የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ: የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጁን ተማሪ አባረረ፤“ቤተ ክርስቲያን በማታውቃቸው እንቅስቃሴዎች መገኘቱ ተረጋግጧል”/ኮሌጁ/

  • ፍኖተ ሕይወት ተስፋ ተሐድሶ” የተሰኘየፕሮቴስታንታዊ ድርጅት እንቅስቃሴ ተሳታፊ ነበር
  • በድርጅቱ ምልምሎች ምረቃ፥ መቋሚያ በማደልና ከበሮ በመምታት ቀሣጢነቱን አረጋግጧል
  • የቀን እና የማታ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት በተከታታይ ማጣራቱ ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል
  • የተወሰደው ርምጃ ለኮሌጁ ማኅበረሰብ ይፋ አለመደረጉ አስተዳደሩን ለትችት እየዳረገው ነው
  • መ/ር ሰሎሞን ኃ/ማርያም በጎይትኦም ያይኔ ቦታ በአስተዳደር ምክትል ዲንነት ተመድበዋል

*                *                *

Aschalew Yosef's complete dismissal
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ በቤተ ክርስቲያን በማይታወቁ እና ኮሌጁ በማይቀበላቸው የኑፋቄ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አግኝቸዋለኹ፤ ያለውን አንድ ተማሪ ማሰናበቱ ተገለጸ፡፡

አስቻለው ዮሴፍ ኤዳኦ የተባለው ይኸው ግለሰብ፣ በኮሌጁ የማታው ዲፕሎማ መርሐ ግብር የሦስተኛ ዓመት ተማሪ የነበረ ሲኾን፤ አስተዳደሩ ባገኘው ጠንካራ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ተከታታይ ማጣራት ሲደረግበት መቆየቱ ተጠቅሷል፡፡

በቁጥር 924/05/04/08 በቀን 06/08/2008 ዓ.ም. በበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ፥ ተማሪ አስቻለው ዮሴፍ፣ በተደረገበት ክትትልና ማጣራት ቤተ ክርስቲያን በማታውቃቸው እና ኮሌጃችን በማይቀበላቸው የሃይማኖት እንቅስቃሴዎች ውስጥ መገኘቱ እንደተረጋገጠ ገልጿል፤ በኮሌጁ ሕግና ደንብ መሠረትም፤ ከማታው መርሐ ግብር መሰናበቱን አስታውቋል፡፡

በክትትሉና ማጣራቱ ከተረጋገጡት ጉዳዮች ዋነኛው፤ አስቻለው ዮሴፍ ኤዳኦ፣ፍኖተ ሕይወት ማኅበረ መድኃኔዓለም ተስፋ ተሐድሶበተሰኘ ፕሮቴስታንታዊ ድርጅት እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ መኾኑ ነው፡፡ በማረጋገጫነት ከተያዙት ማስረጃዎች ውስጥም ከኹለት ዓመት በፊት የተቀረፀ የድርጅቱን ምልምሎች የምረቃ በዓል የሚያሳይ ቪዲዮ እንደሚገኝበት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በቪዲዮው እንደሚታየው፣ ፕሮቴስታንታዊው ድርጅት በኑፋቄው አስተምህሮ አጥምቆ ለስምሪት ያዘጋጃቸውን ዐሥር ሠልጣኞች ባስመረቀበት መርሐ ግብር ላይ፣ አስቻለው ዮሴፍ ከሌሎች ሦስት ግብረ አበሮቹ ጋር የተገኘ ሲኾን፤ የራሳቸው ያልኾነውንና የራሳቸው በማስመሰል የሚቀሥጡበትን መቋሚያ በማደል እና ከበሮ በመምታት እያጀበ ቀሣጢነቱን አረጋግጧል፡፡

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሻሸመኔ ከተማ አጥቢያዎች እንደሚሰብክ ይናገር የነበረው አስቻለው ዮሴፍ፣ በኮሌጁ የማታው መርሐ ግብር ሊመዘገብ የቻለው፣ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በተጻፈለት የአባልነት መረጃ መሠረት እንደኾነ በደብዳቤው ጠቅሷል፡፡

ግለሰቡ ራሱን ደብቆ እስከሚመረቅበት ሦስተኛ ዓመት ድረስ መዝለቁ፤ ኮሌጆቻችንን የሤራው ማእከል አድርጎ የሚንቀሳቀሰውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን አደጋ አሳሳቢነት በውል እንደሚያሳይ የተናገሩ ምንጮች፣ ከአቀባበል አንሥቶ ያሉ አሠራሮች ሊጠናከሩና በቀጣይነት ሊፈተሹ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ኮሌጁ በደረሱት ጥቆማዎች መሠረት አስፈላጊውን ክትትልና ማጣራት አድርጎ በቀሣጢው አስቻለው ዮሴፍ ላይ የወሰደውን ርምጃ ምንጮቹ አድንቀዋል፡፡ አስቻለው ከሦስት ሳምንት በፊት በክፍል ውስጥ በመማር እያለ በአስተዳደሩ ተጠርቶ እንደወጣ አለመመለሱን አክለው የገለጹት ምንጮቹ፤ ውሳኔው በኾነ መልኩ ለኮሌጁ ማኅበረሰብ ይፋ ሳይደረግ መቆየቱ ግን ጥያቄ እንደፈጠረባቸው አልሸሸጉም፡፡

Aschalew Exposed
በሌሎች አስረጅዎች እንደሚታየው፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ቀሣጢው አስቻለው ዮሴፍ÷ “እውነተኛውን ወንጌል እንዳልሰበክንና ገና በጨለማ ውስጥ እንዳለን” የሚለፍፉ ፀረ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጀንዳ ያላቸውን አካላት ዓላማ በኅቡእ የሚያስፋፋ የጥፋት መልእክተኛ ነውና ጉዳዩን በድብቅ የመያዙ አስፈላጊነት በርግጥም አሳማኝ ኾኖ አይታይም፡፡ እንዲያውም ግለሰቡ፣ በቤተ ክርስቲያናችን የክህነት ማዕርግ የሚጠራ እና መሳይ-አገልጋይ-ኾኖ የሚታይ በመኾኑ ጉዳዩ ለከፍተኛው ውሳኔ ሰጭ አካል ቀርቦ ሊመረመርና እንደአግባቡም የማያዳግም አስተማሪ ርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ ባለፈው መጋቢት ወር ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት በተወገዱት ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ቦታ በተመደቡት የኮሌጁ አስተዳደር ምክትል ዲን ጎይትኦም ያይኔ ምትክ፣ መ/ር ሰሎሞን ኃይለ ማርያም መመደባቸው ታውቋል፡፡

Mmr. Solomon Hailemariam

የአስተዳደር ምክትል ዲኑ መ/ር ሰሎሞን ኃይለ ማርያም

ከ1984 ዓ.ም. አንሥቶ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ልዩ ልዩ መምሪያዎች እና ድርጅቶች በጸሐፊነት እንዲኹም በሠራተኛ አስተዳደር ሓላፊነቶች የሠሩት መ/ር ሰሎሞን፤ ከኮሌጁ በሥነ መለኰት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ የድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ እና የኹለተኛ ዲግሪ ምሩቅ እንደኾኑ ተገልጧል፡፡

 

 

 

 

Advertisements

One thought on “የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ: የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጁን ተማሪ አባረረ፤“ቤተ ክርስቲያን በማታውቃቸው እንቅስቃሴዎች መገኘቱ ተረጋግጧል”/ኮሌጁ/

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: