ከቦሌ መድኃኔዓለም ለየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እና ለኤልያስ ተጫነ በ“ስጦታ” የተበረከተላቸው 104 ሺሕ ብር እያነጋገረ ነው፤ “ሲያንስባቸው ነው”/ዋና ጸሐፊው/

 • “ስጦታው”፥ የካቴድራሉ መደበኛ የደመወዝ ጭማሬ መፈጸሙን ተከትሎ የተደረገ ነው
 • ካህናቱ እና ሠራተኞቹ አለውድ በግድ ለመዋጮ ፈርመዋል፤ ካልፈረሙትም ተቆርጧል
 • ዋና ጸሐፊው ተስፋ ማርያም ነጋሽ እና ሒሳብ ሹሙ ግርማይ ሐዲስ አስፈጽመውታል
 • “ለምስጋና ነው” የሚሉት ዋና ጸሐፊው“መኪናም ቢሸለሙ ሲያንስባቸው ነው” ይላሉ 

***

 • ሰበካ ጉባኤው የሥራ እና የሒሳብ ሪፖርት ሳያቀርብ እንዲወርድ ግፊት እየተደረገ ነው
 • “ፓትርያርኩ አዘውናል” በሚል ግፊት የሚያደርጉት፥ አለቃው እና ዋና ጸሐፊው ናቸው
 • ከቃለ ዐዋዲው ውጭ በኾነ የምርጫ ቅድመ ዝግጅት ሰበካ ጉባኤውን ለማቋቋም ይሠራሉ
 • በሙስናው አቀባባዮች ላይ አብነታዊ የኾነ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል

***

(አዲስ አድማስ፤ ማሕሌት ኪዳነ ወልድ፤ ሚያዝያ ፳፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)

bole med

የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለምና መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ወአቡነ አረጋዊ ካቴድራል

የደመወዝ ጭማሬ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስለተደረገላችኹ የአንድ ወር የደመወዝ ጭማሬአችሁን ለስጦታ አዋጡ ተብለን በግዳጅ ሰጠን፤ ሲሉ አንዳንድ የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለምና መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ወአቡነ አረጋዊ ካቴድራል ካህናትና ሠራተኞች አስታወቁ፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የካቴድራሉ ካህናት ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ የደመወዝ ጭማሬው በሀገረ ስብከቱ ሲጸድቅ እንዲከፈላቸው የተወሰነው ካሳለፍነው ጥር ወር ጀምሮ ነበር፡፡ ክፍያውን ሳይፈጽም እስከ የካቲት ወር የቆየው አስተዳደሩ ግን፣ ካህናትንና ልዩ ልዩ ሠራተኞችን ሰብስቦ፣ “ይህን ያደረጉልንን የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ እና የሒሳብ እና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ልናመሰግናቸው ይገባል፤” በማለት ኮሚቴ ማዋቀሩን ይገልጻሉ፤ ኮሚቴውም ካህናቱን ሳያወያይ የጥር ወር ጭማሬን በፈቃዳቸው ለመተው እንደወሰኑ አድርጎ በግቢው ፊርማ ማሰባሰብ ይጀምራል፤ ያልፈረሙ ጥቂት ሠራተኞች ቢኖሩም ደመወዛቸው ግን ለስጦታው በሚል ተቆርጧል፡፡  

ለ164 ያህል ካህናትና ሠራተኞች ከጥር ወር አንሥቶ የተደረገው የደመወዝ ጭማሬ ከ450 እስከ 880 ብር እንደሚደርስ የጠቆሙት ምንጮቹ፤ 104 ሺሕ 90 ብር ከፈረሙትም ካልፈረሙትም ደመወዝ ተቆርጦ ለምስጋና በሚል ለሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና የሒሳብ እና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ በስጦታ መልክ ተሰጥቷል፤ ብለዋል፡፡ 

“ሙስና ኃጢአት ነው ብዬ እያስተማርኩ ለስጦታ በሚል የዞረውን ፊርማ አልፈርምም ብያለሁ፤” ያሉ አንድ የካቴድራሉ ካህን፣ “የጥር ወሩ ጭማሬ ግን ከደመወዜ ላይ ከመቆረጥ አልዳነም፤” ብለዋል፡፡

የካቴድራሉ ሊቃውንት በዘንድሮው የገብረ ሰላም በዓል በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል (ፎቶ: አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት)

የካቴድራሉ ሊቃውንት በዘንድሮው የገብረ ሰላም በዓል በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል(ፎቶ:አ/አበባ ሀ/ስብከት)

በመጋቢት ወር መጨረሻ የካቴድራሉ ማኅበረ ካህናት የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ማድረጋቸውን ምንጮቹ አውስተው፤ የጥር ወር ጭማሬአቸው ከደመወዛቸው ላይ መቆረጡ አግባብ እንዳልኾነ በመጥቀስ ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው አስተዳደሩን ቢጠይቁም፤ ዋና ጸሐፊው “ብትፈልጉ ከኪሴ እሰጣችኋለሁ” ሲሉ እንደተሣለቁባቸው ተናግረዋል፡፡

የተባለው ስብሰባ አለመካሔዱን የጠቀሱት ዋና ጸሐፊው መጋቤ ጥበብ ተስፋ ማርያም ነጋሽ በበኩላቸው፤ “እኔም የሰጠኹት ምንም አስተያየት የለም” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ በየኹለት ዓመቱ የሚደረገውን የደመወዝ ጭማሬ ለማጸደቅ ቀደም ሲል ለአምስት እና ለስድስት ወራት ይቆይ እንደነበር የገለጹት ዋና ጸሐፊው፤ የአሁኑ ጭማሬ በስምንት ቀናት ውስጥ ጸድቆ በመምጣቱ ሀገረ ስብከቱን ለማመስገንና የምስጋናው መገለጫ የሆነ ስጦታ ለማበርከት ካህኑና ሠራተኛው እንደተስማማ ገልጸዋል፡፡

“ከሠራተኛው ደመወዝ የተቆረጠ ገንዘብ የለም፤” የሚሉት ዋና ጸሐፊው፣ እርሳቸውም ደመወዛቸው ከነጭማሬው ከተከፈላቸው በኋላ የምስጋናውን መዋጮ ከኪሳቸው መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ መዋጮውን ለማሰባሰብ የተዋቀረው ኮሚቴ፤ ካህናቱና ሠራተኞቹ በተገኙበት ለኹለት የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች የምስጋና ስጦታ መስጠቱን የገለጹት ዋና ጸሐፊው፣ በወቅቱ የተበረከተላቸው የተጠቀለለ ነገር እንደነበርና መጽሐፍ ቅዱስ ነው ብለው እንደሚገምቱ አስረድተዋል፤ የተበረከተውም “ጭማሬው ከጸደቀ በኋላ በመሆኑ ስጦታ እንጂ ጉቦ ሊባል አይችልም፤” በማለት ተከላክለዋል፡፡

ዋና ጸሐፊው በአንድ በኩል ይህን ይበሉ እንጂ አያይዘው እንደተናገሩት፣ “ለነበረው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር እንኳን መቶ ሺሕ ብር መኪናም ቢሸለም ሲያንስበት ነው፤” ብለዋል፡፡

ከአምስት የምስጋና ኮሚቴው አባላት አንዱ እንደነበሩ የተናገሩት መምህር ሰሎሞን ዓለሙ፤  “ካህናቱንና ሠራተኞቹን ካስፈረምን በኋላ ለሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች የሰጠነው የአንድ ወር የደመወዝ ጭማሬአችንን ነው፤ ገንዘቡን የወሰድነው ከገንዘብ ቤቱ ሲሆን መቶ ምናምን ሺሕ ብር ነው፤” ሲሉ ስጦታው የብር መሆኑንና ከደመወዝ መቆረጡን አረጋግጠዋል፡፡ ስጦታውን ተቀብለዋል የተባሉት የቀድሞዎቹ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እና የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ከቦታቸው መነሣታቸው ታውቋል፡፡

ሊቀ ማእምራን የማነ፣ በሕገ ወጥ መልኩ ከሥራ አስኪያጅነቱ ጋር ደርበው ይዘውት ወደቆዩት የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ዋና ጸሐፊነት በፓትርያርኩ ቀጥተኛ ደብዳቤ ሲመለሱ፤ የሒሳብ እና በጀት ዋና ክፍሉን ለረጅም ዓመታት ሲፈራረቁበት የነበሩት ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ ደግሞ፤ ያለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዕውቅና በተመሳሳይ መልኩ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የገዳማት መምሪያ በጸሐፊነት ተመድበዋል፡፡

***

ማስታወቂያ፡- የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት በኾነው በአዲስ አበባ፣ በመጋቢት ወር የተደረገውን የሥራ አስኪያጅ እና የዋና ክፍሎች ሓላፊዎች ለውጥ ተከትሎ ጥያቄዎች እየተነሡ ነው፡፡ በዋናነት ከሚነሡት ሦስት ጥያቄዎች አንዱ፥ ርምጃው የሀገረ ስብከቱን፥ የመዋቅር፣ የአደረጃጀት እና የአሠራር ለውጥ በሚያግዝ መልኩ ከተጠያቂነት ጋር አለመፈጸሙ ነው፡፡

በዝውውር የተወገዱት ሓላፊዎች አጥቢያዎችን እንክት አድርገው የበሉና ቤተ ክርስቲያኒቱን ያራቆቱ ናቸው፤ የሚሉት ተቺዎቹ፤ ከማንኛውም ሓላፊነት ታግደው፣ በደላቸው ከሕግ እና ከዲስፕሊን አንጻር ታይቶ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ይጠይቃሉ፡፡ ይኸውም፣ ጋንግሪን ወደ መኾን ደረጃ የከፋውን የሙስና፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ዕጦት ለመቅረፍ አብነታዊ እንደሚኾን ያምናሉ፡፡ በአዲስ መልኩ ተመድበው የሚመጡ ሓላፊዎችን በሙስና የሚያበሳብሱ ነባር አማሳኞች አኹንም በሀገረ ስብከቱ እንዳሉ የሚጠቅሱ ሲኾን፤ የሚወሰደው ርምጃ ለእነኝኽም የመታረም ዕድል ከመስጠት አንጻር የራሱ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ካህናት እና ሠራተኞች እየቀረበ እንዳለው የመብት እና የፍትሕ ጥያቄ ኹሉ፤ በቀድሞው የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ – ኤልያስ ተጫነ አስተዳደር ስለተፈጸሙ በደሎች የሚያትትና ለተለያዩ አካላት የተሠራጨ ጽሑፍ ለእኛም ደርሶን ተመልክተነዋል፡፡ ጽሑፉ ከተሠራጨ ወራትን ያስቆጠረ ቢኾንም፤ ለውጡ ተጠያቂነትንም ሊያካትት እንደሚገባ የሀገረ ስብከቱን ሠራተኞች ጨምሮ በተለያዩ ወገኖች እየቀረበ ያለውን ሐሳብ ከመደገፍ አኳያ ጽሑፉ ባለው ተገቢነትና እስፈላጊነት፣ በቀጣዩ ጦማር እንደምናስተናግደው ከወዲኹ እናስታውቃለን፡፡

Advertisements

4 thoughts on “ከቦሌ መድኃኔዓለም ለየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እና ለኤልያስ ተጫነ በ“ስጦታ” የተበረከተላቸው 104 ሺሕ ብር እያነጋገረ ነው፤ “ሲያንስባቸው ነው”/ዋና ጸሐፊው/

 1. anonymous May 8, 2016 at 2:17 pm Reply

  Des yilal.

  • Anonymous May 9, 2016 at 5:40 am Reply

   Adebabay lay siletesetew shilmat titachihu ebakachihu lebond keserategnaw Tewatito medreshaw sillaltawekew bir 400shih nigerun

 2. Anonymous May 19, 2016 at 8:33 am Reply

  Yeye debiru 20% Aliyas yemitekembet mehonun yawikalu?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: