የሰዋስወ ብርሃን ቅ/ጳውሎስ ኮሌጅ: መናፍቃንንና ምንደኞቻቸውን ማጥራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፤ የተባረረው ከፍ ያለው ቱፋ ከፍተኛ ውሳኔ እንዲተላለፍበት ተጠይቋል

  • የኮሌጁ አስተዳደር ጉባኤ ከማታ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት ጋር ተወያይቷል
  • የበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ: በሃይማኖት ድርድርም ኾነ መሸማቀቅ የለም፤ ብለዋል
  • ዘካርያስ ሐዲስ: ለተጠርጣሪዎች በሽምግልና ተልከዋል፤ መባሉን አስተባብለዋል

Kefyalew Tufa's complete dismissal
መንፈሳዊ ኮሌጆቻችን፣ የቤተ ክርስቲያናችን ነባር አስተምህሮ በዘመናዊ አቀራረብ የሚሰጥባቸው የወንጌላውያንና ዘመናውያን ምሁራን መፍለቂያ ምንጮች ናቸው፡፡ የአብነት ትምህርቱን ከዘመናዊው ጋር አዋሕደው በመሠልጠን ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ አገልግሎት የሚሰጡ ሊቃውንትንም እያፈሩ ቆይተዋል፡፡

የነበረውና ወደፊትም የሚኖረው የቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮና ትውፊት ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ፤ የክርስቶስን ወንጌል ያልሰሙ እንዲሰሙ፣ የሰሙ በእምነታቸው ጸንተው የሃይማኖት ፍሬ እንዲያፈሩ፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ወገኑን የሚወድ፣ ለሀገርና ለወገን ዕድገት የሚያስብ ለዚኽም የሚጥር ትውልድ የማፍራት ርእያቸውና ተልእኳቸው በስኬት ይቀጥል ዘንድ ግና አስተዳደራዊና አካዳሚያዊ ሥራዎቻቸው እንዲኹም የፋይናንስ አቅሞቻቸው ሊጎለብቱ ይገባል፡፡

ከዚኽ አኳያ፣ የኮሌጆቹን አስተዳደር ሞያዊነት ማጠናከር፤ የመምህራኑን ሃይማኖት ማረጋገጥና የማስተማር ክህሎታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንዲኹም የሥርዐተ ትምህርቱ አቀራረጽና የመማርያ መጻሕፍቱ ዝግጅት ተፈትሾ እንዲሠራባቸው ማድረግ፥ የትምህርቱን ጥራት በመጠበቅ በሃይማኖታቸው የጸኑ፣ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ያላቸው፣ በነገረ መለኰት በቂ ግንዛቤና ዕውቀት ያዳበሩ ደቀ መዛሙርት ለማውጣት የሚያስችሉ ቁልፍ ነጥቦች ቢኾኑም፤ የደቀ መዛሙርት ምልመላና ቅበላም ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ደረጃ በየጊዜው ውሳኔ የተላለፈበት ጉዳይ ነው፡፡

ይኹንና መመሪያውን ጠብቆ በጥብቅ ዲስፕሊንና በጥራት ምልመላውንና ቅበላውን ማከናወኑ ያለበት ውስንነት በተለይም መናፍቃንና ሰርጎ ገብ ምንደኞቻቸው በገዛ ኮሌጆቻችን እየፈጠሩብን ለሚገኙት ተጽዕኖና ችግር ዋነኛ መንሥኤ መኾኑ ታምኖበታል፡፡ ከሦስቱም ኮሌጆቻችን በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወንጌላውያንን ማፍራቱ አስደሳች ቢኾንም የቅበላ አቅምን ከተፈላጊው ብቃትና ጥራት ጋር ለማጣጣም በኹሉም ፕሮግራሞች(በድኅረ ምረቃ፣ በመደበኛ፣ በተመላላሽ፣ በማታው ክፍለ ጊዜና በርቀት) ከመግቢያ መስፈርቱ ጀምሮ ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥብቅ ቁጥጥር ማካሔድ ያስፈልጋል፡፡ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ባለፈው ሰኞ ከደቀ መዝሙርነት ያባረረው የመናፍቃኑ ምንደኛ ከፍ ያለው ቱፋ፣ ሾልኮ የገባበት ተጨባጭ ማስረጃዎች በዚኽ ረገድ ያሉብንን ክፍተቶች የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡

የኮሌጆቹን የውስጥ ይዘት በማጥናት ለበለጠ ዕድገት ለማብቃት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት ምልዓተ ጉባኤውና ከዚያም ወዲኽ በቋሚ ሲኖዶስ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች የሚጠቀሱ ሲኾኑ፤ ውሳኔዎቹን ለማስፈጸም የተቋቋሙ ኮሚቴዎችን ከሚመሩት አባቶች አንዱ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፥ ኮሌጆቹን ከመናፍቃንና ምንደኞቻቸው የማጥራቱ እንቅስቃሴ ለውዥንብሮች ሳይጎናበስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

his grace abune hizkiel

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል: የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ

ትላንት ከቀትር በኋላ በኮሌጁ አዳራሽ በተጠራና ከ650 በላይ የማታው መርሐ ግብር የሴሚነሪ ደቀ መዛሙርት በተሳተፉበት ውይይት፣ የኮሌጁ አስተዳደር፣ በከፍ ያለው ቱፋ ላይ ስለወሰደው ርምጃና በይቀጥላልም እያደረጋቸው ስላሉት ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች የበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በተገኙበት ገለጻ አድርጓል፡፡

ተማሪው ለራሱ ከመጠንቀቅ አልፎ በአጠገቡና በየክፍሉ የሚገኙትንም በንቃት እንዲከታተል ያሳሰቡት ብፁዕነታቸው፣ ከቤተ ክርስቲያን መጠቀም ብቻ ሳይኾን ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅም የኹሉም ድርሻ እንደኾነ በመጥቀስ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል – “ኹላችኁም እምነታኹን ጠብቁ፤ ብዙዎቻችኹ የቤተ ክርስቲያን ሠራተኞችና ቀዳሽ አገልጋዮች ናችኹ፤ የያዛችኹት ሞባይል ስብሰባ ለመቅረጽ ብቻ ሳይኾን በቅርባችኹ በየክፍላችኹ ስላሉትም ማስረጃ ያዙበት፡፡”

“በጀት መድቦ የሚያሳድደን ማኅበረ ቅዱሳን ነው፤” በሚል እንቅስቃሴውን ለማሸማቀቅና ለማዳከም የሚነዛ የሰርጎ ገቦች አሉባልታና ሐሜት መኖሩን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ “ማኅበረ ቅዱሳን በጀት አይመድብልኝም፤ ማኅበረ ቅዱሳንም አያዘኝም፤” ሲሉ ጥረቱ በወሬ እንደማይፈታ ገልጸዋል፡፡

በተባረረው ከፍ ያለው ቱፋ ላይ የተወሰደውን ርምጃ ለመቀልበስና በክትትል ውስጥ ያሉትን ደቀ መዛሙርት ጉዳይ በሽምግልና ለማድበስበስ እየተደረገ ነው ስለሚባለው ሙከራም ብፁዕነታቸው ሲናገሩ፥ “የሚሸማቀቅ ያለ ከመሰለው ተሳስቷል፤ በሃይማኖቴ ወደ ኋላ አልልም፤ ሽማግሌ ነኝ የምትለውም እስኪ ና፤ ማንም በሥራዬ እንዲገባብኝ አልፈልግም፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠኝ ሓላፊነት ነው፤ በሃይማኖት ድርድር ይኹን መሸማቀቅ የሚባል ነገር፤ ኹላችኁም ማስረጃ አምጡ፤ አጣርተን ርምጃ እንወስዳለን፤” ሲሉ የተጋድሎውን ቀጣይነት አስታውቀዋል፡፡

ኮሌጁን ከመናፍቃን ተጽዕኖና መሠሪነት በመከላከል በዕውቀትም በመንፈሳዊ ሕይወትም ምሳሌ የኾኑ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠባቂ ደቀ መዛሙርት መፍለቂያ ብቻ ለማድረግ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መቆየታቸውን ውይይቱን የመሩት የአስተዳደር ምክትል ዲኑ መ/ር ማሞ ከበደ አስታውሰዋል፡፡

“በጎችን በበረታቸው በማቆየትና ቀበሮዎችን ወደ ጎድጓዳቸው በመመለስ” ኮሌጁን የማጥራት ተጋድሎው፣ በቅርቡ ቀኖናዊ ውሳኔ በሚተላለፍባቸው ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መ/ር ማሞ ገልጸዋል፤ በቤታቸው የሞላውን ትተው ከሌሎች አዳራሽ ሲቀላወጡ በተደረሰባቸው ላይም ከፍተኛ ክትትል እየተደረገ እንዳለና አስተዳደሩም ተገቢ ነው ብሎ ባመነበት ወቅት አስተማሪ ርምጃ እንደሚወሰድ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

ከቀኑ 9፡00 እስከ 11፡00 በዘለቀው በዚኹ ስብሰባ ደቀ መዛሙርቱ፣ ኮሌጁ የወሰዳቸው ርምጃዎች ሲጠበቁ የቆዩና አግባብነት ያላቸው እንደኾኑ በማድነቅ ከበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ ለተላለፉ መመሪያዎችና ከአስተዳደር ምክትል ዲኑ ለተሰጡ ማሳሰቢያዎች ከፍተኛ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በማታው ክፍለ ጊዜ የሦስተኛ ዓመት ሴሚነሪ ተማሪና ከተሳታፊዎቹ አንዱ የኾኑት የሲ.ኤም.ሲ ቅዱስ ሚካኤል አለቃ መልአከ ምሕረት ዘካርያስ ሐዲስ፣ ቀደም ሲል በተላለፈው ዘገባ ከተጠርጣሪዎቹ ለአንዱ ሽምግልና ተልከዋል መባላቸውን በስብሰባው ላይ አስተባብለዋል – ሽማግሌ እርሱ ነው እየተባልኩ ነው፤ እኔ በሽምግልና አልሔድኩም፤ በሃይማኖቴ እንደማልደራደር ያውቃሉ፤ በግል ስለሚጠሉኝ እንጂ በእንተ ስማ ለማርያም ብለን የበላንባትንና የተማርንባትን ቤተ ክርስቲያን አንክድም፤ ብለዋል በማስተባበያቸው፡፡

የተመላላሽ ሴሚነሪ ተማሪ የነበረው ከፍ ያለው ቱፋ፣ ከኮሌጁ አንዳንድ ደቀ መዛሙርትን በተለያዩ ስልቶች ወደ መናፍቃን አዳራሽ በመውሰድና በማስኮብለል፤ ኅትመቶቻቸውን በኅቡእ በማሰራጨት፤ የቤተ ክርስቲያን ያልኾነን ትምህርትና ሥርዐት የቤተ ክርስቲያን እንደኾነ በማስመሰል በቤት ለቤት መርሐ ግብሮች በፕሮቴስታንታዊ ዘይቤ ኑፋቄን በማስፋፋት ሲንቀሳቀስ እስከ ሦስተኛ ዓመት ቆይቷል፡፡ የምንደኛነት ተልእኮው በሰነድና በድምፅ የመተማመኛ ማስረጃዎች እንዲኹም በምስክሮች ቃል ተረጋግጦበት ከኮሌጁ ደቀ መዝሙርነት ቢባረርም፤ ከኑፋቄው አደገኛነት አንጻር ማስረጃዎቹ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ተመርምረው ከፍተኛ እና አስተማሪ ውሳኔ እንዲተላለፍበትም እየተጠየቀ ይገኛል፡፡

 

Advertisements

2 thoughts on “የሰዋስወ ብርሃን ቅ/ጳውሎስ ኮሌጅ: መናፍቃንንና ምንደኞቻቸውን ማጥራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፤ የተባረረው ከፍ ያለው ቱፋ ከፍተኛ ውሳኔ እንዲተላለፍበት ተጠይቋል

  1. annan April 8, 2016 at 8:28 am Reply

    ግብዝነት የተሞላበት ስራ፡፡ በዚህ ሁኔታ አያዋጣም አንድ ቀን ቤ/ክ ብቻዋን ከግብዞቿ ጋርትቀራለች

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: