ቅዱስ ሲኖዶስ: በቤተ ክርስቲያን መተዳደርያ ደንብ/ቃለ ዓዋዲ/ ማሻሻያ ረቂቅ እየተወያየ ነው

  • የቤተ ክርስቲያንን ኵላዊነት እንዲያገናዝብ እና ከሀገሪቱ ሕጎች እንዲጣጣም ይጠበቃል
  • በመንግሥት እና በሚመለከታቸው አካላት ተቀባይነት እና ዕውቅና እንዲያገኝ ይደረጋል
  • ከሥራ ቋንቋ አማርኛ ሌላ በተለያዩ የሀገርና የውጭ ቋንቋዎች እንደሚተረጎም ተጠቁሟል
  • ቃለ ዓዋዲ፣ የአስተዳደርን ጨምሮ ልዩ ልዩ ደንቦች የሚጠሩበት አጠቃላይ ስያሜ ነው
  • በ2004 ዓ.ም. የተወሰነው የማሻሻሉ ሥራ ከአራት ዓመታት በላይ ሲጓተት ቆይቷል

*           *           *

kale awadi 1991በማኅበረ ካህናት እና በማኅበረ ምእመናን አንድነት ተደራጅታ፣ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የምትመራው ቤተ ክርስቲያናችን፣ የምትተዳደርበት የቃለ ዓዋዲ ማሻሻያ ረቂቅ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡

ቃለ ዓዋዲው፣ በ1991 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ ከተሻሻለ በኋላ ላለፉት 17 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየ ሲኾን፤ የቤተ ክርስቲያንን የአስተዳደር ሥራ ከወቅቱ አንፃር በብቃት ለመምራት ውስንነት እንዳለበት፤ በፍርድ ቤቶችና በመንግሥት አካላት ዘንድም የዕውቅና እና የተቀባይነት ተግዳሮት እንደገጠመው በተለያዩ ሪፖርቶች ተገልጧል፡፡

የቃለ ዓዋዲው ማሻሻያ፥ የኵላዊት እና የአንዲት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የደረሰበትን ዕድገት ያገናዘበ እንዲኹም ከሀገሪቱ ሕጎችና ደንቦች ጋር የተጣጣመና ተቀባይነት ያለው ኾኖ እንዲዘጋጅ፣ በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሚወጡ የጋራ መግለጫዎችና ውሳኔዎችም ሲጠየቅ ቆይቷል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዳደርን በሚመለከት የበላይ ሕግ በኾነው ሕገ ቤተ ክርስቲያን እንደተደነገገው፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለተደራጀችው ቤተ ክርስቲያናችን፣ ሕጎችን፣ ደንቦችንና ልዩ ልዩ መምሪያዎችን የማውጣት፣ የማሻሻልና የመሻር ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ በግንቦት 2004 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤው፣ በሥራ ላይ የሚገኘው የ1991 ዓ.ም. ቃለ ዓዋዲ እንዲሻሻል ወስኗል፤ ለሥራውም፣ አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ አራት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና አንድ የሕግ ባለሞያ የሚገኙበት ዐቢይ ኮሚቴም ሠይሟል፡፡

የጠቅላይ ጽ/ቤቱን የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያሬድንና የመምሪያው ዋና ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጨን ጨምሮ ዐሥር አባላት የሚገኙበት ዐቢይ ኮሚቴው፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራውን ለመጀመር ተቸግሮ የቆየ ሲኾን፤ ካለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር አንሥቶ ስምንት አባላት ያሉት የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋምና ከማደራጃ መምሪያው ጋር በመተባበር ባደረገው ጥረት የማሻሻያ ረቂቁን ለአኹኑ ምልዓተ ጉባኤ ማቅረቡ ተገልጧል፡፡

በረቂቁ፣ ግብአት የኾኑ ጽሑፎችና አስተያየቶች ከየአህጉረ ስብከቱ መሰብሰባቸውንና በሕግ ተቀባይነት ያላቸውና የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ ሥራ ከዘመኑ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ኹኔታ አንፃር ለመምራት የሚያስችሉ ሌሎችም ሐሳቦች በቃለ ዓዋዲው ማሻሻያ መካተታቸው ተጠቅሷል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በካህናትና በምእመናን ኅብረት እንድትደራጅ ታስቦ በትእዛዝ ዐዋጅ ቁጥር 83/65 ተፈቅዶ የወጣው ቃለ ዓዋዲ፤ በምልዓተ ጉባኤው ውሳኔ ለአራተኛ ጊዜ ተሻሽሎ ከጸደቀ በኋላ በመንግሥትና በሚመለከታቸው አካላት ዘንድ ዕውቅና እንዲያገኝ የሚደረግ ሲኾን፤ ከቤተ ክርስቲያን ማዕከላዊ አስተዳደር የሥራ ቋንቋ/አማርኛ/ በተጨማሪ በሌሎች የሀገርና የውጭ ቋንቋዎች እንደሚተረጎም ተጠቁሟል፡፡ Abune-theophilos

የቤተ ክርስቲያን መተዳደርያ ደንብ፣ “ቃለ ዓዋዲ ዘይሰብክ በገዳም” የሚለውን የነቢዩ ኢሳይያስ ቃል መሠረት በማድረግ፣ ቃለ ዓዋዲ በሚል ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው፣ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት መለያየታቸው ከመታወጁ ቀደም ብሎ፣ ጥቅምት 15 ቀን 1965 ዓ.ም. ሲኾን የፈረሙበትም አመንጪው እና መሥራቹ ኹለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ነበሩ፡፡

ቅዱስነታቸው፣ ከመተዳደርያ ደንብ በተጨማሪ፥ ግንቦት 1 ቀን 1965 የጸደቀው የቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት እና መጻሕፍት አመዘጋገብ፤ ታኅሣሥ 16 ቀን 1967 ዓ.ም. የጸደቀው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ ደንቦችንም በፊርማቸው ያወጡት ቃለ ዓዋዲ በሚል ስያሜ በመኾኑ እንደ ነጋሪት ጋዜጣ የቤተ ክርስቲያናችን ልዩ ልዩ ደንቦች የሚወጡበት አጠቃላይ ስያሜ ነው፡፡

በተለይ በቃለ ዓዋዲው የሚመራው የሰበካ አስተዳደር መንፈሳዊ ጉባኤ፣ በሠለጠነው ዓለም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ምእመናን ቤተ ክርስቲያንን በጋራ እንዲያስተዳድሩና እንዲያገለግሉ አስችሏቸዋል፡፡ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ፣ በሰበካ አስተዳደር መንፈሳዊ ጉባኤ አባልነት ተመዝግቦ በየዓመቱ የአባልነት አስተዋፅኦ እየከፈለ ሙሉ መንፈሳዊ አገልግሎት ያገኛል፡፡

ከ1967 ዓ.ም. ወዲኽ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በመላ ሀገሪቱ እና በውጭው ዓለም በ64ቱ አህጉረ ስብከት የተቋቋመው የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ÷ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ለራስ አገዝ ልማት መጎልበት፣ ለካህናት ኑሮና ለምእመናንም የማያቋርጥ አገልግሎት ዋስትና በመኾኑ በተገቢው የአሠራር ደንቦች እና መመሪያዎች በየጊዜው ሊጠናከር ይገባዋል፡፡

ምልዓተ ጉባኤው፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን የመክፈቻ ንግግር፣ የብፁዕ ዋና ጸሐፊውንና የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን ዓመታዊ ሪፖርት አዳምጧል፡፡  

Advertisements

2 thoughts on “ቅዱስ ሲኖዶስ: በቤተ ክርስቲያን መተዳደርያ ደንብ/ቃለ ዓዋዲ/ ማሻሻያ ረቂቅ እየተወያየ ነው

  1. […] Source: ቅዱስ ሲኖዶስ: በቤተ ክርስቲያን መተዳደርያ ደንብ/ቃለ ዓዋዲ/ … […]

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: