ሀገር አቀፉ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፥ የፀረ ተሐድሶ ኑፋቄ ቋሚ ጉባኤ ያቋቁማል፤ በዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ጥቆማው በንቃት ይሳተፋል

፭ኛው ሀገር አቀፉ ዓመታዊ ስብሰባ የዛሬ ረፋድ ውሎ

በ፭ኛው ሀገር አቀፍ ዓመታዊ ስብሰባ፣ የዛሬ፣ እሑድ በዓለ ጰራቅሊጦስ ረፋድ ውሎ

ካለፈው ዓርብ፣ ሰኔ 10 ቀን ጀምሮ በመካሔድ ላይ የሚገኘው፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ፭ኛው ዓመታዊ ስብሰባ፣ ሀገር አቀፍ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ቋሚ ጉባኤ እንደሚያቋቁም ተጠቆመ፡፡

ከየአህጉረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ የክንውን ሪፖርቶች የቀረቡለት ዓመታዊ ስብሰባው፤ ከፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር ኮሚሽን በመጡ ባለሞያ እንዲኹም፤ በሉላዊነትና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አደጋዎች ዙሪያ በተሰጡ ገለጻዎች ላይ በስፋት ሲወያይ የቆየ ሲኾን፤ በአኹኑ ሰዓትም በመምሪያው መሪ ዕቅድና በቀጣዩ በጀት ዓመት ቁልፍ የትግበራ ጉዳዮች በመወያየት ላይ እንዳለ ተጠቅሷል፡፡

የጉባኤውን የትላንት አብዛኛውን ውሎ የያዘውና ለዛሬም ያደረው አጀንዳ፤ ለቤተ ክርስቲያን የህልውና ስጋት የኾነውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ የማጋለጥና የመከላከል ጉዳይ ነው፡፡ በዚኽ ረገድ የማደራጃ መምሪያው እንቅስቃሴ፣ በግለሰቦች ጥረት የተወሰነና የሚጠበቅበትን ያኽል እንዳልሠራ የተቸው ጉባኤው፣ “መምሪያው ወቅቱ የሚጠይቀውን አገልግሎት መስጠት አልቻለም፤” ብሏል፡፡

በመርሕ ደረጃ ከተወሰኑ ገለጻዎችና “የመዝሙርና የሥርዐተ ትምህርት ወጥነት” እየተባለ በየዓመቱ፣ በተደጋጋሚ ከሚቀርቡ የወረቀት ላይ ሪፖርቶች ባሻገር፣ ጉባኤው፥ በመሪ ዕቅዱ ገቢራዊ ክንውኖችና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይም እየተወያየና እየተከራከረ የጋራ አቋም ይዞ መሥራት እንዳለበት ልኡካኑ ተናግረዋል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት፣ በየአህጉረ ስብከቱ እየተቋቋመ ያለው የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ፤ በማደራጃ መምሪያው ደረጃም ተቋቁሞ፣ በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሚመራውን የጠቅላይ ጽ/ቤቱን የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ ማገዝ፤ በየአህጉረ ስብከቱ፣ የቋሚ ጉባኤያቱን ምሥረታ መከታተልና ከሰርጎ ገቦች የተጠበቁ መኾናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባው ተገልጧል፡፡

ሀገር አቀፉ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴና የመረጃ ልውውጡ፤ በዚኽ መልኩ፣ በማዕከል እየተቀናጀና የጠራ አቅጣጫ እየተሰጠበት ካልተሠራ ውጤታማ ለመኾን እንደሚያዳግት ተመልክቷል፡፡ በዚኽም መሠረት፣ ከ21 እስከ 25 አባላት የሚኖሩት፣ ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ በዓመታዊ ስብሰባው እንደሚቋቋም ተጠቁሟል፡፡

ይኸው ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ፡-

 • ከማደራጃ መምሪያውና ከሀገር አቀፉ አንድነት ሥራ አመራር፣ ተወካዮች ይኖሩታል
 • በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሚመራውን የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ቋሚ ጉባኤ እየደገፈ ይሠራል
 • በግለሰቦች ትጋት የተወሰነውን የመምሪያውን የፀረ ተሐድሶ ጥረት መዋቅራዊ ያደርጋል
 • የአህጉረ ስብከት አንድነት ጉባኤያትን፣ መረጃዎችና የእንቅስቃሴ አቅጣጫዎች ያቀናጃል
 • ከግንቦት 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ከአ/አበባ አንድነት ሲቀርቡ ለቆዩ መረጃዎች ምላሽ ያስገኛል
 • በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ፣ የሰ/ት/ቤቶችን ጥቆማና ምስክርነት የመስጠት ድርሻ ያጠናክራል

በዓመታዊ ጉባኤው፡-

 • የኑፋቄ ነክ ጉዳዮች፣ “መዋቅር ጠብቀው ይምጡ” መባሉ በከፍተኛ ደረጃ አወያይቷል
 • ስለተሐድሶ ኑፋቄ አደጋ፣ የዋና ሓላፊው የግልና የማኅበር አቋም አሻሚ ነው፤ ተብሏል
 • መምሪያው፥ ወቅቱ የሚጠይቀውን መሥራት አልቻለም በሚል በአፈጻጸሙ ተተችቷል
 • የሊቃውንት ጉባኤና የሕግ አገልግሎቱ፣ የፀረ ኑፋቄ ዝግጁነትና ምላሽ መጠናከር አለበት
 • በ24 ሰዓት ቴሌቭዥኑ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ሱታፌ በግልጽ እንዲታወቅ ጉባኤው ጠይቋል
 • የቃለ ዐዋዲው የ30 ዓመት የዕድሜ ገደብ፣ በማሻሻያው እንዲጤን በድጋሚ አስታውሷል

በማደራጃ መምሪያው፡-

 • 5ሺሕ መዝሙረ ማሕሌት መጽሐፍ ተሰራጭቶ፣ 10ሺሕ ለዳግም ስርጭት ተዘጋጅቷል
 • በድምፅ የተዘጋጀው የመዝሙረ ማሕሌት ሲዲ፣ ለየአህጉረ ስብከቱ በነፃ ይሰራጫል ተብሏል
 • ከ5ሺሕ የሕፃናት ሥርዐተ ትምህርት መመሪያ መጽሐፍ፣ የተሰራጨው 2ሺሕ አይሞላም
 • ድረ ገጹ ትክክለኛ መረጃን በማሰራጨት ወደር የማይገኝለት ሥራ ሠርቷል ተብሏል
 • በመስቀልና በጥምቀት ክብረ በዓላት፤ በፓትርያርኩ “እንኳን አደረስዎ” ተሳትፎ ተደርጓል
 • የበጀት እጥረትየማደራጃ መምሪያው ዋነኛ ችግር እንደኾነ በዋና ሓላፊው ተገልጿል፡፡

eotc ssd 5th gen assembly 001በ፭ኛው ሀገር አቀፍ አንድነት ጉባኤ ዓመታዊ ስብስባ ዝግጅት፡-

 • የተሳታፊዎች ቁጥር ከአምናው አንሷል፤ ጥሪዎች በወቅቱ አለመተላለፋቸው ቢጠቀስም…
 • በዋና ሓላፊው አግላይነት የተሰላቹ ወጣቶች፤ መምሪያውን ከማገዝ መራቃቸውን አሳይቷል
 • ዋና ሓላፊው አብዝተው ከጮኹበት“የበጀት እጥረት” ይልቅ “ምዝበራና ብክነት” ችግሮች ናቸው
 • የተደራጁ ሰንበት ት/ቤቶችና የአባሎቻቸው ቁጥር፣ በግምታዊ አኃዝ እንጂ በወጉ አይታወቅም
 • አህጉረ ስብከቱን፣ ቅኝት የሚደግፍበት አሠራር አለመኖሩ በዐቢይ ጉድለት ተቀምጧል
 • ዋና ሓላፊው፣ በተሐድሶ ኑፋቄ እውንነትና አደጋ ላይ አቋማቸውን ማስረገጥ ይኖርባቸዋል፡፡
Advertisements

One thought on “ሀገር አቀፉ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፥ የፀረ ተሐድሶ ኑፋቄ ቋሚ ጉባኤ ያቋቁማል፤ በዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ጥቆማው በንቃት ይሳተፋል

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: