የቀድሞው የአ/አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ: የሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ዓምባገነናዊና አማሳኝ አመራር በቀድሞው ዋና ሓላፊ ሲፈተሽ

“ሀገረ ስብከቱ ልምድ ባለው ረዳት ሊቀ ጳጳስ የቅርብ ክትትል እና የትምህርት ዝግጅትን፣ ሞያዊ ብቃትን፣ ልምድንና መንፈሳዊነትን መሠረት አድርጎ በሚገባ በተዋቀረ የአስተዳደር ጉባኤ እስካልተመራ ድረስ፥ የሥራ ብልሽቱ እና ተበዳይ አልቃሹ እየበዛ እንደሚሔድ እርግጠኛ ነኝ፡፡” 

/መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድ ይፍራው፤ የቀድሞው የሀ/ስብከቱ የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ሓላፊ/

*          *          *

የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት በኾነው በአዲስ አበባ፣ በመጋቢት ወር የተደረገውን የሥራ አስኪያጅ እና የዋና ክፍሎች ሓላፊዎች ለውጥ ተከትሎ ጥያቄዎች እየተነሡ ነው፡፡ የመጀመሪያው፥ ሓላፊዎቹ በፓትርያርኩ ቀጥተኛ ውሳኔና ከልዩ ጽ/ቤታቸው በወጡ ደብዳቤዎች የተነሡበትና የተመደቡበት መንገድ፣ ቀደም ሲል ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ የተሠራውን ስሕተት የሚደግምና የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ተጠሪ የሆነለትን የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ሥልጣን የሚጋፋ መኾኑ ነው፡፡ ኹለተኛው፥ የአህጉረ ስብከት ማዕከል በኾነው አዲስ አበባ ምደባው፣ ብቃትንና ልምድን መሠረት ያደረገ ኹሉን አካታች መኾን ሲገባው ቀድሞም የነበረውንና ቤተሰባዊ እስከመኾን የደረሰውን የአንድ ወገን ብዙኅነት ያስቀጠለ ነው፤ የሚለው ትችት ነው፡፡

ሦስተኛውና ዋነኛው ጥያቄ፥ ርምጃው የሀገረ ስብከቱን የመዋቅር፣ የአደረጃጀት እና የአሠራር ለውጥ በሚያግዝ መልኩ ከተጠያቂነት ጋር አለመፈጸሙ ነው፡፡ “የተወገዱት ሓላፊዎች አጥቢያዎችን እንክት አድርገው የበሉና ቤተ ክርስቲያኒቱን ያራቆቱ ናቸው፤” የሚሉ ተቺዎች፤ ከማንኛውም ሓላፊነት ታግደው፤ በደላቸው ከሕግ እና ከዲስፕሊን አንጻር ታይቶ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ይጠይቃሉ፡፡ ይኸውም ጋንግሪን ወደ መኾን ደረጃ የከፋውን የሙስና፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ዕጦት ለመቅረፍ አብነታዊ እንደሚኾን ያምናሉ፡፡ በአዲስ መልኩ ተመድበው የሚመጡ ሓላፊዎችን በጥቅመኝነት የሚያበሳብሱ ነባር አማሳኞች አኹንም በሀገረ ስብከቱ እንዳሉ የሚጠቅሱ ሲኾን፤ የተጠያቂነት ሥርዐቱ ለእኒኽም የመታረም ዕድል በመስጠት የራሱ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይገልጻሉ፡፡

ለሦስቱም ችግሮች ቀዳሚው የመፍትሔ ርምጃ፣ እንደ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ድንጋጌ ሓላፊነትን ከተጠያቂነት ጋር የሚገልጽ፤ የፓትርያርኩንና የረዳት ሊቀ ጳጳሱን ድርሻ ቆጥሮ የሚያሳውቅ ልዩ ቋሚ መተዳደርያ ደንብ ማዘጋጀት እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡ የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም አጀንዳውን ያሳደረው በዚኹ መንፈስ ነበር፡፡ በየዕለቱ የቅርብ ክትትል የሚጠይቀው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በፓትርያርኩ ምርጫና በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ የሚካሔደውን የረዳት ሊቀ ጳጳስ ምደባ በእጅጉ በሚሻበት ኹኔታ ውስጥ ይገኛል፡፡

ሀገረ ስብከቱ፥ የአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያት፣ ፍትሕ ፈላጊ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ጉዳያቸውን የሚሰማላቸው አጥተው በየዕለቱ ሲጉላሉ የሚታዩበት እንደኾነ የሚገልጹ ወገኖች፤ የአስተዳደር ጉባኤውም ከሥራ አስኪያጁ ጀምሮ የትምህርት ዝግጅትን፣ ሞያዊ ብቃትን፣ ልምድንና መንፈሳዊነትን መሠረት በማድረግ በፓትርያርኩ መመሪያ እና በረዳት ሊቀ ጳጳሱ አስፈጻሚነት ዳግመኛ መዋቀር እንዳለበትና ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጋር የተቋረጠው ግንኙነቱም ወደ መደበኛነቱ ተመልሶ ሊጠናከር እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

Melake Tsion Aba Hiruy Wodyeferaw
መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው፣
በቀድሞው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ሓላፊ በመኾን ከየካቲት 2007 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 2008 ዓ.ም. ድረስ ለዐሥር ወራት ሠርተዋል፡፡ “ሊቀ ጳጳስ የሌለበት ሀገረ ስብከት መኖር የለበትም፤” የሚሉት መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ፥ “ፓትርያርኩ የአስተዳደር ጉባኤውን ሰብስበው ያለውን ችግር በየዕለቱ መጠየቅና መረዳት እስካልቻሉ ድረስ በሥራ አስኪያጁ ሪፖርት ብቻ በሀገረ ስብከቱ አጥቢያዎች፣ ካህናት እና ምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ ሊአገኙት ይችላሉ ብዬ አላምንም፤” ይላሉ፡፡

“አዲስ አበባ የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ስለሆነ፤ ወጥ እንዲሁም ሓላፊነትን ከተጠያቂነት ጋር የሚገልጽ ቋሚ የሆነ ሕግ እስከሚዘጋጅ ድረስ ባለበት ይቆይ፤” የሚለው የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ለመልካም እንደኾነ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ቢያምኑም፤ ይግባኝ ሰሚ የሌለበት የግል ተቋም እስከሚመስል ድረስ በቀድሞው ሥራ አስኪያጅ ግፍ ሲፈጸም በማየታቸው፤ እንደ ቀድሞው ሊቀ ጳጳስ መመደቡ ጥሩ እንደሆነ ለራሳቸው ለሥራ አስኪያጁ ተናግረው እንደነበር ያወሳሉ፡፡ ይህም እምነታቸው በሥራ አስኪያጁ ዘንድ “በእጅጉ እንደ ጠላት እንድታይ አድርጎኛል፤” ይላሉ፡፡

የቀድሞው ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤ ድኻውን ሠራተኛ እንደፈለጉ ከደረጃ እንዲያወርዱ፤ ያለደረጃ እንዲያሳድጉ፤ ያለአግባብ ከሥራቸው እያፈናቀሉ እንዲያስለቅሱ፤ በሀገረ ስብከቱ ሀብትና ንብረት እንዳሻቸው ፈላጭ ቆራጭ እንዲሆኑ ያደረጋቸው የሊቀ ጳጳስ አለመኖር ብቻ ሳይኾን ከአስተዳደር ጉባኤው ጋርም ለመሥራት ባለመፈለጋቸው ነው፡፡ ሥራ አስኪያጁ፣ ከየአድባራቱ ተጣርተው በሚመጡ ሪፖርቶች ላይ የአስተዳደር ጉባኤውን ሰብስበው እያወያዩ በመወሰን ፈንታ አፍነው ይይዛሉ፡፡ በዚኽም ሳቢያ በየደብሩ ብጥብጡ በእጅጉ እየሰፋ በመሔዱ ካህናቱም ሆነ ምእመናኑ ብሶታቸውን ለመግለጽና ጩኸታቸውን ለማሰማት ሀገረ ስብከቱን ሲያጨናንቁና ሰሚ አጥተው ሲያለቅሱ ይውላሉ፡፡

ይልቁንም የቀድሞው ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ፤ ሠራተኛ ከቢሮ ከወጣ በኋላ በምሽት እየገቡ ለቤተ ክርስቲያን ሳይኾን ለግላቸው ያለታዛቢ ያሻቸውን ይሠራሉ፡፡ የአስተዳደር ጉባኤ ሳይሰበሰብና በአጀንዳ ተቀርፆ ውይይት ሳይካሔድበት ቃለ ጉባኤ ተሠርቶ እንዲፈረምበት የጉባኤውን አባላት ይጫናሉ፡፡ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ እንደሚጠቅሱት፥ “በስብሰባ ያልተወያየንበትን አልፈርምም” በማለታቸው ከሥራ አስኪያጁ ጋር ቅራኔአቸው እየሰፋ ሔዷል፡፡

ሥራ አስኪያጁ በሚመሯቸው የአስተዳደር ጉባኤው ስብሰባዎችና ለተለያዩ ጉዳዮች በሚቋቋሙ ኮሚቴዎች ላይም ቢኾን፤ የራሳቸውን መናገርና ቃላት ማሣመር ብቻ እንጂ ሌሎች ሲናገሩም ኾነ የተሻለ ሐሳብ ሲያመጡ መስማትን ፈጽሞ እንደማይሹ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ይገልጻሉ፡፡ በአጀንዳዎች ላይ፣ ሥራ አስኪያጁን በመደገፍ ብቻ ሳይሆን የማምንበትንና ትክክል መስሎ የታየኝንም ሳልፈራ ስለምናገር ያዝኑና ይበሳጩ ነበር፤ ያሉት መልአከ ጽዮን በተለይም፤ ሥራ አስኪያጁ በዋና ጸሐፊነት ደርበው ይሠሩ የነበረበት የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር የ160 ሚሊዮን ብር የሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክት ክለሳ በአስተዳደር ጉባኤው እንዲጸድቅ በቀረበበት ወቅት የጉባኤውን አቅምና ሥልጣን የሚመለከት ጥያቄ በማንሣቴና ጉባኤውም ጥያቄዬን ተቀብሎ ለሥራ አስኪያጁ የማይመች ውሳኔ በማሳለፉ ጥላቻቸው በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን እንዲኽ ያስረዳሉ፡-

ትልቁና ዋናው ለዚህ ያበቃዎት፤ ከ160 ሚልዮን ብር በላይ የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሕንጻ ሥራ ፈቃድ የያዘ ፕሮጀክት እንዲጸድቅልዎ በማሰብ ለአስተዳደር ጉባኤ ለውይይት በቀረበበት ወቅት እኔ፥ ይህን ያህል ገንዘብ የያዘ ፕሮጀክት እኛ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ማየትና መወሰን እንችላለን ወይ? አቅማችንስ ይፈቅዳል ወይ? ከሀገረ ስብከቱስ ይህን ፕሮጀክት ተመልክቶ የሚረዳ ባለሞያና የኮንስትራክሽን ልምድ ያለው ሰው ከእኛ ውስጥ አለ ወይ? ብዬ ጠይቄአለሁ፡፡ በእውነቱ፥ ገንዘቡም እጅግ ብዙ ከመሆኑ አንጻር የአስተዳደር ጉባኤው አባላት ጥያቄዬን ተቀብለው የጉባኤውን አቅምና ድርሻ ያወቀና የተገነዘበ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

የግንባታ ፕሮጀክቱን ለመፍቀድ ከሕግም ከሞያዊ አቅምም አኳያ እንደማይችል የተረዳው የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ፤ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጨረታ በማውጣት በገለልተኛ ባለሞያ አስጠንቶ እንዲወስን ነበር የወሰነው፡፡ እርስዎ ግን፣ ይህ ውሳኔ ባልጠበቁት መልኩ በመወሰኑና ሐሳቡንም በመጀመሪያ ያመጣሁት እኔ ስለነበርኩኝ ከዚያ ቀን ጀምሮ በእኔ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እንዲአድርብዎት ሆኗል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አቅምን ከማገናዘብ ጋር ሓላፊነትን በትክክል ለመወጣት ስል ሐሳቤን በመግለጼ እኔም እጅግ በማንነቴ እኮራበታለሁ፤ እርስዎም ትክክለኛ ውሳኔ የተወሰነ መሆኑን አውቀውት ትምህርት ሊወስዱበት ሲገባዎ እንደ አለመታደል ሆኖ ጥላቻን ፈጠረብዎ፡፡

የአድባራት አለቆችን ዝውውር ከጥቅመኝነትና ነቀፌታ ነፃ ስለማድረግ፤ ለሀገረ ስብከቱ በሽልማት የተሰጠ ጄኔሬተር ገቢ ሳይደረግና የአስተዳደር ጉባኤው ሳይወስን ወዳጅነትን ለመሸመት ሲባል ለሌላ መሰጠቱ፤ በሀገረ ስብከቱ ገንዘብ ለግለሰቦች መኪና ገዝቶ ስለመሸለም ሐሳብ መነሣቱ፤ የሊቀ ጳጳሱ መኪኖች የሥራ አስኪያጁ መዘነጫና የማነ ማለት እኔ ነኝ ለሚሉ የጥቅም ጓደኞቻቸው መንሸራሸርያ መኾናቸው እንዲኹም የተጠያቂነትን ሥርዐት የሚያዛባ ተደራራቢ ሥልጣናቸው መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ከቀድሞው ሥራ አስኪያጅ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ጋር ከተወዛገቡባቸው ጉዳዩች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡

ሊቀ ማእምራን የማነ፥ከመንግሥት አካላት ጋር ውያለሁ፤ ከሚኒስትሮች ጋር አብሬ ሠርቻለሁ፤ ሚኒስቴር እገሌ አጎቴ ነው፤ ከአቦይ እገሌ ጋር ራት በልቼ፤ ምክትል ኮሚሽነር የቅርብ ዘመዴ ወዳጄ ነው፤” እያሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩም የታዘቧቸው መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ፣ “ከሚኒስትሮች ጋር ከሠሩና ከባለሥልጣኖች ጋር ከዋሉ ምነው እንዲህ ዓይነቱን ኢሰብአዊ የሆነ አሠራር የሚሠሩት? የተማርኩት ከዚያ ነው ሊሉን ነው?” ሲሉም ጠይቀዋቸዋል፡፡

መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ፣ ለሊቀ ማእምራን የማነ የሥራ ዘመን አሳፋሪና አሳዛኝ የሚሉት በልጃቸው ሕክምና እና በሽልማት ስም ከየአጥቢያው ወርቅ እና ብር መሰብሰባቸውን ነው፡፡ ወርቅ እና ብሩን ከየክፍላተ ከተማው እና ከየአጥቢያው ለመሰብሰብ የቻሉት ለቤተሰባዊ ችግራቸው ስለታዘነላቸው ወይም በአመራራቸው ስለተወደዱ ሳይኾን በፍርሃትና ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ እንደነበር መልአከ ጽዮን ይናገራሉ፡፡ “ለእንዲህ ዓይነቱ ድፍረትዎ ሰው ዝም ቢል እግዚአብሔር ዝም አይልምና አንገትዎን የሚያአስደፋ ነገር እንዳያመጣብዎት ቢአስቡበት መልካም ነው፤” ሲሉ ከአምስት ወራት አስቀድሞ ለሥራ አስኪያጁ በአድራሻ በጻፉላቸው ደብዳቤ አሳስበዋቸው ነበር፡፡

ሀገረ ስብከቱ ልምድ ባለው ረዳት ሊቀ ጳጳስ የቅርብ ክትትል እና በሚገባ በተዋቀረ የአስተዳደር ጉባኤ እስካልተመራ ድረስ፥ የሥራ ብልሽቱ እና ተበዳይ አልቃሹ እየበዛ እንደሚሔድ እርግጠኛ ነኝ፤ የሚሉት መልአከ ጽዮን፤ “ድርጊትዎ ጊዜውን ጠብቆ ብድሩን በዕጥፍ እንደሚመለስልዎት አልጠራጠርም፤” ብለው ነበር – በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ለቀድሞው ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ባደረሷቸው ደብዳቤ፡፡

የቀድሞው ሥራ አስኪያጅም፣ ተራማጅ እና የለውጥ መሪ ነኝ እያሉ በየአጋጣሚው እንደ መደስኮራቸው ምክሩን ሰምተው አካሔዳቸውን መመርመር ይገባቸው ነበር፡፡ በምትኩ የያዙት ግን በቂምና በጥላቻ ከሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ሓላፊነት ወደ ክፍለ ከተማ ያወረዷቸውን መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራውን በየምክንያቱ ማሳደድ ነበር፡፡ በመጨረሻም ከዓመት በፊት በሕገ ወጥ ምደባቸው በር በርግደው እና የግቢ ጥበቃ ገፍትረው ከገቡበት ሀገረ ስብከት፣ ባለፈው መጋቢት ወር በቀንደኛ ሌብነት ተገሥጸው የመባረር ያኽል ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡

ዛሬ ጥያቄው፣ የሀገረ ስብከቱን ተቀማጭ ገንዘብ ውለታ መግዣ እያደረጉና ንብረቱን አላግባብ እያባከኑ በሥልጣን ለመሰንበት ያደርጉት የነበረ መራወጥ ሳይኾን፤ እንደ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ ካሉ የለየላቸው አማሳኝ ግብረ አበሮቻቸው ጋር የፈጸሙት ተግባር በአግባቡ ተገምግሞና ተጣርቶ ለሕግ ተጠያቂነት የመቅረባቸው ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም፤ በሀገረ ስብከቱ የአራት ተሽከርካሪዎች ግዥና የአጠቃቀም ብክነት፤ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ልዩነት የታየበት የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር የግንባታ ማሻሻያ፤ ከቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ካህናትና ሠራተኞች በምስጋና ሽፋን፤ ከእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በሕክምና ርዳታ ስም በመዘበሩት በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠር ብር ማሳያነት መጋለጣቸው እንደቀጠለ ነው፡፡

የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ሓላፊ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው፣ “ነገ ከነገ በኋላ እውነተኛ ዳኛ ሲገኝ ታሪክ ይፈርዳል” ሲሉ ለሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ማሳሰቢያም ማስጠንቀቂያም የሰጡበት ደብዳቤ ከተጻፈ ወራትን ያስቆጠረ ቢኾንም፤ ይህን ጥረት ከማገዝ አኳያ ባለው ተገቢነትና አስፈላጊነት በቀረበበት መልኩ ተስተናግዷል፡፡ በጥሞና ተመልክተው ሐሳብና አስተያየት በመስጠት እንዲወያዩበት ተጋብዘዋል፡፡


ቀን፡- ኅዳር 12 ቀን 2008 ዓ.ም

Lique Maemeran Yemane ZeMenfes KidusAba Hiruy complaints
ለ፡- ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ እና የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ

አዲስ አበባ፤

ጉዳዩ፡ያለሕግ በሌለዎት ሥልጣን የሥራ ሽግሽግ በሚል በቁጥር 653/3/08 በቀን 3/3/08 ዓ.ም ደረጃውን ባልጠበቀ መልኩ የተጻፈውን ደብዳቤ የምቃወመውና የማልቀበለው መኾኑን ለኹለተኛ ጊዜ ስለማሳወቅ ይኾናል፤

የሰብአዊ መብቶች መከበር ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ትኩረት ባገኙበት፤ ሰዎች ሥራቸውን ተሸማቀውና አለቃቸውን በመፍራት ሳይሆን ግዴታቸውንና መብታቸውን ዐውቀው እንዲሠሩ ጥረት በሚደረግበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ ይህን ጽሑፍ ለኹለተኛ ጊዜ ለመጻፍ የተገደድሁት፣ ሥራዬን በታማኝነት ከምሠራበት ያለምንም ምክንያት በዓምባገነንነት እና በማን አለብኝነት ከደረጃ በማውረድ ከሀገረ ስብከት ወደ ክፍለ ከተማ በተራ ሠራተኛነት ተቀይረዋል በሚል የተጻፈብኝ ደብዳቤ በጣም ስላሳዘነኝ ነው፤ በተጓዳኝም ግርምት ስለፈጠረብኝ ነው፡፡

ያሳዘነኝ፥ ቤተ ክርስቲያናችን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ ስለ ሰው ቀርቶ የራሳቸውን ማንነት እንኳን በማያውቁና ባልተረዱ፤ የግል ጥቅማቸውን እንጂ እውነትን በማይደፍሩ ይሉኝታ በሌላቸው ሰዎች እየተመራች ከመቼውም ጊዜ በላይ በመልካም አስተዳደር ዕጦትና ብልሽት ቁልቁል እየሔደች መኾኑ ነው፡፡ በስምና በቃላት ብቻ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነን በሚሉት በእነኝህ ዓይነቶቹ ግለሰቦች መመራቷን ከቀጠለች ወደፊት የሚደርስባት አደጋና ውድቀት ከአሁኑ እጅግ የበለጠና የከፋ እንደሚሆን ስላሳሰበኝ ነው፡፡

ግርምት ሊፈጥርብኝ የቻለው ደግሞ፤ አብረን በምንሠራበት ወቅት አንድም ቀን ለማይሆን ነገር ተባባሪና  የሕገ ወጥ ጥቅም ተካፋይ ለመሆን ባለመፍቀዴ፤ ጥቅመኝነትንና ወገንተኝነትን እንጅ እውነትን ሊደፍሩ በማይወዱ መሪዎች ነን ባዮች የተፈጸመብኝ በደል በመሆኑ ነው፡፡ ሊቀ ማእምራን የማነ፥ እኔን ከደረጃ አውርደው ከአጠገብዎ ለማሸሽ የፈለጉበትና የደፈሩበት ምክንያቱ ምን እንደኾነ እኔ ተረድቻለሁ፡፡ ምናልባት ያላወቅሁ ከመሰልዎና ካልተረዱት በጥቂቱም ቢኾን እንደሚከተለው ልግለጽልዎት፡፡


ገና ወደ ሀገረ ስብከቱ ተመድበው ሲመጡ ጀምሮ፣ ሥራዎ ሰላም የሰፈነበት እና የፍቅር ሥራ እንዲሆንልዎ፤ ቅዱስነታቸውም ሁልጊዜ እንደሚናገሩት የመልካም አስተዳደር ሥርዓት እንዲሰፍን ከሚመኙ ሰዎች አንዱ ስለነበርኩኝ፤ በጊዜው ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም ዕጦት እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቴ ለማረጋጋት ስል ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ጋር በመቀራረብ እንድትወያዩና ተመካክራችሁ በአንድነት ለቤተ ክርስቲያንና እርስዎንም አምነው ለሾምዎት ለቅዱስ አባታችን እንዲሁም ለምትመሩት ካህናት እና ሕዝበ ምዕመናን ሰላም ሲባል ሁሉን ትታችሁ በሰላም እንድትሠሩ ሁል ጊዜ እርስዎንም ሆነ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስን እየቀረብኩኝ አነጋግራችሁና ለማቀራረብ እደክም እንደነበረ ያውቃሉ፤ ነገር ግን በራስዎ ካለመተማመንና በራስዎ መመራት ካለመቻል የተነሳ ይመስለኛል ለሰላሙ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ እኔን ወገንተኛ አድርገው ከማየትዎም ባሻገር ሰላሙ ተፈጥሮ ከሊቀ ጳጳሱ ከብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ጋራ አብሮ መሥራት አስፈላጊ ስላይደለ ዐርፈው ተቀመጡ የሚል ማስጠንቀቂያ ተነገሮኝ ነበረ፡፡ ሰላምን የማይወድ ሰው ዓላማው፥ የሥራ ለውጥ ማምጣት ሳይኾን የሥራ ነውጥ መፍጠር ነው፡፡

እርስዎም አገርም እንደሚያውቀው ሁሉ፤ በተለይ በዚህ በእርስዎ የአስተዳደር ዘመን በየአድባራቱ መቼም ሆኖና ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ችግሮች እየተፈጠሩ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም ከሀገረ ስብከቱ ወደ የአድባራቱ ልኡካን ተልከው ችግሮች ተጣርተው ሪፖርታቸው ከመጣና እጅዎ ከገባ በኋላ ወዲያው በአስተዳደር ጉባኤ ታይቶ ውሳኔ ሊሰጠው ሲገባ ጀሮ ዳባ ልበስ ሆኖ አፍነው ይይዙታል፡፡ እኔም በተለያየ ጊዜ፣ ለምን በጉባኤ አይተን መፍትሔ አንሰጣቸውም እያልኩ እርስዎንም ሆነ የሚመለከታቸውን ሰዎች እናገር ነበር፡፡ እርስዎ ግን በአስተዳደር ጉባኤ ታይቶ መፍትሔ እንዲሰጥ ፈቃደኛ ካለመሆንዎ ባሻገር በየደብሩ ብጥብጡ እጅግ እየሰፋ በመሔዱ ካህናቱም ሆነ ሕዝበ ምዕመናኑ ብሶቱን ለመግለጽ ጩኸቱን ለማሰማት ሀገረ ስብከቱን ሲአጨናንቅና ሰሚ አጥቶ ሲአለቅስ ይውላል፡፡ ይህ ደግሞ የሥራ ለውጥ ሳይኾን አኹንም የሥራ ነውጥ ይባላል፡፡

እንደሚያውቁት ሁሉ፤ በአስተዳደር ጉባኤ በሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ፣ እርስዎን በመደገፍ ብቻ ሳይሆን የማምንበትንና ትክክል መስሎ የታየኝን ሳልፈራ ስለምናገር ብዙ ጊዜ የእኔ አቋም ለእርስዎ አይመችዎትም፤ በዚኽም ሲበሳጩና ሲአዝኑ ይታዩ ነበር፡፡ መሪ የሆነ ማንኛውም ሰው የፈለገውን እንደዳሻው ማድረግና መናገር ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎች ምን ይላሉ፤ ምን ያስፈልጋቸዋል፤ ብሎ ማሰብና ሰዎች ሲናገሩም መስማት ግድ ይለዋል፡፡ እርስዎ ግን የራስዎን መናገር እና ቃላት ማሳመር ብቻ እንጂ ሌሎች ሲናገሩም ሆነ የተሻለ ሐሳብ ሲአመጡ መስማትን ፈጽሞ አይሹአትም፡፡ ለዚህም ነው እኔን በማን አለብኝነት ለመቀየር የተገደዱት፡፡

ትልቁና ዋናው ለዚህ ያበቃዎት፤ ከ160 ሚልዮን ብር በላይ የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሕንጻ ሥራ ፈቃድ የያዘ ፕሮጀክት እንዲጸድቅልዎ በማሰብ ለአስተዳደር ጉባኤ ለውይይት በቀረበበት ወቅት እኔ፥ ይህን ያህል ገንዘብ የያዘ ፕሮጀክት እኛ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ማየትና መወሰን እንችላለን ወይ? አቅማችንስ ይፈቅዳል ወይ? ከሀገረ ስብከቱስ ይህን ፕሮጀክት ተመልክቶ የሚረዳ ባለሞያና የኮንስትራክሽን ልምድ ያለው ሰው ከእኛ ውስጥ አለ ወይ? ብዬ ጠይቄአለሁ፡፡ በእውነቱ፥ ገንዘቡም እጅግ ብዙ ከመሆኑ አንጻር የአስተዳደር ጉባኤው አባላት ጥያቄዬን ተቀብለው አቅማቸውንና ድርሻቸውን ያወቀና የተገነዘበ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

የግንባታ ፕሮጀክቱን ለመፍቀድ ከሕግም ከሞያዊ አቅምም አኳያ እንደማይችል የተረዳው የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤም፤ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጨረታ በማውጣት በገለልተኛ ባለሞያ አስጠንቶ እንዲወስን ነበር የወሰነው፡፡ እርስዎ ግን፣ ይህ ውሳኔ ባልጠበቁት መልኩ በመወሰኑና ሐሳቡንም በመጀመሪያ ያመጣሁት እኔ ስለነበርኩኝ ከዚያ ቀን ጀምሮ በእኔ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እንዲአድርብዎ ኾኗል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አቅምን ከማገናዘብ ጋር ሓላፊነትን በትክክል ለመወጣት ስል ሐሳቤን በመግለጼ እኔም እጅግ በማንነቴ እኮራበታለሁ፤ እርስዎም ትክክለኛ ውሳኔ የተወሰነ መሆኑን አውቀውት ትምህርት ሊወስዱበት ሲገባዎ እንደ አለመታደል ሆኖ ጥላቻን ፈጠረብዎት፡፡

በተለይም እርስዎ ወደዚህ የአስተዳደር ሥራ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ፣ በተለያዩ አድባራት ለተፈጠሩ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት የአስተዳደር ጉባኤ ባለመሰብሰብዎና መፍትሔ ባለመሰጠቱ ችግሩ በበዛ ቁጥር በየደብሩ ሰዎችን ማሳሰሩን እንደመፍትሔ ሲወስዱ ቆይተዋል፡፡ ይህ ደግሞ የእርስዎ እና የሀገረ ስብከቱ የአመራር ድክመት ስለመሆኑ፤ በይበልጥም የችግሩ መበራከት አደጋ የሚያመጣ መሆኑን በተደጋጋሚ ስለምነግርዎት ሊዋጥልዎት ባለመቻሉ ወደ ጥላቻ ወስደውታል፡፡

ይልቁንም በሀገረ ስብከቱ እንደተለመደው ማክሰኞ እና ኃሙስ የአስተዳደር ጉባኤ ሰብስበው ከማወያየት እና መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ፣ ቀን ሥራ ሳይገቡ እንደፈለጉ በመሆን ባለጉዳዩን ሲያጉላሉ ከዋሉ በኋላ ሠራተኛው ከቢሮ ሲወጣ ከዐሥራ አንድ ሰዓት በኋላ ቢሮ እየገቡ ያለታዛቢ ለቤተ ክርስቲያኗ ሳይሆን ለግልህ ያሻዎን ብቻ ለመሥራት በመፈለግዎ፤ የአስተዳደር ጉባኤውንም ለመሰብሰብ እንደ ጦር  ስለፈሩት ሥራዎች እየተበላሹ ከመምጣታቸው በፊት እነግርዎት ነበረ፡፡ ይኹንና እርስዎ ብቻ መናገርን እንጂ እንዲነገርዎት ስለማይፈልጉ ጥላቻ ፈጠረብዎት፡፡

ጉባኤ ሳይሰበሰብ፤ በአጀንዳ ተቀርጾ ሳንወያይበት ቃለ ጉባኤ ተሠርቶ እንድፈርም ሲቀርብልኝ፣ በስብሰባ ያልተወያየንበትና ሕግን ያልጠበቀ በመሆኑ አልፈርምም እያልኩኝ ብዙ ጊዜ በመመለሴ ቅሬታ ሊአሳድርብዎት ችሏል፡፡

ከየትኛውም ጊዜ በተለየ መልኩ ማንኛውም ሠራተኛ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ነጻነቱን የተገፈፈበትና የመናገር መብቱ የተነፈገበት፤ የሰው ልጅ ሰው መሆኑ የተረሳበት ጊዜ እስኪመስል ድረስ ያለአግባብና ያለፈቃዱ ከቦታው እየተፈናቀለ ባለበት ሁኔታ እርስዎ ግን፤ ለሚመስልዎት ደረጃውን ያልጠበቀ ዕድገት፤ በሺሕዎች የሚቆጠር የደመወዝ ጭማሬ፤ በክፍት ቦታዎች በሚፈልጉትና በሚያስደስትዎት ሁኔታ ያለጉባኤ ውሳኔ መቅጠርንና መመደብን ተያይዘውታል፡፡ አቤት ባዩ ከመቼውም ጊዜ በላይ የበዛበት ዘመን በመሆኑ ይህ ያለሕግ ሰዎችን መቀየር፤ መቅጠር፤ ማገድ፤ ማሳደግ፤ ወዘተ…የመሳሰሉ ነገሮች ሁሉ ቆመው በአስተዳደር ጉባኤ እየታየና እየተወሰነ እንዲሠራ በተደጋጋሚ ግፍ አይብዛ፤ ፍትሕ የሰፈነበት ሥራ እንሥራ ብዬ በመጠየቄና በመናገሬ ሊዋጥልዎ አልቻለም፡፡

በአስተዳዳሪዎች ቅያሬ ዙሪያ፥ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ጊዜ ወስደን አጥንተን ያለምንም አድልዎ እና ቅሬታ ማዘዋወር እንጂ አንድም አስተዳዳሪ ከአሁን ቀደም እንደሚነገረው ተሸጥኩ፤ ተለወጥኩ እንዲልና እኔም መታማት እንደማልፈልግ ሀገረ ስብከቱም መታማት እንደሌለበት ብዙ ጊዜ እንደተነጋገርን ያውቃሉ፡፡ በመሆኑም የእኔ ሐሳብና አቋም እርስዎ በሚፈልጉት መንገድ ባለመሔዱ ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ እንደፈለጉትና እንደአሰቡት መቀያየር ባለመቻልዎ ከፍተኛ ቅሬታ አሳድሮዎብታል፡፡ ስለሆነም ይህን ደብዳቤ ሊጽፉብኝ ችለዋል፡፡

አንድ ባለሥልጣን ታች ወርዶ ፀሐፊ ከላይ ሆኖ ሓላፊ(ሥራ አስኪያጅ) ኾኖ መሥራት ሕግና መንግሥት ባለበት ሀገርና በየትኛውም ተቋም አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ እርስዎ ግን ከላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ኾነው በሺሕ የሚቆጠር ደመወዝም አበልም ይበላሉ፡፡ ወረድ ብለው ደግሞ የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፀሐፊ በመሆን ደመወዝም አበልም ይበላሉ፡፡ በጣም ይገርማል፡፡ እንዲያው በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዕውቀት ያላቸውና በቤተ ክርስቲያን ሞያ ብዙ የደከሙና የተማሩ የሉም? አልቀዋል ማለት ነው? እርስዎ ብቻ ነዎት ምሁሩ ማለት ነው? ወይስ ነጻነታቸውና ማንነታቸው በዚህ በእርስዎ ዘመን ተወስዶባቸዋል ማለት ነው? እንዲያው በግል የተሰጠዎ ልዩ ጊፍት እስኪመስል ድረስ ምነው እኔ ብቻ ነኝ አሉ? እስኪ ጭንቅላትዎ ያስብ፤ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ምሁራን ለሀገራቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው ትርፍ፣ ሕዝብ እና ኹለተኛ ዜጋ ሆነዋል ማለት ነው? መልሱን ለእርስዎና ይህ ደብዳቤ ለሚደርሳቸው አንባብያን ሁሉ፤ እንዲሁም ወቅትና ጊዜ ጠብቆ ፍርድንና የሥራ ዋጋን ለሚከፍል ጌታ ልተወው፡፡

እባክዎ ይህ ኹሉ ግፍ መቼም ቢሆን አይለቅዎትምና ግፉ በቶሎ ሳይደርስብዎ የዕለት ጉርስ አጥተው የሚንገላቱ ንጹሐን ኢትዮጵያውያንና የቤተ ክርስቲያን ምሁራን በተለይም በዚህ የሥራ አስኪያጅነትዎ ዘመን እየተንገላቱ፤ እየተራቡ፤ እያለቀሱ ያሉ ሰዎች በዝተዋልና አንዱ ይብቃዎ፡፡ እንዲያው ሃይ ባይ ባለሥልጣን ቢያጡም እንኳ እግዚአብሔርን በመፍራት ለቤተ ክርስቲያን ዐይናማ ምሁራን ሲሉ አንዱን ሥራ መርጠው ቢይዙ ለመጪው ዘመንዎ ጥሩ ይሆንልዎታል የሚል አቋሜን ስለተረዱ ቅር ተሰኝተዋል፡፡

ሌላው ያስከፋዎ፤ የሀገረ ስብከቱ መኪኖች ከተገዙ በኋላ ለግዢው ለደከሙ ሰዎች በሚል በሃገረ ስብከቱ ገንዘብ የግል ወዳጅ ወይም ጥቅም ለማፍራት፤ በዚህ ስምም የእንካ ለእንካ ሥራ ለመሥራት በአስተዳደር ጉባኤው ፊት “የመኪና ሽልማት ቢገዛላቸው” ብለው ተናግረዋል፡፡ እኔም፤ ይህን ኮሚቴው በጥናቱ ይሥራው፤ እርስዎ ኮሚቴ ካቋቋሙ ሥራውን ለኮሚቴው ቢተውት ብዬ በጉባኤው ፊት ተናግሬአለሁ፤ ኮሚቴውም ከተቋቋመ በኋላ ተሰብስቦ የራሱን ወሳኔ ሲአሳልፍ፥ እንዲህ ዓይነቱ ሽልማት በቅዱስ ፓትርያርኩና በቅዱስ ሲኖዶስ የተከለከለ መሆኑን ጠቅሶ፤ በእርሰዎም ላይ ጥያቄ የፈጠረበት በመሆኑ ትዕዛዝዎን ተችቶ አልፏል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ገንዘብ እንዲህ ዓይነት ሕገ ወጥ ነገር ብንሠራ የሚያስጠይቅ በመሆኑ ሓላፊነት አንወስድም በሚል ኮሚቴው የተናገሩትን ውድቅ በማድረግ ሓላፊነቱን ወደ ራስዎ መልሶታል፡፡ እኔም ከኮሚቴው አባላት አንዱ ስለነበርኩኝ፣ ይህን ያደረገ አባ ኅሩይ ነው፤ በሚል እጅግ እንደተናደዱና እንደተበሳጨህ ዐውቄአለሁ፡፡ ስለሆነም እኔን ለመቀየር የተነሣሱበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡

በዘንድሮው የጥቅምቱ ሲኖዶስ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ እና ቅዱስ ሲኖዶስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን አስመልክቶ፣ ወጥ እንዲሁም ሓላፊነትን ከተጠያቂነት ጋር የሚገልጽ ቋሚ የሆነ ሕግ እስከሚዘጋጅ ድረስ የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ስለሆነ ባለበት ይቆይ፤ ሲል ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መኖሩ ለጊዜው አስፈላጊ አለመሆኑ ታምኖበት መወሰኑ ለመልካም እንደሆነ አምናለሁ፡፡

እርስዎ ግን የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ወደ ጎን ትተው፣ ሀገረ ስብከቱ ይግባኝ ሰሚ የሌለበት የግልህ ተቋም እስከሚመስል ድረስ የሚሠሩትን ግፍ ዐይቼ ሊቀ ጳጳስ ቢኖር እንዲህ እንደፈለጉ ሊሆኑ እንደማይችሉ ስለማምን እንደ ቀድሞው ሊቀ ጳጳስ መመደቡ ጥሩ እንደሆነ ተናግሬ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ እውነትና የማምንበት ስለሆነ አሁንም በርግጠኝነት እናገራለሁ፥ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ቢኖር ኖሮ ድኻውን እንደፈለገዎት መቀያየርና ማስለቀስ እንደማይችሉ እምነቴ መሆኑን ስለተረዱ ይህ የእኔ ሓሳብ በእርስዎ ዘንድ እጅግ እንደ ጠላት እንዲያዩኝ አድርጎዎታል፡፡

ማወቅ ያለብዎ፤ ቅዱስ ፓትርያርኩም ሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ሀገረ ስብከቱ ያለሊቀ ጳጳስ ባለበት ይቆይ ብሎ የወሰነው እርስዎ ድኻውን ሠራተኛ እንደፈለጉ ከደረጃ እንዲያወርዱ፤ ያለደረጃ እንዲያሳድጉ፤ ያለአግባብ ከሥራቸው እያፈናቀሉ እንዲያስለቅሱ፤ በሀገረ ስብከቱ ሀብትና ንብረት እንዳሻዎ ፈላጭ ቆራጭ እንዲሆኑ ተፈቅዶ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ቅዱስነታቸው ሥራ እንደሚበዛባቸው ቢታመንም ሊቀ ጳጳስ እስካልተመደበ ድረስ የአስተዳደር ጉባኤውን ሰብስበው ያለውን ችግር መጠየቅና መረዳት እስካልቻሉ ድረስ እርስዎን ብቻ በማግኘትና የሚናገሩትን በመስማት አምነው የሀገረ ስብከቱን ችግርና በሕዝቡና በካህናቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ ሊአገኙት ይችላሉ ብዬ አላምንም፡፡

የሥራ ብልሽቱ፤ ተበዳይ አልቃሹ እየበዛ እንደሚሔድ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እርስዎ ደግሞ መሰለችዎት ብቻ ካልሆኑ በቀር ቅዱስነታቸውን ማንም እንዲያገኛቸው አይፈልጉም፤ ምክንያቱም እንደሚጋለጡ ስለሚሰጉ፡፡ ወዳጄ ሊቀ ማእምራን አይምሰልዎት፤ አንድ ቀን ቅዱስነታቸው እውነቱን የሚነግራቸውና የሚአስረዳቸው የተገኘና የደረሱበት ዕለት እውነቱ ሲገለጥ መባረርዎት ብቻ አይደለም፤ ዛሬ ከላይ በመሆን እንደሚቀልዱና እንደሚሥቁ ነገ ከአስለቀሷቸው ሰዎች እግር ሥር ሆነው የሚአለቅሱበት ዘመን እንደሚመጣና በፈጸሙት ግፍ ተጠያቂ እንደሚሆኑ፤ ከዚህም ሁሉ በላይ ሁሉን ከሚችል ጌታ እግዚአብሔር ብድሩን ቆመው እያዩ እንደሚከፍልዎት በእግዚአብሔር ርግጠኛ ነኝና ያስቡበት፡፡   

ሊቀ ማእምራን የማነ፥ እርስዎ አዲስ አበባ ከገቡ ብዙ ዓመት እንደሆንዎ ይናገራሉ፡፡ በዘመንዎ አሳፋሪና አስገራሚ የሆነ፤ ለማንም ተደርጎ የማያውቅ ርዳታ አግኝተው እንደማያውቁ ያስታውሳሉ? (ገንዘብ ማዋጣት ባልችልም ጤና ያጡ ቤተሰብዎትን እነሱ ምንም ኃጢአት አልሠሩምና እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዲልክላቸው ጸሎቴ ነው) በሕክምና ስም፤ በወርቅ ሽልማት ስም ከየአጥቢያው የሚሰበሰበው ብር ምን ይባላል? ሰው ወዶኝ፤ የቤተሰብ ችግር በመኖሩ አዝኖልኝ፤ ገንዘቡን እየሰጠኝ ይመስልዎታል? ወይስ ሥልጣንዎን መከታ በማድረግ ችግር ላይ እንዳይጥሉት እርስዎን በመፍራት? እውነቱ ሲነገርዎ ደስ እንደማይልዎት ብረዳም፣ ይህ ድርጊት ሥልጣንን መከታ በማድረግ የሚከናወን የኪራይ ሰብሳቢነት ሥራ መሆኑን ሁሉም የሚያውቀው እንደሆነ እንዲረዱና ጊዜውን ጠብቆ ብድሩ በዕጥፍ እንደሚመለስልዎት አልጠራጠርም፡፡

በሌላ በኩል እስኪ እንዲያው ራስዎን ወይም ማንነትዎን ያዩትና ያወቁት አይመስለኝም፡፡ ከዚህም የተነሳ ቤተ ክርስቲያኗን የመናቅዎ ብዛት እየሠሩ ያሉትን በትንሹ ልንገርዎ፡፡ በ2008 ዓ.ም የጥቅምቱ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላላ ጉባኤ ለሀገረ ስብከቱ በሽልማት የተሰጠ ጄኔሬተር ለሀገረ ስብከቱ ገቢ ሳይሆን፤ ለሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ በሥርዓቱ ቀርቦለት ሳይወሰንና ሳይፈቅድ በማንአለብኝነት የግል ተቋምዎ ይመስል በገዛ ሥልጣንዎ ለሌላ ሀገረ ስብከት ስጦታ ሰጭ ኾነዋል፡፡

????????????????????????????????????

የተገዙ መኪኖች ባለቤት የሌላቸው እስኪመስል ድረስ፣ የማነ ማለት እኔ ነኝ እያሉ በስምዎ ለሚነግዱ ሓላፊዎች መንሸራሸሪያ እየሆኑ ታይተዋል፡፡ ለሊቀ ጳጳሱ ተብሎ የተገዛውን መኪና እርስዎ መያዝዎና እንደፈለጉ የሚዘንጡበት መኾንዎ የበላይ የለብኝም፤ ቆራጭ ፈላጭ እኔ ብቻ ነኝ ብለው ነው፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ ድፍረትዎ ሰው ዝም ቢል እግዚአብሔር ዝም አይልምና አንገትዎን የሚያስደፋ ነገር እንዳያመጣብዎ ቢአስቡበት መልካም ነው፡፡

በሌላ በኩል በጣም የሚገርመኝ፤ እርስዎ በተደጋጋሚ ከመንግሥት አካላት ጋር ውያለሁ፤ ከሚኒስትሮች ጋር አብሬ ሠርቻለሁ፤ ሌላም ብዙ ብዙ ይላሉ፡፡ እንዲያውም፤ ሚኒስቴር እገሌ አጎቴ ነው፤ ከአቦይ እገሌ ጋር ራት በልቼ፤ ምክትል ኮሚሽነር የቅርብ ዘመዴ ወዳጄ በማለት ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ለመኾኑ ድኻውንና ምንም የማያውቁ ምስኪኖችን ለማሸማቀቅ ካልሆነ በቀር እርስዎ ከሚኒስትሮች ጋር ከሠሩና ከባለሥልጣኖች ጋር ከዋሉ ምነው እንዲህ ዓይነቱን ኢሰብአዊ የሆነ አሠራር የሚሠሩት? የተማርኩት ከዚያ ነው ሊሉን ነው?

ብዙ መረጃ ያላቸው ነገሮች ነበሩኝ፡፡ መጻፍ እንደነበረብኝ ባምንም ለአኹኑ በአጭሩ በዚህ ይብቃኝ፡፡ ያለሕግ በሌለዎት ሥልጣን የጻፉብኝን ደብዳቤ ከአሁን ቀደም በ5/3/08 በተጻፈ ደብዳቤ እንዲነሣልኝ ጠይቄዎ መልስ ስለአልሰጡኝ ለኹለተኛ ጊዜ ይህን ደብዳቤ ለመጻፍ ተገድጃለሁ፡፡ ስለዚኽ አኹንም ደረጃዬን ያልጠበቀ ከመኾኑም ባሻገር ነገ ከነገ በኋላ እውነተኛ ዳኛ ሲገኝ ታሪክ ይፈርዳልና ከዚያ በፊት መብቴ ተጠብቆ እንዲነሣልኝ በድጋሜ እጠይቃለኹ፡፡

እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንንና ሀገራችንን ከፈተና ይጠብቅልን፡፡ አሜን፡፡

መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንደይፍራው

ግልባጭ፤

ለቅዲስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት

ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፤

ለመንበረ ፓርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት

ለመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤት አስተዳደር መምሪያ፤

ለሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ዋና ክፍል

ለሀገረ ስብከቱ ሒሳብና በጀት ዋና ክፍል

ለሀገረ ስበከቱ ቁጥጥር ዋና ክፍል

ለሀገረ ስብከቱ ሕግ አገልግሎት ዋና ክፍል፤

 

ለክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር.

ለክቡር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን፣ የፊዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር

ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት

ለሀገር ውስጥ ደኅንነት

ለአዲስ አበባ ደኅንነት ቢሮ

ለአቶ አሰፋ ዐቢዩ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮምሽነር፤

አዲስ አበባ፤

Advertisements

5 thoughts on “የቀድሞው የአ/አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ: የሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ዓምባገነናዊና አማሳኝ አመራር በቀድሞው ዋና ሓላፊ ሲፈተሽ

 1. Anonymous May 10, 2016 at 2:07 pm Reply

  my Goodness ! Aba Hiruy! what are you talking about? are you saying that you are clean from corruption? are you telling us you are educated enough ? I do agree with you about Yemane. why do not you go back to us, as you know, you are not Ethiopian, but American.
  by

 2. garedew May 10, 2016 at 3:37 pm Reply

  እኔ እምለው አባ ህሩይን ምስክር እድርጋችሁ ስትቀርቡ አታፍሩም? የቤተክህነቱን ሴት የጨረሰ አውደልዳይ መነኩሴ!!!! ታሳፍራላችሁ

 3. hana May 11, 2016 at 6:14 am Reply

  ምን እንኳን የማነ ቤተ ክርስቲያኒቱን ክፉኛ ቢበድልም ኅሩይ ግን መቼም ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ለመሆነ የሞራል የስነ ምግባር አቅም የለውም ፡፡ እራሱ የሚያሽከረክረው የግል መኪና የሚያከራየው ቤት ከየት አመጣው በየትኛው ደሞዝ … የዘረኝነቱስ ነገር እንደ ኅሩይ የከፋ አለ፡፡ ጥቅሙ ሲነካ እዛ ቤት እራሱን ጻድቅ የማያረግ ማን አለ፡፡ ኅሩይ አትፎግረንን በሚገባ እንተዋወቃለን ፡፡

 4. Anonymous May 12, 2016 at 6:24 pm Reply

  ምቾትና ተድላ በበዛበት ሃገር ላይ ሆኖ ነገሮቹን አንዲህ መናገር “የፈሪ ዱላ” አያስመስልቦትም ትላንት አርሶ የዚህ ችግር ፈጣሪ፤ ተባባሪ አነበሩምእውነት ነው ስለ 160 ሚሊዮን ተከራክረው ይሆናል ግን ስንተ ሚሊዮን ምዕመን በእናንተ የአስተዳደር፣የፍትህ እጦት አደተሰነካከለ ሃይማኖቱን የካደው ስንቱ በፍረደ ገምድልነት ከስራው የተባረረው …………..

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: