፭ኛው ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ ተጀመረ፤ የመ/ር ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተ የ፳ ዓመት “ለውጥ የለሽ” አመራር ገደብ እንዲበጅለት ተጠይቋል

eotc ssd 5th gen assembly1

፭ኛው ሀገር አቀፉ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ በጸሎት በተጀመረበት ወቅት(ፎቶ: የሰንበት ት/ቤቴ ማስታወሻዎችና ሰንበት ት/ቤቴ)

በየዓመቱ፣ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ሳምንት የሚካሔደው፣ ሀገር አቀፉ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ፣ አምስተኛውን ዓመታዊ መደበኛ ስብስባውን፣ ዛሬ፣ ዓርብ፣ ሰኔ 10 ቀን 2008 ዓ.ም.፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የመምሪያ ሓላፊዎች በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ጀምሯል፡፡

ዓመታዊ ጉባኤው፤ ከስትራተጅያዊ ዕቅዱ አኳያ የበጀት ዘመኑን የቁልፍ ጉዳዮች ዕቅድ ክንውኖች፣ ከማደራጃ መምሪያውና ከየአህጉረ ስብከቱ በሚቀርቡ ሪፖርቶች ከማዳመጥና ከመገምገም ባሻገር፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዓበይት ወቅታዊ ጉዳዮች በኾኑት፡- የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ሤራ፤ የፀረ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይመክራል፤ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ የመዝሙርና የትምህርት አገልግሎት እንዲኹም የመረጃ ግንኙነት ወጥነት መሠረት የሚጣልበትም ነው፤ ተብሏል፡፡

የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ሓላፊዎችና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጨምሮ ከ350 ያላነሱ የ45 አህጉረ ስብከት አቀፍ አንድነት ጉባኤያት ልኡካን የሚሳተፉበት ይኸው ዓመታዊ ስብሰባ፤ እስከ መጪው እሑድ፣ በዓለ ጰራቅሊጦስ ይቆያል፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ደረጃ ዓመታዊ ስብሰባውን በአዘጋጀው፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የአምስት ዓመት (2005 – 2010 ዓ.ም.) መሪ ዕቅድ መሠረት፤ የመንበረ ፓትርያርክ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕፃናት፣ አዳጊዎችና ወጣቶች፤ በቤተ ክርስቲያን ዶግማና ሥርዓት የተኮተኮቱ፤ ሕግን የሚጠብቁና የሚያስጠብቁ፤ በየዘመናቸው ለክርስትና መከፈል የሚገባውን የመንፈሳዊ ተጋድሎ ዋጋ በመክፈል ከትውልድ ወደ ትውልድ ክርስትናን ከነሙሉ መገለጫዎቹ የሚያሸጋግሩ ኦርቶዶክሳውያንን የማፍራት ርእይ አለው፡፡

eotc ssd 5th gen summit

የሰንበት ት/ቤቶች፤ የነገዋ ቤተ ክርስቲያን አለኝታዎች

ቅዱስ ሲኖዶስ በ2005 ዓ.ም. ያጸደቀው ይኸው የማደራጃ መምሪያው ስትራተጅዊ ዕቅድ፣ በቁልፍ የትግበራ ዕቅዶቹ የተሻለ የማደራጀትና የማስተባበር አቅም እንደሚጠይቅ የሚናገሩ ወገኖች፣ መምሪያው ለዚኽ በሚያበቃ ኹለንተናዊ ቁመና ላይ አይገኝም፤ ይላሉ፡፡

በተለይም ከዘመኑ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች አስተሳሰብ፣ ሥነ ልቡና፣ አቅምና ኹኔታ አንፃር “ለውጥ የለሽ ነው” የሚሉትና በምዝበራ ቅሌቶች እንደተዘፈቀ የሚከሡት፣ ያለፉት ኻያ ዓመታት የመምሪያው ዋና ሓላፊ የመ/ር ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተ አመራር፣ በቅጡ ተገምግሞ ማስተካከያ ሊደረግበት እንደሚገባ፤ ይኸውም በዘንድሮው ሀገር አቀፍ ጉባኤ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አባላት በስምንት ገጾች የደረሰንንና በኃይለ ቃላት የተሞላውን አስተያየት ለጡመራ መድረኩ እንዲኾን ተቀናብሮ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፤

መ/ር ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተ፤ የሰንበት ት/ቤት ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ

መ/ር ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተ፤ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ

 • አቅም ማነስና በምግባር ዝቅጠት፣ ሊመሩን ቀርቶ ሊከተሉን የማይችሉተብለዋል፤
 • “ወጣቶቹ ካልተሰደቡ አናታችን ላይ ይወጣሉ፤ ፊት አትስጧቸው” ብለው ይናገራሉ፤
 • በአባቶች መካከል የሚፈጠረውን አለመግባባት በማጋጋል ወጣቱን ለአድማ ይቀሰቅሳሉ፤
 • ወደሚመጥናቸው ቦታ ይዛወሩ፤ የዋና ሓላፊነቱም የሥልጣን ዘመን ገደብ ይበጅለት

*          *          *

 • በመጽሔት ስርቆት የተጀመረው የዋና ሓላፊው ምዝበራ“ወደ መቶ ሺሕዎች አድጓል”
 • የመስቀልና የጥምቀት በዓላት በጀት፣ በወጣቱ ስም የዋና ሓላፊው መጠቀሚያ ኾነዋል
 • በሰንበት ት/ቤቶች መገልገያ ሽፋን፣ የነጋዴ ዕቃ እየላኩ ኮንትሮባንዳቸውን ያጧጡፋሉ
 • ለዘንድሮው ጉባኤ ዝግጅትም፣ ያለፕሮፎርማ ግዥ አናካሒድም በመባሉ ተበሳጭተዋል

*          *          *

 • የመምሪያውን የፎቶ ኮፒ ማሽን ዕቃዎችና ወረቀቶች በምሽት ወደግል ሱቃቸው ያግዛሉ
 • የቢሮው የፎቶ ኮፒ ማሽን፣ ኹሌም፣ ተበላሽቷል እየተባለ የግላቸው ግን ሲሠራ ይውላል
 • ከመምሪያው ይልቅ ለግላቸው በሚሠራው ተሽከርካሪ ጥገና የሥራ ማስኬጃው ባክኗል  
 • ም/ል ሓላፊውና ሠራተኞች፣ ምዝበራቸውን ሲቃወሟቸው በፓትርያርኩ ስም ያስፈራራሉ

*          *          *

 • “ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በምንም መልኩ እንዲጠናከሩ አይፈልጉም፤” የሚባሉት ዋና ሓላፊው፣ የሥልጣን ዕድሜያቸውን ያራዘሙት በሌሎች ትክሻ ነው፤
 • በቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ መማር ቢጀምሩም፣ ሌክቸሩን የሚረዱት በድምፅ እየቀረፁ በማስተርጎም ነው፤ ይህም እየቆየ ኀፍረት ኾኖባቸው “ያለሚጠት” ከኮሌጁ ተሰናብተዋል፤

 • “የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ካልተሰደቡ አናታችን ላይ ይወጣሉ፤ ፊት አትስጧቸው” በማለት፣ በተደጋጋሚ በመድረክ ወጣቶችን የሚያዋርድ በጣም አሳፋሪ ንግግር ያዘወትራሉ፤
 • አመራራቸውን ከመጥላት የተነሣ፣ በዋናነት በሚያስተባብሩት የቅዱስ ፓትርያርኩ፣ የእንኳን አደረስዎት ፕሮግራሞች ላይ የሚያገለግሉ መዘምራንን ለማግኘት እስከመቸገር ተደርሷል፤ 
 • የሥራ ማስኬጃ በጀቱን፣ “መኪና ላሠራበት” በሚል የማጭበርበርያ ስልት፣ ከጋራዥ ቤቱ ጋር በመመሳጠር ቢሮውን ባዶ አስቀርተውታል፤ በዚኽ፣ ምንም ግምገማ አለመደረጉም እንዲፈነጩ አድርጓቸዋል፤ 
 • በየዓመቱ ለመስቀል በዓል ከሚበጀተው ላይ ቢያንስ 80ሺሕ ብር፤ ከጥምቀት በዓል በጀት ቢያንስ 20ሺሕ ብር፤ ለመኪና ከሚበጀተው በጀት ላይ 25ሺሕ ያጭበረብራሉ፤ ከ2008 .. የመስቀል በዓል ብቻ ለግብዣ በሚል 14ሺሕ ብር በላይ አጭበርብረዋል፤ ስለ ግብዣው የመምሪያው ሓላፊዎችና የአዲስ አበባ አንድነት አመራሮች የሚያውቁት ነገር የለም፤

enqo theft

መምህር ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተ፣ በ2008 ዓ ም የጥምቀት ክብረ በዓል፤ የአዲስ አበባ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮችን ምሳ የጋበዝኩበት ነው፤ በማለት ለማወራረጃ ያቀረቡት የሐሰት ደረሰኝ ነው፤ በአንድ የምሳ ሰዓት ብቻ በግብዣ ስም፥ የ35 ኪሎ ሥጋ፣ የ100 ቢራ፣ የ14 ለሰላሳ፣ የ14 አክሱማዊት ወይንና የ3 ሮያል ቶኒክ ወጪ አደረግኹ በማለት 9ሺሕ 626 ከ04 ሣንቲም አወራርደዋል። ይህ ኹሉ ሲኾን አንድም የመምሪያዉ ሠራተኛ ጉዳዩን አያውቀውም፤ ተጋበዙ የተባሉት የአ/አበባ አመራሮችም አያውቁትም! Enqo theft3

ዋና ሓላፊው መ/ር ዕንቊ ባሕርይ፣ በአ/አበባ ሀ/ስብከት አንድነት አመራሮች ግብዣ ስም ለግል ጥቅማቸው ያዋሉትንና በተሳሳተ ደረሰኝ ያቀረቡትን የጥምቀት ክብረ በዓል ወጪ፤ የጠቅ/ቤተ ክህነት ሒሳብና በጀት ክፍልን እንዲኹም ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን በማሳሳት እንዲወራረድ አድርገዋል፡፡

አሠራሩን በመቃወም፣ ገንዘቡ ወደ ሒሳብ ክፍሉ እንዲመለስ በወቅቱ የጠየቁትን የመምሪያውን ምክትል ሓላፊ መ/ር ይቅር ባይ እንዳለን ከቦታቸው እንዲነሡ  ለማስነሣት ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው ተገልጧል፡፡

ከልምድ አንፃር የሀገር አቀፍ ጉባኤው ጠቅላላ ተስተናጋጆች እንኳ በአንድ ሙሉ ቀን ከዚያ ባነሰ መጠን እየተስተናገዱ፣ የአዲስ አበባ አመራሮች በአንድ ምሳ ግብዣ 35 ኪሎ ሥጋ በሉ መባሉ አሥቂኝ ነው፡፡ እውነታው ግን፣ ዋና ሓላፊው ክፍያውን የባለቤታቸው ዘመድ ናቸው ለተባሉት ሉካንዳ ከፈጸሙ በኋላ፣ በየዕለቱ እየሔዱ በኪሎና በካሳ እየቀናነሱ ሥጋውንም ቢራውንም መረከባቸው ነው።

ይህ አሳፋሪ ድርጊት በዚህ ብቻ ያበቃ አልነበረም። ለዘንድሮ ሀገር አቀፍ ጉባኤ የተበጀተውን ገንዘብ ለማጭበርበር ቢሞክሩም፣ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የተሠየመው ኮሚቴ፣ “በፕሮፎርማ ያልተደገፈ ግዥ አናካሒድም” በማለቱ ምክንያት ፀጉራቸውን እስከ መንጨት ደርሰዋል፤ የመመሪያው የበታች ሠራተኞችም “ባንተ ሌብነት አንገባም” በማለት ሕገ ወጥ ትእዛዛቸውን ወጊድ ስላሏቸው ለትልቅ ውርደት ዳርጓቸዋል።


 • የነጋዴዎችን ንዋያተ ቅድሳት“የሰንበት /ቤቶች መገልገያ ነው” እያሉ ዶላር እየተቀበሉ፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሳያውቁ በቀጥታ ለኤርፖርት ጉምሩክ ደብዳቤ እየጻፉ ኮንትሮባንዳቸውን ያጧጡፋሉ፤   
 • በኮፒራይት ጉዳይ በፍርድ ቤት የተያዘው ክሥ ለቀጣዩ ዓመት ጥቅምት መቀጠሩ ቅር ያላቸው ቢመስልም፣ ኔ ወዳጅ ያደረግኋቸዉ ቅዱስ ፓትርያርኩ ክሡ እስኪፈጸም ማንም እንዳይነካኝ ቃል ገብተውልኛል በማለት ሲናገሩ ተደምጠዋል፤ 
 • በቀድሞውም ይኹን በወቅቱ ፓትርያርክና በብፁዓን አባቶች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር፤“አቋማችንን ከፓትርያርኩ ጋር ማድረግ አለብን” እያሉ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶችን ለአድማ ይቀሰቅሳሉ፤ “በአባቶቻችን መሀል አንገባም” ብለው የሚቃወሟቸውን ወጣቶች የመምሪያውን እገዛ እንዳያገኙ ያደርጋሉ፤ የማዳራጃ መምሪያውን ድረ ገጽ ለግላቸው በመቆጣጣር፣ “እያንዳንዳሽ እጽፍብሻለኹ!” በማለትም ያስፈራሩበታል፤ 
 • ለአብነት ያኽል፡- ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ላይ፣ የሥራ ዕንቅፋቶች እንዲፈጠሩ ከአንዳንድ አማሳኝ አለቆች ጋር መክረዋል፤  የቀድሞው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ “የማኅበረ ቅዱሳን አባል ናቸው፤ የቅዱስነትዎን ትእዛዝ አይቀበሉም፤” በማለት አባቶች እንዲቃቃሩ ሠርተዋል፤ ወጣቶችን ሰብስበው ቅዱስነታቸው ዘንድ በመሔድ መቃቃሩን ለማጋጋልና በከንቱ ለመወደድም ሞክረዋል፤ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በሥራ አስኪያጅነት እንዳይመረጡም ቀስቅሰዋል፤ በ2001 ዓ.ም. ብፁዓን አባቶችን ከደበደበው ኮሚቴም ጋር አብረው ነበሩ፤
 • በ2007 ዓ ም በተካሔደው 4ኛው ታላቁ ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ ወቅት፣ የጉባኤው ተሳታፊዎች ከአዳራሽ ወጥተው ለፓትርያርኩ የመብት ጥያቄ እንዲያቀርቡ ከተስማሙ በኋላ ፖሊሶች ወደ ግቢ ሲገቡ፣ የሰንበት ተማሪዎቹ ከቁጥጥሬ ውጭ ናቸው፤ ይለቀሙ፤ በማለት በዝማሬ ብቻ ለጥያቄ ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ የተሰለፉ ወጣቶችን ለማሳሰር ሠርተዋል፤ ፖሊሶቹ ነገሩን በመረዳታቸውና በእነዶ/ር ያየህ ነጋሽ ከፍተኛ ጥረት ጉዳዩ መሥመር በመያዙ ግን አልተሳካላቸውም፤
 • የዋና ሓላፊው አመራር ካልተስተካከለ በማንኛውም በዓል ላይ ተገኝተን ለማገልገል እንቸገራለን፤ ያልተማረ አይመራንም፤ በስማችን የተጭበረበረው የገንዘብ ምዝበራም ይጣራልን! ትክሻችን ዝሏል፤ ከዚኸ በኋላ / ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተን አንሸከምም፤ ወረብ የሚያስጠኑት እንደኾነ በየአጥቢያዎቻችን አሉ፤ እነርሱ ይበቁናል፤ ማኔጅመንቱ ለተማረ አካል ይሰጥልን፤
 • የመምርያው ሓላፊዎች ሹመት እንደ ብፁዓን ዋና ሥራ አስኪያጆችየአገልግሎት ዘመን ገደብ ይኑረው፤ የመ/ ዕንቊ ባሕርይ 20 ዓመት ለውጥ የለሽ አመራር  ይበቃናል። ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፥ እንደ እኒኽ ላሉት ዝገቶች የሚመጥናቸውን ቦታ ካልሰጣቸው፣ ራሱ ወጣቱ መጥረጉ እንደማይቀር ይህ መልእክታችን ቀይ መብራት እንደኾነ ኹሉም እንዲረዳው እንፈልጋለን፡፡
Advertisements

3 thoughts on “፭ኛው ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ ተጀመረ፤ የመ/ር ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተ የ፳ ዓመት “ለውጥ የለሽ” አመራር ገደብ እንዲበጅለት ተጠይቋል

 1. Gebereamlak June 17, 2016 at 11:19 am Reply

  የቤ/ክርስቲያን ነገርማ ሆነ ተብሎ የተዘረጋ በቤተክርስቲያን ባልሆኑ ሰዎች መያዙ በግልፅ እየታየ እና እየጎላ የመጣ እዉነታ ነዉ፡፡
  35 ኪግ ስጋ …… አሁን አሁን በፆም ጭምር የስጋ ደረሰኝ በየአድባራቱ እየመጣ ነዉ፡፡
  መላዉ ክርስቲያን እነዚህን ሰዋች ለይቶ ከቤቱ ማስወጣት ይጠበቅብናል፡፡

 2. Tourist Dilla June 19, 2016 at 1:23 am Reply

  ፅሁፉ ደካማ ጎን ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑ ተአማኒነቱን አሳጥቶታል።
  ይህን ያህል አመት በመምሪያ ሀላፊነት ያገለገሉ ሰው ምንም ጠንካራ ጎን የላቸውም፤ምንም የሰሩት ስራ የለም ተብሎ መቅረቡ አሰልቺ ብቻ ሳይሆን የተለመደው ድክመታችን “ስናደንቅ መላክ” “ስናወርድ ሰይጣን” ከማሳየት ያለፈ ትርጉም አልሰጠኝም።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: