የደ/አፍሪቃ ፍ/ቤት: አባ ጥዑመ ልሳነ አዳነን ከካቴድራሉ አገደ፤ የልዩ ጽ/ቤቱ ትእዛዝ ለአደጋ አጋልጦታል፤ ምእመናኑ ቅ/ሲኖዶስን ተማፀኑ

 • በማናቸውም የካቴድራሉ አገልግሎት እና አስተዳደራዊ ተግባራት ሚና አይኖራቸውም
 • የመጋቤ ብርሃናት አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎርዮስ ምደባ፣ በእነንቡረ እድ ኤልያስ ተሰናክሏል
 • ያለሕጉ በታገደው ሰበካ ጉባኤ ምትክ፣ ያለደንቡ ምርጫ እንዲካሔድ ልዩ ጽ/ቤቱ አዝዟል
 • የፍ/ቤቱን ትእዛዝ የሚጥስና በሀገሪቱ ሕግ የካቴድራሉን ህልውና ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው
 • ቅ/ሲኖዶስ፥ ለአንድነት የሚበጅና ሀ/ስብከቱን በሰላም የሚመራ ውሳኔ እንዲሰጥ ተጠይቋል

*                *                *

south africa court orde rooo
በደቡብ አፍሪቃ የጆሐንስበርግ ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅና የጆሐንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኃኔዓለም ካቴድራል አስተዳዳሪን መጋቤ ሃይማኖት አባ ጥዑመ ልሳነ አዳነ ትኩንና ሰባት ግለሰቦችን፣ ከካቴድራሉ ጋር በተገናኙ ማናቸውም ጉዳዮች እንዲታገዱ ወሰነ፡፡

ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና ከደብሩ አስተዳዳሪ የሰነድ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ፣ በአንደኛ አመልካች የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ እና በኹለተኛ አመልካች በካቴድራሉ የሰንበት ት/ቤት እንዲኹም በመልስ ሰጪዎች በመጋቤ ሃይማኖት አባ ጥዑመ ልሳንና ሰባት ግለሰቦች መካከል የነበረውን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው ከፍተኛ ፍ/ቤቱ፣ ከትላንት በስቲያ፣ ግንቦት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ፤ ተከሣሾችን በማገድ አራት ትእዛዞችን ሰጥቷል፡፡

በከፍተኛ ፍ/ቤቱ የመዝገብ ቁጥር 18204/16 በመልስ ሰጪዎች÷ መጋቤ ሃይማኖት አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ እና ሰባት ግለሰቦች፡- ዘነበ ረዳኢ፣ ታምራት ለገሰ፣ ኢሳይያስ ነጋ፣ ቴዎድሮስ አሠይመኝ፣ ቤተ ሌዊ፣ ዲ/ን ሉቃስ ገንሱ እና ዲ/ን ኤልያስ ተክሉ ላይ የተላለፉት ትእዛዞች፡-

 • በጆሐንስበርግ 15ኛዶሪስ ጎዳና፤ ቱድሆፕ ጎዳና እና ቤሪያ ወደሚገኘው የካቴድራሉ ቅጽር ግቢ፣ የአስተዳደሩ ጽ/ቤት እና የሰንበት ት/ቤቶች እንዳይገቡ፤
 • በጆሐንስበርግ 15ኛዶሪስ ጎዳና፤ ቱድሆፕ ጎዳና እና ቤሪያ በሚገኘው የካቴድራሉ አገልግሎት እና ከአገልግሎቱ ጋር በተገናኙ ተግባራት እንደይሳተፉ፤
 • በጆሐንስበርግ 15ኛዶሪስ ጎዳና፤ ቱድሆፕ ጎዳና እና ቤሪያ የሚገኘውን ካቴድራል ማናቸውም አገልግሎቱንና ከአገልግሎቱ ጋር የተገናኙ ተግባራትን እንዳያውኩ፤ እንዳያስተጓጎሉ፤
 • የካቴድራሉን የዕለት ተዕለት አሠራርና የባንክ ሒሳቡን ማንቀሳቀስ ጨምሮ መንፈሳዊ አገልግሎቱንና ከአገልግሎቱ ጋር የተገናኙ ማናቸውንም ተግባራት በተመለከተ የአስተዳደር ጉባኤውን አባላትንና አገልግሎቱን የሚሳተፉ ምእመናንን በጣልቃ መግባት፣ በማስፈራራት፣ በማገት እንዳያውኩ

የሚሉ ናቸው፡፡ ይኹንና ሥራ አስኪያጁና አስተዳዳሪው የከፍተኛ ፍ/ቤቱን ትእዛዝ ተፈጻሚ ባለማድረግና በመተላለፍ፣ በሀገሪቱ ሕግ ተመዝግባ አገልግሎቷን የምትሰጠውን ቤተ ክርስቲያን መሠረተ ህልውና እና የሕዝቡን የእርስ በርስ አንድነት ለአደጋ ማጋለጣቸውን እንደቀጠሉ ተገልጧል፡፡

አወዛጋቢው መጋቤ ሃይማኖት አባ ጥዑመ ልሳን፣ ትእዛዙን በመጣስ፣ “የደብሩን ሰበካ ጉባኤ አውርጄ በምትኩ አዲስ ሰበካ ጉባኤ ተክቼ ነው የምሔደው” በማለት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ምእመናኑን ከፋፍሎ የሚያጋጭና ጉዳዩ ዳግመኛ ለጸጥታ አካሉ ከደረሰም የካቴድራሉን ሕጋዊ ህልውና እስከ ወዲያኛው ጥያቄ ውስጥ የሚከት እንደኾነ ከስፍራው ለጡመራ መድረኩ የደረሰ ተማኅፅኖ ይጠቁማል፡፡ ከቀናት በፊት ለጡመራ መድረኩ የተላከው ተማኅፅኖ የሚከተለውን ይላል፡-


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

ከደቡብ አፍሪካ ጆሐንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ምእመናን፤
አፋጣኝ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ፡-

በመጋቤ ሃይማኖት አባ ጥኡመ ልሳን አዳነና በደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት በተነሣው አለመግባባት ምእመናን ለኹለት ጎራ ተከፍለው አላስፈላጊ ድብድብ ውስጥ በመግባታቸው ቅዱስ ሲኖዶስ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ፣ መጋቤ ሃይማኖት አባ ጥኡመ ልሳን አዳነ በአስቸኳይ ወደ አገር ቤት ገብተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ወስኖ ጠርቷቸዋል፡፡

ይህን ደብዳቤም፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ የሱማሌና የአርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ ደቡብ አፍሪቃ ድረስ መጥተው ከሰጡ በኋላ ለምእመኑ ቃለ ወንጌል እና ቡራኬ ሰጥተው ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል።

his grace abune yared tour south africa
ይኹንና ብፁዕነታቸው፣ የካቴድራሉን ሕዝብ ለኹለት ከፍለው እያደባደቡ ያሉትን መነኵሴ ተነሥተዋል ብለው ከሔዱ ከ15 ቀናት በኋላ ደግሞ ሌላ ደብዳቤ ከፓትርያርኩ ቢሮ መጣ ተባለ፤ የቱን እንቀበል?

መጋቤ ሃይማኖት አባ ጥዑመ ልሳንም÷ የዝውውር ደብዳቤውን በመተው፣ “የደብሩን ሰበካ ጉባኤ አውርጄ በምትኩ አዲስ ሰበካ ጉባኤ ተክቼ ነው የምሔደው” በማለት ለእሑድ ግንቦት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በድጋሜ ሕዝቡን ለድብድብ እያዘጋጁት ይገኛሉ።

አኹን የሚሰማው ወሬ ሰዉን እርስ በርስ ሊያጋድል የሚችል ነውና፣ በምእመናኑ ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት በእግዚአብሔር ስም ለሚመለከተው ክፍል እንድታደርሱልን እንጠይቃለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ


ውዝግቡ በዚኽ መልኩ ለደረሰበት ደረጃ በዋናነት የሚወቀሰው፣ በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የተደረገው ተደጋጋሚ ጣልቃ ገብነት እንደኾነ ተጠቅሷል፡፡

ይኸውም፣ የመጀመሪያው፡- ቋሚ ሲኖዶስ ሚያዝያ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በወሰነው መሠረት፣ በአዲስ የተመደቡት የመጋቤ ብርሃናት አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎሬዎስ አካሔድ፣ ከሥራ ይልቅ ለአጭር ጊዜ ብቻ በሚቆይ የቱሪስት ወይም የጎብኚ ቪዛ ካልኾነ ማለቱ ነው፡፡ 

አካሔዱ፣ ቤተ ክርስቲያን በተመዘገበችበት የሀገሪቱ ሕግ መሠረት፥ ሥራ አስኪያጁ፣ የባንክ ሒሳብን ማንቀሳቀስን ጨምሮ በማንኛውም የሀገረ ስብከቱና የካቴድራሉ ጉዳዮች ከመወሰን የሚያርቃቸውና ተቀባይነት የሚያሳጣቸው እንደኾነ ከተሞክሮም የታወቀ ነው፡፡ ምደባው፣ የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነትና የካቴድራል አስተዳዳሪነት ኾኖ ሳለ በቱሪስት/ጎብኚ እንጂ በሥራ ቪዛ መሔዱ የመጋቤ ሃይማኖት አባ ጥዑመ ልሳን አዳነን ስሕተት ከመድገም በቀር ሌላ ፋይዳ እንደሌለው መጋቤ ብርሃናት ሃይማኖት አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎሬዎስም ለልዩ ጽ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡

Aba tekle yared goregorewos sent to SA
ይኹንና በልዩ ጸሐፊው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃና በውጭ ጉዳይ መምሪያው ዋና ሓላፊ ነውረኛው አባ ቃለ ጽድቅ ክፉ ምክር ሰሚ ባለማግኘታቸው በቋሚ ሲኖዶስ የተወሰነላቸው ምደባ ሳይፈጸም ተስተጓጉሏል፡፡ በውሳኔው እንደተገለጸው፣ መጋቤ ብርሃናት አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎሬዎስ፣ በአስተዳደር ሓላፊነታቸውና በትምህርታቸው፣ ከሀገሩና ከቀዬው ተፈናቅሎ በዝርወት የሚገኘውን ሕዝበ ክርስቲያን በእምነቱና በተቀደሰው ባህሉ ጸንቶ ይኖር ዘንድ ለማስተማርና ለማስተባበርም አልቻሉም፡፡

በኹለተኛ ደረጃ፡- በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 6 መሠረት የሀገረ ስብከት ዋና ጽ/ቤት ተጠሪነቱ የቤተ ክርስቲያንን የሥራ አስፈጻሚነት እና የአስተዳደር ተግባር በበላይነት ለማከናወን ሥልጣን የተሰጠው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም የሚወስናቸው ውሳኔዎች ለአህጉረ ስብከት የሚተላለፉት በጠቅላይ ጽ/ቤቱ በኩል ሲኾን፣ ጥያቄዎች ከአየህጉረ ስብከቱ ሲቀርቡም የሚፈጸሙት በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አማካይነት እንደኾነ በአንቀጽ 42 ንኡስ አንቀጽ 1 ተደንግጓል፡፡

Liyu Tsihifet Bet
ነገር ግን፣ ልዩ ጽ/ቤቱ እና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ቁጥጥር ሥር መኾን የሚገባው የውጭ ጉዳይ መምሪያ፣ እኒኽን ድንጋጌዎች በመጣስና በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔዎች አፈጻጸም ላይ ሻጥር በመሥራት የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ በፓትርያርኩ ቀጥተኛ ትእዛዝ እንዲታገድ፤ የሒሳብና የሥራ ሪፖርት ባልቀረበበት ኹኔታ ሌላ የሰበካ ጉባኤ ምርጫ እንዲካሔድ ለአወዛጋቢው አስተዳዳሪ ፈቃድ ሰጥተዋል፡፡ በዚኽም ሳቢያ በተማኅፅኖው እንደተጠቆመው፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ በጎራ ተከፋፍሎ እንዲታወክ ምክንያት ኾነዋል፡፡

ስለ አህጉረ ስብከት መቋቋም በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 1/ለ እንደሰፈረው፤ አህጉረ ስብከቱ የሚቋቋሙባቸውን ሀገሮች ሕገጋተ መንግሥታት ያገናዘበና ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ጋር የተጣጣመ ፖሊሲና የመተዳደሪያ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚወጣ ቢጠቆምም እስከ አኹን ባለመውጣቱ፣ ቤተ ክርስቲያን በተመዘገችበት ሀገር ሕግ መመራቱ ለጊዜው ግድ ኾኖ ይታያል፡፡

በመኾኑም፣ ከሚላኩት የሥራ ሓላፊዎች አካሔድ ጀምሮ ከትላንት በስቲያ የደቡብ አፍሪቃ ከፍተኛ ፍ/ቤት ከሰጠው ትእዛዝ አንጻር፣ በመካሔድ ላይ የሚገኘው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፥ ለሕዝበ ክርስቲያኑ አንድነት መጠበቅ ሲባል በጥሞና እንዲመለከተውና ሀገረ ስብከቱን በሰላም ለማስተዳደርና ለመምራት የሚያስችል ውሳኔ እንዲሰጥበት ይጠበቃል፡፡ ቀደም ሲል የተዘገበው የፓትርያርኩ ተቃውሞ ቢኖርም፣ ልዩ ጽ/ቤቱ እና የውጭ ጉዳይ መምሪያው እንዳፈተታቸው የሚኾኑበት ጉዳይም በተጀመረው የአደረጃጀትና የአሠራር እርማት መልክ ሊያስዘው ይገባል፡፡

“ለቤተ ክርስቲያን እንጂ ለማንም የወገንኩ አይደለኹም” ያሉ ሌላው የስፍራው ሐራዊ ምንጭ፣ ለጡመራ መድረኩ ባደረሱት መልእክት፣ ጉዳዩን በኹለት በመክፈል ኹሉንም ወገኖች የሚመለከት ነው ያሉትን አጠቃላይ መፍትሔ አመላክተዋል፡፡ እንደ ጥቆማው

– ሀ –

አጠቃላይ ጉዳዮችን በተመለከተ፡-

 • በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት፣ ጉዳዩ ባለበት ደረጃ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት እየተመራ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ይግባኝ ሰሚ እንዲኾኑና ቅዱስነታቸውም ኾነ ልዩ ጽ/ቤታቸው ከቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት መቆጠብ ይኖርባቸዋል፤
 • በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ጵጵስና እና የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ ከጆሐንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኃኔዓለም ካቴድራል ጥገኝነት መላቀቅና ቢቻል በግዥ አልያም በኪራይ በሚያገኙት ቦታ ራሳቸውን መቻል አለባቸው፤
 • የአገልግሎት ዘመኑን የጨረሰው ሰበካ ጉባኤ፣ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት የሥራ፣ የሒሳብና የኦዲት ሪፖርት ለማኅበረ ካህናት፣ ለማኅበረ ምእመናንና ለየሰንበት ት/ቤቶች ጠቅላላ ጉባኤ አቅርቦ ኹሉም የተሳተፈበት ግልጽ ምርጫ መካሔድ ይኖርበታል፤
 • በየሰንበት ት/ቤቱ እና በማኅበረ ካህናቴ መካከል፤ በሕዝብ እና በሕዝብ መካከል የሰላም ውይይት ተካሒዶ ይቅርታ እና ዕርቅ መደረግ አለበት፤

– ለ –

Aba Tiume Lisan Aba Tekle Yared

ነባሩ ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሃይማኖት አባ ጥዑመ ልሳነ አዳነ(በግራ) እና በአዲስ የተመደቡት መጋቤ ብርሃናት አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎርዮስ(በቀኝ)

በቋሚ ሲኖዶስ የተመደቡበትን አዲስ ሥራ አስኪያጅ እና የነባሩን አመላለስ በተመለከተ፡-

 • ነባሩ ሥራ አስኪያጅ እዚያው ሳሉ ለአዲሱ ሥራ አስኪያጅና ለየአድባራቱ ለተመደቡት አለቆች የግብዣ ደብዳቤ ልከው ሲገኙም ከሕዝበ ክርስቲያኑ አስተዋውቀው ሥራ እንዲያስጀምሩ፤
 • በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት፣ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለተጠሩት መጋቤ ሃይማኖት አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ የተጻፈላቸው ደብዳቤ፣ በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በግልባጭ እንዲያውቀው እንደተደረገ ኹሉ፣ በፍ/ቤት የተያዘውም ጉዳይ፣ በኤምባሲው በኩል አግባብነት ያለው የሀገሪቱ መንግሥታዊ አካል እንዲያውቀው ቢደረግ(እንደ ክሡ አቀራረብ ከሀገር አወጣጣቸው ላይ ነባሩ ሥራ አስኪያጅ ያላቸውን ስጋት በመገንዘብ)፤
 • ለነባሩ ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሃይማኖት አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ፣ ያልተከፈላቸው የአንድ ዓመት ከስምንት ወራት ደመወዝ ታስቦ እንዲከፈላቸው፤
 • የስንብት/የሽኝት እና የአቀባበል መርሐ ግብር፣ የተመረጡ የብዙኃን መገናኛዎች(የመድኃኔዓለሙን ውዝግብ ያሰራጨው የሀገሪቱ ቴሌቭዥን ጨምሮ) በተገኙበት ቢከናወን ለጠፋው ስማችን ማስተካከያ ይኾናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

Advertisements

2 thoughts on “የደ/አፍሪቃ ፍ/ቤት: አባ ጥዑመ ልሳነ አዳነን ከካቴድራሉ አገደ፤ የልዩ ጽ/ቤቱ ትእዛዝ ለአደጋ አጋልጦታል፤ ምእመናኑ ቅ/ሲኖዶስን ተማፀኑ

 1. ተስፋኹን May 30, 2016 at 1:46 pm Reply

  በስመአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ እሜን!
  እኔ ምለው እግዚአብሄር ባወቀ አባ ጡመ ልሳን ፈቃደ እግዚአብሔር ምን ማለት እንሆነ ሳያውቁ ቀርተው ነው..
  በቃ ሲኖዶስ ሾማቸው ደግሞ ሲኖዶስ አነሳቸው ከዚህ በላይ ግርግር መፍጠር ምን የሚሉት አጀንዳ ነው.
  ከዚህ ቀደም ለነማ እንሆነ ነው ለሳቸው የዚህ አገር ሚዲያ ጠርተን የምናሰናብታቸው. የጠራቸውን ሲኖዶስ ቸል ብለው በዚህም በዚያም ሰውን ለማጋደል ነው ?
  ደሞዛቸውንም ለምን ሄደው የቀጠራቸውን አካል አይጠይቁም ። እጄ እረጅም ነው ቆይ አሳያችኻለው እያሉ እዛቱ ነው ያሉት .።
  ከ20 አመት በላይ አብሮ የኖረን ክርስቲያን አለያይተው አጣሉ ። የቤተክርስቲያኗን ህልውና ክብር አበላሹ።
  ዜጎቹ ድሞ እርም ብለው ቀሩ ምን ቀራቸው ና ነው ።
  እግዚአብሔር በሰላም ብቻ ወደሀገራቸው ይመልሳቸው

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: