በቡሌ ሆራ ገርባ ከተማ የምእመናን ደኅንነትና የእምነት ነፃነት አስጊ ኾኗል፤ በፋሲካ እርድና የሉካንዳ ንግድ በተፈጠረ ሁከት ለድብደባና ለእስር ተዳርገዋል

 • በአንዳንድ ባለሥልጣናት ግፊትና በተደራጀ ኃይል የጥላቻ ቅስቀሳ ይካሔድባቸዋል
 • ጭምብል አጥልቆ፣ ገጀራ እና ጦር ይዞ ካህናትንና ምእመናንን እየመረጠ ያጠቃል
 • የመኖርያ እና የንግድ ቤቶቻቸውን እየለየ በድንጋይ ይደበድባል፤ ዝርፊያ ይፈጽማል
 • በጾም ሉካንዳዎችን በግድ ያስከፍታል፤ የሚዘጉቱም በፋሲካው እንዳይሠሩ ይከለክላል

*                *                 *

 • ጥንታዊውን የገርባ ደብረ ሰላም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ለመጉዳት ተሞክሯል
 • ደወል በማሰማት ደብራቸውን የተከላከሉ ምእመናን በሁከተኛነት ተወንጅለው ታስረዋል
 • ምእመኑ፥ ተጎጅም ተከሣሽም መደረጉን የሀገር ሽማግሌዎች በስብሰባ ላይ ተቃውመዋል

*               *                *IMG_20100101_191310

 • ለምእመናኑ የደኅንነት ስጋትና ለዞኑ ጥያቄ ወረዳው የሚሰጠው ምላሽ ርስበሱ ይጋጫል
 • ለወረዳው አነስተኛ ጸጥታ ኃይል እየመጣ ነው ሲል ለዞኑ ጥያቄ ግንሰላም ነው ይላል
 • የማረጋጋት ዓላማ ያላቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎችና ምክክሮች እንደቀጠሉ ናቸው፤ ተብሏል

*                *                *

 • “የሃይማኖት ግጭትም አይደለም፤ የብሔረሰብ ግጭትም አይደለም፤ ችግሩ የተወሰኑ ሰዎች ስሜት እና አጀንዳ ነው፤ ሕዝቡ አብሮ የኖረ ነው፤ ነገም አብሮ የሚኖር ነው፤ ግለሰብ ጠብ አጫሪዎች እና በሕዝቡ ወይም በሃይማኖት ተቋማት ሽፋን በመጠቀም የብጥብጥ ሙከራ የሚያደርጉ በየመሥሪያ ቤቱም ኾነ በየሃይማኖት ተቋማቱ ሊኖሩ ይችላሉ፤ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ ከመጠየቅ ጀምሮ የከተማችንን ችግር እኛው በራሳችን ተነጋግረን መፍታት አለብን፡፡”

/የከተማው ነዋሪ አባት/

*               *               *

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፮ ቁጥር ፰፻፶፪፤ ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)

hagere-maryamበኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ቡሌ ሆራ ወረዳ ገርባ ከተማ፣ ከሑዳዴ ጾም እና የፋሲካ እርድ ጋር በተያያዘ ከበዓሉ ቀን ጀምሮ ሁከት ተፈጥሮ እንደነበር የተገለጸ ሲኾን፤ በቡድን ተደራጅታችሁ ሁከት ፈጥራችኋል በሚል የታሰሩ ከኻያ ያላነሱ ሰዎችም ፍ/ቤት ቀርበው በነፃ እና በዋስ ተለቀዋል፡፡

በጾም ወቅት የከተማዋ ሉካንዳ ቤቶች እንዳይዘጉ ሲከላከሉ ነበር በተባሉ ግለሰቦች ስጋት ተፈጥሮ መቆየቱን የተናገሩ የከተማዋ ነዋሪዎች፤ በጾሙ ተዘግቶ ለፋሲካው በተከፈተ ሉካንዳ ቤት ደግሞ፤ ሕገ ወጥ እርድ ተካሒዷል በሚል ሁከቱ መቀስቀሱን ጠቁመዋል፡፡ በሁከቱ በሉካንዳው ላይ ጉዳት የደረሰ ሲኾን ባለቤቱን ጨምሮ የከብቱን ቆዳ ገዝቷል የተባለ ነዋሪ እና ሥጋም ለመሸመት ሞክሯል የተባለ ሌላ ሰው በማዘጋጃ ቤቱ ታስረው መዋላቸው ተገልጧል፡፡

በበዓሉ ማግሥት፣ የሉካንዳው ባለቤት ይቅርታ ጠይቆ የከብቱ ሥጋ ከተወገደ በኋላ ሉካንዳው ሥራውን ቀጥሎ የዋለ ሲኾን፤ ከቀትር በኋላም የከተማው አስተዳደር ሓላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት በጉዳዩ የምክክር ስብሰባ ተካሒዶ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ስብሰባው ምሽቱን መጠናቀቁን ተከትሎ ግን፣ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች የወረዳውን ሊቀ ካህናት፣ በከተማው የሚገኘውን የገርባ ደብረ ሰላም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና የሰበካ ጉባኤ አባላት በድንጋይ እሩምታ ሲያሳድዱ፣ መኖርያ ቤቶቻቸውንም እየለዩ በመደብደብ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ የከተማዋ ፖሊስ ኹኔታውን በተኩስ ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ በነበረበትም ወቅት፣ ግለሰቦቹ የቤተ ክርስቲያኑን ክልል በመክበባቸው እና ደወልም በመሰማቱ ሁከቱ መባባሱ ተገልጿል፡፡

Bule Hora Gerba violence

በከተማዋ የሚገኘው የአንድ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን ሉካንዳ ቤት፥ ከሥርዐተ እምነቱ በተፃራሪ በጾም እንዳይዘጋ፤ በፋሲካው ደግሞ በቄራው ተጠቅሞ እንዳይሸጥ በተደራጀው ኃይል መከልከሉ ለሁከቱ የወዲያው መንሥኤ ኾኖ ተጠቅሷል፡፡ በፋሲካው ጠዋት ሉካንዳ ቤቱ በተደራጀው ኃይል የድንጋይ ውርጅብኝ የተሠባበረ ሲኾን፤ ባለሉካንዳውን ጨምሮ ከርሱ ሥጋ ሸምተዋል፤ የከብት ቆዳ ገዝተዋል የተባሉ ኹለት ምእመናንም በእስር ውለዋል፡፡

በቀጣዩ ቀን በወረዳው ባለሥልጣናት በተጠራውና የሁከቱን መንሥኤ በመለየት ላይ ያተኮረ ነበር በተባለው ስብሰባ፤ ፖሊስ፥ በቡድን ተደራጅተው ሁከት ፈጥረዋል በሚል፣ በሰሙት ደወል ቤተ ክርስቲያናቸውን ለመከላከል በምሽት ከየቤታቸው የወጡ በርካታ ምእመናንን ማሰሩን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ከእኒኽም ጋር፤ ከበዓሉ ማግሥት ጀምሮ በሕገ ወጥ እርድ ሰበብ በወረዳዋ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ ከኻያ የማያንሱ ግለሰቦች፣ ማክሰኞ እና ኃሙስ በቡሌ ሆራ ፍ/ቤት የቀረቡ ቢኾንም፤ ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ በቂ መረጃ አላገኘኹባቸውም በማለታቸው በነፃ እና በዋስ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡

ሁከቱ የዓመት በዓሉን እርድ እና የሉካንዳ ገበያ መነሻ ያደረገ ይኾናል ብለው እንደሚገምቱ የተናገሩ አንድ የሃይማኖት አባት፤ “ጉዳዩ የሃይማኖት ግጭትም አይደለም፤ የብሔረሰብ ግጭትም አይደለም፤ ችግሩ የተወሰኑ ሰዎች ስሜት እና አጀንዳ ነው፤” ሲሉ በእምነትና ጎጣዊ ንግዳዊ ግብ ሊኖረው እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

“ሕዝቡ አብሮ የኖረ ነው፤ ነገም አብሮ የሚኖር ነው፤” ያሉት እኚሁ አባት፤ በግለሰብ ደረጃ ያሉ ጠብ አጫሪዎች እና በሕዝቡ ወይም በሃይማኖት ተቋማት ሽፋን በመጠቀም የብጥብጥ ሙከራ የሚያደርጉ በየመሥሪያ ቤቱም ኾነ በየሃይማኖት ተቋማት ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ ከመጠየቅ ጀምሮ የከተማችንን ችግር እኛው በራሳችን ተነጋግረን መፍታት አለብን፤ የሚሉ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች፤ የማረጋጋት ዓላማ ያላቸውን ስብሰባዎች እንደቀጠሉ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

መንሥኤውንና ተጠያቂውን አካል በትክክል ለይቶ መፍትሔና እልባት ለመስጠት የሚደረገው ጥረት ባለመቋጨቱም እንዲኽ ነው የሚል መረጃ ለመስጠት እንደሚያስቸግር አስታውቀዋል፡፡ የከተማዋን ፖሊስ እና የአስተዳደር ሓላፊዎች በስልክ ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ጥሪው ስለማይመልስ አስተያየታቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡

[“ጀባአስሬ ሥላሴ” በመባል የሚታወቀው ታቦት፣ ጥንት በአካባቢው ከነበረበት ጫካማ ቦታ ወደ ሀገረ ማርያም ከተማ በ1960ዎቹ ተዛውሮ ከቆየ በኋላ፤ 15 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኘው ወደ ገርባ ከተማ የመጣው በስፍራው ተወላጅ ሽማግሌዎች ጥያቄ ነበር፡፡ ዛሬ የከተማዋ ውበት ኾኖ የሚታየው ባለሦስት ጉልላቱ የደብረ ሰላም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የተተከለውም በ1971 ዓ.ም. ነው፡፡

በሀገር አባትነታቸው የሚታወቁት ኦርቶዶክሳውያኑ ሽማግሌዎች ቱኬ ዋቆ፤ ጃርሶ አዶላ እና ሾኖራ ገታም የደብሩ አቅኚዎች ሲኾኑ“ከተማዋ የአንድ ወገን ሳትኾን እያንዳንዱ ማንነቱን ጠብቆ በመተባበር የኖረባትና የሚያድግባት ናት፤” በማለት ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ሰላም እየመከሩና እየገሠጹ ይገኛሉ፡፡]

 

Advertisements

One thought on “በቡሌ ሆራ ገርባ ከተማ የምእመናን ደኅንነትና የእምነት ነፃነት አስጊ ኾኗል፤ በፋሲካ እርድና የሉካንዳ ንግድ በተፈጠረ ሁከት ለድብደባና ለእስር ተዳርገዋል

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: