ቅ/ሲኖዶስ: በፀረ ተሐድሶ ኑፋቄ አጀንዳ መወያየት ጀመረ፤ ሕዋሱ ምልምሎቹን በኤጲስ ቆጶስነት ለማሾም እየሠራ እንዳለ ተጠቁሟል

 • የተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ጥቆማና ምርጫ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግበት ተጠይቋል
 • ብፁዓን አባቶች፣ በአደረጃጀትና በእንቅስቃሴ የአህጉረ ስብከታቸውን ተሞክሮ አቀረቡ
 • የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ የወራት አፈጻጸም በጥቅሉ ተገምግሟል
 • በልዩ ጽ/ቤቱና በአባ ቃለ ጽድቅ ያለው የኑፋቄው ስጋት ዛሬም ትኩረት ተሰጥቶታል
 • የፀረ ተሐድሶ ጉባኤውን ከአጥቢያ እስከ አህጉረ ስብከት ማዋቀሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል
 • ኑፋቄውን በሚያጋልጡና በሚያመክኑ ተጨማሪ ስልቶች ላይ ምክክሩ ነገም ይቀጥላል

*                     *                     *

Holy synod Gin2008

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ(ፎቶ: አ/አ ሀ/ስብከት)

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና ታሪካዊ ትውፊት እንዳይፋለስ የመጠበቅና የማስጠበቅ፤ አገልግሎቷም የተሟላ እንዲኾን የማድረግ ዓላማዎች ያሉት ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለትምህርተ ሃይማኖታችንና ለመዋቅራዊ አንድነታችን የህልውና ስጋት የኾነውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ለማጋለጥና ለማምከን ስለሚደረገው የመከላከል እንቅስቃሴ መወያየት ጀመረ፡፡

ምልዓተ ጉባኤው፣ በዛሬ፣ ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. የቀትር በኋላ ውሎው፣ “ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ አንፃር የመናፍቃን እንቅስቃሴ ጉዳይ” በሚል በተ.ቁ(15) በያዘው አጀንዳ መነጋገር እንደጀመረ ተገልጿል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ከኑፋቄው ተጽዕኖና ተጨባጭ አደጋዎቹ በትይዩ፣ በማስረጃ ለማጋለጥ እና በትምህርት ለመከላከል ያደረጓቸውን እንቅስቃሴዎችና የወሰዷቸውን ርምጃዎች፣ ከየአህጉረ ስብከታቸው ተሞክሮ በመነሣት አብራርተዋል፡፡

በጥቅምቱ ምልዓተ ጉባኤ በተወሰነው መሠረት፣ ማኅበረ ካህናትን፣ ማኅበረ ምእመናንን፣ የሰንበት ት/ቤቶችንና ማኅበረ ቅዱሳንን ያሳተፈ የፀረ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ በወረዳዎችና በአጥቢያዎች በማቋቋም የሚካሔደው አድማሳዊ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተጋድሎ ተጠናክሮ እንደቀጠለ፣ ከብፁዓን አባቶች ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ምዕራብ ሸዋ፣ ጅማ እና ምሥራቅ ወለጋ አህጉረ ስብከት በአርኣያነት የተጠቀሱ ሲኾን፣ ሌሎች አህጉረ ስብከትም በአርኣያነት እንዲማሩበ በውይይቱ አጽንዖት ተሰጥቶታል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ የወራት እንቅስቃሴ በጥቅሉ የገመገመ ሲኾን፤ በየአህጉረ ስብከቱ የሚቋቋሙት የፀረ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤዎች ዕቅዶቻቸውንና አፈጻጸሞቻቸውን እስከ መንበረ ፓትርያርኩ ድረስ በኢንፎርሜሽንና በሪፖርት እንዲያቀርቡና ከማዕከል በሚሰጠው አቅጣጫና መመሪያ መሠረት እንዲያገለግሉ ቀደም ሲል የተላለፈው ውሳኔ ተጠብቆ ሊሠራበት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

Holy Synod01
የብፁዓን አባቶች ገለጻ እንደሚያሳየው፣ በየአህጉረ ስብከቱ የሚደረገው የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተጋድሎ የሚያበረታታ ቢኾንም፣ ኑፋቄው በቤተ ክርስቲያናችን ማንነትና ማዕከላዊ አንድነት ላይ ከጋረጠው አደጋ አኳያ ገና አጥጋቢ/በቂ እንዳልኾነ በምልዓተ ጉባኤው ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ ለዚኽም በቃልም በኅትመትም በየጊዜው ለሚረጩት ኑፋቄዎች በቂ ጽሑፋዊ ምላሽ በመስጠት ረገድ ያሉ ውስንነቶች በዓይነተኛ ማሳያነት ተጠቅሰዋል፡፡

ከአህጉረ ስብከቱ ባሻገር በማእከል፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት እና የውጭ ጉዳይ መምሪያው እንደ አደረጃጀት ማሻሻያው ኹሉ ከኑፋቄው ሤራም አንፃር በጥልቀት እንዲፈተሽ ምልዓተ ጉባኤው ሲያሳስብ፣ መነሻው፣ የመምሪያው ዋና ሓላፊ መልአከ ሰላም አባ ቃለ ጽድቅ የእምነት አቋም ነበር፡፡ በትእዛዛቸው በሓላፊነት ላይ ያስቀመጡት ርእሰ መንበሩ፣ ስለ ግለሰቡ ማስረጃ ከቀረበላቸው ርምጃ እንደሚወስዱ ዛሬም በምልዓተ ጉባኤው ፊት አረጋግጠዋል፡፡

የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄው ወኪሎች ሌት ተቀን እየሠሩበት ያለው ሌላዊ ወቅታዊ ጉዳይ ደግሞ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ በአጀንዳነት የያዘው የአዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የኑፋቄው ሕዋስ፣ በሢመቱ አጋጣሚ ምልምሎቹን አስርጎ በማስገባት በማዕርገ ክህነቱ ከፍተኛ ቦታ ለመያዝ እየሠራ በመኾኑ፤ በዕጩነት በሚቀርቡ ቆሞሳትና መነኰሳት ጥቆማና በምርጫው ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡ የኑፋቄው የውስጥ አርበኞች፣ “የራሳችንን ሰው ለማስገባት ሠርተናል፤ ዝግጅታችንን ጨርሰናል” ማለታቸውም ተጠቅሷል፡፡

በዚኽ ረገድ የሚፈጠር መዘናጋት፣ የኑፋቄው ሕዋስ፣ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ አባልነት የደረሱ ኹለት ሦስት ኤጲስ ቆጶሳትን ብቻ ይዞ የቤተ ክርስቲያንን ማእከላዊ አስተዳደር ለመፈታተንና ከተሳካለትም ለማናጋት በመሣርያነት የሚጠቀምበት በመኾኑ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በተለይ የተሿሚዎችን ጥቆማ በቀኖናውና በሕጉ መሠረት፣ ከአህጉረ ስብከት ጀምሮ የማኅበረ ካህናትን፣ የማኅበረ ምእመናንንና የሰንበት ት/ቤቶችን ተሳትፎ በማረጋገጥ፤ ከሲሞናዊነትና ከጎጣዊ መሳሳብ በመጠበቅ አደጋውን ለመቀነስ እንደሚቻል ተገልጧል፡፡

ምልዓተ ጉባኤው፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን ውጤታማና ዘላቂ በኾነ መልኩ ለማጋለጥና ለመከላከል ያስችላሉ ባላቸው ተጨማሪ ስልቶች በነገው የግማሽ ቀን ውሎው በመምከር፣ ተጋድሎውን የሚያጠናክርና በመመሪያነት የሚያገለግል ዐቢይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

Advertisements

9 thoughts on “ቅ/ሲኖዶስ: በፀረ ተሐድሶ ኑፋቄ አጀንዳ መወያየት ጀመረ፤ ሕዋሱ ምልምሎቹን በኤጲስ ቆጶስነት ለማሾም እየሠራ እንዳለ ተጠቁሟል

 1. Fekadu Gashaw June 4, 2016 at 10:23 am Reply

  ሰሞኑን “አባ ሰላማ” በተሰኘው የኑፋቄ መዝሪያ ብሎጋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:-
  “……….ስለዚህ ቅዱስ ፓትርያርኩ አሁን በሚሾሙት ጳጳሳት ላይ በአቡነ ጳውሎስ ጊዜ የተፈጸሙትንና እስካሁን ለሲኖዶሱ በሽታ የሆኑትን ጳጳሳት ዓይነት በመሾም ሌላ ችግር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ እየወጡ ባሉ አንዳንድ መረጃዎች አንዳንድ ጠንካራ አባቶች ለጵጵስና መታጨታቸው ለቤተክርስቲያን ተስፋ ነው፡፡ ከዚህ የተሻለ ዕድልና ጊዜም የለምና……………….”
  ይህ አባባላቸው ሁለት ጉዳዮችን ያሳየናል፡፡
  1ኛ- የአባ ማትያስ ዘመነ ፕትርክና ምን ያህል እንደተመቻቸው “ከዚህ የበለጠ አጋጣሚ የለምና….. ” በማለት አረጋግጠውልናል፡፡
  2ኛ- አሁን ሊካሔድ በታሰበው ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ላይ የራሳቸውን ሰዎች አስርጎ ለማስገባት ብዙ እንደሠሩና እየሠሩም እንደሆነ ያሳያልና እጅጉን ጥንቃቄና ትግል ያስፈልጋል፡፡
  ጥንቃቄ! ጥንቃቄ! ጥንቃቄ!

 2. ቴዎድሮስ ግደይ June 4, 2016 at 11:19 am Reply

  በውጭ ሃገር ስለሚገኙ አቢያተ ክርስቲያን ችግር የማይወራበት ምክንያት ምንድን ነው? በውጭ ላለነው ምዕመናን የሚስማማ ቃለ ዓዋዲ የማይቀረፅበት ምክንያትስ ምን ይሆን ? በተለይ በማንቸስተር ዮናይትድ ያለው የምዕመኑ ችግር ብፁዕ አቡነ እንጦስ ማብራሪያ ለምን አይሰጡም ።እባካችሁ ጉዳዩ እንዲነሳ በቅርበት የሚያውቁት አቡነ ሉቃስ አቡነ ሄኖክም ጭምር ማነጋገሩ መልካም ነው።

 3. Gorgorios June 4, 2016 at 11:20 am Reply

  ይበል ነው፡፡

 4. Anonymous June 4, 2016 at 1:09 pm Reply

  ዘረኝነት ኑፋቄ አይደለም ወይ ገንዘብ ወዳድነት ኑፋቄ አይደለም ወይ
  ክረስቶስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ የተሰቀለበትን መስቀል ከጨበጡ በላ የመንጋው ጠባቂ ሆነው በሊቀጳጰስነት ደረጃ ከባድ ኃላፊነት ከተቀበሉ በላ የስጋ ዘመዶቻቸውን በተመደቡበት ሀገረስብከት ያለውድድር ሥራ ማስቀጠርስ ኑፋቄ አየደለም ወይ የበታች የቤተክህነት ሠራተኞችንስ በቂመኝነት በተበቃይነት ማሳደድ ኑፋቄ አይደለም ወይ ለእነርሱ አስተሳሰብ የማይገዙትን የየሀገረስብከቱን ሥራአስኪጆች እንደቤት ሠራተኞቻቸው አልፈለግህም ብሎ ከህግ ውጭ ማባረርስ ኑፋቄ አይደለም ወይ ስለዚህ የኑፋቄው ዘመቻ የሃይማኖት ህጸጽ ባለባቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በእነዚህም ጭምር መሆን አለበት ከዚህ ውጭ ዋናውን በሽታ( ካንሰሩን) ትቶ ጉንፋኑን ማሳደድ ነው የሚሆነው ፡፡ የአባቴ ቤት የጸሎት ቤት ነው እናንተ ግን የሻጮችና የለዋጮች ዋሻ አደረጋቸሁት ተብሎ የተመዘዘው ጅራፍ አሁን ይፈለጋል ብጽአን አባቶች አያሉ ማሻቃበጡ ሰማያዊ ሀብት አያሰጥም እውነት ኮሶ ነው ለመሻር ግን የግድ መጨለጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህው ነው፡፡

 5. Haileeyesus Teka June 7, 2016 at 1:18 pm Reply

  ከዘረኝነትና ሙስና ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዳሉ ሁላችን አናውቃልን ይህ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ነው። ኑፋቄ ግን ወሳኝ ሃይማኖታዊ መሠረትን የሚነካ የአስተምህሮ በሽታ በመሆኑ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠውና ከአስተዳደራዊ ችግር ጋር ተጨምሮ በመታየተ መኮሰስ የሌለበት ጉዳይ ነው። ለመሆኑ ጉንፋን የቱ ነው? ካንሰሩስ? ለእኔ ከኑፋቄ በላይ ካንሰር አይታይኝም። ቤተክርስቲያን በሁሉም ችግሮች ላይ ጠንካራ እርምጃዎችን ማድረግ ቢያስፈልጋትም እንደ ኑፋቄ ግን አጣዳፊ የሆነ የለም።

 6. zefunoteselam June 7, 2016 at 1:30 pm Reply

  በ አእ ወው ነተቱ አ በባ ተቶ ቸቻ ቸች ነን ተታረሪ ከክ ሰ ረርተታ ቸች ኀኃ ለል ተ ገግ በባረራ ወዊ ነተቱ

 7. Anonymous June 8, 2016 at 3:57 pm Reply

  ነፋቄን የመሰለ ክህደት አሳንሶ የቤተክረስቲያንን የስተዳደር በደል አገዝፎ ለማየት አይደለም ኑፋቄ ከካነሰር የበለጠ መግለጫ ሊሰጠው ይገባል ገዳይነቱ ነፍስን ጭምር በመሆኑ ነገር ግን የአስተዳደር በደል ተብሎ የተገለጸው ከሀማኖት ምግባር ውጭ የሆነው ዘረኝነት አሳዳጅነት ይቅርታ የለሹ ቂመኝነት ክህነትን የሚያስቀማ ነው፡፤በቤተክርስቲያን ውስጥ በመንጋው ጠባቂት የተሠየመ አባት ያልተሠጠውን ተግባር ሲፈጽም የተበደሉት ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ኮብልለው የኑፋቄው መዝሪያ ምቹ እርሻ መሆናቸው በተግባር የተገለጠ ሀቅ ነው ፡፡ ቁምነገሩ የመንጋው ጠባቂ አባት ከዘረኝት ከምላስ ተቀባይነት ከአሳዳጅንነት ከሙስና ከቂም በቀል ራሱን ለይቶ ሲኖር የኑፋቄውም የፍልሰቱም ጎርፍ ጸጥ ይላል፡፡ ካልሆነ ግን………

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: