የባንኮ ዲሮማው ባለ9 ፎቅ የገበያ ማዕከል: በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተመረቀ፤ “ትንሣኤ ሕንፃ” ተብሏል፤ ብር 17 ሚልዮን ዓመታዊ ገቢ ያስገኛል

 

Banko de Roma new bld complex inagurationbanko de roma bld inaguration

የመንበረ ፓትርያርኩ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ከ122 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያሠራውና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ “ትንሣኤ ሕንፃ” ተብሎ የተሠየመው የባንኮ ዲሮማ ግቢው ሕንፃ(ፎቶ: አ/አ ሀ/ስብከት)


 • ከ42 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅ/ጽ/ቤቱ ያስገነባው ሕንፃ፣ ዐዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው
 • ባሉን ክፍትና በመልሶ ማልማት በሚሰጡን ትክ ቦታዎች ለመገንባት አጋዥ ተሞክሮ ተገኝቷል
 • የገቢው 70 በመቶ ለአገልግሎት ሲውል፣ 30 በመቶ ለቀጣይ ልማት በዝግ ሒሳብ ይቀመጣል
 • ባቢሎናዊ መንፈስ፣ ወኔ ገዳይ አሉባልታ፣ የወንዝ ቆጠራና የጥሎ ማለፍ አባዜ መሰናክል ነበሩ
 • በየ3 ዓመቱ የሚሾሙ ብፁዓን አባቶች፣ ቢያንስ አንድ ሕንፃ ቢሠሩ የሚል ሐሳብ ተጠቁሟል፡፡

*          *          *

 • የሕንፃው ገቢ ሌሎች ሕንፃዎችን እንደሚወልድና ቀጣይ ልማት እንደምናካሒድ ተስፋ አለኝ፡፡

/ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/

 • ሞራላዊ ጥንካሬ ባይኖር፣ ሕንፃው ቆሞ መተረቻ በኾን ነበር፤ በብዙ ወጀብ ውስጥ ተጠናቋል፡፡

/ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ /

 • አባቶች ያወረሱንን ቤቶች እያስተዳደርን ነው፤ አኹን በራሳችን በጀት ገንብተናል፤ እንቀጥላለን!!

/ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፤ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስና የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የበላይ ሓላፊ/

 • ቅ/ሲኖዶስ፣ ሕንፃውን የሚንከባከብ የምሕንድስና ባለሞያዎች ዘርፍ እንደሚሠይም እንጠብቃለን፡፡

/አቶ ተስፋዬ ውብሸት፤ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ/

*          *          *

 • እስከ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ፕትርክና የተሠሩ 626 ቤቶችንና ሕንፃዎችን እያስተዳደርን ነው
 • ከ280 በላይ ቤቶችና ታላላቅ ሕንፃዎች ገና ባለመመለሳቸው ጥረቱ እና ሒደቱ እንደቀጠለ ነው
 • በፌዴሬሽንና በተወካዮች ም/ቤቶች፣ በኦሮሚያ ሲቪል ሰርቪስና በፊንፊኔ ሆቴል ካሳና ቦታ ተገኘ
 • የፍልውኃ ሆቴልና የኢሕአዴግ ጽ/ቤት ሕንፃ ያልተጠና “ግምት”፣ የሚገባንን ጥቅም አሳጥቶናል
 • በተመላሽ ቤቶች ርክክብ ግድፈት የቀሩብን ይዞታዎች አሉ፤ አስመላሽ አባላቱ ጥንቃቄ ያድርጉ!

*          *          *

ከግማሽ ምእት ዓመታት ፍፃሜ በኋላ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዕውቅና ለንግዳዊ ዓላማ የተሠራው ባለዘጠኝ ፎቅ የቤተ ክርስቲያናችን ኹለገብ ሕንፃ፣ ትላንት፣ ግንቦት 27 ቀን 2008 ዓ.ም.፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አባላት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከ22 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋርና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወካይ በተገኙበት ተባርኮ ተመረቀ፡፡

ሕንፃው፣ ከቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትና ከኹለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ክህነት በኋላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ መገንባቱ፣ ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን የሥራ ርምጃ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንደ መክፈት የሚቆጠርና የምሥራች የሚያሰኝ እንደኾነ ተገልጿል፡፡

በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ እና በቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አቅራቢነትና በቅዱስነታቸው አጽዳቂነት፣ “ትንሣኤ ሕንፃ” ተብሎ መሠየሙን ፓትርያርኩ በምረቃው ወቅት አስታውቀዋል፡፡

His Holiness Abune Mathias the 1st
ቀደምት አባቶቻችን፣ ቤተ ክርስቲያናችን፣ በገቢ ምንጭና በአመራር ራሷን እንድትችል በማሰብ ሠርተው ያስረከቡን ሕንፃዎችና ቤቶች፣ ቅርሶቻችንንና ዕሴቶቻችን ከመኾናቸውም በላይ ለቤተ ክርስቲያን ህልውና መጠናከር ለምናደርገው ጥረት ስለሚረዱን በከፍተኛ ጥንቃቄና ክብካቤ እንዲያዙ ያሳሰቡት ፓትርያርኩ፤ የአባቶችን አሠረ ጽድቅ በመከተል የቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታዎች በአግባቡ ተከብረውና ተጠብቀው እንደ ባንኮ ዲሮማው ያሉ ተጨማሪ ሕንፃዎች እንዲሠሩባቸው መትጋትና መከታተል የኹላችንም በይበልጥም ደግሞ፣ የድርጅቱ ከፍተኛ ሓላፊነት መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡

“ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ሕንፃ ለሃይማኖታችን ዕድገትና ጥበቃ፣ ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያና ለበጎ አድራጐት እንዲኾን እመኛለኹ፡፡ ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ህልውና የማይከፍሉት መሥዋዕትነት ስለሌለና ባንኮቻችን ምእመናን በመኾናቸው በማስተባበር እና ሕንፃው በሚያስገባው ገቢ ሌሎች ሕንፃዎችን እንደሚወልድ፣ ባዶ ይዞታዎቻችንም ላይ እንደሚበዛ ተስፋ አድርጋለኹ፤” ብለዋል ቅዱስነታቸው፡፡ በወርኃ ጥቅምት 2005 ዓ.ም. ውሳኔው፣ ግንባታው እንዲካሔድ ከፈቀደው ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ሓላፊዎችና ሥራውን እየተከታተሉ ለፍፃሜ ያበቁትን የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት አመራሮች እንዲኹም የግንባታ ተቋራጩንና ተቆጣጣሪውን መሐንዲስ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አመስግነዋቸዋል፡፡

በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ፣ ቸርችል ጎዳና ዋና መንገድ፣ የቀድሞው ባንኮ ዲሮማ ቅጽር ውስጥ የሚገኘው ሕንፃው፣ በ1631 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ያረፈ ሲኾን፣ ወለሉንና ከወለል በታች ያሉትን ሦስት ዕርከኖች ሳይጨምር ዘጠኝ ፎቆች ያሉት(2B+G+9)፣ ዘመኑን የዋጀና ዘመኑን የሚመስል የንግድ ሕንፃ በመኾኑ በታሪክ ምዕራፍ ራሱን የቻለ ቦታ እንደሚኖረው ተዘግቧል፡፡

የመንበረ ፓትርያርኩን ሕንፃዎች በመሥራት የሚታወቀው ዛምራ ኮንስትራክሽን የሥራው ተቋራጭ ሲኾን፣ አፍሪ ኮንሰልት ደግሞ አማካሪ ድርጅቱ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ የሕንፃ ተቋራጩ የግንባታ ፕሮጀክቱን፣ በሐምሌ ወር 2005 ዓ.ም. ሲረከብ ሥራውን በ730 ቀናት ለማጠናቀቅ ውል ቢፈጽምም፣ በአሠሪው ድርጅት ጥያቄ ተጨማሪ ሥራዎች በመታከላቸው፣ በፓርቲሽን ሥራና ጥራት ያላቸውን ዕቃዎች ለማስመጣት ሲባል እስከ አኹን ሊቆይ መቻሉን የፕሮጀክት ሓላፊው ተናግረዋል፡፡

የዋናው ሕንፃ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት የአካባቢውን ሕንፃዎች ደኅንነት ለመጠበቅና መሠረታቸው እንዳይናጋ የተካሔደው የማጠናከርያ ግንባታ ብቻ ዐሥራ አራት ወራት መውሰዱን ሓላፊው አስታውሰው፣ ዋናው ሕንፃ በኹለት ዓመት ውስጥ በከፍተኛ የጥራት ደረጃ መገንባቱን አስረድተዋል፡፡ በወጪውም በኩል፣ አስቀድሞ ከታሰበው ብር 218‚636,061.23 እስከ አኹን የተከፈለው ከብር 122 ሚሊዮን ያልበለጠ በመኾኑ ከተገመተው ባነሰ ክፍያ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ነው የተጠቆመው፡፡

የሕንፃው ጽዳት በኹለት ወራት ውስጥ ተጠናቆ በቅርቡ ለቢሮ፣ ለሬስቶራንት፣ ለካፊቴሪያዎችና ለሱቆች…ወዘተ አገልግሎት ዝግጁ ሲኾን፤ በዓመት 17 ሚሊዮን ብር ገቢ ለቤተ ክርስቲያን ሊያስገኝ እንደሚችል የድርጅቱ ጥናት ያሳያል፡፡ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት፣ የገቢው 70 በመቶ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ ሲውል፤ ቀሪው 30 በመቶ ለቀጣይ ልማቶች በዝግ ሒሳብ ተቀማጭ እንደሚኾን ገልጸዋል፡፡

የመሠረት ድንጋይ በተጣለበት ወቅት፣ “ቦታው፥ የመኪና ፓርኪንግ ነው፤” በሚል ልማቱ ያልገባቸው ባለድርሻ አካላት ነን ባዮች፣ ግንባታው ጨርሶ እንዳይጀመር፣ የቀድሞውን ፓትርያርክ በግል ፕረሶች ሞግተው እንደነበር፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመልእክታቸው አስፍረዋል፡፡ለሕንፃው ዘላቂ አገልግሎት ወቅታዊ ክብካቤ አስፈላጊ በመኾኑ፣ የተሟሉ ባለሞያዎች ያሉት የምሕንድስና ዘርፍ በቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲሠየም የጠየቁት ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ፣ “የቤተ ክርስቲያናችንን አደራ ከግቡ ለማድረስና የአባቶቻችንን የልማት ውርስ አጠናክረን ለመቀጠል ቁርጠኛ መኾናችንን ለወዳጅም ለጠላትም ለማረጋገጥ እንወዳለን፤” ብለዋል፡፡

የዚኽ ዘመናዊ ሕንፃ ለውጤት መብቃት፣ ቤተ ክርስቲያናችን ባሏት ክፍት ይዞታዎቿም ኾነ መንግሥት ለመልሶ ማልማት ብሎ ባፈረሳቸው ቤቶች ምትክ በሚሰጣቸው ቦታዎች ለምታካሒዳቸው አዲስ ግንባታዎች በቂ ተሞክሮ እንደሚያስገኝላት ታምኖበታል፡፡ በርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መልካም አጋጣሚ በተከናወነው የሕንፃው ምረቃው ላይ የተገኙትን የአህጉረ ስብከት መሪዎች በማነሣሣት በኩልም አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተመልክቷል፡፡

His Grace Abune Samuel
እስከ አኹን ቤተ ክርስቲያን ስታከናውን የቆየችው አባቶች ያወረሱንን ቤቶች ማስተዳደር ብቻ እንደነበር የገለጹት የድርጅቱ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ “በአኹኑ ጊዜ ግን ቤቶችንና ሕንፃዎችን ከማስተዳደር ጎን ለጎን ግንባታዎችን እያከናወንን እንገኛለን፤ ዛሬ የተመረቀው ሕንፃም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና በራሳችን የገቢ በጀት የተገነባ ሲኾን፤ ወደፊትም ሰፊ ጥናት እያደረግን በቅዱስ ሲኖዶሳችን ውሳኔ ወደተሻለ እንቅስቃሴ እንገባለን ብለን እናምናለን፤” ሲሉ ልማቱ ከይዞታዎቻችን ባሻገር ከመንግሥት ጋር በሚደረግ ውይይት በምናገኛቸው ሰፋፊ ቦታዎችም ላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ፡፡

በድርጅቱ ሓላፊዎች እንደተገለጸው፣ በቀጣይ፥ በአራዳ ክፍለ ከተማ የቀድሞ ወረዳ 12 ቀበሌ 16 በሚገኘው ጦሳ ሬስቶራንትና ተጓዳኝ በኾኑ አራት ይዞታዎቻችን ላይ ቤተ ክርስቲያናችን መልሶ ማልማት እንድታካሒድ፤ እንዲኹም፣ በከተማው የቀላል ባቡር ዝርጋታ ሳቢያ በደጃች ውቤ በመልሶ ማልማት ለተነሣብንና በባሻ ወልዴ ችሎት በምትክ በተሰጠን አንደኛ ደረጃ 750 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ግንባታ ለማካሔድ በአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ከሊዝ ነፃ በተፈቀደው መሠረት፤ የቢዝነስ ሥራ አዋጭነት ለማስጠናት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት የአንድ ሚሊዮን ብር ወጪ አጽድቋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ፣ ለአፍሪቃ ኅብረት ጽ/ቤት የጸጥታ ጥበቃ መኖርያ በተወሰደው የርእሰ ገዳማት ወአድባራት አኵስም ጽዮን ቦታ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ጎሮ ሳይት እና በሲ.ኤም.ሲ በተሰጠን 800 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ምትክ ቦታ ኹለት ዘመናዊ የመኖርያ አፓርታማዎችን ለመሥራት መታቀዱ ተጠቁሟል፡፡ በምረቃ ላይ ተገኝተው የሕንፃ ሥራውን ያደነቁት የከተማው አስተዳደር ተወካይ አቶ ኤፍሬም፣ “ለወደፊትም መንግሥት ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፤” እንዳሉ ተዘግቧል፡፡

በሕንፃ ሥራው ወቅት ከአማካሪ ድርጅቱ በተጨማሪ የግንባታ ጥራቱንና የክፍያውን ትክክለኛነት በማረጋገጥ የቁጥጥር ድጋፍ ያደረጉ አራት ከፍተኛ ባለሞያዎች(ኢንጅነር ግርማ አበበ፣ ኢንጅነር ታደሰ ግርማይ፣ ኢንጅነር ዳናት ማርሥሩ እና አርክቴክት ፍቅረ ሥላሴ ካሣሁን) ስለ ትሩፋት አገልግሎታቸው ከቅዱስነታቸው እጅ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

His Grace Abune Mathewos
የተደራጀ አመራርና የሥራ ፍላጎት እስካለ ድረስ በአጭር ጊዜ ትልቅ ውጤት እንደሚያስገኝ በግንባታ ፕሮጀክቱ የታየ ቢኾንም፥ የገንዘብ እጥረት፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱን የከበበውሞራልና ወኔ ገዳይ አሉባልታ፣ በአስተዳደሩ አካባቢ የሚውለበለበውና ሥር እየሰደደ የመጣው ከላይ እስከ ታች የወረደ የወንዝ ቆጠራ እና የጥሎ ማለፍ አባዜ መሰናክሎቹ እንደነበሩ ተሰናባቹ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ አውስተዋል፡፡

“ከብዙ ዝግመት በኋላ ባጀት ተበጅቶ ሕጋዊ በኾነ የሰነድ ሽያጭ ጨረታ አሸናፊው ታውቆ ሥራው ቢጀመርም፣ በውስጡ የሚውለበለቡት አሉባልታዎች የሞራልና የወኔ ጥንካሬ ባይኖር ኖሮ ሕንፃው ቆሞ፣ ይኼ ተጀምሮ የቆመው ሕንፃ የእነማን ነው? እየተባለ መተረቻና መዘባበቻ በኾን ነበር፤” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ የሕንፃው ሥራ ሊጠናቀቅ የቻለው በብዙ ወጀብ ውስጥ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን እያላት ያጣችውና ተርፏት የተቸገረችው፤ ብዙዎች ቀድመዋት ከማዶ ኾነው ተመልሰው ወደ ኋላ የሚመለከቷት፤ በዚኹ ችግር በመኾኑ፣ “ምንም ዐሥር ሰዓት ቢኾን እንኳ ዐሥራ ኹለት ሰዓት ስለአልኾነ ብንነቃ የተሻለ ነው፤” ሲሉ መክረዋል፡፡ “አባቶቻችን ሞተው እንኳ የሚነሡት ስለሠሩ ነው፤ መኩሪያዎቻችንና ዘውዶቻችን ኾነው እንደ ቅርስ የሚታዩ ቤቶችንና ሕንፃዎችን አቆይተውልናል፤ እኛም ቆመን እንኳ እንዳንረሳ ታላቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤” ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡

ባለፈው ዓርብ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ምርጫና ውሳኔ መሠረት፣ ያለፉት ሦስት ዓመታት የዋና ሥራ አስኪያጅነት ሓላፊነታቸውን በውጤት የሚያስረክቡት(በፋይናንስ ረገድ 29 ሚሊዮን ብር የነበረውን የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ተቀማጭ 200 ሚሊዮን ብር አድርሰውታል) ብፁዕነታቸው፤ ለተተኪ ብፁዓን ዋና ሥራ አስኪያጆችም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል – በየሦስት ዓመቱ የሚሾሙ ብፁዓን አባቶች በሥራ ዘመናቸው ቢቻል ኹለት ከዚያም በላይ ካልተቻለ ግን አንድ ሕንፃ ለመሥራት ቢሞከር ይኼም ሲታሰብ በዘጠኝ ዓመት ሦስት ሕንፃ ይፈጠራል ማለት ነው፤ ቢታሰብበት እላለኹ፡፡”

his holiness abune paulos laying the foundation stone

የባንኮ ዲሮማው ሕንፃ ዕብነ መሠረት በ2004 ዓ.ም. በተቀመጠበት ወቅት

በቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ በቀድሞው ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ እና በአፍሪ ኮንሰልት አርክቴክሮችና ኢንጅነሮች ማናጀር ኢንጅነር ገብረ መስቀል ተስፋዬ የጋራ ምክክር በ1999 ዓ.ም. ሐሳቡ የተጠነሰሰው፣ የዛሬው የባንኮ ዲሮማ ምሩቅ ሕንፃ፣ ዕብነ መሠረቱ የተጣለው፣ በኅዳር ወር 2004 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ነበር፡፡ የቀድሞው የባንኮ ዲሮማ ሕንፃ፣ ለምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም መቀደሻና ማወዳሻ ገቢ እንዲያስገኝ በጣሊያናዊ መሐንዲስ የተሠራ ሲኾን፤ ገንዘቡም፣ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ከስደት መልስ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልን ካሠሩ በኋላ ከተረፈው የተገኘ ነበር፡፡

*          *          *

ቤተ ክርስቲያናችን በቀድሞው መንግሥት ከተወረሱባት ሕንፃዎች፣ ቪላዎች፣ አፓርትመንቶች፣ የቁጠባ ቤቶችና መጋዘኖች መካከል፣ በአስመላሽ ኮሚቴው አማካይነት እስከ አኹን 626ቱን ያስመለሰች ሲኾን ከዚኽ ውስጥ 342ቱ ለመኖርያ ቤት፣ 284ቱ ደግሞ ለድርጅቶች የተከራዩ ናቸው፡፡ ከሕንፃዎቹ መካከል ፒያሳ የሚገኘውና በተለምዶ “መሐሙድ ሙዚቃ ቤት” ተብሎ የሚጠራው ጽርሐ ምኒልክ መታሰቢያ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያናችን ከ42 ዓመት በፊት አስገንብታ ያከራየችው የመጀመሪያው የኪራይ ሕንፃ ነበር፡፡

Ato Tesfaye Wubshet, the gen mgr.

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ አቶ ተስፋዬ ውብሸት

አዲሱን የባንኮ ዲሮማ ሕንፃ አስገንብቶ ለሥራ ዝግጁ በማድረጉ ሒደት የታለፉት መሰናክሎች፣ በተሰናባቹ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብቻ ሳይኾን፣ በሌሎች የድርጅቱ ሓላፊዎች አስተያየት ላይም ተገልጿል፡፡ በምረቃው መርሐ ግብር በተሠራጨው መጽሔት ላይ አስተያየቶቻቸውን ከየፎቶ ግራፎቻቸው ግርጌ ያሰፈሩት ሓላፊዎቹ፣ የመሰናከሉ ምንጮች ናቸው ያሏቸውን አካላት፣ ቅንዓተ ቤተ ክርስቲያን የጎደላቸው፣ ከመገንባት ይልቅ በክፉ ምክርና በአሉባልታ የተካኑ ባቢሎናውያን ናቸው፤ ብለዋቸዋል፡፡ “ዐዲስ የታሪክ ምዕራፍ” መኾኑ ስለተገለጸው የሕንፃው ምረቃ፣ ሓላፊዎቹ ካሰፈሩት አስተያየት ለጥቅስ ያኽል የተወሰደውን ከዚኽ በታች ይመልከቱ፤

 • ቤተ ክርስቲያናችን፥ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ በሦስቱ ኮሌጆች፣ በየአጥቢያዎቹና በየአህጉረ ስብከቱ ጥሩ፣ ጥሩ ሕንፃዎችን እየሠራች፣ አምጡ ሥሩ ስትል የነበረች፣ በሥራም ለምእመናን አርኣያ ምሳሌ ኾና ቀርባለች፤ ተነሥታለች፡፡ የነበሩትን በማደስ፣ የተጀመሩትን ለመፈጸም፣ የታቀዱትን ለመተግበር መለያየቱን፣ መተማማቱን፣ መተቻቸቱን ወደ ጎን በማድረግ ሰላምን፣ አንድነትን፣ ስምምነትንና ፍቅርን ተላብሰን ሥራችንን በትጋት እንድንቀጥል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይኹን፡፡

  /መጋቤ ሥርዓት ዳንኤል ወልደ ገሪማ፤ የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ/

 • አገልጋዮችን እየደገፈ ቤተ ክርስቲያንን የሚያጠናክር ነው፤ የሚያሰናክሉት በአባቶች ይገሠጹ!

/መጋቤ ብርሃናት ተክለርትዕ ገብረ ወልድ፤ የድርጅቱ የሠራተኛ አስተዳደር ዋና ክፍል ሓላፊ/

 • ባለፍናቸው ውጣ ውረዶች ልምዶችን ገብይተናል፤ ለበለጠ ሥራ በቁጭትና በቁርጠኝነት እንነሣ!

/አቶ ታምሩ አበራ፤ የዕቅድና ልማት ዋና ክፍል ሓላፊ/

 • ለውጤት የበቃው በአበው ጸሎት፣ በድርጅታችን አመራሮችና ሠራተኞች የጋራ ጥረት ነው፡፡

/መጋቤ ሠናያት ያዘው ማሞ፤ የድርጅቱ የደንበኞች አገልግሎት ዋና ክፍል ሓላፊ/

 • ይህ ውብ ሕንፃ ነው፡፡ ውጤት፣ በመራራ ትግል የሚያልፍ አሸናፊነት ነው፡፡ በድል፣ ሕንፃው ለፍጻሜ በቃ፡፡ ለነገራችን ኹሉ ትምህርት ኾኖ፣ ፊት ለፊታችን ይታያል፡፡ ለሚማር፣ ታላቅ መፋረጃ ምስክር ኾነው፡፡

/መምህር መክት ፋንቱ፤ የድርጅቱ ጠቅላላ አገልግሎት ዋና ክፍል ሓላፊ/

 • የቤተ ክርስቲያንን መብትና ጥቅም በማስቀደም፣ በቡድን የመሥራት ባህልን በማዳበር ጠንክረን በመሥራታችን በቀዳሚነት የተገነባው ሕንፃ፣ ለአመራሩ ብቃትና ዝግጅት ማሳያ ስለኾነ ሊበረታታ ይገባል፡፡

/አቶ ወንድሙ መልኬ፤ የድርጅቱ የሕግ አገልግሎት ዋና ክፍል ሓላፊ/

 • “በጻድቃን ልማት ከተማ ደስ ይላታል፤”/ምሳ 11÷10/ እንዲል. በአባቶቻችን አርቆ አሳቢነት የተወጠነው ልማት በዚኽ ዘመን አጣብቂኝ ውስጥ አልፎ ለድል ሲበቃ ማየት የትላንቱን የአባቶቻችንን ተጋድሎ ያስታውሳል፡፡

/መ/ር ሱራፌል ታደሰ፤ የድርጅቱ ሱፐርቫይዘር/

Advertisements

6 thoughts on “የባንኮ ዲሮማው ባለ9 ፎቅ የገበያ ማዕከል: በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተመረቀ፤ “ትንሣኤ ሕንፃ” ተብሏል፤ ብር 17 ሚልዮን ዓመታዊ ገቢ ያስገኛል

 1. Anonymous June 5, 2016 at 12:20 pm Reply

  Ato tesfaye wubshet; aba matiwes beserawu sera yante mekofes yasaznal

  I

 2. Anonymous June 6, 2016 at 5:17 am Reply

  Please be positive. Whatever it is he is the manager.

 3. Gebrekidan June 6, 2016 at 6:17 am Reply

  It is Good Start. KeneYemane; Mekerat; Zekarias amleto lezih mebkatu Temsgen New. Gin Yemane Yezerefewes Birr? Teyaki Yelem? Zarem Goitom musinawin Gemrotal…

 4. teddy June 6, 2016 at 6:22 am Reply

  እባካችሁ ስለ ቤተ ክርስቲያን አምላክ ስለ መድኃኔዓለም ብላችሁ ከ70 ሚሊዮን ዓመታዊ ገቢው ላይ ቢያንስ 10 ሚሊዮኑን ለገዳማት፣ለአብነት ት/ቤት፣እንዲሁም ድረሱልን አጥምቁን ልጅነትን አሰጡን ለሚሉ በጠረፋማው የሀገራችን አካባቢ ለሚገኙ ወገኖቻችን ማስተማሪያ አድርጉት!!!

 5. shigute June 8, 2016 at 8:55 am Reply

  thank you

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: