ፓትርያርኩ: የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና፣ ማንነት፣ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚቀርቡትን የሰንበት ት/ቤቶች ጥያቄዎች መመለስ ግዴታ ነው፤ አሉ

 • ሀገር አቀፉ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ ባለ15 ነጥቦች መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ
 • ሀገር አቀፍ የፀረ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ፣ በአህጉረ ስብከት ቋሚ ጉባኤያት ተወካዮች ይቋቋማል
 • የተሐድሶ መናፍቃን የጥፋት ማስረጃዎች፣ ለቅዱስነታቸው እና ለቅዱስ ሲኖዶሱ ይቀርባሉ
eotc ssd 5th gen assembly participants with his holiness

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስና የካናዳ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ፣ ከ፭ኛው ሀገር አቀፍ ዓመታዊ ስብሰባ ተሳታፊዎች ጋር

በየዓመቱ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ሳምንት የሚካሔደው፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ፣ ከሰኔ 10 እስከ 12 ቀን 2008 ዓ.ም.፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አዳራሽ ሲያካሒድ የቆየውን ፭ኛውን ዓመታዊ ስብሰባውን፣ ባለ15 ነጥቦች የጋራ አቋም መግለጫ በማውጣት ዛሬ ማምሻውን አጠናቀቀ፡፡

ከ25 አህጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤያትና የሰንበት ት/ቤቶች ዋና ክፍሎች የተውጣጡ ልኡካን የተሳተፉበት ጉባኤው፣ በጋራ መግለጫው፡- የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ማኅበራትን፣ ፀረ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ለማስቆም፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አካላት አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስዱ፤ መጠነ ሰፊ ጥፋታቸውን የሚያሳዩና በሀገር አቀፉ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መረጃ ክፍል የተሰበሰቡ ማስረጃዎችንም፣ ለቅዱስ ፓትርያርኩና ለቅዱስ ሲኖዶስ ለማቅረብ እንዲፈቀድለትም ጠይቋል፡፡

በአገር ዓቀፉ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የተሰበሰቡትና የተደራጁት ማስረጃዎች፣ መሠረታቸው፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ከግንቦት 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ሲቀርቡ የቆዩ ናቸው፡፡ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን የማጋለጡንና የመከላከሉን ተጋድሎ፣ በብሔራዊ ደረጃ ለማጠናከር፣ ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች የፀረ ተሐድሶ ጉባኤ በየአህጉረ ስብከቱ ልኡካን የማቋቋም ሒደቱ እስኪጠናቀቅም፣ የአንድነቱ የመረጃ ክፍል ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አንድነት ጋር በመቀናጀት በጋራ መግለጫው የተመለከቱትን አስቸኳይ ተግባራት እየፈጸመ እንዲቆይ በዓመታዊ ስብሰባው ተወስኗል፡፡

በየአጥቢያውበተሳሳተ አመክንዮ ከመንግሥት የፍትሕ አካላት ጋር በመተባበር፣  በሰንበት ት/ቤቶች አባላት ላይ የሚደርሰው እስር፣ ወከባና እንግልት እንዲቆም በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እንዲሰጥም ሀገር አቀፉ ጉባኤ በጋራ የአቋም መግለጫው ተማፅኗል፡፡

የሙከራ ስርጭቱን እየጀመረ በሚገኘው የቤተ ክርስቲያናችን የ24 ሰዓት የቴሌቭዥን አገልግሎት፣ ከመምሪያው ጀምሮ እስከ አጥቢያ ያለው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በጋራ እንደሚሠራ ሀገር አቀፍ ጉባኤው በመግለጫው አረጋግጦ፣ በቃለ ዓዋዲው እና በ1986 ዓ.ም. ውስጠ ደንብ ላይ የተጠቀሰው የሰንበት ት/ቤቶች የዕድሜ ገደብ እንዲነሣም በድጋሚ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡

eotc ssd 5th gen assembly closing ceremony
በዓመታዊ ስብሰባው የመክፈቻና የመዝጊያ መርሐ ግብር የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ÷ ጥያቄዎቹ፣ የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና፣ ማንነት፣ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ፣ በመቆርቆር የቀረበ እስከኾነ ድረስ ተቀባይነት እንዳለውና ቤተ ክርስቲያንም ምላሽ የመስጠት ግዴታ እንዳለባት ተናግረዋል፡፡

ለአባቶቻችን ለቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታ እንደተነገራቸው፣ በዚኽ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ቀን  መንፈስ ቅዱስን ጸጋ ለማግኘት በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ እንጸናለን፤ ወጣቶችን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን ለሰንበት ት/ቤቶች የሰጠችውን ድርሻ ለማንም አልሰጠችም፤ ለእናንተ የማናደርገው ነገር የለም፤ እናንተም የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ ብቻ መስማት ይኖርባችኋል፤ በአቋም መግለጫችኹ ያቀረባችኹት ጥያቄ፣ ከእውነትና ከቤተ ክርስቲያን ፍቅር አንፃር በመቆርቆር ያቀረባችኹት ስለኾነ ቤተ ክርስቲያን ጥያቄአችኹን ተቀብላ የማስተናገድ ግዴታ አለባት፤ እኔም ጥያቄውን የማስፈጸም ግዴታ አለብኝ፤ ጥያቄአችኹን ተቀብለናል፤ አብረን እንወጣዋለን፤” ብለዋል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፡፡

በዓመታዊ ስብሰባው እንዲሳተፉ ከሚጠበቁት የ47 አህጉረ ስብከት የአንድነትና የሰንበት ት/ቤቶች ዋና ክፍሎች ልኡካን፣ ከ130 የማይበልጡ የ25ቱ አህጉረ ስብከት ተወካዮች ብቻ መገኘታቸው፣ ማደራጃ መምሪያው ጥሪውን ባስተላለፈበት መንገድ ላይ ጥያቄና ጥርጣሬ ፈጥሯል፡፡

ካለፉት ዓመታዊ ስብሰባዎች ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው፣ በተሳታፊ ቁጥሩ ብቻ ሳይኾን የታወቀውን የወትሮ ግለት/momentum/ ያጣ ነው፤ ይላሉ፣ ጥቂት የማይባሉ ተሳታፊዎች፡፡ በስብሰባው የተገኙት፣ መዋቅሩን ጠብቆ በሚደርሳቸው ጥሪ ሳይኾን በራሳቸው መንገድ ባገኙት መረጃ መኾኑን ጠቅሰው፣ የመምሪያው ዋና ሓላፊ፣ በመርሐ ግብሩ አመራር ላይ ለወሳኝ ጉዳዮች ትኩረት ከመስጠት አኳያ ይኹነኝ ብለው የሚፈጥሯቸውን ጫናዎችና ተንኮሎች በመኮነን መታረም እንደሚገባው አስጠንቅቀዋል፡፡

*               *               *

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ ፭ኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ የጋራ መግለጫ ዐበይት ነጥቦች፤

በመምሪያው ዘገባም ኾነ ከ25 አህጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤያትና የሰንበት ት/ቤቶች ዋና ክፍል በቀረቡ ሪፖርቶች፣ የሰንበት ት/ቤቶች የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማፋጠን እጅግ በርካታ ተግባራት እያከናወኑ ነው፡፡ ይኹንና፡-

 • በየአህጉረ ስብከቱ የመናፍቃንና የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖ
 • በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ እየደረሱ ያሉ የአስተዳደር በደሎች
 • የበጀት እና የመምህራን እጥረት
 • የመሰብሰቢያና የመማሪያ ቦታ አለመኖር
 • የአንዳንድ አህጉረ ስብከት ስፋትና ለትራንስፖርት አመቺ አለመኾን አገልግሎቱን እየተፈታተኑ ያሉ ዋና ዋና ችግሮች ኾነው ተመዝግበዋል፡፡

በሪፖርቶችም ኾነ በጥናታዊ ጽሑፎች የተጠቀሱትን ዋና ዋና ችግሮች በመለየት በተደረገ የጋራ ሰንበት ት/ቤቶች በጋራ የምንሠራቸውና የምንስማማባቸው የአቋም መግለጫዎች፡-

 • የሰንበት ት/ቤቶችን የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ(ከ2006 – 2010 ዓ.ም.)፣ በቀሩት ጊዜያት ለመፈጸምና ለማስፈጸም ቃል እንገባለን፤
 • የሰንበት ት/ቤቶችን የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ፣ የየአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያቱ ዕቅድ አካል እንዲኾንና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ መምሪያዎችም ከዕቅዳቸው ጋር እንዲያገናዝቡት እንዲደረግ እንጠይቃለን፤
 • በአገር ዓቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴና መጠነ ሰፊ ጥፋትን አስመልክቶ፣ በመረጃ ክፍል የተሰበሰቡና የተደራጁ ማስረጃዎችን በአገር ዓቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ለቅዱስነትዎና ለቅዱስ ሲኖዶስ እንድናቀርብ እንዲፈቀድልን እንጠይቃለን፤
 • “ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ” በሚል የወጣው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ማኅበራት የክሕደት መግለጫ፣ በሊቃውንት ጉባኤ ምላሽ እንዲሰጠው በአንድነት እንጠይቃለን፤
 • የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ማኅበራቱን ፀረ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ለማስቆም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አካላት አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን፤
 • በአንዳንድ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎች፣ በሰንበት ት/ቤቶች ላይ እየደረሱ እስር፣ እንግልትና ወከባ እንዲቆምልን በአጽንዖት እንጠይቃለን፤
 • የመንግሥት የፍትሕ አካላትም ከአጥፊዎች ጋር በመተባበር የሰንበት ት/ቤት አባላትን ከማሰርና ከማንገላታት እንዲታቀቡ እንዲደረግ በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል መመሪያ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን፤
 • በቃለ ዓዋዲው እና በ1986 ዓ.ም. በውስጠ ደንቡ ላይ የተጠቀሰው የሰንበት ት/ቤቶች የዕድሜ ገደብ እንዲነሣልን በድጋሚ እንጠይቃለን፤
 • ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚወክል የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ስርጭት በመጀመሩ፣ ከመምሪያው ጀምሮ እስከ አጥቢያ ያለው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በጋራ ለመሥራት ቃል እንገባለን፤
 • ተወካዮቻቸውን ያልላኩ ሰንበት ት/ቤቶች ተለይተው፣ ታውቀው በጠቅላይ ቤተ ክህነት የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰድባቸው እንጠይቃለን፤
 • የቤተ ክርስቲያናችንን ኹለንተናዊ ችግር ለመፍታት ከመንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን ጋር ተባብረን የምንሠራ መኾናችንን እንገልጻለን፡፡the patriarchate ssd 5th gen assemblyeotc ssd 5th gen assembly release1 eotc ssd 5th gen assembly release2 eotc ssd 5th gen assembly release3
Advertisements

2 thoughts on “ፓትርያርኩ: የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና፣ ማንነት፣ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚቀርቡትን የሰንበት ት/ቤቶች ጥያቄዎች መመለስ ግዴታ ነው፤ አሉ

 1. Anonymous June 20, 2016 at 5:37 am Reply

  ሰንበት ተማሪ በአግባቡ በእግዚአብሔር ቃል አልተቀረፀም ለዚህ ነው የሚያወሩት ሁሉ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ቃና የሌለው ለሦስት ቀናት ተሰብስበው ሲያወሩ አንድም ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ቃል መስፋፋት አላወሩም ይልቁኑ ተጨማሪ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለማሳደድ ነው አቋም ይዘው የተለያዩት

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: