋ የምታሰማበትን የብዙኃን መገናኛ፣ ምእመናን ኹሉ እንዲደግፉና እንደ ዓይናቸውም ብሌን እንዲጠብቁት ጥሪ አቀረቡ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ “ለረጅም ጊዜ በጉጉት ስትጠባበቁት የነበረውን የታላቋ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድምፅ፤ እግዚአብሔር ለፍጡራን በሰጠው አእምሮ በተሠራ በዚህ የብዙኃን መገናኛ ለመስማት በመብቃታችኹ እንኳን ደስ አላችኹ!!” በማለት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን አገልግሎት (EOTC tv.) የሙከራ ስርጭቱን በይፋ መጀመሩን፣ ትላንት፣ ኃሙስ፣ ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጽ/ቤታቸው በሰጡት ቃለ ቡራኬ አብሥረዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን እውን ያደረገችው የብዙኃን መገናኛ ስርጭቱ፤ የምእመናን ሀብትና ንብረት፤ እንዲኹም፣ የቤተ ክርስቲያን ልዕልና መገለጫ መኾኑን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በቃለ ቡራኬአቸው ተናግረዋል፡፡

በጣቢያው የሚተላለፈው ነገረ ሃይማኖት፣ ቤተ ክርስቲያናችን ከብዙ ተጋድሎ ጋር ለረጅም ዘመናት ጠብቃ ያቆየችው እንደኾነ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፣ ምእመናን ኹሉ ድጋፋቸውን በመስጠት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲያሳድጉት፣ እንዲንከባከቡትና እንደ ዓይናቸው ብሌን እንዲጠብቁት አሳስበዋል፤ ለኻያ ዐራት ሰዓት መጠቀም የሚያስችል ቻናል የሚኾነው፣ የምእመናን ድጋፍ ሲታከለበት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

ምእመናን፥ ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን፣ ሥርዓተ አምልኮን፣ ደማቁን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሲማሩ፣ “ኢትዮጵያንም እዚያው ታገኙአታላችኹ፤” ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፤ ጣቢያው፣ ሃይማኖታዊ ሰብእና ያለው ጤናማ ማኅብረሰብ ለመገንባት የታሰበበት እንደኾነ ጠቁመው፤ በተለይም ወጣቶች፣ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን በንቃትና በምልአት እንዲከታተሉ፤ ድጋፋቸውንም አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ቅዱስነታቸው፣ የሙከራው ስርጭቱን መጀመር ባበሠሩበት በዚኹ ንባባዊ መግለጫ ላይ ከተገኙት ብፁዓን አባቶች መካከል፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፤ የብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢና የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፤ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፤ የሐዋሳና ቦረና አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እና የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ አባታዊ መልእክታቸውን ማስተላለፋቸው ታውቋል፡፡

ይኸው የቅዱስነታቸውና የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ማብሠርያ ቃለ ቡራኬ እና መልእክት፤ በሙከራ ስርጭቱ ላይ በተደጋጋሚ እንደሚተላለፍ ለመረዳት ተችሏል፡፡

*               *               *

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን!

‹‹አማን አማን እብለክሙ ዘይሰምዕ ቃልየ ወየአምን በዘፈነወኒ ይረክብ ሕይወተ ዘለዓለም፤ እውነት እውነት እላችኋለኹ፤ ቃሌን የሚሰማ በላከኝም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛል፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይሔድም›› (ዮሐ. 5፥24)

በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ወምእመናት በሙሉ!

የመልካም ስጦታ ኹሉ ባለቤት የኾነው እግዚአብሔር አምላካችን በእርሱ ቅዱስ ፈቃድ ቃሉን በዚህ ሚዲያ በምልአት ለመስማት ስላበቃን ክብርና ምስጋና፣ አምልኰት እና ስግደት ለእርሱ ይኹን፡፡ እናንተም ለረጅም ጊዜ በጉጉት ስትጠባበቁት የነበረውን የታላቋ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድምፅ፤ እግዚአብሔር ለፍጡራን በሰጠው አእምሮ በተሠራ በዚህ የብዙኃን መገናኛ ለመስማት በመብቃታችኹ እንኳን ደስ አላችኹ!!

የእግዚአብሔር ቃል ከኹሉ በላይ ነው፤ ፍጥረታት በሙሉ የተፈጠሩትና ጸንተው የቆሙት በእግዚአብሔር ቃል ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ዘላለማዊ እንደ መኾኑ ሕያው ነው፤ ፍጡራንም በእርሱ ሕይወትነት ሕያዋን ኾነው ይኖራሉ፤ ዛሬም ኾነ ወደፊት ሰዎች ከፍርድ ነፃ ኾነው የዘለዓለምን ሕይወት የሚያገኙት ይህን ቃል በመመገብ ነው፤ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ የኾነ ሕይወት ሊኖር አይችልምና፡፡

ይህ እውነት የታወቀውና ሊታወቅ የሚችለው በእግዚአብሔር መገለጥ ብቻ ነው፤ የእግዚአብሔር መገለጥ በሦስት ነገሮች ታይቶአል፤ ይኸውም፡-

 1. እግዚአብሔር በፍጥረቱ አማካይነት ተገልጦአል፤
 2. በመረጣቸው ቅዱሳን ሰዎች አማካይነት ተገልጦአል፤
 3. ሰው ኾኖ በመገለጥ ራሱን ለዓለም ገልጦአል፡፡

ከዚህ አንጻር የክርስትና ሃይማኖት መሠረትና መነሻ የእግዚአብሔር መገለጥ እንጂ ፍልስፍና፣ ወይም ሌላ አመክንዮ አለመኾኑን እዚህ ላይ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ አኳያ የቤተ ክርስቲያን ቀዳሚና ዓቢይ ተልእኮ፣ በእርሱ የተገለጠውንና የማይለወጠውን ሕያው ቃል ለዓለም ሁሉ ማድረስ እንጂ በየጊዜው የሚለዋወጠው፣ በሕፀፅ የተሞላውና የሰዎች ቁሳዊ መላምት የኾነው ጥበበ ሰብእ አይደለም፤ በተለይም ኢትዮጵያ ሀገራችን፤

 • ቀደም ሲል በሕገ ልቡና (በሕገ ተፈጥሮ)
 • ቀጥሎም በሕገ ኦሪት (በቅዱሳን ነቢያት በኩል)
 • በኋላም በሕገ ወንጌል (በሥግው ቃል)

የኾነውን የእግዚአብሔር መገለጥ መሠረት አድርጋ ከብዙ ዘመናት በፊት አምልኮተ እግዚአብሔርን የተቀበለች ሀገር ናት፤ ይህ ሃይማኖታዊ እውነታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ለዘመናት ተጠብቆ የኖረ፣ ያለና የሚኖር እንደኾነ ከቃሉ በተጨማሪ ታሪካችንና ቅዱሱ ባህላችን በግልጽ እየመሰከሩት የሚገኝ እውነት ነው፡፡

ታላቋና ገናናዋ ቤተ ክርስቲያናችን ከብዙ ተጋድሎ ጋር ለረጅም ዘመናት ጠብቃ ያቆየችውን ነገረ ሃይማኖት ዛሬም ባለበት ብቻ ሳይኾን፤ በመላው ዓለም ለማስፋፋት የዘመኑ መሣሪያ መጠቀም ተገቢ እንደኾነ ጥርጥር የለውም፡፡

በመኾኑም በአኹኑ ጊዜ፣ ቤተ ክርስቲያናችን ያልደረሰችበት ክፍለ ዓለም የለምና በየትኛውም ክፍለ ዓለም የሚገኙ ልጆችዋ ኹሉ፣ በእርስዋ በኩል በቀጥታ የሚተላለፈውን የእግዚአብሔር ቃል በምልአት ያዳምጡና ይሰሙ ዘንድ እነኾ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአውሮፓ፣ በካናዳ፣ በሰሜን አሜሪካና በላቲን አሜሪካ ያሉትን ምእመናን ኹሉ ሊያዳርስ የሚችል፥ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ሥርጭት›› እውን አድርጋለች፡፡

ይህ የብዙኃን መገናኛ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሀብትና ንብረት፤ እንዲኹም፣ የቤተ ክርስቲያኗ ልዕልና መገለጫ እንደመኾኑ መጠን፣ ምእመናን ኹሉ ድጋፋቸውን በመስጠት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊያሳድጉት፣ ሊንከባከቡትና እንደ ዓይን ብሌን ሊጠብቁት ይገባል፤ ጣቢያው የምእመናን ድጋፍ ከታከለበት ኻያ ዐራት ሰዓት በሙሉ መጠቀም የሚያስችል ቻናል እንደኾነም ከወዲኹ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

በዚህ ሚዲያ ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን፣ ሥርዓተ አምልኮን፣ ደማቁን የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ስትማሩ ኢትዮጵያንም እዚያው ታገኙአታላችኹ፤ ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያ እና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአንድ ሣንቲም ኹለት ገጽታ ናቸውና፤ በአንድ ወንጭፍ እንደሚባለው ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስትማሩ ስለኢትዮጵያም የግድ ትማራላችኹ ማለት ነው፡፡

በመጨረሻም፤

ቤተ ክርስቲያናችን ከሌላው ሥራ ኹሉ ለሚዲያ አገልግሎት ቅድሚያ መስጠቷ፥ ዐዋቂውም ኾነ ወጣቱ ትውልድ፥ ስለሃይማኖቱ እና ስለታሪኩ፣ ስለሀገሩና ስለማንነቱ፣ ስለባህሉና ስለትውፊቱ ማወቅ የሚገባውን ዐውቆ የባለቤትነትና የታሪክ ጠባቂነት ሓላፊነትን እንዲሸከም በማድረግ፣ በዚህች ሀገር ሃይማኖታዊ ሰብእና ያለው ጤናማ ማኅብረሰብ ለመገንባት ታስቦ እንደኾነ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ስለኾነም ኹላችኁም ምእመናን ወምእመናት፣ በተለይም ወጣቶች፤ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያናችኹን በንቃት እንድትከታተሉ፤ ድጋፋችኹንም አጠናክራችኹ እንድትቀጥሉ አባታዊ መልእክታችንን ከአደራ ጭምር በእግዚአብሔር ስም እያስተላለፍን፤ ከዛሬ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብዙኃን መገናኛ ሥርጭት ሙከራ በይፋ የተጀመረ መኾኑን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር ይባርካችኹ፤ ይቀድሳችኹ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
አሜን!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Advertisements

3 thoughts on “ቅዱስ ፓትርያርኩ: ምእመናን፣ የቴሌቭዥን አገልግሎቱን እንዲደግፉና እንደ ዓይን ብሌን እንዲጠብቁት ጥሪ አቀረቡ

 1. Angile June 25, 2016 at 3:14 am Reply

  በዚህ ሚዲያ ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን፣ ሥርዓተ አምልኮን፣ ደማቁን የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ስትማሩ ኢትዮጵያንም እዚያው ታገኙአታላችኹ!

  ምእመናን፥ ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን፣ ሥርዓተ አምልኮን፣ ደማቁን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሲማሩ፣ “ኢትዮጵያንም እዚያው ታገኙአታላችኹ! ጣቢያው!

 2. Anonymous July 2, 2016 at 6:51 pm Reply

  That is great news! may God be with us

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: