ቋሚ ሲኖዶስ: ለደቡብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎርዮስን በሥራ አስኪያጅነት ሾመ፤ አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ ወደ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተጠርተዋል

መጋቤ ብርሃናት አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎርዮስ

መጋቤ ብርሃናት ቆሞስ አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎርዮስ

ቋሚ ሲኖዶስ፥ በዛሬ ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው፣ በአስተዳደራዊ ውዝግብ ሲታመስ በቆየው የደቡብ አፍሪቃ አህጉረ ስብከት እና የጆሐንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኃኔዓለም ደብር ጉዳይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በውሳኔው መሠረት፣ ላለፉት ዓመታት አህጉረ ስብከቱን በሥራ አስኪያጅነት ደብሩንም በአስተዳዳሪነት ሲመሩ ከሰበካ ጉባኤው ጋር በፈጠሩት ውዝግብ፣ ለምእመናኑ አንድነትና ከሀገሪቱ ሕግም አንፃር ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ህልውና ከፍተኛ ስጋት ጋርጠዋል የተባሉት አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንዲመለሱ ተጠርተዋል፡፡

በምትካቸው፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የጎፋ ጥበበ እድ ካህናት ማሠልጠኛ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ፣ መጋቤ ብርሃናት ቆሞስ አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎርዮስ የተመደቡ ሲኾን አህጉረ ስብከቱን በሥራ አስኪያጅነት ከመምራት ባሻገር የጆሐንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኃኔዓለም ደብርንም በእልቅና ያስተዳድራሉ፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን የአብነት ትምህርት በሰፊው የደከሙትን መጋቤ ብርሃናት አባ ተክለ ያሬድን “ብጥር መሪጌታ ናቸው” ይላሉ፤ የሊቅነትና ክህነታዊ ሞያቸውን በቅርበት የሚያውቁላቸው፡፡ የመዝገብ ቅዳሴ፤ የዝማሬ መዋስዕት፣ የአቋቋም እና የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜን በሚገባ ተምረው በመምህርነትም በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ያስተማሩ ሲኾን በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሊቃውንት ጉባኤም በአባልነት ሠርተውበታል፡፡

መጋቤ ብርሃናት ቆሞስ አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎርዮስ በአስተዳደርም ረገድ ሰፊ ልምድ አላቸው፡፡ አኹን በሥራ አስኪያጅነት ከሚመሩት የጎፋ ጥበበ እድ የካህናት ማሠልጠኛ ቀደም ሲል፤ በሐዋሳ ሀገረ ስብከት የሐዋሳ ዙሪያ ወረዳ ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናትና የወንዶ ገነት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፤ የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፤ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜን በተማሩበትና በመምህርነትም ባስተማሩበት የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምክትል ዲንና በኋላም ዋና ዲን እንዲኹም የጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት መምሪያ ዋና ሓላፊ ኾነው ሠርተዋል፡፡

የተሿሚው ሥራ አስኪያጅ አዲሱ ምደባቸው፤ ይኸው በአገልግሎትና በተለያዩ ተቋማት ሓላፊነታቸው ያካበቱት ልምድ በተለየ ምኅዳር ተፈጥሮ በቆየ የቤተ ክርስቲያን ችግርና ተግዳሮት የሚፈተንበት ይኾናል፡፡

በአህጉረ ስብከቱ፣ ላለፉት ኹለት ዓመታት በተፈጠሩ አለመግባባቶች የተራራቁና እስከ ዓምባጓሮ የደረሱ ምእመናንን በአባታዊ ፍቅር አቀራርቦ በይቅርታና ዕርቅ ሰላምንና አንድነትን ማስፈን ቀዳሚውን ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ ከዚኽም በማስከተል፥ በሃይማኖትና በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ረገድ በአገልጋዮችና በምእመናን ውስጥ ያሉ ችግሮችን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንፃር እየመረመሩ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝና ውሳኔ እንዲሰጠው በማድረግ መንፈሳዊነትን ማጽናትና አገልግሎትን በጋራ መፈጸም፤ ለሙስናና ዝርክርክነት ለተጋለጠው አሠራርም የቤተ ክርስቲያናችንን የመልካም አስተዳደር መርሖዎችና የሀገሪቱን ሕግ ያገናዘበ አሳታፊና ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ይጠበቃል፡፡

የኵላዊት ቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት በጥኑ የሚተፈታተኑ ጎጠኝነት/አካባቢያዊነት፣ ቡድንተኝነትና አማሳኝነት ተጠብቆ እነኝኽን ተግባራት በንጽሕና ማከናወን ከተቻለ ምደባው፣ ኢትዮጵያውያን ምእመናንና ልጆቻቸው የማንነታቸው፣ የማኅበራዊ አንድነታቸውና የመጽናኛቸው ምልክትና ማእከል ላደረጓት የደቡብ አፍሪቃ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ትልቅ ዕድል እንደሚኾን አያጠያይቅም፡፡ ደቡብ አፍሪቃውያን፥ “የጥቁሮች ቤተ ክርስቲያን”፤ “የአፍሪቃ ቤተ ክርስቲያን”፤ “የኛ ቤተ ክርስቲያን” ለሚሏት ቤተ ክርስቲያናችን መጠናከርና መስፋፋትም የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡

ከችግሩ አሳሳቢነት አኳያ የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ በእጅጉ የዘገየ ቢኾንም፤ የመጋቤ ብርሃናት አባ ተክለ ያሬድ ምደባ ሊያስመሰግን የሚችለው፣ ከቀደመው ውዝግብ ተሞክሮ የእናት ቤተ ክርስቲያንን አንድነት በማጠናከር ቤተ ክርስቲያናችንን ተስፋ ለሚያደርጓት ኹሉ ለመድረስ የሚቻልበት አቅም ሲፈጠር ነው፡፡ የአህጉረ ስብከቱ አገልጋዮችና ምእመናን ኹሉ በዚኹ መንፈስና አቅጣጫ እንዲተባበሯቸው ጥሪያችንን እያቀረብን መልካም የአገልግሎትና የውጤት ዓመት እንመኝላቸዋለን፡፡

ባለፈው ቅዳሜ፣ የአህጉረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና በሚገኝበት በጽርሐ ጽዮን ጆሐንስበርግ መድኃኔዓለም ደብር፤ በአባ ጥዑመ ልሳን አዳነ አወዛጋቢ አስተዳደር ሳቢያ ስለተፈጠረውና የሀገሪቱ ቴሌቭዥን “አሳፋሪ” ሲል በቪዲዮ አስደግፎ ያስተላለፈውን አሳዛኝ የቤተ መቅደስ ውስጥ ዐምባጓሮ በተመለከተ፣ ሳምንታዊው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባለፈው ቅዳሜ ያወጣው ዘገባ ከዚኽ በታች ቀርቧል፡፡


የጆሐንስበርግ መድኃኔዓለም አስተዳደራዊ ውዝግብ ምእመናኑን ለዐምባጓሮ አደረሰ

 • በግጭቱ በስምንት ምእመናን ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል
 • ሰበካ ጉባኤው በአስተዳዳሪውና በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ላይ ክሥ መሥርቷል
 • የመንበረ ፓትርያርኩ የውጭ ጉዳይ መምሪያ ሓላፊ፣ ግጭቱን በማባባስ ተወቅሰዋል

(አዲስ አድማስ፤ ዓለማየሁ አንበሴ፤ ሚያዝያ ፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)

በደቡብ አፍሪካ ጆሐንስበርግ በሚገኘው የጽርሐ ጽዮን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የተነሣ ውዝግብ ወደ ዐምባጓሮ ተሻግሮ አንዲት የአራት ወር ነፍሰ ጡርን ጨምሮ በ8 ምእመናን ላይ ጉዳት የደረሰ ሲኾን 5 ምእመናን ለእስር መዳረጋቸውንና ጉዳዩም በሀገሪቱ ፍ/ቤት እንደተያዘ ምንጮች ገለጹ፡፡

Aba Tiume Lisan Adane

አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ

የጆሐንስበርግ ምንጮቻችን እንደሚሉት፤ ለተፈጠረው ዐምባጓሮ መነሻው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሰበካ ጉባኤ እና በቅርቡ በአስተዳዳሪነት በተሾሙት አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ነው፡፡ አስተዳዳሪው፤ በተጭበረበረ ሰነድና ቤተ ክርስቲያኗ በሌላት የሥልጣነ ክህነት ተዋረድ (Deputy Bishop) ተብለው የደቡብ አፍሪካ ሀገረ ስብከትና የደብሩ አስተዳደር ሆነው ተሹመዋል፤ በሚል በሰበካ ጉባኤው ዘንድ ቅሬታ መፈጠሩን የጠቆሙት ምንጮች፤ በየጊዜው ውዝግቡ እየተባበሰ መሔዱን ይናገራሉ፡፡

ከኢትዮጵያ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የውጭ ጉዳይ መምሪያ ሓላፊ ጨምሮ ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ያሉበት አጣሪ ኮሚቴ በቋሚ ሲኖዶስ ተልኮ እንደነበር ያስታወሱት ምንጮቹ፤ በተለይም የመንበረ ፓትርያርኩ የውጭ ጉዳይ መምሪያ ሓላፊ መልአከ ሰላም ቃለ ጽድቅ ለሽምግልና ተልከው ግጭቱን አባብሰው ነው የተመለሱት፤ ሲሉ አምርረው ወቅሰዋቸዋል፡፡ የኮሚቴው አባላትም በአቋም እንዲከፋፈሉና ለቋሚ ሲኖዶሱም የተለያዩ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ምክንያት መኾናቸውን እንደሰሙ ገልጸዋል፡፡

አባ ጥዑመ ልሳን ቀደም ሲል ደብሩን ለኹለት ዓመት ካገለገሉ በኋላ በገዛ ፈቃዳቸው ከሓላፊነታቸው በመልቀቅ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ነበር፤ የሚሉት የሰበካ ጉባኤው አመራሮች፤ በድጋሚ የደቡብ አፍሪካን የሥራ ፈቃድ ሳያሟሉ በጎብኚ ቪዛ በመግባት “ከፓትርያርኩ ሹመት ተሰጥቶኛል” በማለት የአስተዳዳሪነቱን ቦታ መልሰው መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህም በሰበካ ጉባኤው ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ በመፍጠሩ ለደቡብ አፍሪካ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ተደጋጋሚ አቤቱታ ማቅረባቸውን የሰበካ ጉባኤው ም/ሰብሳቢ አቶ ዳዊት ሰሎሞን ለአዲስ አድማስ በስልክ ገልጸዋል፡፡

ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤትም አቤቱታ ማቅረባቸውን የጠቀሱት አቶ ዳዊት፤ የቅዱስ ሲኖዶሱን ምላሽ እየተጠባበቅን ባለንበት ወቅት፤ አባ ጥዑመ ልሳን፤ “ከፓትሪያርክ አባ ማትያስ የሰበካ ጉባኤውን የሚያግድ ደብዳቤ ተልኮልኛል፤” በማለት በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበው ምእመን ሊያነቡ ሲሉ ዐምባጓሮው መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

በዐምባጓሮውም 8 ምእመናን ጉዳት የደረሰባቸው ሲኾን በተለይ አንዲት የአራት ወር ነፍሰ ጡር ወድቃ በመረገጧ ክፉኛ በመጎዳቷ ሆስፒታል ገብታ ሕክምና እየተደረገላት እንዳለ ም/ሰብሳቢው ተናግረዋል፤ 5 ምእመናንንም መታሰራቸው ታውቋል፡፡

ግጭቱን ተከትሎ የሰበካ ጉባኤው፣ በአስተዳዳሪው በአባ ጥዑመ ልሳን ላይ በፕሪቶርያ ፍ/ቤት ክሥ ያቀረበ ሲኾን፤ የአስተዳዳሪውን የሥራ ፈቃድ ጨምሮ በርካታ ቅሬታዎች ቢቀርቡለትምጉዳዩን በቸልታ ተመልክቷል በሚል የደቡብ አፍሪካ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርም ክሥ ተመሥርቶበታል፡፡

ሚኒስቴሩ ለፍ/ቤቱ በሰጠው ምላሽ፣ የተጠቀሱበትን ክሦች እንደሚቀበልና ለጉዳዩ አፅንዖት ሰጥቶ የማስተካከያ ርምጃ እንደሚወስድ፣ ለአስተዳዳሪው የሰጠውን ፈቃድም እንደሚሰርዝ ማሳወቁን የጠቀሱት የሰበካ ጉባኤው የሕዝብ ግንኙነት ተጠሪ አቶ ይልማ ሸዋ፤ አባ ጥዑመ ልሳንም ለክሡ መልስ አቀርባለኹ፤ ማለታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካውያን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን፤ “የጥቁሮች ቤተ ክርስቲያን”፤ “የአፍሪካ ቤተ ክርስቲያን”፤ “የኛ ቤተ ክርስቲያን” እያሉ እንደሚጠሩዋትና የስደተኞች ቤተ ክርስቲያን አድርገው እንደማያዩዋት ያስረዱት የሕዝብ ግንኙነት ተጠሪው፣ በዐምባጓሮው ሳቢያ ግን ልጆች ወደ ደብሩ ለመምጣት ስጋት እንዳደረባቸው ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል የሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በተከሠተው ውዝግብ ዙሪያ በቅርቡ ዘገባ እንደሚያቀርብ መስማታቸውን የገለጹ ምእመናን፤ ይህም የሀገርንና የቤተ ክርስቲያኒቱን መልካም ገጽታን ያበላሻል፤ ብለዋል፡፡

Advertisements

7 thoughts on “ቋሚ ሲኖዶስ: ለደቡብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎርዮስን በሥራ አስኪያጅነት ሾመ፤ አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ ወደ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተጠርተዋል

 1. senay April 21, 2016 at 1:23 am Reply

  ለአባ ተክለ ያሬድ መልካም የስራ ዘመን

  • kassu April 21, 2016 at 10:04 am Reply

   Let pray to save our church nothing comes from division

  • Anonymous April 21, 2016 at 2:22 pm Reply

   Aba Tekleyared Ewnetegna yebetekrstiyan Lij lik Memhir new Minaw Aba matias zeregninetun leafta titew liyu tsehafiyachew biyadergut kedebtra ayshalachewm leloch patriyarkochima Thefiwochachew Papasat neberu yalemetadelnew

  • ጫላ April 22, 2016 at 5:03 am Reply

   እነ ቄስ መአዛ እነ ቄስ ሶምሶን እነ ዲ/ ን ሉቃስ ህዝቡን እንዳባላቹት እግዚአብሄር የስራቹን ይስጣቹ

 2. yora April 22, 2016 at 10:42 am Reply

  I never advice

 3. ስራቹ ያስከፍኝ April 24, 2016 at 6:42 pm Reply

  እናንተ የምትገርሙ ትላንት ሳይላኩ ነው የመጡት ስትሉ ነበር ዛሬ ደግሞ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተጠርተዋል ትላላቹ ያልላካቸው አካል ምን ብሎ ነው ተመለሱ የሚላቸው እርሳቸውስ ሳይላኩ ከመጡ የት ነበርኩ ብለው ነው የሚመለሱት በጣም የሚገርመኝ አባቶች ፃፃሳት መተው ሰላም ይስጡን ስንል አባ ጥኡመ ልሳን እምቢ እያሉ ነው ጉዳቸው እንዳይጋለጥ ስትሉ ከረማቹ አሁን አባቶቹ መተው ውሳኔ ሲሰጡ ደሞ ሌላ ታሪክ ይዛቹ ብቅ አላቹ ባህሪያችሁን እንደ እስስት አትቀያይሩ አቁዋም ይኑራቹ ይህ የጆበርግ በተክርስትያን በተደጋጋሚ አባቶች ተቀያይረውበታል ይሄ እስከመቼ ይቀጥላል አባቶችን የመሾም ስራ ከፃፃሳት እየወጣ በእንደናንተ አይነት ወንበዴ ሰወች እና ሙሉ መዝሙር ከነ አዝማቹ መዘመር በማይችሉ ሰንበት ተማሪዎች እጅ እየገባ ነው:: የምታወራው እንቶፈንቶ ምን ያህል ችግር እያስከተለ ሰለመሆኑ ግድ የለህም:: በቃ ተወን! ዝርዝር ውስጥ ከገባን ብዙ ስሞችን እየጠቀስን ያልታወቁ ሰወችን ችግር ማጋለጥ በጣም ቀላል ነው ግድ የለህም ተወን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: