የቅ/ላሊበላ ቤተ ሩፋኤል እና ቤተ ገብርኤል አብያተ መቃድስ: በ15 ሚ. ብር ወጪ ተጠገኑ

conservation and consolidation of Lalibela project111

በከፍተኛ ባለሞያዎችና በላቀ ቴክኖሎጂ ጥገና የተደረገላቸው ቤተ ሩፋኤልና ቤተ ገብርኤል

  • ዩኔስኮ፣ የዓለም ቅርስ ፈንድና የአሜሪካ መንግሥት በገንዘብና በሞያ ደግፈዋል
  • ቤተ ክርስቲያን፥ ከጸሎት እና ጥብቅ ክትትል ጋር በባለቤትነት ተሳትፋለች
  • ለይምርሐነ ክርስቶስ ጥገና የ150 ሺሕ ዶላር የጥናት ስምምነት ተፈርሟል
  • ደብሩ በአ/አበባ ሕንፃ ለማስገንባትና አስጎብኚ ቢሮ ለመክፈት ዐቅዷል

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፮ ቁጥር ፰፻፶፮፤ ቅዳሜ ሰኔ ፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)

በዩኔስኮ የዓለም አስደናቂ ቅርሶች የተመዘገቡትና የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አካል የኾኑት የቤተ ሩፋኤል እና ቤተ ገብርኤል አብያተ መቃድስ፤ በረጅም ጊዜ አገልግሎት እና በተፈጥሮ በደረሰባቸው የመሠንጠቅና የማፍሰስ ጉዳት የተነሣ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ የነበሩ ሲኾን፤ በ15 ሚሊዮን ብር ወጪ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታገዘ ውጤታማ ጥገና እንደተደረገላቸው ተገለጸ፡፡

ከዩኔስኮ፣ ከዓለም ቅርስ ፈንድ(World Monument Fund) እና ከአሜሪካ መንግሥት(American Ambassador’s Fund) በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተካሔደውን የጥገና ፕሮጀክት በሓላፊነት ያሠራው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የቅርስ ጥበቃ መምሪያዋና በደብሩ አስተዳደር በኩል፤ ከፕሮጀክቱ ጥናት እስከ ፍጻሜው ድረስ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በባለቤትነት መሳተፏ ታውቋል፡፡

አምስት ዓመት በወሰደው የፕሮጀክቱ ጥናት መሠረት፣ ኦልሚ ኦሊንዶ የተባለ አገር በቀል ደረጃ አንድ ኮንትራክተር የአብያተ መቃድሱን ጥገና ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሲያካሔድ የቆየ ሲኾን፤ የፌደራል ሳይንቲፊክ ኮሚቴ ያስተባበራቸው ኢትዮጵያውያን የሥነ ሕንፃ እና የሥነ ምድር ባለሞያዎች ከታዋቂ የእንግሊዝና የጣሊያን ጠበብት ጋር መሳተፋቸው ተጠቅሷል፡፡

የውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን አካባቢ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያቀፈ ኮሚቴም፣ ለፕሮጀክቱ መሳካት የበኩሉን ድርሻ እንደተወጣና፤ የደብሩ አስተዳደርና ማኅበረ ካህናት ጸሎትም እገዛ እንዳደረገ፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ በስፍራው በተካሔደ የምረቃና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ መርሐ ግብር ላይ ተገልጿል፡፡

ዓለም አቀፍ ቅርሱን ከማዳንና ለትውልድ ከማሸጋገር አንፃር በጥገናው ከፍተኛ ሥራ መሠራቱ በተገለጸበት በዚኹ መርሐ ግብር፤ በዩኔስኮ የአፍሪቃ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ኢ.አልፋኢ ራይት፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሺያ ሃስላች፣ የፌደራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ከፍተኛ ሓላፊዎች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም መለሰ፣ የአማራ ክልል የሥራ ሓላፊዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲኹም በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

Complition of the conservation and consolidation project

የጠቅ/ጽ/ቤት ም/ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ መልእክት ሲያስተላልፉ

በዓለም ቅርስነት የሰፈሩት የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት፣ ከ800 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩና ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍለው የተሠሩ 11 ውቅር አብያተ መቃድስ ያሉት ሲኾን፤ እነርሱም በሦስት ምድብ የተከፈሉ ናቸው፡፡ ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ሚካኤል፣ ቤተ መስቀል፣ ቤተ ጎልጎታ(ደብረ ሲና) እና ቤተ ደናግል ምድብ አንድ፤ ቤተ ዐማኑኤል፣ ቤተ መርቆሬዎስ፣ ቤተ ገብርኤል- ሩፋኤል እና ቤተ አባ ሊባኖስ ምድብ ኹለት፤ ከኹለቱ ምድቦች ፈንጠር ብሎ የሚገኘው ቤተ ጊዮርጊስ ደግሞ ምድብ ሦስት በመባል ይከፈላሉ፡፡

ከዐሥራ አንዱ ውቅር አብያተ መቃድስ፣ ቤተ መድኃኔዓለም በግዙፍነቱ፤ ቤተ ዐማኑኤል እና ቤተ ማርያም ባለደርብነታቸው(በፎቅነታቸው)፤ ቤተ አባ ሊባኖስ ከዋናው አለት ጋር የተያያዘ በመኾኑ፤ ቤተ ጊዮርጊስ በመስቀል ቅርፅ በመሠራቱና ረቅቂ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የተከወነበት በመኾኑ የየራሳቸው ልዩ ባሕርይና መስሕብ አላቸው፡፡ የስፍራውን የቱሪስት ፍሰት ያጠናክራል የተባለ አስጎብኚ ቢሮ በአዲስ አበባ ለመክፈትና ሕንፃም ለማስገንባት የደብሩ አስተዳደር መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡

የይምርሐነ ክርስቶስ ደብር ቤተ መቅደስ

የይምርሐነ ክርስቶስ ደብር ቤተ መቅደስ

በተያያዘ ዜና፣ የአብያተ መቃድሱን ጥገና በቴክኒክና በገንዘብ የደገፈው የዓለም ቅርስ ፈንድ፣ ከላሊበላ የ5 ሰዓት የእግር መንገድ ርቀት በተመሳሳይ ጉዳት ላይ ለሚገኘው የይምርሐነ ክርስቶስ ደብር ኪነ ሕንፃ የቅድመ ጥገና ጥናት፤ 150 ሺሕ ዶላር መለገሡንና ስምምነቱም፣ በፈንዱ የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ስቴፈን ባትልና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መካከል ከኹለት ወራት በፊት በመንበረ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት መፈረሙ ተገልጿል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: